አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 02 November 2017

ጅማ ጥቅምት 23/2010 በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግዱና አፍራሽ ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላትን እንደሚያወግዙ በጅማ ከተማ የሚገኙ የሐይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች አስታወቁ።

የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ በጅማ ከተማ ተካሒዷል።

ከተሳታፊ የሃገር ሽማግሌዎች መካከል የከተማው ነዋሪ ሃጂ  መሀመድ በድሩ እንደተናገሩት ሰሞኑን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥፋቶች የኦሮሞን ህዝብ የማይወክሉ ናቸው።

አደጋውን ከመከላከል ጎን ለጎንም በከተማቸው የተለየ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ እንግዳ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሌላው የኮንፍረንሱ ተሳታፊ መምሬ ሽፈራው ከበደ "ሁሉም የሚከተለው ሀይማኖት ጥቃትና በደል በሌሎች ላይ መፈጸም ስለማይፈቅድ ይህ አይነቱን ተግባር ልናወግዝና ልንርቅ ይገባል "ብለዋል።

"በተለይ ቤት አከራዮችና ባለ ሆቴሎች ማንነቱ ለማይታወቅና አድራሻ ለሌለው ግለሰብ አገልግሎት ከመስጠት ልንቆጠብ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ የሀገር ሽማግሌ አብዱራህማን ታጁ በበኩላቸው "የኦሮሞ ህዝብ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥላቻ ኖሮት አያውቅም" ብለዋል።

"ኦሮሞ እንደማንኛውም የሀገሪቱ ብሄረሰቦች አንድነትን፣ሰላምንና ልማትን አጥብቆ የሚሻ ነው" ያሉት የሀገር ሽማግሌው ሰሞኑን በክልሉ የተፈጸሙ ጥፋቶች ህዝቡን እንደማይወክሉ አስረድተዋል።

መንግስት አጥፊዎችን አድኖ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀው የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማደፍረስ አስበው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ግለሰቦች ላይም ተገቢው ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል።

የሰላም ኮንፍረንሱን የመሩት የጅማ ከተማ ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ደመቀ የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡን በመምከርና በማስተማር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው መሆኑን ገልጸው አጥፊዎችና በችግሩ ውስጥ እጃቸው ያለ አካላትን በማጥራት እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።

በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ 150 የሚሆኑ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ  ጥቅምት 23/2/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን በሕብረተሰቡ ላይ የሚስተዋለውን መዘናጋት በመመለስ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ  ስርጭትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

 በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት በዞኑ ከ54 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎት መሰጠቱ ተመልክቷል።

 በመምሪያው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስፋፋትና ማጠናከር የሥራ ሂደት ባለሙያ አቶ ሰለሞን ለቤዛ እንዳስታወቁት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሽታውን በመከላከል በኩል ሕብረተሰቡ እየተዘናጋ መጥቷል።

 በእዚህም በዞኑ በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና በተለይም ወጣቱ ለአደጋው የበለጠ ተጋላጭ መሆኑን አስረድተዋል።

 ባለሙያው እንዳሉት፣ ችግሩን ከግምት ውስጥ ያስገባ የመከላከያ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የማስተማር ሥራ እየተከነወነ ይገኛል።

 ለእዚህም በሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶች ኤች.አይ.ቪን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እንደሌሎች የሥራ መስኮች ዝርዝር ዕቅድ ወጥቶለትና  በውጤት እየተለካ እንዲሄድ የማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።

 "ለዕቅዱ ማከናወኛም ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት በመቶ ገንዘብ እንዲመድቡና በትክክል ለመከላከሉ ሥራ እንዲያውሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተተገበረ ነው" ብለዋል።

 ከእዚህ ጎን ለጎን በየደረጃው ተቋቁመው የቆዩ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ማህበራትን እንደገና በመንግስት በጀት በማጠናከር ሕብረተቡን የማስተማርና የመቀስቀስ ሥራቸውን እንዲያጠናክሩ በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

 እንደአቶ ሰለሞን ገለጻ፣ በእዚህ በጀት ዓመት 429 ሺህ በላይ ዜጎች በፈቃደንነት ላይ የተመሰረተ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎቱ እንዲያገኙ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 54 ሺህ ዜጎች ተመርምረዋል።

 በመመርመሪያ ኪት እጥረት ምክንያት የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ማከናወን እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ባለው መሳሪያ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራቱን አመልክተዋል።

 ምርመራ ካደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች 448 የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ሲሆን ከ55 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ተብሏል።

 በሽታውን ለመከላከል ሲባልም ከ6 ሚሊዮን በላይ ኮንደም ለተጠቃሚዎች እንዲቀርብ መደረጉን አቶ ሰለሞን የገለጹት።

 በሞጣ ከተማ "ሕይወት ብሩህ ተስፋ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ማህበር" ሊቀመንበር መቶ አለቃ ተመስገን አስሬ  ‹ትውልድ ይዳን በኛ ይብቃ› በሚል መርህ ሲደረግ በነበረው ንቅናቄ ጥሩ ውጤት ተገኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

 አሁንም ለተወሰነ ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረውን ትምህርትና ንቅናቄ በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደገና እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

 በደብረማርቆስ ከተማ "ቤዛዊት ኤች.አይ.ቪ/ኤዲስ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች ማህበር " ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት አበበ በበኩላቸው በየትምህርት ቤቱ በመዘዋወር የሕይወት ምስክርነት ቃል ለመስጠት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

 ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ከበጎፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመቀናጀትም ተመርምረው እራሳቸውን ያለወቁ የማህበረሰብ ክፍሎች ራሳቸውን እንዲያውቁ፤ መድኃኒት የጀመሩም እንዳያቋርጡ የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

 በየሴክተሩ "የቡና ጠጡ ፕሮግራም" እንዲጠናከርና በቦታው በመገኘት ውይይቶችን በጋራ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው ወይዘሮ ትዕግስት ጠይቀዋል።

 በዞኑ ከ35ሺህ በላይ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑት መድኃኒት ጀምረዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2010 የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይልና በመሰረተ ልማት ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ገለፁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሀይለሚካኤል በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደርንና የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር ሀላፊ ጋር የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።

የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር በጀርመን ውስጥ 600 ኩባንያዎችን ያቀፈ በአለም ላይ ትልቅ ኔትወርክ ያለው የቢዝነስ ማህበር ነው።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሚስ ብሪታ ዋግነር የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋእለ ነዋያቸውን በሚያፈሱበት ሁኔታ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።

ባለሀብቶቹ በሀገሪቱ በማኑፋክቸሪንግ፣በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እና በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር ሀላፊ ዶክተር ስቴፋን ሌቢንግ በበኩላቸው ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የጀርመን ባለሀብቶች በግብርና እና በአውቶሞቲቭ ዘርፎች ስኬታማ መሆናቸውን ገልፀው ወደፊትም በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሀይለሚካኤል ኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ሀይል  ፍላጎት እንዳላት ገልፀው የማህበሩ አባላት በዚሁ ዘርፍና በግድቦች የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

የባለሀብቶቹ ወደዚህ መምጣት ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

ከአንድ ምእተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮ - ጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት በይፋ የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1905 ነበር።

Published in ፖለቲካ

ፍቼ ጥቅምት 23/2010 በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል 130 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለገሱ፡፡

የዞኑ አደጋ ስጋትና  ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢሊዮን ሙዳ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በሱማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ገንዘቡን የለገሱት በፍቼ ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ነጋዴዎች፤ ባለሃብቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

ተፈናቃዮችን  ለማቋቋም  የዞኑ አስተዳደርና ነዋሪዎች ከቤት ቁሳቁስ ጀምሮ  እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲልም በዞኑ 11 ወረዳዎች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ከደመወዛቸው በመቀነስ ለተፈናቃዮች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ  ለመስጠት መወሰናቸውንም ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

የዞኑ የሀገር ሸማግሌ አቶ ማሞ በላቸው በሰጡት አስተያየት ወንድማማች በሆኑ ህዝቦች መካከል  ግጭት በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎች ተለይተው ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ችግር እንኳን ቢኖር በሰላማዊ መንገድ መፍታት  ሲገባ  የለአግባብ  ዜጎችን ከመኖሪያ ቄያቸው ማፈናቀል ተገቢ እንዳልሆነ በመጥቀስ   ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2010ኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎቿን ከአውሮፓ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በኔትወርክ ለማስተሳሰር እየሰራች መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምዕራብና ደቡብ አፍሪካ አገራት ስብስብ የሆነውና የአገራቱን ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማትን ለማስተሳሰር የሚመክረው  "ኢምቡቱ ኔት ኮኔክት" ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎችንና የምርምር ተቋማትን በኔትወርክ ማስተሳሰር ለትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ያለው ሚና፤ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር  ውጤቶች ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችሉ ስልቶችን ማስቀመጥና ልምድ መለዋወጥ ጉባኤው የሚያተኩርባቸው ነጥቦች ናቸው።

በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም አሰፋ እንዳሉት አገሪቱ  ዩኒቨርስቲዎቿን እርስ በርስ በኔት ወርክ በማገናኘቷ ለንደን በሚገኘው ኢንቡቱ ኔት ኮኔክት ለመግባት ፈቃድ አግኝታለች።

ይህም ከአውሮፓ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላት ሲሆን ዓለም ዓቀፍ ተቋማትንና የምርምር ማዕከላትን የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ከአለም አቀፍ አቻቸው ጋር የመጻህፍት፤ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን ለማግኘትና ምርምሮችን በጋራ እንዲሰሩና ሌሎች ሃብቶችን  እንዲጠቀሙ ያደርጋልም ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ተማሪዎች በሚፈልጉት የትምህርት ክፍል ያሉ የትምህርት ይዘቶችን በክፍል ውስጥ ከተማሩት በተጨማሪ በቪዲዮ መልክ ማግኘት እንዲችሉም የአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትስስሩን ለመፍጠር የተወሰኑ ስራዎች እንደሚቀሩ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በሶስትና አራት ወራት ውስጥ ሁሉንም ዩኒቨርስቲዎች ከአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እናገናኛለን ብለዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመመረቂያ ጹህፎችና የምርምር ውጤቶች የሚቀመጡበት የመረጃ ቋት በዚህ አመት ተግባራዊ እንደሚሆን አንስተዋል።

ይህም ሁሉንም የመመረቂያ ጹሁፎች በአንድ ቋት በማዘጋጀት እያንዳንዱ ጹሁፍ በአገርና በአለም አቀፍ የሚታወቅበት የራሱ መለያ እንዲኖረው በማድረግ ተግባራዊ ይደረጋል።

ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ ማንኛውም ተማሪ ከመመረቁ በፊትና ጥናት ከሰራ በኋላ በሶፍት ኮፒ የማስረከብ ግዴታ እንዲኖርበት በዚህ አመት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የዚህ አሰራር ትልቁ አላማ እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ጥናት ፤ የመመረቂያ ጹሁፍ፤ ጆርናል በአለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው።

አፍሪካ ለአለም የምታበረክተው ጥናትና ምርምር ከ2 በመቶ የማይበልጥ ሲሆን ቀሪው 98 በመቶ በኤሲያ፤ አውሮፓና በምዕራባውያን እንደሚያዝ በመድረኩ ተነስቷል።

 

 

 

አክሱም ጥቅምት 23/2010 በአክሱም ከተማ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የጽዮን ማርያም በዓል ለቱሪዝም ልማት እንዲውል በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ተጠየቀ ።

በየዓመቱ ህዳር 21 ቀን የሚከበረውን የአክሱም ጽዮን ማርያም በዓልን ዘንድሮ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በበዓሉ ዝግጅት ላይ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹምብርሃነ እንደገለፁት በከተማው በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ አካላት አሰራራቸውን በማሻሻል ለቱሪዝም ዘርፍ መጎልበት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ።

አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሰራራቸውን ማሻሻልና ማጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በተለይ በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች በበዓላት ወቅት ያልተገባ ዋጋ በመጨመርና ክፍያን በዶላር የመጠየቅ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው ያስታወሱት አቶ ገብረ መድህን ተቋማቱ የቱሪስት ፍሰትን ከሚቀንሱና ቅሬታ ከሚያስነሱ ድርጊቶች ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስገንዝዋል።

"አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያን በመጠየቅ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

እንደ አቶ ገብረመድህን ገለጻ በከተማው ያሉትን የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችና ጥንታዊ ቅርሶችን ለማስተዋወቅ 70 ገፅ ያሉት መረጃ ሰጭ መጽሔት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ተሰራጭቷል።

በአክሱም ከተማ  "የኮንስላር ኢንተርናሽናል" ሆቴል ሥራ አኪያጅ አቶ ኃይለማርያም ተካልኝ በሰጡት አስተያየት ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶችና ቱሪስቶች ተገቢውን አገልገሎት በመስጠትና ተመጣጣኝ ክፍያ በማስከፈል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተነግረዋል።

በከተማው ያለውን የሆቴሎች ማህበር በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጡን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"በበዓላት ወቅት የሆቴል ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች ሳያውቁ ሠራተኞቻቸው ስህተት ሊፈጥሩ ይችላሉ" ያሉት ደግሞ  የሳቢያን ኢንተርናሽናል  ሆቴል ባለቤት አቶ ተክለ ገብረስላሴ ናቸው።

ይህንን ለማስተካከል ሠራተኞችን ከመቆጣጠር ባለፈ የደንበኞችን ቅሬታ መስማት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቱሪስቶች ዘንድ ቅሬታ የሚያስነሱ ችግሮችን ለመከላከልና በሚሰጠው አገልግሎትም እርካታ እንዲሰማቸው የድርሻቸውን አንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ባለሆቴሎቹና ሥራ አስኪያጆች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ጭማሪ እንደማያደርጉ ገልጸው፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስተካከል በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጧዋል

Published in ማህበራዊ

ሰመራ  ጥቅምት 23/2010 ሕብረተሰቡ በፌዴራል ስርአቱና በህገ መንግስቱ ላይ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት ተሰሚነት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የጎላ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

 ከየክልሉ የተወጣጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት "ፌዴራሊዝም፣ ህገመንግስትና ብዝሃነት በኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ  በሰመራ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

 በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የግጭት  አፈታት ፣የሰላም፣እሴት ግንባታና  የንቃተ  ህገ መንግስት  ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ ጽሁፉን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ሕዳር 29 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው።

 ከእዚህ በተጨማሪ ክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖራቸውና በእዚህም ብሔር በሔረሰቦች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መምጣቱን አመልክተዋል። 

 ሕብረብሔራዊ የፌዴራል ስርአቱ ከተጀመረ አጭር ግዜ በመሆኑ በሥርአቱ አስተሳሰቦች፣ መርሆዎች፣ ምንነቶችና ልዩ ባህሪያቶች ላይ በሁሉም ደረጃ ወጥና የተሟላ ግንዛቤ አለመኖሩን ተናግረዋል።

 አቶ አስቻለው እንዳሉቱ፣ ብሔር ብሔረሰቦች የቆየ የመቻቻል እሴቶቻቸውን እንዲያዳብሩና የፌደራል ሥርአቱን ለማስቀጠል በህገ መንግስቱ መርሆዎችና በፌዴራል ስርአቱ  ልዩ ባህሪያት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።

 ከብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ጋር ተያይዞ የሚዘጋጁ  የህዝብ መድረኮች በፌዴራል ስርአቱና በህገመንግስቱ ዙሪያ ሕብረተሰቡ ያለውን ገንዛቤ የበለጠ የሚያጎለብቱ መሆኑን ገልጸዋል።

 የሀገርሽ ማግሌዎችና፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የሴቶችና የወጣት አደረጃጀቶች በህገ-መንግስታዊ የፌዴራል ስርአቱ ላይ ያገኘኑትን  ትምህርትም ለሕብረተሰቡ በማሳወቅ ግንዛቤውን ማሳደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 "በእዚህም የሰላምና መቻቻል እሴቶች በህዝቡ ውስጥ የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል

 ከትግራ ክልል የመጡት ወይዘሮ ጃኖ ንጉሴ፣ የብሔር በሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት ያረጋገጠውን ህገ መንግስትና የፌዴራል ስርአቱን በተመለከተ በየመድረኩ የሚገኘውን እውቀት ሌሎች እንዲገነዘቡት ከማድረግ አንጻር ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። 

 በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች ከዚህ የመነጩ በመሆኑ በቀጣይ ችግሩን ለመከላከልና የሰላም እሴቶችን በማስተማር ልማቱን ለማፋጠን እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

 ከድሬደዋ ከተማ መስተዳድር የመጡት የሃይማኖት አባት ቄስ ለተብርህን ቀለመወርቅ በበኩላቸው በከተማቸው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እንዲሁም የህዘቡ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲጠናክር ከመስተዳድሩ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 በየደረጃው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች የሰላም አሴቶችን ለማጎልበት በየቤተ-እምነቱ ምዕመናኑን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

 ከአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የመጡት ሼህ ሰኢድ መሃመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ዞኑ ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ወረዳዎች ቀደም ብሎ ይነሱ የነበሩ ግጭቶችን በመፍታት ሕብረተሰቡ  በአንድነት ተከባብሮ እንዲኖር ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

 መድረኩ በግጭት አፈታት ላይ መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም ያስቻላቸው በመሆኑ " በቀጣይ ከመድረኩ ያገኘሁትን ጠቃሚ ልምድ ለሌሎች በማካፈል ኃላፊነቴን በአግባቡ እወጣለሁ" ብለዋል

 በቀጣይ ሕዳር ወር መጨረሻ በአፋር ክልል የሚከበረውም 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዘቦች ቀን በዓል ምክናያት በማድረግ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ መድረክ  ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

 በመድረኩም ከየክልሉ የተወጣጡ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል ።

 

Published in ፖለቲካ

ሽሬ እንዳስላሴ   ጥቅምት  23/2010 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ታህታይ ቆራሮ ወረዳ አንድ ባለሀብት ከ230 ሽህ ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነቡትን የንጹህ መጠጥ ውሀ ተቋም ትናንት ለአካባቢው ህብረተሰብ አስረከቡ።

 ባለሃብቱ ተቋሙን ያስገነቡት የመጠጥ ውሀ ችግር በነበረበት በወረዳው ልዩ ስሙ  አዲ ምብሉ በተባለ የገጠር ቀበሌ ነው።

 ባለሀብቱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ያስገነቡት  የውሀ  ተቋም በእጅ የሚሰራ ፓምፕ የተገጠመለና  ከ180 በላይ የአካባቢው ነዋሪ ህብረተሰብ አገልግሎት እንደሚሰጥ የወረዳው ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይረጋ ኃይሌ ገልፀዋል።

 ባለሀብቱ አቶ አሊ መሐመድ ኪያር በበኩላቸው " ሳይማር ያስተማረንን ህዝብ ከመደገፍና ከማገዝ የበለጠ ደስታ የሚሰጥ ነገር የለም፣ ስለሆነም አቅሜ የፈቀደውን ተቋም ገንብቼ ለህብረተሰቡ ሳስረከብ ታላቅ እርካታ ተሰምቶኛል"ብለዋል ።

 የታህታይ ቆራሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብራሃለይ አበራ በበኩላቸው በባለሃብቱ የተገነባው የመጠጥ ውሃ ተቋም  ቀደም ሲል በቀበሌው የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ማቃለሉን ተናግረዋል፡፡

 የባለሃብቱ መልካም ስራ ለሌሎች አርኣያ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

 ከቀበሌው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አሚና በያን በሰጡት አስተያየት የተቋሙ መገንባት  ከዚህ ቀደም ውሀ ፍለጋ ከሁለት ሰዓት በላይ  በሚያደርጉት ጉዞ ይደርስባቸው የነበረው እንግልት እንዳስቀረላቸው  ተናግረዋል ።

 "ማለዳ ስንነሳ የሚያስጨንቀን የመጠጥ ውሃ አለመኖር ነበር"ያሉት ሌላው ነዋሪ አቶ መረሳ በላይ በአካባቢያቸው  ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ችግራቸው መቃለሉን አመልክተዋል።

 በትግራይ ክልል ገጠርና ከተማ አካባቢዎች  መንግስት በመደበው  700 ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነቡ ያሉት የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁም አሁን ያለውን የ63 በመቶ የውሃ ሽፋን በ10 በመቶ እንደሚያሳድገው ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2010 የመንግስት የልማት ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማቸውን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ። 

የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቴክኖሎጂ ፎረም "የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት ምርታማነታቸውንና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እናሳድጋለን" በሚል መሪ ሀሳብ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ተካሂዷል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው መንግስቴ በፎረሙ ላይ እንደተናገሩት የልማት ድርጅቶች ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎታቸውን እና አቅማቸውን የማሳደግ ስራ መስራት አለባቸው፡፡

ድርጅቶቹ ከአደጉ አገሮች ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትን ወደራሳቸው አምጥተው በማላመድ አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ አስደግፈው ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ተቋም መፍጠር የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በፎረሙ በ2010 ዓ.ም በመንግስት የልማት ድርጅቶች ስር የሚገኙ የ17 ተቋማት አዳዲስ ቴክኖሎጂን በአሰራራቸው ሊተገብሩ የሚችሉበትንና በዘርፉ ያላቸውን ፍላጎት በሪፖርት መልክ ቀርቧል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አዳዲስ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ለፎረሙ አባላት አስጎብኝቷል፡፡

ፎረሙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሳደግ የተወዳዳሪነት አቅማቸውን እንዲገነቡ፤ እርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እንዲያካሂዱ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተነሳሽነትን እንዲያሳድጉ ማድረግ ግብ  መሆኑም ነው በዚሁ ወቅት የተገለፀው።

የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የልማት ድርጅቶች የፎረሙ አባላት ናቸው።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ፎረም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና የሳይበር ደህንነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ሚያዚያ 16 ቀን 2009ዓ.ም ተመስርቷል፡፡

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2010 በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው እንዲመለሱ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎች ሰብሳቢ አስታወቁ።

የሁለቱም ክልሎች የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት ግጭቱን በጋራ ለመፍታት መወያየታቸው ይታወቃል።

የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎች ሰብሳቢ ገራድ ኩልምየ ገራድ መሀመድ እንደተናገሩት የጎሳ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ግጭቶችን በመፍታት ረገድ እየሰሩት ያለውን ስራ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ሁለቱ ህዝቦች የሚጋሯቸው በርካታ እሴቶች እንዳሏቸው የጠቆሙት ገራድ ኩልምየ፤ "በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ እንዲጀምሩ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች አበክረው ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም  ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ገራድ ኩልምየ በተፈጠረው ግጭት ማዘናቸውን ገልጸው፤ ጦርነትና ግጭት የሚያስከትለውን ችግር ከጎረቤት ሶማሊያ መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በተለይ ወጣቶችን በማስተማር ረገድ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በሁለቱም ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ኮንፍረንሶች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲሰፉ መንግስት በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

ግጭት የነበረባቸው  አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በፍጥነት መመለሳቸውን የተናገሩት ገራድ ኩልምየ "ይህም ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ እንዳልሆነ ያሳያል" ብለዋል።

እነዚህ በደም የተሳሰሩ ወንድማማች ህዝቦች በቅርቡ ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው በመመለስ በጋራ እንደሚኖሩም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋሙ ስራ ጠንክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የትግራይ፣ አማራና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር በማውጣት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን