አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 03 November 2017

ነቀምቴ ጥቀምት 24/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ መንግሥት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ሰዎች የቀረበ የእርዳታ እህል  ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው የተከሰሱ አምስት  ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

 የፍርድ ቤቱ የወንጀል ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ዋቁማ ጡሪ  እንደገለጹት ግለሰቦቹ በጉቶ ጊዳ ወረዳ ሉጎ ቀበሌ  ሰብላቸው በበረዶ ለጠፋባቸው  አርሶ አደሮች  መንግስት ያቀረበውን 103 ኩንታል የበቆሎ እህል  እንደሚያከፋፍሉ አስመስለው በሰኔ ወር 2009  ከመጋዘን አውጥተው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፡፡

 በኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ሲጣራ ቆይቶ በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል፡፡

 ከሱን ሊከላከሉ ባለመቻላቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቅርቡ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከሶስት ወር እስራትና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ የወሰነባቸው መሆኑን  ዳኛው አረጋግጠዋል፡፡

 ተከሳሾቹ  ለግል ጥቅማቸው አውለው የተገኙት በ2008/2009 የምርት ዘመን  በጠፋው ሰብል ምክንያት የተጎዱትን አርሶ አደሮች ለመደገፍ መንግስት የላከው  የእህል  እርዳታ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መካከለኛ  ምዕራብ ቅርንጫፍ ዐቃቤ ሕግ አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው፡፡

 የአካባቢው ህብረተሰብ ለዕርዳታ የተላከው በቆሎ እየተሸጠ መሆኑን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ባደረሰው ጥቆማ  መሠረት የወረዳው  ፖሊስና ሌሎች ህግ አስከባሪዎች ባደረጉት ክትትል ግለሰቦቹ ተይዘው በህግ እንዲቀጡ በፍርድ ቤት በመክሰስ ማስፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ ጥቀምት24/2010 በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ህብረተሰብ አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት በአስተዳደሩ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ12 ሰዎችን ህይወት ህይወት አልፏል፡፡

በድሬዳዋ የትራንስፖርት ጽህፈት ቤት  የመንገድ ደንብ ማስከበር ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ገቢሳ እንደገለጹት በአስተዳደሩ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው፡፡

ይህም ስራ በበዓላት ፣ በአደባባይ፣ በየትምህርት ቤትና በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በየደረጃው ለሚገኘው ነዋሪ  የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ህብረተሰብ አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጓዳኝም በድሬዳዋ ለአደጋ የሚያጋልጡ በጥናት በተለዩ መንገዶች ላይ ምልክትና ማመላከቻዎች እየተለጠፉ መሆኑን ጠቅሰው  በከተማው ባሉ የአሽከርካሪ ትምህርት ቤቶች የትራፊክ አደጋን መከላከል  እንደ አንድ ጉዳይ እንዲማሩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

"የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ግለሰብና ቤተሰብ ጭምር ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል "ብለዋል ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ፡፡

"ለአደጋው ዋና መንስኤው እኛ አሽከርካሪዎች ያለብን የሥነ-ምግባር ችግር ነው፤ ለእግረኛ ቅድሚያ አንሰጥም፤ እንፈጥናለን "ያሉት የታከሲ አሽከርካሪው አቶ ኢብራሂም አደም ናቸው፡፡ 

በከተማው የተበላሸው መንገድም  በፍጥነት አለመጠገን  ለአደጋ መጋለጥ ሌለው ምክንያት እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ወጣት አብደላ ሁሴን የተባለው ነዋሪ በበኩሉ ከታክሲ ተገልብጦ ህይወቱ መትረፉን አስታውሶ በአደጋው አልጋ ላይ መዋሉ በቀን ሥራ የሚያስተዳድራቸው ቤተሰቦቹ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግሯል፡፡

የድል ጮራ ሆስፒታል ዋና ሥራ  አስፈጻሚ አቶ ሙሂዲን ረዲ  እንዳሉት በትራፊክ አደጋ ምክንያት የድንገተኛ የህክምና ክፍል ከፍተኛ ጫና እየተፈጠረበት ይገኛል፤ ችግሩ እየተባባሰ በመሆኑ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

ከሐምሌ 1/2009 መስከረም 30/ 2010  በተከሰተ የትራፊክ አደጋየ 12 ሰዎችን ህይወት ማለፉን፣ በ96 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጹት ደግሞ  የድሬዳዋ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ስታትስቲክስ ቡድን ኃላፊ ዋና ሣጅን ወንድወሰን እንዳለ ናቸው፡

በዚሁ አደጋ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው ንብረት መጥፋቱን ጠቅሰዋል፡፡

አምና በተመሣሣይ ወቅት በደረሰ የትራፊክ አደጋ 5 ሰዎች ብቻ መሞታቸውን ያስታወሱት ዋና ሣጅን ወንድወሰን 95 በመቶ ለአደጋ መከሰት ከአሽከርካሪዎች ጋር የተያያዘ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2010 በህክምና ተቋማት የሚስተዋለውን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ደም የማሰባሰብ ተግባሩን ሊያጠናክር እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።            

የምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎትን የ2010 ዓ.ም ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።  

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ የብሄራዊ ደም ባንክ አገልገሎት ለህክምና ተቋማት ማቅረብ ያለበትን ደም በሚገባው መጠን እያቀረበ አለመሆኑን ተናግረዋል። 

የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል እያደገ ቢመጣም ባንኩ ለልገሳው የሚያደርገው ቅስቀሳ ዝቅተኛ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል ብለዋል።   

በትምህርት ቤቶችና ተቋማት የደም ልገሳ ክበባትን በማቋቋምና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት ደም የማሰባሰቡ ተግባር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።        

ባንኩ በደም ልገሳ ወቅት የሚደረገውን የጤና ምርመራ ውጤት ለለጋሾች በወቅቱ የማድረስ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉበት የጠቀሱት ወይዘሮ አበባ ይህንንም ሊያስወግድ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚከናወነውን ደም የማሰባሰብ ተግባር ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎን የተመለከተው ሲሆን ባንኩ ለወጣቶቹ የሚሰጠውን ድጋፍና ክትትል እንዲያጠናክር አሳስቧል።  

የባንኩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ስዩም ባንኩ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት በትምህርት ተቋማት የደም ልገሳ ክበባትን ለማቋቋም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።       

በተቋማት ኩነቶች ላይ በመገኘት ደም የማሰባሰብ ተግባር ለመጀመር የሚያስችል አሰራር መቀየሱንም ነው  ዶክተር ብርሃኑ የተናገሩት።   

 ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በ2010 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ከ241 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ አቅዷል።        

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2010 የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀማቸው በአንድ ሄክታር ከ24-32 ኩንታል ተጨማሪ ምርት ማግኘታቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

 ተጨማሪ ምርት ማግኘት የቻሉት ዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የተሰኘ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ባደረገላቸው ድጋፍ ነው።

 ከጥቅምት 23-30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው 5ኛው የአረንጓዴ ንቅናቄ ሳምንት "በተፈጥሮ ግብርና የተመረተ ምግብ ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በውይይት ተጀምሯል።

 የንቅናቄ ሳምንቱ የድርጅቱ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶች በሚገኙባቸው አማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎችም በውይይት ይከበራል።

 የሆለታ ከተማ ነዋሪዎቹ አርሶ አደሮች ወርቄ ሹምዬ እና በቀለ ምናለ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ባደረገላቸው የስልጠና ድጋፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያና በርማ ኮምፖስትን በመጠቀማቸው ምርታማ መሆናቸውን ይናገራሉ።

 ቀላል የሆነውን የአመራረት ዘዴ በመጠቀም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 አርሶ አደሮች ቀደም ሲል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ተጠቅመው ያመርቱት የነበረው ምርት የአፈሩን ለምነት በመቀነስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማነታቸውን ሲቀንስባቸው መቆየቱን አውስተዋል።

 የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው ማምረት ከጀመሩ በኋላ የአፈሩ ለምነት ከመጠበቁ ባለፈ በአንድ ሄክታር ከ24-32 ኩንታል ተጨማሪ ምርት እያገኙ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 አንድ ጊዜ የተጠቀሙት የተፈጥሮ ማዳበሪያ እስከ አምስት ዓመት ድረስ የአፈሩን ለምነት ጠብቆ ስለሚያቆይ ከተጨማሪ ወጪ በመታደግ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

 የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአካባቢያቸው ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች ለማዘጋጀት በመቻላቸው ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ እንዳስቀረላቸውም አክለዋል።

 ከኬሚካል ንክኪ የጸዳውን ምርታቸውን ለራሳቸው የምግብ ፍጆታም ስለሚጠቀሙበት ጤናቸው እንዲጠበቅ እንደረዳቸው አብራርተዋል።

 በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ግብረ ሰናይ ድርጅት ከፍተኛ የማህበረሰብ አስተባባሪ ወይዘሮ አዜብ ወርቁ በበኩላቸው ድርጅቱ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች አቅም በመገንባት ዘላቂ የምግብ ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

 ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ስነ-ምህዳርን የጠበቀ የተፈጥሮ ግብርናን በማስፋፋት፣ ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት፣ ከአገር በቀል እውቀትና ባህል ጋር በማቆራኘት በቀላል ወጪ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉም ያግዛል ብለዋል።

 የተፈጥሮ ግብርና አመራረት ዘዴን መከተል የአፈሩን ለምነት ጠብቆ ከማቆየቱ ባሻገር ሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች ሲመረቱ የሚለቀቀውን የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት በመቀነስም የአየር ንብርት ለውጥ በመጠበቅ ጉልህ ድርሻ አለው ነው ያሉት።

 ዘላቂ ልማት መካነ ጥናት በአማራ፣ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ከሃያ ዓመት በላይ ይህን ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱንና በቀጣይ በሌሎች ክልሎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2010 ግንባታቸው የተጓተቱ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ምርት እንዲገቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስጠነቀቀ።

 የስኳር ኮርፖሬሽን የ 2010 በጀት ዓመት እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቦ ተገምግሟል።

 የጣና በለስ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ከዓለም ባንክ በተገኘ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ብድር ነበር በ 2003 ዓ.ም ግንባታቸው የተጀመረው።

 የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በ2004 ዓ.ም በማጠናቀቅ ወደ ምርት ለማስገባት እቅድ ቢያዝም እስካሁን ያለው አፈፃፀም የጣና በለስ አንድ ከ 78 በመቶ እንዲሁም ቁጥር ሁለት ከ 25 በመቶ አይበልጥም።

 በተመሳሳይ የኦሞ ኩራዝ አንድ፣ ሁለት፣ እና ሶስት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው የዜጎችን የስኳር ፍላጎት ማርካት አልተቻለም።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚያብሄር አርዓያ እንዳሉት፣ ግንባታቸው እየተጓተቱ መንግስትን ለኪሳራ ኅብረተሰቡን ለመልካም አስተዳደር እጦት የዳረጉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው።

 የችግሩ መንስኤ "የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ነው" ያሉት ሰብሳቢው፤ ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ለማጠናቀቅ አመራሩ ኃላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

 ኮርፖሬሽኑ በ2008 ዓ.ም፣ በ2009 ዓ.ም እንዲሁም በዚህ ዓመት ያቀረበው እቅድ "በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ" የሚል ተመሳሳይ ይዘት መያዙ በቋሚ ኮሚቴው አስተችቶታል።

 "በየዓመቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት ማቀድ አንድ እርምጃ ቢሆንም መሬት ላይ በተግባር የሚታይ ስራ ካልተሰራ ውጤቱ የዜሮ ድምር ነው" ብለዋል።

 ኮርፖሬሽኑ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ ኃላፊነት ቢሰጠውም፤ በተግባር ግን "ከውድቀት ወደ ውድቀት የሚሸጋገር ተቋም ሆኗል" ነው ያሉት።

 ኮርፖሬሽኑ በቂ ስኳር በማምረት ለአገሪቷ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ቢታሰብም የሚፈለገውን ያህል መጓዝ አልቻለም።

 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ የወጪ ንግድን የማሳደግ ኃላፊነት ቢጣልበትም የኅብረተሰቡን ፍላጎት እንኳን ማርካት ተገልጿል።

 በተመሳሳይ የፋብሪካዎቹ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ተተክሎ ጥቅም ላይ ሳይውል የሚወገድ የሸንኮራ አገዳ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ሳያደርግ፣ መንግስትን ለተጨማሪ ወጭ የሚዳርግ በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል።

 በመሆኑም የፋብሪካ ግንባታ፣ የመሬት አቅርቦትና አገዳ ተከላ፣ የመስኖ ግድብና የቤት ግንባታ ተቀናጅተው መሰራት እንዳለባቸው አቶ ገብረእግዚያብሄር አሳስበዋል።

 የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የስኳር ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አህመድ አብተው በበኩላቸው "በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ አመራሩ በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል።

 በተለይ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ የያዛቸው የበለስ ቁጥር አንድ እና የኦሞ ኩራዝ አንድ ፕሮጀክቶችን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ "በልዩ ትኩረት ይሰራል" ነው ያሉት።

 የግንባታዎቹ መጓተት በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ቅሬታን ከመፍጠሩ ባለፈ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን በመጠቆም።

 ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጭ ብድር ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች አገልግሎት የሚውል ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2010 በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍም ሆነ የህዝቦች የመረዳዳት ባህል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "የህዝቦች የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል!" በሚል ርእስ በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መላው ሕዝብ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገው የነቃ ተሳትፎና ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በተለይም ሰላምን በመጠበቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ተፈናቃዮችን በመርዳት፣ ድርቅን በመቋቋም፣ ልማትን በማፋጠን በኩልድርሻውን እየተወጣ  መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህንን ሚና አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት አመልክቷል።

በኦሮሚያና በሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስና በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘለቄታው መልሶ ለማቋቋም ልዩ ልዩ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ ይህንኑ ጥረት ለማገዝም ሰሞኑን ሦስት ክልሎች የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ በክፉም ይሁን በደጉ ጊዜ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዳላቸው ያወሳው መግለጫው፤ ከአብዝሃነታቸው አኳያ ያዳበሯቸው የመከባበር፣ በሰላም የመኖርና የመቻቻል፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻቸውም ዓለምን እንዳስደነቁ አብራርቷል።

የጽህፈት ቤቱ መግለጫ እንደገለጸው፤ ክልሎቹ ያደረጉት ድጋፍ ከቁሳዊ ጠቀሜታው በላይ የሚያሳየው ቁም ነገር አለ። ድጋፉ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የማይበጠስ ትስስርና መረዳዳት እንዳለ ያንጸባርቃል።

ድጋፉ "ኢትዮጵያውያን በልዩነታቸው ውስጥ የደመቀ አንድነት ፈጥረው የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው" ብሏል መግለጫው።

 

                         የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም.

የህዝቦች የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል!

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ-ሶማሊ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስና በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በዘለቄታው መልሶ ለማቋቋም ልዩ ልዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ይህንኑ ጥረት ለማገዝም ሰሞኑን ሦስት ክልሎች የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ከብሄራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የግጭቱ አጎራባች ክልሎች የሆኑት የሃረሪ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃዮችን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ግጭቶቹ ተከስተውባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የህዝብ ለህዝብ ድጋፍ ተስተውሏል።

በብሄራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካይነት ለተፈናቃዮቹ ማቋቋሚያ እንዲውል የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ላበረከቱት የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ በማስተናገድና በተለያየ መልኩ በመደገፍ ላይ ላሉት የሃረሪ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም ግጭቶች ተከስተውባቸው በነበሩ አንዳንድ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ አካባቢዎች ለታየው አኩሪ ኢትዮጵያዊ የህዝብ ለህዝብ መደጋገፍ ተግባር ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት እውቅና ይሰጣል፤ ምስጋናውንም ያቀርባል፡፡ ይኽው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ በክፉም ይሁን በደጉ ጊዜ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ናቸው። ከአብዝሃነታቸው አኳያ ያዳበሯቸው የመከባበር፣ በሰላም የመኖርና የመቻቻል፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻቸውም ዓለምን ያስደነቁ ናቸው፡፡ በታሪክ ሲወራረዱ የመጡት እነዚሁ ጠቃሚ እሴቶቻችን በአሁኑ ጊዜ በሕዝቦች መፈቃቀድ እውን በሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ይህ የሆነውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከታሪካቸው የወረሱት አብሮነታቸው አሁን ድረስ ስለዘለቀም ብቻ አይደለም። ይልቁንም የጋራ ጥቅማቸው በዘለቄታው ሊረጋገጥ የሚችለው በመፈቃቀድ አንድነታቸውን አጠናክረው ሲጓዙ መሆኑን ከልብ ተቀብለው፣  እየሄዱበት ባለው ትክክለኛና አዋጭ መንገድ መሆኑም ሊታወቅ ይገባዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ክልሎቹ ያደረጉት ድጋፍ ከቁሳዊ ጠቀሜታው በላይ የሚያሳየን ቁም ነገር አለ። ድጋፉ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ምን ያህል የማይበጠስ ትስስርና መረዳዳት እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል መላ ኢትዮጵያውያን በልዩነታቸው ውስጥ የደመቀ አንድነት ፈጥረው የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።

ድህነትን ታሪክ ለማድረግና በሂደትም አገራችን ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ማማ ከፍ ለማድረግ እንደምንችል በእርግጠኝነት እንድንናገር የሚያደርገንም በፌዴራላዊው ስርዓታችን አማካኝነት በአዲስ መልክ እንዲቃኝ የተደረገው ይኸው የሕዝቦች ትስስር  ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ህዝቦች በአካባቢዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው፣ የመሪነትና የፈፃሚነት ሚና እንዲጫወቱ ያስቻለው የፌዴራል ሥርዓታችን እያስመዘገባቸው ካሉ እያንዳንዱ የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ስኬቶቻችን ጀርባ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ማሰለፍ የቻለ ነውና። የአገራዊ ስኬቶቻችን ሁሉ ምንጭ ፌዴራላዊው ስርዓታችን  ነው፣ ወይም ደግሞ የፌዴራላዊው ስርዓት ባለቤትም ሆነ ጠባቂው ሕዝቡ ነው የምንለውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል።

እንደስኬቶቻችን ሁሉ ችግሮች ሲያጋጥሙንም የሚፈቱት በመላው ህዝባችን ተሳትፎ እንደሆነ ያለፍንበት ሂደት አስተምሮናል።  ኢትዮጵያውያን የበርካታ አንፀባራዊ ድሎች ባለቤት የሆኑት በየወቅቱ ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በጋራ እየፈቱ በመጓዛቸው እንጂ መንገዳቸው ሁሉ የተቃና ሆኖላቸው አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። አሁን ባለንበት ወቅትም ቢሆን ያጋጠሙንን እንቅፋቶች በዘለቄታው መፍታት የምንችለው በሕዝቦቻችን የጋራ ርብርብ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም መላው ሕዝባችን ሰላምን በመጠበቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ተፈናቃዮችን በመርዳት፣ ድርቅን በመቋቋም፣ ልማትን በማፋጠን እና በመሳሰሉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተጫወተው ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።  

Published in ፖለቲካ

አክሱም ጥቅምት 24/2010 የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም አባል ተማሪዎች በአካባቢው የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ አርሶአደሮችን እያገዙ ነው ተባለ።

 በተቋሙ የህግ ተማሪና የፎረሙ ፕሬዚዳንት ተማሪ ሽሙዬ አበራ እንዳለው፣ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቅ ዝናብ እንዳይበላሱ እየሰበሰቡ ያሉት ከ1 ሺህ 500 በላይ  ተማሪዎች ናቸው።

 እንደተማሪ ሽሙዬ ገለጻ፣ ተማሪዎቹ በተለይ የዕድሜ ባለጸጎችና አቅመ ደካሞችን ሰብል ቅድሚያ በመሰብሰብና እገዛ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።

"አርሶ አደሩ ዓመት ሙሉ የደከመበት ሰብል ከተበላሸ እኛም እንጎዳለን" ያለው ወጣት ሹሙዬ፣ ተማሪዎቹ የጀመሩት እገዛ ሰብሉ ተሰብስቦ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

 ዩኒቨርሲቲው ልዩ ልዩ የተማሪዎች ክበባትን በማቋቋም በትራፊክ አገልግሎት፣ በአካባቢ ጽዳትና በሌሎች ማህበራዊ ተግባራት ከሕብረተሰቡ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑንም ተማሪ ሽሙዬ አያይዞ ገልጿል።

 በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ጥበቡ ታደሰ በሰጠው አስተያየት፣ በፎረሙ አማካኝነት አርሶ አደሮችን በማገዙ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል።

 " የአካባቢው ሕብረተሰብ ለኛ ጥሩ አመለካከት አለው፤ ተንከባክቦናል" የሚለው ተማሪ ጥበቡ፣ ተማሪዎች በፈቃደኝነት ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ማድረጋቸው ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክር የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል።

 "በአቅሜ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ በማድረጌ ደስታ ተሰምቶኛል" ያለው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የማናጅመንት ተማሪ ፍቅረማርያም ብርሃኑ ነው።

 "በሰላም ፎረሙ የሚሰራው ሥራ ከማህበረሰቡ ጋር እርስ በርስ ያለንን መደጋገፍ የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይም ለልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ የማደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብሏል"

 "ሽማግሌዎችና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ነው የሰብል ማሰባሰብ ተሳትፎቻን ያጠናከርነው" ያለችው ደገሞ በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊ ተማሪ ሃይማኖት ጣፈጠ ናት።

 ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ስራ እንደተሰራ አስታውሳ፣ ዘንድሮም ተመሳሳይ ሥራ በመስራት እገዛቸውን ማጠናከራቸውን ተናግራለች።

 "በሌሎች ዩኒቨርሲቲ ያሉ የተማሪዎች ክበባት በጋራ በመሆን  ሕብረተሰቡን ማገዝ ይኖርባቸዋል " ስትልም ወጣት ሃይማኖት ገልጻለች።

 በተማሪዎቹ የሰብል መሰብሰብ ሥራ ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ወልደሃወርያት ካሳሁን እንዳሉት፣ ሰብላቸው በተማሪዎቹ መሰብሰቡ ለሠራተኛ ያወጡት የነበረውን ሁለት ሺህ ብር አስቀርቶላቸዋል።

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ጥቅምት 24/2010 በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የኬሚካል ርጭት ስራ እየተካሄደ ነው

 በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን እንደገለጹት የኬሚካል ርጭት ስራው እየተካሄደ ያለው   ከጥቅምት 22 ቀን 2010 ጀምሮ በአውሮፕላን በመታገዝ ነው፡፡

 የወፍ መንጋው የተከሰተው ወረዳዎች  ጅሌ-ጥሙጋ፣ ዳዋጨፋ ፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

 ቢሮውም ከፌደራል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና ችግሩ ከተከሰተባቸው ዞኖች ጋር በመተባበር የግሪሳ ወፍ መንጋው የሚያድርባቸውን ቦታዎች በባለሙያዎች ተለይቶ የኬሚካል ርጭቱ  ስራ መቀጠሉን አቶ አሻግሬ ተናግረዋል፡፡

 ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በአንድ ቀበሌ የታየው የወፍ መንጋ በወረዳዎች በዘጠኝ ቀበሌዎች መስፋፋቱን ጠቁመዋል፡፡

 እንደ ባለሙያው ገለፃ በወረዳዎቹ የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ ብዛት 11 ሚሊዮን ይገመታል ።

 በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ለሁለት ቀናት 35 ሄክታር ቦታ ላይ በተካሄደ የኬሚካል ርጭት የደረሰ የማሽላ ሰብልን ከመንጋው ጥቃት መታደግ መቻሉን ጠቅሰዋል ።

 "ለመከላከሉ ስራ 950 ሊትር የፀረ ግሪሳ -ወፍ ኬሚካል ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው" ብለዋል ።

 ከኬሚካል ርጭት ስራው በተጓዳኘ  አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ የግሪሳ ወፍ መንጋውን እየተከላከለ መሆኑን ባለሙያው ጨምረው ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2010 የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ምዝገባና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ።

 ኬሚካሎችን መመዝገብና ፍቃድ መስጠት፣ የኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜ ገደብ፣ የማምረትና ከውጪ የማስገባት ሂደት  ውይይት የተካሄደባቸው ጉዳዮች ናቸው።

 የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴዓታው አቶ ቆሬ ጫዋቻ ግብርናን በሚመለከት ከጸረ አረም ተባይና ሌሎች ከምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ ከኬሚካል ጦር መሳሪያዎችና ከጨረራ መከላከያ ውጪ ሌሎች ኬሚካሎችን የሚመለከት አዋጅ ባለመኖሩ ረቂቁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

 ረቂቅ አዋጁ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የሚያስችል አገራዊ ስርዓት በመዘርጋት የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት፣ ከማጓጓዝ፣ ከማከማቸት፣ ከማምረትና ከመጠቀም ሂደት ጋር ተያይዞ በሰውና በእንስሳት ጤና፣ በአካባቢ ደህንነት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

 ለረዥም ጊዜ በመከማቸታቸውና በአያያዝ ጉድለት የሚበላሹ ኬሚካሎችን በአደገኛ ኬሚካሎች አወጋገድ ስርዓት ለማስወገድ አዋጁ ማስፈለጉንም ነው የተናገሩት።

 አዋጁ ስራ ላይ ሲውል የግልጸኝነትና የተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት ኬሚካሎች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉና የአካባቢ ብክለት እንዳያስከትሉ ለመከላከል ያግዛልም ብለዋል።

 በረቂቅ አዋጁ ከውጭ የሚገቡና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ከ18 ወራት በታች የሆኑ ኬሚካሎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለው አንቀጽ  በአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች ስላሉ ቢስተካከል የሚል ሃሳብ ቀርቧል።

 በተጨማሪም የላቦራቶሪ ኬሚካሎችን በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ የተካተተ ነገር ባለመኖሩ ቢታይ የሚል ሃሳብም ተሰንዝሯል።

 ሚኒስቴሩ በአካባቢ ላይ ብክለት የሚያስከትሉ ነገሮችን በመለየት በበላይነት መከታታል ሲገባው  በዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባቱ በኬሚካል ግዥ፣ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ፣ በማምረትና ከውጭ በማስገባት ሂደቱ ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ሃሳብም   ተንጸባርቀቋል፡፡

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የኬሚካሎችን አወጋገድና ብክለት ከመቆጣጠር ባለፈ የቅድመ መከላከል ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

 በኬሚካል የሚደርሰውን ብክለት ለመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 በውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኬሚካል አምራቾችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

አምቦ ጥቅምት 24/2010 በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበር ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች የአምቦ ከተማ ነዋሪዎራች ከ600 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡

 የከተማዋ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ  ለኢዜአ እንደገለፁት ነጋዴዎች፣ የእድር አባላትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ድጋፉን ያደረጉት የተፈናቀሉት ወገኖች ለማቋቋም የሚደረገውን ርብርብ ለመደገፍ  በሚቻልበት ላይ  ከተወያዩ በኋላ ነው።

 ገንዘቡንም ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

 ተፈናቃዮቹን  ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት  የከተማዋ ህብረተሰብ እያሳየ ያለው ተሳትፎ አበረታች መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ድጋፍ የማሰባሰቡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

 ድጋፍ ካደረጉት መካከል  በከተማዋ በንግድ ስራ የተሰማሩት  አቶ መስፍን ተክሌ በሰጡት አስተያየት የተፈናቀሉት ወገኖች ለመርዳት  አቅማቸው የፈቀደውን ያክል በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ከዚህ በፊትም በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚውል ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሳቸውን ይታወቃል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን