አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 11 November 2017

መቀሌ ህዳር 2/2010 የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ80 ሺህ ለሚበልጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና ጥገና ስራ የሥራ እድል እፈጥራለሁ አለ።

 በትግራይ ክልል በዘርፉ ለመሰማራት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና የወሰዱ 42የኢንጂነሪንግ ምሩቃን ወጣቶች በመቀሌ ከተማ ዛሬ ተመርቀዋል።

 በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አገር አቀፍ ኮንዶሚኒየም ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋይ ንረአዮ እንደገለፁት፣በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ፍላጎት ከፍተኛ ነው።

 በየጊዜው የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በጋራ መኖሪያ ቤቶች በግል ባለሃብቶች በሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች በውሃ ተቋማትና ሌሎችም አካባቢዎች  በባለሙያ የታገዘ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

 ተቋሙም አሁን ባለው አቅም የበርካታ ደንበኞቹን የሀይል ፍላጎት ለማሟላት እንደሚቸገር ገልጸው "ከከፍትኛ የትምህርት ተቋማት በኤሌክትሪካል ፣ በመካኒካልና በሲቪል ምህንድስና የተመረቁ ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራው ማሰማራት አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

 በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠር በመግለጽ በአዲስ አበባ ከተማና በትግራይ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

 "በቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር  ተመሳሳይ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራው ለማሰማራት ጥረት ይደረጋል" ያሉት አቶ ተስፋይ በዚህ ዙርም መሰረታዊ እውቀት የሚያስጨብጥ ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

 ለ15 ተከታታይ ቀናት የተሰጠው ስልጠም ባለ15 ኪሎ ቮልት የሀይል ማስተላለፊያ የኤሌክትሪክ ገመድ ከመዘርጋት ጀምሮ እስከ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ መግጠም ድረስ ያሉትን ስራዎች ያካተተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 ከዚህ በኋላ ከተቋሙ የሚሰጣቸውን ስራ በመቀበል ተቋራጭ ሆነው በአገር አቀፍ የኤሌክትሪፊኬሽን ስራዎችና በሌሎችም ፕሮጀክቶች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

 ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህንድስና ምሩቅ የሆነው ወጣት በረከት ገብረዮሐንስ እንደተናገረው የተሰጠው ስልጠና ቀጣይ የስራ አማራጩን የሚያሰፋበትን እድል የሚፈጥር ነው።

 የተሰጠ ስጠናም የኤሌክትሪክ ምሰሶ ከመትከል ጀምሮ እንደ ቆጣሪ መግጠምና መሰል ስራዎች በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፉ በመሆናቸው ውጤታማ ስራ ለማከናወን እንደሚያግዘውም ተናግሯል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ ህዳር 2/2010 በመስኖ በሚያመርቱት የአትክልት ምርት ዓመታዊ ገቢያቸውን ማሳደግ እንደቻሉ የጌዲኦ ዞን አርሶአደሮች ተናገሩ፡፡

በዞኑ በበጋ ወራት ሰባት ሺህ 143 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከአንድ ሚሊዮን 34 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የዞኑ እርሻና ተፈትሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገልጿል ፡፡

በዲላ ዙሪያ ወረዳ የአንዲዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱልቃድር አቡበከር ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ የመስኖ ልማት ከመጀመራቸው በፊት ቡናና እንሰት ብቻ ነበር የሚያመርቱት ፡፡

በእዚህም ዓመታዊ ገቢያቸው ከአምስት ሺህ ብር ያልዘለለ ነበር፡፡

እንደ አርሶአደሩ ገለጻ፣ በ2004 ዓ.ም መስኖ በመጠቀም አትክልት ማምረት ከጀመሩ በኋላ ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡

በውሃ መሳቢያ ሞተር ከወንዝ ውሃ በመጥለፍ ሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ ጥቅል ጎመንና ቃሪያ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያመርቱ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ዙር ምርታቸው በአማካይ እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ገልጸው " በአትክልት ምርት ካገኘሁት ገቢ ባለ 46 ቆርቆሮ ክዳን ቤት ሰርቺያለሁ" ብለዋል ፡፡

ከአርሶ አደር አብድልቃድር ተሞክሮ ወስጂያለሁ የሚሉት የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ኤልያስ ታደሰ አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በሩብ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቃሪያ ማምረታቸውን ገልፀዋል ፡፡

ከምርቱም ከሦስት ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውንና ዘንድሮም የመስኖ ሥራቸውን በሥፋት ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል ፡፡

"አርሶ አደሩ ለመስኖ ያለው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ የተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው" ያሉት ደግሞ የአንዲዳ ቀበሌ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዱኛ ከበደ ናቸው ፡፡

ዘንድሮ በቀበሌው 57 ሄክታር በመስኖ በማልማት ሰባት ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማምረት የታቀደ ሲሆን አምና ከለማው ጋር ሲነጻጸር የ28 ሄክታር ብልጫ አለው ፡፡

የዞኑ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት ያሬድ በበኩላቸው በዘንድሮ የምርት ዘመን በዞኑ ሰባት ሺህ 143 ሄክታር መሬት በመስኖ እንደሚለማ ገልጸዋል ፡፡

ከዚህም ፣ አንድ ሚሊዮን 34 ሺህ 50 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የገለጹት።

አጠቃላይ ከሚለማው መሬት ስድስት ሺህ 707 ሄክታር ለጓሮ አትክልት ልማት የሚውል ሲሆን ቀሪው ለሥራሥር ፣ ለአገዳና ለጥራጥሬ ሰብሎች እንዲሁም ለሸንኮራ አገዳ፣ ለእንሰትና ፍራፍሬ ልማት የሚውል ነው ፡፡

የአርሶ አደሩን የውሃ አማራጭ ለማስፋትም 185 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ ሦስት መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል ፡፡

ከነባር የውሃ አማራጮች በተጨማሪ አንድ ሺህ 493 ሄክታር ማልማት የሚችሉ አዳዲስ የእጅ ጉድጓድ፣ የኩሬ፣ የቤተሰብ ገንዳ፣ የምንጭና አነስተኛ ወንዝ ጠለፋ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ወይዘሮ ሰላማዊት እንዳሉት፣ እስካሁን ዘንድሮ ከሚለማው መሬት ሦስት ሺህ 971 ሄክታር የሚሆነውን የሚያለሙት አርሶ አደሮች ተለይተዋል ፡፡

በ2009 የምርት ዘመን ሰባት ሺህ 139 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ በወቅቱ ባጋጠመ የፀጥታ ችግር ሊለማ የቻለው ሦስት ሺህ 422 ሄክታር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም 528 ሺህ 648 ኩንታል ምርት ብቻ መሰብሰቡን ወይዘሮ ሠላማዊት ተናግረዋል ፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 የአሜሪካው ኦሃዮ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ አንድ ጤና ኢኒሼቲቭ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ ከፈተ።

 የቅርንጫፉ መከፈት ኢትዮጵያ የእንስሳት ኃብቷን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚ እንድትሆን አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

 ኢኒሼቲቩ በኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ሆኖ ተመዝግቧል።  

 በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የአንድ ጤና ፕሮግራም በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጥበቃ፣ በተቀናጀ ጤና፣ በጥናትና ምርምር፣ በፖሊሲና ትግበራ ላይ ይሳተፋል።

 ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራትና ከሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችና ወረርሽኝን ለመከላከል ለ10 ዓመታት ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል።

 የኢኒሼቲቩ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ወንድሙ ገብረየስ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ፣ የደን መመናመንና የከተሞች መስፋፋት ለዓለም ተለዋዋጭነትና ለበሽታዎች መበራከት ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል። 

 በአዲስ አበባ የሚከፈተው የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ የተቀናጀ የጤና አጠባበቅ ተግባራትን እንደሚያፋጥንም አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው የዜጎችን ሕይወት በየጊዜው ከሚከሰቱ ወረርሽኞች ለመከላከል፣ የዜጎችን አኗኗር ለማሻሻልና ለባለሙያዎች አቅም ግንባታ የሚኖረው ሚና የጎላ እንደሆነም አክለዋል።

በኢትዮጵያም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን የአቅም ችግር ለመፍታት የራሱ ሚና እንደሚኖረው ፕሮፌሰር ወንድሙ ጠቁመዋል።

የኦሐዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብሩስ ሚክፌሮ በበኩላቸው የዓለም ሕዝቦች ፍልሰትና ትስስር በዳበረበት በዚህ ዘመን በማንኛውም ስፍራ የሚከሰት የተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ ለየትኛውም የዓለም አካባቢ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል። 

 የእንስሳትና ዓሳ ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በእንስሳት ኃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

 እንደ ዶክተር ምሥራቅ ገለጻ ይህ ሊሆን የቻለው በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቻው የቁም እንስሳት በሽታዎች መበራከት ነው።

 በዓለም የሚከሰቱ አዳዲስና ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ አህጉር ዘለል በሽታዎች የሚደርሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታት በጋራ መቆም እንደሚያሻም አመልክተዋል።

 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት ያለውን የቤተ ሙከራ ክፍተት ለመድፈን መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል። 

 በሁሉም የጤና መስኮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

 ዓለም አቀፉ አንድ ጤና ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር ለመሥራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርሟል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባላት ሠላም በማስፈንና ግጭቶችን በመከላከል ረገድ ህብረተሰቡን በማስተማር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገለፁ።

ምክር ቤቱ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል። 

ምክር ቤቱ ዛሬ 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በአገሪቷ ሠላምና ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በ2009/10 የእቅድ ክንውን ሪፖርቱ ላይ ተወያይቷል።

በጉባኤው የተሳተፉት የሁሉም ክልሎች የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቶች በሠላም መስፈንና ግጭቶችን በመከላከል ረገድ ግንዛቤ በመፍጠር የተጣለባቸውን ሕብረተሰቡን የማስተማር ግዴታ እንደሚወጡ ነው የተናገሩት።

የኦሮሚያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አህመድ ሳሌ "ኦሮሚያ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው፤ እኛ ውስጥ የሌለ ብሔረሰብ የለም በሠላም እየኖርን ነው አብረን ነው ያለነው።"ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱራህማን ሀሰን ሁሴን በበኩላቸው"እኛና የኦሮሞ ህዝብ አንድ ነን በተለይ ጎረቤት ስለሆንን አንድ ባህል አለን፤ ስለዚህ በመሃላችን የተከሰተው ግጭት በጣም ይሰማናል፤ በጣም አዝነናል ሁላችንም የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ነው አንድ ያደረገን ማክበር ይገባናል።"

የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሃጂ አባብ አብጅብል እንዳሉት "የኢትዮጵያ ህዝብ ትላንት ርሃብተኛ ፣ ቁስለኛ ነው በየመስጊዱና በየቤተክርስቲያኑ ያለቅስ ነበር ይሔ ሁሉ ቀርቶ አላሃ ይሄን አይቶ ባለ ልማቶች ነን ዛሬ ለዓለም ተምሳሌት እየሆንን ነው ያለነው፣ ልማታዊ መንግሥት ሰርቷል። ዛሬ ወደ ኋላ ወደ ቀድሞ እንመልሳለን ብለው የሚሯሯጡ ኃይሎች አሉ ይሄንን እንቃወማለን።"

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሃመድ ሸሪፍ ሐሰን "እዛ የተጫረው እሳት ሌላ ቦታ ላይ አይደርስም ተብሎ አይጠበቅም፤ እያንዳንዱ በተለይ የክልል መስተዳድሮች፣ ክልል ላይ ያሉት የመጅሊስ አመራሮች ይሄንን ትኩረት ሰተን እንዲህ አይነት ነገሮች እንዳይከሰቱ በከፍተኛ ደረጃና ጥንቃቄ ልናስተምርና ልንቀሰቅስ ይገባል።" ነው ያሉት ፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ"ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በሰላም አብሮ ተከባብሮ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና የሃይማኖት ብዝሃነትን የምታስተናግድ ሀገር ናት። በእርግጥ ይህ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሰላም አሁን ደግሞ በአንዳንድ ጥገኛ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች ሲደፈርስ ይታያል፤ ይሄን የሰላም ማጣት በመጀመሪያ ደረጃ ልናስወግድ የምንችለው በማስተማር ነው።" ብለዋል

 የምክር ቤቶቹ ፕሬዚዳንቶች አገሪቱ የምትታወቅበትን የመደጋገፍ፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች የሚሸረሽሩና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ያለሙ የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ እንደሚታገሉም በአፅንኦት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል "የሃይማኖታችን መሰረቱ ሰላም በመሆኑ ጠቅላይ ምክር ቤቱ የአብሮነት እሴት እንዲጎለበት ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አበክሮ ይሰራል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሃፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው ለዘመናት የዘለቀው የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ጠንካራ እሴት መሰረቱ የሃይማኖት አስተምህሮ ሲሆን ሌላው ከአብሮነት ታሪክ የተወረሰው ሰላማዊ ግንኙነት ውጤት ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከኢትዮጵያዊነት እሴቶች ባፈነገጠ መልኩ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስና ያለመረጋጋት ሁኔታ በሃይማኖቶች አስተምህሮ ተቀባይነት የሌለውና የአብሮነትና የመከባበር እሴትን እንደሚቃረን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና ጠቅላይ ምክር ቤቱ የክልሎች እስልምና ምክር ቤቶችን አቅም ለማጎልበትና መንፈሳዊና ልማታዊ አገልግሎታቸውን ከግብ ለማድረስ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 12 ቶዮታ ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪዎችን አስረክቧል።

ተሽከርካሪዎቹ በጠቅላይ ምክር ቤቱና በክልሎች የተጀመሩ እቅዶችን ከግብ ለማድረስ እንዲሁም ወደ ታችኛው እርከን መዋቅሮች በመውረድ የህዝበ ሙስሊሙን ችግሮች ለማድመጥና ተደራሽነታቸውን ለማጎልበት አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል። 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 በማረሚያ ቤቶች መልካም አስተዳደር ለማስፈንና የሕግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር በሙያዊ ብቃት የታነፀ ባለሙያ ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

 በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የአሌልቱ ማሰልጠኛ ተቋም በመካከለኛ አመራርነትና በማረሚያ አባልነት ለሶስት ወር ያሰለጠናቸውን 440 ሰልጣኞች አስመርቋል።

 የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ረጋሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የሙያ ብቃትና የስራ ትጋት ያለው ሰራተኛ ካለ የተቋም ራዕይ፣ ተልእኮና እቅድ ይሳካል፤ ውሳኔዎችም በሙያዊ ብቃት የተደገፉ ይሆናሉ።

 ተቋሙ የሙያ ብቃትና የስራ ትጋት ያላቸው አባሎችና ሰራተኞችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ተመራቂዎቹ የዚሁ አካል መሆናቸውን መገንዘብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ታራሚዎችና ቤተሰቦቻቸውን በቅንነት እንደሚያገለግሉ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

 የማሰልጠኛ ተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ሙላቱ ጫንያለው ለመጀመሪያ ጊዜ በማረሚያ አባልነት የተመረቁት 142 ሰልጣኞች በተቋሙ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የቆዩና ስልጠናውን በፍላጎታቸው መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

 በመካከለኛ አመራርነት የሰለጠኑት 298 መካከለኛ አመራሮች የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን ጨምሮ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላና ሀረሪ ክልሎች የተውጣጡ ናቸው።

 ተመራቂዎቹ በቆይታቸው መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና መውሰዳቸውን የገለጹት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ሙላቱ በቂ የንድፈ ሀሳብ ስልጠና እንደተሰጣቸውም አክለዋል።

 ተመራቂዎቹ በበኩላቸው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ባገኙት እውቀትና ልምድ ታራሚዎችና ቤተሰቦቻቸውን በቅንነት ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

 

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 የስዊዘር ላንድ ሲካ ግሩፕ የኬሚካል አምራች ኩባንያ በ10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ያስገነባውን የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ አስመረቀ።

 ሲካ አቢሲኒያ የኬሚካል ፋብሪካ በሚል የሚጠራው ተቋም ሆለታ አካባቢ ግንባታው የተጀመረው በ2008 ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ሶስት የኬሚካል ዓይነቶችን ማምረት እንደጀመረ ተገልጿል። 

 የፋብሪካው የገበያ ማናጀር አቶ ፍፁም ንጉሴ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው ለግንባታ ስራ የሚሆኑ ውህዶች፣ ለመስታወትና ለባኞ ቤቶች መገጣጠሚያ ሲልከን፣ ከባክቴሪያ ነፃ የሆነ ወለል ለመስራት የሚያስችለውን ኢፖክሲ ኬሚካል ዓይነቶች ማምረት ጀምሯል።

 ፋብሪካው የራሱ የላቦራቶሪ ክፍሎች እንዲሁም የስልጠና ማዕከል እንዳሉት ገልፀዋል።

 ለፋብሪካው ግብዓቶች የተለያዩ ምርቶችን ከውጭ እንደሚያስገቡ የጠቆሙት አቶ ፍፁም፤ ከስኳር ፋብሪካዎችና ከሌሎች ፋብሪካዎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶች በአገር ውስጥ ላቦራቶሪ በመመርመር የኬሚካል ይዘቱ አይቶ ለመጠቀም እንዲቻል ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

 ይህም ለግብዓት መግዣ የሚውለውን የውጪ ምንዛሪ ከማውጣት ለማስቀረት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

 ፋብሪካው የሀገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን 50 በመቶ ሊሸፍን እንደሚችል ጠቁመዋል።

 በሲካ ግሩፕ የአፍሪካ ኃላፊ ኢቮ ሻድለር እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማቶች መስፋፋትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣት ፋብሪካውን ለመክፈት ምክንያት ሆኗቸዋል።

 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውሰጥ የፋብሪካው መከፈት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶችን እዚሁ ለማምረት ያስችላል።

 ፋብሪካው የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርም ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

 የሌሎች አገሮች ኩባንያዎችም በተመሳሳይ መልኩ "በዘርፉ ይሰማራሉ" የሚል እምነት መኖሩን ጠቁመው፤ መንግስት ለኩባንያዎቹ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ተናግረዋል።

 ፋብሪካው ለጣሪያ መገጣጠሚያ የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ለማምረት እየተዘጋጀ መሆኑን የተጠቆመ ሲሆን፤ ወደፊት ምርቶችን ወደ ተለያዩ አገሮች እንደሚልክ ተገልጿል።

 ሲካ ግሩፕ በዓለም ከ99 በላይ ፋብሪካዎች ያሉት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ነው።

 

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ህዳር 2/2010 የስኳር እጥረት በኑሯቸው ላይ አሉታዊ  ተጽእኖ  እንዳሳደረባቸው በነቀምቴ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በከተማዋ የቀበሌ ዜሮ ሶስት ነዋሪ ወይዘሮ ትእግስት ቀኖ  እንዳሉት ኑሮቸውን የሚመሩት በማህበር ተደራጅተው ሻይ አፍልተው በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ነበር ።

በከተማው ስኳር እንደልብ በነበረበት ወቅት በቀን ሶስት  ኪሎ ስኳር ተጠቅመው በሚያፈሉት ሻይ በቂ የሚባል ገቢ እንደነበራቸው አመልክተዋል።

አሁን ግን በከተማው ስኳር ከጠፋ ወራት በመቆጠሩ ቡና አፍልተው በመሸጥ ብቻ ኑሯቸውን ለመግፋት ቢገደዱም አብዛኛዎቹ የቡና ደንበኞች ስኳር ተጠቃሚ በመሆናቸው ገበያቸው መዳከሙን ጠቅሰዋል።

በስኳር መጥፋት የተነሣ ቁርስ ቤታቸውን ለመዝጋት መቃረባቸውን የገለፁት ደግሞ  ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ነጋሣ ናቸው፡፡

ስኳር ካገኙ ከሶስት ወር በላይ እንደሆናቸው ያመለከቱት ወይዘሮ እመቤት በስኳር እጦት ምክንያት የሻይ ፣ ወተትና የጭማቂ ገበያው ከተስተጓጎለ መሰነባበቱን ጠቁመዋል ።

የገበያው መቀዛቀዝ ቀርቶ ለቤተሰብ ፍጆታ የሚያስፈልገውን እንኳን አጥተው መቸገራቸውን ጠቁመው የሚመለከተው አካል መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ሳራ ሙሴ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ከመስከረም ወር ወዲህ ስኳር ከከተማው በመጥፋቱ በፍጆታም ሆነ በንግድ ስራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የንግድና የገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍርዲሣ ገመዳ ስለጉዳዩ  ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የስኳር እጥረት ያጋጠመው እንደ ሀገር መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሆኖ  መንግስት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ለከተማዋ የሚያስፈልገው ወርሃዊ የስኳር ኮታ 2ሺህ 800 ኩንታል ነው፤ የተላከላቸው ግን 500 ኩንታል ብቻ በመሆኑ ለ44 ሺህ አባወራዎች ማዳረስ አይችልም።

በቅርቡ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን 2ሺህ 800 ኩንታል  ስኳር ለህብረተሰቡ እንደሚከፋፈልና ችግሩ እንደሚቃለል አመልክተዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ህዳር 2/2010 የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በጥልቅ ተህድሶ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን 857 መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በማጣራት ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

 የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን የሕዳር 11 በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ ብአዴን አመራሩ የተሰለፈበትን ዓላማ የመሳት ችግር አጋጥሞት ነበር።

 በተለይ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ከባድ ጥርጣሬ አሳድሮ ስለነበር ብአዴን ችግሩን ለማጣራት ሰፊ ሥራ ሰርቷል።

 አመራሩን ፊት ለፊት ከመገምገምና ከማስተካከል በተጨማሪ ከድርጅቱ የአሰራር መርህ ውጭ የእውነት አፈላላጊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በልዩ ሁኔታ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

 ግብረ ኃይሉ በየአካባቢው በተቀመጡ የሃሳብ መስጫ ሳጥኖችና በአካል የደረሱትን 857 ጥቆማዎችን የማጣራትና እውነቱን የማግኘት ሥራ መሰራቱንም አቶ አለምነው አመልክተዋል።

 በእዚህም ከቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ 117 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ሆነው መገኘታቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት መሬት ያለአግባብ በመውሰድ፣ ከግብር ስወራና በዝምድና ከመቅጠር ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተረጋግጧል።

 ጥቆማ ከደረሰባቸው 740 መካከለኛ አመራሮችም 355ቱ መሬትን ደራርበው በመውስድና በመሰል ችግሮች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

 በሙስና ችግር ውስጥ የተገኙትን ከኃላፊነት ቦታቸው የማንሳትና ዝቅ ብለው እንዲመደቡ እንዲሁም በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

 እንደ አቶ አለምነው ገለጻ፣ ብአዴን ከህዝባዊነቱ ላለመለየት ችግሮቹን በጥልቅ ታህድሶ በመገምገም የማስተካከል ሥራ እየሰራ ነው።

 ከጥልቅ ተሀድሶ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት የአመራሩን የተዛባ አመለካከት በማስተካከል የአስተሳሰብ ግልጽነትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እየዳበረ መምጣት ከተገኙ ውጤቶች ቀዳሚ መሆኑን አስታውቀዋል።

 ከእዚህ በተጨማሪ ከህዝብ ጥቅም ጎን በመቆም ፊት ለፊት የመታገልና የማስተካከል ልምድ መገኘቱንና የህዝብ ጥረትን የሚደግፍ አመራር ማግኘት እየተቻለ ነው።

 አቶ አለምነው እንዳሉት፣ የሕዝብ አንገብጋቢ ችግር ለይቶ መፍታት፣ ህዝባዊ አንድነትን መገንባት፣ ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትን ማዳበርና መሰል ለውጦች ከጥልቅ ታህድሶ በኋላ በድርጅቱ የመጡ ለውጦች ናቸው።

 በርካታ የሚቀሩና በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

 በቀጣይ የተጀመሩ ለውጦችን በመያዝ ከህዝቡጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመታገል የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አቶ አለምነው አስታውቀዋል።

 "የብአዴን ህዝባዊነትና የአላማ ፅናት ለዴሞክራሲያዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል የድርጅቱን 37 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።

 ጨዋታው በሩዋንዳ  ኪጋሊ ይካሄዳል።

 ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ በምታስተናግደው የቻን ውድድር ለመሳተፍ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ ሶስት ለሁለት በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል።

 ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ለመሳተፍ በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በአንጻሩ ከሜዳዊ ውጭ ያሸነፈው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር የማለፍ ዕድሉን አስፍቷል።

 ቡድኑ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ሁለት ጊዜ መሪ መሆን ቢችልም ውጤቱን ማስጠበቅ ካለመቻሉ ባለፈ የሜዳ ዕድሉንም መጠቀም አልቻለም። 

 የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ግቦች የተቆጠሩት በግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሃኑ ስህተት ነበር።

 የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወንዶች እግር ኳስ ቡድን በሱዳን ተሸንፎ ከ2018ቱ የቻን ውድድር ውጪ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። 

 ሆኖም ግብፅ በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) በውድድሩ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ጥያቄ አለመቀበሏን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የማጣሪያ ጨዋታ አድርገው አሸናፊው ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር እንዲሳተፍ ካፍ ውሳኔ አስተላልፏል።

 የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ 16 አገሮች የሚካፈሉበት ሲሆን የዘንድሮው ውድድር ለ5ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።

Published in ስፖርት

 ባህርዳር ህዳር 2/2010 በአማራ ክልል ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

 በቢሮው የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ እንደገለጹት የተሰበሰበው በመኽር ወቅት በተለያየ ሰብል ከለማው ከአራት ሚሊዮን 300 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ነው።

 የደረሰ ሰብልን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ጉልበት በማስተባበርና ሰራተኛ በመቅጠር ጭምር ትኩረት ሰጥቶ እየሰበሰበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 ቀድሞ የደረሰ የገብስ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎና የጥራጥሬ ሰብል  የተሰበሰቡ ሲሆን አሁንም አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ ቀሪውን ሰብል ከእርጥበትና ከብክነት በጸዳ መልኩ እየተከታተለ እንዲሰበስብ አሳስበዋል።

 ከአጨዳ ጀምሮ ሰብሉ ተወቅቶ ወደጎተራ እስኪገባ ድረስ  የምርት ብክነትን ለመቀነስም ለግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ቀደም ብሎ ስልጠና ተሰጥቷል።

 ባለሙያው እንዳሉት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ካለፉት ዓመታት የተሻለና የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት መኖሩና የተፈጥሮ አደጋ አለመከሰቱ በምርት ዘመኑ ከ130 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።    

 በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የዱርጌ ማሽንት ቀበሌ  አርሶ አደር ብርሃን ይመር በምርት ዘመኑ አራት ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ፣ ስንዴና ባቄላ ሰብል ማልማታቸውን ገልጸዋል።

 ያለማቋረጥ በአካባቢው ይጥል የነበረው ዝናብ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ጋብ በማለቱ የቢራ ገብስን ጨምሮ ከግማሽ በላይ የሚሆን ሰብላቸው መሰብሰባቸውን አመለክተዋል፡፡

 ካለሙት አምስት ሄክታር ከሚጠጋ መሬት የደረሰ የጤፍና የባቄላ ሰብላቸውን መሰብሰባቸውን የተናገሩት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የጠጠር ጥጃጎጥ ቀበሌ አርሶአደር ተመስገን ደሴ ናቸው። 

 ባለፈው ዓመት በክልሉ በመኽር ከለማው አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ95 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን