አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 09 November 2017

ባህር ዳር ጥቅምት 30/2010 በአማራ ክልል በተቀናጀ አግባብ እየተከናወነ ካለው የተፋሰስና የመስኖ ልማት የተሻለ ተሞክሮ እንዳለ ማየታቸውን የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ።

 በርዕሰ-መስተዳደሩ የሚመራ የክልሉ አመራሮች ቡድን በባህር ዳር ዙሪያ ያለውን የአባገሪማ ተፋሰስና የአንዳሳ የመስኖ ልማትን ጎብኝተዋል።

 ከጉብኝታቸው በኋላ ርዕሰ-መስተዳደሩ እንደተናገሩት ከአማራ ክልል ጋር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር የሁለቱን ክልል ህዝቦች ተጠቀሚ የሚያደርጉ የልምድ ልውውጦች ሲደረጉ ቆይተዋል።

 ዛሬ በተደረገው የልምድ ልውውጥም አርሶ አደሩ ተፈጥሮን በመጠበቅና በማልማት ተጠቃሚ እንደሆነ ማየታቸውን ገልጸው ይሔም በክልላቸው ያለውን ክፍተት ለማስተካከል መልካም ተሞክሮ የተወሰደበት እንደሆነ አስረድተዋል።

 የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ማሞ ተሰማ በበኩላቸው አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት መራቆት ክፉኛ የተጎዳ እንደነበር አመልክተዋል።

 ከ2004 ጀምሮ አካባቢውን በጥናት በመለየት፣አርሶ አደሩን በማስተማር በተፋሰስ ልማት ተከልሎ በመልማቱ መሰረታዊ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።

 በወረዳው የአባገሪማ ተፋሰስን ጨመሮ 200 ተፋሰሶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እርከን በመስራት፣ ችግኝ በመትከል፣ እንስሳትን አስሮ በመቀለብ በተገኘው ስኬት አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ በእንስሳት ማድለብና በግብርናው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 በቡድን ተደራጅተው አካባቢውን በማልማትና በመጠበቅ በእንስሳት ማድለብና በአትክልትና ፍራፍሬ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ የጎንባት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ገዳሙ አግማስ ናቸው።

 ቀደም ሲል ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ አካባቢው የነበረውን የደን ሃብት በመጨፍጨፍ ለበረሃማነት ተጋልጦ እንደነበር አስታውሰው ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነው ስራም ለውጥ ማየታቸውን ጠቁመዋል።

 በዚህም ባለፈው ዓመት እንስሳት በማድለብና የተሻሻሉ የብርቱካን፣ የማንጎ፣ የአቦካዶና የሙዝ ዝርያዎችን አልምተው በመሸጥ 140 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

 የተፋሰሱ አባላትም በማህበራቸው ከ70 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት መቆጠባቸውን አመልክተው በቀጣይ ዘላቂ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን በባለሙያ በማስጠናት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልፀዋል።

 በጉብኝቱ ላይ የሁለቱም ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳደሮችን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የግብርና ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምርት የማያስተጓጉል የግብዓት አቅርቦት ስርዓትን መፍጠር እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ገምግሞ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በቆዳ እና በቆዳ ውጤቶች  ምርት ላይ መስትጓጎል እንዳይፈጠር  በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

ግብዓት የሚሰበሰብበትንና የሚከማችበትን አግባብን ማሻሻል እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ በሚገቡት ግብዓቶች ላይ የሚፈጠሩትን የሎጂስቲክ ችግሮች የሚያቃልል ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ የግብዓት አያያዝ ጥራትን የሚያጎለብቱ  ቴክኖሎጂዎችን  ተግባራዊ  ማድረግ  እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ  በበኩላቸው፤ የግብዓት እጥረት ዘርፉን በዋናነት እየተፈታተነው እንደሆነ ተናግረዋል።

የእንስሳት እርድ ወጥ በሆነ መልኩ ያለመከናወኑ በዘርፉ የተሰማሩ  ፋብሪካዎች  ግብዓት በበቂ ሁኔታ እንዳያገኙ ማደረጉንም  ገልጸዋል።

እነዚህ ፋብሪካዎች ዘጠና በመቶ የሚሆነውን ግብዓታቸውን በተለያዩ በዓላት ወቅት በሚፈጸም እርድ እንደሚያገኙ የጠቆሙት አቶ ወንዱ፤  "ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  አገሪቷ ወደ ውጭ አገር የምትልከውን የስጋ ምርት ማሳደግ አለባት" ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ እና በዘረፉ ለተሰማሩ አምራቾች ደግሞ የክምችት ሂደቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ባለሙያዎች የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ እንደቀሰሙ አቶ ወልዱ ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ ጥቅምት 30/2010 ሰብሎችን አፈራርቀው መዝራት ከጀመሩ ወዲህ የእፅዋት በሽታን በመቀነስ ምርትና ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንዳስቻለቸው በባሌ ዞን የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

 የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ ሰብልን አፈራርቆ ለመጠቀም  አመቺ  የሆኑ የጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ሰብሎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጾዋል ፡፡

 በአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ ሰብልን አፈራርቀው   ከሚጠቀሙ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ጫላ ደኑ እንደተናገሩት ከዚሀ በፊት በአንድ ማሳ ላይ ተመሳሳይ ሰብል እየደጋጋሙ ስለሚዘሩ ስንዴ ማሳቸው በዋግ  ይጠቃ እንደነበር አስታውሰዋል ፡፡

 በዚህ ልማዳዊ ዘዴ ከሚያለሙት የስንዴ ሰብል የሚያገኙት ምርት በሄክታር ከ15 ኩንታል ያነሰ እንደነበርም ተናግረዋል ።

  ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከግብርና ባለሙያዎች ያገኙትን ስልጠናና ሙያዊ ምክር ተግባራዊ በማድረግ አፈራርቀው መዝራት በመጀመራቸው የዋግ በሽታን ለመቀነስና በሄክታር በአማካይ እስከ 65 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት አስችሏቸዋል፡፡

 የሲናና ወረዳ ኦቦራ ቀበሌ አርሶ አደር ሙልአታ በርሲሳ በበኩላቸው  ሰብልን አፈራርቀው መዝራት ከጀመሩ ወዲህ የመሬት ለምነታቸው እየጨመራ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

 በዚህም ከቀደም ሲል ተመሳሳይ ሰብል ደጋግመው በማልማት ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው ከ20 ኩንታል የማይበልጥ የስንዴ ምርት ወደ 45 ኩንታል ከፍ ማለቱን አስታውቀዋል፡፡

  በሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የጥራጥሬ ሰብሎች ተመራማሪ አቶ ታደለ ታደሰ እንደተናገሩት ሰብልን አፈራርቆ መዝራት ምርታማነትን ከ20 እስከ 25 በመቶ መጨመር እንደሚቻል በምርምር መረጋጋጡን ነው  የጠቆሙት ፡፡

  የማዳበሪያ ፍጆታንም  ከ25 እስከ 30 በመቶ እንደሚቆጥብ ተመራማሪው  ተናግረዋል፡፡

 ማዕከሉ የጥራጥሬ ሰብል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ከ17 በላይ ምርጥ ዝሪያዎችን  በምርምር በማውጣት ማሰራጨቱን አስረድተዋል ።

 በተለይ ባለፈው ዓመት በሀገር አቀፍ የዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ከታዩ በኋላ የተለቀቁት የአተር፣ ባቄላና ምስር ዝርዎች በአማካይ በሄክታር ከ30 እስከ 45 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ፡፡

 ከነባር ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸሩም ከእጥፍ በላይ ምርታማ እንደሆኑና ለአፈራርቆ መዝራት አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

 በዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት  ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን አስተባባሪ አቶ አለምእሸት አለማየሁ በበኩላቸው በመኽር ወቅት እየለማ ካለው 300 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 60 ሺህ የሚሆነው መሬት በአፈራርቆ መዝራት የተሸፈነ ነው ።

 በባሌ ዞን እየለማ ባለው የመኽር አዝመራ ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ጥቅምት 30/2010 አርሶ አደሩ በተቀናጀ የተባይ መከላከል በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኝ ማህበረሰብ ተኮር የዕፅዋት ኪሊኒኮችና የሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን ማስፋፋት እንደሚገባ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ።

 በመላው አገሪቷ በአሁኑ ጊዜ በ100 ወረዳዎች የሚገኙ የእፅዋት ክሊኒኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ተብሏል ።

 ህብረተሰቡ በዕፅዋት ጥበቃ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና የመፍትሄው አካል ለማድረግ ያለመ የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

 በሚኒስቴሩ የዕፅዋት ጤና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ወልደሃዋሪያት አሰፋ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት የተቀናጀ የተባይ መከላከል ፓኬጅ  አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ግልፅ ግንዛቤ ይዘው የችግሮቹ የመፍትሄ አካል እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡

 በሙከራ ደረጃ በኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የተጀመረው ይኸው ፕሮጄክት  በዕፅዋት ጥበቃ ዙሪያ ህብረተሰቡ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

 እየተገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ማህበረሰብ ተኮር የዕፅዋት ኪሊኒኮችና የሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

 በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘቢድዮስ ሳላቶ በበኩላቸው በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዘር ልውውጥ፣ ንግድ፣ በትራንስፖርትና ተያያዥ ጉዳዮች የፀረ ሰብል ተባዮች እንደሚዛመቱ ገልጠዋል።

 ተባዩ የሚያስከትለውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል የዕፅዋት ጤና ጥበቃ ክሊኒኮችና የአርሶ አደሩ ማሰልጠኛ ማዕከላት በተቀናጀ የተባይ መከላከል ፓኬጅ ላይ ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

 ''ነፍሳትና የተለያዩ አረሞችን ጨምሮ ቀድሞ ለመከላከል  የሚያስችል የፍተሻና የአሰሳ ሥርዓት መዘርጋትና ማህበረሰብ ተኮር የእፅዋት ክሊኒኮችን ማጠናከር አለብን'' ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት በትግራይ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ 50 የእፅዋት ክሊኒኮችን ጨምሮ በመላው አገሪቷ በ100 ወረዳዎች ክሊኒኮች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 በሰብል ላይ  ከቡቃያው ጀምሮ የሚከሰቱ ችግሮች አርሶ አደሩ ማወቅ እንዲችልና ራሱ የመፍትሄው አካል እንዲሆን ለማድረግ ማህበረሰብ ተኮር ክሊንኮችን በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጠዋል።

 የሰብል ተባይ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ከ40 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስከትል የገለፁት ደግሞ  በኢትዮዽያ ግብርና ምርምር የዕፅዋት ጥበቃ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዶክተር በላይ ሀብተገብርኤል ናቸው።

 ችግሩን ለማቃለል ማህበረሰብ ተኮር የዕፅዋት ኪሊኒኮችና የሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን ከማጠናከር በተጨማሪ የእፅዋት ባለሙያዎችን አቅም፣ ክህሎትና ዕውቀት መገንባት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 ኒውዝላንድ በምግብ ማቀነባበሪያና በእንስሳት ልማት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታካፍል ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጠየቁ።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኒውዝላንድ አምባሳደር ብሩስ ሼፐርድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አሰናብተዋል።

ኒውዝላንድ በምግብ ማቀነባበሪያና በእንስሳት ልማት ስኬታማ ታሪክ ያላት አገር ስትሆን፤በአለም ላይ 35 በመቶ የምግብ ማቀነባበሪያና የእንስሳት ምርቶችን ገበያ ተቆጣጥራለች።

ይህንን ስኬታቸውን በኒውዝላንድ ባለሃብቶች ተሳትፎም ሆነ "መንግስት ለመንግስት በሚደርጉ ግንኙነቶችና ልምድ ልውውጦች ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ማምጣት ይቻላል" በሚሉት ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አሸብር ጌትነት እንደገለጹት፤ ይህንን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ በእንስሳት ልማት በግብዓትነት መጠቀም እንደሚገባ ዶክተር ሙላቱ አንስተዋል።

የኒውዝላንድ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው መዋዕለ ንዋያቸውን በሚያፈሱበት ሁኔታ ተመካክረዋል።

በተጨማሪም የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይም መክረዋል።

አዲስ የሚሾሙት አምባሳደርም የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማዳበር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ዶክተር ሙላቱ ተናግረዋል።

ተሰናባቹ አምባሳደር ብሩስ ሼፐርድ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ እድገት መልካም መሆኑንና አገራቸውም ልማቱን መደገፍ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉ ጠቁመው፤ መንግስታቸውም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን መቀራረብ የበለጠ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኒውዝላንድ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው እ.አ.አ በ2014 ሲሆን፤ ተሰናባቹ አምባሳደር ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግለዋል።

ኢትዮጵያ ከኒውዝላንድ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን የምታካሂደው አውስትራሊያ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ነው።

በኒውዝላንድ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማሪያም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአገሪቷ ጠቅላይ ገዢ ፓትሲ ሪዲ ጥቅምት 2009 ዓ.ም ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

በዚሁ ወቅት ሁለቱ አገሮች አብረው መስራት በሚያስችሏቸው በምግብ ዋስትናና ከአየር ትራንስፖርት ጋር የተያያዙ ስምምነቶችን እንዲፈርሙም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች የህዝብ ኮንፈረንሱ እንደተጠናቀቀ ወደ ቀድሞ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር ወስጥ መገናኛ ብዙኃን በአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

 ግጭቱ የተከሰተበት አካባቢ "ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግጭቱ ምክንያትም ህገ ወጥ ነጋዴዎች መሆናቸው ስለተረጋገጠ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

 በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ግጭቱ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በአካባቢዎቹ ሰላም ከማስፈን ጀምሮ ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።

 እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማርያም ገለጻ "መንግስት ግጭቱ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ለመመለስ ሶስት አበይት ዕቅዶችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።"

 በአካባቢው ሰላም ማስከበር የዕቅዱ የመጀመሪያው አብይ ተግባር ሲሆን፤ በግጭቱ የተሳተፉ የፖለቲካ አመራር አባላትን መለየት፣ የህዝብና የአመራር የሰላም ኮንፈረንሶችን ማካሄድና ለግጭቱ መፈጠር መንስኤ የሆኑትንና ጉዳት አድራሾችን በቁጥጥር ስር ማዋል ሁለተኛው እቅድ ነው።

 ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ግጭቱን እንዲመረምር መደረጉን ጠቁመው፤ በምርመራው ውጤት መሰረት መንግስት እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

 በዚህም አሁን በሁለቱም ክልሎች የሰላም ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ መሆናቸውን አመልክተው፤ "የግጭቱ ዋና ዋና ተሳታፊዎች በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ቀጥሏል" ብለዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ኮንፈረንሶቹ እንደተጠናቀቁ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ ይጀመራል።

 ከዚህ ባለፈ ክልሎች የፌደራሊዝም ስርዓት በዘረጋላቸው አሰራር መሰረት የተጀመረው የክልሎች ከክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

 "ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተካሂዷል፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ የትግራይና አማራ ክልሎች እንደዚህ እያለ ሁሉም ክልሎች ከጎረቤት ክልል ህዝብ ጋር ከተገናኙ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ የማጠቃለያ ዝግጅት ይኖራል" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 በቅርቡ የተደረገው የምንዛሬ ዋጋ ማሻሻያ ኢኮኖሚውን እያነቃቃው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአገር ወስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው "አገሪቷ ከውጭ የምታስገባቸው የካፒታል ዕቃዎች እየጨመሩ መምጣታቸውና የውጭ ንግዱ በመቀዛቀዙ መንግስት የውጭ አገሮች የምንዛሬ ዋጋ ማሻሻያ እንዲያደርግ አድርገውታል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ እድገት በየዓመቱ "ከዓለም ቀዳሚ ከሚባሉት አገሮች መካከል ሲጠቀስ ቆይቷል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ስድስት ጊዜ የምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በየጊዜው የተደረጉት ማሻሻያዎችም አገሪቷ ከ400 ቢሊዮን ብር በ2009 ዓ.ም ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ ለማንቀሳቀስ እንዳስቻላት ተናግረዋል።

ዘንድሮም የአገር ወስጥ ቁጠባ፣ የውጭ ንግዱንና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተወሰደው የምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ኢኮኖሚውን እያነቃቃው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም "የአገር ወስጥ ቁጠባ በ30 በመቶ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ18 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ በ12 በመቶ እንዲሁም የውጭ ንግዱ በተለይም የቡና ንግድ በ19 በመቶ እድገት ማሳየታቸው ለኢኮኖሚው መነቃቃት በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው" ብለዋል።

ዘንድሮ ከግብርናው የመኸር ሰብሎች  ከፍተኛ ምርት እንደሚሰበሰብ በምርት ቅድመ ትንበያ ግምገማ መረጋገጡ ኢኮኖሚው የበለጠ መነቃቃት እንደሚታይበትም  ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ በፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ጭማሪው ምክንያታዊ ባለመሆኑ መንግስት በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚቀጥልበትም አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈ መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ዓምና ወደነበረበት ነጠላ አሃዝ ለማድረስ የዋና ዋና የፍጆታ ምርት አቅርቦት ስራው እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በስኳር ዕጥረት ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ ለተከሰተው እንግልት "መንግስት ኃላፊነቱን ወስዷል ይቅርታ እንጠይቃለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሩ በድጋሚ እንደማይከሰት አስታውቀዋል።

በተያያዘም ዜና ሼህ ሙሃመድ አሊ አላሙዲ አስመልክተው ሲገልጹ፤ "በሳውዲ ዓረቢያ በእስር ላይ መሆናቸው ከተሰማ በኋላ ባለሃብቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አጋር በመሆናቸው መንግስት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው" ብለዋል።

"መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ከሳውዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር በዲፕሎማሲው መስክ እየተነጋገረ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ባለሃብቱ በሳዑዲ በህግ ጥላ ስር በመሆናቸው በኢትዮጵያ ያለው ንብረታቸውን ሳዑዲ እንዲታገድ ብትፈልግ ኢትዮጵያ እንዴት ታየዋለች? የሚል ጥያቄም ከጋዜጠኞች ተነስቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም "ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ነች፤ ባለሃብቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያጠናክሩ መንግስት ክትትልና ድጋፉን ይቀጥላል" ብለዋል። 

   

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 የአፋር ክልል የዘንድሮውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለማክበር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ሕዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም የሚከበረውን 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችና  የኪነ ጥበብ ማህበራት በተደረገላቸው ግብዣ የበዓሉን ዝግጅት ስፍራዎችና የቱሪስት መስህብ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።

የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የሚከበር ሲሆን፤ለዝግጅቱ  የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማትና የእንግዶች ማረፊያ ስፍራዎች ግንባታ መጠናቀቁም ነው የተገለፀው።

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም የቱሪዝም ማስፋፋትና ፓርኮች ልማት ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብዱልቃድር እንደተናገሩት፤ ቀሪ ስራዎችም የዝግጅቱ ቀን ከመድረሱ በፊት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ።

ለበዓሉ 15 ለእንግዳ ማረፊያነት የሚያገለግሉ አዳዲስ ሆቴሎችና ሎጆች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ አስቀድሞ የነበሩ ከ20 በላይ ሆቴሎች እድሳት ተደርጎላቸው በአዲስ መልክ ስራ እንደጀመሩም ገልፀዋል።

በበዓሉ ወቅት የማረፊያ ችግር እንደማይገጥም የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልን ጨምሮ ሌሎች ከ1ሺ 500 በላይ አልጋዎች መዘጋጀታቸውን አቶ አህመድ ተናግረዋል።

''ማረፊያዎቹና ሆቴሎቹ የክልሉን ሞቃታማነት ሊቋቋሙ የሚችሉ ተደርገው የተሰሩና ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው በመሆኑ ሙቀቱ እንግዶችን አያሳስባቸውም'' ብለዋል።

ተጨማሪ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች፣ የዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ፣ የክልሉን ባህላዊ አሰራር የተከተሉ የእንግዳ ማረፊያዎችና በዓሉን ለማክበር የሚያስችል የስታዲየም ግንባታ መካሔዱን ተናግረዋል።

ለዚሁ በዓል የተገነባውና ሰላሳ አምስት ሺ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየም ተጠናቆ ሳር የበቀለበት ሲሆን፤ የመግቢያ በሮችና የጣሪያ ስራ ብቻ እንደሚቀረው ነው ያስረዱት።

የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ወክለው በዓሉን ለመታደም ለሚመጡ ልዑካን በሰመራ ከተማ 480  የአፋር ባህላዊ ቤት መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በበዓሉ የአየር ንብረት "መለዋወጥን ለመቋቋም እንዲቻልና  የመስተንግዶ ችግር እንዳይኖር እየተሰራም ነው" ብለዋል።

በክልሉ የጋቢረስ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን አሊ አቀባበል የተደረገላቸው የጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ቡድን በክልሉ በነበራቸው የአራት ቀናት ጉብኝት አዋሽ ፓርክን ጨምሮ የአዋሽ ወረዳ የመስኖ እርሻዎችን ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም  በዱብቲ ወረዳ የአላሎባድ ፍልውሃ፣ የጭቃ እሳተ ገሞራ፣ የዱብቲ ወረዳ ዳበልና ሃልበሪ ቀበሌ የመስኖ እርሻ፣ የሰመራ ከተማ  የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማረፊያ ጎጆዎች፣ የእንግዳ ማረፊያ ሎጅዎች፣ የአየር ማረፊያውንና ስታዲየምን ተዟዙረው ተመልክተዋል።

ጎብኝዎቹ በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት በአፋር ገና ያልተሰራበት ብዙ የቱሪዝም ሃብት እንዳለና የክልሉ መንግስትም መዳረሻዎቹን በማስተዋወቅ አካባቢውን የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መስራት እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በዓሉን ለማስተናገድ አፋር በጥሩ አቋም ላይ መሆኗን በሌሎች ክልሎች ከነበረው ልምድ በመነሳት ይገልፃል።

የአፋር ክልል የአርብቶ አደርና ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አባሂና ኮባ በበኩለቸው እንደገለጹት፤ ክልሉ እንግዶችን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነው።

የሰው ልጅ መገኛ ወደ ሆነችው  አፋር ያለምንም ስጋት እንዲመጡ ለበዓሉ ታዳሚዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በ2009 ዓ.ም የ11ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ''ህገ መንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ በሀረር ከተማ መከበሩ ይታወሳል።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡ የሚማረርባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳለበት የከተማዋ ምክር ቤት አስታወቀ።

 አስተዳደሩ በበኩሉ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት "የተለየ የመልካም አስተዳደር እቅድ አውጥቼ እየሰራሁ ነው"ብሏል።

 ምክር ቤቱ  አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።

 በተጨማሪም የአዲስ አበባ ምክር ቤት በከተማ አስተዳደሩ የቀረበውን የ2010 በጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር እቅድ ገምግሞ አጽድቋል።

 በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ዶክተር ታቦር ገብረመድሀን  እንደተናገሩት፤ በመዲናዋ ነዋሪውን የሚያማርሩ የመልካም አስተዳደር፤ የኪራይ ሰብሳቢነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በየተቋማቱ፣ በአመራሩና በፈጻሚው አካላት ይስተዋላሉ።

 በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ተጨባጭ እቅድ አውጥቶ የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ እና ችግሮችን መፍታት እንደሚገባው አንስተዋል።

 በመዲናዋ የመብራትኤሌትሪክ ሃይልና የውሃ መቆራረጥ፣ የመንገድና የትራንስፖርት እጦት፣ ህገ ወጥ ንግድ፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለመቻል ነዋሪውን ያማረሩ ችግሮች በመሆናቸው በእቅዱ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

 ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ በሚያስችል ሁኔታ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚገባ ነው አባላቱም ያሳሰቡት።

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው  ህብረተሰቡ የተማረረባቸው የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከተማ ድረስ ተለይተዋል።

 ህብረተሰቡ የተማረረባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ "የአጭር፤ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ" ብሎ በመለየት በ2010  በቁርጠኝነት ለመፍታት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

 በተጨማሪም የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በስፋት የሚታይባቸውን የመንግስት ተቋማት በመለየት "ችግሮች መቼ እና እንዴት መፈታት እንደሚገባቸው የጊዜ ገደብ ተቀምጧል" ብለዋል።

 ይህንንም የሚከታተል በከንቲባው የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በየወሩ አፈጻጸሙ እየተገመገመ ተጠያቂ የሚደረግበት ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

 ችግር ያለባቸው ተቋማት ላይም የማያዳግም  እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስረአት ስርዓት መዘርጋቱን ነው ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ የተናገሩት።

 ምክር ቤቱ ከተማ አስተዳደሩ ያቀረበው የመልካም አስተዳደር እቅድ ላይ ውይይት አድርጎ አጽድቋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2010 በመንገድ ይዞታ ውስጥ ልዩ ልዩ ተግባራትን በሚያከናውኑ አካላት ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ ንብረቶችን የማንሳትና አካባቢውን ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ክፍት የማድረግ ስራ እንደሚያከናውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

 በመንገዶች ላይ የግንባታ ግብዓትና ተረፈ ምርት ማከማቸት፣ የመንገድ ላይ አጥር ማጠር፣ የጎሚስታ አገልግሎት መስጠትና የጋራዥ ስራ መስራት፣ መንገድን ያለ ፈቃድ መቁረጥና ህገ ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ ከልዩ ልዩ ተግባራቱ የሚጠቀሱ ናቸው።

 በንግድ ቤት በሮች ላይ በሚገኝ የእግረኛ መንገድ ላይ ዕቃ ማስቀመጥና የተሽከርካር እጥበት እንዲሁም መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ማቆም በከተማዋ ሚስተዋሉ ህገ ወጥ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።

 ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በመንገድ ይዞታ ውስጥ የተጠቀሱትን ተግባራት በሚያከናውኑ አካላት ላይ ከፖሊስና ከደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤትጋር በመተባበር ንብረቶችን የማንሳትና አካባቢዎቹን ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ክፍት የማድረግ ስራ ከህዳር 2  2010  ጀምሮ ይከናወናል።

 ንብረቶችን የማንሳትና አካባቢዎቹን ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ክፍት የማድረግ ስራ በመዲናዋ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚከናወን ተጠቅሷል።

 በከተማዋ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

 ስለሆነም ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ይህንን አውቀው ከተጠቀሰው ቀን በፊት በመንገድ ይዞታ ላይ የተከማቹ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ባለስልጣኑ አሳስቧል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን