አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 06 November 2017

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2010 የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በአፋጣኝ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጠየቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን በቀረበው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ረቂቅ አዋጅ 600/2000 ላይ ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ የሁሉም ክልሎች የትራንስፖርት ፅህፈት ቤቶች፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ማህበራትና የህብረተሰቡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የአዋጁ መሻሻል ለሰው ህይወትና ንብረት ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት በኃላፊነት የሚያሽከረክሩ ባለሙያዎችን ማፍራትን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ለ4 ሺህ 554 ሰዎች ሞት፣ ለ10 ሺህዎች የአካል መጉደልና በ100 ሚሊዮን ብር ለሚገመት የንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸው ተገልጿል።

በመሆኑም ለውይይት በቀረበው ረቂቅ የመንጃ ፍቃድ አዋጅ 11 የሚሆኑ አንቀፆች የተሻሻሉ ሲሆኑ ሶስት አዳዲስ አንቀፆች ታክለዋል።

ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ደረጃ ከአራት ዓመት የሥራ ልምድ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፍቃድ እንዲሰጥ፣ ፍቃድ የሚሰጠው 10ኛ ክፍል ያጠናቀቀና ዕድሜው ከ22 ዓመት በላይ መሆን አለበት የሚሉ አዳዲስ አንቀፆችም ተካተዋል።

ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ረቂቅ አዋጁ ፈጥኖ ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለበት ነው ሃሳባቸውን የገለጹት።

ከአዲስ አበባ ማሰልጠኛ ተቋም የመጡት አቶ ተስፋዬ ንጉሴ በተቋማት ሳይሆን በቤተሰቦቻቸው ኃላፊነት ከሰለጠኑ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ የፅሑፍና የተግባር ፈተና ከተቋማት መውሰድ ይችላሉ የሚለው በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የብቃት ማረጋገጫ ጥያቄ አያስነሳም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።

ከህዝብ ተሽከርካሪዎች ማህበር የተወከሉት አቶ ቃሲም ሃሚልም ዕድሜ ለማጭበርበር የሚቀርቡ የሃሰት ምስክር ወረቀቶችን ከመቆጣጠር አኳያ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ምን ታስቧል ሲሉ አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በትራፊክ አደጋ ሳቢያ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት ለመቀነስ አዋጁ ፈጥኖ ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም ረቂቅ አዋጁን የሁሉንም ባለድርሻዎች ሃሳብ በማካተት አፅድቆ በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓመት እስከ 100 ሺህ ተሽከርካሪዎች እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው የብቃት መረጋገጫ ፍቃድ ፍላጎትና የማሰልጠኛ ተቋማት ተደራሽነት አለመመጣጠን፣ የተቋማቱ ክፍያ መወደድና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አኳያ የቤተሰብ ስልጠና በአዋጁ እንዲካተት መደረጉ ፍትሃዊና ትክክለኛ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ከስምንተኛ እስከ 10ኛ ክፍልና ከዛ በላይ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎችና ሌሎች የማረጋገጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ የዕድሜ  ማስረጃን ለመቆጣጠር ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ተሽከርካሪዎች ደረጃ የሥራ ልምድ ምዘና የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፍቃድ ወጥነት ባለው አገር አቀፍ የመረጃ ማዕከል ቋት አማካኝነት ተመዝኖ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።   

አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያገለገለ ሲሆን የአሁኑ የተሽከርካሪዎች ረቂቅ አዋጅ ለሶስተኛ ጊዜ እየተሻሻለ ነው።

 

 

Published in ማህበራዊ

ደብረ ማርቆስ ጥቅምት 27/2010 የወተት ላሞችንና በጎችን ዝርያ በማሻሻል ከወተትና ሥጋ ምርት ሽያጭ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አንዳንድ የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶአደሮች ገልጹ።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ100 ሺህ በላይ በጎችንና ላሞችን ዝርያ ለማሻሻል የታቀደ ሲሆን እስካሁንም 22 ሺህ የሚሆኑትን ማዳቀል እንደተቻለ ተመልክቷል።

በዞኑ የጎዛምን ወረዳ ሰንተራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አየነው ገድፍ እንዳሉት፣ የአካባቢ ዝርያ ያላቸውን ላሞች የውጭ ደም ካላቸው ኮርማዎች ጋር  በማዳቀል ዝርያቸው እንዲሻሻል ማድረጋቸውን ተናገረዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በማዳቀል የተወለዱ ጥጆች አሁን ላይ ወልደው እያንዳንዳቸው በቀን ከዘጠኝ እስከ 11 ሊትር ወተት በመስጠት ተጠቀሚ እንዳደረጓቸው ገልፀዋል።

ለበርካታ ዓመታት የአካባቢ ዝርያ ያላቸውን ላሞች ያረቡ እንደነበር ያስታወሱት አርሶአደሩ፣ በእዚህም በቀን ከአንድ ሊትር በላይ ወተት እንደማያገኙ  ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተዳቀሉት ላሞች የሚያገኙትን ወተት አባል ለሆኑበት "ፈንድቃ የወተት ልማት ማህበር" በማስረከብ በወር ከአንድ ሺህ 500 ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የደብረኤልያስ ወረዳ የዋሚት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ገረመው አዲሴ በበኩላቸው ከአራት ዓመት በፊት በሰው ሰራሽ ዘዴ ሦስት ላሞችን በማዳቀል ያገኟቸው ጥጆች  በአሁኑ ወቅት ወልደው ወተት መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል።

እነዚህ ላሞች እያንዳንዳቸው በቀን ከስምንት ሊትር በላይ ወተት እያገኙ መሆናቸውንና የሚያገኙትን ወተትንም በአካባቢው ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች በማከራየት በወር ከአንድ ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአካባቢ ዝርያዎች ፈጥኖ የሚደርሱና የተሻለ የሥጋ ምርት መስጠት የሚችሉትን የዋሸራ በግ ከአካባቢ ዝርያ ጋር በማዳቀል የተሻለ ዝርያ ማግኘት መቻላቸውን የገለፁት ደግሞ በአነደድ ወረዳ የንፋሳም ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ስሜነህ ባለው ናቸው ።

በተከታታይ ባደረጉት የማዳቀል ስራም ከአስር የማያንሱ የተሻሻሉ የበግ ግልገሎች ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ግልገሎቹ በአቋማቸውም ሆነ በስጋ አያያዛቸው የተሻሉ በመሆናቸው ከአካባቢው በጎች በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ከእዚህ በተጨማሪም በጎቹ የውልደት መጠናቸው ከአካባቢው የበግ ዝርያ የተሻለና በአንዴ ሁለት፤ አልፎ አልፎም ሦስት ግልገሎችን በመውለድ ገቢያቸውን እንዳሳደጉላቸው አስረድተዋል።

በዞኑ እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የእንስሳት እርባታ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ አላምነህ  ለኢዜአ እንደተናገሩት የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመት ከ100 ሺህ በላይ በጎችንና ላሞችን ዝርያቸውን ለማሻሸል ታቅዶ በሩብ ዓመት ብቻ ከ22 ሺህ በላይ ማዳቀል መቻሉን ገልፀዋል።

ከነዚህ መካከል 17 ሺህ የሚሆኑት በጎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የወተት ላሞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

አቶ ሙሉጌታ አንዳሉት ዘንድሮ በተካሄደው ዝርያ የማሻሻል ሥራ ከ12 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ባለፈው ዓመትም በተለያየ የማዳቀል ዘዴ ከ65 ሺህ በላይ ላሞችና የዋሽራ በጎችን በማዳቀል ከ49 ሺህ በላይ ጥጆችና ግልገል በጎችን ለማስወለድ መቻሉን ባለሙያው አብራርተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ  ጥቅምት 27/2010  በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ለታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ፡፡

የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ዋንጫው በከተማው በሚኖረው ቆይታ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በከተማው ከሚገኙ ባለሃብቶች መካከል የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ ባለቤት አቶ እስክንድር ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በድርጅታቸው ስም ለህዳሴው ግድብ  የ1 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል።

"የግድቡ ግንባታ አገሪቱ ያለባትን የሃይል እጥረት ይቀርፋል የሚል እምነት ስላለኝ ድጋፉን ሳደርግ በደስታ ነው " ብለዋል ።

በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ ዱካለ ዋቃዮ በበኩላቸው የዋንጫውን ወደ ከተማዋ መግባት ምክንያት በማድረገ የ700 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲልም ስራቸውን በሚሰሩባቸው ሲዳማ ዞንና ባንሳ ከተማ በሁለት ዙር የ1 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ግድቡ ተጠናቆ ስራ እስኪጀምር ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

"በግድቡ ግንባታ ላይ  የበኩሌን አሻራ በማኖሬ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል" ያሉት ደግሞ በነዳጅ ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ያንጣራ ሜና ናቸው፡፡

ዋንጫው በከተማው መግባቱን ተከትሎ የ100 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የገለፁት አቶ ያንጣራ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የ240 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአዳሬ የደረጃ አንድ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ እንዳለ ሀሳ  በበኩላቸው በአባላቱና በማህበሩ ስም የ836 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የማህበሩ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል " ብለዋል ።

በሃዋሳ ከተማ የባጃጅ ሞተር ሳይክል አስመጭ አቶ አለቃ ከበደ በበኩላቸው "የአባይ ግድብ የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናከረ፣ ለጋራ ጉዳይ እንድናብር ያደረገን አገራዊ ፕሮጀክት ነው" ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ የግማሽ ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልፀዋል።

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ እንዳሉት የከተማው ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎችና ልማት ወዳድ ነዋሪዎች ለከተማው እድገት የጎላ ሚና እያበረከቱ ነው፡፡

"የከተማው ማህበረሰብ በከተማው ብቻ ሳይሆን በክልላዊና አገራዊ የልማት ስራዎችም የመሳተፍ የዳበረ ልምድ አለው"  ብለዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ ባለህብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ በግል፣ በድርጅትና  በማህበራቸው ስም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ድጋፋቸውን ሲያበረክቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።

"ዋንጫው በከተማው በሚኖረው የአንድ ሳምንት ቆይታ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል" ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባው ገለፃ በዋንጫው የአንድ ቀን ቆይታ ብቻ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰብሰቧል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2010 ኢትዮጵያ የአየርላንድ ባለሀብቶች በተለይ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ ተሰማርተው እንዲሰሩ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየርላንዱን የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚኒስትር ሳይሜን ኮኔቬይ ቲ.ዲ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

አየርላንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዴሊቨሪ ዩኒት ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብረሃ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤የአየርላንድ ባለሀብቶች የአገራቸውን የካበተ ልምድ በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠዋል።

አየርላንድም በኢኮኖሚው መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላትም ተገልጿል።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚኒስትር ሳይሜን ኮኔቬይ ቲ.ዲ፤ አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት አላት። 

አየርላንድ በተለይ የኢትዮጵያን የገጠር ኢኮኖሚ ልማት እንደምትደግፍ ገልጸው፤ ባለሀብቶቿ በግብርናው ዘርፍ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው የኢኮኖሚ ትብብር እንዲያድግ ያሳዩትን ፍላጎት አድንቀዋል። 

የኢትዮጵያና የአየርላንድ ሁለንተናዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1994 ሲሆን፤ ሁለቱም አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን በዚያው ዓመት ከፍተዋል።

በአየርላንድ የድጋፍ መርሃ-ግብር አማካኝነት ለኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እስካሁን 136 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአየርላንድ ባለሀብቶች ራዲሰን ብሉ ዓለም አቀፍ ሆቴልን ጨምሮ በ17 ኩባንያዎች 727 ሚሊዮን 516 ሺ ብር በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርጋለች።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  ጥቅምት27/2010 የኢትዮጵያ ሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን በአየር ትራፊክ ቁጥጥር ለአንድ አመት ያሰለጠናቸውን 17 የጅቡቲ ሰልጣኞችን አስመረቀ።

ተመራቂዎቹ የዘመኑ የ3D አቬዬሽን ትሬዲኒግ ማዕከል ሲሙሌተርና ሌሎች ተያያዥ ስልጠናዎችን የወሰዱ መሆናቸው ተገልጿል።

ስልጠናው ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከአንድ አመት በፊት በዘርፉ በጋራ ለመስራት ባደረጉት ስምምነት መሰረት የተሰጠ ሲሆን ጅቡቲ  150 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጓ በምርቃቱ ላይ ተገልጿል።  

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ እንዳሉት፤ ስልጠናው በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ብቃት ያለውና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ጉልህ ሚና አለው።

ስልጠናው በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ የአየር ትራንሰፖርት አካባቢ እንዲኖር ያስችላልም ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ጅቡቲ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጠንካራ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በባቡር፣ በአየርና በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፎች በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የሁለቱ አገራት አቪዬሽን ዘርፍ ማደግ ለአገራቱ ሁለንተናዊ ግንኙነት መጎልበት የላቀ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው በአየር ትራፊክ ቁጥጥር ላይ ሲሰጥ የነበረው የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠና ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን የስልጠና ማዕከል ከተመሰረተ ግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በኢትዮጵያና በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ  የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 27/2010 የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የከተማና የገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥ አመርቂ አይደለም ተባለ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2010 ዓ.ም እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴሩ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩና የተጓተቱ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶችን በአፋጣኝ አጠናቆ ወደ ስራ እንዲያስገባ አሳስቧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ዩሱፍ ሚኒስቴሩ በከተማና በገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥ አመርቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን፣ የውሃ መገኛ ጥናት፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የውሃ ስራዎች ግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማስፋፋት ረገድ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ስራዎችን ማስጨረስና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይኖርበታልም ብለዋል።

ከተጓተቱ ስራዎች መካከል የጅግጅጋ 2ኛ ዙር የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት፣ በአፋርና በቤኒሻንጉል ክልሎች የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች የማሰራጫ መስመር ግንባታና ከአላማጣ ወልዲያ የማከፋፈያ ኔትዎርክ ግንባታዎች ተጠቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህን የተጓተቱ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንዲገቡና ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ አለባቸው ነው ያሉት።  

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ በከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋኑን 75 በመቶ፣ በገጠር ደግሞ 78 በመቶ ለማድረስ እቅድ ይዟል።

በዚህም የጅግጅጋ፣ የቀብሪደሃርና የፊቅ ከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።

በገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ በተረደገው ጥረትም በሶማሌ ክልል 5፣ በአፋርና በደቡብ ክልሎች 2፣ በቤኒሻንጉል 8፣ በጋምቤላ 2 እና በኦሮሚያ 3 ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግም ተችሏል።

ያም ሆኖ ችግሮችን ለመፍታትና ውጤታማ ስራ ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባው ነው የተጠቆመው።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው የተጀመሩ ስራዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ የበጀት፣ የግብዓትና የሰው ኃይል ውስንነት እንዳለበት አመልክተዋል።

በቀጣይ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2010 ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ላመረታቸው የእንስሳት ክትባቶች የገበያ ችግር እንዳጋጠመው ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ማርታ ያሚ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2010 በጀት ዓመት እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሩብ ዓመቱ ለአገር ውስጥ ገበያ 60.26 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት በማቅረብ 28 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 51 ሚሊዮን ዶዝ በመሸጥ 23 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል።

በተመሳሳይ በሩብ ዓመቱ ለውጭ አገራት ገበያ ስምንት ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት በመሸጥ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ የተገኘው ገቢ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።

ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ከሸጠው የእንስሳት ክትባት ያገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  የ37 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ዶክተር ማርታ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ በበኩላቸው የእንስሳት ክትባቶች በክልሎችና በውጭ አገራት ያላቸው የገበያ ተፈላጊነት ከፍተኛ ቢሆንም የክትባቶቹ ተደራሽነት የሚፈለገውን ያህል አይደለም።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በየክልሎቹ ባደረጉት ተደጋጋሚ የመስክ ምልከታ የእንስሳት ክትባት ተደራሽነት በቂ አይደለም የሚል ቅሬታ መነሳቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከመሰል ተቋማት ጋር ያለው የቅንጅት አሰራር ጠንካራ አለመሆን በክልል ላለው የገበያ ተደራሽነት ችግር እንደ ዋንኛ መንስኤ እንደሚታይ ተናግረዋል።

በአፍሪካም ያለው ተደራሽነት በተወሰኑ አገራት ከመመስረቱ ባለፈ የእንስሳት ክትባቱን አገራቱ ለመግዛት ጥያቄ ካላቀረቡ በስተቀር ሽያጭ ማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት አለመፍጠሩ ሌላኛው ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ የሚነሳውን ቅሬታ በመፍታትና ወደ ሌሎች አገራት የምርቱን ተደራሽነት የማስፋት ተግባር ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን  ወይዘሮ አልማዝ አስረድተዋል።

የእንስሳት ክትባቶቹን የገበያ ተደራሽነት ለማስፋት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ማርታ ያሚ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

በአፍሪካ አገራትና በሌሎች አህጉራት ያለውን የገበያ ተደራሽነት ለማስፋትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባባር አዳዲስ የሚመረቱ የእንስሳት ክትባቶችን በተለያዩ አገራት የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ አገራት ሽያጩ የሚከናወነው በየአገራቱ በሚገኙ የኢንስቲትዩቱ ወኪሎች በመሆኑ የገዢዎቹ ፍላጎት በሚፈለገው ፍጥነት ማወቅ አለመቻሉ ችግር እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ይህንንም ለመፍታት በወኪሎች ያለውን የእንስሳት ክትባቶች ሽያጭ በመቀየር ከአገራቱ መንግስት ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ የተቀናጀ የግብይት ስርአት መፍጠር በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት ጉዳይ እንደሆነ ዶክተር ማርታ አስረድተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአጠቃላይ በ2010 በጀት ዓመት 325 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት በመሸጥ 295 ሚሊዮን ብር ለማግኘት እቅድ የያዘ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አስተያየት መሰረት እቅዱን ለማሳከት እንደሚሰራም ዶክተር ማርታ ገልጸዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ወልዲያ ጥቅምት 27/2010 በሰሜን ወሎ ዞን ከዶላር ምንዛሪ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በሸቀጦች ላይ አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 321 ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ። 

የዞኑ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አያሌው ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት ያደረገውን የዶላር ምንዛሬ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ከዞን እስከ ወረዳ በሚገኙ ከተሞች መድረኮችን በማዘጋጀት ከ15 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን በማወያየት ቀደም ሲል ባስገቡት የውጭና የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ነጋዴዎች ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው የተጋነነ ገንዘብ ጨምረው ሲሸጡ መገኘታቸውን ተረጋግጧል።

ከጥቅምት 21 ቀን 2010 ጀምሮ በተካሄደ ቁጥጥር እነዚህን ነጋዴዎች ጨምሮ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ በተገኙ፣ ደረሰኝ በማይሰጡና የእቃዎችን የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር በማይለጥፉ ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡

በተደረገው ክትትል የዳቦ ዱቄት በ17 በመቶ፣ ሲሚንቶ በ33 በመቶ ፣ የብረታብረት ምርት በ68 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ህገ በተላለፉ  አራት ነጋዴዎች ላይ ክስ ተመስርቶ እያንዳንዳቸው 3ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉን ገልጸዋል

አራት ዳቦ ቤቶችም በድጎማ የሚሰጣቸውን ዱቄት ለነጋዴ አሳልፈው ሲሸጡ በመገኘታቸው ንግድ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በወልድያ ከተማ በሸቀጦች የችርቻሮ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ፋጡማ አሊ በሰጡት አስተያየት ንግድ ቤታቸው የታሸገው ጅምላ ነጋዴዎች ዋጋ በጨመሩባቸው ሸቀጦች ላይ እርሳቸውም የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ያሉ ጅምላ አከፋፋዮች ለሚሸጡት እቃ ህጋዊ ደረሰኝ ስለማይሰጡ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባም አስተያየት ሰጭዎቹ ጠይቀዋል።

የግንባታ ሥራ ተቋራጭ የሆኑት አቶ ጌታየ መሰለ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ወራት የአርማታ ብረቶች ባለ 8 ቁጥር ከ110 ወደ 200 ብር፣ ባለ 10 ቁጥር ከ160 ብር ወደ 300 ብር፣ ባለ 12 ቁጥር ከ200 ብር ወደ 400 ብር ዋጋ በመጨመሩ ተቋራጮች ሥራ ማቆማቸውን አመልክተዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ከ39 ሺህ 980 በላይ የንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች እንዳሉ መምሪያውን ጠቁሟል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር  ጥቅምት 27/2010 የሥራ ፈጠራ ክህሎት ትምህርትን በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመደበኛነት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፌዴራል ከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና አጄንሲ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ፈጠራ ማስተባበሪያ ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችል ውይይት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጌቱ አብዲሳ እንደገለጹት የስራ ፈጣሪነት ትምህርት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ለመስጠት ዝግጅት ተጀምሯል።

ተማሪዎች የስራ ክቡርነት ባህልን እያዳበሩ እንዲያድጉ ትምህርቱ ከአፀደ ህፃናት እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ከሌሎች ትምህርቶች ጋር ተካቶ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ የስራ ፈጠራ ትምህርት ራሱን ችሎ ለመስጠት መታሰቡን ገልፀዋል።

ትምህርቱ የሚሰጥበትን ስርዓት ለመዘርጋት የማስፈፀሚያ መመሪያ ተዘጋጅቶ በባለድርሻ አካላት እንዲተች እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ከባለድርሻ አካላት የሚገኘውን ተጨማሪ ሃሳብ በማካተትና ለመማር ማስተማር የሚያግዙ መፅሃፍትን በማዘጋጀት በሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱን ለመጀመር ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትምህርቱን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠትም በመላ ሃገሪቱ በማስተማር ላይ የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የስነ ምግባርና የስነ ዜጋ መምህራን ስልጥና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ለማሳደግም በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ማስተባበሪያ ማዕከላት ተቋቁሞ አጫጭር ስልጠና እየሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

''በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማስተባበሪያ ማዕከላቱን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው'' ብለዋል።

የፌዴራል ከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስት በበኩላቸው የምክክር መድረኩ አላማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ስትራቴጂን ለዩኒቨርሲቲዎችና ባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ ነው።

የስራ ፈጠራ ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ራሱን ችሎ እንዲሰጥ ኤጀንሲው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።      

ዩኒቨርሲቲዎችም የስራ ፈጠራ ማዕከላትን በማቋቋም ወጣት ምሩቃን በተማሩት ልክ ስራ የመፍጠር ባህል ተላብሰው እንዲወጡ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ማዕከሉ ከተቋቋመ ከ2007 ጀምሮ እስካሁን ከሶስት ሺህ ለሚበልጡ ተመራቂ ተማሪዎችና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መስጠቱን የገለፁት ደግሞ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስራ ፈጠራ ልማት ማበልፀጊያ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ማስተዋል ብርሃኑ ናቸው፡፡

የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የሚያመነጩት የፈጠራ ሃሳብ ተሞክሮ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው  የምክክር መድረክ ላይ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ማይጨው ጥቅምት 27/2010 የግብርና ምርታቸውን በሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች አማካኝነት በቀጥታ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በትግራይ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ገልጹ።   

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንደመኾኒ ወረዳ ነዋሪና "የእምበባ ጊዮርጊስ" ሕብረት ስራ ማህበር አባል አርሶ አደር ሞላ አለማየሁ በ2008/2009 ዓ.ም ያመረቱት የስንዴ ምርጥ ዘር ዩኒየናቸው ተረክቧቸዉ ያለ ውጣ ውረድ ሙሉ ለሙሉ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በምርት ዘመኑ ያገኘሁትን ምርጥ ዘር ሳይባክን በአንድ ጊዜ በሽያጭ በማስረከብ ገንዘብ አግኝቻለሁ" ያሉት ደግሞ የአምባላጌ ወረዳ ነዋሪና  "የብርሃን ዓይባ ሕብረት ሥራ ማህበር" አባል አርሶ አደር ሚካኤለይ ዮሐንስ ናቸው።

የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያና ገበያ ልማት ኤጄንሲ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ ደቡባዊና ማዕከላዊ ዞን የሚገኙ ሁለት የህብረት ስራ ዩኒየኖቹና በስራቸው በዘር ብዜት የተሰማሩ 60 ማህበራት ከአባሎቻቸው ምርት በመረከብ ለሌሎች አርሶ አደሮች እያሰራጩ ይገኛሉ።

ዩኒየኖቹ ከአባል አርሶ አደሮቹ የሚረከቡትን ምርጥ ዘር ጥራቱን በሚጠብቅ መልኩ አዘጋጅተው ለሌሎች አርሶ አደሮች በማሰራጨት በክልሉ የዘር እጥረት በማቃለል የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም አቶ ሰለሞን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ ዩኒየኖቹ ተቋቁመው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ገቡተዉ አንድ ዓመት ባልመላ ጊዜ ወስጥ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራት ያለ የስንዴና የጤፍ ምርጥ ዘሮችን ለአከባቢው አርሶ አደሮች አቅርበዋል።

"በዘንድሮ መኸር ወቅትም ለሚያከናውኑት ተመሳሳይ ተገባር ማስፈፀሚያ 16 ሚሊዮን ብር በብድር እንዲያገኙ ይደረጋል" ብለዋል ።

የሕብረት ሥራ ማህበራቱ አባል አርሶ አደሮች ተደራጅተው በኩታገጠም ማሳ ላይ የምርጥ ዘር ልማት እንዲያካሂዱና ዩኒየኖቹም ምርቱን በዘመናዊ መንገድ አዘጋጅተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል ።

ዩኒየኖቹ ክልሉ በመደበው ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የምርጥ ዘር ማምረት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን የሚረዳቸውን የቢሮና የዘር ማከማቻ መጋዘኖች ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ የሕብረት ሥራ ማህበራቱ 2 ሺህ 700 አርሶ አደሮችን በአባልነት አቅፈዋል ።

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን