አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 08 November 2017

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2010 የኖርዌይ መንግስት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያደርገውን የገንዘብና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚቀጥል የአገሪቱ ልዑል ሃኮን ማግነስ ገለጹ።

የኖርዌዩ ልዑል ሃኮን ማግነስ፣ልዕልት ሜቲ ማሪት እና ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በሰብአዊ መብት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሸነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚዓብሄር ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት  ኖርዌይና ኢትዮጵያ የብዙ አመታት ግንኙነት አላቸው።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የላቀ ደረጃ ለማድረስ  ኖርዌይ ስለ ኢትዮጵያ የልማቱ ፣ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ሀላፊነት ከመወጣት አኳያ እየሰራ ያለው ስራ፣ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙትን ግጭቶች ፣ ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት አንድምታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በልማትና ሰብዓዊ መብት ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምን እንደሆኑ፣በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ላይ ኮሚሽኑ ምን እንደሚሰራ፣በማረሚያ ቤቶች ጨምሮ የክትትል ሪፖርትና የምርመራ ስራዎች ምን ደረጃ እንዳለ ተወያይተናል ብለዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ስለግጭቶቹ የሚቀርቡ ዘገባዎች የተጋነኑ መሆናቸውንና ኮሚሽኑ ያረጋገጠው ሪፖርት ላይ ተወያይተን መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የኖርዌይ መንግስትም በኮሚሽኑ የተጣራው ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለህዝብ መቅረቡ መልካም መሆኑን እንደገለፁ ተናግረዋል።

ኖርዌይ የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን  በገንዘብና በተቋማዊ አቅም ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀውልናል ብለዋል።

የኖርዌይ መንግስት በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አማካኝነት በዲሞክራሲ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ የሚያደርገው ድጋፍ ከአራት አመት በፊት መቋረጡን ዋና ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል። ።

ኖርዌይ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1992 በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ ከ12ቱ የኖርዌይ የልማት ትብብር አገራት አንዷ ሆናለች።   

Published in ፖለቲካ

ሰመራ ጥቅምት 29/2010 በሰመራ ከተማ የዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል የሚሰጠውን አገልግሎት ከጊዜ ወደጊዜ እያሻሻለ መምጣቱን የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ተናገሩ።    

ከአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ጋሊሜዳ ቀበሌ የመጡት ወይዘሮ አስያ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት ከጥቂት ዓመታት በፊት በሆስፒታሉ ተመርምሮ  የሚፈለገውን መድኃኒት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር።

በእዚህ ምክንያት ከግል መድኃኒት ቤቶች በመግዛት ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዓመታት በፊት የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ከመስተንግዶ ጀምሮ ክፍተት ይስተዋልባቸው እንደነበር ገልጸው ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሆስፒታሉ እነዚህን ችግሮቹን በመፍታት የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ሆስፒታሉ ለነፍሰጡሮች በሚሰጠው የአምቡላንስ አገልግሎት ላይ የሚስተዋልበትን ክፍተት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከሎግያ ከተማ የመጡት አቶ አሊ ሁመድ የተባሉ ሌላው ተገልጋይ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከሁለት ዓመት በፊት በሆስፒታሉ በቂ የሕክምና መሳሪያዎች ባለመኖራቸው ለተጨማሪ ምርመራ ወደሌላ የጤና ተቋማት መሄድ ግድ ይል ነበር።

ሆስፒታሉ ከጊዜ ወደጊዜ ይህን ችግር እየፈታ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ጥሩ መስተንግዶና የአስተኝቶ ሕክምና አገልግሎት ሳይቀር እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ቀደም ሲል ኃኪሞቹ በጊዜ ስለማይገቡ በተለይ ለመውለድ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ነፍሰጡር እናቶች ረጅም ዓአት ይሰቃዩ ነበር "ያሉት ደግሞ ከዱብቲ ጉርሙዳሌ ቀበሌ የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ አብዱ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ለወሊድ የሚመጡ እናቶች በአልትራሳውንድ የተደገፈ ፈጣን ምርመራ ተደርጎላቸው በሰላም እየወለዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይሁንና የአምቡላንስ አገልግሎት ጥያቄ ሲቀርብ ብዙ ግዜ "መኪና የለም፤ ወደ ሌላ ቦታ ሂዷል" የሚል መልስ እየተሰጠ በመሆኑ በእዚህ በኩል ሆስፒታሉ ቅሬታውን እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ማሄ አሊ በበኩላቸው እንደተናገሩት በሆስፒታሉ ቀደም ሲል በቂ የሰው ኃይልና የሕክምና መሳሪያዎች ባለመኖሩ ለሕብረተሰቡ በቂ ሕክምና ሲሰጥ አልነበረም።

በእዚህም ሕብረተሰቡ ወደደሴና መቀሌ እንዲሁም ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመሄድ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ሲዳረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፣ ሆስፒታሉ በ2004 ዓ.ም የሆስፒታሎች ማሻሻያ ሪፎርም በመተግበር በሰውኃይል፣ በግብአትና በሕክምና መሳሪያዎች በማደረጃት የተሻለ አገልገሎት ለመስጠት እየሰራ ይገኛል።

በተለይም ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ሕብረተሰቡ የተለያዩ ስፒሻሊስት ኃኪሞችን በከፍተኛ ደመወዝ በመቅጠርና በሕክምናና በቤተሙከራ መሳሪያዎች በተሸለ ሁኔታ በማደራጀት ሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከጤና ጥበቃ ሚነስቴር በተገኘ የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ስድስት አልጋ ያለው ከፍተኛ ሕሙማን መከታተያ ክፍል በማዳራጀት ከጥቅምት ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

የአምቡላንስ አገልግሎቱ ክፍተት እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ማሄ፣ ተሽከርካሪዎች ውስን መሆናቸው ለሕብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር መነጋገር  ጥረት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን ነው።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2010 ኢትዮጵያና አዘርባጃን በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ።

 ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የአዘርባጃን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤልማር ማማድያሮቭን በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

 ሁለቱ አገሮች በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ በሚያስችላቸው ሁኔታዎች ዙሪያ መነጋገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮምዩኒኬሽንና የፕሮቶኮል ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።

 አገሮቹ በንግድና ኢንቨስትመንት ዝቅተኛ ግንኙነት እንዳላቸው በመገንዘብ አገሮቹ በዘርፋ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ጠንክረው ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

 በትምህርቱ ዘርፍ ያላቸውን የጠነከረ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንቱም ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግላጻቸውን ነው አቶ አሸብር ያስረዱት።

 ከዚህ በፊት የአዘርባጃን ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ጥናት ለማድረግ መጥተው እንደነበር አስታውሰዋል።

 በትምህርት ዘርፍ ብዙ ኢትዮጵያውያን በአዘርባጃን ርዕሰ መዲና ባኩ እንደተማሩና በቀጣይም በምህንድስና፣ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች መማር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን አብራርተዋል።

 አዘርባጃን በባህልና ቱሪዝም ያላትን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መምከራቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

 የአዘርባጃን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤልማር ማማድያሮቭ በበኩላቸው፤ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ የአዘርባጃን ባለሀብቶች በማዕድን ዘርፍ እንዲሰማሩ ሀሳብ እንዳነሱላቸው ነው የተናገሩት።

 አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ በየአገራቱ ባሉ አማራጮች ዙሪያ የሚመክር የቢዝነስ ፎረም ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ  መምከራቸውን ተናግረዋል።

 በአጠቃላይ ሁለቱ አገሮች በዘርፈ ብዙ መስኮች ትብብራቸውን በማጠናከር ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ለመስራት እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል።

 ኢትዮጵያ በአዘርባጃን ኤምባሲዋን መክፈት በምትችልበት ሁኔታ መነጋገራቸውና ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነትታቸውን እንደሚያሳድገው ለፕሬዝዳንቱ እንደገለጹላቸውም ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

 "ኢትዮጵያ በቀጣናው በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉና መሪ ከሆኑ አገሮች አንዷና የምስራቅ አፍሪካ ዋነኛ ማዕከል ናት። አዘርባጃንም በምስራቅ አፍሪካ ለምታደርጋቸው ስራዎች አገሪቷን ዋነኛ መዳረሻ ታደርጋለች"  ብለዋል ሚኒስትሩ።

 ኢትዮጵያና አዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1992 ሲሆን፤ አዘርባጃን በአዲስ አበባ ከሶስት ዓመት በፊት ኤምባሲዋን መክፈቷ የሚታወስ ነው።

 አዘርባጃን በባህል ኢንዱስትሪ፣ በዘመናዊ ግብርና እና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የዳበረ ልምድ ያላት አገር መሆኗን መረጃዎች ያስረዳሉ።

 አገሪቷ በእስያ ፓሲፊክ ካሉ 42 የአካባቢው አገሮች መካከል 165 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ ሀብት ባለቤት በመሆን 16ኛዋ ባለጸጋ አገር ናት።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2010 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የእቅድ ዝግጅትና አፈጻጸም ሪፖርት አቀራረብን ለማስተካከል የሚያስችል አዲስ ደንብ ጸድቆ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን ብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

አዲሱ አሰራር በሪፖርት አላላክ የጊዜ ሰሌዳና ይዘት ላይ ለውጥ የሚያመጣና ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።

ተቋሙ በ2010 ዓ.ም ሊሰራቸው ያቀዳቸውን ተግባራት በተወካዮች ምክር ቤት ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚህ ወቅት የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት፤ በፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ወጥ የሆነ የእቅድ አዘገጃጀትና የአፈጻጸም ሪፖርት አላላክ ክፍተት ይስተዋላል።

ይህን ስርዓት መዘርጋት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ተቋማት ወጥ የሆነ የእቅድና ሪፖርት አላላክ ስርዓት ስለማይከተሉ  መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲሱ አሰራር ዘመናዊና ወጥ የሆነ አካሄድን ስለሚከተል ተቋማቱ ላይ የሚታዩ የእቅድና ሪፖርት አላላክ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚችል ነው ያነሱት።

ከዚህ በፊት ተቋማት ባቀዱት ልክ ያለመፈጸማቸውና ወጥ የሆነ የሪፖርት አላላክ ስርዓት ያለመከተላቸው አዲሰ አሰራር ለመተግበር እንዳስገደደ ተናግረዋል።

አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ የአደረጃጀት ጥናትና የሪፖርት ማንዋሎችን የማዘጋጀት ስራ እንዲሁም ሌሎች የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ በቅርብ "በተመረጡ ተቋማት ላይ ሙከራ ይደረጋል" ነው ያሉት።

ይሄን ማስፈጸም የሚያስችል አዲስ ደንብ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተግባራዊ የሚደረግው አዲሱ የእቅድና የሪፖርት አላላክ ስርዓት ተጠያቂነትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመው፤ "ይህንኑ ተግባራዊ የማያደርጉ ተቋማትን ተጠያቂ የሚያደርግ ስርዓት አብሮ ይዘረጋል" ብለዋል።

የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ታደሰ በበኩላቸው፤ በተቋማት መካከል ወጥ የሆነ የሪፖርት አላላክ ስርዓት አለመኖር በርካታ ተቋማት ላይ ክፍተት ሲፈጥር መቆየቱን አንስተዋል።

ይህን ጉዳይ ለማስቀረት ኮሚሽኑ ዘግይቶም ቢሆን አዲስ አሰራር መዘርጋቱ በጥሩ ጎኑ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ገነት አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ

 አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ ከተካሔደው ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ በአዲስ አበባ ሰባተኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ በተካሔደው ጉባዔ የህብረተሰቡን የልማት፣ የሰላም፣ ጸጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

 በኮንፈረንሱ ማጠናቀቂያ  ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ስራዎችን ማከናወን ይቀራል።

 የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን የመለየትና የመፍታት፣ የአመራር አባላት አቅም ማነስ ችግሮችን የመለየት፣ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እና ድክመቶችን መፍታት የሚሉት ጉዳዮች በኮንፈረንሱ ውይይት የተደረገባቸው ናቸው።

 ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ በልማት ምክንያት የተነሱ አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተወስቷል።

 ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ድርጅቱ በማዕከል ያስቀመጠውን አቅጣጫ በተመለከተ በሁሉም ደረጃ ባሉ የአመራር አባላት   ውይይት መደረጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በኦሮሚያ ክልል በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ቢቀጥል ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

 የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው ለማስቀጠል አባላቱ የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።

 በከተማዋ ለልማት ተነሺዎች የሚከፈለው ካሳና ተነሺዎችን ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ስራ በቂ አይደለም ተብሏል።

 በየደረጃው ካለው የድርጅቱ አመራር አባላት የአንዳንዱ የመፈጸም ብቃት አነስተኛ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባም ተጠቅሷል።

 ከአቃቂ ክፍለ ከተማ ጉባኤውን የታደመችው ወይዘሪት ወይንሸት ሽመልስ "የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በልማት የሚነሱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብላለች።

 አርሶ አደሩ በሚከፍለው ካሳ እየተጠቀመ ባለመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁማለች።

 ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመጣው አቶ ዘሪሁን ሁንዱማ በበኩሉ፤ የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ቋንቋውን ለማሳደግ እንዲችል "በድርጅቱ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው" ብሏል።

 ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እያደረገ ያለው እርምጃ አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንሚገባ ተናግሯል።

 የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሻፊ ኡስማን፤ የህዝቡን ተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የበለጠ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች እንዲቀጥሉ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ጠቁሟል።

 የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የኦህዴድ/ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ድሪባ ኩማ እንዳሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ እየታዩ ያሉት ለውጦች አበረታች ናቸው።

 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የመለየትና ተገቢውን ካሳ የመክፈልና ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ "የመልካም አሰተዳደር ክፍተቶችን የመፍታት ስራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል።

 አርሶ አደሩ ከከተማዋ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የአርሶ አደሩን ልጆች በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመሩ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል።

 ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ በልማት ምክንያት የሚነሱ አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 የተጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ ለማሳካት መላው የከተማ ነዋሪ ከአስተዳሩር ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 29/2010 የውጭ አገር ጉዲፈቻን የሚከለክል ሕግ መውጣቱ አግባብ አለመሆኑን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ገለጹ።

 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቤተሰብ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በተለይም በሕፃናት የውጭ አገር ጉዲፈቻ የሚመለከተው አንቀጽ ላይ ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከበጎ አድራጎት ፣ማኅበራትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

 የቤተሰብ ሕጉን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ፣ በአደራ ቤተሰብና በመልሶ ማቀላቀልና ማዋሐድ ብቻ እንዲያድጉ በማድረግ የውጭ አገር ጉዲፈቻን የሚመለከቱ አንቀጾች እንዲሰረዙ ተቀምጧል።

 በውይይቱ ላይ በሕፃናት ማሳደጊያ ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንደገለጹት፤ በቅድሚያ በውጭ አገር ጉዲፈቻ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አሰራሮች መተግበር ይኖርባቸዋል።

 በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ላይ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም፤ በአገሪቷ እየጨመረ ከመጣው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ሕፃናት ቁጥር አንጻር ግን ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

 በተለይም የአካል ጉዳት፣ የአዕምሮና ሌሎች ሕመም ላለባቸው ሕፃናትን ማሳደግ የሚችሉ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻና የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት እጥረት መኖሩ ተጠቅሷል።

 በነባሩ አዋጅ 213/1992 መሠረት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት የሚደገፉበት ሁኔታና የወላጅ ፍቅር እንዲያገኙ ማድረግ በረቂቁ የተካተተ ሲሆን፤ የውጭ አገር ጉዲፈቻ የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

 ሆኖም ግን በማሻሻያ አዋጁ ይህንን አማራጭ መሰረዝ በተለይም የአዕምሮ ወይም የአካል ጉዳት ላለበት ሕፃን "ፍትሃዊ አይደለም" ተብሏል።

 በአሁኑ ወቅት  የውጭ አገር ጉዲፈቻ በመቋረጡም በሕመምና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ላሉ ሕፃናት እየደረሰባቸው ላለው ጉዳት ተጠያቂው ማነው? በቀጣይስ ሕፃናቱ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ማን ይጠየቃል? የሚል ሐሳብ ተነስቷል።

 በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ለሚያድጉ ሕፃናት በመልካም አስተዳደግ ስለማደጋቸው ማረጋገጫው ምንድን ነው? እና ሌሎች ጥያቄዎችም በውይይቱ ላይ የተነሱ ተጨማሪ ጥያቄዎች ናቸው።

 ሕፃናትን ወደ ውጭ አገር በጉዲፈቻነት በመላክ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የሚያገኙ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ፣ በውጭ አገር ችግር ያጋጠማቸውን ሕፃናት ጉዳይ በቅርብ መከታተልና ሌሎች አማራጮችን መከተል በመፍትሔነት ተነስቷል።

 በሚኒስቴሩ የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተግይበሉ እንዳሉት፤ በቤተሰብ አዋጁ ላይ ሕፃናትን በውጭ አገር ጉዲፈቻ ማሳደግ የመጨረሻው አማራጭ ቢቀመጥም በስፋት እየተሰራ ያለው ግን እንደ አንደኛ አማራጭ ተወስዶ ነው።

 በመሆኑም ከአገሪቱ በጉዲፈቻ የሚወጡ ሕፃናት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ  ነው ማሻሻያ ያስፈለገው ብለዋል።

 የውጭ አገር ጉዲፈቻ ሕፃናት ላይ የማንነት ጥያቄና ውስብስብ ችግሮችን በመፍጠሩና በጉዲፈቻ ላይ የሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እያገኙ መሆኑንም አንስተዋል።

 የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፤ በጉዲፈቻ ሳቢያ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ የሕፃናት ቁጥር እየጨመረ ለመምጣቱ የመንግሥት መዋቅር አካላትም ተሳትፎ በመኖሩ አደረጃጀቱን ማስተካከል እንደሚገባ አንስተዋል።

 አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ሕመም ላይ ያሉ ሕፃናትን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ለማሳደግ የሚያስችል አቅም አለመፈጠሩ ተነስቷል።

 የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ "በውጭ አገር ጉዲፈቻ አንቀጹ ላይ ክፍተቶች ካሉ ማሻሻል እንጂ መሰረዝ መፍትሄ አይደለም" ብለዋል።

 በማሻሻያ አዋጁ ላይ የሚደረገው ውይይት የሕግ ባለሙያዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መንገድ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ጥቅምት 29/2010 ትግራይ ባለው የመስኖ ልማት የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የዘርፉ ምርት ገበያ ተኮር ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ ለኢዜአ እንዳሉት ቀደም ሲል በክልሉ ይካሄድ የነበረው የመስኖ ልማት ለየት ባለ አዲስ መንገድ  እንዲመራ እየተደረገ ነው።

በተመሳሳይ አካባቢ የሚገኙ የመስኖ ልማት ቦታዎችን መሰረት ያደረገው አዲሱ አሰራር አርሶአደሮች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርትን ወደ ገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ ያሉትን ሂደቶች በጋራ የሚወያዩበትና የሚወሱንበት ነው።

አዲሱ አሰራር  የመስኖ ልማት የሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ አርሶአደሮች የተለያዩ አዝርእቶች ስለሚያመርቱ የገበያ ችግር እንደማያጋጥማቸው ዶክተሩ አትንኩት ጠቁመዋል።

አርሶአደሮቹ በአንድ ላይ እየተወያዩ ስለሚሰሩ የተሻለ ምርት ለማግኘትና የውሃ ብክነት እንዳይኖር የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙዋቸውም አስቀድመው መፍታት ያስችላቸዋል ነው ያሉት። 

በአሁኑ ወቅት በክልል ደረጃ  በምስራቃዊና ደቡባዊ ዞኖች ሁለት የመስኖ አውታሮች በሙከራ ደረጃ ተመርጠው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመስኖ አውታሮቹ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ከገበያ ትስስር ድረስ የሚኖሩት ሂደቶችና ምርታማነት ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ባለሙያዎች ትምህርት የሚቀስሙበትና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ሞዴል በመሆን ያገለግላሉ፡፡

ከየወረዳዎችና  ከየቀበሌዎቹ ደግሞ አንድ የመስኖ ልማት የሚካሄድበት ቦታን  በመለየት ባለሙያዎች  እንዲማሩባቸውና ወደ አርሶአደሮቹ ለማስፋት የተግባር ስራዎች መጀመራቸውን ኃላፊው አመልክተዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በስራ እድል ፈጠራ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

 ስምምነቱን ከከተማይቱ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፣ ከሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮዎችና ከሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች ጋር ነው ያደረገው።

 የስምምነት ሰነዱ ወጣቶችንና ሴቶችን በስራ ባህል፣ በመደራጀት ጠቀሜታ፣ በብድር አወሳሰድና አመላለስ፣ በአመለካከት ቀረጻ ዙሪያ  ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡

 የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ከስምምነቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በከተማዋ የሚገኙ ስራ ፈላጊዎች በፍላጎታቸውና ክህሎታቸው እንዲሰማሩ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 ይሁን እንጂ "በስራ ፈላጊዎች ላይ የሚስተዋለው ስራ የማማረጥ ችግር ሙሉ በሙሉ ያልተቃለለና ቀጣይ ሥራዎችን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

 ስራ ፈላጊዎች በአመለካከት፣ በመለወጥና በክህሎት ዳብረው ወደ ስራ የሚገቡበትን አማራጭ በመፍጠር "የአገሪቷን ህዳሴ ለማስቀጠል የጋራ ውል ስምምነት ሰነዱ ጉልህ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል።

 ይህም ድክመቶችን "የምናቃልለበትና ጥንካሬዎችን አጎልብተን የምንሄድበት እንዲሆን የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ሲሉ የቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።

 የዜጎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ለማፋጠን ስራ ፈላጊ ዜጎች በተለይም ወጣቶች ከፍተኛ  የስራ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና የዳበረ የስራ ባህል ሊኖራቸው ይገባል።

 በዚሁ ወቅት የተገኙ ባለድርሻ አካላት  እንደሚሉት፤ ፍትሃዊ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግርና የሼዶች መሰረተ ልማት ያለመሟላት በስራ እድል ፈጠራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።

 በመሆኑም "ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ የስራ እድሎችን በማመቻቸት የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል" ብለዋል።

 በዚህም እድገት ተኮርና እሴት ፈጣሪ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የወጣቱን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ለ161 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙን ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2010 በአፍሪካ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ላይ የሚመክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው ስብሰባው በአፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከህዳር 5 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በኮሚሽኑ አዳራሽ ይካሄዳል።

በጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መሪዎች፣ተወካዮች፣ገበሬዎች፣የግል ተቋማት፣ምሁራን እና ሲቪል ማህበራት የሚሳተፉ ሲሆን በዘርፉ የአገራት አፈጻጸም ሪፖርትና ጥናት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

ጉባኤው "የምንፈልጋት አፍሪካን ዕውን ለማድረግ  የወጣቶች የመሬት ባለቤትነትና የማህበራዊ ኢኮኖሚ ሽግግር ሁሉን አቀፍና ሚዛናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን በዕውቀት መምራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል።

የአፍሪካ መሬት ፖሊሲ ማዕከል አስተባባሪ ጆን ካግዋንጃ  እንደገለጹት፣ የስብሰባው ዓላማ  የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ዓመት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ቃል በገባው መሰረት ለወጣቶች  ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው።

የአፍሪካ መሬት የእድገት መሰረትና አንጡራ ሃብት መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው የአፍሪካ መሬት በስርዓት ቢመራና ቢተዳደር "በእርግጠኝነት ድህነትንና ኢፍትሐዊነትን መቀነስ ይቻላል" ብለዋል።

ጉባኤውም በአፍሪካ የመሬት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ሁሉን አሳታፊ ፖሊሲዎች ላይ ከመምከር በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሬት አስተዳደር ሥርዓት የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎችና ግኝቶችን መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይም ውይይት ይደረጋል።

Published in ኢኮኖሚ

ፍቼ ጥቅምት 29/2010 የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር በተሀድሶ የተጀመሩ የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ያልተቆጠበ ጥረት እንደሚያደርጉ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የኦህዴድ አመራሮችና አባላት አስታወቁ፡፡

ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተወጣጡ ስድስት መቶ የሚሆኑ አመራሮችና አባላት በፍቼ ከተማ ሲያካሄዱ የቆየው ድርጅታዊ ኮንፍረንስ ዛሬ አጠናቀዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ማብቂያ ወቅት አስተያየታቸውን ከሰጡት አመራሮች መካከል  አቶ አባቡ ወርዶፋ የአርሶ አደሩንና የከተማ ነዋሪ ሕዝብ ጥያቄ የነበሩት የመንገድ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግሮች በከፊል መፍትሔ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሰራር ብልሹነት የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች ግን ትኩረት ሰጥተው በመስራት የድርኛቸውን ለመወጣት እንደተዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የወጣቶችና የሴቶች የስራ አጥነት ችግሮች ለማቃለል ከሕዝቡ ጋር መሰራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው በክልሉ  ሕዝቦች መካከል የተጀመረው የአንድነት መንፈስ በማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ለአካባቢው ልማት አባላቱና አመራሩ አንድነታቸውን አጠንክረው  ከሕዝብ ጋር ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙልጌታ ታዬ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት ለወጣቶች  በሰጠው ትኩረት ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው  ኘሮጀክቶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው በህዝቦች ሕዝብ መካከል የተፈጠረው የአንድነት ስሜት በመጠቀም ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲጎብት እንደ አመራር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የኩዩ ወረዳ የአስተዳደር ክፍል ኃላፊ አቶ ንጉሴ አለሙ  በበኩላቸው ሁለገብ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የዞኑ ነዋሪዎች ኑሮን ለማሻሻል አቅማቸውን አሟጠው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ለልማት፣ ለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር መስፈን የድርሻቸውን ሚና በመጫወት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል፡፡

የፍቼ ከተማ አስተዳደር  አባል አቶ አየለ ደጀኔ ኦህዴድ ህዝባዊ አመለካከት በመያዝ የህዝቡን  የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች  ለመመለስ የሚያደረገውን ጥረት ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ለሶስት ቀናት  የተካሄደውን ኮንፍረንስ የመሩት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ እሸቱ ደሴ  በበኩላቸው የኦህዴድ አመራሩና አባላቱ ባለፉት ዓመታት ለእድገት  እንዳደረጉት ሁሉ ወደፊትም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ይሄውመ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ  በተሻለ እውቀት ፣ ክህሎትና አመለካከት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በተሀድሶ የተለዩ ችግሮች በአሁኑ ወቅት በከፊል መፍትሄ እያገኙ መሆኑን ጠቁመው  ብልሹ አሰራር በማስተካከል  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን   አመራሩ  ከህዝቡ ጋር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸዉም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ እሸቱ እንዳመለከቱት በተለይ የአርሶ አደሩን ሕይወት በሚለውጥ ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፤ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም  ነዋሪዎች ድህነትን ለማሸነፍ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ እጅጉ የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩልነት የሚታዩበትን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የልማት በማስቀጠል እድገትን ለማፋጠን የሚደረገውን የህዝብና የመንግስት ጥረት  ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርጅቱ አባላትና  አመራሮች  በቁርጠኝነትን መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ባለ አስር  ነጥብ  የአቋም መግለጫ በማውጣት ማምሻውን አጠናቀዋል፡፡

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን