አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 01 December 2017

አዲስ አበባ  ህዳር 22/2010 የሕብረት ስራ ማህበራት በግብርና ምርቶች የውጭ ግብይት ድርሻቸውን ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

 የፌደራል ሕብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ በሕብረት ስራ የውጪ ግብይት ላይ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ውይይት አካሂዷል። 

 የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት "ሕብረት ስራ ማህበራት ግብርናን በማዘመን አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።"

 ሆኖም ማህበራቱ በግብርና ምርቶች ግብይት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ግብይት ድርሻቸውን በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ደረጃውን የጠበቀ የመጋዘን እጥረት፣ የፋይናንስና የሰው ሃይል አቅርቦት ችግሮች ሆነዋል።

 እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የመስራት ክፍተቶት አሉ።

 በመሆኑም ሕብረት ስራ ማህበራት ምርት በመሰብሰብና እሴት በመጨመር ረገድ ለአገርና ለውጪ ገበያዎች በማቅረብ ለአባሎቻቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግ  ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

 በውይይቱ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የድርሻቸውን በመወጣት ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ እንደሚሉት የሕብረት ስራ ማህበራቱን የውጭ ግብይት ድርሻ ለማሳደግ በዘርፉ ያሉ አካላት በጋራ ተቀናጅቶ መስራት ለአርሶ አደሩም ሆነ አገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

 በንግድ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙልጌታ በበኩላቸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ተናቦና ተቀናጅቶ መስራት ግድ ይላል።

 በዚህም ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀትና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

 ባለፉት 25 ዓመታት ዘርፉን ለማጠናከር በተሰራ ስራ ከ17 ሚሊዮን በላይ አባላትን ያፈሩ ከ82 ሺ በላይ መሰረታዊ የሕብረት ስራ ማህበራት፣ 381 የህብረት ስራ ዩኒየኖችና 3 የሕብረት ስራ ፌዴሬሽኖች በተለያዩ የስራ ዘርፎች መደራጀታቸውን የኤጀንሲው መረጃ ያስረዳል።

 በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በሕብረት ስራ ማህበራት ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን በአይነትና በመጠን በማሳደግ የውጭ ገበያ ድርሻቸውን አሁን ካለበት 7 በመቶ ወደ 40 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዟል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2010 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋ መውረድን ተከትሎ አንስቶ የነበረውን የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻ ዳግም ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በክልሎች በተከፈቱ የወርቅ ግዥ ማዕከላት አቅራቢዎች የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ ባንኩ ነጋዴዎቹን ለማበረታታት ወርቅ ለግብይት በቀረበበት ወር ያለውን የክፍያ ዋጋ መሰረት በማድረግ ሰፊ የመምረጫ ጊዜ ሲሰጥ እንደነበር አስታውሷል፡፡

ይህም የወርቁን ትክክለኛ ዋጋ የማያሳይና ባንኩን ለከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

የዚህ ዓይነቱ አሰራር እንዲቀር መደረጉን ያወሳው የባንኩ መግለጫ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የወርቅ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ መንግስት አቅራቢዎችን በማበረታታት ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን አገራዊ ጥቅም ለማሳደግ መወሰኑን አውስቷል።

በዚህም ብሄራዊ ባንኩ አገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የ30 ቀናት የዋጋ መምረጫ ማበረታቻውን እንደገና ተግባራዊ ማድረጉን ገልጿል፡፡

እንዲሁም ባንኩ የወርቅ ግዥ የሚፈጽመው በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ መሆኑን አውስቶ፤ አቅራቢዎች ወርቅ በብዛት እንዲያቀርቡ ለማበረታታት የፖሊሲ እርምጃ መውሰዱንም በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በፖሊሲ ማሻሻያውም ቀደም ሲል ሲሰጥ ከነበረው ዋጋ ጭማሪ የአንድ በመቶ እና የሦስት በመቶን ወደ አምስት በመቶ ከፍ በማድረግ በእያንዳንዱ ግዢ ላይ ለነጋዴዎች ተጨማሪ ክፍያ እየተፈጸመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዝቅተኛ ወርቅ አቅራቢዎችን ለማበረታታት የቅበላ ጣራውን ከ150 ግራም ወደ 50 ግራም ዝቅ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

ባንኩ ማበረታቻውን ከጥቅምት 4 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ ተግባር ላይ ማዋሉን በማስታወቅ ወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ባንኩ ባዘጋጀው ማበረታቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል፡

በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ወርቅ ወደ ማዕከል ይቀርብ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ ግብይቱን በአንድ ማዕከል ማከናወኑ የአቅራቢዎቹን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በክልሎች የግዥ ማዕከላት ተከፍተው ግብይቱ እንዲከናወን መደረጉን አብራርቷል፡፡

የክልል የግዥ ማዕከላት መከፈት አቅራቢዎች ረጅም ጉዞ ሳያደርጉ፣ የትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎች ሳይኖርባቸው ወርቃቸውን እንዲሸጡ በመደረጉ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት መቻላቸውን ጠቁሟል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2010 የኢትዮጵያን ሕዳሴ  ለማፋጠን ለሕብረ-ብሔራዊነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለፀ።

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ኃላፊዎችና አባላት፤ የዴሞክራሲ ተቋማትና የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞች 12ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን ዛሬ አክብረዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሕብረ-ብሔራዊነትን ለማጠናከር ባለፉት አስርት አመታት በተሰራው ስራ ዜጎች ስለ ሕገ-መንግስቱና ፌደራል ስርዓቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ቢደረግም ቀጣይ ስራ በስፋት መሰራት አለበት።

ሕብረተሰቡ ስለ ፌደራል ስርዓቱና ሕገ-መንግስቱ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ችግሮቹ እየተፈጠሩ መጥተዋል፣ይህ የሆነው ደግሞ በፌደራል ስርዓቱ ላይ መግባባት ባለመፈጠሩ ሳይሆን ስርዓቱን ከማስፈፀም ጋር ተያይዘው በሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ አስፈጻሚ ግለሰቦች በሚፈጥሯቸው የመልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ብሔርተኝነት ሕብረ-ብሔራዊነትና ፌደራሊዝም የበለጠ እንዳይጎለብት ችግር ሆነዋል።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች መነሳታቸውን ለአብነት ያነሱት አቶ ያለው በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዜጎች እኩል ተጠቃሚ አለመሆናቸውንም ጠቁመዋል።

''በፌደራል ስርዓቱ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል ግን ወጣቱ በበቂ ሁኔታ የስራ እድል አልተፈጠረለትም፤ በአገሪቱ ውስጥ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ግን ህብረተሰቡን ሊያረካ የሚችል ልማት አልመጣም'' ብለዋል።

ከፌደራል ስርዓት ጋር ተያይዞ በክልሎች ድንበር ላይ ለተፈጠሩ ቀውሶች ተጠያቂዎቹን መንግስት በህግ ለመጠየቅ እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

በቀጣይም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን፣የመልካም አስተዳደርና የፍትኃዊ ተጠቃሚነት ስራዎችን በማጠናከር ለአገራዊ አንድነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "በህገ-መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሐሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ይከበራል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2010 "የ12ኛ የብሄሮች ብሄረሰቦችን በዓል ስናከብር በእስካሁኑ ስኬታማ ጉዟችን ያጋጠሙንን ችግሮች እየፈታን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቃላችን እያደስን መሆን አለበት" ሲል የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አሳሰበ።

ጽህፈት ቤቱ ህዳር 29 ቀን 2010  የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ቀንና ሌሎች ጉዳዮችን በማስመልከት "በዕኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ይበልጥ ይጠናከራል" በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ ልኳል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች በዓል ሲከበር "በህዝቦች የጋራ ጥረት የገነባናትን አዲሲቷ ኢትዮጵያ የበለጠ ለማድመቅ ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል" ሲል መግለጫው አትቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በየክልሉ የተከበረው በዓል የብሄሮችን እርስ በእርስ መቀራረብና አንድነት ማጎልበቱን ጠቁሞ፤ በተጨማሪም የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ልማት ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጿል።

የዘንድሮው በዓል ሲከበር እንደ አገር ለላቀ ውጤት በጋራ ለመንቀሳቀስ የአብሮነት ቃል የሚታደስበት ሊሆን እንደሚገባም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አሳስቧል።

መንግስት በጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያተተው መግለጫው፤ ወጣቱም ጤናውን እየጠበቀ ለአገራዊ ግንባታ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።

የመግለጫውን ሙሉ ይዘት ከስር ያገኙታል

 በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

 በዕኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ይበልጥ ይጠናከራል!

 የፊታችን  ሕዳር  29  ቀን  2010  ዓ.ም  የኢትዮጵያ  ብሔር  ብሔረሰቦች  ቀን፦ በህገመንግስታችን  የደመቀ  ህብረ ብሄራዊነታችን  ለህዳሴያችን!  በሚል መሪ ቃል በአፋር ብሄራዊ ክልል  በሰመራ ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡

 በአገራችን ታሪክ ብዝሃነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበትን ዕለት አስመልክቶ በየዓመቱ የሚካሄደውን በዓል ሁሉም ክልሎችና መስተዳድሮች በየተራ የማስተናገድ ዕድል አግኝተዋል፡፡

 በዓሉ በዕኩልነት፣ በመቻቻል፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ መርህ ላይ የተመሠረተውን ዲሞክራሲያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን ይበልጥ ለማዳበርና የአገራችንና የአስተናጋጅ ክልሎችን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው። በተጨማሪም  በየአስተናጋጅ ክልሎቹ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲፋጠኑ፣ ግለሰብ ባለሃብቶች በሆቴልና በሪል እሴት ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ፣ የአስተናጋጅ ክልል ከተሞች እንዲያድጉ የማድረግና የመሳሰሉ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎችንም እያስገኘልን መሆኑ ይታወቃል።

 በዓሉ ህዝባችን መብቱና፤ ነፃነቱ ተከብረውለት ለፈጣን ልማትና ለአገር ግንባታ እንዲረባረብ ብሄራዊ መግባባትን እና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡  በተለይም የዘንድሮው በዓል የሚከበረው ህዝቦች ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብትና ጥቅም አስከብረው የፌዴራል ሥርዓቱን የበለጠ ከማጠናከርና ከመቀጠል አኳያ የመጡበትን የተሃድሶ ጉዞ በመገምገም ለላቀ ውጤት ለመነሳሳት ቃል በመግባትና እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍጥነት በመራመድ ነው፡፡

 መንግስት ባስቀመጠው የተሃድሶ መስመር፣ በሁለንተናዊ መልኩ የታዩበትን ድክመቶች ሁሉ በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ የብሔሮችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የፌዴራላዊ ስርዓቱ የበለጠ እንዲጠልቅና እንዲደምቅ ለማድረግ ትክክለኛውን መስመር ይዞ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ በህዝቦች የነቃ ተሳትፎ፣ አንድነትና ትብብር ጉዞው እንደሚሰምርም በጽኑ ያምናል።

 ከልማት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ከመፍታት ይልቅ ለግል ብልጽግና ሲባል በተጓዳኝ የሚፈፀምን የሃብት መቀራመት ችግርና የህዝቦችን አንድነት ሊሸሸረሸሩ የሚችሉ ያልተገቡ አካሄዶችን ለማረም መንግሥት በሥር ነቀል መንገድና መልሶ መላልሶ የውስጥ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል። ተሃድሶ ሲጀመር እንደተቀመጠው የተለዩት ችግሮች በአንድ ጀምበር ታርመው የሚያልቁ አይደሉምና! በመሆኑም ለዚህች አገርና መንግስት በጎ የማይመኙ ኃይሎች ከሚሉት በላይ ድክመቶቹን አንድ በአንድ ከህዝብ ጋር  ሆኖ በሚገባ ለይቶና መውጫ መንገዶችን አበጅቶ ለመፍታት በቀጣይነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ 

 የዚህ ውጤት መመዘኛው የተሟላ የህዝብ እርካታን ማምጣት ነው፤ ከዚህ አንጻር የህዝባችንን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቀሪ ሥራዎችም በቀጣይነት እየተከናወኑ ነው። እነዚህኑ ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ የህዝብ ተሳትፎና ትብብር መንግሥት እንደሚፈታቸውም ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

 በተለይም አገር የመረከብን ታላቅ አደራ የተሸከመው የአገራችን ወጣት በአንድ በኩል የስራ ባህሉን ቀይሮ ህይወቱን ከአንድ ደረጃ ወደሌላኛው እያሸጋገረ አኩሪ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል።

 በሌላ በኩል ደግሞ ማንንም ተጠቃሚ የማያደርገው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ቅስቀሳ ሰለባ እንዳይሆን፣ ለዕውቀትና ለሥራ እጅግ ውድ የሆነውን ጊዜውን በአልባሌ እንዳያባክን፣ በተለይም እንደ አገር በመዘናጋታችን የተነሳ እንደ አዲስ እያገረሸ ላለው የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ በጥብቅና በቀጣይነት መስራት ይኖርበታል። ይህንን ጥረቱን ማገዝ የወላጆችም፣ የመምህራንና የሌሎችም ባለድርሻ አካላትና የመላው ህብረተሰብ ሃላፊነት እንደሆነም ሊታወቅ ይገባዋል።

 በጥፋት ኃይሎች እንቅስቃሴ ምክንያት በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚደረጉት አንዳንድ እንቅፋቶች መሰረት የሌላቸው በመሆናቸው እንደወትሮው ሁሉ ይከሽፋሉ፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት ስር የሰደደ መተሳሰብና መቻቻል ባጎለበቱ ህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር የሚደረግ የውስጥም ይሁን የውጭ የጥፋት እንቅስቃሴ የሚዘልቅ ውጤት አያመጣምና፡፡

 በመሆኑም ከፊታችን የሚጠብቀንን በዓል ስናከብር በእስካሁኑ ስኬታማ ጉዟችን ያጋጠሙንን ችግሮች እየፈታን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ በህዝቦች የጋራ ጥረት የገነባናትን አዲሲቷ ኢትዮጵያ የበለጠ ለማድመቅ ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2010 የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላትና ባለሙያዎች የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር 'የከረረ ብሄርተኝነት' አስተሳሰብ የመቀየር ኃላፊነታቸውን በተግባር ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።                

 የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት/ብአዴን/37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ወረዳ ደረጃ ተከብሯል።        

 ህብረ-ብሄራዊነት፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነትና ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በሚል ርዕስ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።                 

 የመወያያ ጹሁፉን ያቀረቡት የወረዳው አመራር አባል አቶ ሰይፈ ደርቤ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን በአገሪቷ የነበረውን የእኩልነት፣ የኢኮኖሚና የብሄር ጥያቄዎች ዘላቂ እልባት እንዲያገኙ ታግሏል።       

 ''በዚህም ህዝቡ ባለፉት 26 ዓመታት ተጠቃሚ የሆነበት እድገት ተመዝግቧል'' ብለዋል።          

 በተለይ የመገናኛ ብዙሁን አመራር አባላትና ባለሙያዎች ''የከረረ ብሄርተኝነት አመለካከት የህዝቡን አንድነት የሚጎዳ በመሆኑ ለዚያ የማይመች ምህዳር በመፍጠር በኩል ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው'' ነው ያሉት።    

 የብአዴን ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ወረዳ ሰብሳቢ አቶ ሰብስቤ ከበደ በበኩላቸው፤ የሚዲያው አመራርና ባለሙያው ለህብረተሰቡ የሚፈጥረው ግንዛቤ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።                

 ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመጡት አቶ ሙላት ካሳዬ በበኩላቸው፤ የልማታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን እንዲያሸንፍ መስራት እንደሚገባ ያነሳሉ።       

 በአገሪቷ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በህብረተሰቡ ውስጥ ማስረጽ "ቁልፍ ጉዳይ ነው" ይላሉ።

 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢሄዴን/ ተወካይ አቶ ኤሊያስ አዋቱ እንደሚሉት፤ በህዝቡ ዘንድ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በሚጠበቀው ደረጃ እንዳይጎለብት በማድረግ በኩል በማህበራዊ ሚዲያው የሚደረገው ዘመቻ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው።             

 በበዓሉ ላይ የብአዴን እህት ድርጅቶች የድጋፍ መልዕክት ያቀረቡ ሲሆን፤ በትግሉ ለተሰው ሰማዕታት የህሊና ጸሎትም ተደርጓል።                        

Published in ፖለቲካ

ቤይጂንግ ህዳር 22/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና ገበያውን ይበልጥ ማስፋት የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

አየር መንገዱ ባለፈው ወር ከቦይንግ ኩባንያ ግዥ ፈጽሞ የተረከበውን ቦይንግ 787-9 ዘመናዊ አውሮፕላን በዚህ ሣምንት ወደ ቻይና መዲና ቤይጂንግ በረራውን ጀምሯል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና ሞንጎሊያ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በርታ ለኢዜአ እንደገለጹት ቻይናውያን ቀዳሚ የአየር መንገዱ ደንበኞች ናቸው።

ቻይና በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ ከፍተኛ ቁጥር ካለው የህዝቧ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ለአየር መንገዱ ጠቃሚ ገበያ መሆን ችላለች ብለዋል። 

ብዙ አፍሪካውያንና ቻይናውን ከአፍሪካ ወደ ቻይና አሊያም ከቻይና ወደ አፍሪካ ለሚያደርጉት ጉዞ አየር መንገዱን ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሆነ ገልጸው ይህን ፍላጎት ማርካት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ አየር መንገዱ በቻይና ቤይጅንግን ጨምሮ አምስት መዳረሻዎች ሲኖሩት ገበያውን ይበልጥ ለማስፋት በቅርቡ ስድስተኛ መዳረኛውን እንደሚከፍትም አቶ ያሬድ አመልክተዋል።

"ቤይጂንግ፣ ሻንጋይ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ጓንጆና ቼንዱ የአየር መንገዱ የቻይና መዳረኛዎች ናቸው" ያሉት ዳይሬክተሩ "በቅርቡም ሼንጄን፣ ቾንቺንግ እና ጄንጁ ከተሞች ተጨማሪ መዳረሻዎቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በነባር የአየር መንገዱ መዳረሻዎችም የበረራ ድግግሞሹን በማሳደግ የቻይና ገበያውን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን በረራውን ወደ ቤይጂንግ የጀመረው ዘመናዊ አውሮፕላንም 315 መንግዶችን የመያዝ አቅም ያለው ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፍና ትርፋማ አየር መንገድ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአምስት አህጉሮች ባሉት ከ100 በላይ መዳረሻዎቹ በዓመት ከስምንት ሚሊዮን በላይ መንገዶችን ያጓጉዛል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ ህዳር22/2010 የአዲስ አበባ ከተማን ጽዳት ለማሻሻል የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀቱን የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ አስታወቀ።

ፅህፈት ቤቱ "እኔ አካባቢዬን አጸዳለው እናንተስ?"  በሚል መሪ ሃሳብ  ከህዳር 22 እስከ ህዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባሉት ቀናት ከህብረተሰቡ የተወጣጡ አካላት እና ከወረዳ እስከ ከተማ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት የህዝብ ንቅናቄ መድረክ  ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የንቅናቄው ዋና አላማም  የከተማዋን ጽዳትና ውበት በዘላቂነት ሊያረጋግጥ የሚችል ተግባር ለማከናወን የደረቅ ቆሻሻና ሌሎች ተረፈ ምርቶች ነዋሪዎችና ተቋማትን በማሳተፍ ጽዳቱን ከእያንዳንዱ ቤት ለመጀመር ነው።

በአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ቢሮ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ እንዳሉት በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ፋይዳ ያላቸው እንቅስቃሴዎች እየሰፉ መጥተዋል።

በመሆኑም የመዲናዋ ነዋሪና ከፍጆታ አገልግሎት የሚገኙ ተረፈ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል።

የከተማዋን ጽዳት ውብትና አረንጓዴ ልማት በነዋሪውና በመንግስት የተቀናጀ ተሳትፎ በዘላቂነት ለማሻሻል እንዲሁም ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ ለጎብኝዎች ሳቢና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን የህዝብ ንቅናቄ መድረኩ ማስፈለጉን ገልፀዋል ።

70ሺ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን  በንቅናቄው ዓላማና አስፈላጊነት ላይ በማወያየት የጋራ መግባባት መፍጠር የንቅናቄው ግብ ነው፡፡

በመሆኑም የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ፤ የአካባቢ ብክለትና የሙቀት መጨመር በሰውና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ለማዘመን የታሰበ መሆኑንም ወይዘሮ ቆንጅት ገልጸዋል።

የከተማዋን ገጽታ ግንባታ በማሻሻል ለነዋሪዎቿ የምትመችና  በአህጉሪቱ ካሉ ከተሞች ተመራጭ ከተማ ለማድረግ  ሁሉን አቀፍ የህዝብ ተሳትፎ ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑም ተነግሯል፡፡

አዲስ አበባን የማጽዳት ስራው የፌደራልና የክልል ከተሞች ከፍተኛ አመራሮችን በማሳተፍ ህዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በዚሁ ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ተመሳሳይ ተግባር የሚካሄድ ሲሆን ስራው በየወሩ በቋሚነት ተጠናክሮ  እንዲቀጥል አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግም  ምክትል ስራ አስኪያጇ ገልጸዋል ።

Published in ማህበራዊ

ጊምቢ ህዳር 22/2010 በምእራብ ወለጋ ዞን ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመከላከል ዙሪያ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ።

በዞኑ ጤና መምሪያ የኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ሂደት ፈፃሚ አቶ አማኑኤል ለሜሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ ከጥቂት አመታት ወዲህ በአመራሩም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው መዘናጋት የቫይረሱን ስርጭት እንዲጨምር አድርጎታል።

"ከአምስት ዓመት በፊት ከዜሮ ነጥብ 16 በመቶ በታች ደርሶ የነበረው የቫይረሱ ስርጭት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስከ ዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ድረስ በተደረገው ግምገማ ስርጭቱ ወደ ዜሮ ነጥብ 23 በመቶ ከፍ ብሏል" ብለዋል።

እንደ አቶ አማኑኤል ገለፃ በ2009 በጀት አመት የኤች አይ ቪ ደም ምርመራ ካደረጉ 150ሺህ ከሚሆኑ ሰዎች መካከል 348ቱ ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቷል፡፡

"የምርመራው ውጤት ባለፉት ዓመታት ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።

በአመራሩ ዘንድ ትኩረት መነፈጉ ስርጭቱ እንዲጨምር አድርጓል የሚሉት አቶ አማኑኤል ከመስሪያ ቤቶች ስራ ማስኬጃ ይቆረጥ የነበረው ሁለት በመቶ መቆሙን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተገኘው መድረክ ሁሉ ይካሄድ የነበረው ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር መገታቱም ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ የጠፋ በማስመሰሉ በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች ተጠቃሽ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትም በተለያዩ መድረኮችና ትምህርት ቤቶች ሁሉ ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ የማስተማር ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ስርጭቱ ጎልቶ በሚታይባቸው ጊምቢ፣ ነጆና መንዲ ከተሞች ነፃ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምርመራና የምክር አገልግሎት በመስጠት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተቀናጀ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጊምቢ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ ወጣት ሂካ ገመቹ በሰጠው አስተያየት "ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የሚሰጠው ትምህርት ቀንሷል" ብሏል፡፡

በተለይ በትምህርት ቤቶች በተቋቋሙ ክበባት አማካኝነት ይሰጥ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቀነሱን በማሳያነት አንስቷል፡፡

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አብዮት ዳኒኤል በበኩላቸው ጤና ተቋማት ላይ ዘወትር ጠዋት በቫይረሱ ዙርያ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡

"የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ ስራ መሰራት ይኖርበታል" ብለዋል።

አቶ መኮንን ባይሳ በበኩላቸው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመገናኛ ብዙሀንም ሆነ በየስብሰባው ከኤች አይ ቪ ቀን ክብረ በዓል ውጪ ለጉዳዩ ትኩረት አለመሰጠቱ በሽታው የጠፋ እንደመሰላቸው ተናግረዋል።

በዞኑ የዓለም ኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በሶስት ከተማ አስተዳደሮችና በ21 ወረዳዎች መዘናጋትን ማስወገድና ስርጭቱን በማስቆም ላይ ትኩረት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት እንደሚከበር ታውቋል ።

 

Published in ማህበራዊ

ማይጨው ህዳር 22/2010 የተሻሻሉ የሰብል መውቂያ መሳሪያዎችን በመጠቀም የምርትና የጊዜ ብክነትን መከላከል መቻላቸውን ያነጋገራቸው የትግራይ ደቡባዊ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶ አደር ኪሮስ ከበደው እንደገለጹት የዘንድሮ መኸር ምርታቸውን በሰብል መውቂያ ማሽን በመጠቀም መሰብሰባቸው የጊዜና የምርት ብክነት ችግራቸውን መፍታት ችለዋል።

ዛሬ ላይ በአንድ ሰዓት የሚሰበስቡትን ምርት ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ የሁለት ቀናት ድካም ከማስፈለጉም በላይ የሚባክነውም መጠን ከፍትኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመምሪያው የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሃይለ ካሳ በበኩላቸው በመኸሩ እርሻ ከለማው ሰብል ውስጥም በ80 ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኝና ለምርት የደረሰውን አዝርዕት የመሰብሰብ ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የተቀረው በ43 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የስንዴና የማሽላ ሰብል ደግሞ ወቅቱን ካልጠቀበ የዝናብ ውሃ ለመታደግ የአጨዳና የመሰብሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜም ለዞኑ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የአውድማ መውቂያ ቴክኖሎጂዎች ድጋፍ በመስጠት የድህረ-ምርት ብክነትን እስከ 30 በመቶ መከላከል መቻሉንም አስረድተዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2010 ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርአተ -ጾታ እኩልነት እና ማብቃት ተቋም ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ የግል ድርጅቶች መርዳት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተመካክሯል።

የአለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው በአፍሪካ ከሰህራ በታች ባሉ አገራት ከሚኖሩ ሴቶች ከ20 እስከ 70 በመቶ ያህሉ ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት የስርአተ -ጾታ እኩልነት እና ማብቃት ተቋም የኢትዮጵያ ተወካይ ለቲ ቺዋራ እንዳሉት የአፍሪካን ሴቶች ከጥቃት በመከላከል በኢኮኖሚ እራሳቸውን ችለው ጠንካራ እንዲሆኑ ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ነው።

በተለይም ሴቶች በኢኮኖሚ ጠንካራ ከሆኑ ለጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነ የሚናገሩት ተወካይዋ ይህንን ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ወሳኝ ነው።

ይህንን ሃሳብ የሚደግፉት የማሪያ ማገገሚያ ማእከል ዳይሬክተር ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ማእከሉ የሚመጡ ሴቶች የስነ ልቦና፣ የህክምናና የሙያ ስልጠናዎችን ያገኛሉ።

የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካና እናት ባንክ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ በስራ እድል ፈጠራና በሌሎች ድጋፎች እየተሳተፉ መሆኑን ለአብነት በማንሳት ሌሎች ተቋማትም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገችውና  የጾታዊ ጥቃት  ሰለባ የሆነች ወጣት እንዳለችው በማሪያጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማረፊያና ማገገሚያ ማዕከል ከስነ ልቦና ችግሯ  በማገገም በጸጉር ሙያ ሰልጥናለች።

ነገር ግን እሷንና ሌሎች መሰል ጥቃት ደርሶባቸው አገግመው የሙያ ባለቤት የሆኑና ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን ሴቶች የሚደግፍ ተቋም ያስፈልጋል ትላለች።

በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ የግል ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በስልጠናና በስራ እድል ፈጠራ ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በኢንዱስትሪ ውስጥ ካለፉ ቱር ኦፕሬሽን፣ ፍሮንት ኦፊስ ላይ እንደዚህ አይነት ሙያውን ይዘው ከመጡ  ቅድሚያ እነሱን ልንቀጥር ቃል እገባለሁ"  ያሉት ከካራቫን ሆቴልአቶ በላይ ነጋሽ ናቸው፡፡

ከሼባ ሌዘርአቶ ስለሺ ተሰማ "ችግሩ የደረሰባቸው ሴቶች ሌሎችም ለዛ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ትሬኒንግ በመስጠት ሴቶችን ማሳተፍ ይቻላል ይህን ማድረግ የምንችልበት ሁኔታ አለ" ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስርአተ -ጾታ እኩልነት እና ማብቃት ተቋም "ማንንም ወደ ኋላ እንዳንተው ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም" በሚል መሪ ቃል የ16 ቀን የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ እያካሄደ ነው።

ደምበል ሲቲ ሴንተር፣ አፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ብርቱካናማ ቀለም መብራት እስከ ታህሳስ አንድ የሚኖራቸው ተቋማት የዘመቻው አካል መሆናቸውን እወቁልን ብለዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን