አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 09 October 2017

መቀሌ መስከረም 29/2010 በትግራይ ክልል በገቢ አሰባሰብ ላይ የላቀ ሥራ ላከነወኑ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ሠራተኞችና ድጋፍ ላደረጉ አካላት የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ።

 የገንዘብና የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማት የተሰጣቸው 280 ሠራተኞችና ድጋፍ ያደረጉ አካላት ሲሆኑ የግብር አሰባሰብ ሥርአቱን ለማዘመን አዲስ ሶፍት ዌር ሰርተው ባልስልጣኑን የደገፉ ሁለት ሠራተኞችም በልዩ ሁኔታ እያንዳንዳቸው ብር 10 ሺህ ተሸልመዋል።

 ትናንት ማምሻውን በመቀሌ የሰማዕታት ሐውልት መሰብሰቢያ አደራሽ በተዘጋጀው የሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ከሰራተኞቹ በተጨማሪ የክልሉ ምክር ቤት፣ የክልሉ ንግድ ምክርቤት እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት፣ ላብቶፕና ገንዘብ ተሸልመዋል።    

 በሽልማት ሥነስርአቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አዲስዓለማ ባሌማ የባልስልጣኑ ሠራተኞች ግብር በአግባቡ እንዲሰባሰብ ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በተለይ ግብር ከፋዩ ማህበረሰቡ ግብሩን በፍላጎቱና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በወቅቱ እንዲከፍል እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

 "ግብር አንድ ሃገር የተሻለ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ዋንኛ መሳሪያ ነው" ያሉት ዶክተር አዲስ ዓለም፣ የሚሰበሰበው ገቢ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

 በመሆኑም በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከትን በማስወገድ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ግብር ከፋዮች ፍትሃዊ የሆነ ግብር እንዲከፍሉ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

 ባለስልጣኑ ህዝቡ በፍላጎቱ ግብር የሚከፍልበት የአሰራር ስርዓት በማመቻቸቱና ሠራተኞቹም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ያሳዩትን መልካም ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

 የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልደገብርኤል አጽብሃ በበኩላቸው፣ የግብር አሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ተከታታይ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

 ከዚህ በተጨማሪ የባለስልጣኑ ሠራተኞች አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

 ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ በተካሄዱ ተከታታይ ሥራዎች የባለስልጣኑ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል።

 ለዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከግብርና ከተለያዩ ገቢዎች አራት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉንና ገቢው የዕቅዱ 104 በመቶ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

 በተለይ ባለፉት ሦስት ወራት በተካሄደው ግብር የመሳብሰብ ሥራ የ "ሐ" ግብር ከፋዮች 100 በመቶ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት አከራዮች 83 በመቶ ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸው ለዚህ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

 ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርአት መዘርጋት፣ የሠራተኛው ተነሳሽነት ማደግና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባለስልጣኑ የገቢ መሰብሰብ አቅም ለማደጉ ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።

 የላቀ ሥራ በማከናወን ለሽልማት ከበቁት የባልስልጣኑ ሠራተኞች መካከል የሕጣሎዋጅራት ወረዳ ገቢዎች ሠራተኛ ወጣት ሰምሃል ደስታ ሽልማቱ ልዩ የሥራ መነሳሳት እንደፈጠረባት ገልጻለች።

 የባለስልጣኑን የግብር አሰባሰብ ሪፎርም ተከትለው በመስራታቸውና ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ ቆጥረው ማስረከብ በመቻላቸው ለሽልማት መብቃታቸውን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የእንደርታ ወረዳ ገቢዎች ሠራተኛ አቶ ሐየሎም መኮንን ናቸው።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ መስከረም 29/2010 የኢትየዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ክልል ለሚገኙ 10 መካከለኛ ከተሞች ካርታ ሰርቶ አስረከበ፡፡

ኤጀንሲው ካርታውን ያስረከበው ትናንት በሀዋሳ ከተማ ለክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ነው፡፡

ርክክቡ የተካሄደው ለአስሩ ከተሞች  የቅየሳ፣ የጥራት ቁጥጥር፣ የመስመርና ሌሎች ጉዳዮችን ማሳያ በማካተት ካርታ ለመስራት መጋቢት 2008 ዓ.ም ከክልሉ ጋር በተፈጸመው ውል መሰረት መሆኑን በኤጀንሲው የፕላንና ፕሮጀክት ዝግጅትና ግምገማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ዋቅቶላ ገልጸዋል፡፡

የካርታው ስራ 179 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሸፈነ ሲሆን ከ14 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ ተደርጎበታል ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት፡፡ 

የክልሉ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይልማ ሱንታ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ካርታው ለከተሞች   እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡

ካርታው የተሰራላቸው ከተሞች አለታ ወንዶ፣ ሺንሺቾ፣ ዱራሜ፣ አረካ፣ ለኩ፣ ዳዬ በንሳ፣ ሀደሮ፣ ሳውላ፣ ተርጫና ይርጋጨፌ ናቸው ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሀን  መስከረም 29/2010 የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን ለመጎብኘት ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን የሚመጡ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

 በመምሪያው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ባለሙያ ወይዘሪት ራሄል ነጋሽ እንደተናገሩት በዞኑ የወፍ ዋሻ ደን፣ የሚሊኒከ ቤተ መንግስት ፣ የመንዝ ጓሳ ተራራ፣ የለብቃ እየሱስ ፍል ዉሃ፣ የአቡነ መልከጼዴቅ ገዳምና ሌሎች ከአምስት በላይ የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ፡፡

 እነዚህን መዳረሻዎች ጨምሮ ከዋና ዋና መንገዶች የራቁ የመስህብ አካባቢዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ በመስህብ ስፍራዎች አካባቢ አምስት ሎጅዎች ተገንብተው አራቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

 በቅርቡም ሱርአርማ የተባለውና በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ላይ የሚሰራ ማህበር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በባሶና ወራና ወረዳ የገነባውን "የጎሽ ሜዳ የማህበረሰብ ሎጅ" በማጠናቀቅ ለማህረሰቡ ማስረከቡን ወይዘሪት ራሄል አመልክተዋል።

 ሎጁ በቀን 24 እንግዶችን የሚያስተናግዱ አልጋዎች፣ የምግብ አዳራሽና የመዝናኛ ክፍሎች ያሉት ሲሆን የማብሰያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል የሚሰራ የመብራት አገልግሎት እንዲሟላላት መደረጉንም ጠቁመዋል።

 ባለሙያዋ አንዳሉት፣ ዘርፉን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ባህላዊ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት፣ በማስጎብኘት፣ መንገድ በመምራት፣ ምግብ በማብሰልና በሌሎች ተያያዥ የሥራ መስኮች 8ሺህ 212 ሰዎች በማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ዘርፍ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

 በዘላቂ የተፈጥሮ ሀበት ልማትና አጠቃቀም ማህበር የወፍ ዋሻ ማህበረሰብ ተኮር ኢኮቱሪዝም ባለሙያ አቶ አንዱዓለም ዓለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በደብረ ብርሃንና ሌሎች የቱሪስት መደረሻ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተገንብተዋል።

 በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ግንባታና ሌሎች መሰል ፕሮግራሞች አካባቢዎቹን በመንገድ የማስተሳሰር ሥራ እየተሰራ መሆኑም አመልክተዋል።

 የጎሽ ሀገር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ግብአትና ቱሪዝም ሕብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተክለአረጋይ ማሞ አሳታፊ የደን አጠቃቀም በአካባቢው መተግበር ከጀመረ  ወዲህ  ህገወጥ የጣዉላ ንግድ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል 

 ደኑን በመጠበቃቸውም አካባቢውን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

 በዞኑ ከተፈጥሮ ደን በሻገር የሚኒሊክ ቤተመንግስት፣ የመልከጼዴቅ ገዳም እና መንዝ ጓሳ የቱሪስት መስህብ ሃብቶች የሚገኙ በመሆኑ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አቶ ተክለአረጋይ ተናገረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2010 የአለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይከበራል።

የ2017 የአለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት "የአፍሪካ አረንጓዴ ልማትን ማሳደግ" በሚል መሪ ሐሳብ  ከጥቅምት 7-10/2010ዓ.ም ቀን በአዲስ አበባ እንደሚከበር ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በዓሉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን በጉባኤው  ከ300 በላይ የተለያዩ አገራት የሃይል ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች፣ በሃይል ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ውሳኔ ሰጭዎች ይሳተፋበታል ተብሏል።

በመድረኩም አገራት ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ያከናወኗቸው ተግባራት ይገመገማሉ፣የአረንጓዴ ልማትን በአፍሪካና በአለም ለማስፋፋት የመፍትሄ ሀሳቦችና የተለያዩ ጥናቶች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ለፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊነት አገራት ሊያደርጉት ስለሚገባው አስተዋፅኦ እና የመንግስታቱ ድርጅት የዘላቂ የልማት ግቦች ስለሚሻሻሉበት ሁኔታም ይወያያሉ።

ውይይቱ ተሳታፊዎች ፋይናንስ ለሚያስፈልጋቸው የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጮችን የሚያፈላለጉበት፣የታዳሽ ሀይል ኢንቨስትመንትን የሚያሳድጉበትም ይሆናል።

በማደግ ላይ ያሉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚሰሩት ስራ የፋይናንስ ድጋፍ ማሳደግ፣የውሃና ምግብ እጥረትን ለመከላከል የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ አማራጮች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ ዘላቂነት ያለው እና ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን መሰረት ያደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችን ማሻሻልና መተግበር ውይይት የሚደረግባቸው ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ለመተግበር የቀረጸቻቸውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎች ፋይዳ በመድረኩ ገለጻ በማድረግ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ እንድታገኝና እስካሁን በዘርፉ ያከናወነቻቸውን ስራዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ይጠቅማታል ተብሏል።

በተጨማሪም በአገሪቱ እየተሰሩ ያሉና በአገልግሎት ላይ ያሉ የታዳሽ ሀይል ልማትና የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችም በጉባኤው ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ሲኡል በማድረግ አገራት ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የዕውቀት፣የገንዘብና መሰል ድጋፎችን የሚያደርግ በመንግስታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስፈጸም የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2010 በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች መካከል ተከሰቶ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።

አባላቱ  በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጥፋት ያደረሰውን ግጭት አውግዘዋል። 

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷ።

በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደገለጹት፤ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በተከሰተው ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት የሚወገዝ ነው።

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው መኖራቸውን ያስታወሱት የምክር ቤት አባላቱ፤ አንዳንድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ህዝቦች በራሳቸው መፍትሄ አመንጭተው በሰላማዊ መንገድ ሲፈቱ መኖራቸውን ነው አባላቱ ያነሱት።

ይሁንና የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ብጥብጥ እንዲያመራ በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋ ንብረት እንዲወድም እንዲሁም ዜጎች እንዲፈናቀሉ መደረጉ "አሳዛኝ ድርጊት ነው" ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባል አቶ አለባቸው ላቀው፤ "እንዲህ ዓይነት ድርጊት በእኛ በኢትዮጵያውያን ያልተለመደና በማንም ላይ እንዲደርስ የማንፈልገው ነው" ብለዋል።

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በራሳቸው መፍታት የሚያስችል ጥበብ እንዳላቸውና ይህን ጥበብ ጠብቀው እንዲያቆዩ መደገፍ እንደሚገባ ነው ያነሱት።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ዱቤ ጅሎ እንዳሉት፤ በግጭቱ ምክንያት የደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም በምክር ቤትም በመንግስትም ደረጃ የሚወገዝ ነው።

የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም እንዲሁም ህዝቦች ተረጋግተው ከኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ ያደረጉ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩን አቶ ዱቤ ገልጸዋል።

በግጭቱ ምክንያት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የምክር ቤቱ አባላት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት። 

በ2010 የምክር ቤቱ የስራ ዘመን በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ዓይነት ግጭት በሌሎች አካባቢዎች እንዳይደገም በትኩረት እንደሚሰራም ነው አባላቱ ያረጋገጡት።

Published in ፖለቲካ

ጅማ መስከረም 29/2010 " ኤቦ " የተባለው የየም ብሔረሰብ  የዘመን መለወጫ በዓል ትናንት በጅማ ከተማ በደማቅ ስነ ስርዓት ተከበረ።

በዓሉን ያከበሩት በጅማና አካባቢው የሚኖሩ  የብሔረሰቡ አባላት ናቸው፡፡

በየም ልማት ማህበር የጅማ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል ኪያ በዓሉ የብሔረሰቡ አባላትን  እርስ በርስ በማገናኘትና አንድነት በማስጠበቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን በበዓሉ ስነ ስርዓት ወቅት ገልጸዋል፡፡

አቶ ገብረሚካኤል እንዳሉት የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ በዓል "ኤቦ " መከበሩ  የብሔረሰቡ ጭፈራ፣ ሙዚቃ ፣ቋንቋ፣ የሙዚቃ መሳሪያ፣የስራ ባህልና ሌሎችንም የጋራ  እሴቶች በመጠቀበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል።

በጅማ ከተማ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ በደማቅ ሥነ ሥርዓትና በተደራጀ መልኩ ሲከበር መቆየቱም ጠቅሰዋል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ የየም ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለተከታታይ ሰባት ጊዜ ድጋፍ በማድርግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ፀጋዬ ብዙአየው በበኩላቸው" የኤቦ አዲስ ዘመን መለወጫን ስናከብር ያለንን እርስ በእርስ መፈቃቀርና አንድነት ይበልጥ በማጠናከር መሆን አለበት "ብለዋል።

ከአካባቢው ርቀው የሚኖሩ የብሔረሰብ  ተወላጆች በዓሉን ባሉበት  ማክበራቸው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ በጋራ የሚደሰቱበት እና ናፍቆታቸውን የሚወጡበት ቀን በመሆኑ የጎላ ፋይዳ እንዳለው  ጠቅሰዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል  ወይዘሮ አስካለች ደኔቦ  በሰጡት አስተያየት "የኤቦ በዓል ስናከብር አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በመርዳት ነው" ብለዋል።

ሌላው የብሔረሰቡ ተወላጅ አቶ ተሾመ ደስታ በዓሉ ከመስከረም 17 ጀምሮ ያለምንም የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት የብሄረሰቡ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ በድምቀት ሲያከብሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዓሉም ሲከበር ባህላዊ  የአስተዳደር ስርዓትን፣ አኩሪ የቁጠባ ባህል፣ ፍትሃዊ የግጭት አፈታት፣ የመረዳዳትና የመከባበር እሴቶችን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች መሆኑም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር መስከረም 29/2010 በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተከስቶ የነበረው አስከፊ ድርቅ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቋቋም መቻሉ ሀገሪቱ ድርቅን የመቋቋም አቅም መፍጠሯን ያሳያል ሲሉ በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበር የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገለፁ፡፡

 በአደጋ መከላከል ዙሪያ የትምህርት ፕሮግራም ከፍተው የሚያስተምሩና ምርምር የሚያካሂዱ 12 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።

 ዳይሬክተሩ ሚስተር ዮሴፍ ኤት ቸሎቼ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት አገራት አደጋ ከመድረሱ በፊት መከላከልና ከደረሰም በኋላ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችል አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡

 አደጋ  በደረሰ ጊዜ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ በየአካባቢው በጎ ፈቃደኞችን በማፍራት ሊደርስ የሚችለውን ችግር በመቀነስ ማህበራቸው የዳበረ ልምድ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

 ''ኢትዮጵያም እንደ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ያሉ ድርጅቶች የሚያመጡትን ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ለህብረተሰቡ የሚደርስበት ስርዓት በመዘርጋት አደጋዎች የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ የቻለች አገር ናት'' ብለዋል።

 ለእዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያደርግ አቅም መፍጠሯንም እንደማሳያ ጠቅሰዋል፡፡

 በቀጣይም ማህበራቸው በአፍሪካ ለውጥ እንዲመጣ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

 የፌዴራል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ከፍተኛ አማካሪ አቶ ታደሰ በቀለ በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በተለይ የድሃ ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገው የሴፍትኔት ፕሮግራም ተሳታፊዎች በሚያገኙት የገንዘብና የእህል ድጋፍ ምግባቸውን ለመሸፈን ባለፈ ጥሪት እንዲያፈሩ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በተጨማሪም በየአካባቢው በሚከናወን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተፈጥሮ ቀድሞ ደን ወደነበረበት እንዲመለስና የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡

 ''በአገሪቱ ከዓመት በፊት የከፋ ድርቅ ቢከሰትም ተጠቂዎች አካባቢያቸውን ሳይለቁ አስፈላጊውን የምግብና የመጠጥ አቅርቦት ድጋፍ በመደረጉ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ማድረግ ተችሏል'' ብለዋል።

 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም መብራት በበኩላቸው እንዳሉት፣ አፍሪካ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በተደጋጋሚ የሚከሰትባት አህጉር ናት።

 የሚደረገው እርዳታና ድጋፍ ዘላቂ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ እንዲፈጸም ዩኒቨርሲቲዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል'

 ''ውይይቱም የሚደረጉ እርዳታዎች ለምን መሰረታዊ ለውጥ አላመጡም፣ ለውጥ ለማምጣት ምን መሰራት አለበትና የባለድርሻ አካላት ድርሻ ምን መሆን አለበት የሚለውን ለይቶ ለማቅረብና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው" ብለዋል።

 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም በአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና፣ ዘላቂ ልማት፣ አየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተያየዥ የትምህረት ፕሮግራሞች ከፍቶ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ዛሬ በተጀመረውና ለሦስት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ላይ 12 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ጉዳዮ የሚመለከታቸው የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 የውይይት መድረኩ ቀደም ሲልም በሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪሽየስ፣ ጀኔቫ፣ ጃፓን፣ ጋናና ናይጀሪያ መካሄዱን ከአዘጋጆች የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ነጌሌ መስከረም 29/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ከ75 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በበጋ ወራት  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ለማሰማራት መታቀዱን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የወጣቶች ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ ወይዘሮ ጌጤነሽ ኃይሉ እንዳሉት፣ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ወጣቶቹን በነገሌ ቦረና፣ በአዶላና ሻኪሶ ከተሞች እንዲሁም በ14 የዞኑ ወረዳዎች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማሰማራት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ወጣቶቹ ከሚሰማሩባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መካከል ትምህርት፣ ጤና፣ ሕብረተሰብ አቀፍ ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ይገኙባቸዋል።

ወይዘሮ ጌጤነሽ እንዳሉት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ድረስ የሚቆይ ሲሆን ከተሳታፊዎቹ መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ወጣቶቹ በትርፍ ጊዜያቸው በሚያከናውኑት የበጎ ፈቃድ ሥራ ግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ሁለት ወራት 218 ሺህ የዞኑ ወጣቶች 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ልዩ ልዩ የልማት ሥራ ያከናወኑ ሲሆን፣ በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዞኑ ሊበን ወረዳ የካላዳ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ያኔ ሀለኬ በበኩሉ፣ " ቀደም ሲል ያከናወንኩት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሥራ ባህሌን ከማሳደጉ ባለፈ የሥራ ልምድ አግኝቼበታለሁ" ብሏል።

በዘንድሮው በጋም  ለሁለተኛ ጊዜ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት፣ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍና በክረምት የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብ ማቀዱን ተናግሯል።

በየዓመቱ በችግኝ ተከላ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት ሥራዎች እንደሚሳተፍና በበጋ ወራትም ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ  ሌላው የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወጣት ቴዎድሮስ ልኡልሰገድ ነው።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር መፈጸሙ የሥራ ባህልን ከወዲሁ አንዲለማመድ ማድረጉን ገልጾ፣ ሌሎች ወጣቶችም ትርፍ ጊዜያቸውን ለበጎ አገልግሎት  በማዋል ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክቷል። 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መስከረም 29/2010 በትግራይ ክልል በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አካባቢን በመጠበቅና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አበረታች ውጤት መገኘቱ ተገለፀ ።    

ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ ሃገራትና ከአለም ባንክ  የተውጣጡ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አባላት በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ "ድድባ" ቀበሌ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ጎብኝተዋል።

በዚህም በፕሮጀክቱ ድጋፍና በህዝብ ትብብር በወረዳው ባሉ አምስት ቀበሌዎች ውስጥ በ12 ተፋሰሶች ላይ በተከናወኑ የእርከን፣ ክትርና ሌሎች የአፈረና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ያገገሙ አካባቢዎችን ተመልክተዋል።

የልዑካን ቡድን አባላቱ በዚህ ወቅቱ እንዳሉት፣ ህዝቡ ባከናወናቸው የአረንጋዴ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች አካባቢውን ከአፈር መከላት አደጋ መታደግ እንደተቻለ ግንዛቤ አግኝተዋል።

የ"ግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲ" ተወካይ ዶክተር መሐመድ ባካሪ በሰጡት አስተያየት የሕብረተሰቡ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃና ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በጉብኝታቸው ያለቴክኖሎጂ ህዝቡን በማነሳሳት ብቻ የተጎዳ መሬት ድኖ ለልማት መዋሉን መመልከታቸውን ተናግረዋል ።

በዓለም ባንክ የስነ አካባቢ ዳይሬክተር ሚስስ ጁሊያ ባክናል በበኩላቸው፣ ፕሮከጅቱ በትግራይ ክልል ያለው አፈጻጸም ከሌሎች ሀገራት የተሻለ ስለመሆኑ በአካል ያዩበት እንደሆነ ተናገረዋል።

"በህዝብ ተሳትፎ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መሬት ከመሸርሸርና መራቆት ድኖ የተረጋጋ የአየር ሁኔታ በማየቴ ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

በአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት ኢኮኖሚስት ሚስስ ርብቃ ፊሸር "ለዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት ያደረግነው ድጋፍ በተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን አረጋግጠናል፤ በቀጣይ ሀብት በማሰባሰብ ድጋፋችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የእንደርታ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋይ ገብረተኸለ እንዳሉት በአርሶአደሩ ተሳትፎ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከዚህ ቀደም በአካባቢው ተራቁተው የቆዩ አካባቢዎች በእፅዋት ተሸፍነዋል ።

ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ 26 ወረዳዎች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በትግራይ ግብርናና ገጠር ልማት የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መሐሪ ገብረመድህን ናቸው።

በፕሮጀክቱ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶችን በማዳን አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት ለመቀየር መቻሉን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ከ70ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተሳታፊ ሲሆኑ ለመሬታቸው የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው መሬቸውን በዘላቂነት በመንከባከብና በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል

"አርሶ አደሩ ለይዞታው ዋስትና በማግኘቱ ከዚህ ቀደም ከእርሻ መሬት ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ግጭቶች ቀርተዋል " ብለዋል ።

በተለይም በፕሮጀክቱ የታቀፉ ወጣቶችና ሴቶች በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ እንዲሁም በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የስራ ባህላቸው አየጎለበተና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን አቶ መሀሪ አስታውቀዋል ።

የድድባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተኪኤን ገብረ ጊዮርጊስ  በሰጡት አሰተያየት  ከሶስት ዓመት በፊት አካባቢያቸው አፈሩ የተሸረሸረ ፣ምንም አይነት ዛፍ የማይበቅልበትና የተራቆተ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"በፕሮጀክቱ ታቅፈን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራታችን  አካባቢው ወደ አረንጓዴነት ተለውጦ የደረቁ ምንጮች ውሀ ማፍለቅ ችለዋል " ያሉት አርሶአደሩ፣ ይህም የእንስሳት መኖ ከማግኘት ባለፈ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶአደር ብርሃኑ ረዳ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ታቅፈን እርከን፣ የጎርፍ መቀልበሻና መከላከያ እንዲሁም የውሀ ማቆሪያ ጉድጓድ በመስራታችን መሬታችንን ማዳን ችለናል " ብለዋል ።

የማሳቸው ለምነተ በመመለሱና እርጥበት በመቋጠሩ በሄክታር ከ20 አስከ 25 ኩንታል ምርት እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡

Published in አካባቢ

ባህርዳር  መስከረም 29/2010 በአማራ ክልል በቀጣዮቹ ስምንት ዓመታት ተጨማሪ 900 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

 ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል።

 የቢሮው ኃላፊ አቶ ይልቃል ከፋለ ለኢዜአ እንደገለጹት በየደረጃው የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋፋት አሁን ያለውን ዝቅተኛ ሽፋን ለማሳደግ ትምህርት ቤቶቹን መገንባት አስፈልጓል ።

 ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በመንግስት፣ በህብረተሰቡና በአጋር የልማት ድርጅቶች ትብብር መሆኑን ተናግረዋል።

 አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች እንደሚገነቡና እያንዳንዳቸው 1ሺህ 200 ተማሪዎችን ማስተናገድ አቅም እንደሚኖራቸው አመላክተዋል ።

 በክልሉ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 516 ብቻ በመሆናቸው የደረጃው የትምህርት ሽፋን 42 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

 አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶችም በከተሞች አካባቢ እንደሚገኙ ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 እንደ ቢሮ ኃላፊው  ገለፃ በመጭዎቹ ስምንት አመታት ትምህርት ቤቶቹ ተገንበተው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የትምህርት ሽፋኑ ወደ 74 በመቶ ያድጋል።

 የትምህርት ቤቶቹ በገጠር የቀበሌ ማዕከላትና መጋቢ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች እንደሚገነቡ ተናግረዋል ።

 "ለዚህም ስፍራዎቹን የመለየትና የግንባታ ቦታ መረጣ ስራ ተካሂዷል " ብለዋል።

 ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ሲያደርግ የቆየውን የገንዘብ፣ የቁሳቁስ አቅርቦትና የጉልበት ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

 አጋር አካላትም የሚያደርጉትን ድጋፍ በማጠናከር ለእቅዱ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ  ኃላፊው  ጠይቀዋል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን