አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 10 November 2017

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 በዘንድሮው ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቪሽን ሳምንት 144 ግለሰቦች እና አንድ ተቋም እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተገለጸ።

በብሔራዊ የሳይንስ፣የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሳምንት ከሚሸለሙት መካከል 106ቱ ወንዶች ሲሆኑ 38ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ከነዚህ መካከል አምስቱ በፈጠራና ምርምር 140ዎቹ በአጠቃላይ ትምህርት፣ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት እና ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡ ተማሪዎችና መምህራን ናቸው።

ሦስተኛው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሳምንትም ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ይከበራል።

ለሦስተኛ ጊዜ የሚከናወነው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሳምንት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ  በበዓውደ ርዕይና በፓናል ውይይት ነው የሚከበረው።።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር  ጌታሁን መኩሪያ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ አውደ ርዕዩ ለወጣቶች፣ ለተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለአንድ ሳምንት ክፍት ሆኖ ይቆያል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር ያስገነባቸውና ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲቀስሙ የሚያስችሉ አምስት የ"ሳይንስ ካፌዎች"  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደሚመረቁ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ተናግረዋል።

እንዲሁም ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሚደረገው የመዝጊያ ስነ ስርአት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  በስምንተኛው ብሔራዊ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ  ጉልህ አስተጽዖ  ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማትና እውቅና እንደሚሰጡ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ አሳውቀዋል።

ከ2002 ዓ.ም እስካለፈው ዓመት ድረስ ለ1 ሺ 456 ግለሰቦችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት መሰጠቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ሚዛን ህዳር 1/2010 ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቅው በጀት ዓመት ባከናወናቸው ተግባራት ያገኘውን የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ ለማስቀጠል እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንዳሉት ፣ ተቋሙ በአሶሳ ከተማ ከጥቅምት 6 አስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደ 35ኛ ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ላይ የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ አግኝቷል፡፡

የተማሪ አደረጃጀቶችን ማጠናከር፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር የቅርብ ክትትል ማድረጉና ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በጥምረት መስራቱ በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አስችሏል፡፡

"ያለሰላም የተቋሙን ተልዕኮ ማሳካት አይቻልም" ያሉት ዶክተር ፋሪስ፣ ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ጅምሮች በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ሰላም በተቋሙ ውስጥ እንዲሰፍን በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥና ከውጭ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ያካተተና በተቋሙ የበላይ አመራር አካላት የሚመራ የሰላምና ጸጥታ ኮማንድ ፖስት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ በወር አንድ ጊዜ በመሰብሰብ የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ይገመግማል፡፡

የሰላምና ጸጥታ ችግር መንስኤ የሚሆኑ የተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቅሬታዎችን በቅርበት በመከታተል ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱ ለተቋሙ ሰላም መረጋገጥ ድርሻው የጎላ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ውስጣዊ አደረጃጀቶችን ማጠናከርና ከአካባቢው ማሕበረሰብ ጋር በጥምረት የሚደረገው ቅንጅታዊ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ፋሪስ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገባቸው የሰላም እሴቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለጸችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው አራተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ስንዱ በላይ ናት፡፡

ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርሱ ጉዳዮች መነሻቸውን መለየትና ከምንጫቸው ማስቆም ዋናው መፍትሔ እንደሆነ ጠቁሟ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ለሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክታለች፡፡

"ለአዲስ ገቢ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች የኛን ልምድ በማጋራት ሰላማዊና ውጤታማ ቆይታ እንዲኖራቸው እንሰራለን" በማለት ተማሪዋ ተናግራለች፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 ኅብረተሰቡ በመንግሥት የተጀመረውን የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በመቀላቀልና በባለቤትነት በመምራት ከዳር ማድረስ እንደሚገባው የመንግስት ኮምዩኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

ጽህፈት ቤቱ "ድሎቻችንን መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ነው!" በሚል ርዕስ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ እንዳለው መላው ኢትዮጵያዊ በመንግሥት የተጀመረውን የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በመቀላቀልና በባለቤትነት በመምራት ከዳር ማድረስ ይገባዋል።

የአገሪቷ ሠላም በአስተማማኝ መልኩ እንዲጠበቅና የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ዕድገቶች እንዲፋጠኑ የኪራይ ሰብሳቢት አመለካከትና የጸረ ሠላም ኃይሉን በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት አስፈላጊ ነውም ብሏል።

ለዚህም ሁሉም ዜጋ እንደ ወትሮው ሁሉ በመንግሥትና በመላው ኅብረተሰብ በሚካሄደው የተቀናጀና የጋራ ርብርብ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቋል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

 

 

 

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

ሕዳር 01 ቀን 2010 ዓ.ም

ድሎቻችንን መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ነው!

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው፣ የአገራቸውን ጉዳይ ደግሞ በጋራ የሚወስኑበትን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስርተው መተዳደር ከጀመሩ አስርተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የቅራኔ ምንጮች የነበሩ ጉዳዮችን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋታቸውም አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም በራቀው የአፍሪካ ቀንድ እየኖረች በአንጻራዊነት ከመቼውም ጊዜ የተሻለች ሰላማዊት አገር መሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም የሰላም ዘብ መሆን ችላለች።

ህዝቦቻችን ሰላም በማግኘታቸውም ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልማት በማዞር ልማታቸውን እያፋጠኑና ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። የልማቱ ድምር ውጤትም አገራችንን በማያቋርጥ ፈጣን የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገኝ አስችሏታል። ይህም ለዘመናት ትታወቅበት የነበረውን መጥፎ ገጽታ ቀይሮት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ የዓለም አገራት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ አገር አድርጓታል። ከድህነትና ኋላቀርነት የምትላቀቅበትና ወደከፍታ ማማ የምትወጣበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑንም በተግባር ማረጋገጥ ችላለች።

እነዚህና ሌሎችም በርካታ ድሎች የመመዝገባቸውን ያህል ግን በየጊዜው የተከሰቱ ፈተናዎችም አጋጥመዋል። ዋናው ነገር ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ በመንግሥትና በህዝቦቻችን የጋራ ትግል እየፈታናቸው መምጣታችን ነው።

አሁን ባለንበት ወቅትም ቢሆን የሰላማችንን፣ የፈጣን ዕድገታችንን እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን ሂደት እየተፈታተኑ ያሉ እንቅፋቶችን ፊት ለፊት እየተጋፈጥን ነው የምንገኘው፡፡ ህዝባችንን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ሌሎችም  በጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የተለዩ ልዩልዩ ችግሮች በሚፈቱበት አግባብ ላይ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደሥራ ለመግባት ተሞክሯል። ከተከናወኑት አበረታች ሥራዎች መካከልም በወጣቶች ላይ በስፋት የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተደረጉ ጥረቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ ይቀረናል በሚል ተጨማሪ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሥርዓቱ ጤናማ ሆኖ መቀጠል የግል ጥቅማቸውን እንደሚያቋርጠው የተረዱ ያለአግባብ የመበልጸግ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ከጸረ ሰላም ሀይሎች ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ትግል ለማፈን ሲፍጨረጨሩ ታይተዋል። በሰላማዊ ህዝቦች መካከል ቅራኔን እስከመፍጠርና የአገራችንን ሰላም እስከማደፍረስ ብሎም ገጽታዋን እስከማበላሸት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ሞክረዋል።

ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባሮቹ ላይ የተጀመረው አገራዊ ትግል የአገራችን እና የህዝቦቿ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ነው። እንደዚያው ሁሉ ብሄር ተኮር ግጭቶች እንዲከሰቱና አለመረጋጋት እንዲኖር ምክንያት የሆኑትን ሃይሎች ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል ከዳር ማድረስ ለመንግሥት አካላት ብቻ የሚተው ተልዕኮ አለመሆኑንም በውል መገንዘብ ያሻል።

የአገራችን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ እንዲጠበቅ፣ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ እድገታችን እንዲፋጠን ብሎም ፈጣኑን የእድገት ጉዟችንን ለመቀልበስ እየተፍጨረጨረ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢ እና የጸረ ሰላም ሃይል በአስተማማኝ ሁኔታ ድባቅ መምታት የሚቻለው እንደወትሮው ሁሉ በመንግሥትና በመላው ህዝባችን በሚካሄድ የተቀናጀና የጋራ ርብርብ ብቻ ነው። በመሆኑም መላው የአገራችን ህዝቦች፣ በመንግሥት የተጀመረውን የጸረ- ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደወትሮው ሁሉ በመቀላቀልና በባለቤትነት በመምራት ከዳር እንዲያደርሱትና ለድል እንዲያበቁት መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል። ያስመዘገብናቸውን ድሎች መጠበቅና ማስቀጠል የምንችለው እንደወትሮው ሁሉ በህዝቦቻችን የላቀ ተሳትፎና ባለቤትነት ብቻ ነውና!

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 ኢትዮጵያ በኢጋድ ውስጥ የምትጫወተውን ሚና የትሮይካ አባል ሀገራት አድንቀዋል፡፡

የኢጋድ አባል አገሮች በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያደረጉ ያለውን ጥረት በተመለከተ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጻ አድረገውላቸዋል።

ትሮይካ የተሰኘው የሶስትዮሽ ቡድን እንግሊዝ፤ አሜሪካንና ኖርዌይን ያካተተ ሲሆን፤ አገሮቹ በደቡብ ሱዳንና ሱዳን የሰላም ሂደት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ናቸው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ጋር በመሆን ለአገሮቹ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ልዩ መልክተኞች የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች የደቡብ ሱዳን ሰላም በተፋጠነ መልኩ እውን እንዲሆን ተግባራዊ እያደረጉት ያለውን ጥረት በተመለከተ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለሰ አለም ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በአዲስ አበባ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ለአምባሳደሮቹና ልዩ መልዕክተኞቹ አብራርተዋል።

በስምምነቱ መሰረት የእስካሁኑ ሂደት በሁሉም ተቀናቃኝ ወገኖች ዘንድ የተኩስ አቁም ለማድረግ፣ መግባባቶችንና ለውጦችን ማምጣቱን ገልጸዋል።

የኢጋድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰላም ሂደቱ ዙሪያ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሃይሎችን ለማግባባት ያደረጉትንም ተጨማሪ ጥረት ለአባል አገሮቹ ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የደቡብ ሱዳን ሲቪክ ማህበራትን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችን በማካተት ሰላም ስለሚሰፍንበት ሁኔታ ለማማከር የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያደረጉትን ጥረት ዶክተር ወርቅነህ ማብራራታቸውንም ነው የጠቆሙት።

የትሮይካ አባል አገሮች እስካሁን ለሰጡት ድጋፍና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዶክተር ወርቅነህ ምስጋናቸውን በመግለጽ በቀጣይ እገዛቸውን  እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

አምባሳደሮቹና ልዩ መልእክተኞቹ ኢጋድ እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ በተለይም ኢትዮጵያ እየተጫወተች ላለችው የመሪነት ሚና እውቅና መስጠታቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ኢጋድ የአደራዳሪነት ሚና ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም በጥረቱ  የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

በገለጻው የአሜሪካ፣ ኖርዌይና እንግሊዝ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ልዩ መልክተኞች፣ በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደርና ሌሎች የፖለቲካ አማካሪዎች ተገኝተዋል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ህዳር 1/2010 በትግራይ ክልል በክረምት ወራት የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው ወረዳዎችን ለይቶ ድጋፍ ለማቅረብ ጥናት እያካሄደ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአደጋ መከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያና የምግብ ዋስትና የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ መስፍን ወልዱ እንዳሉት፣  ጥናቱ እየተካሄደ ያለው  በ2009/2010 የምርት ዘመን በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ ያጠቃቸው ወረዳዎችን  ለመለየት ነው፡፡

ይህም በክልሉ በመኸሩ ወቅት የክረምት ዝናብ ዘግይቶ  በአዝርዕት ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ በትክክል በማወቅ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ለማቅረብ ያስችሏል፡፡

ለዚህም  የምርት መጠን የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ ወደ ጥናት ስራው ተሰማርቷል።

ጥናቱ የዝናብ እጥረት በታየባቸው በክልሉ ራያና ዓዘቦ ፣ አላጀ ፤ እንደርታ ወረዳዎችን ጨምሮ  በ16 ወረዳዎች  ድርቅ ያጠቃቸውና  ደህና ምርት ያገኙ  ቀበሌዎችን የመለየት ጥናት ቡዱኑ እያካሄደ ነው።

የጥናቱ  ዓላማ ምን ያህል አርሶ አደሮች በድርቅ የተጠቁ መሆናቸውን ለይቶ በማረጋገጥ  የአስቸኳይ ጊዜ የቀለብ ድጋፍ ለማድረግ ነው።

በ2008/2009 የምርት ዘመን በክልሉ የዝናብ እጥረት ባጋጠማቸው 31 ወረዳዎች በተካሄደው ጥናት ከ300ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የምርት መቀነስ አጋጥሟቸው ነበር፡፡

ለአርሶ አደሮቹ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በየወሩ  ምግብ ፣ ምስርና ዘይት እየቀረበላቸው መሆኑ አቶ መፍስን አስታውሰዋል፡፡

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የሰሓርቲ ሳምረ ወረዳ የዓደቂዓላ  ቀበሌ  አርሶ አደር ሰይፉ ልኡል  በሰጡት አስተያየት "  ባለፈው ዓመት የዘራሁት ስንዴና ጤፍ  ፍሬ ላይ ሲደርስ የዝናብ እጥረት ስላጋጠመ  ከጠበቁት 20 ኩንታል ምርት አምስት ኩንታል ብቻ አግኝቻለሁ" ብለዋል።

ይህም ለስድስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ለዓመት ቀለብ እንደማይበቃ ጠቁመው  በዚህም ምክንያት በየወሩ ግማሽ ኩንታል ስንዴ የቀለብ ድጋፍ ከመንግስት እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በአካባቢያቸው በክረምቱ ወቅት  የዝናብ መቆራረጥ በማጋጠሙና የዘሩት  የስንዴ፤ ገብስና በቆሎ በውርጭ በመመታቱ የጠበቅኩት ምርት እንዳላገኙ የገለጹት ደግሞ በእንደርታ ወረዳ  የደብረ ቅብኢ  ቀበሌ  አርሶ አደር ኪሮስ መሓሪ ናቸው፡፡

ችግራቸውን ለመቃለል  በየወሩ ስንዴ፤ ምስርና ዘይት እየቀረበላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 እንግሊዝ የኢትዮጵያ መንግስት የባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር ሊያም ፎክስ የተመራውን የልዑካን ቡድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱ በሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ላይ ያተኮረ ነበር።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በአገሪቱ ያለውን የመንግስትና የግሉን ዘርፍ ሽርክናና የግል ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ለመስራት መታሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

 ይህን ለማድረግ በእንግሊዝና መሰል አገራት ያለው የዳበረ ልምድ ይጠቅመናል ብለዋል።

 በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለልዑኩ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወደ አገሪቱ የሚመጡ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ተቋማት ጉልበትን በስፋት በመጠቀም ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ቢሆኑ እንደሚመርጡ አስገንዝበዋል።

 የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር ፎክስ በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት የአገራቸው የንግድ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ተሳትፎና ድጋፍ የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።

 በርካታ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ሁለቱንም አገራት መጥቀም እንደሚችሉ የገለጹት ሚኒስትሩ የተካሄደው ውይይት ያለውን ፍላጎት በፍጥነት ወደ ተግባር ለመተርጎም እንደሚረዳ ነው ያመለከቱት።

 የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ኢነርጂና ቴሌኮሙኒኬሽን የልዑካኑን ትኩረት የሳቡ መስኮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 መንግስት የውጪም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የግሉን ዘርፍና የመንግስትን ሽርክና ለማጠናክር እየሰራ ያለው ስራ  አበረታች መሆኑን የገለጹት ዶክተር ፎክስ አገራቸው በዘርፉ ያላትን ልምድ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን አክለዋል። 

 የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ንግድ ፋይናንሱን በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዱ የአገራቱን የንግድ ግንኙነት እንደሚያሻሸለውም ነው የገለጹት። 

 በኢትዮጵያ ከ320 በላይ የእንግሊዝ ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን የአገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደገ በመምጣት ከ15 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ኢኮኖሚ

 

ጋምቤላ ህዳር 1/2010 በጋምቤላ ከተማ የዶላር ምንዛሬ ማሻሻያን ምክንያት በማደረግ በግንባታ እቃዎችና መሳሪያዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ኢዜአ ያነጋገረቸው  ተጠቃሚዎች ገለጹ።

 የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።

 ከነዋሪዎች መካከል በአነስተኛ ግንባታ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሰለሞን አለባቸው በሰጡት አስተያየት ከዶላር ምንዛሬ መጨመር ጋር ተያይዞ ለሕንጻ ግንባታ ሥራ የሚያገለግሉ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል።

 በተለይ በግድግዳ ቀለም፣ በሚስማር፣ በሲራሚክና በሌሎችም የግንባታ እቃዎች ላይ ከሃምሳ እስከ 100 ብር የሚደረስ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰዋል ።

 በዚህም ኮንትራት የያዙትን የግንባታ ስራቸውን ለማቋራጥ መገደደቸውን ገልጸዋል።

 በአንድ የበር ቋሚ ብረት፣ ላሜራና የአርማታ ብረት ላይ ከ70 እስክ 100 ብር የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የገለጹት ደግሞ በብረታ ብረት ሥራ የተሰማሩት አቶ ዮሐንስ ተስፋዬ ናቸው።

 የብረት ዋጋ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ በር፣ መስኮትና ሌሎች የብረታ ብርት ሥራዎችን የሚያሰሩ ደንበኞቻቸው በግማሽ ያህል መቀነሳቸውን ተናግረዋል። 

 በግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መንግስቱ አባተ በሰጡት አስተያየት የግንባታ እቃዎች ከሚያስመጡበት ቦታ በ17 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

 ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ያስገቧቸውን የግንባታ እቃዎች በነባሩ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታይዶር ቻንባንግ እንደገለጹት፣ በጋምቤላ ከተማ የዶላር ምንዛሬ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 72 ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸው ታሽገዋል።

 አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ቤታቸውን ከማሸግ ባለፈ በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

 አብዛኞቹ የታሸጉት የንግድ ድርጅቶች የግንባታ እቃ አቅራቢዎች መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ በእነዚህና በሌሎች ሸቀጦች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽሙ በሚገኙ አካላት ላይ መሰል እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

 እንደ አቶ ታይደር ገለጻ በአሁኑ ወቅት ከክልል እስከ ወረዳ ዋጋን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

 በጋምቤላ ከተማ ከ3 ሺሀ 600 በላይ ነጋዴዎች በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ከክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ  የተገው  መረጃ  ያመለክታል፡፡  

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 አገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ስያሜ መለወጥ ላይ ባለመስማማታቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ያዙ።

 ፓርቲዎቹ የምርጫ ቦርድ ስያሜና አወቃቀርን ጨምሮ በአደረጃጀቱ ላይ ለመደራደር በያዙት ቀጠሮ ዛሬ ተገናኝተዋል።

 ባካሄዱት ድርድርም የምርጫ ቦርድ የምርጫ ኮሚሽን ተብሎ እንዲጠራ የአሥራ አንዱ ፓርቲዎች ጥምረት ሃሳብ አንስቷል።

 ኢህአዴግ፣ ኢራፓ፣ የገዳ ስርዓት፣ መኢብንና መኢዴፓ በበኩላቸው የምርጫ ቦርድ የሚለውን ስያሜ ለማስለወጥ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት አላገኘንም ሲሉ መደራደሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

 የቦርዱን ስያሜ መቀየር ብቻውን ለውጥ አያመጣም፣ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ቦርዱን በሚያጠናከሩ ይዘቶች ላይ ተወያይቶ እንዲሻሻል በማድረግ ነውም ብለዋል።

 ገዥው ፓርቲ አሁን ያለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ስያሜ ቢቀጥልና በተለይም የቦርዱ ስብጥር፣ የስራ ዘመን፣ የአባላቱን ብዛት ጨምሮ ስልጣንና ተግባሩ ላይ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ሃሳብ አቅርቧል።

 ኢራፓ፣ የገዳ ስርዓት፣ መኢብንና መኢዴፓ ኢህአዴግ ያቀረበውን ሐሳብ እንደሚጋሩት ገልጸዋል።

 በሌላ በኩል አስራ አንዱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሚለው ስያሜ ወደ ኮሚሽን ሊቀየር ይገባል ሲሉ መደራደሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

 አስራ አንዱን የፓለቲካ ፓርቲዎች የወከሉት አቶ ትዕግስቱ አወል ስያሜው ብቻ ሳይሆን የውስጥ አደረጃጀቱን በተመለከተ የሚለወጥና የሚሻሻል ሃሳብ እንዳላቸውም አክለዋል።

 ፓርቲዎቹ በዚህ ሐሳብ ላይ መግባባት ላይ ባለመድረሳቸው ቀጣይ ድርድር ለማካሔድ ለሕዳር 5 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2010 የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አስር አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶች በዚህ ዓመት እንደሚጀምር አስታወቀ።

ይህ የተገለጸው ዩኒቨርሲቲው "የከተማ ችግር ፈቺ የትምህርት ዓይነት ናቸው" ብሎ በምርምር የለያቸውን የትምህርት ዘርፎች ግምገማ በአውደ ጥናት አቅርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በቅድመ ምረቃ መርሃግብር ዘጠኝ የትምህርት ዓይነቶችን የሚሰጥ ሲሆን፤ ሶስት የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ በድህረ ምረቃ ይሰጣል ተብሏል።

በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢ የመጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የከተማ ትራንስፖርት አስተዳደር፣ የከተማ መሬት አስተዳደር፣ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር፣ የህዝብ አስተዳደርና የትምህርት አስተዳደር ከአስሩ አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብረሃነመስቀል ጠና በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በከተሞች የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለል አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶችን ማስተማርና የማህበረሰብ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ የትምህርት ዓይነቶችን መክፈት አስፈላጊ ሆኗል።

ይህም ደግሞ በትምህርት ተቋማት ዘመናዊ የላብራቶሪ አገልግሎት ለመዘርጋት፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት በትምህርት ጥራት የተደገፈ ለማድረግና "የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎችን በስፋት ለማስረጽ ያግዛል" ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በከተማዋ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማቃለልና በከተማዋ ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ያለው ሚና የጎላ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ክፍል ኃላፊና የሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይስሃቅ ግርማይ እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ከማሟላት አኳያ ዩኒቨርሲቲው የሚያፈራቸው ባለሙያዎች ያላቸው ሚና የጎላ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለዘላቂ የከተማ ልማት የሚሰራ የከተማ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ቢንቀሳቀስም የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የዩኒቨርሲቲውን መሰረተ ልማት ለማሻሻልና ለዩኒቨርሲቲው እድገት ወሳኝ የሆኑ ግብአቶችን ከማሟላት አኳያ ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የተለያዩ ከተማ ተኮር ስርአተ ትምህርቶችን ከመቅረጽ አኳያ ያደጉ አገሮችን ተሞክሮ በመቅሰም ወደ አገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየርም ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የስርዓተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናቱ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፤ በአስሩም የትምህርት ዓይነቶች ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድ  ይጠበቃል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ህዳር 1/2010 በትግራይ ክልል የሚገኘው የኩሐ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ የዓይን ሕክምና ትምህርት መስጠት ሊጀምር እንደሆነ አስታወቀ።

 የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኪኤለ ሐጎስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፣ ኮሌጁ የዓይን ሕክምና ትምህርቱን በተያዘው ህዳር ወር አጋማሽ ይጀምሯል።

 ስልጠናው በሀገሪቱ ያለውን መካከለኛና ከፍተኛ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች እጥረት ለማቃለልና የተለያዩ የዓይን በሽታዎችን ለመከላከል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

 ከእዚህ ጎን ለጎን የዓይን ሕሙማን በአቅራቢያቸው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

 እንደአቶ ሚኪኤለ ገለጻ ኮሌጁ ከ25 በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ፤ 10 ተማሪዎችን ደግሞ በዲፕሎማ ደረጃ ተቀብሎ በቀለምና በተግባር የታገዘ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችለውን ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ አዘጋጅቷል።

 የመምህራን፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመጻህፍትና ለተግባር ትምህርት የሚውሉ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች መሟላታቸውንም ጠቁመዋል።

 በትምህርቱ የቀላል ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ መከላከልን መሰረት ያደረገ ስልጠና እንደሚሰጥም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

 የሆስፒታሉ የሕክምና ኬዝ ቲም ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ወረደ በበኩላቸው፣ ትምህርቱ በዓይን ጤና ላይ በቂ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች በንድፈሀሳብና በተግባር ተደግፎ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

 በኮሌጁ በንጽህና ጉድለት፣ በዕድሜ መግፋትና በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱ እንደ ትራኮማ፣ ሞራና ሌሎች የዓይን ሕመሞችን ለማከም የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

 ከእዚህ በተጨማሪ የዓይን መነጽሮችን እየሰራ ለዓይን ሕሙማን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ወይዘሮ ሙሉ አስረድተዋል።

 ኮሌጁ በዚህ ዓመት ከ10 ሺህ በላይ ለሆኑ የዓይን ሕሙማን የሞራ ቀዶ ሕክምና በነጻ ለመስጠት ያቀደ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሕክምና አገልግለቱን መስጠቱ አሰታውቀዋል።

 ኮሌጁ በአስር ዓመት ዕድሜው ከ70 በላይ ተማሪዎችን በመካከለኛ የዓይን ሕክምና ሙያ አሰልጥኖ ወደ ሥራ አሰማርቷል ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን