አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 06 December 2017

አዲስ አበባ ህዳር 27/2010 የግብርና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ የሚያስችል ዓለም ዓቀፍ አውደ ርዕይ የፊታችን አርብ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።        

 አምስተኛው የግብርና መሳሪያዎች፣የምግብ ማምረቻ ቴክኖሎጂ እና የማሸጊያ መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ የንግድ አውደ ርዕይ ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ተብሏል።         

 የአውደ ርዕዩ አዘጋጆች ኢቴል የማስታወቂያና ኮሙዩኒኬሽን ድርጅት እና የቱርኩ ላዲን የአውደ ርዕዩዎችና ስብሰባዎች አዘጋጅ ተቋም በዝግጅቱ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።               

 በአውደ ርዕዩ ላይ ከሰባት አገራት የተውጣጡ 73 ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ስድስት ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።   

 ከህንድ፣ጣልያን፣ፈረንሳይ፣ቱርክ፣ጀርመንና ኬንያ የመጡ ኩባንያዎች ሲሳተፉ፤ ከህንድ 46 ኩባንያዎች በአውደ ርዕዩ ላይ በመሳተፍ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

 የኢቴል ማስታወቂያና ኮሙዩኒኬሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኃይማኖት ተስፋዬ እንደገለጹት፤ አውደ ርዕዩ በግብርናው ላይ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ሴክተሩን ለመደገፍ ያግዛል።  

 ተሳታፊ ኩባንያዎቹ የግብርናና ተያያዥ ቴክኖሎጂዎችን በዘርፉ ላሉ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራልም ብለዋል፡፡   

የግብርና ቴክኖሎጂዎች የሚያመርቱ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በዘርፉ ካሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል። 

 አውደ ርዕዩ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ፣ባለኃብቶችን በማገናኘት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና የገበያ ዕድሎችን ለማስፋት ጠቀሜታ እንዳለው ወይዘሮ ሐይማኖት አብራርተዋል።

 ''ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩልም አውደ ርዕዩ ትልቅ ሚና ይጫወታል'' ብለዋል።   

 የቱርኩ ላዲን ና አውደ ርዕዩዎችና ስብሰባዎች አዘጋጅ ተቋም ፕሮጀክት ማናጀር ሚስተር መርት ጉል በበኩላቸው በአውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች ቁጥር ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ።          

 ከአራት ዓመት በፊት የመጀመሪያው ኤግዚቢሽን ከ 20 የማይበልጡ ኩባንያዎች እንደተሳተፉና ባለፈው ዓመት 65 ኩባንያዎች መሳተፋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።      

 "ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎችን ቀልብ እየሳበች መሆኗ ኤግዚቢሽኑን በየዓመቱ በኢትዮጵያ እንድናዘጋጅ ማድረጉን ሚስተር መርት ገልጸዋል።  

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 27/2010 ኢትዮጵያ 3ኛውን የአፍሪካ የጥርስ ህክምና እና መድሐኒት ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ በቀጣይ ሳምንት አዲስ አበባ ታስተናግዳለች።

ዓውደ ርዕዩ በጣልያን የንግድ ድርጅት፣ የጣልያን ጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ተዘጋጅቷል።

"የጥርስ ህክምና እና መድሃኒት ዘረፍ አዳዲስ እይታዎች" በሚል መሪ ቃል ከታህሳስ 5 እስከ ታህሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚደረገው ዓውደ ርዕይ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ የጥርስ ህክምና እና መድሃኒት አምራቾች ይሳተፋሉ።

ይህም በጥርስ ህክምና ዘርፍ ዓለም የደረሰባቸውን የህክምና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታ ከመቅረባቸው ባሻገር የዘርፉ አምራቾች ፤አከፋፋዮች ፤ ባለሙያዎችና ተጠቃሚዎች መካከል ትስስር ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የጣሊያን ንግድ ድርጅት ኮሚሽነር ሲሞና ኦትኦሪ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፖለቲካል ማዕከልነቷና ለሎጀስቲክስ ምቹነቷ በተጨማሪ ከሰሃራ በታች ላሉ አገራት ካላት አቅም አኳያ ለኤግዚሽኑ አስተናጋጅነት ተመራጭ አድርጓቷል ብለዋል።

የኤግዚቢሽኑ ሳይንሳዊ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር ራናቶ ጉላ በበኩላቸው በዓውደ ርዕዩ በሁሉ አቀፍ የጥርስ ጤንነት፣ ባለሙያዎች በዕለት ከዕለት የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ጥናታዊ ምርምሮች ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

የምግብ፤መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሳይ ወልደማርያም "ኢትዮጵያ የፋርማሲቲካል ዘርፍ ልማት ትኩረት በመስጠት የ10 ዓመት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ አድርጋለች" ብለዋል። 

በዘርፉ የተሰማሩ ግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ለመሳብም የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሩ መንደር ለመገንባት ጥልቅ ጥናት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ዓውደ ርዕዩ አገሪቱ ትኩረት ያደረገችባቸውን ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎችና ማበረታቻዎችን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

"ዓውደ ርዕዩ በባለድርሻ አካላት መካከል የእውቀት ሽግግርና ልምድ ልውውጥ በማድረግ በአገራችን የጥርስ ህክምና መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የጥርስ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሉቀን ታደሰ ናቸው።

በኢትዮጵያ የጥርስ ባለሙያው ጥራት ያለው መሳሪያና የህክምና ምርት እያገኘ አለመሆኑንና ከህክምና ተማሪዎች ጀምሮ የግልና የመንግስት የዘርፉ ተቋማት ስለሚሳተፉ ከአምራቾች ጋር በቀጥታ ለመገናኘትና ወደፊት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአፍሪካ የጥርስ ህክምና እና መድሐኒት ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ የኬንያ፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ ሲሆን ዓለም አቀፍ አምራቾች ወደ አፍሪካ ገበያቸውን ለማስፋፋት ባላቸው እቅድ ላይ ይወያያሉ ተበሎ ይጠበቃል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው አውደ ርዕይ ከ2 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን በቂሊንጦ እየተገነባ ያለውን የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት እንደሚደረግም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

አንደኛውና ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የጥርስ ሕክምና አውደ-ርዕይ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ለሁለት ተከታታይ ጊዜ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ህዳር 27/2010 የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ኢትዮጵያዊያን ባህላቸውን ከማንፀባረቅ በዘለለ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ እንደሆነ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር የሆኑት ዶክተር ስንታየሁ ካሳዬ እንደገለጹት በዓሉ ብሄሮች ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታሪካቸውን ፤ባህላችውንና መልካም ልምዳቸውን የሚለዋወጡበትና እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁበትመድረክ ነው።

"አንዱ ብሄረሰብ የሌላውን ባህልና እሴቶች እንዲያውቅ ከማድረግ ባለፈ ተወያይተው አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር አንድነታቸውን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው" ብለዋል።

በየዓመቱ እየተገናኙ በሃገራቸው ጉዳይ ላይ የሚመክሩበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩም ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀምና የፌዴራል ስርዓቱ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ዶክተር ስንታየሁ ገልጸዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት የቆየውን የአብሮ የመኖር ፣የመስራት፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ችግራቸውን በጋራ የመፍታት እሴቶቻቸውንና ማህበራዊ  ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

አሁን በሃገሪቱ እየተገነባ ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ኃይማኖቶች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖሊቲካል ሳይንስ ስትራቴጂክ ጥናት መምህር አቶ መረሳ ጸሃዬ ናቸው።

ስርዓቱ የህዝቡን የመሬትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የመለሰ ከመሆኑም በላይ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን እና ብዝሃነትን ያጎናጸፈ መሆኑን አስረድተዋል።

የህገ-መንግስትና የፈደራሊዝም ባህል ባለመዳበሩም ትምክህት፣ጠባብነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና ሌሎች ተግዳሮቶች ግን ገና ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች መሆናቸውን አቶ መረሳ  ጠቁመዋል።

ችግሮቹን ህገ-መንግስታዊና የፌደራል ስርዓታችንን በማዳበርና በማሳደግ እንዲሁም ተፈፃሚነቱን በማጠናከርና የማስፈፀም አቅማችንን በማጎልበት መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ

ባሀርዳር ህዳር 27/2010 በአማራ ክልል ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩና የማይተኩ ቅርሶችን ለመጪው ትውልድ በአግባቡ ለማስተላላፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ቅርሶችን ለመጠገንና ለመንከባከብ የዘርፉ ባለሙያና የበጀት እጥረት ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ተግልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው የቡድን መሪ አቶ ግርማ መላኩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት ታሪካዊ ቅርሶች በአያያዝና እንክብካቤ ጉድለት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው።

መንግስት ቅርሶችን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከቅርሶች ብዛትና ዓይነት አንጻር በሚፈለገው መጠን እየተሰራ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ቅርሶች በተለያየ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ቀደም ሲል ለመጠገን የተደረገው ጥረትም ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል።

በመሆኑም ቅርሶች በተሰሩበት ቁስ በጥንቃቄ መልሶ በመጠገንና በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ በአግባቡ የማስተላለፍ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልኡል ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ነባርና ጥንታዊ ቅርሶችን መልሶ ለመጠገን የቴክኖሎጂ እጥረት ችግር እንዳለ ገልጸዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በሙያው ሃገራዊ እውቀት ያለው ባለሙያና የበጀት እጥረት ቅርሶችን በአግባቡ ለመጠገን እንቅፋት መሆኑን አስታውቀዋል።

ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ በሚደረገው ጥረትም ሕብረተሰቡ ከመንግስት ባልተናነሰ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ልዑል አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ባደረገው የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ከአማራ ክልል የተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

 

Published in ማህበራዊ

አክሱም ህዳር 27/2010 የኩሓ አጠቃላይ ሆስፒታል ከ700 በላይ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ሆስፒታሉ ህክምናውን የሰጠው ከትግራይ ጤና ቢሮና ሂዩማሊያን ካታራክት ከተባለ በጎ አድራጊ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከህዳር 22/2010ዓ.ም.  ጀምሮ ለስድስት ቀናት በአክሱም ከተማ በሚገኘው የዓይን ህክምና ማዕከል ውስጥ ነው።

ህክምናው በነጻ የተሰጠው ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አንድ ሺህ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ መሆኑን  የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ሐጎስ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም  ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ በተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ነጻ የህከምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም ሲልም በአላማጣ፣ሁመራና መቀሌ ከተሞች ውስጥ በዘመቻ በተካሄደው ህክምና በአይን ግርዶሽ ምክንያት ማየት ተስኗቸው የቆዩ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ታክመው መዳናቸውንም ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

" የአይን ሞራ ህመም ዋንኛ መንስኤው የንጽህና ጉድለት ነው " ያሉት ስራ አስኪያጁ፣መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና  አገልገሎት እንዲሰጥ  በሆስፒታሉ የአይን ህክምና ባለሙያዎች ትምህርት መስጠት መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡

በሚቀጥሉት ስምንት ወራት በክልሉ ወደሚገኙ አስር ወረዳዎችን በመንቀሳቀስ አገልግሎቱ በዘመቻ ይሰጣል ተብሏል፡፡

በህክምናው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ላዕላይ አድያቦ ወረዳ  የአዲ ዳዕሮ   ከተማ ነዋሪው ወይዘሮ ብርስእላ ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት በአይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት  ታመው ማየት ሳይችሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

" አሁን በተደረገልኝ ህክምና ሁለቱም አይኔ ማየት ችሏል "ብለዋል።

 

ከናዕዴር አዴት ወረዳ የመጡ አቶ ንጉሰ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ለአምስት ዓመታት ማየት ተስኗቸው የነበረው አሁን በተደረገላቸው ነጻ የህክምና እርዳታ ብርሀናቸው መመለሱን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ህዳር 27/2010 በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰሩ መሆናቸውን የሁለቱ ክልል ምክር ቤቶች አባላት ገለጹ።

የሁለቱ ክልል ምክር ቤት አባላት ትናንት በነቀምቴ ከተማ ተገኝተው የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ አድማሱ ሉሉ እንዳሉት፣ በምክር ቤቶች የሚወጡ ህጎች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝበፐቹን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው የልምድ ልውውጡ የሕዝቦችን ግንኙነትና አንድነት ይበልጥ የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ አድማሱ እንዳሉት፣ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ ምክር ቤቶች ያላቸው አደረጃጀትና ልምድ በተሞክሮነት የሚወሰድ ነው።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጠ በበኩላቸው እንዳሉት የልምድ ልውውጡ  በምክር ቤቶች አሰራርና አደረጃጀት በኩል ያሉትን ጠቃሚ ልምዶች በመለዋወጥ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዋነኛ ዓላማ አለው።

ከእዚህ በተጨማሪ ለረጅም ዘመናት በአብሮነት የቆየውን የሁለቱን ክልል ሕዝቦች የእርስ በርስ ትስስር እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።

የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ በጋብቻና በዝምድና የተሳሰረ የቆየ ታሪክ እንዳለው ገልጸው፣ የእዚህን እሴት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ምክር ቤት ምክትል አፌ-ጉባኤ ወይዘሮ ውዲቱ ጥላሁን በሰጡት አስተያየት ሁለቱ ምክር ቤቶች የጀመሩት ግንኙነት ለሕዝቦች የጋራ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመደጋገፍ ባህል ከማዳበር አኳያም ምክር ቤታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

"ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት የሚሯሯጡ አካላትን ሴራ ለማክሸፍ ዛሬም እንደትላንቱ በጋራ ልንቆም ይገባል" ብለዋል።

የሁለቱ ክልል ምክር ቤቶች እያደረጉት ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የፌዴራሊዝም ስርዓት ግንባታን ከማጠናከር አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ምክር ቤት አፌ-ጉባኤ አቶ ሙሉጌታ ፈይሳ ናቸው።

"በልምድ ልውውጡ የተሻሉ ተሞክሮዎችን ያገኘንበት ነው" ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ለመድረኩ ቀጣይነት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

አቶ ሙሉጌታ አንዳሉት፣ የለምድ ልወውጡ በግምገማና ክትትል፣ በአሰራርና አደረጃጀት እንዲሁም በሌሎችም የምክር ቤት የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ልምድ ልውውጡም የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ በክልሎቹ የወጣቶችና ሴቶችን ግንኙነት ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ የነቀምቴ ከተማ ምክር ቤት ተወካዮች በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት በቀጣይ ወደ አማራ ክልል በመሄድ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ተወካዮች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ አንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይም ወደአዲስ አበባ በማቅናት ተሞክሮ ይቀስማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ኢዜአ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 27/2010 ከሶስት ዓመት በፊት በከፍተኛ ወጪ የተገዛ 183 ሺህ ኩንታል ፖታሽየም አስካሁን ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በየወሩ ለባንክ ወለድና ለመጋዝን ኪራይ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን  የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓቶችና እርሻ መሣሪያዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ አምስት ድርጅቶች ለግብርና ውጤታማነት የተሻለ ዓቅም ለመፍጠርተ ተጣምረዉ የመሰረቱት ድርጅት ነዉ፡፡

ኮርፖሬሽኑ በማዳበሪያ ግብይትና አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እርምጃ እንዲወሰድባቸዉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለዉ ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ያለዉ የማዳበሪያ አቅርቦት ረጅም ሂደት ያለው በመሆኑ የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም፡፡

የተገዙት ማዳበሪያዎች በወቅቱ ከመጋዘን እየወጡ ባለመሆናቸዉ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ለአብነትም በ2007 ዓ.ም የተገዛ 183 ሺህ ኩንታል ፖታሽየም በመጋዘን ተከማችቶ ይገኛልም ብለዋል፡፡

"ይህም በየወሩ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለመጋዝን ኪራይ እንድናወጣ ተገደናል" ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም ብቻ በመጋዘን ተከማችተዉ ቶሎ ባልተነሱ የማዳበሪያ ክምችት በባንክ ወለድ፤ ቅጣትና የውጭ ምንዛሬ ጭማሪ ምክንያቶች 114 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንደወጣ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከወጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ በሚከሰት የፋይናንስ እጥረት፣ የወደብ እና ትራንስፖርት አጠቃቀም ችግር ፣ የክፍያ መዘግየት ፣ ተገዝተዉ ወደ አገር ዉስጥ የገቡ ማዳበሪያዎችን ቶሎ አለመረከብ የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

"እነዚህ ሁሉ ችግሮች በዋናነት አርሶ አደሩን እየጎዱት ስለሆነ በአገሪቱ ቀልጣፋ የማዳበሪያ ግብይት እና አቅርቦት ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት በአፋጣኝ ሊበጅ ይገባል" ብለዋል፡፡

የእርሻ እና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ችግሩ መኖሩን አምነው የማዳበሪያ ግብይትንና አቅርቦቱን የሚመራ ከሁሉም የሚመለከታቸዉ አካላት የተውጣጣ ስትሪንግ ኮሚቴ በፌደራል ደረጃ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙትን የማዳበሪያ ምጠና ማቀነባበሪያ  ፋብሪካዎች ወደ ስራ በማስገባት በክምችት ላይ ያሉ ማዳበሪያዎችን ለግብዓትነት ለማዋል እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ዶክተር ካባ የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለመፍታትም ለማዳበሪያ ግዥ የሚሆን ተዘዋዋሪ ገንዘብ ተይዞ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ከማዳበሪያ ፍላጎት ጥናት እስከ አቅርቦት የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንም አውስተዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሳዬ ዘሪሁን በበኩላቸዉ በማዳበሪያ ግዥና ስርጭት የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በቶሎ እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከክልል የመጡ በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የሚሳተፉ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በማዳበሪያ ግብይት፣ አቅርቦትና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ እልባት የሚሰጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ ለማካሄድ ለታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር  27/3/2010 አዲስ አበባ ህዳር 27/2010 ጣሊያን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ የአንድ ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገች።

 የድጋፍ  ስምምነቱን  በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ቢሮ ዳይሬክተር ሚስ ጊኔቭራ ለቲዚያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ጊሊያን ሜልሶፕ በአዲስ አበባ ፈርመዋል።

 820 ሺህ ሕጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርገው የዚህ ፕሮጀከት ስምምነት ፣ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን ድጋፉ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በተለይ የህጻናት ልደት ምዝገባን ለማጠናከር ያለመ ነው።

 የኦሮሚያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መርድ ጉደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፕሮጀክቱ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ፣የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት፣መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግና ተያያዥ ስራዎችን ለማዘመን ያግዛል።

 ጣልያን ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው አጠቃላይ የልማት ስራዎች ድጋፍ ከሚያደርጉ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ መካከል ተጠቃሽ አገር ናት።

 ጣልያን የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት ኢጋድ አጋር አካላት ፎረም የጋራ ሊቀመንበር ስትሆን በፎረሙ ለሚከናወኑ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት።    

 ከ300 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ያላቸው ኢትዮጵያና ጣልያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከጀመሩ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኗቸዋል።

 በኢትዮጵያ የተቀናጀ፣ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ አላማ ያደረገና ለሶስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ የ125 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ትብብር ስምምነት አገራቱ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

Published in ማህበራዊ

ፍቼ ህዳር 27/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው  ዓመት ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ ማካሄዱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ምርጫ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አስታወቀ።

አስተባባሪው አቶ አባቡ ዘውዴ ዛሬ እንደገለጹት የተመለመሉት የምርጫ አስፈጻሚዎቹ  በዞኑ 13 ወረዳዎች ለሚገኙ ምርጫ ክልሎች  የሚያገለግሉ ናቸው። 

ካለፈው ሳምንት ወዲህ የተመለመሉት የምርጫ አስፈጻሚዎች 65 ሲሆኑ እነዚህም በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል አምስት ሆነው የሚመደቡ ይሆናል፡፡

ከተመለመሉት  መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አዲስ ምርጫ አስፈፃሚዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ነባር ናቸው፡፡

ምርጫ አስፈጻሚዎቹ  በተያዘው  ዓመት  የሚካሄደውን  የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤት አባላት ምርጫ  ነፃ ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለፀ  በህብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎችና የአስተዳደር አካላትን ጭምር በማሳተፍ  የተመለመሉት የምርጫ አስፈፃሚዎቹ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛና በህዝብ ውስጥ  አመኔታ ያተረፉ  ናቸው።

ያለ አድሎ ሁሉንም ወገን በታማኝነት ለማገልገልና የምርጫውን ስራ በትጋት ለመስራት የሚያስችል  የትምህርት ዝግጅትና መልካም ስነ ምግባር እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይም በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን  ለማስፈፀም  በሚያስችላቸው ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተመልክቷል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 27/2010 በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ድጋፍ መደረጉን የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድና የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት አፈጻጻም ዛሬ አቅርቧል።

ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢ በተከሰተ ግጭት ከ900 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ለተፈናቀሉትና በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለተጠለሉ ዜጎች በመንግስት፣በህብረተሰቡና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች  የምግብ፣ የመጠለያና ሌሎች ድጋፎች መደረጉን ገልጸዋል።

ከተረጂዎቹ መካካል 629 ሺህ የሚሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው።

መንግስት ለተፈናቃዮቹ ከ48 ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም በጸጥታና በመሰረተ ልማት ችግሮች እርዳታውን በፍጥነት የማድረስ ችግር ገጥሞት እንደነበር ጠቁመዋል። 

"የአደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከት የመንግስትን አቅም እየተፈታተ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ ችግሩን ለመፍታት ተረጂዎችን መልሶ በማደራጀት በኩል የሚሰራው ስራ የክልሎች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

በቅርቡም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱና የማደራጀት ስራ ለማከናወን የቅድመ ዝግጀት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበር ክንፌ በበኩላቸው እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች የሚደረገውን ድጋፍ በተሻለ ሁኔታ ለማቀላጠፍ ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና ከተረጂነት ነጻ ለማውጣት የሚደረገው ስራ ማቀላጠፍ እንዳለበት ምክር ቤቱ አሳስቧል።

በመረጃ ክፍተት ሊረዳ የሚገባው ዜጋ እርዳታ እንዳያገኝ የሚያደረጉ አመራሮችንና ሰራተኞችን በህግ የሚጠየቁበትን አሰራር መዘረጋት እንዳለበት ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ አንድም ዜጋ በእርዳታ እጥረት ሳቢያ ህይወቱን እንዳያጣ የሚያደርገውን ጥረትና፣ ለሴቶች፣ ለህጻናትና ለነፍሰ ጡር እናቶች በተለየ ሁኔታ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ወይዘሮ ጀምበር አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን