አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 03 December 2017

አዲስ አበባ ህዳር 24/2010 ኡራጓይ በ2018 ለምታስተናግደው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ከ17 በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይይጄሪያ አቻው ጋር ባደረገው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ አንድ እኩል ወጥቷል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ናይጄሪያ በ22ኛው ደቂቃ በፕሪሺየስ ቪንሰንት ጎል መሪ የነበረች ቢሆንም በ63ኛው ደቂቃ ታሪኳ ደቢሶ ለቡድኗ የአቻነቷን ጎል አስቆጥራለች።

ናይጄሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እድሏን ስታሰፋ የኢትዮጵያ ከ17 በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሜዳ እድሉን ሳይጠቀም ቀርቷል።

የማጣሪያው የመልስ ጨዋታ ታህሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በናይጄሪያ ቤኒን ከተማ በሚገኘው ሳሙኤል ኦግቤዲያ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።

በድምር ውጤት ያሸነፈው ቡድን በቀጣዩ ዙር ከካሜሮንና ከአልጄሪያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር የካቲት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።

ከትናንት በስቲያ የካሜሮን ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ የአልጄሪያ አቻውን አራት ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን ማስፋት ችሏል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ከኬንያ አቻው ጋር እንዲጫወት ተመድቦ የነበረ ቢሆንም የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን በማግለሉ ከናይጄሪያ ጋር እንዲጫወት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) መወሰኑ የሚታወስ ነው።

16 ቡድኖች በሚሳተፉበት ውድድር ሶስት የአፍሪካ አገራት የመሳተፍ ኮታ አላቸው።

የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ፊፋ ዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሲሆን፣ በቀጣይ ለስድስተኛ ጊዜ በዑራጓይ አዘጋጅነት ከኅዳር 11 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ይከናወናል።

 

 

Published in ስፖርት

ጅቡቲ ህዳር 24/2010ጅቡቲ ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት እንደምታጠናክር አስታወቀች።

 የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት 110ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ አክብሯል።

 ንግድ ምክር ቤቱ የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትም ተከፍቷል።

 የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አብድልቃድር ካሚል መሀመድ የንግድ ትርዒቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ዝግጅቱ የመጀመሪያ ቢሆንም አገሪቷ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ የሚያሳይ ነው።

 የንግድ ትርዒቱ ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ከማገዙ ባሻገር ጅቡቲ የሌሎችን ልምድና ተሞክሮ እንድትወስድ ያስችላታል።

 አገሪቷ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እየጣረች መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

 እንደ እርሳቸው ገለጻ የአጋርነትና የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ የጅቡቲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመሰረት ድንጋይ ነው።

 የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ በንግድ ትርኢቱ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የግብጽ፣ የፈረንሳይ፣ የጃፓንና የቱርክን ጨምሮ 250 የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

 ለአራት ቀናት የሚቆየውን ኤግዚቢሽን አምስት ሺህ ያህል ሰዎች እንደሚጎበኙትም ይጠበቃል።

 በንግድ ትርዒቱ ጅቡቲን የንግድ ከተማ ለማድረግ መታቀዱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ከተሳታፊ ኩባንያዎች አንጻር ውጤታማ መሆኑን ነው የተናገሩት።

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር የባህል ሙዚቃ ቡድን ዝግጅቱን በማቅረብ የንግድ ትርኢቱን አድምቆታል።

 የጅቡቲ ንግድ ምክር ቤት እ.አ.አ በ1907 ነው የተመሰረተው።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረብርሃን ህዳር 24/2010 በአማራ ክልል በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

በክልሉ በሰሜን ሽዋ ዞን ሀገረ ማሪያም ከሰም ወረዳ በሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የተገነባ  ዘመናዊ የመድኃኒት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በፋብሪካው ምረቃ ላይ እንደተናገሩት ክልሉ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በተለይም አዳጊ ለሆነው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ቀድሞ በመለየትና ባለሃብቱን በተሻለ ቅልጥፍና በማስተናገድ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልፀዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በኢንዱስትሪ ዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

"የመድሃኒት ፋብሪካው መገንባትም  መከላከልን መሰረት ያደገረውን የጤና ፖሊሲ ከማስተግበር ጎን ለጎን ለጤና ተቋማት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማቀላጠፍ በተወሰነ መልኩ የሚያግዝ ነው" ብለዋል።

በቀጣይም በመድሃኒትና መሰል ተፈላጊ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መሬት በማዘገጀትና መሰረተ ልማቱን በማሟላት ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሰራ አቶ ገዱ አስታውቀዋል።

የፋብሪካው ሊቀመንበር ሚስተር ዋንግ ሹሪን በበኩላቸው እንደገለጹት የመድሃኒት ፋብሪካው በቻይናው ሂዩማን ዌል ኸልዝ ኬር ግሩፕ የተገነባ ሲሆን ከ30 በላይ የመድኃኒት ዓይነቶችን የማምረት አቅም አለው።

ፋብሪካው የሚያመርታቸውን መድሃኒቶች በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ ሃገሮች በማቅረብ በገበያው ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ግብ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

ወደ ሙሉ ማምረት ሲገባም ከ300 ለሚበልጡ  ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል።

የፋብሪካውን ግብዓት ለጊዜው ከቻይና የሚያስመጣ ሲሆን በቀጣይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የመድኃኒት መስሪያ ግብዓቶችን በኢትዮጵያ የማምረት እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ ጉዳዮች አማካሪ ሚስዝ ሊዮ በበኩላቸው "የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው" ብለዋል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት አጋጣሚ በመጠቀም በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የመድሃኒት ፋብሪካው መገንባትም የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ሌሎች የቻይና ባለሃብቶች መጥተው እንዲያለሙ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይም ከፌደራልና ከክልል እንዲሁም ከዞኑ የተወጣጡ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ህዳር 24/2010 የኢትዮጵያ ፕሪመየር ሊግ  አምስተኛው ሳምንት ዛሬ በተካሄደው ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ  ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸፈ፡፡

 ወልዋሎ አዲግራት የማሸነፊያውን ጎል ያስቆጠረው በ75ኛው ደቂቃ ላይ በ11 ቁጥር  ሙሉአለም ጥላሁን አማካኝነት ነው፡፡

 ከእረፍት በፊት የወልዋሎ ክለብ ተጨዋቾች በ10ኛው፣ በ12ኛውና በ34ኛው ደቂቃዎች ላይ ግብ የሚሆኑ ሙከራዎች አድረገው በቡናው በረኛ ከሽፎባቸዋል፡፡

 ከእረፍት መልስ ደግሞ የቡና ክለብ ተጨዋቾች ጫና ፈጥረው በ55ኛውና በ62ኛው ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

 በአዲግራት ከተማ ስፖርት ሜዳ የተካሄደውን የዛሬው  ጨዋታ  በመሃል የመሩት ፌደራል ዳኛ ሰሎሞን ገብረ ሚካኤል   ለአንድ የቡና እና ለሁለት የወልዋሎ  ተጨዋቾች የቢጫ ካርድ አሳይተዋል፡፡

 ከጨዋታው በኋላ የወልዋሎ አሰልጣኝ ብርሀነ ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት " በጥሩ ሁኔታ ተጫውተን በማሸነፍ ሶስት ነጥብ  ይዘን መውጣት ችለናል " ብለዋል፡፡

 የቡና ምክትል አሰልጣኝ  ሀብተወልድ ደስታ  በበኩላቸው አልፎ አልፎ የነበረው የሰዓት ማባከንና የዳኝነት ሁኔታ  እንዳላስደሰታቸው ገልጸው በስፖርት ተመልካቹ ጨዋነት ግን  መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

 የአዲግራትና አካባቢው ስፖርት አፍቃሪ እንዲሁም  የሁሉቱ ክለቦች ደጋፊዎች ተጨዋቾቹን በማበረታታ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ስሜት ድጋፋቸውን መስጠታቸውን በስፋራው  የነበረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ዘግቧል ።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 24/2010 በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና (ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ) የመክፈቻ ጨዋታ ኬንያ ሩዋንዳን ሁለት ለዜሮ አሸነፈች።

 በካካሜጋ ስታዲየም የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኬንያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

 በ26ኛው ደቂቃ መስኡድ ጁማ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራትና በ38ኛው ደቂቃ ደግሞ ደንካን ኦቲዬኖ ከረጅም ርቀት ባገባት አስደናቂ ግብ ኬንያ ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።

 በዚሁ መሰረት ኬንያ አምስት ቡድኖች የሚገኙበትን ምድብ አንድ በሶስት ነጥብ መምራት የጀመረች ሲሆን በአንጻሩ ሩዋንዳ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

 በዚሁ ምድብ በማቻኩስ ስታዲየም ሊቢያና ታንዛኒያ ጨዋታቸውን ከቀኑ አስር ሠዓት ጀምሮ እያካሄዱ ነው።

 በእስካሁኑ ውጤትም ሁለቱም ቡድኖች ግብ አላስቆጠሩም።

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ይጫወታል።

Published in ስፖርት

ወልዲያ ህዳር 24/2010 በወልዲያና በመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለቦች መካከል ዛሬ ሊካሔድ የነበረው ግጥሚያ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መራዘሙን የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ልባሴ አሊጋዝ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በወልዲያ ሼህ አላሙዲን ስታዲየም ሊካሔድ የነበረው ግጥሚያ ዛሬ ጠዋት በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል በተነሳ ግጭት ምክንያት ሊካሔድ አልቻለም።

በግጭቱ ምክንያትም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ የንብረት ጉዳት መድረሱን አስታውቀው የጸጥታ አካላት ባደረጉት ጥረት መረጋጋት መፈጠሩንም ተናግረዋል።

በሁለቱ እግር ኳስ ክለቦች መካከል ሊካሄድ የነበረው የ5ኛ ሳምንት ጨዋታም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ሃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።

Published in ስፖርት

መቀሌ ህዳር 24/2010 የልብ ህመም የሚያስከትለውን የቶንሲል በሽታን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን  በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የዓይደር ጤና ሳይንስ  ኮሌጅ ገለጸ፡፡

የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አማኑኤል ኃይሌ እንዳሉት በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከሚገኙ የልብ ህሙማን መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በቶንሲል በሽታ ምክንያት  " ሩማቲክ " በተባለ የልብ ህመም የተጠቁ ናቸው።

አብዛኛው ጊዜ በሽታው ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ተደብቆ  ከቆየ በኋላ ሲታወቅ  ለቀዶ ህክምና የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡

የበሽታው ስፋትና የሚያሰከትለውን ጉዳት ለመለየት  ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አቻዎቹ  ጋር በመሆን ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ነው ዶክተር አማኑኤል ያመለከቱት።

የዓይደር  ሪፈራል ሆስፒታል ሚለና ከተባለ  ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር 160 ለሚሆኑ የልብ ህሙማን  መድኃኒት በመስጠት በሽታው ከሚያደርሰው ጉዳት ለመታደግ ድጋፍ ማደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

ከውጭ ሃገር ከፍተኛ የልብ ህክምና ባለሙያዎች አስመጥተው በጋራ በመቀናጀት የቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ህሙማንን  እየረዱ  መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሆስፒታሉ በራሱ አቅም የልብ ቀዶ ህክምና በመስጠት  ህብረተሰቡ ከከፍተኛ ወጪ ለመታደግ አቅዶ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡

የቶንሲል በሽታ  80 በመቶ በቫይረስ 20 በመቶው ደግሞ በባክተሪያ በጉሮሮ ላይ የሚከሰት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኮሌጁ የውስጥ ደዌ ህክምና ትምህርት ክፍል የልብ ህመም ስፔሻሊስት ዶክተር አብርሃ ኃይሉ ናቸው፡፡ 

በሽታው በቀላሉ ታክሞ  መዳን እንደሚቻልና  ህክምና ካልተደረገለት ለልብ ህመም በመዳረግ ለሞት እንደሚያጋልጥ ገልጸዋል፡፡

"በሽታው በተጨናነቀ ክፍል ከተጠቃ ሰው በትንፋሽ ፣በሳልና በማስነጠስ  ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በመሆኑ ምልክት ሲታይ ቶሎ ወደ ህክምና በመሄድ መታከም ይገባል "ብለዋል።

በጀርመኑ ዊተን የተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት የልብ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ክሪስትን ለይነር በበኩላቸው በቶንሲል በሽታ ምክንያት የሚከሰተው " ሩማቲከ " የልብ ህመም ለመከላከል ከዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ሆስፒታሉ ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የስፔሻላይዜሽን ስልጠናና የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ የልብ ህሙማን የህክምና እርዳታ ለማግኘት  እየተጠባበቁ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 24/2010  ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና የውድድር አማራጮችን ማስፋትን ዓላማ ያደረገው የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች ክለቦችና ተቋማት አገር አቋራጭ ውድድር ዛሬ በጃን ሜዳ ተካሂዷል።

 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለጹት ውድድሩ በቀጣይ አገሪቷን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን ለመመልመልና ለእነሱም የውድድር አማራጮች ለማስፋት ነው የተካሄደው።

 በየካቲት ወር ለሚካሄደው የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር አትሌቶች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና ወቅታዊ ብቃታቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ አንጻርም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ በቀጣይም መሰል ውድድሮችን በክልል ደረጃ እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

 ውድድሩ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶችና ወንዶች፣ በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶችና የስምንት ኪሎ ሜትር አንጋፋ አትሌቶች የርቀት አይነት ተከናውኗል።

 የአንጋፋ አትሌቶች ከሀምሳ ዓመት በላይ እና በታች በሚል ሁለት ምድብ ተከፍለው ውድድራቸውን አካሂደዋል።

 በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች እትሌት መለሰ ብርሃኑና አትሌት መኩሪያ ዘለቀ በቅደም ተከተል 1ኛ እና 2ኛ የወጡ ሲሆን አትሌት አለምነህ ይርሳው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል።

 በ10 ኪሎ ሜትር ሴቶች አትሌት ጌጤ አለማየሁ ከኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ስትሆን አትሌት እናትነሽ አላምረው ከአማራ ክልል፣ አትሌት ብርዛፍ ታረቀ ከጉና ንግድ ስፖርት ክለብ ተከታትለው ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

 በ10 ኪሎ ሜትር አትሌት ደራራ ደሳለኝ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛ የወጣ ሲሆን አትሌት ቢተው አደም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ፣ አትሌት ታዬ ግርማ ሶስተኛ ሆነዋል።

 ከ50 ዓመት በላይ የአንጋፋ አትሌቶች የስምንት ኪሎ ሜትር ውድድር ካሱ መርጊያ፣ ለማ በላይና ታደለ በቀለ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 ከ50 ዓመት በታች የአንጋፋ አትሌቶች በተመሳሳይ ርቀት በተካሄደው ውድድር ገዛኸኝ ገብሬ፣ አያሌው እንዳለና ዳንኤል ቄቤሎ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

 በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች አማራ ክልል አንደኛ በመውጣት የቡድን አሸናፊ ሲሆን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብና ኦሮሚያ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።

በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ኦሮሚያ የቡድን አሸናፊ ሲሆን፣ አማራ ክልልና ኦሮሚያ ፖሊስ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።   

 በተመሳሳይ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ኦሮሚያ ክልል በቡድን ያሸነፈ ሲሆን አማራ ክልልና ኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ስፖርት ክለብ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈደሬሽን ለውድድሩ አሸናፊዎች ሽልማት 100 ሺህ ብር ወጪ አድርጓል።

 ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡ አትሌቶች የብርና የሜዳሊያ ሽልማት ያገኙ ሲሆን ለቡድን አሸናፊ የስፖርት ክለቦችም የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሎሬት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉና የፌደሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለአትሌቶቹ ሽልማቶቹን አበርክተዋል።

 በውድድሩ ከ400 በላይ የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማትና አንጋፋ አትሌቶችና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች መሳተፋቸውም ተገልጿል።

 የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና ተቋማት አገር አቋራጭ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 24/2010 በኬንያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2017 የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና (ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ) ጨዋታ መካሄድ ጀመረ።

አዘጋጇ ኬንያና ሩዋንዳ በካካሜጋ ስታዲየም የሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ከደቂቃዎች በፊት ተጀምሯል።

ከመክፈቻው ጨዋታ በኋላ ከቀኑ በአስር ሠዓትም ሊቢያ ከታንዛኒያ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ለመሳተፍ ባለፈው ሐሙስ ወደ ካካሜጋ ከተማ ያመራ ሲሆን ከነገ በስቲያ ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ጨዋታውን የሚያደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚገኝበት ምድብ ሁለት ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ ይገኛሉ።

በምድብ ሁለት ኡጋንዳና ብሩንዲ ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት የሚጫወቱ ሲሆን በምድብ አንድ ከነገ በስቲያ ዛንዚባር ከሩዋንዳ ከቀኑ ስምንት ሠዓት፣ ኬንያ ከሊቢያ ከቀኑ በአስር ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሊቢያ በውድድሩ የምትሳተፈው በተጋባዥነት ነው።

ለ39ኛ ጊዜ በሚካሄደው የ2017 የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና በሁለት ምድቦች ዘጠኝ ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን እስከ ታህሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ይዘልቃል።

የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ከሚሳተፉት ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ የነበረ ቢሆንም በያዝነው ሳምንት "የኬንያ ወቅታዊ የደህንነት ጉዳይ ያሰጋኛል" በሚል ራሱን ከውድድሩ አግልሏል።

ውድድሩ እ.አ.አ በ1926 ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኡጋንዳ 14 ጊዜ ዋንጫ በማንሳት የበላይነቱን ስትይዝ ኬንያ ስድስት፣ ኢትዮጵያ አራት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል።

Published in ስፖርት

ቤጂንግ ህዳር 24/2010 በአፍሪካ የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና አራማጅ ፓርቲዎች የትብብር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ጥሪ አቀረበ።

በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አዘጋጅነት “የተሻለ ዓለም ለመፍጠር የጋራ ኃላፊነት እንወጣ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የፓርቲዎች የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ከመድረኩ ቀደም ብሎ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የምክክር ፎረም የአፍሪካን ፓርቲዎች በመወከል ንግግር አድርገዋል።

አፍሪካዊያን ፓርቲዎች አሕጉራዊ ልማት ለማረጋገጥ የጋራ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም በዚሁ ጊዜ ጠይቀዋል።

ፓርቲዎች በልምድ ልውውጥና በሌሎች የትብብር መስኮች አቅማቸውን በማሳደግ አሕጉራዊ ትስስራቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም አስምረውበታል።

በዚህ ረገድ ቻይና በውስጠ ዴሞክራሲ ግንባታና አመራር በማፍራት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዙሪያ ድጋፍ እንድታደርግ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

መድረኩ ለሰው ልጅ ምቹ የሆነች ዓለም በጋራ ለመፍጠር የተወጠነውን ሀሳብ ገቢራዊ ለማድረግ መደላድል የሚፈጥር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው ኢሕአዴግ ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ዓለም አቀፍ ትብብሩን እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የጋራ ልምዶችን በመቀመር የልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሃሳብ አገራዊና አሕጉራዊ ዕድገት የሚረጋገጥበት እንዲሆን ለማስቻል ከአፍሪካ ፓርቲዎች ጋር ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ቻይና ባስተናገደችው በዚሁ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ ከ120 አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ሺፒንግ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ትብብር ማጎልበት ያስችላል ያሉትን ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርገዋል።

ፍኖተ ካርታው “መከባበርና የጋራ ተጠቃሚነት” የሚሉ ቁልፍ ጽንሰ ሃሳቦችን ያካተተ ሲሆን የቤጂንግ ኢኒሼቲቭ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን