አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 12 November 2017

መቀሌ ህዳር 3/2010 በትግራይ ስቴዲየም ዛሬ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኘሪሚየርሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ የመቀሌ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ባዶ ለባዶ በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ፡፡

በጨዋታው የመቀሌ ከተማ አምስት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሁለት የግብ ሙከራዎችን አሳይቷል።

የመቀሌ ከተማ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ዮሐንስ ሳህሌ በሰጡት አስተያየት ''በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ብናደርግም ድል ከእኛ ጋር ባለመሆኑ ውጤት ተጋርተን ወጥተናል'' ብለዋል።

የወልዋሎ አዲግራት ዋና አሠልጣኝ አቶ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ''የተጎዱ ተጫዋቾች ስለነበሩን በመከላከል ላይ ያተኮረ ጨዋታ መርጠን ተከላካዮቻችን ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል፤ በውጤቱም ደስተኞች ነን'' ሲሉ ገልፀዋል።

በስቴዲየሙ ከ50 ሺህ በላይ ተመልካቾች ጨዋታውን የተከታተሉ ሲሆን ጨዋታውም ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት እንደነበር አሰልጣኞቹ ተናግረዋል።

Published in ስፖርት

ድሬዳዋ ህዳር 3/2010 ከኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራርን በመከላከል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን በድሬዳዋ አስተዳደር ስር የሚገኙ የኦህዴድ አባላትና አመራሮች አስታወቁ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አባላትና ደጋፊዎች ለሶስት ቀን በድርጅቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያካሄዱት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

በጉባኤው የተሳተፉ አመራሮችና አባላት ለኢዜአ እንደገለፁት የሥርዓቱ አደጋ የሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን በቁርጠኝነት ለመከላከል ተዘጋጅተዋል፡፡

ሥልጣንን ለግል ጥቅምና መደላደያ የሚያውሉ አንዳንድ አመራሮችን  በፅናት በመታገል ስልጣን የህዝብ መገልገያነቱ ፀንቶ እንዲዘልቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በአስተዳደሩ የኡሉልሞጆ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ዑስማን መሐመድ በሰጡት አስተያየት የድርጅቱን አንድነት ጠብቆ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተደራጀ መንገድ ምላሽ ያለመስጠት ችግሮች መኖራቸው በጉባኤው  ተመልክቷል።

"ጉባኤው እያንዳንዱ አመራርና አባል ያሉበትን ክፍተቶች በጥልቀት የፈተሸበትና አምና በጥልቅ ተሃድሶው ህዝቡ ላቀረባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የድርሻቸውን ለመወጣት አቋም ይዞ የወጣበት ነው ብለዋል ።

አቶ ዑስማን እንዳሉት በአስተዳደሩ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት ቢደረግም የሚፈለገው ውጤት አልመጣም፡፡

ችግሩን ለመፍታትና የወጣቱን የሥራ ጥያቄ ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎችን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ለማስኬድ ጉባኤው ምቹ ሁኔታ  መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ አቶ ፋሚ መሐመድ ናቸው፡፡

ወይዘሪት ሰአድ መሐመድ በበኩላቸው በአንዳንድ አመራሮች የሚስተዋለውና በደማቸው ዘልቆ የገባውን ሥልጣንን ለራስ ጥቅም የማዋል ተግባር የማጥራት ጉዳይ ቀዳሚ ስራ መሆኑን በጉባኤው የጋራ ድምዳሜ የተያዘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

"ከምን ጊዜ በላይ የተፈጠረውን አንድነትና መነቃቃት በመጠቀም ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል" ብለዋል፡፡

የሳታፊ አባላትና አመራሮች የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በሀገሪቱ ብሎም በድሬዳዋ እየተመዘገቡ የሚገኙትን የልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የሰላም ውጤቶች እንደሚያጠናክሩ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤያቸውን አጠናቀዋል፡፡         

 

Published in ፖለቲካ

አርባ ምንጭ ኅዳሴ 3/2010 በደቡብ ክልል ከገጠሩ ክፍል ሀብት በማሰባሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማዋል እየተከናወነ ያለው ተግባር በመልካም ተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ክልሉ ከአርሶና አርብቶ አደሩ ያሰባሰበው ድጋፍ በገጠሩ ህዝብ በግድቡ ግንባታ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ያስቻለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል አስመልክቶ በተሰበሰበው ገቢ የአርሶና አርብቶ አደሮች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡

"የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤትና መላው አመራር የገጠሩን ህዝብ በግድቡ ግንባታ ለማሳተፍ የተከተሉት መንገድ በሌሎች ክልሎች በመልካም ተሞክሮነት ሊወሰድ ይገባል " ብለዋል ።

በገጠሩ ያለው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን ለማበርከት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ተሳትፎ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳተፎ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው በበኩላቸው በክልሉ ለግድቡ ግንባታ የገጠሩ ህዝብ ተሳትፎ ሊጨምር የቻለው አመራሩና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተቀናጅተው በመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፌደራልና ክልል መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ የኤፍ ኤምና የማህበረሰብ ራዲዮኖችና ሚኒ ሚዲያዎች ለገጠሩ ህብረተሰብ መረጃ በማድረስ እየተጫወቱ ያለው ሚና ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል ።

"በክልሉ እስካሁን ዋንጫው በተዘዋወረባቸው አከባቢዎች የሚገኘው አርሶና አርብቶ አደር ከቦንድ ግዥ ውጭ 4 ሺህ 72 ሰንጋዎችና ወይፈኖች፣ 1ሺህ 960 በጎችና ፍየሎችን  በስጦታ አበርክቷል " ብለዋል ።

የከበሩ ማዕድናት ከሚመረትባቸው አከባቢዎችም ከ600 ግራም በላይ ወርቅ፣ ቡናና ሰሊጥን ጨምሮ የጥራጥሬ ሰብሎችና 90 የሚሆኑ በቅሎዎችና ፈረሶች ለግድቡ ግንባታ በድጋፍ መሰብሰባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ላቀ ጥላዬ በበኩላቸው በገጠር ያለው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በዓይነትና በጉልበት የሚያበረከተውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ አርሶ አደሮች ከቦንድ ግዢው በተጨማሪ ለስድስት ተከታታይ ዓመት በአባይ ተፋሰስ አከባቢ የተጎዳ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን የግድቡን በደለል የመሞላት ተጋላጭነት ለመከላከል አስተዋፆ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል ።

የኦሮሚያ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ አሚን አብዱ በበኩላቸው በክልሉ  የገጠሩን ህዝብ በስፋት በማሳተፍ ለግደቡ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ልምድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

በጋምቤላ ክልል እየተዘዋወረ ያለው የህዳሴ ችቦ ወደ ክልሉ ሲደርስ አርሶና አርብቶ አደሩን ይበልጥ ለማሳተፍ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት በአርባምንጭ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ዓመታዊ ምክክር መድረክ በየክልሉ የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በጋራ ለመስራት በመስማማት ትናንት ተጠናቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ህዳር 3/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቀ ከቦንድ ግዥ በተጨማሪ በምርምር ስራ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

የህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል ምክንያት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች ለግድቡ ግንባታ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቶ አያኖ በራሶ ለኢዜአ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል ገብቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በቦንድ ግዥ፣ በዕውቀትና በግድቡ ዙሪያ በክልሉ  በሚደረጉ የውይይት መድረኮች ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠት ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች በስጦታና በቦንድ ግዥ ያበረከቱት 30 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግላቸው ለሶስተኛ ጊዜ በወር ደሞዛቸው የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርምር ረገድም ራሱን የቻለ የውሀ ዘርፍ እንዳለው ጠቁመው ምሁራኑ ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ በሃገሪቱ ያለውን የውሀ ሃብት የበለጠ መጠቀም የምንችልበትን ሁኔታን በምርምር በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በኬሚስትሪ የትምህርት መስክ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዮርዳኖስ ገብረስላሴ እንደገለጸችው አባይ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ትልቁ ሀብት ነው፡፡

ወንዙ ለሀገሩ ጥቅም እንዲሰጥ የግድቡ መገንባት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁማ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣቱ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡

የኮምፒውተር ሳይንስ አራተኛ አመት ተማሪ የሆነው ታደሰ አይጠገብ በበኩሉ ሀገራችን በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ የሆነው አባይ ተገድቦ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ጥቅም ላይ መዋሉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት እንደሚያስችል ተናግሯል፡፡

"የህብረተሰቡ የሀይል ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የተነሳ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የመቆራረጥ ችግር ማስቀረት ያስችላል" የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Sunday, 12 November 2017 19:25

አወዛጋቢው ጉባኤ

ይሁኔ ይስማዉ

ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጠዋት ላይ የተለያዩ ክለቦች፤ አመራሮች፣ የክልሎች እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች፣ የአሰልጣኞች ተወካይ፣ የዳኞች ተወካይና ሌሎች  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ የስም ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

በተመሳሳይ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጉባኤው በሚካሄድበት መሰብሰቢያ አዳራሽ  መግቢያ ላይ መግቢያ ባጅ እየወሰዱ ናቸው።

ከጉባኤው መጀመሪያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጉባኤውን እንዲዘግቡ የተጋበዙ መገናኛ ብዙኃን ውስን መሆናቸው ጥሪው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንን ያገለለ ከመሆኑም በላይ ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የክልሎች መገናኛ ብዙኃን አለመጋበዛቸው አንዱ አስገራሚ ጉዳይ ነበር።

ጉዳዩን የሰማው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፌዴሬሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ያደረገበት መንገድ አግባብነት የሌለው በመሆኑ እንዲስተካከል ለፌደሬሽኑ አሳውቋል።

የቁጥር ገደብ የተጣለባቸውም ሆነ በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው ያልተካተቱት የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ለምን አንገባም እያሉ የፌደሬሽኑን አመራሮች ቢጠይቁም ምላሽ ሳይሰጣቸው በመጉላላታቸው አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

ብዙዎቹ ተስፋ ሳይቆርጡ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በድንገት ሁሉም እንዲገቡ በመፈቀዱ ወደ ጉባኤው አዳራሸ ገብተዋል፡፡

በትርምስ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ይጀመራል ከተባለበት 1 ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው።

በጠዋቱ መርሐ ግብር ከ3 ሰዓት ከ 45 ደቂቃ ጀምሮ ለ5 ደቂቃ የጉባኤውን አጀንዳ ለማጽደቅ ቀጠሮ ቢያዝለትም በሁለተኛ ቀን ጠዋት ላይ ይደረጋል ተብሎ በእቅድ የተቀመጠው አዲሱን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ የመምረጡ ጉዳይ ሰፊ ክርክርና የውይይት ጊዜ ወስዷል።

የክርክሩ መነሻ ደግሞ የእጩዎቹ ምርጫ ይራዘም ወይስ በዚሁ ጉባኤ ላይ ይመረጥ የሚለውን ለመወሰን ሲሆን በ5 ደቂቃ ይጠናቃቃል የተባለው ጉዳይ ትልቅ መከራከሪያ ሆኖ ከ 2 ሰዓት በላይ ጊዜ ወስዷል።

የአጀንዳው መጽደቅ ሰባት ያህል ርእሰ ጉዳዮች ቢኖሩትም ከ2 ሰዓት በላይ የፈጀው ክርክር ምርጫውን በተመለከተ ብቻ ነበር።

ከጉባኤው አባላት አንዱ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የምርጫው መራዘም ለምን እንደ አማራጭ እንደቀረበ ማብራሪያ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች ምላሽ ሰጥተውበታል።

የምርጫው መራዘም ክልሎች በስራ አስፈጻሚነት የሚያቀርቧቸው እጩዎች አንድ ብቻ መደረጉ ስህተት በመሆኑና አስመራጭ ኮሚቴ ከተፈለገም ያንን ለማከናወን  መሆኑን ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ምላሽ ከተሰጠ በኋላም አሁንም ክርክሩ ሊቆም ባለመቻሉ 68 በ 62 በሆነ የአብላጫ ድምፅ የምርጫው ጊዜ እንዲይራዘም ተወሰነ።

ምርጫው በአብላጫ ድምጽ እንዲራዘም ሲወሰን ሌላ አዲስ ክስትት አሳይቶ አልፏል፡፡ ይህም ስራ አስፈጻሚዎቹ ሳይግባቡ የተግባቡ ለመምሰል ያደረጉት ማስመሰል እርስ በርስ መተማመመን እንደሌላቸው ያሳየ ክስተት ነበር።

በምክትል ፕሬዝዳንቱና በአንዳንድ ስራ አስፈጻሚዎች በኩል በድምጽ ብልጫ ይራዘም የሚለው ሀሳብ ትክክለኛነቱ አጠራጣሪ በመሆኑ እንደገና ይቆጠር የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ የጉባኤው መሪ አቶ ጁነዲን ባሻ ቆጠራውን ያደረኩት እኔ አይደለሁም፣ቆጠራውን የተመረጡ ሰዎች በግልጽ ያከናወኑት ነው በማለት በጥቂት ስራ አስፈጻሚዎች ድጋሚ እንዲደረግ የቀረበውን ሀሳብ ውድቅ አደረጉ።

ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ተላከ በተባለው ደብዳቤ ምክንያትና ከዚያ ፊትም ባለፉት አራት ዓመታት በስራ አስፈጻሚነት የገቡት የፌዴሬሽኑ ስዎች እርስ በእርስ መስማማቶች እንደሌሉ በመገናኛ ብዙሃንና በፌደሬሽኑ ሰዎች ሲነገር የነበረው እውነት ለመሆኑ ፍንጭ ጥሎ አልፏል።

በዚህ ወቅት በስራ አስፈጻሚች መካከል ስላለው አለመግባባት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትና ምክትላቸው እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሀሳብ ሰንዝረዋል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በስራ አስፈጻሚዎች በኩል ሁሉም የራሱ  ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚደረግ የሀሳብ ክርክር እንጂ ግጭት የለም ሲሉ ጠዋት ላይ ተናግረው ነበር።

ከሰዓታት ቆይታ በኋላ የፌዴሬሸኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን በሻ ደግሞ እርስ በእርስ አለመግባባቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በሁለተኛው ቀን መርሃ ግብር የፌደሬሽኑ መተዳደሪያ የማሻሻያ ረቂቅ ደንብና የተራዘመው ምርጫ በምን መልኩ፣የት፣ መቼ መከናወን እንዳለበትና ከሁሉም በላይ ደግሞ የምርጫውን ሁኔታ የሚከተታሉ አስመራጮችን የመምረጡ ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚሁ መሰረት የስራ አስፈጻሚዎችና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲካሄድ ተወሰነ።ይሁን እንጂ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ሳይነሳና እልባት ሳያገኝ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

የአስመራጭ ኮሚቴውን ምርጫ በተመለከተ አማራ ክልልን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ ተካ አስፋው አስመራጭ ኮሚቴው የግድ መመረጥ እንደነበረበትና ገለልተኛ አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርጫው እንዲካሄድ ካልተደረገ የቀኑ መራዘም አስፈላጊ አልነበረም ሲሉ  ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል እጩ የሆኑት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አስመራጭ ኮሚቴ መምረጥ እንደማይቻል ተናግረዋል።"አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ አሁን እየተሰራበት ያለው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አይፈቅድም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው አስመራጭ ኮሚቴ ለምን እንዳልተመረጠ ለቀረበላቸው ጥያቄ ''የጉባኤው አባላት ጠቅላላ ጉባኤው አልቋል ሳይባል ነው የተበተኑት'' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ የሆነው በዋናነት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚፈልጉና የማይፈልጉ በሁለት ጎራ የተከፈሉ አስተሳቦች በመፈጠራቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

አቶ ጁነዲን በጉባኤው ማጠቃለያ ዕለት ከተቻለ ከሰዓት በኋላ አባላቱ እንዲሰባሰቡ በማድረግ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል ቢሉም ጉዳዩ ሳይቋጭ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን ውሎ የፊፋ ተወካይ የነበሩ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴውን አለመመረጥ ለፊፋ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ከ45 ቀናት በኋላ ይደረጋል የተባለው ምርጫ ቀደም ብሎ አዳዲስ ጉዳዮች ይሰሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ሀሳብና አስተያየት ለመስጠት ይደረግ የነበረውን ፉክክር ስመለከት አንደኛ ክፍል እያለሁ መምህራችን ጥያቄ ጠይቀው የማውቃት ከሆነ እድሉን አግኝቼ መልሱን ለመመለስ ከመቀመጫዬ ከፍ በማለት እጄን ዘርግቼ ላይ ታች ሳራገብ የነበረውን ሁኔታ እንዳስታውስ አድርጎኛል።

ሁለተኛው ጉዳይ  ከአንደኛ ክፍል ቆይታዬ ጋር ተያይዞ የመጣልኝ  ሀሳብ ለመናገር  የነበረኝ ድፍረት ሲሆን፤ ይኽው ድፍረት አይሉት ልጅነት በፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት በኩል ታይቷል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ጠቅላላ ጉባኤው መጀመሪያ ሊደረግ ታስቦ ከነበረበት ቦታ በተለያዩ ሁኔታዎች የተቀየረበትን ምክንያት ሲያብራሩ የአገርን ባህልና ወግ በሚፃረር መልኩ ሐሳባቸውን የገለፁበት ሁኔታ ታይቷል።

ሶስተኛው ጉዳይ በልጅነት እድሜ የሚደረግውን አይነት ቀልድ ይሁን ቁም ነገር በማይታወቅ መልኩ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለፉት አራት ዓመታት የነበረው ስራ አስፈጻሚ እግር ኳሱን ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ አምጥቶታል በማለት የገለጹበት መንገድ ነው።

ጉዳዩን ያነሱት በተለይ ከእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር ጋር አያይዘው ሲሆን በፊት በፊርማ ወቅት ይከፈል የነበረውን አሁን በወርሃዊ  ደመወዝ  እንዲለወጥ በማድረግ መንግስት ከግብር  ማግኘት ያለበትን ጥቅም በአግባቡ እንዲያገኝ አድርገናል ብለዋል።  

በእርግጥም  የተጨዋቾች ክፍያ አሁንም የቁጥጥርና የክትትል ክፍተት ያለበትና ገና ሰፊ ስራ የሚጠይቅ ቢሆንም ወርሃዊ ክፍያ መደረጉና ተጨዋቾች የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ መደረጉ የሚያስመሰግን ነው።

የዝውውር ጉዳይ ግን አሁንም ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በደንብ ሊታይ እንደሚገባ የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ወክለው በጉባኤው ላይ የታደሙት አቶ ሚካኤሌ አምደመስቀል አሳስበዋል።

ለደደቢት እግር ኳስ በ75 ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ አልጫወትም በማለት ለሌላ ክለብ  በ23 ሺህ ብር የፈረመ ተጨዋች አለ።ይሄ የሚያሳየው በብዙ ክለቦች በኩል አሁንም ያልጠራና ትክክለኛ ያልሆነ የተጨዋቾች ዝውውር እንዳለ ነው ሲሉ ነበር አቶ ሚካኤል የተናገሩት።

በተጨዋች ዝውውር ላይ አሁንም አሰራሩን በአግባቡ ተግባራዊ የማያደርጉ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ተጨዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ እንዲያገኙ መደረጉ ብቻውን እግር ኳሱን ፕሮፌሽናል ያደርገዋል ወይ የሚለው ዋና ሀሳብ ነው።

የአገሪቱ ክለቦች አደረጃጀት፣ አሰለጣጠን ፣የተጨዋቾች ምልመላና በእነዚህ ውሰጥ የሚካተቱ ዝርዝር ሀሳቦችና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ሳይሰሩ እግር ኳሱን ሙያዊ ስነምግባሩን በጠበቀ መንገድ እንዲመራ አድርገነዋል ማለቱ ከቀልድነት ያለፈ ቦታ አይኖረውም።

Published in ዜና-ትንታኔ
Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ ህዳር 3/2010 የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመሮጫ ቲሸርትና ቁጥር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መሰጠት እንደሚጀምር አዘጋጅ ቢሮው አስታወቀ።

በ2010 ዓ.ም የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተመዝጋቢዎች መለያ ቁጥራቸውን ሳይለጥፉ መሳተፍ እንደማይችሉ አዘጋጅ ቢሮው ከዚህ ቀደም መግለጹ የሚታወስ ነው።

የውድድሩ ተሳታፊዎች የሚሰጣቸውን የመሮጫ ቁጥር በሚለብሱት የሩጫ ቲ-ሸርት ደረት ላይ መለጠፍ ግዴታ እንደሆነም እንዲሁ።

ይህ የውድድር ቁጥር ልዩ የመለያ ኮድ ያለው በመሆኑ በህገ-ወጥ መልኩ ታትመው የሚሸጡ ቲሸርቶችን ለመከላከል የሚያስችል ነው ተብሏል።

ሊካሄድ 15 ቀናቶች በቀሩት የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመሮጫ ቲሸርትና ቁጥር ለተሳታፊዎች ከህዳር 8 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኤግዚቢሽን ማዕከል መሰጠት እንደሚጀምር ነው ቢሮው ያስታወቀው።

የዘንድሮ የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ህዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን 44 ሺህ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና የታላቁ ሩጫ ውድድር ከመካሄዱ አንድ ቀን በፊት በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የህጻናት ሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ገልጿል።

በዚህ ውድድር 3 ሺህ 500 ህጻናት እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአካል ጉዳተኞች መካከል የሚካሄደውን ውድድር ጨምሮ እድሜያቸው ከ11 ዓመት በታች ለሆኑ ሴቶችና ወንዶች በ3 የተለያዩ የእድሜ ክልል ተከፍሎ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

 

Published in ስፖርት

ህዳር 3/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስካይትራክስን የአራት ኮከብ ደረጃ  ምስክር ወረቀት አገኘ፡፡

ጥቅምት 29/2010 ዓ.ም ለንደን በተካሔደው ልዩ ስነስርዓት  ነው ታዋቂው የአየር ትራንስፖርት ደረጃና ጥራት መዳቢ ድርጅት የምስክር ወረቀቱን ያበረከተለት፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤድዋርድ ፕላይስትድ እንዳሉት አየር መንገዱ የሀገሪቱን ባህልና እንግዳ ተቀባይነት የማስተዋወቅ ኃላፊነቱን  በመወጣት ላይ ነው፡፡

አየር መንገዱ ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረውን አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ መቀየሩንም ነው ያብራሩት፡፡ ለዚህም በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተረከባቸውን አዳዲስ አውሮፕላኖች በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የአራት ኮከብ እውቅና የምስክር ወረቀቱ በኢትዮጵያ አየር መንግድ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ደንበኛ ተኮር አየር መንገድ እንደመሆኑም  የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እውቅና ማግኘታቸው አስደሳች መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡

አየር መንገዱ በላቀ አገልግሎት አሰጣጡ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ሽልማቶችን ቢያገኝም አሁን በዘርፉ ባለሙያዎች ተጠንቶ  ያገኘው ደረጃ ለአየር መንገዱ ምርትና አገልግሎት እውቅና የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ለአየር መንገዱ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞችም መስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሽልማቱ የደንበኞችን አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚያነሳሳም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሁን በፊትም የስካይ ትራክስን በአፍሪካ ምርጥ የአየር መንገድ ስታፍ ሽልማት ለሁለት ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን በቅርቡም የድርጅቱን በአፍሪካ ምርጥ ዓለም ዓቀፍ አየር መንገድ ሽልማት መውሰዱን ቮይስ ኦንላይን አስታውሷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ህዳር 3/2010 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ያስተዋወቃቸውን የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎች በማልማት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

 በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ ቀበሌ 10 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አበበ ''ደይ መረጭ'' በተባለው አረም ምክንያት ላለፉት 25 ዓመታት ምንም ዓይነት ባቄላ አምርተው አያውቁም ነበር፡፡

 በዚህም ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

 "ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማእከል የተገኘውን ''አሸንጌ'' የተባለውን የባቄላ ዝርያ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በመዝራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው" የገለፁት፡፡

 ዘንድሮ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻለውን የባቄላ ዝርያ መዝራታቸውንና አዝመራው የተሻለ ቁመና ላይ ስለሚገኝ እስከ 50 ኩንታል ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

 ከ200 በላይ የሚሆኑ የቀበሌው አርሶ አደሮችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል የተሻሻለውን የባቄላ ዝርያ መዝራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

 በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳ የበጤ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በድሩ ኡስማን በበኩላቸው አካባቢው በአቀንጭራ አረም የሚጠቃ በመሆኑ ከአንድ ሄክታር መሬት የሚያገኙት የማሽላ ምርት ከስምንት ኩንታል እንደማይበልጥ ተናግረዋል  ።

 አንዳንዴም ምንም ዓይነት ምርት እንደማያገኙ አስታውሰዋል፡፡

 በመኸር የዘር ወቅት ''ብርሃን'' የተባለውን የማሽላ ዝርያ ተጠቅመው ያለሙት ማሳ በአቀንጭራ አለመጠቃቱንና የተሻለ ፍሬ መያዙን አመልክተዋል፡፡

 በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳ የመነደፈራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈንታው አሊ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የተገኘውንና ''ዶርፐር''   የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የበግ ዝርያ ከምርምር ማዕከሉ አግኝተው በማዳቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 ከማእከሉ  ባገኙዋቸው  በግ ዝርያዎችን በማራባት   በሶስት ዓመት ውስጥ 40 የሚደርሱ በጎች ባለቤት እንድሆን አስችሎኛ ብለዋል ።

 "በኑሮዬም ለውጥ አግኝቻለሁ" የሚሉት አርሶ አደር ፈንታው የተሻሻሉት የበግ ዝርያዎች እድገታቸው ፈጣንና ከፍተኛ የስጋ መጠን ያላቸው ስለሆኑ ገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ እንደሚያወጡ አስረድተዋል፡፡

 "ገበያ ላይ ከአካባቢ የበግ ዝርያዎች ከ400 ብር በላይ ብልጫ ስላላቸው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል፡፡

 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ ጋሻው እንዳሉት ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ችግሮች የሚፈቱ  በሰብልና ተፈጥሮ ኃብት ልማት፣ በእንስሳት ልማትና በደን ምርምር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው ፡፡

 በብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ እውቅና ያገኙ 56 የሰብል ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ማድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

 በተለይ ብርሃን፣ ጎብዬ፣ ሆርማትና አብሽር የተባሉት የማሽላ ዝርያዎች አረም፣ በሽታንና ድርቅን የሚቋቋሙ፣ ከአካባቢው ዝርያ ቀድመው ለምርት የሚደርሱ በመሆናቸው በአርሶ አደሩ ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

 እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ማዕከሉ በ2009/2010 የምርት ዘመን በሶስቱ ዞኖች ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተሸሻሉ የሰብል ዝርያዎች የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም እስከ 120 ሺህ ኩንታል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 በተጨማሪ የስጋ ምርታቸው የተሻሻሉ፣ በፍጥነት የሚያድጉና ገበያ ላይ የተሸለ ዋጋ የሚያወጡ ከደቡብ አፍሪካ የተገኙ "ዶርፐር" የተባሉ የበግና "ቦር" የተባሉ የፍየል ኮርማዎች ለ77 አርሶ አደሮች ተከፋፍለው 567 የተዳቀሉ ፍየልና በጎች ተወልደዋል፡፡

 በ2009/2010 የምርት ዘመንም 15 ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀዋል፡፡

 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ 30 ዓመታት እንደሆነው ታውቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሀን  ህዳር  3/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን በየደረጃዉ ለሚገኙ 18 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች በለውጥ መርሀ ግብሮች፣ በመልካም አስተዳደር ፅንሰ ሀሳብና አተገባበር ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ሲቨል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሲሳይ አማኑኤል ለኢዜአ እንደገለጡት ለ15 ቀናት የሚሰጠው ስልጠና በሰባት ሰነዶች ትኩረት ያደረገ ነው።

 ስልጠናው ሰራተኞች በመመሪያዎችና ደንቦች በቂ እውቀት ጨብጠው ግልጽነት በመፍጠር የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል ።

 "እንዲሁም ሰራተኛውን በእውቀትና በክህሎት በማብቃት ከህብረተሰቡ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ሰራተኛው በሰራው ልክ እንዲመዘን የሚያግዝ መሆኑንም ነው " ብለዋል ።

 ከተሳታፊዎች መካከልም ወይዘሮ እንግዳጌጥ ሀይሉ በሰጡት አስተያየት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዝርዝር በመለየት ስራዎችን በእቅድ ለመምራት ግንዛቤ ፈጥሮላቸዋል ።

 በዞኑ ግብርና መምሪያ የግብርና ግብአቶች አቅርቦትና ስርጭት ባለሙያ አቶ ቸርነት ይጥና እንዳሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመፍታት ስልጠናው አቅም የፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

 በቀጣይ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ አቅርቦትን  አርሶ አደሩን ባሳተፈ እቅድ ላይ እንዲወሰን ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

 በዞኑ አደጋ መከላከልእና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሰራተኛ ወይዘሮ ትእግስት ገብረማሪያም በበኩላቸው አድሎአዊ አሰራርን በምን መንገድ መከላከል እንደሚቻል እውቀት ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን