አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 01 November 2017

ደብረ ብርሃን ጥቅምት 22/2010 በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ ቀበሌዎች የሀገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ በተሰራው የወሰን ማካለል ሥራ የህዝብ ጥያቄዎች እየተፈቱ መሆናቸው ተገለጸ።

 የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች በየበኩላቸው እንዳሉት፣ በሁለቱ ወረዳዎች የተካሄደው የወሰን ማካለል ሥራ በውስጥና በውጪ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ያራምዱት የነበረውን አፍራሽ ድርጊት የሚገታ ነው።

 በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሙጤ ፈጫ ቀበሌ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች የጀውሃ ገጠር ቀበሌዎች መካከል የወሰን ማካለል ሥራ ተካሄዷል።

 የሙጤ ፈጫ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ወንድወሰን አለማየሁ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በወሰን ያለመግባባት ምክንያት የጀውሀ ከተማ እድገት አስካሁን ሲጓተት ቆይቷል።

 "በኩታ ገጠም አንድላይ እየኖርን ያለን ህዝቦች በመሆናችን ጥያቄያችንን በሀገር ሽማግሌ መፍታቱ ለሌሎች አካባቢዎችም ትምህርት ይሰጣል " ብለዋል።

 የወሰን ጥያቄው መፍትሄ ማግኘቱ  ሰላምና ልማትን በጋራ ለማፋጠን ከማገዙም በላይ ሁከት ለመፍጠር የሚያስቡ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለህግ ለማቅረብ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

 ከአንጾኪያ ገምዛ የመጡት የሃገር ሽማግሌ አቶ ጌታቸው እድነው በበኩላቸው፣ በአንድ ላይ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ለጋራ እድገትና ተጠቀሚነት የሚበጅ አለመሆኑን ጠቁመዋል። 

 እንደ አንድ ቤተሰብ በሚተያዩ ህዝቦች መካከል አልፎ አልፎ ሲፈጠር የነበረ አለመግባባት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሌሎች የልማት ሥራዎች እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

 "በአሁኑ ውቅት ስናነሳው የነበረው ጥያቄ በጋራ ውሳኔ መፈታቱ በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲጠናከር ከማድረጉ በተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራችን ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርጋል" ብለዋል።

 የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አስተዳዳሪዎች በየበኩላቸው እንዳሉት፣ በሁለቱ ወረዳዎች የተካሄደው የወሰን ማካለል ሥራ በውስጥና በውጪ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ያራምዱት የነበረውን አፍራሽ ድርጊት የሚገታ ነው።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄችን ህዝቡ እርስ በእርሱ እየተናገገረ በመተማመን እየፈታቸው ይገኛል።

በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሙጤ ፋጫ ቀበሌና በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የጀውሃ የገጠር ቀበሌዎች መካከል እስካሁን ግልጽ የሆነ የአስተዳደር ወሰን እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

ይህም በአካባቢው ያለው የአሸዋ ማዕድን "ይግባኛል" በሚል ምክንያት ተደጋጋሚ አለመግባባቶች እንዲከሰቱ ሲያደርግ መቆየቱን ነው የገለጹት።

በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሃይማኖት አክራሪነት የሚነሱ የፀጥታ ችግሮች ተጋላጭነት ስጋት እንደነበረም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የወሰን ማካለሉ  በመግባባት እንዲፈታ መደረጉ በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ህዝብን ለማጋጨት ያራምዱት የነበረውን አፍራሽ ቅስቀሳ ለመግታት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ፍታሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ከማስቻሉ በላይ የአክራሪዎችን እንቅስቃሴ በተደራጀ አግባብ ለማክሸፍ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በጥልቅ ታሃድሶው  በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ይነሱ የነበሩ የወሰን ችግሮችም በተመሳሳይ በሃገር ሽማግሌዎች እየተፈቱ መሆናቸውን አቶ ግርማ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ቦሰትና ፈንታሌ ወረዳዎች ከምንጃር ወረዳ ጋር ተመሳሳይ የወሰን ችግር  በህዝባዊ ውሳኔ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኦሮሞ ቤሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው "በሁለቱ ወረዳዎች የተካሄደው የወሰን ማካለል ሥራ በውስጥና በውጪ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ለዓመታት ሲፈጽሙት የነበረውን እኩይ ተግባር ይገታል " ብለዋል።

የጥፋት ኃይሎች በብሔረሰብና በሃይማኖት አክራሪነት ህዝብን ከህዝብ ለመለያየት ያደርጉት የነበረውን አንቅስቃሴ በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል። 

እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፣ በሀገር ሽማግሌዎች የተካሄደው የወሰን ማካለል ሥራ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ህዝቡ ችግሩን በራሱ መንገድ መፍታት መቻሉ ለልማትና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

የህዝቡን ውሳኔ መንግስት እንደሚያከብርና በቀጣይም አካባቢውን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የጅውሃ ቀበሌ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይትና የወሰን ማካለል ሥራ የሁለቱ ዞኖች የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና አመራሮች ተገኝተዋል ።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ጥቅምት 22/2010 በትግራይ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን ለማቃለል በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትግራይ ደቡባዊ ዞን በእምባአላጀ ወረዳ በዓዲሽሁ ከተማ ከ6 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባውን የውሃ ተቋም አስመርቋል።

በቢሮው የመጠጥ ውሃአቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርአቶተስፋአለም ይሕደጎ በምረቃው ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት በ2010 ዓም መጨረሻ በአጠቃላይ  ከ570 ሺህ በላይ  ህዝብ  ተጠቃሚ  የሚያደርጉ  የመጠጥ ውሃ  አቅርቦት ስራዎች ቢሮው በመስራት ላይ ነው የሚገኘው።

 በክልሉ የተለያዩ የገጠር አካባቢዎችና ከተሞች በ700 ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነቡ ያሉት የውሃ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁም አሁን ያለውን የ63 በመቶ የውሃ ሽፋን በ10 በመቶ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

 የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጉዑሽ ሃይሉ በበኩላቸው"አሁን የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት 22 በመቶ የነበረውን የዓዲሽሁ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን መቶ በመቶ ለማዳረስ ያግዛል" ብለዋል።

 በወረዳው ካለው 124ሺህ ህዝብ እስከ አሁን 83ሺህ የሚሆነው የንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው፣መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተጨማሪ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

 የከተማውን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው ስራም የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ፣ ከሁለት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የመስመር መዘርጋትን ጨምሮ 200 ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚይዝ ማጠራቀሚያና የቦኖ ውሃ ማደያም ተገንብቷል።

 የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ገነት በርሄ ቀደም ሲል የነበረው  ውሃ  ከሳምንት በላይ እየጠፋ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁን ይሔንን ችግር ለማቃለል ታስቦ በተመቻቸላቸው የውሃ አቅርቦት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

 ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ በላይ ባይርኡ በበኩላቸው  ቀደም ሲል በነበረባቸው የውሃ ችግር ጀሪካን በመያዝ ራቅ ያለ ቦታ እየሔዱ ጊዜና ጉልበታቸውን ከማባከናቸውም ባለፈ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ ለመጠቀም ይገደዱ ነበር ።

 አሁን ላይ ይሔንን ችግር ሊያስወግድላቸው የሚችል ስራ በአካባቢያቸው በመከናወኑ ለውሃ ፍለጋ የሚያባክኑትን ጊዜም ሆነ ጉልበት በመቆጠብ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመንከባከብ እንደሚያውሉት ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረብርሃን /ማይጨው ጥቅምት 22/2010 በአማራ ሰሜን ሸዋና  በትግራይ ደቡባዊ ዞኖች በመኸሩ ወቅት ከለማው መሬት የደረሰው ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመጠበቅ እየተሰበሰበ ነው፡፡

 በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ዘለቀ እንደገለጹት በዞኑ በምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎ ከለማው 498ሺህ ሄክታር መሬት እስካሁን 71 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ተሰብስቧል፡፡

 አርሶ አደሩ በደቦና  በአንድ ለአምስት የልማት ቡድን አደረጃጀት ጭምር በመተጋገዝ  ሰብሉን የመሰብሰብ ስራው እንደቀጠለ ነው፡፡

  እስካሁን ታጭዶ ከተሰበሰቡ ሰብል ውስጥ  ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴና  ባቄላ የሚገኝበት ሲሆን   በተጓዳኝም በመውቃት ወደ ጎተራ የማስገባት ስራ እየተካሄደ ነው።

 ቀሪውንም  የመሰብሰቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ባለሙያዋ ጠቁመው  አርሶ አደሩ በሚሰበስብበት ወቅት ከብክነት በፀዳ መንገድ እንዲያከናውን ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

  የሴት አርሶ አደር ዓለም አይደፈር በዞኑ ቀወት ወረዳ የተሬ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በመኸሩ ወቅት ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት ላይ ማሽላና ጤፍ ማልማታቸውን በሰጡት አስተያየት ተናገረዋል፡፡

 የደረሰ ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳባቸው  ካለሙት መሬት እስካሁን ግማሹ የሸፈነው ጤፍ  መሰብሰባቸውን ጠቁመዋል። 

 አርሶ አደር አበበ ታየ በበኩላቸው  በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የማሾ ሰብል ሰብስበው መውቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

 አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ሌላው የደረሰ ሰብላቸው በአደረጃጀታቸው አማካኝነት የመሰብሰብ ስራቸውን እንደቀጠሉ ነው።

 በዞኑ ከለማው መሬት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንደሚኖረው ነው የተመለከተው፡፡ 

 በተመሳሳይ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ143 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በልዩ ልዩ ሰብል ለምቶ ይገኛል፡፡

 በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የአዝርዕት ልማት ቡድን መሪ አቶ ኃይሌ ካሳ እንደገለጹት የዞኑ አርሶ አደሮች  ከለማው የስንዴ ፣ የገብስ፣ የጤፍና አተር  ሰብል ውስጥ የደረሰው ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመጠበቅ በማጨድ ሰብስበው የመከመር ስራ  ጀምረዋል፡፡

 አርሶ አደሮቹ ስራውን እያከናወኑ ያሉት በልማት ቡድን ተደራጅተው  ነው፡፡

 በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎችን በማንቀሳቀስ ጭምር የአርሶ አደሩ የሰብል በዘመቻ በመሰብሰብ እንዲሳተፉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ቡድን መሪው  ጠቅሰዋል።

 የኦፍላ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የስነ አዝርዕት ልማት ባለሙያ አቶ ጣዕመ ሓዱሽ በበኩላቸው በመኸሩ ወቅት በዕቅድ የተያዘውን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለምቷል፡፡

 በአሁኑ ወቅት  የወረዳው አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ  ዝናብ እንዳይበላሽባቸው የመሰብሰብ ስራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

 በመኸሩ የምርት ወቅት ቢጫ የዋግ በሽታ ተቋቁሞ ለምርት የሚደርስ የገብስ ምርጥ ዘር ማልማታቸውን የተናገሩት ደግሞ  የወረዳው አርሶ አደር ብርሃኑ ረዳ ናቸው፡፡

 አሁን ላይ የገብስ ሰብሉ የደረሰ በመሆኑ በማጨድ መሰብሰብ እንደጀመሩ የተናገሩት አርሶ አደር ብርሃኑ በግማሽ ሄክታር ካለሙት ከዚሁ ሰብል 25 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ነው ያመለከቱት፡፡ 

 አርሶ አደር ካህሳይ አብርሃ በበኩላቸው የክረምቱ ዝናቡ  ዘግይቶ ቢጀምርም በአጭር ጊዜ የሚደረስ ምርጥ የጤፍ   ዘር ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡

 የጤፍ ሰብሉ የደረሰ በመሆኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከመጣሉ በፊት እያጨዱ መሆናቸውንና ካለሙት ሩብ ሄክታርም 12 ኩንታል የጤፍ  ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አያሌው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የትግራይ፣ አማራና የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ድጋፍ አድርገዋል።

ክልሎቹ እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር  ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ  ድጋፉ በብሄራዊ አደጋና ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኝነት ለተጎጂዎች እንደሚደርስም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቃዮች መቋቋሚያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያየ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋምና ለማቃለል ክልሎች እርስ በእርስ የሚያደርጉት መደጋገፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ሁሉም የአገሪቷ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እያከናወኑ ያሉትን ተግባርም አድንቀዋል።

መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ጋር በጋራ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

መንግስት ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የሰላም ጉባዔዎችን እንደሚያካሄድ ጠቁመው፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም መስፈንና የተጀመረውን ልማት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያውያን እንደቀደመው ሁሉ ለአካባቢ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

Published in ማህበራዊ

አክሱም ጥቅምት22/2010 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ታሕታይ ማይጨው ወረዳ አንዲት የ66 ዓመት አዛውንት አስገድዶ የደፈረ ወጣት በሰባት ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ።

 በዞኑ የአክሱም ምድብ ችሎት ቅጣቱን ያስተላለፍው ተከሳሹ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት ላይ በታሕታይ ማይጨው ወረዳ ልዩ ስሙ "ማይዓጽሚ"  በተባለ ስፍራ የግል ተበዳይዋን አስገድዶ መድፈሩን በሰውና በማስረጃ በመረጋገጡ ነው።

 ሰለሞን ግደይ የተባለው የ18 ዓመት ወጣት አስገድዶ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በማሰብ በግል ተበዳይ ላይ ጥቃት መፈጸሙን በክሱ ላይ ተመልክቷል።

 በእዚህም የፌደራል ዓቀቤ ህግ የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ወጣቱን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መስርቶበት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ አድርጓል።

 ጉዳዩን ሲያጣራ የቆየው ዓቀቤ ህግ ተከሳሹ የግል ተበዳይዋን በሌሊት በር ሰብሮ በመግባት የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙን ባቀረበው የክስ ዝርዝር መዝገብ ላይ አመልክቷል።

 ተከሳሹ ክሱን አስመልክቶ ምላሽ ሲሰጥ " በወቅቱ መጠጥ ስለጠጣሁ ያደረጉትን ነገር አላውቅም" ብሎ ተከራክሯል።

 ዓቃቤ ህጉ ስለ ድርጊቱ አፈጻጸም በሰውና በሰነድ ማስረጃ አስደግፎ ጉዳዩን ለፈርድ ቤቱ በማቅረቡ ግለሰቡ በሰባት ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

 ተከሳሹ ደርጊቱን አለመፈጸሙ በሚገባ ሊከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ እንደሆነና ጨለማን ተገን አድርጎ በመፈጸሙ በከባድ ቅጣት እንዲቀጣ በማለት ዓቃቢ ህግ የቅጣት ማክበጃ አቅርቧል።

 የተከሳሽ ጠበቃ በበኩሉ ግለሰቡ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለበትና የቤተሰብ ጧሪ መሆኑን ከማሕበራዊ ፍርድ ቤት ድጋፍ እንዳለው በመጥቀስ የቅጣት ማቅለያ እንዲያዝለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

 የግራ ቀኝ ክርክሩን ሲያዳምጥ የቆየው የትግራይ ማዕካላዊ ዞን ፍርድ ቤት የአክሱም ምድብ ችሎት ዛሬ ጥቅምት 22 ቀን 2010  በዋለው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው በማለት ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሰባት ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ ከመንግሥት ጋር በሽርክና መስራት የሚያስችል ፖሊሲ መዘጋጀቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገለጸ።

 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2010 ዓ.ም የሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ እቅዶች ዛሬ ገምግሟል።  

 ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አገሪቷ ለመሰረተ ልማት አቅርቦት ከውጭ የምትበደረው ገንዘብ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። 

 "በመሆኑም የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ ከመንግሥት ጋር በሽርክና እንዲሰራ የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጅቷል" ብለዋል። 

 ዶክተር አብርሃም ረቂቅ ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን ገልጸው፤በተያዘው በጀት ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል። 

 በሌላ ዜና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚኒስቴሩ በቀጣይ ማከናወን ባለበት ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥቷል።

 ቋሚ ኮሚቴው ተጀምረው በጊዜው የማይጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች ቁጥጥር ፣ወጪ ቅነሳና የቢሮ ኪራይ  እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል ምን እየተሰራ እንደሆነ ጠይቋል።     

 ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ወጪ ቅነሳን ተግባራዊ አንዲያደርጉ ወጪ መቆጠብ የሚያስችል ሰንድ ተዘጋጅቶ ለተቋማት መሰራጩቱን አስረድተዋል።   

 አንገብጋቢ የቢሮ እጥረት ያለባቸው መስሪያ ቤቶች ካልሆኑ በስተቀር ቢሮ መከራየት እንደማይቻል አቅጣጫ እንደተቀመጠ የተናገሩት ዶክተር አብረሃም፤ በተቋማት ያለ አግባብ የሚፈጸሙ ግዥዎች እንዲቆሙ መደረጉንም ጨምረው አብራርተዋል።  

 የመግሥት ኃላፊዎች የሚጠቀሟቸው መኪናዎች ከአገር ውስጥ እንዲገዙ የሚያዘውን መመሪያ ገቢራዊ ማድረግ  ከወጪ ቅነሳ ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል። 

 የግብርና፣ኢንዱስትሪና ማዕድን ምርቶችን በብዛት  ወደ ውጭ በመላክ ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ  የተለያዩ ማበረታቻዎች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።

 ይሁን እንጂ አገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ በዘርፉ ይበልጥ ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

 የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረገው ክትትል በመስክ ምልከታ ታግዞ እንደሚካሄድ ተናግረው፤ "ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ታደሰ እንደገለጹት፤ሚኒስቴሩ ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ላይ የጀመራቸው የቁጥጥር ተግባራት ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል።  

 ሚኒስቴሩ የጸረ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለይቶ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

 "የፈዴደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እንዲስተካከሉ ያቀረባቸውን ሀሳቦች በተያዘው ዓመት ለመፍታት ይበልጥ መትጋት ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ጥቅምት 22/2010 በአማራ ክልል የሲቪል ሰርቫንቱን አመለካከትና ክህሎት ለማጎልበትና ለህዝቡ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስልጠና መጀመሩን የክልሉ ስቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

 በቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በልስቲ ወርቁ እንዳስተወቁት ስልጠናው የሰራተኛውን የእውቀት ክፍተት የሚሞላ ነው።

 ስልጠናው በመልካም አስተዳደር፣ በለውጥ ፕሮግራሞች፣ በዜጎች ቻርተር ፅንሰ ሃሳብና አተገባበር ዙሪያ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው የመንግስት ሰራተኞች የስነ-ምግባር ኮድና የስበሰባ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያዎች በውይይት እንዲዳብሩ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።

 በዚህም አገልግሎቱ የላቀ፣አመለካከቱ የጎለበተ፣በግልፅነትና ተጠያቂነት መንፈስ ተግባራትን በውጤታማነት መፈፀም የሚችል ስቪል ሰርቫንት ለማፍራት ግብ የተጣለ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በክልል ደረጃ ከጥቅምት 21 እስከ 27/2010 በሚሰጠው ስልጠና ላይ መግባት ካለባቸው 48 ተቋማት መካከል 36ቱ ስልጠናውን መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

 በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚሰጠው ስልጠናም ከጥቅምት 28 እስከ ህዳር 12 የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው፤ ከ350 ሺህ በላይ ሰራተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑም አቶ በልስቲ አስታውቀዋል።

 በየደረጃው የሚሰጠው ስልጠና እንዲሳካ ከአምስት መቶ በላይ አሰልጣኞች ቀድመው መሰልጠናቸውን ጠቁመው በዚህ ምክንያት በአገልግሎት እጦት ህብረተሰቡ እንዳይጉላላ ተቋማት ሰራተኞችን በፈረቃ እንዲያሳትፉ ይደረጋል ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምክር ቤቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

 የምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤትንና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን የ2010 ዓ.ም እቅድ ተመልክቷል።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ስርጭቱ እየተስፋፋ እንደሆነና ምክር ቤቶቹም አገልግሎት በመስጠት ረገድ ክፍተቶች ይስተዋልባቸዋል ነው ያሉት።

 የምክር ቤቶቹ መጠናከር ህብረተሰብ ዓቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ለመፍጠርና ቫይረሱን ባለበት ደረጃ ለማስቆም ያለው ሚና የጎላ እንደሆነ ገልጸው ምክር ቤት ባልተቋቋመባቸው አካባቢዎችም በአዲስ መልክ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

 ጽህፈት ቤቱ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባውም ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።

 በጽህፈት ቤቱ የእቅድ ክትትል ረዳት ዳይሬክተር  አቶ ነጻነት አኒቆ የስርጭቱ መጠን እንዳይባባስ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በተከሰተባቸው በአዲስ አበባና በጋምቤላ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

 በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

 በሌላ በኩል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው በማድረስ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉበት ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል።

 በየክልሉ ባሉ የጤና ተቋማት የሚገኙ ላብራቶሪዎች እጥረትና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን የህክምና መሳሪያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።

 የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ከዩኒቨርስቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎችንና የምርምር ውጤቶችን በተመለከተ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 የኖርዌይ ልዑል ሃኮን እና ልዕልት ሜቴ ማሪት በመጪው ሳምንት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ።

 የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝቱን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የኖርዌይ ልዑል ሃኮን እና ልዕልት ሜቴ ማሪት ከጥቅምት 27 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ።

 ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግርም መግለጫው አስታውቋል።

 የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በፖለቲካ፣ በልማት እርዳታዎችና በሚስዮናዊነት ስራዎች ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በንጉሱ አፄ ኃይለሥላሴና በኖርዌይ ንጉሳዊ ቤተሰቦች መካከል ጠንካራ ትስስር መፈጠሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 ሁለቱ አገራት እ.አ.አ 1995 የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን አዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ በአፍሪካ ትልቁ ስትራቴጂክ ማዕከል መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ ኢምባሲ ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 አትሌት አሞኘ ሰንደቁ በቻይና የሶንግሿን ሿዋሊን የወንዶች የማራቶን ውድድርን በሸበጥ ጫማ ሮጦ አሸነፈ።

 የቻይናው ዕለታዊ የዜና ምንጭ ፒፕልስ ዴይሊ ቻይና ባሰፈረው ዘገባ አትሌት አሞኘ በሸበጥ ጫማ እንዲሮጥ ያስገደደው ምክንያት ይፋ ባይሆንም አትሌቱ በነጠላ ጫማ ሮጦ ማሸነፉ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝቷል።

 እንደ ብዙዎቹ  አስተያየትም ይህ ድል አፍሪካዊያን አትሌቶች በረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር አሸናፊ የሚሆኑት ባላቸው አቅምና ብቃት  መሆኑን የሚያሳይ ነው።

 አፍሪካዊያን አትሌቶች ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻፀሩ ካለምንም የቁሳቁስ ድጋፍ በራሳቸው የግል ጥረት እንደሚያሸንፉ ምስክር ይሆናል ሲሉ ነው የተናገሩት።

 የአትሌት አሞኘን  በሸበጥ ጫማ ሮጦ ማሸነፍ ያዩ ቻይናዊያን የአትሌቱን የግል ብቃት አድንቀዋል፣ ወደ ፊትም ገናና ስመ ጥር የማራቶን ሯጭ እንደሚሆን መስክረውለታል።

 ጥቂት ግለሰቦች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ሸበጥ  ጫማው የተሻለ አቅም ይፈጥርለታል በሚል ሀሳባቸው የሰጡም አሉ።

 አትሌቱ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ ወስዶበታል።

 በዚህ ውድድር አሸናፊ በመሆኑ 20 ሺህ  የቻይና  ዮዋን  ገንዘብና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

 አትሌቱ ከሳምንት በፊትም በቻይና ጅንግዩዋን ማራቶን በተመሳሳይ  መልኩ በሸበጥ  ጫማ ሮጦ አሸናፊ ነበር።

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን