አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 04 December 2017

አዲስ አበባ ህዳር 25/2010 የፋርማሲ ሙያ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ መምጣቱ አሳስቦናል ሲሉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማህበር 4ኛውን የኢትዮጵያ የፋርማሲ ባለሙያዎች ቀን "ከምርምር እስከ ጤና እንክብካቤ የፋርማሲ ባለሙያዎች አገልግሎት አሰጣጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ አክብሯል።

ቀኑን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት  ለህብረተሰቡ በሙያው ላይ አመኔታ ለማጣቱ ተጠያቂው ባለሙያው ነው፣ አመኔታውን መመለስም የራሱ ተግባር ነው የሚል ሀሳብ በስፋት ተነስቷል።  

የፋርማሲ ባለሙያው አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን እንደገለጹት ባለሙያዎች ደንበኞች ወደ መድኃኒት ቤቶች በሚመጡበት ወቅት የሚይዙበት መንገድና ሥነ ምግባር ላይ የሚስተዋለው ችግር ሙያው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ከበሬታ እንዲያጣ እያደረገው ነው።

በተለይም የፋርማሲ ባለሙያዎች የስነ ምግባር ጉድለት ህብረተሰቡ በሙያው ላይ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖረው እያደረገ ነው ብለዋል።

"በዘርፉ ተመርቀው በሚወጡ ባለሙያዎች ዘንድ ያለው የክህሎትና የተግባር እውቀት ክፍተትም ሌሎች ወደ ሙያው እንዳይገቡ እያደረገ ነው" ሲሉ አቶ ኃይለስላሴ ገልጸዋል።

ችግሮቹን በመፍታት ሙያው ያለውን ተቀባይነት ለማሳደግ የፋርማሲ ባለሙያዎች የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

ሌላዋ ፋርማሲስት ወይዘሮ ዮዲት አሰፋ በበኩላቸው ባለሙያው የፋርማሲ ሙያ ከሌሎች የህክምና ዘርፎች ጋር ያለውን ልዩነት ለህብረተሰቡ ከማስገንዘብ አንጻር በቂ ስራ እንዳልተሰራ ገልጸዋል።

ፋርማሲስት ስራው መድሃኒት መሸጥ ነው የሚል አስተሳሰብ ከህብረተሰቡ እንደሚነሳና ይህም በባለሙያዎቹ ዘንድ ሙያውን የማስተዋወቅ ስራ እንዳልተሰራ የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

የፋርማሲ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በተግባር ደረጃ ከህመምተኛው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ዝቅተኛ በመሆኑ ተመርቀው ወደ ስራ በሚገቡበት ጊዜ ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ እንዳይሆን አድርጎታልም ብለዋል።

"በፋርማሲ ትምህርት ቤቶችና በሆስፒታሎች መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ አለመሆን የተሻለ የፋርማሲ አገልግሎት እንዳይኖር አድርጓል" የሚሉት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ለገሰ ጨልባ ናቸው።

የፋርማሲ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አብዛኛውን የትምህርት ጊዜ በንድፈ ሀሳብ የሚያሳልፉ በመሆናቸው በሆስፒታሎች ከህሙማን ጋር እንዲሁም በመድሃኒት አቅርቦት ዙሪያ ስላሉ ጉዳዮች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።

ሆስፒታሎች የፋርማሲ ባለሙያዎች የተግባር ስራ እንዲሰሩ የሚያሳዩት ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፋርማሲ ሙያ እንደ ህክምና ሙያ ሁሉ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ያላሰለሰ ጥረት ልናደርግ ይገባል ሲሉ ነው ዶክተር ለገሰ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መለሰ ጎጂ በበኩላቸው ማህበሩ በሙያው ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው ይላሉ።    

ችግሮችን በመለየትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስትራቴጂክ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፋርማሲ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተግባር ሙከራ ጊዜያቸውን ለማሳደግ ከመንግስት ጋር በመነጋገር የትምህርት አሳጣጥ ስርዓቱ ላይ ማሻሻያ መደረጉንም ገልጸዋል።

የባለሙያዎችን የስነ ምግባር ችግር ለመቅረፍም ማህበሩ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች የጀመረውን ተከታታይ ስልጠና እንደሚቀጥልና የተጠያቂነት ስርዓቱም እንደሚጠናከር ነው ፕሬዝዳንቱ ያብራሩት።

የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተሻለ የፋርማሲ አገልግሎት ለመስጠት ከማንም በላይ ባለሙያው በመቀጠልም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

በ1964 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማህበር ከሁለት ሺህ በላይ አባላት አሉት።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ህዳር 25/2010 የህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት በየደረጃው የተቋቋሙ የትምህርትና ቅስቀሳ ኮሚቴ አባላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራ የደቡብ ክልል ኮሚሽን በክልሉ ለሚገኙ የአራተኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ የትምህርትና ቅስቀሳ ኮሚቴ አባላት በሃዋሳ ከተማ ስልጠና እየሠጠ ነው፡፡

የብሔራዊ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ወልደማርያም እንዳሉት አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከየካቲት 4 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ለእዚህም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የህዝብና የቤት ቆጠራ መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመረዳት ቆጠራው እንዲሳካ በየደረጃው የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ 

በክልሉ ለሚካሄደው ቆጠራ አስካሁን ድረስ የቆጠራ ካርታ የማጠናቀቅ፣ የቆጠራ ኮሚሽን ኮሚቴ የማቋቋምና በአደረጃጀት የማስተሳሰር ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡

ቆጠራው ጂፒኤስ የተሰኘ አቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ በተገጠመለት ታብሌት የእጅ ኮምፒውተር በመጠቀም እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም አገሪቱ ካስገባቻቸው 180 ሺህ ታብሌት ኮምፒውተሮች 30 ሺዎቹ ለክልሉ እንደሚደርሱ ጠቁመዋል፡፡

ቆጠራው ቴክኖሎጂውን የመጠቀም ልምድና እውቀት ባላቸው መምህራን፣ የጤናና የግብርና  ባለሙያዎች እንደሚካሄድም አስረድተዋል።

አቶ ብርሃኑ አንዳሉት በክልል 28 ሺህ 954 የቆጠራ ጣቢያዎች የተለዩ ሲሆን 2 ሺህ ተቆጣጣሪዎችም ይሳተፋሉ፡፡

ስልጠናው ለተቋቋመው የትምህርትና ቅስቀሳ ኮሚቴ አባላት የቆጠራውን ዓላማና አስፈላጊነት በአግባቡ አውቀው ትምህርታዊ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

በሦስተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ የክልሉ ሕዝብ ቁጥር 16 ሚሊዮን እንደነበረም አቶ ብርሃኑ አስታውሰዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ስሜ አንበሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በጋሞ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞንና ባስኬቶ ልዩ ወረዳ ከዞን እስከ ቀበሌ የቆጠራ ኮሚቴ ማቋቋሙንና ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

በቆጠራው የተመሰከረ ስነ ምግባር ያላቸው፣ የተማሩና በተሰማሩባቸው ሥራዎች የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ሠራተኞች አንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

ከሃዲያ ዞን በስልጠናው የተሳተፉት አቶ ተመስገን ተረፈ በበኩላቸው ስልጠናው የተጣለባቸውን አደራ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትክክለኛውን የህዝብና የቤት ቆጠራ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በመዘጋጀቱም ሥራው ቀላልና ተአማኒ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ከክልሉ 12 ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳ የተውጣጡ 170 ሰልጣኞች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ 

ለቆጠራው በአገር አቀፍ ደረጃ መንግስት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት የመደበ ሲሆን ከ180 እስከ 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችም በቆጠራ ሥራው ይሳተፋሉ ተብሎ አንደሚጠበቅ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 25/2010 መገናኛ ብዙሃን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መቀነስ የሚያስችል ዘላቂነት ያለው ስራ እየሰሩ አይደለም ተባለ።

ተቋማቱ ችግሩን ለመቅረፍ የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ሊያስተካክሉና በፈጠራ የታገዘ የዘገባ አይነት ሊከተሉ ይገባልም ተብሏል።

በተባበሩት መንግስታት የጾታ እኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ተቋም 'በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ የመገናኛ ብዙሃን ሚና' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከጋዜጠኞች ጋር መክሯል።

የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር የሚዲያ ተቋማት ከ16ቱ ቀን ንቅናቄና ከሴቶች ቀን በዓል ባለፈ በስራዎቻቸው ስለሚደርስባቸው ጥቃት በቂና ዘላቂ ሽፋን እየሰጡ አይደለም ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ተቋማትም ተገቢውን መረጃ ለሚዲያ ተቋማት ከመስጠት አንፃር ትብብራቸው አናሳ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የምክክሩ ተሳታፊ ጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየትም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም የህብረተሰቡን ግንዛቤ የመቀየር ስራ በዘላቂነት እየሰሩ አለመሆኑን አምነዋል።

ውጤታማ ስራ ለመስራት መገናኛ ብዙሃኑ የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ማስተካከልና በዘርፉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን አቅም ማጎልበት ላይ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

ጋዜጠኛ ሰሎሜ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንዳለችው መገናኛ በዙሃን  በሴቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አልሰጡም፡፡  

ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ በበኩሏ በጉዳዩ ላይ ለሚሰሩ ስራዎች ኩነት መፈጠርን መሰረት ከማድረግ ባለፈ በዘላቂነት የህብረተሰቡን የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር አቅም ፈጥሮ መስራት እንደሚገባ ተናግራለች።

የጥቃት ክስተቶች ላይ ተመስርተው የሚወጡ ዘገባዎችም አንዳንድ ጊዜ ችግሩን የሚያባብሱ መሆናቸውን ነው ጋዜጠኞቹ የገለጹት።

ሴቶች ላይ አሲድ የመድፋትና የተለያዩ የግድያ አይነቶች በሚዲያ ከተዘገቡ በኋላ ጥቃቱ እየበዛ መጥቷል ነው ያሉት።

ችግሩን ለመፍታት የጋዜጠኛውን ትክክለኛና አስተማሪ ስራ የመስራት አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘለቄታዊ ስራ ባለመሰራቱ የተነሳ ሴቶች ጥቃትን አምነው እስከመቀበል መድረሳቸውን የተናገሩት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካና ኢትዮጵያ ሴቶች ተወካይ ሌቲ ቺዋራ ናቸው።

የሴቶች ጥቃት በዕድሜና ክልል ሳይወሰን በሁሉም ቦታና ሴቶች ላይ እየደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን አስመልክቶ ባወጣው ጥናት 65 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በባሎቻቸው መመታትን አምነው ይቀበሉታል።

በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሶስት በመቶ የሚሆነውን አገራዊ የምርት እድገታቸውን ዝቅ እንደሚያደርገው ነው የጠቀሱት።

እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገራት ደግሞ በዓመት 19 ሚሊዮን ዶላር በጥቃቱ ምክንያት ያጣሉ።

የዚህ ምክንያትም የአብዛኛውን ህዝብ አስተሳሰብ የመቀየር አቅም ያላቸው መገናኛ ብዙሃን በዘርፉ ያላቸው አስተዋጽኦ አናሳ መሆን ነው።

ታዋቂና ትልቅ ቦታ ያላቸው ሴቶች ጭምር የችግሩ ሰለባ በመሆናቸው የመገናኛ ብዙሃኑ በይበልጥ ታች ባሉት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት ተወካይዋ።

ለዚህም የተለመደውን መንገድ በመተው በአዲስና ፈጠራ በታከለበት የአሰራር ስልት ዘገባዎችን ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ህዳር 25/2010 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ ዜጋ ከማፍራት ጎን ለጎን ህገ- መንግስቱን በአግባቡ ተገንዝቦ ለለውጥ የሚተጋ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አግባብነትና ጥራት ኤጄንሲ አስታወቀ።

በሐራምቤ እና ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች አስተባባሪነት የኦሮሚያ ክልል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 12ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ አክብረዋል።

"በህገ መንግስታችን የደመቀ ሕብረ- ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በዓሉ ሲከበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አግባብነትና ጥራት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሞህዬ እንዳሉት ተቋማቱ ዜጎችን በእውቀት በማነጽ በኩል ገንቢ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ይሁንና "የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ትርጉም ያለው ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ መስራት አለባቸው" ብለዋል።

ለእዚህ ደግሞ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት ባለፈ ህገ- መንግስቱን በትክክል ተገንዝቦ ለለውጥ የሚተጋ ትውልድ መቅረፅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

"በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶችና አንድነት ላይ ጥልቅ የሆን ጥናትና ምርምር በማካሄድ የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት በዓሉ ትልቅ መሳሪያ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

በዓሉ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መከበሩ ተማሪዎች እርስ በርስና የባህል ትውውቅ እንዲያደርጉ ከማድረጉ ባለፈ  አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንትና የሐራምቤ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት አቶ ፈይሳ አራርሳ በበኩላቸው ተተኪው ትውልድ ህገ- መንግስትን ተገንዝቦ ለሀገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ተቋማቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ምንጩ ህገ- መንግስቱ ነው" ያሉት አቶ ፈይሳ፣ ተማሪዎች የሁሉም ብሔሮች ማንነትን የማክበርና የማስከበር  ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ወጣቱን ኃይል ሽፋን በማድረግ የህዝቦችን አንድነት ለመሸርሸር የሚደረጉ ማናቸውም ጥረቶች ቦታ እንደማይኖራቸው በዓሉ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የበዓሉ መከበር ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ከመሆኗ በተጨማሪ በመፈቃቀድ ላይ የተገነባች መሆኗን ለተማሪዎች ለማስገንዘብ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ- መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን ዕኩልነትና ነፃነት በአደባባይ የሚያንፀባርቁበት  ዕለት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዲርብሳ ዱፌራ ናቸው።

ለወጣቱ ትውልድ በህገ መንግስቱ ዙሪያ ግንዛቤ በማስጨበጥና አርአያ በመሆን በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ምሁራን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ህገ- መንግስቱ ለዜጎች የሰጠውን መብት ሳይሸራረፍ ሥራ ላይ መዋል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የብዝሃነትና አንድነት መገለጫ ከመሆን ባለፈ ሁሉም በእኩልነት የሚስተናገዱበት መድረክ በመሆኑ ለሀገር አንድነትና መልካም ገፅታ ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ሃራ ገላና ናት።

በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተማሪዎች፣ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ የክልልና የፌደራል መንግስት ሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ህዳር 25/2010 በጎንደር ከተማ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት በማህበራት ለተደራጁ 6ሺህ ነዋሪዎች የግንባታ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የከተማው የህብረት ስራ ማህበራት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳነማርያም ፍሰሃ ለኢዜአ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ለ258 የቤት ስራ ማህበራት የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ታቅዷል።

ተደራጅተው ገንዘብ መቆጠብ ለጀመሩ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ነባር የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቦታ ከሚሰጣቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

እስካሁን 157 ማህበራት ከቤት  ግንባታው  ግምት 20 በመቶ ተሰልቶ 62 ሚሊዮን ብር መቆጠብ እንደቻሉ የገለፁት ኃላፊው "ቀሪዎቹ ማህበራት የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ እንዲያስገቡ ይደረጋል "ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከቦታ ዝግጅት በተጓዳኝ የማህበራት አባላቱ ቀደም ሲል  በራሳቸውም ሆነ በትዳር አጋራቸው የግል መኖሪያ ቤት የሌላቸው መሆኑን የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ኪዳነማርያም ጠቁመዋል።

"በማህበራት ለተደራጁ ነዋሪዎች በነፍስ ወከፍ 150 ካሬ ሜትር የግንባታ ቦታ ይሰጣል" ያሉት ኃላፊው ቦታዎቹ በቅድሚያ የመንገድ፣ የመብራትና ውሃ መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉላቸው አስታውቀዋል፡፡

"በዚህ ዓመት የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ የሚሰጣቸው ማህበራት ላለፉት ስድስት ዓመታት የተደራጁ ናቸው" ብለዋል።

ቀደም ሲል የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተረክበው ለበርካታ ዓመታት ወደ ግንባታ ያልገቡ ማህበራትን በጥናት የመለየት ስራ በቅርቡ እንደሚጀምርም ተጠቅሳል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ ያለ በቂ ምክንያት ወደ ግንባታ ያልገቡ ማህበራትን በጥናት በመለየት ጉዳያቸውን በማጣራት ቦታ  እስከ መንጠቅ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል።

በመንገድ ችግር ሳቢያ ወደ ግንባታ መግባት ያልቻሉ ነባር የቤት ልማት ህብረት ስራ ማህበራትን ችግር ለመፍታት  ሰራል ተብሏል።

በጎንደር ከተማ በ802 የቤት ልማት ህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ 17ሺህ ቤት ፈላጊ የከተማ ነዋሪዎች የግንባታ ቦታ ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 25/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና (ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ) ነገ ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር ይጫወታል።

በምድብ ሁለት የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ነገ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን በካካሜጋ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ያደርጋል።

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ 22 ተጫዋቾችን ይዞ ባለፈው ሳምንት ከኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በምዕራብ በኩል 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ካካሜጋ አቅንቷል።

ዋልያዎቹ ከህዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በውጤት ማጣትና በአቋም መዋዥቅ በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ አመኔታ ያጣው ቡድኑ ባለፉት 10 ዓመታት ከታዩ ብሔራዊ ቡድኖች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

በቅርብ ጊዜ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባደረጋቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤታማ መሆን አልቻለም።  

ብሔራዊ ቡድኑ በህዳር ወር በወጣው የፊፋ የአገራት ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃም 145ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለአራት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ሻምፒዮን የሆነው እ.አ.አ በ2006 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው ውድድር ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ በሚገኝበት ምድብ ሁለት የሚገኙት ኡጋንዳና ብሩንዲ በማቻኩስ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ባካሄዱት ጨዋታ ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ትናንት በሻምፒዮናው መክፈቻ በምድብ አንድ አዘጋጇ ኬንያ ሩዋንዳን ሁለት ለዜሮ ስታሸንፍ በዛው ምድብ የሚገኙት ሊቢያና ታንዛኒያ ያለ ምንም ግብ ተለያይተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለውድድሩ ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች የ60 ሺህ ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን ትናንት ይፋ አድርጓል።

Published in ስፖርት

መቀሌ ህዳር 25/2010 የአካል ጉዳተኞች ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የትግራይ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ።

 የቢሮው ምክትል  ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንም ምክንያት በማድረግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት አካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ የሚያደረጉ ህገ መንግስታዊ ህጎችና ድንጋጌዎች ቢኖሩም በአግባቡ ሲተገበሩ አይታይም።

በትግራይ ክልል ብቻ 96 ሺህ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ የጠቆሙት ምክትሏ፣ ከእነዚህ ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሆኑት 20 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"የእዚህ ዋና መንስኤ የአካል ጉዳተኞች ችግር የህዝብ ችግር ነው የሚል አመለካከት ባለመፈጠሩ ነው" ያሉት ኃላፊዋ፣ መብታቸውን ለማረጋገጥ መንግስታዊና መንግስታዊ ያለሆኑ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ አንደሚገባ አሳስበዋል።

ወይዘሮ ንግስቲ እንዳሉት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "ጠንካራና ዘላቂ ማሕበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ቃል  በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች  በበፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ነገ ይከበራል።

በክልሉ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት አንድ ፎረም መስርተው በዓሉን በባለቤትነት የሚያከብሩት መሆኑ የዘንድሮውን በዓል የተለየ እንደሚያደርገው አስታወቀዋል።

በመቀሌ ከተማ ከሚኖሩ አካል ጉዳተኞች መካከል አቶ ገብረኪዳን ሐዱሽ እንደገለጹት ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠ ህገ መንግስታዊ መብት በተግባር እንዲረጋገጥ ማንኛውም የልማት ዕቅድና ክንውን አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ የኖርበታል።

ሌላዋ አካል ጉዳተኛ ወጣት ገነት ኪዳነ በበኩሏ "የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ መብት የሚያረጋግጥ ህገ መንግስት ቢኖረንም በየደረጃው በሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ቸልተኝነት ምክንያት በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ እየሆንን አይደለንም" ብላለች።

በየቤቱ ጧሪና ጠያቂ የሌላቸው በርካታ አካል ጉዳተኞች እንደሉ ጠቁማ፣ የአካል ጉዳተኞቹን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት አንዲሰሩ ጠይቃለች።

"ሴቶች ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ ለተለያዩ ተደራራቢ ችግሮች ይጋለጣሉ" ያለቸው ወጣቷ፣ የእንዚህን የሕብረተሰብ ከፍሎች ችግር ለመፍታት መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክታለች።    

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ 25/2010 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም ለማስፈን ለምታደርገው ጥረት ጃፓን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

ግጭትን ቀድሞ መከላከል በሚል ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለተውጣጡና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በኢፌዴሪ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺኒቺ ሳይዳ ዛሬ ስልጠናው ሲጀመር እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአህጉሩ ሰላም ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት የጃፓን ድጋፍ አይለያትም።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም የሰፈነባት አገር መሆኗንና በአህጉሩ ሰላም ለማምጣትም የግንባር ቀደምነቱን ሚና በመጫወት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቷን ተናግረዋል።

ለሰላም ማስከበር ተልእኮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በማሰለፍ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከዓለምም ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደተሰለፈች ጠቅሰዋል።

ጃፓን ይህን የኢትዮጵያን ጥረት በገንዘብ፣ በባለሞያና በስልጠና እየደገፈች እንደሆነና ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

እየተሰጠ ያለው ስልጠና የተለያዩ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ የሚቀስሙበትና አገራት በሰላም ማስከበር ስራ ላይ ግጭት ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተ በኋላ እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ልምድ የሚለዋወጡበት ይሆናል ብለዋል።

የማሰልጠኛ ተቋሙ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ኃብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው ጃፓን ለተቋሙ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሞያዎችን በመመደብ በቅርበት ከሚሰሩ አገራት ቀዳሚዋ ናት ብለዋል።

ድጋፉ በግጭት አፈታት ፣ በቅድመ መከላከል፣ በማስተዳደርና ከግጭት በኋላ መልሶ ማገገምን ለሚመለከቱ አጀንዳዎች የሚውል ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ግንባር ቀደም እንደመሆኗ ከስኬቷ በስተጀርባ ያለውን ልምዷን ለአገራት ታካፍላለች ከሌሎችም ልምድ ትቀስማለች ሲሉም ተናግረዋል።

ስልጠናው አገሪቱ በሰላም ማስከበር ዙሪያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክርና ሂደቱን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመምራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነም አመልክተዋል።

ስልጠናውን ከሚከታተሉ 29 ተሳታፊዎች መካከል 11ዱ ከሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ማሊ፣ ላይቤሪያ፣ ካሜሮን፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳንና ማዕከላዊ አፍሪካ የተውጣጡ ናቸው።

ለሁለት ሳምንታት የሚሰጠውን ስልጠና የጃፓን መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት በትብብር አዘጋጅተውታል።

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ህዳር 25/2010 በበጀት ዓመቱ የሀገሪቱን የግብርና ወጪ ምርት በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎችን በብዛትና በጥራት ለውጪ ገበያ ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ትናንት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ መንግስቴ እንደተናገሩት ከግብርና ዘርፉ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ የ2010 በጀት ዓመት የወጪ ሰብል ምርት ልማትና ግብይት ማስፈጸሚያ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

"በ2009/2010 የመኸር ወቅት በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከለማውና ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎች ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ምርት ይጠበቃል" ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ከሚጠበቀው ምርት ውስጥ 1 ሚሊዮን 319 ሺህ ቶኑን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።

"በዘንድሮ በጋ ወራት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ልማት ይሸፈናል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሽንብራ፣ ቦለቄና ሰሊጥን ጨምሮ በመስኖ ከሚለማው ሰብል 25 በመቶ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ በግብርናው ዘርፍ የወጪ ሰብል ምርቶች ግብይት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት፣ የአርሶአደሩን የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻልና ግብይቱን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ይሰራል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልኬ ታደሰ በበኩላቸው ክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እንደ ሰሊጥ፣ ሽንብራና ቦሎቄ የመሳሰሉ ምርቶች በስፋት የሚለሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2009/2010 ምርት ዘመን በመኸር ወቅት ከለማው የሰሊጥ ምርት በተጨማሪ በእርጥበት አዘል 330 ሺህ ሄክታር መሬት በጥራጥሬ ሰብል መሸፈኑን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ እየለማ ካለው መሬት ውስጥ 127 ሺህ ሄክታሩ ለውጪ ገበያ በሚቀርብ የሽንብራ ሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

የማዕካለዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በበኩላቸው በመተማ፣ በቋራ፣ በጠገዴና በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች 250 ሺህ ሄክታር መሬት በሰሊጥ መልማቱን ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ ከአማራ ክልል 11 ዞኖች የተውጣጡ የግብርና ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡ 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 25/2010 "በአፍሪካ መዋቅራዊ ሽግግር እውን እንዲሆን ጠንካራ፣ ልማታዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ለብልሹ አሰራር የማይደራደር አስተዳደራዊ ስርዓት ለማስፈን በቁርጠኝነት መስራት አለብን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉባኤ "መልካም አስተዳደር ለመዋቅራዊ ሽግግር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው በአህጉሪቱ መዋቅራዊ ሽግግር ለማስፈን የሚረዱ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ምክክር ይደረጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለጹት በአፍሪካ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ከአህጉሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ የፖሊሲ መፍትሄ አስፈላጊ ነው።

ለዚህ ይረዳ ዘንድም አፍሪካዊያን ፈጣንና ሁሉን አቀፍ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ከቻሉት የሰሜን ምስራቅ እስያ አገራት ተሞክሮዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በዘርፉ ወደኋላ እንደመቅረታችን እነዚህ አገራት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በሄዱበት ጎዳና ከገጠሟቸው ችግሮች በመማር ያቀድነውን ሽግግር ማፋጠን አለብን" ነው ያሉት።

በሂደቱ የሚፈጠሩ ስህተቶችን ለማረም ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ላለፉት 10 ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ እድገት መመዝገቡ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ አገራት ተወካዮችና የምጣኔ ሃብት ምሁራን እየተሳተፉበት ነው።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን