አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 08 October 2017

አክሱም መስከረም 28/2010 የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ፖሊስ ጽህፈት ቤት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ሲሳተፉ አገኘዋቸው ያላቸውን 21 ደላሎች በህግ ቁጥጥር ሥራ ማዋሉን አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ አስተባባሪ ኮማንደር ጸሐዬ አረፋይኔ ትናንት ለኢዜአ እንዳሉት፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ ተሰማርተው ቆይቷዋል የተባሉት ደላሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በ2009 በጀት ዓመት መጨረሻ ፖሊስና ህዝቡ በቅንጅት ባደረጉት የክትትል ሥራ ነው።

ኮማንደር ጸሐዬ እንዳሉት አራት ሴቶችን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ህገ ወጥ ደላሎቹ በአሁኑ ወቅት በ12 የክስ መዛግብት ተከሰው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ይገኛል።

ፖሊስ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አደረጃጀትና በሕብረሰተቡ የነቃ ተሳትፎ ደላሎቹ መያዛቸውን ጠቁመው፣ የፍትሕ አካላት ከነዋሪው ህዝብ አደጃጀት ጋር በመቀናጀት እያከናወኑት ያለው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

እንደ ኮማንደር ጸሐዬ ገለጻ በዞኑ "አሕፈሮም፣ መረብ ለኸ፣ ወርዒ ለኸና ዓብይ ዓዲ"  ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በብዛት የሚፈጸምባቸው ወረዳዎች ናቸው።

ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በተሰራው ሥራም በአሁኑ ወቅት በወረዳዎቹ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መምጣቱን ጠቁመዋል።

"ሕብረተሰቡ በህገ ወጥ ስደት ላይ ያለውን ግንዛቤና አመለካከት ማደጉን ተከትሎ ደላሎችን ለመጠቆም ሆነ ዝውውሩን ለመከላከል እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚመሰገን ነው" ያሉት ኮማንደሩ፣ የተጀመረው የህዝብና የመንግስት ቅንጅታዊ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የዞኑ የወጣቶች ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ለአከ አባይ በበኩላቸው፣ በ2009 በጀት ዓመት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከ52 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

"ወጣቱ የስደት አስከፊነትና አደጋን በመረዳት በአገሩ ሰርቶ የመለወጥ ፍላጎቱ እየጨመረ ነው" ያሉት አቶ ለአከ፣ የፍትሕ አካላት ከወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የሚያደረግት ወንጀልን የመከላከል ሥራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በወርዒ ለኸ ወረዳ የ"ሕንዛት" ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ግደይ በርሄ በሰጡት አስተያየት፣ በአካባቢያቸው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ አብዛኛው ወጣቶች ስደትን ሳይመርጡ በመስኖ፣ እንስሳት እርባታና ማዕድን ልማት ዘርፍ ተደራጅተው ውጤታማ እየሆኑ ነው።

መንግስት በየጊዜው በሚሰጠው ስልጠና ህገ ወጥ ስደት መፍትሔ እንደማይሆን ለወጣቶች እያስተማረ መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቶች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መስከረም 28/2010 የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን በምስራቅ ወለጋ ዞን ለሚገኙ የአይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂዎች ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ተወካይ አቶ ተሰማ ጃለታ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎቱ የተሰጠው ተቀማጭነቱ እንግሊዝ አገር ካደረገው ''ፋይቲግ ብላይንድነስ ኢን ኢትዮጵያ'' ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው፡፡

ከመስከረም 22 እስከ መስከረም 27ቀን 2010 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ በሚገኘው የኮሚሽኑ ክሊኒክ ውስጥ በተሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎት በምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኙ 230 የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህሙማን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ህክምናው ከእንግሊዝ አገር የመጡ አምስት የዓይን ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪሞችና በሰባት ነርሶች አማካይነት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ከዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምናው በተጨማሪ ለ1 ሺህ 587 ሰዎች የዓይን ምርመራና ሕክምና እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

ከዞኑ ከሊሙ ወረዳ ገሊላ 01 ቀበሌ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ወይዘሮ ዳላሶ ጎቡ በሰጡት አስተያየት አንድ ዓይናቸው ማየት ካቆመ 3 ዓመት እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡

አሁን ግን ያለምንም ክፍያ ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸው ማየት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የነቀምቴ ከተማ 07 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቀጄላ ኩምሣ በበኩላቸው አንድ ዓይናቸው ከአንድ ዓመት ወዲህ ማየት ማቆሙን ገልጸው አሁን በተደረገላቸው ቀዶ ህክምና ብርሃናቸው መመለሱን ገልፀዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

መስከረም 28/2010 የሴቶችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ገለጸ።

ሊጉ ያለፈውን ዓመት የሥራ አፈፃፀም በመገምገም የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ ስራዎች ላይ ውይይት ዛሬ አካሂዷል።

ሊጉ በዓመታዊ ግምገማው እንዳመለከተው፤ ከትምክህትና ጥበት በሚመነጩ ግጭቶች ምክንያት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በበለጠ ሴቶች ለጥቃትና ችግር እየተጋለጡ ናቸው።

በዚህ መሰረት ሊጉ የሴቶችን መብትና ጥቅሞችን ለማስከበርና አስቀድሞ ከጥቃቶች ለመከላከል በተያዘው ዓመት በሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት አቅዷል።

የሊጉ አባል ወይዘሮ አስካለ ለማ እኛ ሴቶች ሰላም ሲኖር ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች ነን ሰላም ሲደፈርስ ግን እናት ከነልጇ የአደጋው ገፈት ቀማሽ ስትሆን መመልከት የተለመደ ነው ብለዋል።

እናት ድርጅቱም ሆነ ሊጉ የፌደራል ስርዓቱ አደጋ ብሎ የለያቸው "ትምክህትና ጥበትን" መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የህፃናትና ሴቶች ሰብዓዊ መብቶች መጣሳቸውን የሊጉ አባል ወይዘሮ አልማዝ ነጋ ተናግረዋል።

ወይዘሮ አልማዝ እንዳሉት ሊጉ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ሰፋፊ የውይይት መድረኮችን ለማካሄድ አጀንዳዎች ቀርጿል።

ወይዘሮ አመተረኡፍ ሁሴን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሴቶች ሊግ አደረጃጀቱን በማጠናከር የሰላም ጥቅምን የማስገንዘብ ሥራዎች ለማከናወን የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።

የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰአዳ ኡስማን "በኢህአዴግ የአመራር ደረጃ የምንገኝ ለሴቷ መብትና ጥቅም ቁመናል የምንል በቅድሚያ ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

ሊጉ በ2010 በጀት ዓመት ሰፋፊ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ለማዘጋጀት ማቀዱን ወይዘሮ ሰዓዳ ተናግረዋል።

በሚካሄዱት የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ለግጭት መነሻ እየሆኑ በመጡት የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና ጥበት የአመለካከት ችግሮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልፀው፤ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ እሴቶች ማስረፅም አጀንዳ አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል።  

የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ያካሄደውን ዓመታዊ ግምገማ ዛሬ አጠናቋል።

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌ መስከረም 28/2010 የልማት ቡድኖችን በማጠናከር የሴቶችን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አስታወቁ፡፡

ቢሮው የሴቶችን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ በሚቻልበት ዙሪያ በዘርፉ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ትናንት በመቀሌ ከተማ ውይይት አካሄዷል።

የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር  የትምወርቅ ገብረመስቀል በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ክልሉ በተፈጥሮ ሃብትና በሌሎች የልማት ስራዎች እየተመዘገቡ ባሉ ለውጦች የሴቶች ተሳትፎ የጎላ ነው፡፡

ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረውና የሴቶችን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ እንዲጎለብት በየአካባቢው የተቋቋሙ የልማት ቡድኖችን የማጠናከር ስራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የልማት ቡድኖችን በማጠናከር ዙሪያ የባለድርሻ አካላትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከቢሮው ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በቢሮው የልማታዊ እቅድ ባለሙያ አቶ ሃይለ ወልዱ በበኩላቸው ከ699 ሺህ በላይ የሚሆኑ የክልሉ ሴቶች ዘንድሮ በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡

እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም የልማት ቡድኖችን የማጠናከረና የማደራጀት ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከወዲሁ እየተከናወነ ነው።

በክልሉ በቡድን ተደራጅተው ወደ ልማት እንዲገቡ በእቅድ ከተያዙት ሴቶች መካከል ከ30 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑትን በልማት ተሳትፎአቸውና ተጠቃሚነታቸው ሞዴል ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ  ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ቢሮው ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመትም በክልሉ ከሚገኙ 710 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በ562ቱ ህገወጥ ስደትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የስራ ኃላፊዎችና በዘርፉ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 28/2010 በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የመብት ጥሰቶችና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ሕገ መንግስታዊ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ህዝቦች መብት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ አውደ ጥናት ትናንት በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ፅሀፎች እንዳመለከቱት፤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ህዝቦች መብት ለማክበርና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ህገ መንግስታዊ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር ወሳኝ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የሚታዩ ሁሉም ችግሮች በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ መፍታት የሚቻል ቢሆንም፤ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መጠናከርና  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻል ወቅታዊ ምላሽ እንደሚፈልግ በጥናቶቹ ተጠቁሟል።

ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ እንደገለፁት፤ በህገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ቢወጡ የሰብዓዊ መብትን መድፈር አይኖርም፤ የግጭት መንስኤዎችም ይፈታሉ።

በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ የሚታዩ የዜጎችን የመብት ጥሰቶችና አላስፈላጊ ግጭቶች "በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው" ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ ይሄን ለማድረግ ህገ መንግስታዊ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ ፍሰሃ ባቀረቡት ጥናት አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ህዝቦች የሥራ ቅጥር፣ የአስተዳደር፣ የአገልግሎት ጥያቄ ምላሽ ያለማግኘት እና በፖለቲካ ተሳትፎ መገለል የመሳሰሉ ችግሮች እንደሚደርስባቸው ገልፀዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት የሚያችሉ ህገ መንግስታዊ አሰራሮች ቢኖሩም በየደረጃው የተዋቀሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች የሚነሱትን ጥያቄዎች "በፍጥነት እየመለሱ አይደልም" ብለዋል።

በተለይ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ህዝቦች የሚደርሱ ተጽእኖዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ህገ መንግስታዊ እና አስተዳደራዊ ተቋማት ለዜጋው አመኔታ በሚፈጥር መልኩ ማደራጀትና ማጠናከር ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።

በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የወላይታ ሰዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ አወል አለማየሁ በሰጡት አስተያየት፤ ህገ መንግስታዊ የዴሞክራሲ ተቋማትን ከማጠናከር በተጨማሪ አገራዊ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

"ከክልሎች እስከ ቀበሌዎች ያሉት መዋቅሮች አገራዊ እሴቶች ለማጎልበት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ አይደሉም"ያሉት አቶ አወል፤ ትኩረት በመስጠት ቢሰሩበት በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል በማለት ገልጸዋል።

አውደ ጥናቱን የመሩት አምበሳደር ካሳ ተክለብርሃን እንደገለፁት የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ህዝቦች ሙሉ መብትና ዋስትና የሰጠ ነው።

ይሁን እንጂ የህገ መንግስታዊ ተቋማት አለማጠናከርና የአፈፃፀም ችግሮች መኖራቸውን በመግለፅ በጥናቶቹ የቀረቡ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በራሱ ጥናቶች ተመስርቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል።

ከህግ አኳያ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ህገ መንግስቱ አያግድም "ህገ መንግስታዊ ተቋማት ሓላፊነተታቸውን የሚወጡበት ደረጃ እንዲደርሱ መስራት ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

በአውደ ጥናት ላይ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን የተመለከተ ጥናት የቀረበ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ ቀመር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አመልክቷል።

ቀመሩ በአሁኑ ወቅት ለዘጠነኛ ጊዜ ተሻሽሎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያሳየው ጥናቱ፤ የክልሎች የወጪና የገቢ ማመጣጠን ፍትሀዊ መሆኑን ጠቁሟል።

በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚነሱ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎችን በጥናት ለመመለስ የሚሰሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልም አስፈላጊ መሆኑም በአውደ ጥናቱ ላይ ከተነሱ ነጥቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።

 

Published in ፖለቲካ

ጋምቤላ መስከረም 28/2010 በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ በመጡ ታጣቂዎች ታፍነው ተወስደው ለተመለሱና ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት የደቡብ ክልል የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

የደቡብ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ የሚገኙ ተመላሽ ህጻናት ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ህጻናቱ የተሟላ እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ክልላቸው ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።

ቀደም ሲል የሙርሌ ታጣቂዎቹ በህዝቡ ላይ በፈጸሙት አሰቃቂ ጭፍጨፋና ህጻናቱ ታፍነው በተወሰዱበት ወቅት የክልሉ መንግስት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶት እንደነበርና ህጻናቱም ይመለሳሉ የሚል ተስፋ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባደረጉት ቅንጅታዊ ጥረት ህጻናቱ ተመልሰው በአካል ለማየት በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

ህጻናቱ የተሟላ ድጋፍና እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማገዝ የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ደሴ አረጋግጠዋል።

ህጻናቱ የተሟላ ስብዕና ይዘው እንዲያድጉ ለማስቻል ለተጀመረው ሥራም የደቡብ ክልላዊ መንግስት የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በበኩላቸው፣ የሙርሌ ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማድረግ ህጻናቶችን አፍነው ቢወስዱም በተደረጉ ጥረቶች አብዛኞቹ ህጻናት ወደአገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ከተመለሱት ህጻናት መካከል ብዙዎቹ ቤተሰቦቻቸው የሞቱባቸው መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህ ሕጻናት የተሟላ ሰብዓዊ አገልግሎት አግኝተው እንዲያድጉ የክልሉ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ህጻናቱ አድገው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ላደረገው ድጋፍና አጋርነት ያላቸውን ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ከደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ በመጡ የታጠቁ ኃይሎች ከተወሰዱት ከ138 ህጻናት መካከል የተመለሱት ህጻናት ቁጥር 104 መድረሱን ከክልሉ መስተዳድር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ መስከረም 28/2010 በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች የተጀመረው የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች አስታወቁ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በጋምቤላ ክልል የተከናወኑ የመንደር ማሰባሰብና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ከጉብኝቱ በኋላ እንዳሉት በክልሎቹ መካከል የተጀመሩት የሁለትዮሽ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በክልሎቹ መካከል የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ከተጀመረ ወዲህ የህዝቦች አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በሁለቱ ክልሎች በተደረገው የተሞክሮ ልውውጥ፣ የማስፈጸም አቅም ግንባታና የልማት መደጋገፍ ሥራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በጋምቤላ ክልል ህዝቡን በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ዘላቂ ለማድረግ የተከናወኑት ሥራዎች ስኬታማ እንደነበሩ በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሁለቱ ክልል ህዝቦች አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲጎለብት የተጀመረው የልማት ትብብርና የመደጋገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በበኩላቸው እንዳሉት፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተጀመረው የልማት ትብብርና የመደጋገፍ ሥራዎች የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት እያጠናከረው መጥቷል።

ክልሉ ከደቡብ ክልል፣ ከፌዴራል መንግስትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት ያገኘውን እገዛ በመጠቀም ህዝቡን በመንደር በማሰባሰብ በዘላቂነት የልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

አቶ ጋትሉዋክ አንዳሉት፣ የደቡብ ክልል ለጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና አመራሩ ቀደም ሲል ከነበረበት የጠባብነት፣ የጎሰኝነትና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ወጥቶ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር እንዲከተል ማድረግ ተችሏል።

በአሁን ወቅት ክልሉ በሰላምና በልማት የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በሁለቱ ክልሎች የተጀመረው የልማት ትብብርና መደጋገፍ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ላለፉት ሁለት ቀናት በአኝዋክና በኑዌር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ  የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላትና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ድሬደዋ መስከረም 28/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/ በሽታ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ  ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  የአተት በሽታ በከተማው ጠረፋማ ቀበሌዎች ተከስቷል፡፡

ከመስከረም 20 እስከ 26 ቀን 2010 ባሉት ቀናት በእነዚሁ ቀበሌዎች 127 ነዋሪዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡     

በሽታውን ለመቆጣጠርም በሽታው በተከሰተባቸው የገጠር አካባቢዎችና  በሣቢያን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለህሙማን የሚያገለግሉ የህክምና ማዕከላትና የጤና ባለሙያዎች ቡድኖች ተቋቁመው አስፈላጊው  ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በበሽታው ከተያዙት ውስጥም አብዛኛዎቹ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ፣ ሽንት ቤትን በንፅህና በመጠቀምና  አትክልትና ፍራፍሬን አብስሎ በመጠቀም ከበሽታው ራሱን እንዲከላከል ጥሪ አቀርበዋል፡፡

በሣቢያን ሆስፒታል ህሙማንን እያከሙ የሚገኙት የጤና መኮንን ትዕግስቱ የማነ በሰጡት አስተያየት ምልክት የታየበት ሰው ፈጥኖ ወደ ህክምና ቢመጣ በቀላሉ እንደሚድን ጠቁመዋል፡፡

በአተት ተይዘው በሣቢያን ሆስፒታል ህክምና ሲሰጣቸው የነበሩት ወይዘሮ ዜይኑ ኡስማኤል ‹‹ከመጣሁ ሶስት ቀኔ ነው፣ አሁን ታክሜ በመዳኔ ወደ ቤቴ ልመለስ ነው፤ የታመሙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል እንዲመጡ ኃላፊነቴን እወጣለሁ›› ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጅማ መስከረም 28/2010 በጅማ ዞን የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረው ጥረት አበረታች ቢሆንም አሁንም ምላሽ ያላገኙ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች ተወካዮች የተሳተፉበት የልማትና የሰላም የውይይት መድረክ በጅማ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ተሳታፊዎች በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ የዞኑን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው፡፡

በተለይ በክራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች ለረዢም አመታት የተያዘና ያለማ መሬት በማስመለስ ለስራ አጥ ወጣቶች መተላለፉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የመልካም አስተዳደር ጥያቄያቸው ምላሽ እያገኘ መሆኑን ማሳያ ናቸው፡፡

የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሃመድዜን ተማም በሰጡት አስተያየት በዞኑ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት አበረታች ቢሆንም አሁንም ምላሽ ያላገኙ የልማት ጥያቄዎች አሉ፡፡

ለአብነትም ጅማ ዞንን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው ዋና መንገድ በመበላሸቱ ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ ነው፡፡

ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እያደረሰ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ከሊሙ ኮሳ ወረዳ የተሳተፉት አቶ ሱልጣን አባፊራ በበኩላቸው በወረዳዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ህገወጥ የደን ጭፍጨፋ አካባቢውን እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሶከሩ ወረዳ የተሳተፉት አቶ ተማም አባዱራ በበኩላቸው በሚኖሩበት አካባቢ የመብራት፣ የውኃ፣ የመንገድና የመሳሰሉት የመሠረተ ልማት ችግር በመኖሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሃቢባ ስራጅ የጅማ ዞን  ከጥልቅ ተሃድሶ  በኋላ  በቂ ባይሆንም ለውጦች እየታዩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በአመርቂ ሁኔታ ለመመለስ የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡

የጅማ ዞን አስተዳደር አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ የሚፈልገው ልማት ዕውን የሚሆነው አሰተማማኝ ሰላም ሲኖር በመሆኑ ህብረተሰቡ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከተሃድሶ በኋላ መንግስት በርካታ የህብረተሰቡን ጥያቄ የመለሰ ቢሆንም ከችግሩ ስፋትና ከህብረተሰብ ፍላጎት አንጻር የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

''በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን እርካታ በበለጠ ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ ይጠበቅናል'' ብለዋል፡፡

በህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ በዞኑ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 28/2010 የዊልቼር ቅርጯት ኳስ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት በማካፈል ለስፖርቱ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የኢትዮጵያ ቅርጯት ኳስ ፌደሬሽን አሳሰበ።

በአዲስ አበባ ለ10 ተከታታይ ቀናት ለዊልቼር ቅርጫት ኳስ ስፖርተኞች፣ ለተመረጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ሳይንስ መምህራን፣ ለአሰልጣኞችና ለዳኞች ሲሰጥ የቆየው የዊልቸር ቅርጯት ኳስ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጥበበ ቸኮል በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ለሌሎች በማካፈል ስፖርቱን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ስፖርትን ለማስፋፋት የራሱ ፌዴሬሽን ሊኖረው እንደሚገባና ብሄራዊ ቡድን ማቋቋምም አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ፌዴሬሽኑ የዊልቼር ቅርጫት ኳስን ለማስፋፋት ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመነጋገር የዊልቼር ብስክሌት ለሁሉም ክልሎች እንዲሰራጩ ማድረጉንም ገልጸዋል:: 

ስልጠናውን የሰጡት አሜሪካዊው ጀስ ማርት ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን የዊልቼር ቅርጯት ኳስ ተጫዋቾች ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ በኩል ጥሩ አቅም አላቸው።

ይሁን አንጂ አካልንና የአዕምሮ ቅንጅትን በሚጠይቁ ቴክኒኮች ላይ ልምምድ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

ጀስ ማርት በሚቀጥለው ዓመትም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመምጣት ስልጠና ለመስጠት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

በ19 ዓመት ዕድሜያቸው በመኪና አደጋ የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባቸው አሜሪካዊ ጀስ ማርት በአፍጋኒስታን የወንዶችና ሴቶች የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሲሆኑ በተለያዩ አገራት እየተጋበዙ ስልጠና በመስጠት ይታወቃሉ።

ስልጠናውን ከተከታተሉት 90 ሰዎች መካከል 30ዎቹ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረጡ የስፖርት ሳይንስ መምህራን፣ አሰልጣኞችና ዳኞች ናቸው።

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን