አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 13 November 2017

ማይጨው ህዳር 4/2010 በትግራይ ክልል ለተቋቋሙ የምርጥ ዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የተሻለ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በማይጨው ከተማ የተቋቋመው የ"ሐድነት ራያ" የምርጥ የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ዩኒየን በ6 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸውን አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች ትላንት አስመርቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሃ በዛብህ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ 60 የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ማህበራት ተቋቁመዋል።

ማህበራቱ በተቋቋሙ አጭር ጊዜ ውስጥ የጀመሩት የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ለእዚህም በ2008/2009 የምርት ዘመን 10 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ማምረታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ይሁንና ላመረቱት ምርት የገበያ ችግር እንደገጠማቸው የገለፁት ኃላፊው፣ ለምርታቸው የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

አቶ ፍስሀ እንዳሉት፣ የወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በየአካባቢያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮችን የዘር ፍላጎት በመለየት ማህበራቱ ካቋቋሟቸው ዩኒየኖች ዘር በመግዛት የሚያቀርቡበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ለምርጥ ዘር ምርት ግዥ የሚውል ገንዘብም ከክልሉ መንግስት የሚመደብ ነው።

በተጨማሪም ማህበራቱ ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል ።

ከእዚህ በተጨማሪ ማህበራቱ በመኸር ወቅት ብቻ የሚያካሂዱት የዘር ብዜት ሥራ በቂ ባለመሆኑ በበጋ ወቅት በመስኖ የታገዘ ልማት እንዲያካሂዱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።

በአምባላጌ ወረዳ ብርሃን አይባ የገበሬዎች የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ማህበር አባል ቄስ ግርማይ ሐጎስ በሰጡት አስተያየት በ2009/2010 የመኸር ወቅት በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ምርጥ የስንዴ ዘር ማባዛታቸውን ተናግረዋል።

"ምርጥ ዘሩንም በማህበራቸው አማካኝነት በመሸጥ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ተስፋ አድርጊያለሁ" ብለዋል።

የ"ሐድነት ራያ" የምርጥ የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ዩኒየን ካስመረቃቸው ሕንጻዎች ውስጥ 10 ሺህ ኩንታል የሚይዝ  የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲሁም የዘር ጥራትና ብቅለት ሂደት ምርምራ ቤተ-ሙከራ ይገኝበታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቱ ህዳር 4/2010 በመቱ ዩኒቨርሲቲ የተወሰኑ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት የመማር ማስተማር ሥራው መስተጓጎሉን አንዳንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች እንዳሉት በተቋሙ  ባለፉት 10 ቀናት በቂ ባልሆነ ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱ የተስተጓጎለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ።

ለጊዜው ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ እንዳለው ሰላም የሁሉ መሰረት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው አመራርና ተማሪዎች አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ በኩል በጋራ ተደማምጠው ሊሰሩ ይገባል።

"በተማሪውም ሆነ በዩኒቨርሲቲው አመራር በኩል ችግሮች አሉ" ያለው ተማሪው፣ እርስ በርስ የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል አለመኖር የዩኒቨርሲቲውን ሰላም እየጓዳው መሆኑን ተናግሯል::

"በተማሪዎች ምግብ ቤት የሚስተዋል የመስተንግዶ ችግር እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራር የተማሪውን ጥያቄ የማዳመጥ ፍላጓት አለመኖር  በአሁኑ ወቅት በተቋሙ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ነው" ብሏል።

አንዳንድ ተማሪዎች እርስ በእርስ እንደማይደማመጡና ጥያቄያቸውን በሰከነ መንፈስ ለሚመለከተው አካል ከማቅረብ ይልቅ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር መሞከራቸው የተቋሙን ሰላም አውኮታል ያለው ደግሞ ሌላው የምህንድስና ተማሪ  ነው።

ከዚሁ ትምህርት ክፍል አስተያየቱን የሰጠው ተማሪም የተወሰኑ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት የትምህርት ጊዜው አለአግባብ መባከኑ እንዳሳዘነው ገልጿል።

"አብዛኛው ተማሪ በሰላም መማር ይፈልጋል" በማለት  የመማር ማስተማሩ ሒደት ሳይቋረጥ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብሏል::

በተማሪዎች መካከል የተከሰተ ግጭት ባይኖርም አንዳንድ ተማሪዎች በሁከቱ ጥቃት ይደርስብናል ብለው ከመስጋት የተነሳ ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን ጠቁሟል ።

የዩኒቨርሲቲው የውጭና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኦልቀባ አሰፋ እንዳሉት፣ ተማሪዎቹ ጥያቄያቸውን ከትምህርት ገበታ ሳይለዩ እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዩኒቨርሲቲው አስተዳደራዊ ጉዳዮችና በአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄ አለን ያሉ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሰጉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣታቸው ምክንያትም የመማር ማስተማር ሥራው ዛሬም እንዳልተጀመረ ገልጸዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ በመደረሱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ዛሬ እንደሚጀመር ቢጠበቅም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ትምህርቱ አልተጀመረም ፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 የተቀናጀና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የሚቀረፁ የልማት እቅዶች የጉልበት ስራ ፈጠራን በሚያበረታቱበት መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በጉልበት ስራ ላይ የሚያተኩረው 17ኛው የአፍሪካ የጉልበት ስራ ጉባኤ በአዲስ አበባ በሕብረቱ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ምሁራን የሚሳተፉ ሲሆን  የአፍሪካ አገራት በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ተሞክሮዎቻቸው ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከአለም የስራ ድርጀት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ጉባኤው ''ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት'' በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን ለአምስት ቀናት ይቆያል።

ተስማሚ የሆኑ፣ወጪ ቆጣቢና አግባብ ያላቸውን የምህንድስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ በጉልበት መሰራት የሚችሉ ስራዎችን ከባድ መሳሪያዎችን በመግዛት የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ ለጉልበት ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር የጉባኤው አላማ ነው።

ጉባኤው በስራ አጥነት፣ድህነት እንዲሁም ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሚያበረክቱት የሀብት ፈጠራና የማህበራዊ እድገት ላይ የሚያተኩሩ ፖሊሲዎችን፣ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ለማመንጨትም ያግዛል ተብሏል።

ጉባኤውን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉባኤው አህጉሪቱ የምትፈልገውን ፈጣን፣ ፍትሀዊና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

አገራት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚቀርጿቸው የልማት ግቦችና መስኮች ለስራ ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

በአለም የስራ ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ጆርጅ ኦኮቶ በበኩላቸው አፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ብትሆንም አሁንም በአየር ንብረት ለውጥ በሚመጣ ረሀብና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች ፈተና እንደሆኑባት ጠቅሰው የወጣቶች ስራ አጥነትም ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው ብለዋል።

ችግሩን በስራ እድል ፈጠራ በኩል ለመቅረፍ መንግስታት፣ማህበራዊ ሀላፊነት ያለባቸው ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የስራ እድልን ለመፍጠር ምቹ የሆኑ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየሰራ ነው።

አቶ አህመድ በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ለጉልበት ስራ አመቺ የሆኑ የስራ እድሎችን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

16ኛው የአፍሪካ ጉልበት ስራ ጉባኤ ከሁለት አመት በፊት በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን ኮቶኑ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ህዳር 4/2010 በጎንደር ከተማ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ አመት በ30ሺ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የውጪ ሀገር ቱሪስቶች በበኩላቸው ታሪካዊና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ያለአንዳች ስጋት መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ በክልሉ የሰፈነው ሰላም በሁሉም የክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ  እንደተናገሩት የከተማው የቱሪስት ፍሰት  እየጨመረ መጥቷል፡፡

ለአብነትም በሩብ አመቱ ቁጥራቸው 6ሺ የሚጠጉ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች የከተማውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የጎበኙ ሲሆን ይህ ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በ1ሺ 640 ጨምሯል፡፡

በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም መኖሩ ለቱሪስቶች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት ኃላፊው የቱሪስት ፍሰቱንና ቆይታውን ለማሳደግ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

በርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶች የሚታደሙበትን የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በድምቅት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

''በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩን ተገንዝቤአለሁ ኢትዮጵያ ስመጣም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው'' ያሉት ከአውሮፓ የመጡት ሚስተር ሃልቪ ናቸው፡፡

''የፋሲል ቤተ-መንግስትን ስጎበኝ ሀገር ቤት እንዳለሁ ተሰምቶኛል ምክንያቱም ከደቡባዊ የፈረንሳይ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ'' ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ ካሊፎርኒ ግዛት የመጡት ሚስ ፔትራ በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ጀምሮ ባህርዳር፣ ጎንደርና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ተመልክቻለሁ ጉብኝቱ ጥልቅ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኛል ብለዋል፡፡

''ኢትዮጵያ ውስጥ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በቀላሉ ለመጎብኘት የሚያስችል የአገልግሎት አሰጣጥ አደረጃጀት መኖሩን አረጋግጫለሁ ቱሪስቶች ይህችን ታሪካዊ ሀገር እንዲጎበኙ ነው መልእክት የማስተላልፈው'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳ ዘንድሮ ካለፈው አመት የተሻለ የቱሪስት ፍሰት በሁሉም የክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መኖሩን ገልጸዋል፡፡

''ፍሰቱን ለማስቀጠል የክልሉን ሰላም ይበልጥ ማረጋገጥ ላይ መስራት ነው'' ያሉት ኃላፊዋ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማሻሻልና አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን መጨመር የአመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ሰሜን ጎንደር ዞን በአለም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርስ የተመዘገቡ የአጼ ፋሲል ቤተመንግስትና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡  

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 የለውጥ ሰራዊት ግንባታን የማይተገብሩ ተቋማት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

 የምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።

 እንደ ቋሚ ኮሚቴው ገለጻ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢለዩም በተግባር ውጤት ሲያመጡ ግን አልታዩም።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማዘንጊያ አያቶ "የለውጥ ሰራዊት በመገንባት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመለየትና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገል ጅምሮች ቢኖሩም የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት አልቻሉም" ነው ያሉት።

 በመሆኑም የለውጥ ሰራዊት በመገንባት የተለዩ ችግሮችን በተግባር መፍታት በማይችሉ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

 ተቋማት የለውጥ ሰራዊት ግንባታ መርሆዎች፣ አሰራሮችና መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ሚኒስቴሩ ኃላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

 ህብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሁንም ቅሬታ እያነሳ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጅምር ያለፈና በተጨባጭ የመጣ ለውጥ እንደሌለ በመጠቆም።

 የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር ታገሰ ጫፎ የተሰጠው ማሳሰቢያ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ የተቋማትን የለውጥ ሰራዊት ግንባታ ደረጃ በመከታተል ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

 በተወሰኑ ተቋማት ጠንካራ የለውጥ ሰራዊት ተገንብቶ ችግሮች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ተብለው ተለይተው እየተፈቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ሚኒስቴሩ ክትትል የሚያደርግ የሰው ኃይል ችግር እንዳይገጥመው በዝውውር፣ በደረጃ እድገትና በቅጥር እያሟላ መሆኑንም ተናግረዋል።

 ይህን በማይተገብሩ ተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

 ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና የስራ አመራር ኢንስቲትዩትን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት ገምግሞ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ህዳር 4/2010 በጣና ሐይቅና በዙሪያው የተከሰተው የእንቦጭ አረም የእርሻና የግጦሽ መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ በመውረር ከግብርና ሥራ ውጭ እያደረጋቸው መሆኑን አርሶአደሮች ተናገሩ።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የለምባ አርባቱ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰጡ ዱባለ በሰጡት አስተያየት ባለፉት አምስት ዓመታት ሐይቁን የወረረውን አረም ለማስወገድ አርሶ አደሩ ጥረት ቢያደርግም በአግባቡ መከላከል እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

አረሙ ከዓመት ዓመት እየሰፋና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ እየወረረው መምጣቱን ጠቁመው፤ በዚህም የሩዝ፣ የጤፍ፣ የሽምብራ፣ የማሽላ መሬታቸው ከጥቅም ውጭ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በግጦሽ መሬት ላይ ግጫ፣ ቶካ የተባለ የሣር ዝርያ ይበቅል እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የግጦሽ ቦታው በአረሙ በመወረሩ እንስሳቱ ለመኖ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጣቸውንም ተናግረዋል።

በደንቢያ ወረዳ የጀርጀር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስመኝ ባዩ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የእንቦጭ አረሙ ከዓመት ዓመት እየተስፋፋ በመምጣቱ ለእንቅስቃሴም እንቅፋት ሲፈጥር ቆይቷል።

አረሙ በመስፋፋቱ ዓሣ አስግረው መመገብም ሆነ ለገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት የማስገሪያ ታንኳም ሆነ የሞተር ጀልባ ወደ ሐይቁ የሚገባበት ቦታ እየጠፋ መሆኑን ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ትናንት ሐይቁን ከእንቦጭ የማጽዳት ሥራ አከናውነዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጣና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ሰይፉ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የተከሰተው የእንቦጭ አረም ሐይቁን ለአደጋ አጋልጦታል።

አረሙ እያስከተለ ያለውን ችግር በመገናኛ ብዙሃን ሲከታተሉት ቢቆዩም በአካል ተገኝተው ሲመለከቱት ችግሩ ከተጠበቀውና ከአቅም በላይ ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የባንኩ ሠራተኞችም የአርሶ አደሩን ጥረት ለማገዝና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የእንቦጭ አረምን የማጽዳት ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በገንዘብ ለሚደረገው ድጋፍ የባንኩ ሠራተኞች የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጣና ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን አቶ ካሳ የኔሁን በበኩላቸው፣ በእንቦጭ አረም ማስወገድ ሥራ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ መሳተፋቸውንና አረሙን በሰው ኃይል ለማስወገድ እየተደረገ ያለው ጥረት ብዙም ውጤታማ አለመሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት ዘመናዊ ማሽኖችን በማስመጣት ሕብረተሰቡ በጉልበቱ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ ማግዝ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን ለመግዛት በሚደረገው የገንዘብ መዋጮ የበኩላቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

" በጣና ሐይቅ በቅርቡ በተደረገ ልኬት አምስት ሺህ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት በእምቦጭ አረም መወረሩ ታውቋል" ያሉት ደግሞ  በአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደን፣ ዱር እንስሳት ባለስልጣን የአካባቢ ባለሙያ አቶ ቻላቸው ብናልፈው  ናቸው።

ባለፉት ዓመታት የሕብረተሰቡን ጉልበት በመጠቀም አረሙን ለማስወገድ የተደረገው ጥራት የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ታግዞ አረሙን ለማጽዳት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት አረሙን ለማስወገድ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በሙከራ ደረጃ እንደሚገኙና በቀጣይ ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ለእንቦጭ አረሙ ማስወገጃ ማሽን መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብም የባንክ ሒሳብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከፍቶ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩንም አቶ ቻላቸው ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ህዳር 4/2010 ትግራይ ክልልን ወክለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በመገናኛ ብዙሀን ላይ ላስተላለፉት ያልተገባ  ንግግር ዛሬ ይቅርታ ጠየቁ።

የተፈጠረውን ስህተት ተከትሎም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባልነት ውድድርም ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡

"በመቀሌ ከተማ በመገንባት ላይ ያለውን የትግራይ ስቴዲየም ፣ ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የተቀላቀሉ የመቀሌ ከነማና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በቅርበት እንዲመለከት የፌዴሬሽኑ ጉባኤ መቀሌ ላይ እንዲካሄድ ካለኝ ፍላጎት ጠይቄአለሁ" ብለዋል።

ቀደም ሲል ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት መግለጫ የሴቶችን ኑሮና ህይወት ለማሻሻል የታገሉለትን ዓላማ የሚገልፅ አለመሆኑን ጠቅሰው ታላላቅ የስራ ኃላፊዎችን ሳይቀር በዚህ ደረጃ ማንሳታቸው ተገቢ እንዳልነበረ ተናግረዋል።

የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ባገለገሉባቸው አራት ዓመታት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ሰርቻለሁ ካሏቸው መካከልም ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲገኝና ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫዋቾች ዝውውር ስርዓት እንዲኖር ያደረጉትን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በፌዴሬሽኑ  የነበሩት ችግሮች መልክ እንዲይዙ ከማድረግ ጀምሮ ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት እንዲከተልና ብሄራዊ ቡድኑ የራሱ ማሊያ እንዲኖረው ኢጣሊያ  ከሚገኝ ኩባንያ ጋር በመነጋገር በየዓመቱ ውሉን እየታደሰ  እንዲሰራ የድርሻቸውን መወጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሴቶች እግር ኳስ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲደራጁና ትኩረት እንዲያገኙ ፣ በትግራይ ክልል ያለውን የስፖርት እንቅስቃሴ  እንዲያድግም ድጋፍ መስጠታቸውን አመልክተዋል፡፡ 

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ የክልሉን መንግስትና ህዝብ የማይወክል ንግግር በማድረጋቸው ውክልናውን ማንሳቱ ይታወቃል።

 

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 የቆላ ዝንብ መስፋፋትና መዛመት እየቀነስ መሆኑን የብሔራዊ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ መቆጣጠሪያና ማጥፊያ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የሩብ ዓመት እቅድ ክንውን አድምጧል።

 ደቡብ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ የሚስተዋልባቸውና  ተጋላጭ ናቸው።

 የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር ዶክተር ዳኛቸው በየነ ተናግረው  እየተከናወነ ባለው ተግባር በርካታ የቆላ ዝንብ ተጠቂ አካባቢዎችን ከከፍተኛ የስርጭትና የተጠቂነት አደጋ ማላቀቅ መቻሉን ነው የገለፁት።

 ኢንስቲትዩቱ በበደሌ፣ አሶሳና አርባ ምንጭ ያቋቋማቸው አምስት ጣቢያዎችና ሌሎች የስርጭት መከላከያና ማጥፊያ ማዕከላት ለስርጭቱ መቀነስ ጉልህ ሚና እያበረከቱ መሆኑ ተጠቅሷል።

 ዝንቡ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ወጥመዶችን በመትከል፣ የኬሚካል ርጭት በማድረግና የእንስሳቱን ጀርባ ጸረ-ቆላ ዝንብ መድኃኒት በመርጨት ስርጭቱን መቀነስ መቻሉን የበደሌ የቆላ ዝንብና ገንዲ በሽታ ጥናትና ቁጥጥር ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ደረጄ አለሙ ገልጸዋል።

 ከእነዚህ ስልቶች በተጨማሪም የቆላ ዝንቦችን በማዕከላቱ በማራባት በጨረር የማምከንና የመጨረሻ ደረጃ ቴክኖሎጂ በሆነው ዝንቦች እንዳይራቡ በሚያደርገው በላቦራቶሪ የተራቡና በጨረር የመከኑትን ጫካ ውስጥ ከሚገኙ ጤነኛ ሴት ዝንቦች ጋር በማገናኘት የዘር ፍሬያቸው እንዲመናመንና ቁጥራቸው እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

 በዚህም በኦሮሚያ 16፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 10፣ በጋምቤላ አምስት እና በአማራ ዘጠኝ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የነበረውን የቆላ ዝንብ ስርጭት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወረዳዎች ብቻ የቆላ ዝንብ ስርጭቱን 97 በመቶ መቀነስ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

 ይህ በመሆኑም የአካባቢው አርሶ አደሮች የወተት ላሞችና የውጭ አገር ዝርያዎችን ማላመድ፣ እንስሳት ማድለብና ማዳቀል ችለዋል።

 ኢንስቲትዩቱ በተያዘው በጀት ዓመት የቆላ ዝንብ በስፋት ይታይባቸዋል በተባሉና በጥናት በተለዩ 45 ወረዳዎች ስርጭቱን የመግታት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው የሚገኙ መልካም ተግባራትና ከክልሎች የግብርና ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ጋር ያለውን ትስስር ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 የሚጠቀምባቸውን ኬሚካሎችና መድኃኒቶች የአካባቢ ብክለትና የጤና እክል በማያደርሱበት አግባብ ማስወገድ እንደሚገባውም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በፍጥነት መተግበር እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴርን የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማዘንጊያ አያቶ  እንዳሉት፤ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ትግበራ ዘግይቷል።

በመሆኑም "የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ቀሪ ስራው ተጠናቆ በፍጥነት ወደ ተግበራ ማሸጋገር ይገባል" ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የምዘናው ቀሪ ስራዎችን በቶሎ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አቶ ታገሰ እስካሁን ባለው ሂደት ከ15 ሺህ በላይ ስራዎች ደረጃ እንደወጣላቸው ገልጸው፤ "ቀሪዎቹ አዳዲስ፣ ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀት ያላቸውና ቅሬታ ያቀረቡ ተቋማት ናቸው" ብለዋል።

በመንግስት ተፈቅዶላቸው የመዋቅር ለውጥ የሚያደርጉ ተቋማት ከቀሪዎቹ መካከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው የ104 ተቋማት መዋቅር ጸድቆላቸው ድልድል ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ድልድል ያልተደረገላቸው ከአስር የማይበልጡ ተቋማት አዳዲስ  አደረጃጀትና መዋቅር ያላቸው መሆናቸውንም  ጠቁመዋል።

ክልሎች የአፈፃፀም ደረጃቸው ቢለያይም አብዛኛዎቹ ድልድሉን እስከ ወረዳ መዋቅር ማድረሳቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረሪና አፋር ክልሎች ድልድሉን ወደ ዞንና ወረዳ ለማድረስ ጅምር ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል  የዜሮ ዓመት የስራ ልምድ በስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናቱ ላይ እንደሚካተትም ሚንስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ለተከፈቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግብዓቶችን በአፋጣኝ ሊያሟላ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2010 በጀት ዓመት እቅድና የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል።

በውይይቱ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ግንባታቸው የተጀመሩ አስራ አንድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አስሩ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ቢባልም ቋሚ ኮሚቴው ተቋማቱ የግብዓት ችግር እንዳለባቸው ቅሬታ እያነሱ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ በከፈታቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉ የግብዓት ችግሮችን በማሟላት ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ማድረግ እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በ2010 በጀት ዓመት ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ተጠናቋል ቢባልም ስራውን መጀመር የሚያስችሉ የተማሪዎች ምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች ፤ ፍራሽና አልጋ እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች አለመጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲዎቹ ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን አንስቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህም በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ግንባታቸው ከተጀመሩ 11 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የአስሩ ግንባታ ተጠናቆ በያዝነው በጀት ዓመት ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ግብዓቶችን የማሟላት ስራ በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም በአሁኑ ሰዓት የመሰረት ልማት ስራዎች በተለይ መብራትና ውሃ እየገባላቸው መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውስጥ ግብዓቶችን ጨምሮ ለተማሪዎች መገልገያ የሚውሉ ቁሳቁሶች ግዥ ተጠናቆ ወደ ተቋማቱ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶክተር ሳሙኤል በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናሉ ብለዋል።

ግንባታቸው የተጠናቀቁት እነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በያዝነው ዓመት እያንዳንዳቸው እስከ 1 ሺ 500 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም አላቸውም ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና ተደራሽነቱን ለማስፋት የነባር ዩኒቨርሲቲዎችን የውስጥ አቅም በማጎልበት አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተገነቡ እንደሚገኙ ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተጨማሪም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲጠናከሩም ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረግ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን