አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 05 December 2017

መቀሌ ህዳር 26/2010 ህገ መንግስቱ የፀደቀበት ህዳር 29 የሚከበረው በዓል የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው  የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤዋ 12ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን አስመልክተው ዛሬ እንደገለጹት ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ ህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበር አድርጓል፡፡

ህገመንግስቱ የፀደቀበትን ህዳር 29 በየዓመቱ ሲከበር ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  አንድነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክርና የመፈቃቀር ቃልኪዳናቸውን የሚያድሱበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ የጠባቦችና ትምክህት ኃይሎች መሳሪያ እንዳይሆንና  በሚካሄዱ የልማት ስራዎች የድርሻውን እንዲወጣ የሚያግዝ ትምህርት በቀጣይነት እንደሚሰጥ ወይዘሮ ቅዱሳን ጠቅሰዋል። 

ትምህርቱ በየደረጃው በሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶችና በትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ ጠቁመው በዋነኛነትም ህገ መንግስቱን በሚገባ ለማስገንዘብ የሚያስችል  የማስተማሪያ ሰነድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

"በህገመንግስታችን የደመቀ ህብረብሄራዊነታችን ለህዳሴአችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአፋር ክልላዊ መንግስት ሰመራ በሚከበረው 12ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለመሳተፍ የትግራይ ፣ የኩናማና የኢሮፕ ብሔረሰቦች ተወካዮች ዛሬ ወደ ስፍራው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ዲላ ህዳር 26/2010 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን መሬት የሌላቸው አባወራዎችን በገቢ ማስገኛ ስራና በሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም የሚያሳትፍ ፓኬጅ መቀረጹን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማያም ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ መንስኤ ለመለየት ጥናት ተደርጓል።

በዚህም 12 ሺህ 475 አባውራና እማውራዎች መሬት አልባ ሲሆኑ ከ 0 ነጥብ 1 ሄክታር በታች መሬት ያላቸው 48 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም በዞኑ እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

ችግሩም ዜጎችን ሥር ለሰደደ ድህነት እንዲጋለጡና ለኢኮኖሚያዊ እድገት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት፣ አባወራዎቹና እማወራዎቹ መሬት አልባ የሆኑት በቀደምት ስርዓት በተፈጠረ ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውርስና ሲቸገሩ መሬት ቆርሰው መሸጣቸው ነው፡፡

የመሬት ጥበትም ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኦሞ ማፍክሮ ፋይናንስ ተቋም በአካባቢው ባልተስፋፋበት ወቅት አራጣ አበዳሪዎች ቡናቸውንም ሆነ ትንሽ መሬታቸውን በመቀራመት አርሶ አደሩን ለከፋ ድህነት ሲዳርጉ መቆየታቸውን ነው የገለጹት፡፡

አንዳንድ ባለሃብቶችም በቡና ኢንዱስትሪዎቻቸው አካባቢ መሬት ያለአግባብ በማስፋፋት አርሶአደሮች ከመሬት ባለቤትነት እንዲወጡ መዳረጋቸውን ጥናቱ ማረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት መሬት አልባ አባውራዎችን በገቢ ማስገኛ ሥራና በሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም የሚያሳትፍ ፓኬጅ መቀረጹን ገልጸዋል፡

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻሰፊ መሬት በማይፈልጉና በጓሯቸው ለሚሰሩ ዜጎች በንብ ማነብ፣ በዶሮ  እርባታና በከብት ማድለብ ሥራዎች  እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡

በከተሞች የሚኖሩ መሬት አልባዎችንም በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ገብተው በመስራት ሃብት እንዲያፈሩ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን በጥምር እርሻ የዳበረ ልምድ ያለው ሲሆን አካባቢው ለም በመሆኑ በቡና፣ እንሰትና ፍራፍሬ ምርት ይታወቃል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ህዳር 26/2010 የሃገሪቱን ልማት እና እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ መላው አመራር የትምህርት ልማት ሰራዊቱን በማነቃነቅ መስራት እንዳለበት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ አሳሰቡ።

ለሁለት ቀናት በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት ያለ ትምህርት ልማትና እድገት ማምጣት ስለማይቻል ሁሉም አመራር የትምህርት ልማት ሰራዊቱን በማነቃነቅ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል።

ኩረጃን የሚጸየፍና በድካሙና በልፋቱ ለውጤቱ የሚተጋ ተማሪ ለማፍራትም መምህራን እያበረከቱት ካለው አስተዋጽኦ ጎን ለጎን አመራሩ ለተማሪ ስነ-ምግባርና ውጤት መሻሻል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።

የንቅናቄ መድረኩ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች መላውን ህዝብና የትምህርት ማህበረሰብ በማሳተፍና ለውጥ ማምጣት በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ ከዞን እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች የሚገኘው አመራር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አቶ ደሴ ጠቁመዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አመራሮች ባወጡት የአቋም መግለጫም የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተደረገው እንቅስቃሴ የተገኘውን ውጤት በተማሪ ውጤትና ስነ-ምግባር ላይ ለመድገም በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

"የክልሉን ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቀጣይነት የማረጋገጥ ራዕይ ላይ የተጋረጠውን ፈተና በመቅረፍ በግብር ይውጣ እንቅስቃሴ የተሸበበውን የትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ በተጨባጭ ከተማሪ ውጤትና ስነ-ምግባር መሻሻል ጋር በማስተሳሰር እንሰራለን" ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ዲላ ህዳር 26/2010  በደቡብ ክለል ስድስተኛው መላው የጌዴኦ ዞን ጨዋታዎች ውድድር በዲላ ከተማ በሚገኘው ሁለገብ ስታዲየም ዛሬ ተጀመረ ፡፡

 በውድድሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ የምስራች ዳካ እንደገለጹት በውድድሩ ላይ ከስድስት ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች በ10 የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።

 "ውድድሩ ወንድማማችነትን የምናጠናክርበት አጋጣሚ ነው ያሉት" ኃላፊው ተሳታፊዎች እስከ ፍፃሜው ድረስ ስፖርታዊ ጨዋነትን በማስፈን የውድድሩን ዓላማ እንዲያሳኩም ጥሪ አቅረበዋል ።

 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 4/2010 በሚቀጥለው ውድድር ላይ የስፖርት አፍቃሪው ህብረተሰብ በስፍራው በመገኘት ድጋፉን እንዲሰጥም ጠየቀዋል።

 ለዲላ ዙሪያ እግር ኳስ ቡድን የሚጫወተው ተወልደሚካኤል ሳሙኤል በእለቱ እንደገለጸው ውድድሩ ከተሳትፎ ባለፈ ያለውን ብቃት በማሳየት እራሱን ለተሻለ ደረጃ ለማብቃት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥርለት ነው።

 በውድድሩ ላይም በመልካም ስነ-ምግባርና ስፖርታዊ ጨዋነት የታዳሚውን ቀልብ ለመሳብና ለማስደሰት መዘጋጀቱንም ተናግሯል።

 የወናጎ ወረዳ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነው ተካልኝ መንገሻ በበኩሉ ውድድሩ እስከ መጨረሻው ድረስ አስደሳች ሆኖ እንዲቀጥል የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አስረድቷል ፡፡

 በውድድሩ መክፈቻ ላይ በወንዶች እግር ኳስ ግጥሚያ የተገናኙት የወናጎ እና የኮቾሬ ወረዳዎች አንድ እኩል ተለያይተዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 26/2010 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሚካሄደው ፕሬዚዳታዊና ስራ አስፍጻሚዎች ምርጫ 21 ሰዎች በእጩነት ቀርበዋል።

በፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም  ይደረጋል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳታዊና ስራ አስፈጻሚ ምርጫ  ቅድመ ሁኔታዎች ትክክለኛነት ይጎላቸዋል በሚል እንዲራዘም መደረጉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ምርጫው ታህሳሰ አጋማሽ ላይ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲደረግ መወሰኑና የጉባኤው አባላት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አስመራጭ ኮሚቴ መመረጣቸው ይታወሳል።

የምርጫ ጊዜው ሲራዘም ክልሎች አንድ አንድ እጩ ብቻ እንዲያቀረቡ የሚለውን በማስተካከል ከአንድ በላይ ስራ አስፈጻሚዎች መቅረብ እንደሚችሉ ነው የተገለጸው።

ይህ ተከትሎም በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በእጩ ስራ አስፈጻሚነት የሚወዳደሩት ሰዎች ቁጥር ከ11 ወደ 16 ከፍ ያለ ሲሆን በሰመራው ጉባኤ ከ16ቱ ውስጥ 10 ስዎች ለስራ አስፈጻሚነት ይመረጣሉ።

በእጩ ስራ አስፈጻሚት ከቀረቡት 16 ስዎች መካከል አቶ ዮሴፍ ተስፋው፣ኢንጀነር ኃይለእየሱስ ፍስሀና አቶ አስራት ኃይሌን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀርበዋል።

የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ደግሞ ኮለኔል አወል አብዱራሂምና አቶ ወልደ ገብርኤል መዝገቡን  ሲያቀርብ ከደቡብ ከልል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦን አቅርበዋል።

የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ዶክተር ሲራክ ሀብተማሪያምን በእጩ ስራ አስፈጻሚነት አቅርቧል።

የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ዶክተር ሀይሌ ኢቲቻ እና አቶ ከማል ሁሴንን በእጩነት አቅርቧል።

አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ፣ዶክተር ቻን ጋትኮት ከጋምቤላ አቶ አሊሚራህ መሀመድ ከአፋር ክልል፣ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ከቤኒሻንጉል ጉምዝና አቶ አብዱረዛቅ ሀሰን ከሶማሌ ክልል በእጩ ስራ አስፈጻሚነት የቀረቡ ዕጩዎች ናቸው።

በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንት ለመምራት በፊት ከቀረቡት እጩዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል በእጩ ፕሪዚዳትነት ባቀረበው በአቶ አንተነህ ፈለቀ ቦታ አቶ ኢሳያስ ጂራን ማቅረቡ አይዘነጋም።

ሌሎች ክልልች ጋር የበፊቶቹን እጩዎች  ያቀረቡ ሲሆኑ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮጊስ ከደቡብ ክልል፣አቶ ተካ አስፋው ከአማራ ክልልና አቶ ዳግም መላሼን ከጋምቤላ ክልል በእጩ ፕሪዚዳንትነት  ቀርበዋል።

አሁን ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሪዚዳነት የሆኑት አቶ ጁነዲን ባሻ በድጋሚ  ለቀጣዩ አራት ዓመት እንዲመሩ ድሬድዋ ከተማ አስተዳድር በእጩነት አቅርቧቸዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 26/2010 በአፋር ብሔራዊ ክልል አፍዴራ ወረዳ  ጀርመናዊው በመጎብኘት ላይ እንዳለ በተፈጸበት ጥቃት ሕይወቱ በማለፉ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ።

በአፍዴራ ወረዳ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በቱሪስቶች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የጀርመናዊው ሕይወት ሲያልፍ፤ አንድ ኢትዮጵያዊ አስጎብኝ ቆስሏል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ በጎብኚው ላይ በተፈጸመ የግድያ ወንጀል መንግስት ምርመራ እያደረገ ይገኛል።

ወንጀሉ የተፈጸመው በወረዳው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ትናንት ምሽት ተኩስ በመክፈታቸው መሆኑ ተገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት እንደገለጹት፤ ግድያውን አስመልክቶ የፀጥታ ኃይሎች ምርመራ እያደረጉ ነው።

ድርጊቱም ሙሉ በሙሉ ከተጣራ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

ወንጀሉ በፀረ-ሠላም ኃይሎች መፈጸሙን  ገልጸው ጽህፈት ቤቱ፤ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ሠላማዊና የተረጋጋ መሆኑን ነው ያመለከተው።

የመቁሰል ጉዳት የደረሰበት መቀሌ ወደሚገኘው አይደር  ሪፈራል ሆስፒታል መላኩ ታውቋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ህዳር 26/2010 ወጣቶች የብሄር ብሄረሰቦችን የመከባበርና የመቻቻል ባህል የማዳበር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገነዘበ።

31 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች 12ኛውን የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም አክብረዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት ተማሪዎችን፣ መምህራንና የትምህርት ቤቶች የአስተዳደር ሰራተኞችን በማሳተፍ ሲከበር ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ያለው አባተ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ወጣቶች እርስ በእርስ በመከባበር፣ በመደማመጥ፣ በመደጋገፍና የጋራ ጥቅምን በማስቀደም ልዩነቶችን የማቻቻል ባህል የማዳበር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

በአገሪቷ ልማት እንዲሁም አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድም የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል።

በዓሉ "በአገሪቷ ለተመዘገቡ ዘርፈ ብዙ ድሎች ዕውቅና በመስጠት አንድነታችንን አጠናክረን ህገ-መንግስታዊ የፌዴራል ስርዓታችን ወደ ኋላ እንዳይመለስ ቁርጠኝነታችንን የምናረጋግጥበት ነው" ብለዋል።

ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከፀረ ሰላም ኃይሎች በመጠበቅ ለተጨማሪ ድሎች እንደምንሰራ ቃልኪዳናችንን በማደስ የምናከብረው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና በአጠቃላይ ከወጣቶች የላቀ ተሳትፎ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ህገ መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከውስጣዊና ውጫዊ አደጋዎች መጠበቅ የሁሉም ዜጎች በተለይም የወጣቶች ግንባር ቀደም ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ብሄር ብሄረሰቦች ባደረጉት ትግል ወጣቶች፣ ተማሪዎችና መምህራን የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበርም አውስተዋል።

የትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ በበኩላቸው ህገ መንግስቱ በትምህርት ልማት ዘርፍ ለዘመናት እድል ተነፍገው የቆዩ ዜጎች የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንገድ መክፈቱን ጠቅሰዋል።

ከፍለው መማር የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚነትን ያጎለበተ እንደሆነም አክለዋል።

የሕብረተሰብ ተሳትፎን መሰረት ያደረጉ የትምህርት ልማት ፕሮግራሞች መተግበራቸው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ካስገኛቸው ጥቅሞችና መብቶች መካከል ጠቅሰዋል።

በዓሉ ለሰላምና ለአገር ግንባታ በተለይም ለትምህርት ልማት ሰራው ስኬታማነት እውን መሆን ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

ከብዝሃነታችን የመነጨ አንድነታችን እንዲረጋገጥ መስዋዕትነት በከፈሉ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ስም ቃል የምንገባበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ሰመራ ህዳር 26/2010 በ12ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ የሚሳተፉ የአምስት ክልሎች የህዝብ ተወካዮች ማምሻውን ሰመራ ከተማ ገብተዋል፡፡

 የገቡትም የአማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡

 የክልሉ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ማስተባበሪያ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ አወል ከሌሎች አመራሮችና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ለእንግዶቹ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

 ከአማራ ከመጡ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መስፍን አድማሱ በሰጡት አስተያየት  በአፋር ክልል የተለያዩ ከተሞችና ወረዳ ነዋሪዎች ለቡድኑ  ባደረገው ወገናዊ አቀባበል መደሰታቸወን ገልጸዋል፡፡

 የትግራይ ተሳታፊ ወይዘሮ ሩታ ተስፍዮ  በበኩላቸው ከአፋር አበአላ ወረዳ ጀምሮ ሰመራ እስኪገቡ ድረስ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በባህላዊ ጭፍራ የታጀበ አስደሳች አቀባባል እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዳማ ህዳር 26/2010 በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመነት የዘለቀውን የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች ጠብቆ ለሀገር ልማትና ዕድገት ቀጣይነት መስራት እንደሚገባ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር ገለፁ፡፡

 በቢሾፍቱ ከተማ ዛሬ የተካሄደው የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ትስስር የማጠናከር፣ የአንድነት፣ ሰላምና የልማት ኮንፈረንስ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም ማምሻውን ተጠናቋል።

 የቤንሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የሁለቱ ክልል ህዝቦች ለዘመነት የዘለቀ የመቻቻልና የመከባበር የጋራ እሴት አላቸው።

 ''ይሄንን እሴት በመጠቀም ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት በአንድነት ልንቆም ይገባል'' ብለዋል።

 የክልሉ መንግስት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ይበልጥ ለማስተሳሰር የሚያስችለውን የተቀናጀ እቅድ ይፋ መደረጉን ጠቅሰዋል።

 ''የሁለቱን ክልል ህዝቦች ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዕቅዱን በሙሉ አቅም ለመተግበር መረባረብ  ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡

 የኦሮሞና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር የጋራ እሴቶቻቸውን ለመሸርሸር የሚደረጉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በጋራ መመከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

 ''የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዝብ ተወካዮች ወደ ኦሮሚያ ሲመጡ ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነትና የህዝቦችን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት የሀገርን  ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ማስቀጠል ነው'' ብለዋል።

 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው የህዝቦች አብሮነትና አንድነት ከሌለ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጠቅሰዋል፡፡

 የኦሮሞና የቤንሻንጉል ክልል ህዝቦች ለሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጠናከር ይበልጥ ተቀራርበውና ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 ሁለቱ ህዝቦች የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር አብረው ተሰልፈዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ''አሁንም አንድነታቸውን  ይበልጥ በማጠናከር ለዴሞክራሲያዊት ሀገር ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መጫዎች  ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል።

 በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የህዝብ ለህዝብ ትስስርና የሰለም ኮንፈረንስ ላይ የጋራ የሰላምና ልማት ዕቅድ የፀደቀ ሲሆን የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶች በሁለቱ ክልል ፕሬዝዳንቶችና አመራሮች ተፈርሟል።

 በኮንፈረንሱ ላይ ከኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልል ሁሉም ዞኖችና የከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ ከ500 በላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 26/2010 ሕገ-መንግስቱ ለብሔር ብሔረሰቦች ያጎናጸፋቸውን እሴቶች ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራቸውን በትኩረት እንደሚያከናውኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሰራተኞች ገለጹ።

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች የብሔር ብሔረሰቦች፣ የነጭ ሪቫንና የኤች.አይቪ/ኤድስ ቀንን ዛሬ በፓናል ውይይት አክብረዋል።

ኢዜአ የፅህፈት ቤቱን የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የብሔር ብሔረሰቦችን አብሮነት፣ መቻቻልና አንድነት ለማስቀጠል ስለሚያከናውኗቸው  ተግባራት ጠይቋል።

የጽህፈት ቤቱ የክልል ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሐመድ ሳኒ ህገ መንግስቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉአላዊነት መገለጫና መብታቸውንም ማስጠበቂያ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ህገ መንግስቱ የሰጠውን እሴት እንዲያውቀው የማድረግ ስራ የኮሙኒኬሽን ባለሙያው ነው፤ በዚህ ረገድ እንደ ባለሙያ የሚጠበቅብኝን ለመወጣት ዝግኙ ነኝ ሲሉ መልሰዋል።

የብሔር ብሔረሰቦችን የጋራ መግባባት የሚያጠናክሩ መልዕክቶችን በመቅረጽ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ የሚዲያ ብዝሃነት ጄኔራል ዳይሬክቶሬት የሚዲያ ፖሊሲ ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ገብረስላሴ በበኩላቸው እንደ ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ህብረተሰቡ በህገ መንግስቱ ያሉ እሴቶች እንዲገነዘባቸው ለማድረግ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት እንደሚያደርጉም አክለዋል።

"የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት እንዲከበር በማድረግ ረገድ ህብረተሰቡን የማስተማር ሚናዬን እወጣለሁ" ያሉት ደግሞ የጽህፈት ቤቱ የግንኙነትና የገጽታ ግንባታ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ አብዱራህማን ናስር ናቸው።

የህብረተሰቡ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከማድረግ አንጻርም እንደ አገሪቷ ዜጋ ድርሻ እንዳለቸው ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው በበኩላቸው ህብረተሰቡ ማንነቱን ይበልጥ እንዲያውቅ የማድረግ ስራ በኮሙኒኬሽን ዘርፉ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች በቅርበት በመከታተል ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በህብረተሰቡ መካከል ያሉ የመከባበርና ሌሎች እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የአስተሳሰብ ቀረጻ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በፅህፈት ቤቱ የተጀመሩ ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ወይዘሮ ፍሬህይወት ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን