አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 05 November 2017

ሀዋሳ ጥቅምት 26/2010 በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአቻ ግፊትና በተለያዩ አጋላጭ ምክንያቶች ተዘናግተው ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠና ለሁለት ቀን ተሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስርዓተ ጾታና የኤች.አይ.ቪ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ትግስት ከበደ  እንደገለጹት፣ ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ እንዳይስቱ ተከታታይነት ያለው የሕይወት ክህሎት ስለጠናዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ስልጠናው በተለይ አዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ተማሪዎች ለአካባቢው እንግድነት ተሰምቷቸው በስነ ልቦና ችግር እንዳይጎዱና በአቻ ግፊት ተጽዕኖ ስር እንዳይወድቁ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ተከታታይ ስልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት ዲያሬክተሯ፣ ስልጠናው በዋናነት ለሴቶች ብቻ የሚሰጥ መሆኑ በእነርሱ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እንዳላስቻለ ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የተሰጡ ሰልጠናዎች ያመጡትን ለውጥ ለመገምገም ጥናት መካሄዱን ገልጸው፣ በእዚህም ራሳቸውን የመግለጽ ልምድ ያጎለበቱና ከአቻ ግፊትና ተጽዕኖ ነጻ መሆን የቻሉ ተማሪዎችን መፍጠር እንደተቻለ ጥናቱ መሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ወንዶች ተሳታፊ ባለመሆናቸው ምክንያት የመጣውን ለውጥ የተሟላ ማድረግ አለመቻሉ በጥናቱ በመረጋገጡም በተያዘው ዓመት ስልጠናው ለሁሉም አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንዲሰጥ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ጎንደር እብናት ወረዳ የመጣችውና በዩኒቨርሲቲው ወንዶገነት ካምፓስ የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት ተማሪ የሆነቸው መቅደስ እንየው አንዷ ናት።

ከቤተሰብ እርቃ ስትወጣ የመጀመሪያዋ መሆኑን ገልጻ፣ የተሰጠው የሕይወት ክህሎት ስልጠና በራስ የመተማመን መንፈስን ለማዳበር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ከቤንሻንጉል ክልል የመጣችው ተማሪ ሰላማዊት ለሜሳ በበኩሏ "ከመጥፎ ተግባር በመራቅና በትምህርቴ ስኬታማ ሆኜ ለሀገሬና ለቤተሰቤ ለመትረፍ ስልጠናው በተወሰነ ደረጃ እገዛ ያደርግልኛል" ብላለች፡፡

"ለመዋብና ለሌሎች ተፈጥሯዊ ጉዳዮች ሴቶች ከወንዶች በተለየ ብዙ ነገሮች ያስፈልጉናል" ያለችው ተማሪዋ፣ እርሷ በዚህ ምክንያት አቻዋን በማየት ወደ አላስፈላጊ ነገር ላለመግባትና በትምህርቷ ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ ማቀዷን ተናግራለች፡፡

ከጎንደር ከተማ እንደመጣ የተናገረው ተማሪ አለሙ ተካ በበኩሉ በርካታ ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ጫት መቃም፣ ሲጋራ ማጨስ ለምደው እንደሚመጡ መስማቱን ገልጾ፤ በስልጠናው ለዚህ አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን በመገንዘቡ በግሉ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

በወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህርትና የሕይወት ክህሎት ስልጠናውን የሰጠችው ወይዘሪት ጽዮን ወንድሙ እንዳለቸው ፣ስልጠናው ተማሪዎች በተቋሙ ቆይታቸውም ሆነ በቀጣይ ራሳቸውን በአግባቡ ለመምራት ያስችላቸዋል።

በመምህርንት ቆይታዋ በጣም ከፍተኛ ውጤት ታስመዘግብ የነበረችና በአቻ ግፊት ምክንያት በደረሰባት ችግር ውጤቷ ያሽቆለቆለ  አንዲት ተማሪ አጋጥማት እንደነበር አስታውሳ፣ ይህን መሰል ችግር እንዳይደርስና ተማሪዎች የተሟላ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የስልጠናው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ግርማ መንገሻ እንዳሉት በኮሌጁ የሚመደቡ ተማሪዎች ያላቸውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ አጋላጭ የሆኑ ተግባራትን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በኮሌጁ አቅራቢያ የጫት፣ ሽሻና ጭፈራ ቤቶች እንዳይኖሩ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝና በኮሌጁ አካባቢ ተከፍቶ የነበረ አንድ ጠጅ ቤት የተማሪዎች መደበቂያ በመሆኑ እንዲዘጋ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2018 የቻን ውድድር ከሩዋንዳ አቻው ጋር ዛሬ ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ሶስት ለሁለት ተሸንፏል።

 ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ ለምታስተናግደው የቻን ውድድር ለመሳተፍ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ ሽንፈት ገጥሞታል።

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ17ኛው ደቂቃ በአስቻለው ግርማ ጎል መሪ ቢሆን ቢችልም በ22ኛው ደቂቃ ኤሪክ ሩታንጋ የአቻነቷን ጎል አስቆጥሯል።የመጀመሪያውን 45 ደቂቃ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

 በሁለተኛው አጋማሽ በ65ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ሁለተኛውን ጎል በማስቆጠር ብሔራዊ ቡድኑን መሪ ማድረግ ቢችልም በ78ኛው ሞሀጅር ሀኪዚማና በ80ኛው ደቂቃ አቢዲ ቢራማሂር አከታትለው ባስቆጥሩት ግብ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሸናፊ መሆን ችሏል።

 ሁለቱ ጎሎች የተቆጠሩት በግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሃኑ ስህተት ነው። ብሔራዊ ቡድኑ የሜዳ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

 በዚህም መሰረት የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል ያስመዘገበ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት በኪጋሊ የሚካሄድ ይሆናል።

 የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።

Published in ስፖርት

ሰመራ ጥቅምት 26/2010 ህገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርአቱን በሕብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ በኩል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

 ክልሉ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባባር በህገ-መንግስትና ሕብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ስርአቱ ላይ በየደረጃው ካሉ የክልሉ አመራሮች ጋር  ዛሬ በሰመራ ከተማ ስልጠና ተሰጥቷል።

 በስለጠናው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ስዩም አወል እንደተናገሩት የፌደራል ሥርአቱ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት በማረጋገጥ በሀገሪቱን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ መሰረት ጥሏል።

ሥርአቱ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡ ስለህገ-መንግስቱና የፌዴራል ሥርአቱ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ በባለቤትነት እንዲጠብቀውና እንዲንከባከበው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

 ጸረ ሰላም ኃይሎች በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የህዝቡን ሰላም ለማወክና ልማትን ለማደናቀፍ የፌዴራል ስርአቱን የሚጎዱ ተግባራት ሲፈጽሙ የሚስተዋልበት አጋጣሚ እንዳለም አቶ ስዩም አመልክተዋል።

በመሆኑም በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የህገ-መንግስት እሴቶችና የፌዴራል ሥርአቱ ልዩ ባህሪያት ላይ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን  ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 "ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በሃገሪቱ በተዘረጋው ህገ-መንግስታዊ ሕብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ስርአት የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ድሎች በክልሉ ተመዝግበዋል" ያሉት ደግሞ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ጽህፈት ቤት ኃላፊና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ሲምፖዚየምና ህገ-መንግስት ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ናቸው።

 ኮሚቴው ክልሉ የሚያስተናግደውን 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችንና የፌደራሊዝም ሥርአቱን ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 በቀጣይም ኮሚቴው የሚያዘጋጀው የህገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም ስርአት አስተምህሮት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ንቅናቄ ስራዊት በየደረጃው እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

 አምባሳደር ሀሰን እንዳሉት፣ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መሰረት የሆነው ህገመንግታዊ ስርአቱን በአዲሱ ትውልድ ላይ በአግባቡ ለማረስረጽና ብዥታዎችን ለማጥራት አስከበዓሉ ድረስ ተከታታይ የአስተምህሮት ሥራዎች በየደረጃው ተጠናክረው ይሰራሉ።

 "የኤፌዴሪ ህገ-መንግስት ዓላማዎች፣ መሰረታዊ እሴቶችና የፌዴራል ስርአቱ" በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለአንድ ቀን በተሰጠው ስልጠና ከ200 በላይ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች ተሳታፊ ሆናዋል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ጥቅምት 26/2010 በጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን የማስተዋወቅ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

አባገዳዎቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ ዛሬ በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችንና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ጎብኚዎች መካከል አባገዳ ደንቦቤ አጋ እንዳሉት፣ ወደ ባህር ዳር ከተማ ሲመጡም ሆነ በጣና ሐይቅ የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ሲጎበኙ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

በጉብኝቱ የንጉሳዊያንን ዘውዶች፣ አልባሳት፣ የብራና መጻህፍትና ሌሎች ቅርሶችን መመልከታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

" በጥንት ጊዜ የነበሩ ቅርሶች እንደዚህ ተጠብቀው ይኖራሉ ብዬ አላስብም ነበር " ያሉት አባገዳ  ደንቦቤ፣ በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቱሪስቶች በስፋት እንዲጎበኙ የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

"ጥንታዊ ቅርሶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጪው ትውልድ ለማቆየት እየተሰራ ያለው ሥራ እንዳስደሰታቸው" የተናገሩት ደግሞ ሌላው አባገዳ መኮ ገናሌ ናቸው።

 እርሳቸው እንዳሉት፣ በተለይ ታሪካዊ ቅርሶቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም በስፋት ተዋውቀው የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ቅርሶቹን የማስተዋወቁ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

 በጉብኝቱ በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን የገለጹት አበገዳ መኮ "ልጆቻችንም ድንቅ የሆነውን የሀገራቸውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች መጥተው እንዲጎበኙ በቀጣይ እንሰራለን" ብለዋል።

 "የፈጣሪን ድንቅ ሥራ በሐይቁ ውስጥ እንድናይ የሁለቱ ክልል መንግስታት ላደረጉት ትብብር አድናቆት አለኝ" ያሉት ደግሞ ከአምቦ ከተማ የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ አለማየሁ ዴሬሶ ናቸው።

በተለይ በጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኘውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በሥርአተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲያውቀው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመለክተዋል።

ሐይቁን ከተጋረጡበት አደጋዎች በዘላቂነት ለመከላከል የተፈጥሮ ሃብት ልማት እንክብካቤ ሥራው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አባገዳዎቹና የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል። 

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስ በበኩላቸው በጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ 

የሀገር ውስጥ ቱሪስት እንቅስቃሴ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም  ዘርፉን ለማሳደግ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቁ ሥራ በተለያየ መንገድ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አባገዳዎቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ በዛሬ ውሏቸው የክብርዓን ገብርኤል ገዳምና ሌሎች የሐይቁን ክፍሎች የጎበኙ ሲሆን የቤዛዊት ቤተ መንግስትና የአማራ ህዝቦች ሰማዕታት ኃውልትንም ጎብኝተዋል።

ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የጎበኙ ሲሆን ዘንድሮ የጎብኚዎችን ቁጥር በ30 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

Published in ፖለቲካ

 አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2010 ዛሬ በተካሄደው የቻይና ሀንግዙ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸነፉ።

 በሴቶች ሙሉኃብት ፀጋ በወንዶች አዝመራው በቀለ ናቸው ውድድሩን ያሸነፋፉት።

 በሴቶቹ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ሙሉኃብት ፀጋ 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ8 ሰከንድ በመግባት በኬንያዊቷ አን ቤርዌ 2 ሰዓት ከ31 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን ከሶስት ደቂቃ በላይ አሻሽላለች።

 ኢትዮጵያዊያን የበላይነታቸውን ባሳዩበት በዚህ ውድድር አትሌት ትንቢት ግደይ 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በመግባት 2ኛ ስትሆን አትሌት ፀሐይ ደሳለኝ በ2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ በማጠናቀቅ 3ኛ ወጥታለች።

 በተመሳሳይ በወንዶች ውድድር አትሌት አዝመራው 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በመግባት እ.አ.አ 2016 በኢትዮጵያዊው በጅጋ ረጋሳ ተይዞ የነበረውን 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ ክብረ ወሰን ማሻሻል ችሏል።

 ኬንያዊው ሳሙኤል ቴሁሪ በ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ 2ኛ ሲወጣ፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ አብዲ ፉፋ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት በሶስተኝነት አጠናቋል።

 አብዲ ፉፋ በውድድሩ 3ኛ ቢወጣም በግሉ ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

 ለ31ኛ ጊዜ የተካሄደው የሀንግዙ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

 በሌላ ዜና በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የኒውዮርክ ማራቶን ከቀኑ 11 ሰዓት ከ50 ደቂቃ የሚጀመር ሲሆን በወንዶች የአምናው አሸናፊ ኢትዮጵያዊው ግርማይ ገብረሥላሴ የቅድሚያ ማሸነፍ ግምት አግኝቷል።

 በሴቶች ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ውድድሮች ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ማሪ ኬይታኒ የማሸነፍ ግምት እንደተሰጣት የማኅበሩ ዘገባ ያመለክታል።

Published in ስፖርት

መቀሌ ጥቅምት 26/2010 የትግራይ ልማት ማህበር (ትልማ) በክልሉ ለሚያስገነባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ድጋፍ ለማግኘት ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር የ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኘ።

ማህበሩ ትናንት በመቀሌ ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩን ያዘጋጀው በክልሉ 37 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚያስገነባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ነው።   

የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ታደለ ሀጎስ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ማህበሩ ማዕከላቱን ለማስገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚታየውን ችግር ለማቃለል ነው።

ዶክተር ታደለ እንዳሉት፣ ማህበሩ ትላንት በመቀሌ ከተማ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ተገብቶለታል ።

የሚገነቡት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ባለ አንድ ፎቅ ሕንጻ ሲሆኑ ለሳይንስ ቤተሙከራ፣ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ለዲጅታል ቤተንባብና ለሌሎች አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖራቸው ተመልክቷል።

ማህበሩ እስካሁን የአምስት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ግንባታ ሥራን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍና በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ዶክተር ታደለ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግበር ላይ 120 ሺህ ብር ለመለገስ ቃል ከገቡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሀጂ መሀመድ ዓብደላ አንዱ ናቸው፡፡

"ልማት ማለት የሰውን አዕምሮ ማልማት እንጂ ብር መሰብሰብ ብቻ አይደለም" ሲሉም ሀጂ መሀመድ ተናግረዋል።

ለማዕከላቱ ግንባታ ድጋፍ የሚውል አንድ ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል የገቡት ደግሞ አቶ ይርዳው መኮንን የተባሉ ባለሀብት ናቸው፡፡                                                                                                         

ባለሀብቱ ቃል ከገቡት ገንዘብ በተጨማሪ በየዓመቱ በአባልነት ይከፍሉት የነበረው 25 ሺህ ብር ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር ከፍ እንዲል ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

"በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ ማህበረሰብ ከተገነባ በአገራችን  የተሻለ ልማት እንደሚኖር በመተማመን ለልማት ማህበሩ ድጋፍ አድርጊያለሁ" ብለዋል፡፡

 የትግራይ ልማት ማህበር "8160" ላይ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ገቢ ለማሰባሰብ ዕቅድ ይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩም በገቢ ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

 የትግራይ ልማት ማህበር ባለፉት 26 ዓመታት የክልሉ ምንግስት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች 691 አንድኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማስገነባት ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

 ከእዚህ በተጨማሪ ሁለት ሆስፒታሎች፣ አምስት ጤና ጣቢያዎችና 74 ኪሊኒኮች ማህበሩ ካስገነባቸው ማህበራዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

 

አዲስ አበባ ጥቅምት26/2010 የኳታር ቀይ ጨረቃ ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የ3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

ማህበሩ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ ''አክሽን ፎር ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ'' ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የማህበሩ ዋና ፀሀፊ አሊ ሀሰን አል ሃማዲ እና በኢትዮጵያ የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳሊሁ ሱልጣን ፈርመዋል።

ዋና ፀሀፊ አሊ ሀሰን አል ሃማዲ በስምምነቱ ወቅት የተገኙት በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከማህበሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ዋና ፀሀፊው ለድጋፉ የሚውለው 3 ሚሊዮን ዶላር ከኳታር የልማት ፈንድ የተገኘ መሆኑን ገልፀው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የመጠለያ፣ የውሃ፣ የንጽህና፣ የምግብና የኑሮ ሁኔታን ለመደገፍ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ የ38 ሺህ ሰዎችን ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ችግሮች ለማቃለል እንደሚያግዝም ነው የገለፁት።

የአክሽን ፎር ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳሊሁ ሱልጣን በበኩላቸው ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ የከፋ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመደገፍ ያደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።

የድጋፍ ስምምነቱም በኢትዮጵያ የሚገኙ ችግረኞችን ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ የኳታር ቀይ ጨረቃ ማህበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ገልፀዋል፡፡ 

የኳታር ቀይ ጨረቃ ማህበር እና አክሽን ፎር ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ በ24 ወራት ጊዜ 768 የቤት ውስጥ መፀዳጃ ቤቶችን በስደተኞች መጠለያ ካምፖች አካባቢ ለመገንባት ተስማምተዋል። 

ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶችና ህፃናት የንፅህና መጠበቂያ እቃዎችን ለማቅረብ፣ ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን ለመገንባት እንዲሁም በውሃ ወለድ በሽታዎች ዙሪያ 240 ስልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚሰሩም የኳታሩ ገልፍ ታይምስ አስነብቧል።

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ጥቅምት 26/2010 የጥፋት ኃይሎችን በመመከት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአፋር ክልል የልዩ ድጋፍ ቦርድ በ2010 ዕቅድ ላይ ከክልሉ ሁሉም ወረዳና ዞኖ እንዲሁም ሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራሮች በተገኙበት የጋራ ምክክር መድረክ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

ፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በእዚህ ውቅት እንደተናገሩት በሀገሪቱ የተጀመረው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጎዞ አበረታች ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይሁንና በውጪ ያሉ የጥፋት ኃይሎች በአገር ውስጥ በብልሹ አሰራርና በኪራይ ሰብሳቢነት ከተዘፈቁ ኃይሎች ጋራ ተቀናጅተው የሀገሪቱን ሰላምና ልማት ለማደናቀፍ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

በተለይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደውና ፈቀደው በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የመሰረቱትን የፌዴራል ስርአት ቀጣይነት እንዳይኖረው ለማደናቀፍ የጥፋት ኃይሎቹ እያደረጉት ያለው ጥረት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን አደጋ በጋራ በመመከት የሀገሪቱ ሰላም ይበልጥ እንዲጠናከር የዴሞክራሲ ሥርአቱ እያደገ እንዲመጣና በመፋጠን ላይ ያለው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጠል ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ከበደ አስገንዝበዋል።

ሕብረተሰቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚደርግ ፈጣን ልማት በማረጋገጥና ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሀገሪቱን ሕዳሴ ማረጋገጥ እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ለእዚህም ባላፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስኬቶችን መነሻ በማድረግ ለቀጣይ ድሎች መረባረብ ይገባል" ብለዋል። 

የክልሉን አርብቶ አደር ሕብረተሰብ የልማት ጥያቄ ሊያረካ የሚችል የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ መሰረተ ልማት ሥራዎችን ማፋጠን ተገቢ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በተለይ በክልሉ ውሃን ማዕከል ያደረገውን የመንደር ማሰባስብ ፕሮግራም የበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል የሕብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት ለመቀየር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የፌዴራል መንግስትም የክልሉን ሁለንተናዊ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግና የሚያደርገውን እገዛ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አቶ ከበደ አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ስዩም አወል በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ የሰፈነው የፌደራል ሥርአት የፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በክልሉ አበረታች የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በተለይ የአርብቶ አደሩን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ሕብረተሰቡ ለልማት ምቹ በሆኑ አካባቢዎች ተረጋግቶ ሕይወቱን በዘላቂነት መምራት እንዲችል ለመድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙንም ሆነ ሌሎች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከፌዴራል መንግስትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ክልሉ ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ውይይት ላይ ከ250 በላይ የወረዳና የዞን እንዲሁም የክልል ሴክተር  መስሪያቤት አመራሮች ተሳትፈዋል ።  

Published in ፖለቲካ

ድሬደዋ ጥቅምት 26/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር የተከሰተውን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ (አተት) ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ የጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ።

የድሬዳዋ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የአተት በሽታ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በገጠርና በከተማ ተከስቷል።

በኃኪሞች የተዋቀረው የሕክምና ቡድን በተዘጋጁ ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያዎች ለሕሙማን ተገቢውን የጤና አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም ዶክተር ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በገጠርና በከተማ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከ13 ሕሙማን በስተቀር ሁሉም ድነው ወደየቤታቸው መመለሳቸውንም ዶክተር ሙሉቀን አመልክተዋል፡፡

በግልና በአካባቢ ንጽህና ጉድለት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ያለው ስርጭት እየጨመረ  እንዳይመጣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በ39 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ቤት ለቤት ተዘዋውረው ማስተማራቸውንም ተናግረዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን 20 ሺህ ለሚሆኑ ተማሪዎች ግንዛቤ መፈጠሩን ነው ያስረዱት።

“የውሃ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ በጊዜያዊነት ከማቅረብ በተጨማሪ የውሃ አጋር የማከፋፈልና ሕብረተሰቡ ውሃን አፍልቶ እንዲጠቀም የማድረግ ሥራ ተሰርቷል” ብለዋል፡፡

በተለይ በጎዳና ላይ ምግብ ለሚሸጡና ለሚመገቡ ለበሽታው እንዳይጋለጡ የማስገንዘብ ሥራ መሰራቱን ተናግረው፣ በሕመሙ የተያዙ ሰዎች በሚኖሩበት ቤትና አካባቢው የበሽታ አምጪ ተህዋሲያንን በኬሚካል የማጥፋት ሥራ መሰራቱን ዶክተር ሙሉቀን አስረድተዋል።

በድሬዳዋ “ሳቢያን” እየተበላ በሚጠራው አካባቢ በተዘጋጀው የአተት የሕክምና መስጫ ማዕከል ተኝተው እየታከሙ ከሚገኙት ሰዎች መካከል ተማሪ ኬይሪያ መሀመድ ድንገት የሚያጣድፍ ትኩሳትና ተቅማጥ ሲይዛት ወደ ማዕከሉ በመምጣቷ ሕይወቷ ሊተርፍ መቻሉን ተናግራለች፡፡

“ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ሥፍራ ስላመጡኝ ድኛለሁ፤ በበሽታው የታመመ ሰው ፈጥኖ ኃኪም ቤት መሄድ እንዳለበት ነው የምመክረው” ያሉት ደግሞ በአተት በሽታ ታመው የዳኑት ወይዘሮ ዘይነባ ዩያ ናቸው፡፡

በጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር የጤና ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ደለለኝ በበኩላቸው ባለፉት ሳምንታት በቀን በአማካኝ ሰባት ሰዎች በአተት በሽታ ተይዘው ወደማዕከሉ ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን በተገባደደው ሳምንት ወደማዕከሉ የሚመጣው ሰው ከሁለት እንደማይበለጥ ጠቁመው፣ ይህም የተቀናጀ የመከላከል ሥራው ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ማሳያ  ነው።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ጥቅምት26/2010 ኢትዮጵያዊነት በብሔር ብሔረሰቦች ትስስር የተገነባ በመሆኑ በቀላሉ የሚጠፋም ሆነ የሚደበዝዝ ማንነት አለመሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ በባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ ላይ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝብች የዘመናት ጥረት ትስስር የተገነባች ሃገር ናት።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ፣ በማንነቱ፣ በአንድነቱና በሕብረቱ የማይደራደርና በጠንካራ ገመድ የተሳሰረ የፀና ፍቅር ያለው ህዝብ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊነት በሀገሪቱ ህዝቦች የልብ ማህተም የታተመ በመሆኑ በቀላሉ የሚጠፋም ሆነ የሚጨልም ማንነት አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትናንሽ ጉዳዮች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች የአንድነታችንን ጥንካሬ እየተፈታተኑት ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣  አንዳንዴ የሚፈጠሩ ችግሮች 'ክስተቶች ናቸው' በማለት ከችግሩ ጋር የመላመድ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ማጠናከር የሚቻለው ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የህዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነት አጠናከሮ ማስቀጠል ሲቻል ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል።

"በሀገሪቱ ተዋደው፣ ተፋቅረውና ተሳስበው በሚኖሩ በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግንኙነት መካከል ምንም አይነት የሚከለክል አጥር ሊበጅ አይገባውም" ሲሉም አቶ ለማ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለእዚህች አገር አንድነትና ቀጣይነት የነገ አገር ተረካቢ የሆነውን ወጣት በስነ ምግባር በማነፅ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ማጠናከር የግድ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ አመልክተዋል።

የሀገሪቱ ምሁራንም ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለችግሮች መፍትሄ በመጠቆም ሙሁራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ አቶ ለማ ገለጻ፣ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የዘመናት ግንኙነት ለአፍታም ቢሆን ሳይቋረጥ ተጠናከሮ የሚቀጥል ነው።

"በሁለቱ ክልሎች የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ትስስር ከሌሎች ክልሎች ህዝቦች ጋርም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት አባ ገዳ ቱፋ ደራርሶ በበኩላቸው፣ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ለዘመናት በጉርብትና በዝምድና ተሳስረው የኖሩ ናቸው።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች ከአያት ቅድመ አያት የወረሱትን ጀግንነት ተላብሰውና መስዋዕትነት ከፍለው የአገራቸውን ዳር ድንበር በጋራ አስከብረው የኖሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

"በኦሮሞና አማራ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ አካላት ጥቅማቸው የተነካባቸው እንጂ ችግር መፍጠር የኦሮሞም ሆነ የአማራ ህዝብ መገለጫ ባህሪ ሆኖ አይደለም" ያሉት ደግሞ አባ ገዳ ፈቃዱ ባልቻ ናቸው።

" አብሮነታችን ለሰላማችን፣ ሰላማችን ለአብሮነታችን" በሚል መሪ ቃል የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ ትናንት ማምሻውን የተጠናቀቀ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዛሬ ዕለት የጣና ገዳማትን፣ ቤዛዊት ቤተ መንግስትና የአማራ ሰማዕታት ኃውልትን በመጎብኘት ላይ ናቸው።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን