አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 02 December 2017

ደብረማርቆስ ህዳር 23/2010 ወጣቱ ትውልድ ህገ-መንግስቱንና የፌደራል ስርዓቱን በመረዳት በእውቀት ላይ በተመሰረተ ተሳትፎ የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል እንዲችል የሚያግዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በፓናል ውይይትና በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር ተከብሯል።

በፌደሬሽን ምክር ቤት የንቃተ-ህግ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተክሉ ተሾመ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ወጣቱ ትውልድ የሃገሪቱን ህገ-መንግስትና የፌደራል ስርዓቱን በሚገባ እንዲያውቅ ምክር ቤቱ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

"በተለይም አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ርብርብ ግቡን እንዲመታ የወጣቱን ትውልድ እውቀት ማሳደግ የግድ ይላል" ብለዋል።

እንዲሁም በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማካከል መቻቻልን መሰረት ያደረገ ልማትና እድገት ማምጣት እንዲቻል የፌደራሊዝምን አስፈላጊነትና አተገባበር በተገቢው መንገድ ማሳወቅ እንደሚገባም አብራርተዋል።

"የበዓሉ መከበርም የህብረብሔራዊ ፌደራሊዝም  ለሃገራችን ቀጣይ እድገት መሰረት መሆኑንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው ለተግባራዊነቱ በባለቤትነት መንቀሳቀሰ እንዲችሉ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ታረቀኝ ገሪሶ በበኩላቸው ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ህገ-መንግስቱን እንዲረዱ በስነ ዜጋ እና ስነ-ምግባር ትምህርት በጥልቀት ለማስረጽ ጥረት እየተደረገ ነው። 

ከተሳታፊ ተማሪዎች መካከልም የጋብስት ኮሌጅ የ4ኛ አመት ተማሪዋ ተዋበች ወርቅነህ "የበአሉ መከበር በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራና ልዩነታችንን በአንድነታችን የምናጠናክርበትን ስልት የሚያዳብርልኝ ነው"ብላለች።

የትሮፒካል የጤና ሳይንስ  ኮሌጅ ተማሪ ሀብተወልድ  ደሳለኝ በበኩሉ "የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ አንድነታችንን በማጠናከርና በመተሳሰብ  ለልማትና ለሰላም በጋራ እንድንነሳሳ የሚያደርግ በመሆኑ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው" ብሏል።

"ህብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ትናንት በተካሄደው የፓናል ውይይት ከ200 በላይ የግል ከፍተኛ የትምህር ተቋማት ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በቀረቡ ጥያቄዎች ተወዳዳሪ ለሆኑ አራት ተማሪዎችም የሞባይል ስልክ ቀፎዎች በማበረታቻነት ተበርክቷል።

Published in ፖለቲካ

ሽሬ እንዳስላሴ ህዳር 23/2010 የእርሻና እንሰሳት የእርባታ ስራቸውን በማዘመን ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን በትግራይ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የኩናማ ብሄረሰብ አባላት ገለፁ ።

 የብሄረሰቡ ተወላጆች በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልን በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ትናንት በፓናል ውይይት አክብረዋል።

 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በታህታይ አዲያቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ‘‘ለምለም ‘‘በተባለ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሰመረ ገብረክርስቶስ እንዳሉት ስርዓቱ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተሻሻሉ የግብርና መሳሪያዎችና አሰራሮችን ተጠቅመው የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠዋል ።

 በተያዘው በ2009/2010 የምርት ዘመን መኽር ወቅት በመንግስትና በህብረት ሥራ ማህበር አማካኝነት በቀረበላቸው የእርሻ ትራክተር በመታገዝ አርሰው በዘር ከሸፈኑት ሁለት ሄክታር ማሳ 16 ኩንታል የሰሊጥ ምርት ማግኘታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 “ህገ መንግስቱ ባጎናፀፈኝ መብት የእርሻ ማሳ ባለቤት በመሆን በየዓመቱ በማገኘው ምርት ያለ ምንም ችግር በምግብ ራሴን ችዬ ልጆቼን እያስተማርኩ ነው ” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የብሔረሰቡ ተወላጅ ወይዘሮ ንግስቲ ፍሬኤል ናቸው።

 ሌላው የብሄረሰቡ ተወላጅ ወጣት ሰመረ በኪ በበኩሉ ከብድርና ቁጠባ ተቋም ባገኘው ገንዘብ በከብት እርባታና ማድለብ ተሰማርቶ ገቢውን በማሳደግ ራሱን ማስተዳደር መጀመሩን ገልጿል ።

 የብሔረሰቡ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ቢኖርም በቋንቋው የተዘጋጁ የመማርያ መፅሓፍት እጥረት፣ የኤሌክትርክ መብራት መቆራረጥ፣ ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ አለመኖሩን በውይይቱ ወቅት እንደ ችግር ተነስተዋል።

 በጤና ባለሙያነት የተሰማሩ የብሄረሰቡ አባላት ቁጥር አነስተኛ መሆን በተመለከተም በተሳታፊዎቹ እንደ ችግር የቀረበ ነበር ።

 መድረኩን የመሩት የታህታይ አዲያቦ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትርሐስ ሸቦ እንዳሉት፣ የውይየቱ ተሳታፊዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል ።

 ወይዘሮ ትርሐስ እንዳሉት የመማርያ መፅህፍት ለማሳተምና የብሔረሰቡ የጤና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል ።

 እንዲሁም የብሔረሰቡ አባላት በብዛት በሚኖሩበት ‘‘ለምለም‘‘ በተባለ የገጠር ቀበሌ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ።  

 "የብሄረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ተከብረውና ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ቀደም ሲል በመንግስት ወጭ የተገነባን ሙዚየም ለማጠናከር የክልሉ መንግስት ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድረጓል " ብለዋል ።

 የክልሉ የመንግስትና ህዝብ ግኑኝነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ በበኩላቸው "የብሄረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆኑ ተግዳራቶችን ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ ይደረጋል" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ህዳር 23/2010 የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በሚሰጠው የብድር አገልግሎት በመታገዝ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ደንበኞች ገለጹ።

 ተቋሙ በበኩሉ ደንበኞቹ በየጊዜው የሚሰጡትን አስተያየት ተቀብሎ አሰራሩን ለማዘመን እየሰራ መሆኑ አስታወቀ።

 አስተያየታቸው ለኢዜአ ከሰጡ ደንበኞች መካከል ወጣት ዛፉ ሙሉጌታ እንደገለፀችው ሰርታ የመለወጥ ፍላጎቱ ቢኖራትም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ላለፉት አራት ዓመታት የቤተሰብ ጥገኛ ሆና ቆይታለች።

 መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከአምስት ወጣቶች ጋር ተደራጅተው ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ባገኙት 280 ሺህ ብር ብድር በዶሮ እርባታ ስራ መሰማራታቸውን ገልፃለች፡፡

 "በአሁኑ ወቅት ከ400 የሚበልጡ ዶሮዎችን ገዝተን እያረባን እንቁላል ለመቀሌና አካባቢው ነዋሪዎች እያቀረብን ነው "ብላለች ።

 ከተቋሙ ብድሩን ለማግኘት ስድስት ወራት እንደፈጀባቸው የገለፀችው ወጣት  ዛፉ ተቋሙ አገልገሎት አሰጣጡን እንዲያስተካክል ጠቁማለች።

 የእንደርታ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሃይሉ ደበሳይ በበኩላቸው ከስድስት ዓመታት በፊት ከተቋሙ 500 ብር ብድር ውሰደው የመስኖ ልማት ስራ መጀመራቸው ገልፀዋል።

 "ተቋሙ በድጋሚ በሰጠኝ 100 ሺህ ብር ብድር በመታገዝ የመስኖ ልማት በማጠናከርና ሌሎች የንግድ ስራዎች እያከናወንኩ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል ።

 በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ በመቆጠብ መቀሌ አከባቢ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ  ዘመናዊ  ቤት  መስራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 "ተቋሙ ብድር በወቅቱ በመስጠት በኩል ክፍተት ያለበት በመሆኑ ሊያስተካክል እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

 የደደቢት ማይክሮ ፋይናነስ ተቋም ኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ክፍሎም እንደገለፁት ተቋሙ በክልሉና ሌሎች አካባቢዎች 158 ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ ነው ።

 በቅርንጫፎቹ አማካኝነት ባለፈው ዓመት ለ100 ሺህ ደንበኞች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 የደንበኞችና የብድር ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል በተያዘው ዓመት ለ200 ሺህ ደንበኞች 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 "ተቋሙ በየጊዜው ከደንበኞቹ የሚቀርብለትን አስተያየት ተቀብሎ አሰራሩን ለማሻሻል እየሰራ ነው " ብለዋል።

 እንደ ሀላፊው ገለፃ ተቋሙ በተለይ በብድር አሰጣጥ በኩል ያለበትን ችግር ለማስተካከል የሰው ሃይሉን ከማሟላትና አቅምን ከማሳደግ ባለፈ ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራ ነው ።

Published in ኢኮኖሚ

ሃዋሳ ህዳር 23/2010 ለዘላቂ ለሰላምና አብሮነት መረጋገጥ እንቅፋት የሚሆኑ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን በአግባቡ መፍታት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተናገሩ።

 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች የተሳተፉት የሰላምና የልማት ኮንፍረስ ዛሬ ተካሒዷል።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት ባለፈው አመት በዞኑ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ምንጭ በዞኑ ለሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት ነው።

 "በጌዴኦ ህዝብና በሌሎች ብሄር ተወላጆች መካከል የነበረው ጠንካራ ወዳጅነትና አብሮነት እንዲደፈርስና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደረገው የስራ አጥነት ችግር ጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰብ ሲሆን ችግሮቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈቱ ይገባል" ብለዋል።

 በዞኑ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የጌዴኦን ህዝብ የማይወክል እኩይ ተግባር መሆኑንም ተናግረው የችግሩ የተከሰተውም ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የተሳናቸውና የራሳቸውን ጥቅም በሚያስቀድሙ አመራሮች የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

"መንግስት የግለሰቦችንና የቡድን መብት ሚዛናዊ አድርጎ ለማስከበር ጥረት ያደርጋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥፋት ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድና የህግ የበላይነት እንደሚከበርም አስረድተዋል።

 ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

 በዞኑ በኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ያሉት አቶ ዩሱፍ ጠሃ "ያለፈውን በመተው በቀጣይ የነበረውን አብሮነትና ሰላም በማጠናከር ዙሪያ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተን መስራት አለብን" ብለዋል።

 "በዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶች ወጣቶች በተመሳሳይ እኩይ ተግባር እንዳይሳተፉ የስራ ዕድል ሊፈጥሩላቸው ይገባል" ያሉት አቶ ዩሱፍ ለወጣቶች ብድር እንዲውል ከራሳቸው ድርጅት 300 ሺህ ብር በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ መቆጠባቸውንም ተናግረዋል።

 ከይርጋጨፌ የመጡት ሌላው ተሳታፊ አቶ ዘለቀ ጉዬ በበኩላቸው መንግስት በድርጊቱ በተሳተፉት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ አስተማሪ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠልም እንዳለበት ጠቁመዋል።

 እሳቸው በሚኖሩበት በይርጋጨፌ ከተማ የሚገኙትና ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡት በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል ያለው የተረጋጋ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

 በኮንፍረንሱ ላይ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች የጌዴኦ ዞን አባገዳ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞኑ ነዋሪዎች እንዲሁም ንብረታቸው የወደመባቸው ግለሰቦች የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ቃል ገብተዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  ህዳር 23/2010 የዳኞች የደመወዝ ክፍያ ስርዓትና የጥቅማ ጥቅም አሰጣጥ የስራ ልምድን መሰረት ባለማድረጉ ፍልሰት እየፈጠረ መሆኑን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ገለጹ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አዳም ሰይድ እንደተናገሩት፤ የዳኞች የደመወዝ ክፍያ ስርዓት የስራ ልምድን መሰረት ያላደረገና በቂ አይደለም። ዳኞችም የስራ ዘርፋቸውን እንዲቀይሩ እያስገደዳቸው ነው።

ይህም በፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ የፍርድ አሰጣጥ አገልግሎት እንዳይኖር አንዱ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ክፍያና ጥቅማ ጥቅም  የፍርድ ቤት የስራ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ዝቅተኛ በመሆኑ የሰራተኞች ፍልሰት ችግር መኖሩንም አንስተዋል።

ለዳኞች የትምህርት እድል አለመመቻቸት፣ ዳኞችን ከደህንነት ስጋት ነጻ የሚያደርጉና ከድካምና እንግልት የሚታደጉ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩንም እንደ ችግር አንስተዋል። 

የዳኞች ብዛትና የመዝገቦች ቁጥር አለመመጣጠን፣ የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቁጥር ማነስ ፣ የችሎት ክፍሎችና የቢሮዎች ምቹ አለመሆን፣ የፕላዝማ ቴሌቪዥን እጥረት በስራ ላይ እያጋጠማቸው ካሉት ተግዳሮቶች ውስጥ እንደሚጠቃለሉ ጠቅሰዋል።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ግድየለው ግልበቶ እንደሚሉት፤ ልምድ ያላቸውና የጀማሪ ዳኞች ክፍያ ተመሳሳይ መሆን ዳኞች ስራቸውን እንዲቀይሩ የሚያነሳሳ ነው።

በመሆኑም  ፍርድ ቤቶች "ዳኞችን ስራቸው ላይ ለማቆየት የሚያስችሉ እና መልካም አስተዳዳር የማስፈን ስራዎች ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ አቶ ተፈሪ ገብሩ በበኩላቸው ፤"ዳኞች ስራቸው ላይ እንዲቆዩ ምቹ የስራ አካባቢን ማሟላትና የአቅም ግንባታ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ የዳኞች ደመወዝ በስራ ልምዳቸው መሰረት አለመከፈሉ ተገቢ አለመሆኑን ይስማማሉ።

በመሆኑም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የዳኞች የደመወዝ ደረጃ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

የዳኞችን ብዛትና የመዝገቦችን ቁጥር ለማጣጣም ተጨማሪ የሰው ሀይል ቅጥር በሂደት ላይ መሆኑንም አክለዋል።

ሆኖም ግን ፍርድ ቤቶች በየወሩ "የዳኞችን የስራ አፈጻጸም በመገምገም ተጠያቂ የማድረግና ያላቸውን የሰው ሀይል በአግባቡ ለመጠቀም የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ስራዎችን አጠናክረው ማስቀጠል አለባቸው" ብለዋል።

ይህም የፍርድ መጓተትና የቀጠሮ ርዝማኔን ችግሮች ለማቃለል ያስችላል ነው ያሉት።

የፍርድ ቤቶች የማስቻያ ቦታና የቢሮ እጥረቶችን ለመፍታት ጊዜያዊና ዘለቄታዊ መፍትሄዎች ተነድፈው ወደ ስራ መገባቱንም ጠቅሰዋል።

የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ደመወዝ ለማሻሻል የተዘጋጀው የመዋቅር ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 23/2010 የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎት ለመሰጠትና የግልጸኝነት ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የዳኝነት ፖሊሲና የቀጠሮ አሰጣጥ መመሪያ ለማዘጋጀት ጥናት እየተከናወነ እንደሚገኝ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሰራተኞች፣ ኃላፊዎችና ዳኞች 12 ኛውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዛሬ አክብረዋል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ እንደተናገሩት፤ የዳኝነት ፖሊሲና የቀጠሮ አሰጣጥ መመሪያ ለማዘጋጀት የጥናት ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

በመመሪያው የእያንዳንዱ ጉዳይ ክብደትና ቅለት ተለይቶ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበትን ጊዜ እንደሚያካትት ገልጸዋል።

ይህም "በዳኝነት አሰራር ላይ የተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል" ብለዋል።

በፍርድ ቤቶች የቆዩ ውዝፍ መዛግብትን በማጥራቱ ረገድ ዳኞች በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓቱ መጠናከሩንም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መዛግብትን ማጥራት የተቻለ ሲሆን፤ "በፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤትም እስከ ሚያዚያ ድረስ የማጥራት ስራዎችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ከዓመት በላይ የቆዩ መዛግብትን "የመቀነስ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ነው ያሉት።

የፍርድ ቤቶች የቀጠሮ ርዝማኔም ከሁለት ወር እንዳይበልጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

ይህም "ከፍርድ መጓተት ጋር በተያያዘ ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቀነስ ያስችላል" ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ አቶ ተፈሪ ገብሩ በበኩላቸው፤ በአገሪቷ አንድነትን መፍጠርና የጋራ መግባባትን ማጎልበት የሁሉም ሕብረተሰብ ኃላፊነት ነው።

የአገሪቷን ሰላም የሚያደፈርሱ፣ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አሉታዊ ተግባራትን መከላከልም እንዲሁ በሁሉም ዜጎች በባለቤትነት ስሜት ሊወጣው የሚገባ ተግባር መሆኑንም አክለዋል።

የብሄሮች ፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓሉ ላይ በህብረ ብሄራዊነት፣ በፌዴራሊዝም፣ በዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትና አንድነት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአገሪቷ በህገ መንግስቱ የደመቀ ህብረ ብሄራዊነት ከመተግበር አኳያ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን አውስተዋል።

የወጣቶች የስራ አጥነት ችግርና በተለይም በክልሎች አካባቢ የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩም ተወስቷል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ህዳር 23/2010 በአማራ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከልና ለማስቆም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ።

 “ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የወንዶች አጋርነት” በሚል መሪቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የነጭ የሪቫን ቀን በአማራ ክልል ደረጃ ዛሬ በባህርዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

 የአማራ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀመውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ማህበሩ ባለፈው ዓመት ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

 በተፈጠረው ግንዛቤም ያለዕድሜያቸው ሊዳሩ የነበሩ ከ2ሺህ 200 በላይ ህፃናት ጋብቻ እንዲሰረዝ ማድረግ ተችሏል፡፡

 በፊስቱላ የተጠቁ 258 እናቶችም ህክምና አግኝተው ጤንነታቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

 የግንዛቤ ፈጠራ ስራው አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም በሴቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ፆታዊ ጥቃት ግን በሚፈለገው ደረጃ ሊቀንስ እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡

 የሚፈፀመውን ፆታዊ ጥቃት ለማስቆም የወንዶችን አጋርነት ከማጠናከር ባለፈ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 “ስርዓተ ፆታን መሰረት ያደረገ ፆታዊ ጥቃትን እንከላከል” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ፆታ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዮሐንስ መርሻ በበኩላቸው የፆታዊ ጥቃቶች በሴቶችና ህፃናት ላይ ስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና እያሳደሩ ነው፡፡

 የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅምና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም ህጎች በትክክል እንዲተገበሩ መስራት ችግሮቹን ለመፍታት በመፍትሄነት  አስቀምጠዋል።

 ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሀጂ አህመድ አሊ በሰጡት አስተያየት ''ለትዳር አጋሮቻችንም ሆነ ለሴት እህቶቻችንና ልጆቻችን ፍቅርን እንድንሰጥ ሃይማኖቱ ያዛል'' ብለዋል።

 ከምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ከመሶቦ ቀበሌ የመጡት አርሶ አደር ተዋቸው በላቸው በበኩላቸው ''ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ የወንዶች አጋርነት ምን መሆን እንዳለበት ያገኘሁት ስልጠና አስተሳሰቤን ቀይሮታል'' ብለዋል፡፡

 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ በሀገር ደረጃ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ በተከበረው የነጭ ሪባን ቀን ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። 

 “ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የወንዶች አጋርነት” በሚል መሪቃል በአማራ ሴቶች ማህበር አዘጋጅነት ዛሬ መከበር የጀመረው ይኸው በዓል እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2010 በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 23/2010 ሴት ተመራማሪዎችን የሚያበረታቱ ሁለት ፕሮጀክቶች ይፋ ተደረጉ።

ፕሮጀክቶቹን የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል እና የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም በጋራ አዘጋጅተውታል።

ፕሮጀክቶቹን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እሸቱ ጮሌ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

የመጽሐፍ ፕሮጀክት እና የኢትዮጵያ የሴቶች አካዳሚክ ጆርናል ፕሮጀክት የሚል መጠሪያ ያላቸው ፕሮጀክቶች ለአምስት ዓመት ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው።

የመጽሐፍ ፕሮጀክት ሴቶች በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካና ባህል ታሪክ ውስጥ በየዘመናቸው ያበረከቱትን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ የሚያሳዩ መጽሐፎችን ማሳተም ዋነኛ ዓላማው ነው።

የአካዳሚክ ጆርናል ፕሮጀክት ዓላማ ደግሞ የሴት መምህራንን የምርምርና ሕትመት ችግሮች ለማስወገድ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት ምሁራን የጥናት ክህሎታቸው እንዲዳብርና ውጤቶቻቸው ለህትመት እንዲበቁ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በሁለቱም ፕሮጀክቶች የሚጻፉ መጽሐፍት እና የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በእንግሊዘኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ለህትመት ይበቃሉ።

የሚጻፉትን መጽሐፍት እንዲሁም የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለህትመት ከመብቃታቸው በፊት የሚገምገም የኤዲቶሪያል ቦርድም ተቋቁሟል።

ለሴት ምሁራን የዓቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ከፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ጋር ተያይዞ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በሁሉም የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች ተግባራዊ እንደሚሆንና በቀጣይም የግል ዩንቨርሲቲዎች በፕሮጀክቶች ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋልም ተብሏል።

የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል ዳይሬክተር አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የዲሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴ የሴቶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል ናቸው። 

በትምህርት ሥርአት ውስጥ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም በትምህርት ተቋማት ውስጥ በአስተማሪነት፣በተመራማሪነትና በተቋም መሪነት ያላቸው ሚና አሁንም ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሴቶች በጥናትና ምርምር ያላቸውን እውቀት በማጎልበትና የህትመት ውጤቶችን እንዲያሳትሙ በማድረግ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን የአመራርነት ደረጃ እንዲያሻሻሉ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የሚታተሙ የጥናት ውጤቶችን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥርም እንዲሁ።

ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራርነት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ዳይሬክተሯ ያሳሰቡት።

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጄይሉ ኡመር በበኩላቸው ዩንቨርሲቲው የሴቶችን አመራር ዓቅም ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑንና ፕሮጀክቶቹ የዚህ ዋነኛ ማሳያ ተድርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ መንግስት ለፕሮጀክቶቹ ተፈጻሚነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ለፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልገውን በጀት ማዕከሉ ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ፈንድ እና ፕሮጅከቱን ተግባራዊ የሚያደርጉ የመንግስት ዩንቨርሲቲዎችና አጋር አካላት የሚሸፍኑይሆናል። 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ህዳር 23/2010 የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ ቃል ኪዳኑን በማደስ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተጠቆመ።   

 የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሠራተኞች 12ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል።   

 በህብረ ብሄራዊነትና ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ዙሪያም የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።                     

 የኢንተር ፕራይዙ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አገሪቷ በገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ከነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለመውረድ ተገዳ ነበር።   

 ''የኢትዮጵያ ውድ ልጆች በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት  ወደ ዲሞክራሲና ልማት ጎዳና ለመግባት ችላለች'' ነው ያሉት።  

 የብሄር ብሄረሰቦች መብት በህገ መንግስቱ መረጋገጡ የዜጎች እኩልነት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

 እንደ አቶ ሮባ ገለጻ አገሪቷ በሁሉም መስክ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ኃላፊነቱን በትጋት ሊወጣ ይገባል። 

 ''የብሄር ብሄረሰቦችን ዓመታዊ በዓል ስናከበር ድርጅቱ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት እያሰብን በመሆኑ ሁሉም የድርጅቱ ሰራተኛ ለተሻላ ውጤትና ሁለንተናዊ ለውጥ መዘጋጀት አለበት'' ብለዋል።  

 የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ገብሩ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ''ቀኑ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ዳግም የተወለዱበት በመሆኑ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ '' የተቀመጠ ነው ይላሉ።    

 በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ከአዲስ አበባ ሴት ማህበር በጋራ በመሆኑን የ12ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል አክብረዋል።

 በኢትዮጵያ ድህነትና ኋላ ቀርነት በማሰወገድ ረገድ የህብረተሰቡን በተለይም ሴቶችን በየደረጃው ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ በበዓሉ ላይ ተገልጿል።

 የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መሐመደ ረሺድ እንደገለጹት ሴቶችን በአገር ልማትና ሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ  "በሕገ- መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ከአምስት ቀናት በኋላ በአፋር ከልል መዲና ሰመራ ይከበራል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 23/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የገዛቸውን 850 የአንበሳና የሸገር ከተማ አውቶብሶችን አስመረቀ።

ከነዚህም መካከል 100ዎቹ አውቶብሶች ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ተብሏል።

 ከተገዙት አውቶብሶች ውስጥ ለተማሪዎች የሚያገለግሉት 30ዎቹ  እና ህብረተሰቡን የሚያጓጉዙት 50 ተደራራቢ ዘመናዊ አውቶብሶች የመገጣጠም ስራው ተጠናቆ  አገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተነግሯል።

 ክፍያ የተፈጸመባቸው ቀሪዎቹ 70 የተማሪዎችና 700ዎቹ የብዝኃ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ተጠናቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ ተገልጿል።

 በምርቃው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደተናገሩት በመዲናዋ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የብዝኃ ትራንስፖርት አገልግሎትን በማስፋፋት ላይ ይገኛል።

 በዛሬው እለትም ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የገዛቸውን የከተማ አውቶብሶች ማስመረቁን ተናግረዋል።

 የከተማ አውቶብሶቹ በመዲናዋ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 ለተማሪዎች ሰርቪስ የሚሰጡት የተማሪ አውቶብሶችም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው በጊዜ እንዲደርሱና ሳይደክሙ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ለትምህርት ጥራትና ተሳትፎ  መረጋገጥ አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

 በተማሪዎች አውቶብሶች አገልግሎት ላይ መንግስት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ በዝቅተኛ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ በበኩላቸው በከተማዋ የህዝቡን ቁጥር የሚመጥን የብዝኃ ትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ ችግር ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

በእለቱም ከተማ አስተዳደሩ ባሶቹን ለሚያስተዳድሩት ለአንበሳ አውቶብስና ለሸገር ብዝኃ ትራንስፖርት ድርጅት የ850 አውቶብሶችን ቁልፍ አስረክቧል።

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን