አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 07 November 2017

ጥቅምት 28/2010 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ሰሜን ኮሪያ በአስቸኳይ  የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራሟን  ወደ  ጠረጴዛ ውይይት ማምጣት እንደለባት  አሳሰቡ፡፡

ፕሬዝዳንቱ  በኤዥያ አህጉር  ጉብኝታቸው ሁለተኛዋ   መዳረሻ  ባደረጓት   የሲኦል ከተማ   ከደቡብ ኮሪያ  አቻቸው  ሞን ሊን ዣን ጋር  ጋዜጣዊ  መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መግለጫው ፒዮንግያንግ  ላይ " ስጋት እና ቁጣ"   ፈጥሯል፡፡

ፕሬዝዳንቱ  በአምስቱ  የኤዥያ ሀገራት ጉብኝት  ፕሮግራማቸው ዉስጥ  የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ  ጉዳይ  ዋነኛው አጀንዳ ነው ተብሏል፡፡

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ   ሰሜን  ኮሪያ  የኒኩሌር ፕሮግራሟን ማቆም እንዳለባት ተናግረዋል፡፡

"ደቡብ ኮሪያ ወደ ጠረጴዛው ውይይት መምጣት  እና ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ለደቡብ ኮሪያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ  መልካም   ነው" ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን አሜሪካ  በአከባቢው ወሳኝና አስተማማኝ  የሆነ  የታጠቀ መከላከያ ቢኖራትም " በሰይጣን ላይ" እንጂ በሰሜን ኮሪያ ላይ መጠቀም የለብንም በማለት ነው የገለጹት፡፡

 ቢቢሲ እንደዘገበው ሁለቱ መሪዎችም  ቻይናና ራሺያ  በፒዮንግያንግ ላይ ጫና እንዲያሳድሩም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ሽሬና መቀሌ ጥቅምት28/2010 በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ተሰማርተው ለሚያከናውኑት ስራ ያጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት በመቃለሉ ውጤታማ ለመሆን እንደረዳቸው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞንና መቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

 ብድር ወስደው ሥራ ከጀመሩ የትግራይ ሰሜን ምእራብ ዞን ወጣቶች መካከል በታህታይ ቆራሮ ወረዳ በወተት ኃብት ልማት የተሰማራው ወጣት ገብረሥላሴ አማሃ እንደገለጸው እየሰራ ላለው የወተት ላም እርባታ የ20 ሺህ ብር ብድር ማግኘት ችሏል።

 ይሔም ስራውን የበለጠ እንዲያሻሽለውና እንዲያስፋፋው እያገዘው መሆኑን ገልጾ በቀጣይም ከግብርና ባለሙያዎች ተጨማሪ ምክርና ሙያዊ እገዛም እንደሚሻ ተናግሯል።

 የሽሬ እንዳስለሴ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ፍሬወይኒ ተሰማ በበኩሏ ቀደም ሲል ምንም ስራ ስላልነበራት ቤተሰብ ለማስቸገር ተገዳ ነበር ።

 ከተዘዋዋሪ ብድር በተሰጣት ገንዘብ ተጠቅማ መስራት የጀመረችው የሴቶች የውበት ሳሎን አገልግሎት አሁን ላይ እራሷን እንድትችል እያደረጋት መሆኑን ተናግራለች።

 የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብረሥላሴ ታረቀኝ እንደገለጹት በዞኑ ስምንት ወረዳዎች የሚገኙ ከ10 ሽህ 550 በላይ ወጣቶች ከ234 ሚሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር ተጠቃሚ ሆነዋል።

 ከዚህ ውስጥ አራት ሺህ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ በኮንስትራክሽን በማኑፋክቹሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎትና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ለሚያደርጉት ተሳትፎ በነፍስወከፍ ከ20ሺህ ብር በላይ ብድር እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።

 በተመሳሳይም በመቀሌ ከተማ በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ወጣት ለተብርሃን መረሳ እንደገለጸችው ከጓደኞቿ ጋር በተሰጣቸው የዶሮ እርባታ ስልጠና ተጠቅመው ለመስራት የ200ሺህ ብር ብድር አግኝተዋል።

 ገንዘቡ የመስራት አቅማቸው እንዳሳደገላቸው ገልጻ እየተስፋፋ ለመጣው ስራቸው ተጨማሪ በታ እንዲሰጣቸው ጠይቀው መልስ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም አስረድታለች።

 በንብ ማነብ ስራ በግሏ የተማራችው ወጣት ተክኤ አብርሃ በበኩሏ፣30ሺህ ብር ብድር በመውሰድ በአራት ቀፎዎች ስራዋን መጀመሯን ተናግራለች።

 "ወጣቶች አላማቸውን ለማሳካት ሌሊትና ቀን ለፍተው የስራቸውን ውጤት ማየት አለባቸው እንጂ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚያሰቡ ከሆነ መንገድ ላይ ሊቀሩ ይችላሉ" ብላለች።  

 የከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትና የምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ልዕልቲ ፍሳሃ እንደገለጹት ለወጣቶቹ ከ32 ሚልዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ብድር መሰጠቱንና

ከ10 ሺህ የሚበልጡት ወጣቶችም በሩብ ዓመቱ ወደ ስራ ገብተዋል።

 "በማህበር ተደራጅተውና በግል ለመስራት ለሚፈልጉት ለእያንዳንዳቸው ከ30ሺህ ብር እስከ 200ሺህ ብር ድረስ ተሰጥቷቸዋል" ያሉት ወይዘሮ ልዕልቲ የገበያ ትስስርና 32 ሄክታር የመሰሪያ ቦታ እንደተመቻቸላቸው አስረድተዋል።

 በትግራይ ክልል ከ3 መቶ 77 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ከተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በተጨማሪ የደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም በትኩረት እየሰራ ይገኛል ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ጥቅምት 28/2010 በአገሪቱ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት በከተሞች የሚኖሩ 8 ሚሊዮን ዜጎችን በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በአካባቢና የግል ንፅህና አጠባበቅ ተጠቀሚ የሚያደርግ የ445 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ የሁለት ቀን አውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በወቅቱ እንደገለፁት ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የተመደበው ገንዘብ ከዓለም ባንክ በረዥም ጊዜ ብድርና እርዳታ የተገኘ ነው ።

ፕሮጀክቱ አዲስ አበባንና በሁሉም ክልሎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ 22 ከተሞችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በተለይ በአዲስ አበባ የሚከናወነው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የአካባቢና የግል ንፅህና አጠባበቅ ስራ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ የከተማው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል" ብለዋል ።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ተጠቃሚ ከሚሆኑት የከተማው ነዋሪዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ልጃገረዶች ናቸው ።

በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች ላይ በሚከናወነው ሥራም 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በአካባቢና በግል ንጽህና አገልግሎት ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን 623 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችም ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ያገኛሉ ተብሏል ።

ፕሮጀክቱ የከተሞችን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻልና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ ውሃ ወለድ በሽታዎችን በመከላከል ጤናማና አምራች ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ አስረድተዋል ።

እንደእርሳቸው ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሚከናወን ሲሆን በሀገሪቱ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ድርሿ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ሚስስ ናታሊያ ማይለኮ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ  በመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች አሳክታለች " ብለዋል ።

ይሁንና አሁንም በከተሞች በአካባቢና በግል ንፅህና አጠባበቅ ያልተቀረፈ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል ።

"በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት የሚከናወነው ፕሮጀክት በዘርፉ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ክፍተቶችን በመሙላት በሀገሪቱ የውሃ ወለድ በሽታዎችና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ይጠቅማታል" ብለዋል ።

ፕሮጀጅቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው አወደ ጥናት ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም ባንክ ተወካዮች፣ የከተሞች ከንቲባዎች፣ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች፣ የክልል ጤና ቢሮዎች ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል ።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ጥቅምት 28/2010 ከውጪ የሚገባውን የእንስሳት መድኃኒት በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል የመድኃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እያስገነባ መሆኑን ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በቢሾፍቱ ከተማ የሚካሄደው የፋብሪካው ግንባታ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን  በ2011 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ ማምረት ይሸጋገራል ተብሏል ።

በኢንስቲትዩቱ የክትባት ጥራት ስራ አስኪያጅ  ዶክተር ቅንነት አጥናፉ ለኢዜአ እንደገለፁት ሀገሪቱ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም በቫይረስና በባክቴሪያ አማካይነት በሚከሰቱ በሽታዎች  ምክንያት ከሀብቱ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አልቻለችም።

"በአሁኑ ወቅት በባክቴሪያ አማካይነት የሚከሰቱ የውስጥ ጥገኛ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  መድኃኒቱን ከውጪ እያሰገባን ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አገልግሎት እየሰጠን ነው" ብለዋል።

እንደ ዶክተር ቅንነት ገለፃ እየተገነባ ያለው ፋብሪካ ከውጪ የሚገባውን መድኃኒት መተካት የሚያስችል ነው፤ በእንክብል መልክ 12 ዓይነት የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን ያመርታል፡፡

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት  የሲቨል ሥራው ሙሉ በመሉ ተጠናቆ የማምረቻ መሳሪያዎች ተከላ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት  ኦፊሰር አቶ አወል አብዱጀባር በበኩላቸው  ፋብሪካው እየተገነባ ያለው ፋብቴክ ቴክኖሎጂ በተሰኘው የህንድ ኩባንያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አወል እንዳሉት መድኃኒቶቹ በሀገር ውስጥ መመረታቸው የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረት ባሻገር የሀገሪቱን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

የመድኃኒት ማቀነባበሪያ ማሽኖች ተከላ በሚቀጥሉት አራት  ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ፋብሪካው ከተያዘለት ጊዜ ገደብ ቀድሞ ማምረት እንዲጀምር ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የፋብሪካው መገንባት ተላላፊ የእንስሳት በሽታዎችንና በባክቴሪያ የሚፈጠሩ እንፌክሽኖችን ለማጥፋት የተያዘውን የ2030 ዓ.ም ግብ ለማሳካት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጎባ /ነቀምቴ ጥቅምት28/2010 በባሌና ምስራቅ ወለጋ የዞንና የወረዳ አመራሮች የተሳተፉበት ሰባተኛው የኦህዴድ ድርጂታዊ ኮንፈረንስ በሮቤና ነቀምቴ ከተሞች እየተካሄደ ነው፡፡

 በሮቤ ትናንት በተጀመረው ኮንፈራንስ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የባሌ ዞን የመስኖ ልማት ባለሥልጣን ኃላፊ  አቶ ሙዘይን አቡበከር እንዳሉት በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት በህዝቡ የተለዩ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ነው፡፡

 በተለይ በዞኑ ግንባታቸው ተጀምሮ የተጓተቱና ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ የማልማት አቅም ያለቸው 7 ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

 ወይዘሮ ሙሲና አብደላ በበኩላቸው  ኮንፈረንሱ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮች በምን ደረጃ እየተፈቱ እንደሆነ ለመለየትና የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ  መልካም  አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ባለፈው ዓመት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ተለይተው ምላሽ ያላገኙ ችግሮች በቀጣይነት እንዲፈቱ አቅጣጫ በማስቀመጥ በኩል ኮንፈረንሱ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ ሌላው  ተሳታፊ አቶ ሰይፉ ኢስማኤል ናቸው ፡፡

 የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ጎንፋ  እንደተናገሩት ደግሞ በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ለህዝቡ የተገባውን ቃል በበለጠ ተግባራዊ ለማድረግና የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ኮንፈራንሱ ትልቅ ግብዓት ይሆናል የሚል እምነት እንዳለቸውም ተናግረዋል፡፡

 የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እንደተናገሩት  የድርጅታዊ ኮንፈረንሱ  ዓላማ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያጋጠሙ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ፡፡

 ትናንት በተጀመረውና ለቀጣይ ሶስት ቀናት በሚቆየው የዞኑ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ላይ ከ800 የሚበልጡ በየደረጃው የሚገኙ የወረዳና የዞን አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ፡፡

 በነቀምቴ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው የምስራቅ ወለጋ ኦህዴድ ድርጅታዊ ኮንፍረንስ ተሳታፊ የጉቶ ጊዳ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ሃላፍ አቶ አለሙ ጉተማ በበኩላቸው መድረኩ በቀጣይ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ አመራሩ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡

 የነቀምቴ መምህራን ኮሌጅ መምህር ታረቀኝ ፍቃዱ  ኮንፍራንሱ ከጥልቅ ተሃድሶው ወዲህ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተከናወኑ ስራዎችና የታዩ ችግሮችን በመፈተሽ ለቀጣይ ስራ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

 የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ኢዳኤ እንደተናገሩት ''ኮንፍረንሱ በጥልቅ ተሃድሶ ተለይተው የተተገበሩ እና ያልተተገበሩ ጉዳዮች የሚለይበት መድረክ ነው'' ብለዋል።

 የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብድሳ ያደታ በበኩላቸው ኮንፍረንሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን ለማስወገድ በመካሄድ ላይ ላለው ጥረት ስኬታማነት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

 የምስራቅ ወለጋ ዞን ኦህዴድ ጽዕፌት ቤት ሃላፍ አቶ አባድር አብዳም ''መድረኩ በስራ ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ ለቀጣይ ስራ ስኬታማነት የመፍትሄ አቅጣጫ የምናስቀምጥበት ነው'' ብለዋል፡፡

 ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ላይ ነቀምቴ ከተማን ጨምሮ በምስራቅ ወለጋ ዞን በየደረጃው የሚገኙ ከ1 ሺህ 100 በላይ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

Published in ፖለቲካ

ፍቼ ጥቅምት 28/2010 በኦሮሞና በአማራ ሕዝቦች መካከል የቆየው አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የህዝብ ለህዝብ ኮንፍረንስ ላይ የተሳተፉ የልኡካን ቡድን አባላት ገለጹ።

 በኮንፈረንሱ ላይ የተሳትፈው የልኡካን ቡድኑ አባላት ዛሬ በፍቼ ከተማ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

 ከልኡካን ቡድኑ አባላት መካከል አባ ገዳ ቱሉ በዳዳ "ኮንፍረንሱ በሁለቱ ሕዝቦች እና አመራሮች መካከል የተጀመረው የሰላምና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የራሱን በጎ አስተዋፅኦ ያበረክታል" ብለዋል።

 በተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሕዝቦችን አንድነትና ፍቅር በማጎልበት የሀገሪቱን የሕዳሴ ጉዞ ለማፋጠን መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

 እንደ አባገዳነታቸው ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ሰላም ፣መቻቻልና አብሮነት በህዝቦች ዘንድ ለማስረጽ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ኮንፍረንሱ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

 ሌላው የኮንፈረንሱ ተሳታፊና የዞኑ ነጋዴዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ መከተ ደባልቄ በበኩላቸው የሰላም ኮንፈረንሱ  የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት ከማጠናከር ባለፈ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

 በተለይም በባህል በቋንቋና በታሪክ  ያላቸውን ዝምድና በማጠናከር ረገድ ስፊ ድርሻ የሚጫወት መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል

 የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ሰለሞን ሁንዴ በበኩላቸው "የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሕዝቦችን አንድነትና ወዳጅነት በማጠናከር በወዳጅነት ስሜት መቀበሉና መሸኘቱ ለሌሎችም ጥሩ አርአያ የሚሆን ነው" ብለዋል።

 በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ በሕዝቦች መካከል ሰላም፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት የባህል እሴትን ለማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

 "ኮንፍረንሱ ለሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በጎ ትርጉም የሚሰጥ ፣ የጋራ ትብብርና አንድነትን ለማጠናከር የሚረዳ ነው"ብለዋል።

 በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ እጅጉ በአቀባበሉ ላይ እንደገለጹት በህዝቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የልኡካን ቡድኑ አባላት ያደረጉት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።

 የሕዝብን ፀጥታ ለማወክና የልማት ሥራዎችን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በጋራ ለመቆጣጠርም የተጀመረው ህዝበን ያሳተፈ ጥረት ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2010 የኖርዌዩ ያራ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ምርት ላይ ለመሰማራት ተስማማ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቬን ቶሬ ሆልሴተርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በተለይ በአፋር ክልል በቂ የፖታሽ ማዕድን ያላት በመሆኑ ኩባንያው በማዳበሪያ ማምረት ላይ ቢሰማራ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸውላቸዋል።

ኩባንያው ምርት በሚጀምርበት ጊዜ ለማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳኑም ባለፈ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥን ነው ተብሏል።

የኩባንያው ወደ ሥራ መግባት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ገልጸዋል።

የያራ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቬን ቶሬ ሆልሴተር በበኩላቸው ኩባንያቸው በማዳበሪያ ምርት የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑና በኢትዮጵያ በቂ የፖታሽ ማዕድን በመኖሩ በዘርፉ ለመሰማራት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ስምምነት ላይ በመደረሱም ኩባንያቸው ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመግባት መዘጋጀቱንና ፕሮጀክቱን በቀጣይ ዓመት አጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

ያራ ኢንተርናሽናል የተሰኘው የኖርዌይ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ዛሬ በአፋር ክልል በሞሰሊ ወረዳ በማዳበሪያ ማምረት ስራ ለመሰማራት የሚያስችል የ731 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል።   

ስምምነቱ ለሃያ ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ለሌላ አስር ዓመታት ሊታደስ ይችላል ተብሏል።

ስምምነቱ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ሞቱማ መቃሳና የራያ ዳሎል ቢቪ የፖታሽ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስፈጸሚ ሳንጃይ ራትሆሬ ናቸው የፈረሙት።

ኩባንያው ወደ ሥራ ለመግባት ጥናት ማጠናቀቁንና በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ስለመኖሩ ማረጋገጡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ሞሮኮም በቅርቡ በኢትዮጵያ ድሬዳዋ አካባቢ የማዳበሪያ ምርት ላይ ለመሰማራት 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መድባ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ ጥቅምት28/2010 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል በተያዘው የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ከ417 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

 ምክር ቤቱ የ2010 የመጀመሪያ ሩብ የበጀት ዓመት አፈጻጸምና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

 የብሔራዊ ምክር ቤቱ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በተያዘው የበጀት ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት  ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ነው፡፡

 ከዚህም ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት 417 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ በሀገር ውስጥና ውጭ ከሚኖሩ ዜጎች መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

 የዘንድሮን እቅድ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው፡፡

 የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰበሰበው ገቢ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም አቶ ታገል ጠቁመዋል፡፡

 ባለፉት ሶስት ወራትም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች የግድቡን ግንባታ በመጎበኘታቸው በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሀገራዊ መግባባት ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡

 ስለ ግድቡ ግንባታ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያለውን ትስስር እየተጠናከረ  ነው ተብሏል፡፡

 የቤንሻንጉል ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳልኝ በሪሁን በበኩላቸው ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ  የግድቡን ግንባታ የሚጎበኙ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ገልጸዋል፡፡

 በክረምት ወቅት ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ ባጣለው ከባድ ዝናብና በለውጥ መንገድ ግንባታ ምክንያት የቡድን ጉብኝቶች ሰርዘው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

 ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም  ጉብኝቱ እንደቆመ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ መረጃዎች ሐሰተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት ወደ ግድቡ ግንባታ ቦታ የሚያደርሱ ተለዋጭ መንገድ  ግንባታ መጠናቀቁንና  ለጉብኝት ለሚመጡ ዜጎች  ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አውሰተዋል፡፡

 ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የዘጠኙ ክልሎች ፣ የአዲስ አበባና የድሬደዋ አስተዳደሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤቶች አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2010 የኖርዌይ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ አምራች ዘርፍና በታዳሽ ኃይል ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጥሪ አቀረቡ።

ኖርዌይ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ የኖርዌዩን ልዑል ሃኮን እና ባለቤታቸውን ልዕልት ሜቲ ማሪትን ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል።

የኢትዮጵያና የኖርዌይ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀና በተለያዩ መስኮች የተጠናከረ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ትምህርት፣ የኃይል አቅርቦትና የአስተዳደር ጉዳዮችን አገራቱ በጋራ ከሚሰሯቸው ሥራዎች መካከል ጠቅሰዋል።

ኖርዌይ በተለይ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቷን ማሳየቷንም ጠቅሰዋል።

አገሪቷ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጋለች።  

በተጓዳኝ አገሪቷ ኢትዮጵያ 900 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ተቀብላ ስታስተናግድ ከጎኗ መቆሟን ገልጸው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

ይሁንና አገራቱ በኢንቨስትመንትና ንግድ ያላቸው ግንኙነት ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኖርዌይ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩም ፕሬዝዳንት ሙላቱ ልዑሉን ጠይቀዋል። 

በውይይታቸውም ከልዑሉ ጋር በቀጣይ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች አገራቱ ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸው ከስምምነት መድረሳቸውን አክለዋል።

በሌላ በኩል ኖርዌይ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በተለይም በትሮይካ የአውሮፓ አገራት ቡድን በኩል ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።

በተለይም በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሰራች ጠቁመው ይህ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አንዳለበት ነው ፕሬዚዳንቱ ልዑሉን የጠየቁት።

በድጋፏም ከአፍሪካ ኅብረትና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ ጋር በጋራ እንድትሰራም እንዲሁ። 

ልዑል ሃኮን በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውስተዋል።

"አያቴ ንጉስ ኦላ ከ51 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል እኔም የእሳቸውን ፈለግ ተከትዬ ዛሬ እዚህ በመገኘቴ ደስ ብሎኛል" ብለዋል።

ይህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይና ግንኙነቱ ከዚህ በላይ መጠናከር እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአገራቱ ግንኙነት በአየር ንብረት፣ በትምህርት ተደራሽነት፣ በሥራ ፈጠራ፣ በጤናና ሁሉን አቀፍ ልማት በማምጣት ላይ ያተኮረ መሆኑንም ልዑሉ ተናግረዋል። 

የዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ኖርዌይና ኢትዮጵያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው እድል እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።

ቀጣይ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይም በባለኃብቶች ተሳትፎ ላይ ያተኮረ እንዲሆንና በሌሎች ዘርፎች ላይም እንዲጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያና ኖርዌይ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1947 ኢትዮጵያ በስዊድን ስቶክሆልም ኤምባሲ መክፈቷን ተከትሎ ነው።

ኖርዌይም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1992 በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ ከ12ቱ የኖርዌይ የልማት ትብብር አገራት አንዷ ሆናለች። 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2010 የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የምርት ግብዓት ችግሮች ለመፍታት ሁለት ቢሊየን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ 328/2006 መሰረት የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

በዚህም ድርጅቱ የምርት ግብዓትን ከአገር ውስጥና ውጭ አገራት አምራቾች በመግዛት ባሉት የሽያጭ ማዕከላት በተመጣጣኝ ወጋ በማቅረብ የግልና የመንግስት ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ ግብዓቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል።

ይህ መሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃዎችን ከውጭ አገራት ለማምጣት ይገጥማቸው የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትና ሌሎች ውጣ ውረዶችን በማስቀረት ጊዜና ወጪን ከመቀነስ አንጻር ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑ ተገልጿል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋወሰን አለነ ለኢዜአ እንደገለጹት ለግልና መንግስታዊ ኢንዱስትሪዎች የምርት ግብዓት ለማቅረብ ሁለት ቢሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡

በያዝነው የ2010 የመጀመሪያ ሩብ አመትም ድርጅቱ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የሀገር ውስጥ የተዳመጠ ጥጥ፣ቆዳና ሌጦ እና ለኢንዱስትሪ ጨው ግዥ 32 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን አቶ አስፋወሰን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በግዥ ብቻ የሚያቀርበውን የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ በቀጣይ በራሱ አምርቶ እንደሚያቀርብ አቶ አስፋወሰን ገልጸዋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን