አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 07 October 2017

አዲስ አበባ መስከረም 27/2010 ህገወጥ ላኪዎች መንሰራፋት ምርታቸውን ወደ ውጪ የሚልኩ ባለሀብቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው ተጠቆመ። 

በተለይ ስጋና የስጋ ውጤቶችን በሚልኩ ባለሃብቶች ዘንድ ችግሩ ጎልቶ ይታያል።

ይህ የተገለጸው 'የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ስርአትና ተግዳሮቶቹ' በሚል ሐሳብ ዛሬ በተከናወነ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሞገስ ሀይሌ እንደተናገሩት፤ እነዚህ ህገወጥ ላኪዎች በቸልታ እየታዩ አገሪቷንና ባለሃብቶችን ለኪሳራ እየዳረጉ ይገኛል።

በመንግስት ደረጃ አዋጅ ቢወጣም "ተፈፃሚነቱ ላይ እየተሰራ አይደለም" ነው ያሉት።

የምርት ማጓጓዣ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ አለመግባት፣ የሎጀስቲክ አለመሟላት፣  የመሬት አቅርቦት ችግርና የእንስሳት መኖ በበቂ ሁኔታ ገበያ ላይ አለመገኘት ለወጪ ንግዱ ተግዳሮት ከሆኑ ምክንያቶች መሀል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አቶ ሞገስ ጠቅሰዋል።

የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ጉላዶ በበኩላቸው፤ በወጪ ንግድ ዘርፍ ተፈላጊው ውጤት እንዳይመጣ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አስታውቀው፤ ሚኒስቴሩ ለላኪ ባለሃብቶች ሁኔታዎችን ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለተቀባይ አካል ታማኝ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

በግብይት ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ ወጪ መቀነስ፣ ጠንካራ የግብይት ስራ መፍጠርና የኮንትራት አስተዳደራቸውን ማጠናከር ከባለሃብቱ የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ዶክተር በቀለ ገልጸዋል።

የገቢዎች እና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ነብዩ ሳሙኤል እንደገለፁት፤ የላኪዎች ምርት በጉምሩክ ጣቢያዎች እንግልት እንዳይደርስበት በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ለወጪ ንግዱ መሳካት እየተሰራ ነው።

ከዚህ ቀደም የፍተሻና የምርመራ ጣቢያ አንድ ሲሆን፤ አሁን የጣቢያዎችን ቁጥር መጨመር ተችሏል።

በተጨማሪም ፍተሻና ምርመራውን ምርቱ ባለበት ቦታ ሄዶ በማካሄድ ስራውን ለማቀላጠፍ እየተሞከረ መሆኑንም አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

የአላና ግሩፕ ተወካይ አቶ ግደይ ገብረመድህን እንዳሉት፤ መንግስት ለወጪ ላኪዎች የተለየ ማበረታቻ ማድረግ አለበት።

በወጪ ንግድ ላይ አመርቂ ውጤት ያሳዩ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ለላኪዎች የሚሰጣቸው ማበረታቻ የላቀ እንደሆነ ነው የገለፁት።

አገሪቷ ካላት የእንስሳት ሀብት  ለውጭ ገበያ የምታቀርበው እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን፤ መንሰኤውን ፈልጎ ችግሩን ማቃለል እንደሚገባም ገልፀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምት መስከረም 27/2010 በአራቱም የወለጋ ዞኖች ህብረተሰቡን የሚያረካ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት የሚረዳ የአቅም ግንባታ ስልጠና በነቀምቴ ከተማ ተጀመረ ።

በስልጠናው ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተውጣጡ ከ350 በላይ የመንግስት ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

በኦሮሚያ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ሪፎርም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ታደሰ ስልጠናው ሲጀመር እንደገለጹት ሕብረተሰቡ በሚሰጠው አገልግሎት እርካታ እንዲያገኝ ለማስቻል ስልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

ሠራተኛውን በማብቃት የመልካም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች የተቀላጠፈ መልስ እንዲያገኙ  ሕብረተሰቡን በሳተፈ ሁኔታ  ያሉት ችግሮች ተፈትተው ሕዝቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ  ለማድረግ የሥልጠናው ግብ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በቢሮው የዕቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ላሜሣ አያና በበኩላቸው  የለውጥ ትግበራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል እንዲቻል ለሰራተኞቹና ለስራ ኃላፊዎቹ የተዘጋጀው ሰልጠና  ከትናንት ጀምሮ ለስምንት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስረም 27/2010 በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩ ችግሮችን በመፍታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የደቡብ  ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አባላት ተናገሩ።

 አባላቱ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ 25ኛውን የድርጅቱን የምስረታ በአል ከእህት ድርጅቶች ጋር ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

 በመልካም አስተዳደር፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፤  የመሰረተ ልማት ግንባታ መጓተት፤ ትምክህትና ጠባብነት በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ ችግሮችን እየፈታን ነው ብለዋል።

 እነዚህ ችግሮች በአባሉ ላይም የሚስተዋሉ መሆናቸው ያነሱት አባላቱ በተደረጉ ግምገማዎች የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት አመራሩ ቀደም ሲል ከነበረበት መፋዘዝ በመውጣት ተነቃቅቶ የህዝቡን የልማትና አብዛኛው ህዝብ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በእቅድ ይዞ ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረጉን ተናግረዋል።

 አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ መታገልና ሌሎች የድርጅቱን እሴቶች ከማስጠበቅ አንጻር ጉድለቶች መኖራቸውን በጥልቅ ተሃድሶ ለይተን ለማረም ቆርጠው መነሳታቸውንም አባላቱ በበዓሉ ወቅት ተናግረዋል።

 በዚህም ችግሮችን የመፍታት ሂደት መጀመራቸውን ያነሱት አባላቱ ለአብነትም በክፍለ ከተማው የመሰረተ ልማት፤ የፍሳሽ ማስወገጃ፤ የግብር አከፋፈል፤ የግንባታዎች አለመጠናቀቅና ሌሎች ችግሮችን የመፍታት ሂደት ተጀምሯል።

 እንደ ደህዴን ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆንም የህዝቦችን ጥያቄ ለማስቀጠል በጋራ እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) 25ተኛ አመት የብር ኢዩ በልዩ የምስረታ በአል በተለያዩ ዝግጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 27/2010 አዲስ አበባን ጽዱ ፣ ውብ እና አረንጓዴ የተላበሰች እንድትሆን በሚደረገው ጥረት ሕብረተሰቡ ከከተማይቱ ውበትና መናፈሻ ቢሮ ጎን እንዲሠለፍ ጥሪ ቀረበ።

በከተማዋ ዋና ዋና በተባሉ አካፋይ መንገዶች  መሐል ላይ በተዘጋጀው የአትክልት ሥፍራ ዛፎችና ውብ አበባዎች ተተክለው እንክብካቤ  እየተደረገላቸው ነው፡፡

ነገር ግን ከተማይቱን ጽዱ፣ ውብ  እና አረንዴ እንድትሆን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ  እፅዋቶቹን ከመንከባከብና ከመጠበቅ አኳያ ድክመቶች እንዳሉበት ይስተዋላል።

የቢሮው  ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ  መኮንን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተተከሉ ተክሎች የማህበረሰቡን ጥበቃና አንክብካቤ የሚሹ ቢሆንም በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ በቸልታ እየታዩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

“የተተከሉት አበቦች በህብረተሰቡ እየተረገጡና እየተቀነጠሱ ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጇ ከተማዋን  ውብና አረንጓዴ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ሚና  የጎላ በመሆኑ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውራ ለመቃኘት ባደረገችው ሙከራ ከተማዋን  ለማስዋብ የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ በማጣታቸው እየደረቁና አካፋዮቹም ቆሻሻ እየተጣለባቻው  እንደሚገኙ ታዝባለች።

በመሆኑም ከተማዋን ውብና አረንጓዴ ለማድረግ በቋሚነት ተክሎቹን የሚንከባከብ አካል ሊኖር  እንደሚገባ  ተገንዝባለች።

ህብረተሰቡ አረንጓዴ ሥፍራዎቹንና ሌሎች የተዘጋጁለትን ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በአግባቡ ጠብቆ እንዲገለገልባቸው የማገዝና ምክር መስጠት፣ የአስተዳደሩ ባለሙያዎች ቀጣይ ሥራ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

አስተያየተ ከሰጡን የመዲናዋ  ነዋሪ ውስጥ ወጣት  አበራ አለሙ  ከአሁን ቀደም በማህበረሰቡ ውስጥ ለአረንጓዴ  ተክሎች  ብዙም ትኩረት እንዳልነበርና  በጊዜ ሂደት በጥቂቱ ለውጥ  መኖሩን በመግለጽ  ሁላችንም ለተክሎቹ  ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ብሏል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርቲስት  አለማየሁ ጌታቸው  በበኩሉ ከተማዋን ለማስዋብ የተለያዩ ስራዎች  እየተከናወኑ መሆናቸው የሚበረታታ እንደሆነ ገልጾ  ነገር ግን በተለያዩ ወቅቶች  የሚተከሉ እጽዋቶችን እድገት  የሚከታተል  አካል አለመኖሩን  ተናግረዋል።

በአዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሰረት ከተማይቱ ካላት አጠቃላይ የመሬት ስፋት ውስጥ 22 ሺህ ሄክታር ያህሉ በአረንጓዴ ተክሎች መሸፈን ያለበት ቢሆንም አፈጻጸሙ ከዚህ በታች መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከተሞች በአማካይ ለአንድ ሰው ከ7 እስከ 9 ካሬ የአረንጓዴ ስፍራ መኖር እንዳለበት ይጠበቃል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ መስከረም 27/2010 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የኮንትሮባንድ ንግድን ለመግታት ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድ ትራስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡

 ህጋዊ ንግድን ለማጠንከር ከ32 ሺህ በላይ ስራ አጥና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ836ሚሊየን በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱም ተመልክቷል፡፡

 በቢሮው  የንግድ ማስፋፊያ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መሀመድ አሊ ጣሂር  እንዳሉት የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት በክልሉ ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለማጠናከር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

 በዚህም  ህጋዊ የንግድ ስራዎች እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡

 በክልሉ ቀደም ሲል በኮንትሮባንድ ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ህብረተሰቡን ባማከለ መልኩ ከቀርፅ ነፃ እንዲገቡ መፍቀዱ በአካባቢው ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ አግዟል።

 ባለፈው ዓመት ብቻ ከ30ሺህ በላይ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር በማሲያዝ   የንግድ ፍቃድ እንዲያወጡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

 ጅግጅጋ ከተማ የተደራጀው ኢፍቲን የተባለው የህብረት ስራ ማህበራት ጥምረት ሊቀመንበር ወይዘሮ ራህማ መሀሙድ  በበኩላቸው መንግስት ከቀረፅ  ነፃ የተለያዩ የምግብ ነክ እቃዎችን እንዲያስገቡ ባመቻቸው እድል በመጠቀም ሸቀጦችን ለሀብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አገልገሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 27 ማህበራትን በጥምረት የያዘው ይሄው አደረጃጀት  በምግብ እቃዎች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ለመከላከልና ህጋዊ ንግድ እንዲስፋፋ ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 በጅግጅጋ ከተማ  በንግድ ሰራ ላይ የተሰማሩት  አቶ ፈርሃን አብዲ ቀድም ሲል ባህላዊ አልባሳትና የምግብ ፍጆታ እቃዎች በህጋዊ መንገድ ለማስገባት አስቸጋሪ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

 በዚህ የተነሳም እቃዎችን በኮንትሮባንድ በማስገባት ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው ካለፉት በሦስት ከዓመታት ወዲህ ግን ማህበር በማቋቋም መንግስት ኮንትሮባንድን ለማስቀረት ከቀረፅ ነፃ የፈቀደውን እድል እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ሶማሌ አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ አብዲራህማን ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር  51 ቅርንጫፎችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመክፈት ለህብረተሰቡ የብድርና የቁጠባ  አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 ተቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን እድገት እያስመዘገበ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ መሀመድ" የህብረሰቡን እምነት እና ፈላጉት ተከትልን በመስራታችን ውጤታማ ሆነናል "ብለዋል።

 ከ32 ሺህ በላይ ስራ አጥና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ836ሚሊየን በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

 ተቋሙ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት  ሰባት ዓመታት  ከአንድ ቢሊዮን በር በላይ ብድር በመስጠት ከዚህም 98 በመቶ ማስመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 የተቋሙ ደንበኞች 155 ሚሊዮን ብር መቁጠባቸውን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡

 በጉርሱም ወረዳ ትቅደም ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘይነባ አብዲ ከተቋሙ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ደንበኞች መካከል አንዷ ናቸው፡፡፡

 ከተቋሙ ባገኙት 60 ሺህ ብር ከቀረፅ ነፃ የምግብ እቃዎችን ከሚያስገቡ ማህበራት ጋር የንግድ ትስስር በመፍጠር በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተበደሩትን ገንዘብ በመመለስ መቶ ሺህ ብር ማትረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 27/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም አቀፍ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ሙያተኞችን ለማፍራት እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ።

አየር መንገዱ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 262 ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል  50 በአውሮፕላን አብራረሪነት፣ 66 በአውሮፕላን ጥገና፣ 120 በበረራ አስተናጋጅነት፣ 26 በመሳሪያዎች ጥገና፣ 10 በኢንዱስትሪያል መካኒክስ 16ቱ ደግሞ በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪሲቲ የሰለጠኑ ናቸው።

34ቱ ተመራቂዎች ከካሜሮን፣ ከሩዋንዳ፣ ከኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ከቶጎና ከኮንጎ የተውጣጡ  መሆናቸው ተገልጿል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት፤አየር መንገዱ ከአፍሪካ ከተለያዩ የአቪየሽን ዘርፎች የመጡ ባለሙያዎችን በትምህርና ስልጠና ውጤታማ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

ይህም የተለያዩ የአፍሪካ አገራትና መንግሥታት ሊጠቀሙበት የሚችል ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በአየር መንገዱ የአቪዬሽን አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ደበበ በበኩላቸው፤አካዳሚው በአሁኑ ሰአት በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት የሚችል ማሰልጠኛ ለመሆን እየሰራ ይገኛል።

ለአገሪቱ እድገት ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ያለበትን ማኅበራዊ ሃላፊነት በመወጣት ረገድም ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ተመራቂ ባለሙያዎችም ድርጅቱን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ሰአት በአብራሪነት፣በቴክኒሽያንነት፣በአስተናጋጅነት፣ በፋይናንስና ገበያ ባለሙያነት፣ በደንበኛ አገልግሎትና በአቪዬሽን መሪነት ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። 

92 ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ ከአሁን በፊት በአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር የዓመቱ የተሻለ አገልግሎት ሰጪ ተብሎ መሸለሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተቋቋመ ጀምሮ ከ16 ሺ የሚበልጡ ሰልጣኞችን በተለያዩ የሙያ መስኮች አሰልጥኖ አስመርቋል።

Published in ማህበራዊ

ሀረር መስከረም 27/2010 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  " የላቀ ውጤት ማስመዝገቢያ ዘዴዎች" በሚል ርዕስ ለተቋሙ  መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ እንዳሉት ስልጠናው የሰው ልጅ በኑሮው ውጤታማ መሆን የሚችሉበትን መንገድ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ተሞክሮዎች በማቆራኘት የሚቀርቡበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

"መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኛች ተሞክሮ በመቅሰም ልምዳቸውን ያጎለብቱበታል " ብለዋል ።

በተለይ ሰላማዊና ቅን አስተሳሰብ ማዳበር የተቋሙን የመማር ማስተማር ስራና በተማሪዎች መካከል ያሉትን መልካም ግንኙነቶች ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የተቋሙ አጠቃላይ የስራ ሂደት ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ምሁራን ከቀለምና ሙያ ትምህርት ጎን ለጎን ሰላማዊና ቀና አስተሳሰብን በማስተማር ለአገር እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ   ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው፡፡

ምሁራን ለዜጎች የሚሰጡት የቀለም ትምህርትና የሚያከናውኑት የምርምር ስራ የማህበረሰቡን ህይወት ከመቀየር ባለፈ የላቀ የሀገር እድገትና አስተሳሰብ በማምጣት በኩል አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ።

ዜጎች ሀገሪቱ ያላትን አንጡራ ሐብትና ባህሎችን  በአግባቡ ተጠቅመው የተሻለ ህይወት እንዲመሩ በማሳወቅ ረገድ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው ስልጠና የዋናው ግቢ እንዲሁም ሐረር ከተማ የሚገኘው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እየተሳተፉ ነው።

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ መስከረም 27/2010 በአንድ ዞን ስር መተዳደራቸው ትስስራቸውን በማጠናከር አቅማቸውን አቀናጅተው ለልማት ለማዋል እንደረዳቸው የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከስድስት ዓመት ወዲህ በአንድ ዞን ስር መታቀፋቸው የጋራ ትስስራቸውን አጠናክሮላቸዋል።

የሰገን ከተማ ነዋሪና የኃይማኖት አባት ቄስ አባገዳሙ በቀለ  በአንድ ዞን ታቅፈው መተዳደር በመጀመራቸው ትስስራቸውን አጠናክረው  የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እያጎለበቱ ልማታቸውን እያፋጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ቀደም ሲል በልዩ ወረዳዎች መካከል ይከሰቱ የነበሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች አሁን ላይ እየቀሩ ነው"ያሉት ደግሞ የኮንሶ ወረዳ ነዋሪ አቶ ካጫውቶ ዓለሙ ናቸው ፡፡

"ወረዳዎቹ በአንድ ዞን ስር እንዲተዳደሩ መደረጉ የህዝቡን የተዛባ አስተያየት በመቀየር፣የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ጤናማ እየሆነና ሰላማችን  ዋስትና እያገኘ  መጥቷል " ብለዋል ።

"በአካባቢውም በልማት ተጠቃሚ እየሆንን ነው" ያሉት አቶ ካጫውቶ  ሁሉንም ወረዳዎች ያገናኘ የመኪና መንገድ በመሰራቱ በሸቀጣ ሸቀጥና በግብርና ምርቶች ንግድ ትስስራቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃልገዮ ጂሎ  እንደገለጹት በዞኑ ተበታትኖ የነበረውን የልማት አቅም ለመጠቀም ልዩ ወረዳዎች በአንድ መሰብሰባቸው በጋራ የመልማትና የመጠቀም እድላቸውን አጠናክሯል፡፡

"በልማትና በመልካም አስተዳደር ህዝቡ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል" ብለዋል። 

ዞኑ ከተመሠረተ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል ።

ሶስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገንበተው ተማሪዎች አገልገሎቱን ፍለጋ ይደርሰባቸው የነበረ እንግልት መቅረቱን ጠቅሰዋል ።

በዞኑ የሚገኙ ከ260 በላይ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዓመት ከ153ሺህ በላይ ተማሪዎች በመቀበል የትምህርት ተደራሽነት እየሰፋ መጥቷል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት ከዋና ከተማው ሰገን የሚያገናኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶችም በመገንባት ላይ ናቸው ።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠው ለገበያ ማምረት መጀመራቸውን የጠቀሱት አስተዳዳሪው በልዩ ወረዳነት በነበሩ ጊዜ ወሰን ተሻግረው የማይጠቀሟቸውን የተፈጥሮ ሃብቶች አሁን በጋራ እያለሙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ደኢህዴን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በበኩላቸው አስተዳደራዊ ትስስሩ በአምስቱ ወረዳዎች በአርሶ አደሩ ዘንድ የቆዩ የሥራ ልምዶችና ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል ፡፡

በአማሮ የባህላዊ መስኖ አጠቃቀም፣ በኮንሶ የአፈር ጥበቃ ሥራ፣ በደራሼ ማሳን በእርጥበት የማቆየት ዘዴና በቡርጂ ደግሞ ጠንካራ የእርሻ ዝግጅት ልምዶችን አርሶ አደሩ እርስ በርስ እየተለዋወጠ ነው፡፡

የህዝቡን አንድነት የሚፈታተኑ የጠባብነትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት ባለፈው ዓመት  የተደረገው ተሃድሶ ለወጥ ማምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት አመራሩ በውጤት የታጀበ ተግባር መፈጸም እንዳለበት ጠቅሰው  ህዝቡም ሰላሙና ልማቱ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል ፡፡

Published in ፖለቲካ

ማይጨው መስከረም 27/2010 የተሻሉ ማስተማሪያና የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም  ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጋን ለማፍራት እንደሚጥሩ የራያ ዩኒቨርሰቲ መምህራንና ሰራተኞች ገለጹ።

 ለዩኒቨርሰቲው መምህራንና ሰራተኞች ለአንድ ሳምንት ሲሲጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

 የዩኒቨርሰቲው መምህራን ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ  ባወጡት የአቋም መግለጫ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ችሎታ በማጥናትና የባህሪ ክፍተት በመለየት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

 በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተማሪዎችን የትምህርት አቅም ለማሳደግ  የመደጋገፊያ መርሀግብር በማዘጋጀት፣ አጋዥ መፃህፍትን በመጠቀምና  ተከታታይ ምዘናና ግብረ መልስ  በመስጠት ብቃትና ራዕይ ያለው ባለሙያ ለማፍራት እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

 የለውጥ ትግበራ አሰራር ስርዓት በአግባቡ በመተግበር የሀብት ብክነትን በመቀነስና ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር የተቋሙን ስራ ለማፋጠን  በትጋት ለማሰራት ቃል ገበተዋል ።

 "ከዩኒቨርስቲው ሰልጥኖ  የሚወጣን የሰው ሃይል ስራ የመፍጠር አቅም ምጣኔን  ከ80 በመቶ በላይ ለማድረስ እንሰራለን ሲሉም ሰልጣኞቹ በአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል ።

 የዩኒቨርሰቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሮ ሰይድ በበኩላቸው   የተቋሙ  መምህራንና ሰራተኞች የግልና የስራ ስነ ምግባርን ጠብቀው ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ በመሆን የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

 በተለይ መምህር ሀገርን የሚገነባ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነት የተጣለበት እንደመሆኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ጭምር ግዴታቸውን ለመወጣት ከወዲሁ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 27/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ለወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ገለጸ።

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በ 2009 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና 2010 ዓ.ም እቅድ ላይ ከአባላቱ ጋር ውይይት አድርጓል።

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ እንዳለው ወጣቶች በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ያነሷቸውን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሊጉ ከኢህአዴግ ጋር እየሰራ ነው።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለዩ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ስራ አጥ የሊግ አባላት መካከል ከ 762 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሪው ድርጅት ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታልም ብሏል።

የደህዴን ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት አክሊሉ ታደሰ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው የወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለመፍታት መነሻ እንደሆነ ገልጿል።

የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች አለመኖር፤ የፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ችግር፣ የብድር አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን በጥልቅ ተሃድሶው ተገምግመው ለውጥ የመጣባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጿል።

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ አባል ወጣት አበራ ጋዲሳ በኦሮሚያ፣ አማራና ሌሎች አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ወጣቶች የተሳተፉበትን ምክንያት በመለየት መፍትሄ እንድንፈልግ አግዞናል ብሏል።

በዚህም የወጣቶች መሰረታዊ ጥያቄዎች ተለይተው በአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ በሂደት ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስረድቷል።

ጸረ ሰላም በሆኑ ሃይሎች ግፊት ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ አካሄድ ከመከተል ይልቅ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቡ ወጣቶች መበራከታቸውን ወጣቶቹ ተናግረዋል።

ለወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀምና ስትራቴጂ፣ ሚዲያ ሞኒተሪንግ፣ በግጭት ኮምዩኒኬሽን፣ ፓለቲካዊ ኮምዩኒኬሽን፣ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።

በዚህም በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚራገቡ የሃሰት መረጃዎችን ተቀብለው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚሄዱ ወጣቶችን ቁጥር መቀነስ እንደተቻለም ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን