አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 14 November 2017

ዶሃ ህዳር 5/2010 ኢትዮጵያና ኳታር በኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሚመራው ከፍተኛ ልዑክ በኳታር ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆን የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ዛሬ በቤተ መንግስታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አገራቱ በተለይም ስምምነቱ በዲፕሎማቶች ቪዛ አሰጣጥ እና የኢንቨስትመንት ጥበቃ ዘርፍ በጋራ መስራች የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

የቪዛ አሰጣጡና ፓስፖርትን በሚመለከት የተደረገውን ስምምነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኳታሩ አቻቸው  ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ ጋር ተፈራርመዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና የኳታሩ የኢኮኖሚና ንግድ ሚኒስትር አህመድ ቢን ጃሲም ደግሞ የኢንቨስትመንት ጥበቃ ስምምነቱን ፈርመውታል።

የፊርማ ስነ-ስርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የኳታሩ ኢምር ሸክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን፤  ስምምነቱ በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስር ሃይለማርያም ደሳለኝ በኳታር እያካሄዱት ያለው ጉብኝት በጋራ ጥቅም ላይ  የተመሰረተውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ ነው።

የኳታሩ ኤሚር ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አገራቱ የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች አተገባበር ላይ ውይይት እንደሚደረግም ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በባህረ ሰላጤው ያለው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኩዌት እያደረገችው ያለውን ጥረት እንደምትደግፍም ዶክተር ወርቅነህ ገልጸዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኳታር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያውያኑ ስለ አገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲያውቁ ከማድረግ አንጻር ውጤታማ እንደነበርም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአገራቸው ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በሚያድግበት ሁኔታ ላይ ሃሳብ እንዳነሱ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያኑ በሁሉም የልማት ዘርፎች አገራቸውን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳሳዩም ጠቁመዋል።

በኳታር ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገመታል።  

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ኅዳር 5/2010 የትግራይ ክልል ባህል ማህበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር 122 ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ።

ማህበሩ በመቀሌ ከተማ ዘመናዊ የባህል ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

የትግራይ ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ከክልሉ በተለያዩ መንገዶች ወደ አውሮፓ አገራት ተወስደው የነበሩ 122 ጥንታዊና ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እንዲመለሱ ተደርጓል።

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የቀደምት ጥንታዊ ስልጣኔና የዘመን አቆጣጠር የሚገልጹ የብራና መጻህፍት ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪም ከወርቅ፣ ከብርና ከነሀስ የተሰሩ መስቀሎችን ጨምሮ የተለያዩ ቅርሶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

"ቅርሶቹ በመቀሌ አፄ ዮሐንስ ቤተመንግስት ሙዚየም ውስጥ በክብር ተቀምጠው ለጎብኚዎች እይታ እንዲውሉ ተደርጓል "ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቅርሶቹን በማስመለስ ሂደት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለ ድርሻ አካላትና የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ።

በተያያዘ ዜና ማህበሩ የክልሉ ሕዝብ ማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ አሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት፣ ለማስተዋወቅና ኪነጥበባዊ በሆነ መንገድ ለእይታ ለማብቃት የሚያገለግል የባህል ማዕከል በመቀሌ ከተማ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የመቀሌ ከተማ መስተዳድር ለማዕከሉ ግንባታ የሚሆን 50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነጻ መስጠቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የማዕከሉ የግንባታ ዲዛይን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በነጻ አየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ማዕከሉ ዘመናዊ ሙዚየም፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የቴአትርና ሙዚቃ ማሰልጠኛ፣ የባህልና ቋንቋ ምርምር ማዕከል፣ የህጻናት መዝናኛ ስፍራ ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ይኖሩታል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በህዝቡ፣ በተቋማትና በባለሀብቶች ትብብር የሚሸፈን ነው ።

ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የትግራይ ባህል ማህበር ለክልሉ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ መጎልበት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን አስረድተዋል።

ከ36 ሺህ በላይ የማህበሩ አባላት ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ህዳር 5/2010 የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ስራ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሜትሮሎጂ  ትንበያ መረጃ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴሽን ልማት ዳይሬክተር አቶ ወንድያለህ ሀብታሙ እንደገለፁት የሜትሮሎጂ  ትንበያና ምክረ ሃሳብ ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ 

ይህም የመረጃ ፍሰቱን በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት፣ፈጣን፣ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያ ለአርሶ አደሩ  ተደራሽ በማድረግ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ  ያስችላል፡፡ 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  ሀገሪቱ  የደረሰችበትን  የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት መሰረት ያደረገ የሜትሮሎጂ  ትንበያ፣ የመረጃ ፍሰት ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ ፣የግብርና ትራንስፎርሜሽንና የሜትሮሎጂ  ኤጄንሲዎች የጋራ ግብረ ሃይል አቋቁመው እየሰሩ ናቸው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የአየር  እርጥበት፣በኤልኒኖና ላኒኖ ክስተት ላይ የተሟላ መረጃ በመስጠት ሀገሪቱ በድርቅና ጎርፍ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀልበስ እንዲቻል የሜትሮሎጂ ትንበያ መረጃ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ በበኩላቸው  ኤጄንሲው በሀገሪቱ  1ሺህ 300 በሰው የሚመዘገቡ የአየር ትንበያ መሳሪያዎችና በ240 አውቶማቲክ መመዝገቢያ ማዕከላት መረጃ በመሰብሰብ ለህብረሰተቡ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጤና፣ትራንስፖርት፣ግብርና፣የአየር ንብረት ተለዋወጭነት ባህሪያት ተፅእኖና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የሜትሮሎጂ ምክረሃሳቦችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ኢሳያስ ለማ እንደገለፁት በአየር ትንበያ፣በሰብል በሽታዎች መከላከል፣በዓመቱ ሊኖር የሚችለው የዝናብ መጠን፣የቅድመ ምርትና ድህረ ምርት ትንበያዎች ሲያከናወን ቆይቷል፡፡ 

በዚህም በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብና ትግራይ ክልሎች ለአርሶ አደሩ ምርት ውጤታማነት አስተዋፅኦ እንደነበረው አመልክተዋል።

በየ10 ቀናት የአየር ፀባይ ትንተና በማድረግና ምክረ ሃሳቦችን አደራጅቶ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በተፈጥሮ ሀብት፣በእርጥበት አያያዝ፣በውሃ ማቋር፣በአፈር ጥበቃና በደን ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ማድረግ ተችሏል አስችሏል።

በዞንና በወረዳ ደረጃ የአየር ፀባይ ትንበያ ባለሙያዎች ያለመኖር መረጃውን እስከ ቀበሌ ድረስ ለማውረድ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው ክፍተቱን ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ጠቅሰዋል፡፡

የፌደራልና የክልሎች ግብርና ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ፣የምርምር ማዕከላት ፣የሜትሮሎጂ  ኤጄንሲና ሌሎች አጋር ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበት መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አመልክተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ  ህዳር 5/2010 በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዘንድሮ  ከ625 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት በአነስተኛ መስኖ  ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት በመስኖ ልማቱ ከሁለት ሚሊየን በላይ  አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ፡፡

በዘመኑ የአነስተኛ መስኖ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት የመጨመር ስራ ቀዳሚ ተግባር ይሆናል፡፡ 

እያንዳንዱ አርሶ አደር በግል አልያም በቡድን አስተማማኝ የውሃ አማራጭ እንዲኖረው የማድረግና የመስኖ ፓኬጅ ተከትለው እንዲያለሙ ይደረጋል፡፡

ለማልማት ጥቅም ላይ ከሚውሉት የውሃ አማራጮች መካከል ዘመናዊና ባህላዊ መስኖ ፣ ወንዝን ጨምሮ የገጸ ምድር ውሃ  ይገኙበታል፡፡ 

ለልማቱ አገልግሎት የሚውሉም በእጅ ያሉ 32 ሺህ የሞተር ፓምፕ፣  ከአምስት ሺህ በላይ አዳዲስ የውሃ ማውጫና ማሰራጫ ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርቡም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ እንዲሁም የዘርና ተጓዳኝ ግብአቶች አቅርቦት ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

" ግብዓቱ በተደራጀ ሁኔታ በግብርና ምርት ማሳደጊያና አቅራቢ ድርጅት፣ በደቡብ ገበሬዎች ህብረት ስራ ፌደሬሽንና ዩኒየኖች አማካይነት ይቀርባሉ "ም ብለዋል፡፡

ከምርት ሂደት እስከ ግብይት ድረስ ጣልቃ በመግባት የገበያ ትስስርና የግብይት ስርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ይሰራል፡፡

በጉራጌ ዞን የመስቃን ወረዳ አርሶ አደር ሙሊዩ ዘርጋ በአካባቢያቸው የከርሰ ምድር ውሃ ለመስኖ ተጠቅመው ቡናና አቮካዶ  እንደሚያለሙ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ሄክታር ማሳቸው ከጉድጓድ ውሃ በተጨማሪ የዝናብ ውሃ ማጠራቀም፣ የጅረት ውሃን መሳብና ሌሎች የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በወረዳው የተቦን ቀበሌ አርሶ አደር ብሩክ አሸቴ በበኩላቸው  ሞዴል አርሶ አደር ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረው ለሚያለሙት የፍራፍሬና አትክልት ልማት መስኖን የመጀመሪያው አማራጭ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቆሎንም በብዛት እንደሚያመርቱ የጠቆሙት አርሶ አደሩ የጉድጓድ ውሃ ተጠቅመው አቮካዶ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በማህበር ተደራጅተው የውሃ መሳቢያ ሞተር ለመግዛት ዝግጅት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመት  571 ሺህ ሄክታር በመስኖ መልማቱም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ህዳር 5/2010 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚነት ትግራይን  በመወከል  ለውድድር የታጩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እራሳቸውን ማግለላቸው በክልሉ ተቀባይነት አገኘ፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ  የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ፕሬዝደንት አቶ ሕሸ ለማ  በሰጡት መግለጫ  ራሳቸውን  ከውድድሩ ያገለሉት የአቶ ተክለወይኒ አሰፋ ፌዴሬሽኑ ተቀብሎ ዛሬ ማፅደቁን አስታውቀዋል፡፡

ክልሉን በመወከል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለስራ አስፈፃሚነት የሚወዳደር ምትክ ሰው በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የድርሻውን  የሚወጣ ፣ስፖርቱ በሁሉም ክልሎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲነቃቃ  ሙያዊ ብቃትና  የአመራር ክህሎት  ያለው ሰው ከክልሉ ለመወከል  እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ፌዴሬሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በመገናኛ ብዙሃን ባስተላለፉት ያልተገባ ንግግር ተከትሎ በፈጸሙት ስህተት ይቅርታ በመጠየቅ ራሳቸው ከውድድር ማግለላቸውን ትናንት ተገልጿል፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 5/2010 ኢትዮጵያ የምታከናወናቸውን የልማት ሥራዎች ለመደገፍና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውንም ለማጠናከር እንደሚሠሩ በኢትዮጵ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ከአገሪቷ ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የአስር አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል። 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚካኤል አርተር እንዳሉት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን በአፍሪካ ቀንድና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ስትሰራ ቆይታለች።

በቀጣይ ጊዜያትም ግንኙነቱን በማጠናከር በተለይም በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ሂደት የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም የአሜሪካ ባለ ኃቶብቶች  በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በአምባሳደርነት የሥራ ዘመናቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።   

 

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው  በሥራ ዘመናቸው በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በቀዳሚነትም የኢትዮጵያን የልማት ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸው የጀርመን ባለኃብቶችና የንግድ ማኅበረሰቦች በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ እንደሚሰሩ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የሚካሄዱ የፖለቲካና ምጣኔ ኃብት ማሻሻያዎችን በመደገፍ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በጤናና በትምህርት ጉዳዮች ለውጥ እያመጣች መምጣቷንና አገራቸውም እንደ ምሳሌ እንደምታወሳት የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የኡጋንዳ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሬቤቻ አሙግ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመንግሥታቱ ድርጅት የምታከናውናቸውን ተግባራት ሀገራቸው እንደምትደግፈውም ነው የገለጹት።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት  ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩና በተለይም እ.ኤ.አ በ2063 "የምንሻትን አፍሪካ ለመፍጠር በጋራ እንሰራለን" ነው ያሉት።   

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ጆን ቦርግስታም ደግሞ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ከኅብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ግንኙነት ለማጠናከርና በተለይም ኢትዮጵያና ኅብረቱ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸውን አጋርነት እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዛሬው ዕለት የጆርዳን፣ የኩባ፣ የስዊዲን፣ የማዳጋስካር፣ የስዊዘርላንድንና የአየርላንድን አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤም ተቀብለዋል።

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ ህዳር 5/2010 የሞሪንጋ ተክል ከምግብነት ባለፈ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን መስጠት እንዲችል በምርምር መስክ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቀዳማዊ እምቤት ሮማን ተስፋዬ አሳሰቡ፡፡

"የሞሪንጋን ዕምቅ አቅም ለላቀ ጥቅም ማዋል" በሚል መሪ ቃል በሞሪንጋ ተክል ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ሞሪንጋ (ሀለኮ) በሚበቅልባቸው አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ለምግብነት እየተጠቀመበትና በንጥረ ምግብ ይዘቱ የበለጸገ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ አልተሰራም፡፡

ወይዘሮ ሮማን እንዳሉት በሕብረተሰቡ ላይ በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩና ከአጠቃቀም በሚስተዋሉ ውስንነቶች የተነሳ ከተክሉ ማግኘት የሚቻለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘት እየተቻለ አይደለም፡፡

"በሞሪንጋ ተክል ላይ የተለያዩ ችግር ፈቺ ምርምሮች እየተካሄዱ ቢሆንም የዘርፉ ተመራማሪዎች ተክሉ ሊሰጠው ከሚችለው ጠቀሜታ አንጻር አሁንም ገና ያልተዳሰሱ በርካታ ጥናትና ምርምር የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉ በመረዳት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል፡፡

የሞሪንጋ ተክል ከምግብነት ባለፈ በተለያዩ መንገዶች ተቀነባብሮ ለመድኃኒትነት፣ ለመዋቢያ ምርቶች ግብዓትነት፣ ለእንስሳት መኖነትና ለአፈር ለምነት ጥቅም ላይ ለማዋል ከሌሎች ሀገሮች ምርጥ ተሞክሮ መቀመርና በጥናት መደገፍ እንደሚገባም ቀዳማዊት እመቤቷ አሳስበዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ሞሪንጋ (ሀለኮ) እየተባለ የሚጠራው ተክል ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ለማድረግ በመስኩ በርካታ ምርምሮች እየተካሄዱ ናቸው፡፡

በዋናነት በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ሰገን ሕዝቦችና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በስፋት የሚበቅለውን ይህን ተክል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አዲስ ግኝቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር በመስኩ ለሚከናወኑ ምርምሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ባለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሳምንት ውስጥ ተክሉ ትኩረት ተሰጥቶው ውይይት እንዲደረግበት ተወስኖ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በተወካያቸው በኩል እንዳሉት በክልሉ መንግስት የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሀ ግብር በሞሪንጋ ማቀነባበር ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

እንደርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ሞሪንጋ በክልሉ የምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳለውና ይህንን በሳይንሳዊ ዘዴ ደግፎ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡

በተክሉ ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ለማገዝ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

የሞሪንጋ ተክል በአካባቢው አጠራር ሀለኮ እና ሽፈራው በመባል ይታወቃል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

አዲስ አበባ ህዳር 5/2010 ኢሕአዴግና አራት አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አዋጅ ዝርዝር ማሻሽያ አንቀፆች ላይ ተደራደሩ።

የ11ዱ ተዳራዳሪ ፓርቲዎች ጥምረት 'ምርጫ ቦርድ' የሚለው ስያሜ ወደ 'ምርጫ ኮሚሽን' እስካልተቀየረ ድረስ ምንም ሐሳብ ባለመስጠት  በታዛቢነት ድርድሩን ተከታትለዋል።

ኢሕአዴግ፣ ኢራፓ፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ መኢብንና መኢዴፓ ምርጫ ቦርድ የሚለውን ስያሜ ለማስለወጥ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት እስካላቀረቡ ድረስ 11ዱ ፓርቲዎች ያነሱትን ሐሳብ አልተቀበሉም።

በመሆኑም በዛሬ ውሎ በምርጫ ቦርድ አዋጅ ዝርዝር ማሻሽያ አንቀፆች ላይ ከኢሕአዴግ ጋር የመደራደሪያ ሐሳብ አቅርበዋል።

ኢሕአዴግና አራት አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርዱ አዋጅ 532/99 ከ1 እስከ 61 ያሉት አንቀፆች ላይ የተደራደሩ ሲሆኑ፤ በነገው ውሏቸው ደግሞ ከ62 እስከ 111 ባሉት አንቀፆች ላይ ለመደራደር ዕቅድ ይዘዋል።

አራቱ ተደራራዳሪ ፓርቲዎች በዋናነት በምርጫ አዋጁ አንቀጾች ላይ መሻሻልና መጨመር አለበት ያሉትን የድርድር ሐሳብ አቅርበዋል።

ፓርቲዎቹ ከቦርዱ ዋና ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉትን ጽህፈት ቤቶች ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች የሚመረጡበትን አሰራር መዘርጋት ፤ ቦርዱ ከድጎማ ወደ ቋሚ በጀት መምጣት፤ የምርጫ ሂደቱ ከሰነድ ወደ ኤሌክትሮኒክስ መሸጋገር አለበት የሚሉ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቶች ከሐይማኖት ፣ ከትምህርት ፣ ከሆስፒታሎችና ሌሎች መሰል ተቋማት በምርጫ አንቀጾች ላይ ያለው ርቀት እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አንቀፆች መሻሻል አለባቸው የሚሉ ሐሳቦችም በፓርቲዎቹ ቀርበዋል።

የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ሠራተኞች ከዚህ በፊት ገለልተኛ፤ የክልሉ ሰዎችን አወዳድሮ ይቀይርበት የነበረውን አሁን በተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠው ተጠያቂነታቸው ለቦርዱ እንዲሆኑና እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺህ ባይበልጥ የሚለው ከ1 ሺህ 500 አይብለጥ በሚል እንዲተካም ሐሳብ ቀርቧል።

በተጨማሪ እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ገለልተኛ የሆኑና በሕዝብ የሚመረጡ ከአምስት ያልበለጡ የሕዝብ ተታዛቢዎች የሚለውን ከሦስት እስከ አምስት በሚለው መተካት እንዳለበትም ነው ፓርቲዎቹ የመደራደሪያ ሐሳብ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በበኩሉ፤ የቦርዱ በጀት ቋሚ መሆን፣ በትምህርት ወቅት ከትምህርት ቤቶች የምርጫ ቅስቀሳ 500 ሜትር መራቅ አለበት፤ የእምነትና ሌሎች ተቋማት አካባቢ የማይፈቀድ መሆኑን፣ የዋና ይሁን የክልል ቅርንጫፎች ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች እንዲመረጡ አሰራቧ በግልጽ ማስቀመጡን አንስቷል።

የምርጫ ሥነ-ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ ሊካሄድ ይገባል የሚለውን ሐሳብ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ፤ ከመሰረተ ልማት ዕድገትና አቅርቦት አንጻር ማገናዘብና ማየት ይገባል ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

በአጠቃላይ በገዥው ፓርቲ አዋጁን ተፈፃሚ ከማድረግ ክፍተት ይኖራል፤ በተመሳሳይ በተፎካካሪም ፓርቲዎች ሕግና ሥርዓት ያለማክበር ችግሮች ይታያሉ የሚሉ ሐቦች ቀርበዋል።

ሁሉም ለፖለቲካዊ ሥነ-ምህዳሩ መስፋትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ ተገልጿል።

የ11ዱ አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ ይዘትና የሥራ ድርሻ ላይ ከመደራደር በፊት የምርጫ ቦርድ 'በምርጫ ኮሚሽን' ስያሜ መተካት አለበት በማለት የፀና አቋሙን አንጸባርቋል። 

ኢሕአዴግ በበኩሉ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ስያሜ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ስነ-ምህዳር ጥበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዕድገት አኳያ ስያሜውን ሊያስቀይር የሚችል ምክንያት ይቅረብና እንወያይበት፤ ካልሆነ አንቀይርም የሚል አቋም ይዟል።

Published in ፖለቲካ

ደብረ ብርሃን  ህዳር  5/2010  በአማራ ሰሜን ሸዋ አካባቢ የተጀመሩ  የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመግታት የህዝቡ የተቀናጀ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ከህዝብ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ህዝብ ባለፉት ዓመታት ሰላሙን በመጠበቅ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ የክልሉ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

በተለይ የደብረ ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፍ እያደገች የመጣችው አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ወደ አካባቢው የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ  ባለሀብቶች ከመጨመር ጋር ተያይዞ  ለስራ ፍለጋ ፈልሰው የሚገቡ   የነዋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም  አመልክተዋል ፡፡

በዚህም ሳቢያ ከቅርብ ወራት  ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉትን የወንጀል ድርጊቶችን ለመግታት በሚያስችልት ላይ ከህዝብ ጋር ለመምከር ደብረ ብርሃን መገኘታቸውን አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ብሎም  ለመግታት ህዝቡ እያደረገ ያለውን  ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበትም  አሳስበዋል

የኃይማኖት አባቶችም ሰላምን በማስተማር ወላጆችም ልጆቻቸውን በመምከር ለተሻለ እድገት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው "መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል "ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊሰ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ምንወየለት ጭንቅሎ በበኩላቸው በአካባቢው የወንጀል ደርጊቶችን ለመግታት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባባር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማው ጨለማን ተገን በማድረግ ህይወት አጥፍተዋል፣   የመግደል ሙከራ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ትናንት መያዛቸውንም አመልክተዋል፡፡ 

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሊቀ ዻዻስ አቡነ ቀለኒጦስ  የሀገር እድገት የሚፋጠነው የአካባቢው ህዝብ ሰላምን ሲያሰፍን በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም መክረዋል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መርሻ ሀይሌ በሰጡት አስተያየት የአካባቢውን ልማትና ሰላም መጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ 

በከተማው  የሺሻ ቤቶች መበራከት ለወንጀል ድርጊቶች አመቺነት ስላላቸው  መንግስት እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል፡፡

በግለሰብ መኖሪያ ቤት አከራይና በተከራይ መካከል ያለው ሂደት በህጋዊ መንገድ በማስፈፀም ተሸሸጎ የመፈጸም ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል ደንብ መውጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ 

መቶ አለቃ ላቀው  ተሰማ የተባሉት ነዋሪ  በበኩላቸው ሰላምን ለማወክ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚናፈስ  አሉባልታ ቦታ ሳይሰጡ የአካባቢያቸውን ልማት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ 

ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ጨምሮ  ከ300 በላይ የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ ህዳር 5/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኙ የኦህዴድ አባል የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት ድርጅታዊ ጉባኤ በነቀምቴ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ዛሬ በተጀመረውና ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የኦህዴድ 7ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ከ400 በላይ የድርጅቱ አባል የመንግስት ሠራተኞች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ኢዳኤ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ጉባኤ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወኑ ተግባራትና በታዩ ክፍተቶች ዙሪያ ውይይት ይካሄዳል፡፡

እንዲሁም በአመራሩና በአባላቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮች በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ  እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑንም አቶ ሞገስ አስታውቀዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሱፐርቫይዘር አቶ ዓለምሰገድ ደብሳ በበኩላቸው በጉባኤው በክልሉና በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

"በአሁኑ ጊዜ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት አባላቱ ራሳቸውን በማየትና በመገምገም ለቀጣይ ውጤታማ ስራ እንዲነሳሱ ያደርጋል" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን