አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 04 November 2017

ጎንደር ጥቅምት 25/2010 በሰሜን ጎንደር የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጁ በገጠሩ ህብረተሰብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት በማግኘቱ በሽታን በመከላከል ረገድ ለውጦች መመዝገባቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ፓኬጁን ተግባራዊ ያደረጉ ከ300ሺ በላይ አባወራና እማወራ አርሶ አደሮች የመጸዳጃ ቤት ተጠቃሚ በመሆናቸው ከተላላፊ በሽታዎች እራሳቸውን መጠበቅ መቻላቸውም ተመልክቷል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ደረሰኝ ፈንቴ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 20 የገጠር ወረዳዎች ባለፉት አመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ የህብረተሰቡን የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ልምድ አሳድጎታል።

"በዞኑ 126 ሺህ የተሻሻሉና 319 ሺህ የተለምዶ መጸዳጃ ቤቶች በህብረተሰቡ ተሳትፎ መገንባት ተችሏል" ያሉት ኃላፊው ይሔም ቀደም ሲል በንጽሕና ጉድለት ያጋጥም የነበረውን ተላላፊ በሽታ ለመከላከል እንዳስቻለ ተናግረዋል።

"ከዚህ ባለፈም አርሶ አደሩ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድ በማዳበሩም የግልና የአካባቢ ንጽህናውን ለማረጋገጥ አግዞታል"ብለዋል።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የደጎላ ጭንጫዬ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ስራሽ ጸጋው "እኔና ቤተሰቤ መጸዳጃ ቤት ሰርተን መጠቀም ከጀመርን ወዲህ በተለይ በዝንቦች ሳቢያ በህጻናት ላይ ያጋጥም የነበረውን የአይን በሽታ መከላከል ችለናል" ብለዋል።

"እንደ ተቅማጥ የሆድ ቁርጠትና ሌሎችንም በሽታዎች መቀነስ ችለናል" ያሉት ደግሞ በወገራ ወረዳ ይሳቅደብር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ማንጠግቦሽ ላቀው ናቸው።

በሰሜን ጎንደር በአሁኑ ወቅት በገጠሩ ክፍል ያለው የመጸዳጃ ቤት ሽፋን 40 በመቶ መድረስ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ ጥቅምት 25/2010 በደቡብ ወሎ ዞን ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል አርሶ አደሩ በብክነት በፀዳ መንገድ እየሰበሰበ መሆኑን የዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበራ ይመር እንደገለጹት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል በደረሳቸው የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ መሰረት የደረሰ ሰብልን ከተያዘው ወር  አጋማሽ ጀምሮ እየተሰበሰበ ነው።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም 27 ሺህ ሄክታር መሬት የደረሱ የጥራጥሬ፣ የማሾ፣ የስንዴና የጤፍ ሰብል ተሰብስቧል።

የደረሰው ሰብል ለከፍተኛ ፀሐይ የሚጋለጡ ከሆነ የምርት ብክነት ስለሚያጋጥም አርሶ አደሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰበሰብ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

የአቅመ ደካሞችንና የሴት አርሶ አደር ማሳዎችንም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም በጋራ የመሰብሰብ ስራዎች እየተካሄዱ ናቸው።

በመኸሩ ወቅት የለማው አብዛኛው ሰብል የሚደርሰው ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በመሆኑ የአርሶ አደሮችን፣ ሴቶችን፣ የወጣቶችንና ሌሎች አደረጃጀቶችን በመጠቀም ለመሰብሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡

በ2009/2010ዓ.ም የምርት ወቅት በተለያየ ሰብል ከለማው 412 ሺህ 500 ሄክታር መሬት አስር ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ኩንታል  ምርት ይጠበቃል፡፡

በቃሉ ወረዳ ፎንተኒና አካባቢ  አርሶ አደር ጀማል አህመድ በሩብ ሄክታር መሬት የዘሩት ማሾ በመድረሱ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመተባበር ሰብሰበው መውቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

በማጨድና በመሰብሰቡ ወቅትም የአካባቢው ወጣቶች እገዛ እንዳደረጉላቸውና በወቅቱ ሰብሉ ለብክነት ሳይጋለጥ መሰብሰባቸውንም ጠቁመዋል።

የቃሉ ወረዳ 06 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ከድጃ እንድሪስ የትዳር አጋራቸውን በሞት እንዳጡና የደረሱ ልጆች እንደሌላቻው ገልጸው የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉላቸው ትብብር የደረሰ ሩብ ሄክታር ማሾ ሰብላቸውን እንደሰበሰቡላቸው  ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሯ ከዚህ በተጨማሪ ማሳቸውን በመዝራትና በመንከባከብ አካባቢው ባደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው ተመሳሳይ የመኸር ወቅት  በተለያዩ ሰብል ከለማው መሬት ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡ 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ጥቅምት 25/2010  በጀት ዓመቱ ሶስት ሚሊዮን ለሚሆኑ  ፈቃደኛ ሰዎች  የጤና ምርመራ አገልገሎት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የኤች አይቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስፋትና ማጠናከር ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ውቤ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት  የኤች አይቪ ኤድስን የመከላከሉ ተግባር መቀዛቀዙን ተከትሎ የበሽታው ስርጭት  እየጨመረ መጥቷል።

የበሽታው ስርጭት በክልሉ ቀደም ሲል በተካሄደ ጥናት አንድ ነጥብ 32 የነበረው በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ነጥብ አምስት ከፍ ሊል እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡

"በተለይም በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያና ደብረ ማርቆስን ጨምሮ በ60 የክልሉ ከተሞች የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱ ተረጋግጧል" ብለዋል።

ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በተያዘው በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና ተቀዛቅዞ የቆየውን የመከላከልና የምርመራ ስራ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የስራ ሂደቱ  መሪ እንዳሉት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ በመፍጠር ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑት ፈቃደኛ ሰዎችን የጤና የምርመራ አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

ለመከላከል የሚያግዝ ከ50 ሚሊዮን በላይ ኮንዶም ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን ከአራት ሚሊዮን በላይ መከፋፈሉን አመልክተዋል።

የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶችም ከበጀታቸው ሁለት በመቶ ቀንሰው  30 ሚሊዮን ብር በመመደብ በተቋም ደረጃ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ስራ እያከናወኑ ነው።

በክልሉ ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመቱ 204 ሺህ ሰዎች መካከልም የፀረ-ኤች አይቪ መድኃኒት እየወሰዱ ያሉት 132 ሺህ መሆናቸውን ከጤና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ጥቅምት 25/2010 በሃዋሳ ከተማ በተለያየ የንግድ ስራ ከተሰማሩ ነጋዴዎች አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው ለገዟቸው ዕቃዎችና አገልግሎቶች ደረሰኝ እንደማይሰጡ አንድ ጥናት አመለከተ።

በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ በከተማዋ የሚገኙ የደረጃ ሀ እና የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች የተሳተፉበት ውይይት በሃዋሳ ከተማ ተካሒዷል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ደግፌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ባለስልጣኑ እና የከተማው ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ባካሔዱት ጥናት ውስጥ ከተካተቱ 231 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ለአገልግሎታቸው ደረሰኝ የሚሰጡት 19 ከመቶ ብቻ ናቸው።

እነዚሀ ነጋዴዎች በህጋዊዎቹ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውንና ድርጊቱ በድርጅቶቹ ባለቤቶችና ሃላፊዎች ሆነ ተብሎ የሚፈፀም መሆኑ ጥናቱ ማመልከቱን ተናግረዋል።

በጥናቱ መሰረት በሃዋሳ ከተማ ከሚገኙ 15 ሺህ 530 ደረጃ ሀ ፣ ለ እና ሐ ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ያላቸው 4 ሺህ 55 ብቻ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት በብልሽት ምክንያት የማይሰሩ ሲሆኑ የሚሰሩትንም ሰዋራ ስፍራ የሚያስቀምጡና ከንግድ ፈቃዳቸው ውጭ የሚሰሩም እንዳሉ ጥናቱ ማረጋገጡን ተናግረዋል።

ይሔም ከተማዋ ሊሰበሰብ ከሚገባው ገቢ እጅግ ያነሰ ከመሆኑም በላይ የምታከናውነው ልማት ላይም የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ በከተማው ነጋዴ ዘንድ እየተፈጠረ ያለው ችግር ከአመለካከት እንጂ ከግንዛቤ እጥረት የተከሰተ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተማረና የሰለጠነ ነጋዴ በሚሰራበት ከተማ ውስጥ ለተከሰተው ሰፊ ክፍተት እርምጃ ከመውሰድ በፊት በመወያየትና በመመካከር መግባባት ላይ ለመድረስ ችግሩ ካለባቸው ነጋዴዎች ጋር መምከር ማስፈለጉን አስረድተዋል።

ከዚህ ችግር ውስጥ በፍጥነት የማይወጡ ነጋዴዎች ካሉ የህግ የበላይነትን የማስከበርና እርምጃ የመወሰድ ተግባር እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊና በሃዋሳ ከተማ በባጀጅ መለዋወጫ እቃዎች ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ አዲስ አለማየሁ ጥናቱ የከተማውን ነጋዴ ቁመና ያሳየና የአመለካከት ችግር መሆኑንም ተናግረዋል።

"ለግብር ያለን አመለካከት ዝቅ ያለ ነው ቀደም ሲል ለግብር የነበረኝ ልምድ አነስተኛ ነበር" ያሉት ወይዘሮዋ ወደ ፊት የመጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደባህል አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሚከፈለው ግብር ለጋራ ጥቅም መሆኑን ባለመረዳት እራሳቸውን ጨምሮ በነጋዴው ዘንድ በስፋት ችግሩ የሚታይበት አጋጣሚ መኖሩን የተናገሩት ደግሞ በሉካንዳ ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ፍሬው በቀለ ናቸው። 

"በግብር አከፋፈሉ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥናቱ ውስጥ የነጋዴው ችግርም መታዬት ነበረበት" ሲሉም አስተያታቸውን ሰጥተዋል። 

ትላንት በተካሔደው ውይይት ላይ በሆቴል፣ ባርና ሬስቶራንት ፣ ልብስና ኤለክትሮኒክስ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ህንፃ መሳሪያ መደብሮች እና በሌሎችም የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ጥቅምት 25/2010 የአዋሽ ባንክ የገንዘብ አቅሙን እያሳደገ በመቀጠል ለሀገሪቱ  ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ፡

በንኩ ከ55 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በቢሾፍቱ ከተማ ያስገነባውን ባለ አራት ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት የአዋሽ ባንክ  ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ሀገሪቱ ኢኮኖሚ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቁመው  ባንኩ ለተለያዩ ክፍለተ ኢኮኖሚ የሰጠው የብድር መጠን ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለፃ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል።

በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ትርፍ በማስመዝገብ የመጀመሪያው የግል ባንክ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ከተመሰረተ 23 ዓመታት ማስቆጠሩን የተናገሩት አቶ ፀሐይ በነዚህ ጊዜያት የባንኩን ተደራሽነት ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ከ320 በላይ ቅርንጫፎችን በተለያዩ አካባቢዎች በመክፈት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"ዛሬ ለምረቃ የበቃው የአዋሽ አደአ ሕንፃ ለቢሾፍቱ ተጨማሪ ውበት በመሆን ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል "ብለዋል።

በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ባንኩ 25 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለሕዝብ ያለውን አጋርነት በተግባር ማስመስከሩን ጠቁመዋል።

የባንክና ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁለገብ ሕንፃ መርቀው የከፈቱት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዑመር ሁሴን  እንዳሉት ባንኩ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በፋይናንስ ዘርፉ በመሳተፍ ውጤታማ ሆኗል።

ባንኩ እያስገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል በኦሮሚያ በፋይናንስ ዘርፍ  የሚታየውን የተደራሽነት እጥረት ችግርን ለማቃለል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

ጠረፋማ በሆኑ የክልሉ አከባቢዎች ቅርንጫፎችን ለመክፈት በሚያደርገው እንቀስቃሴ የክልሉ መንግስት ከባንኩ ጎን እንደሚቆም አቶ ዑመር አረጋግጠዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ ጥቅምት 25/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄደው ጨዋታ የአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ቡድን ከመቀሌ አቻው ያለምንም ግብ ተለያዩ፡፡

የአርባምጭ ከነማ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ኳስ ይዞ በመጫወቱ ረገድ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

"ነጥብ የጣልንበት ምክንያትም በአማካይ ክፍል ብልጫ ወስደን መጫወት ባለመቻላችን ነው" ብለዋል፡፡

በአንጻሩ መቀሌለ ከተማ ጠንካራ የመከላከል እንቅስቃሴ ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር በሚኖራቸው  ጨዋታ አሸንፈው ለመውጣት ከወዲሁ ዝግጅት እንደሚደረግም  አሰልጣኝ ፀጋዬ ጠቁመዋል፡፡

የመቀሌ ከተማ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህለ በበኩላቸው  የዛሬው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

"በጨዋታ ታክትክ እርስ በርስ የማንተዋወቅ በመሆናችን በአብዛኛው ጥንቃቄ በተሞላበት  አካሄድ ተጫውተናል" ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ያደረጉት  የወዳጅነት ጨዋታዎች አነስተኛ መሆናቸውንና ለፕሪሚየር ሊጉ ዝግጅትም በቂ ጊዜ አለመኖሩን ፉክክሩ ከባድ እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል፡፡

"ከሜዳቸው ውጭ አቻ መውጣት ለቡድናችን መልካም ነው" ብለዋል፡፡

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2010 ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የማስፋፋት ስራ አገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ሊኖረው እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ህብረተሰቡን ያሳተፈ በአነስተኛ ወጪ ሁሉንም ማህበረሰብ በተለይም የገንዘብ አቅም የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት ሽፋን የሚያገኙበት አሰራር ነው።

የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 365 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ሲሆን፤የፕጀክቱ ውጤታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የአገልግሎቱን ተደራሽነት በየዓመቱ በመጨመር በሂደት በሁሉም የአገሪቱ ወረዳዎች ላይ ለመተግበር ታቅዷል።

በያዝነው በጀት ዓመትም አገልግሎቱን ወደ 536 ወረዳዎች ከፍ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ወረዳዎች ከአባላት መዋጮ የሚሰበሰበውን ገንዘብ አሁን ካለበት 600 ሚሊዬን ብር ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዬን ብር ለማሳደግም ታቅዷል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲን የ2010 ዓ.ም የሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ትናንት ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ እንደገለጹት፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች በህክምና አሰጣት ሂደት ለሚያነሱት ቅሬታ ምላሽ የሚያገኙበት አግባብ በህግ አልተደገፈም።               

''ኤጀንሲው አገልግሎቱ አዋጅ ጸድቆለት በህግ የተደገፈ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል'' ያሉት ወይዘሮ አበባ አዋጁን ለማጽደቅ  የሚደረገው ክትትል መፋጠን እንዳለበትም አሳስበዋል።  

የጤና መድህን አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማሻሻልና የሚፈለገውን ግብዓት ማሟላት እንደሚገባቸው ወይዘሮ አበባ አስገንዝበዋል።

የተለያዩ አካባቢዎቸ ላይ የተገኙ መልካም ተመክሮዎችን በማስፋት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኤጀንሲው በክልሎች ባቋቋማቸው ተቋማት ከአባላት የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ የሚደረገው ክትትል ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ አኖ እንደገለጹት፤ ከአባላት የሚሰበሰብ መዋጮው በወቅቱ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅት ተጠናቋል።

በፌዴራልና በክልሎች ባሉ ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር የሚፈለገውን ያክል አለመሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም በተቋማት መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 25/2010 የሶማሊያ መንግስት በፌደራሊዝምና ስልጣን ክፍፍል ላይ ልምድ የሚቀስሙበት አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አስታወቀ።

 አውደ ርዕዩ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ እና በኢጋድ የሶማሊያ ልዩ ተልእኮ አስተባባሪነት ከህዳር 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

 በኢጋድ የሶማሊያ ልዩ ተልዕኮ ላለፉት ዓመታት በሰላምና ደህንነት እንዲሁም ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ላይ ከሶማሊያ የፌደራል መንግስትና ክልል አስተዳደሮች ጋር በጋራ  ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

 የአውደ ርዕዩ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያና ኬኒያ በዘርፉ ያላቸውን የካበተ ልምድ ለሶማሊያ እንዲያካፍሉ እንደሆነም ተገልጿል።

 በተጨማሪ ከሶማሊያ የሚመጡ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተቋማት እንዴት እንደተዋቀሩና እስከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ እንዴት ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነ ልምድ ይቀስማሉ።

 የሶማሊያ የፌደራል ባለስልጣናትና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከፑንትላንድ፣ጁባላንድ፣ደቡብ ምዕራብ፣ጋልሙዳግ፣ሂርሼብሌ እና ባናዲር ክልሎች የሚመጡ ባለስልጣናት የዓውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ታውቋል።

 የሲቪክ ማህበራት፣ የሴቶችና ወጣቶች ቡድን እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን በዓውደ ርዕዩ እንዲሳተፉ ጥሪ እንደተደረገላቸው ኢጋድ በመግለጫው አስታውቋል።

Published in ፖለቲካ

ሶዶ ጥቅምት 25/2010 የሶዶ ኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱን ተገልጋዮች ገለፁ።

ተገልጋዮቹ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ ህክምና ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረው መጉላላት ቀርቶ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ችለዋል ።

ከኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ልጃቸውን ለማሳከም ወደ ሆስፒታሉ የመጡት አቶ ዘለቀ ዛውጋ በሰጡት አስተያየት በሆስፒታሉ በየደረጃው ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለተገልጋዩ የሚያደርጉት መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን የገለፁት ደግሞ ከሁምቦ ወረዳ አባታቸውን ለማሳከም የመጡት አቶ መርክነህ ጌታ ናቸው፡፡

በሆስፒታሉ እየተሰጠ ባለው ቀልጣፋ አገልግሎት በአንድ ቀን ውስጥ አባታቸው አልጋ አግኝተው  መታከም ችለዋል።

ከዳሞት ጋሌ ወረዳ ህክምና ፍለጋ የመጡት አቶ ዳዊት ሄጋኖ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ በዝምድናና በትውውቅ ላይ ተመስርቶ የነበረው አሰራር አሁን ላይ ተሸሽሎ ማየታቸውን ተናግረዋል ።

" አሁን ላይ ከሆስፒታሉ መግቢያ በር ጀምሮ እስከ ህክምና አሰጣጣጡ ባለው ሂደት የሰራተኞቹ ትህትናና መስተንገዶ የሚያረካ ሆኖ አግኝቸዋለሁ " ብለዋል ።

" በሆስፒታሉ መድኃኒት የለም በሚል ከግል መድኃኒት ቤት እንድትገዛ የሚሰጥህ ትእዛዝም ዛሬ ላይ ቀርቶ በመመልከቴ ተደስቻለሁ " ሲሉ ተናግረዋል ።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኦቶና የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር ብርሃነጸሃይ ተክለወልድ እንደገለፁት በተለያዩ ጊዚያት ከማህበረሰቡ ጋር በተደረጉ የውይይት መድረኮች የተሰበሰቡ አስተያየቶች ለመጣው ለውጥ አስተዋፆ አድርገዋል ።

" በተለይ የገልጋዩ ሲያማርር የነበረው የመድኃኒት እጥረት ችግር ለመፍታት መድኃኒቶችን የማሟላትና ተጨማሪ ሞዴል መድኃኒት ቤት በሶዶ ከተማ ከፍተናል " ብለዋል ።

በዚህ ዓመት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የመድኃኒት ግዥ መፈፀሙንም  ጠቅሰዋል ።

ከራጅና አልትራሳውንድ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የተነሱ ችግሮችን ለማቃለል ከ7 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ሁለት ዘመናዊ የራጅ መሳሪያዎች ተገዝተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል ።

ሌላው በሆስፒታሉ በነበረው የሀኪሞች እጥረት ህሙማን ወደ ሌላ የህክምና ተቋም በመላካቸው ይነሳ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት የ16 ባለሙያዎች  ቅጥር እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ የነበረውን ይዘት ሳይለውጥ ወደ ሪፈራልነት ማደጉ ለችግሩ መንስኤ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ሜዲካል ዳይሬክተሩ የተጠቃሚውን አስተያየት መሰረት በማድረግ የተጀመረው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ጥቅምት  25/2010 በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀው የአብሮነትና የአንድነት ትስስር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን  የሚያጠናክር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡

 " አብሮነታችን ለሰላማችን ሰላማችን ለአብሮነታችን " በሚል መሪ ሀሳብ  የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ተጀምሯል።

 አቶ ገዱ  በምክክር መድረኩ  "ኢትዮጵያዊነት በብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህብረት፣ አንድነትና መከባበር የተገመደ ሀገር ነው" ብለዋል።

 ኢትዮጵያ በህዝቦቿ የጠናከረ የእርስ በእርስ ግንኙነትም አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው   አጥር አድርገው ከወራሪ ጠላት ተጠብቃና ተከብራ የኖረች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

 ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነትም ስር የሰደደና ለረጅም ዘመናት በጉርብትና የዘለቀ ከመሆኑም በላይ በወግና ባህል ተሳስረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው እንደ አንድ የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው።

 የኦሮሞ ህዝብ ማንነቱ ቋንቋው፣ ወጉና ባህሉ በአማራ ህዝብ ዘንድ ተከብሮና ተጠብቆ እየኖረ መሆኑን አመለክተው " የአማራ ባህል፣ ወግና ቋንቋም እንዲሁ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተከብሮ የሚኖር ነው "ብለዋል።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን አንድነትና መጠናከር የማይመቻቸው አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት ሆን ተብሎ ቀን ከሌት በተቀነባበረ ሴራና የጥፋት ዘመቻ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

 ነገር ግን በአስተዋዩ ህዝቦች እምቢተኝነት የዕለት ከዕለት ተንኮሳዎቻቸውን በተባበረ ክንድ እየመከተ እንደሚገኝም አቶ ገዱ አስታውቀዋል።

 አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ ግጭቶችም ኦሮሞ  የአማራውን ሃብትና ንብረት በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ወንድማዊ አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ መቻላቸውን አመልክተዋል።

 በአማራ ክልል ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች እንደሚኖሩ ጠቅሰው  ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆ 257 ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት 100 ሺህ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉን ገልፀዋል።

 

 

 

 

 

 

 በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ለዘመናት የዘለቀው ማህበራዊ ግንኙነትና ትስስር አሁን ከሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ካለቸው ግንዛቤና አመለካከት በላይ የሚበልጥ መሆኑንም አቶ ገዱ አብራርተዋል።

 ወጣቱ ትውልድም ካባቶቹ የወረሰውን የአንድነትና የመተባበር ባህል በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

 በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ ትስስርም በሌሎች ህዝቦችም ቀጥሎ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንደሚያጠናክር ነው አቶ ገዱ የገለጹት፡፡

 የአማራ ክልል ህዝብ ያደረገላቸው አቀባበልና አክብሮት ወንማዊነቱን እንዲሁም ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳየበት መሆኑን የገለፁት ደግሞ አባ ገዳ ሁሴን በዳሳ ናቸው።

 " ትስስሩም የኦሮሞና የአማራ ህዝብ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

 መጋቤ ሰላም አብረሃም ዋላ በበኩላቸው በምክክር መድረኩ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ለረጅም ዘመናት በሰላም በፍቅር ተሳስበው የሚኖሩ ህዝቦች እንደሆኑ የተንጸባረቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

 የምክክር መድረኩ አሁንም ቀጥሎ በቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን