አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 06 October 2017

ዲላ መስከረም 26/2010 በደቡብ ክልል የእንሰት አጠውልግ በሽታን ትኩረት ሰጥቶ መከላከል ካልተቻለ ሰብሉ ከምርት ውጭ የሚሆንበት ደረጃ ሊከሰት እንደሚችል የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አሳሳበ።

ኢንስቲትዩት በተቀናጀ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ዘዴዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትላንት በዲላ ከተማ አካሂዷል፡፡

በኢኒስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አግደው በቀለ እንደገለፁት፣ በክልሉ ከደቡብ ኦሞ፣ ቤንች ማጂና ሰገን ሕዝቦች ዞኖች ከሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር ሁሉም ዞኖች እንሰት አብቃዮች ናቸው ፡፡

ሰብሉ በሚበቅልበት ሁሉም አካባቢዎች የእንሰት አጠውልግ በሽታ ወቅት ጠብቆ እየተቀሰቀሰ በሰብሉ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንን ተናግረዋል።

በእዚህም በሽታው ከማሳ ወደ ማሳ እየተስፋፋ መምጣቱንና ክስተቱ በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ሰብሉ ሙሉ ለሙሉ ከምርት ውጭ የሆኑባቸው ማሳዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል ።

ይህም የእንሰት ተክል ቀስ በቀስ ከምርት ሂደት እየወጣና የአርሶአደሩም ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረጉን  አስረድተዋል፡፡

ዶክተር አግደው እንዳሉት፣ በበሽታው መንሰኤና መከላከያ ዜዴዎች ላይ ሕብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ ባለፈ ተክሉ ምርታማ እንዲሆን እንደ ሌሎች ሰብሎች ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም።

በሽታውን በመከላከል አርሶአደሩ ከእንሰት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ከሌሎች ሰብሎች እኩል ለእንሰት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ለእዚህም በየደረጃው የሚገኝ አመራርን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትና አርሶአደሩን በማንቀሳቀስ የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል ።

በመድረኩ ላይ ስለ በእንሰት ተከል ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በሃዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የዕፅዋት በሽታ ባለሙያ ዶክተር ፍቅሬ ሀንድሮ  በሽታው በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶአደሩ ከዚህ በፊት ዘልማዳዊ በሆነ መንገድ በበሽታው የተጠቃ እንሰትን በማስወገድ የመከላከል ሥራ ሲሰራ ቢቆይም የመከላከሉ መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ባለመሆኑ በሽታው በድጋሚ ወደ መማሳው ይዛመት እንደነበር አመልክተዋል።

ማዕከሉ የደረሰበርት አዲስ የመከላከያ ዘዴ ከነባር ባህላዊ አሰራር ጋር የተጣመረ እንደሆነ በጥናቱ የጠቆሙት ዶክተር ፍቅሬ፣ በሙዝ አብቃይ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።

አርሶአደሩ ባለው የእርሻ መሳሪያ በበሽታው የተጠቃውን እንሰት ካስወገደ በኋላ በመቅበርና ያስወገደበትን መሳሪያ በኬሚካል በማጠብ አሊያም በእሳት በመለብለብ በዘላቂነት መከላከል እንደሚችል አስረድተዋል ፡፡

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው፣ በዞኑ 37 ሺህ 236 ሄክታር መሬት ላይ እንሰት እንደሚለማ ተናግረዋል ።

ተክሉ ለዞኑ ህዝብ የምግብ ዋስትናን ከመጠበቅ ባለፈ በኢኮኖሚና ባህላዊ እሴትነቱ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

በሽታው የሚዛመተበት ሁኔታ ከወቅት ወቅት እንደሚለያይ ጠቁመው፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዞኑ በ22 ሄክታር ማሳ ላይ ጥቃት ማድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"እስካሁን በበሽታው ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን አልሰራንም፤ በቀጣይ እስከ አርሶአደሩ ድረስ ንቅናቄ በመፍጠር ከሌሎች ሰብሎች ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት ሰጥተን የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እንሰራለን" ብለዋል ፡፡

የወናጎ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድሉ ታደሰ በበኩላቸው መድረኩ ከዚህ በፊት በበሽታው ምንነት፣መከላከያ መንገዶችና ቁጥጥር ላይ የነበረብንን ክፍተት እንድንመለከት አድርጎናል" ሲሉ ተናግረዋል ።

በመድረኩ በእንሰት አጠውልግ በሽታ መንስኤ፣ መከላከያ ዘዴዎችና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ መስከረም 26/2010 በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ጉለመኸዳ ወረዳ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወረዳው ነዋሪዎች ገለጹ።

የጉለመከዳ ወረዳ የሻዕቢያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ከፍቶት በነበረው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች አንዱ ነው።

በተለይ በድንበር አዋሳኝ አካባቢ በተቆረቆረችው የወረዳው ዋና ከተማ ዛላንበሳ ከተማ በደረሰው ጉዳት ነዋሪዎቿ ተፈናቅለውና ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገው ቆይተዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃ ሐዱሽ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፣ ለችግር ተዳርጎ የነበረውን የወረዳውን ህዝብ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ሥራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም በአካባቢው ከዓመታት በፊት 183 ሄክታር ብቻ የነበረው በመስኖ የሚለማ መሬት በአሁኑ ወቅት ወደ ሦስት ሺህ ሄክታር ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት።

በመስኖ ልማቱ ቀደም ሲል ይሳተፉ የነበሩ አርሶአደሮች ቁጥርም ከ300 ወደ 16 ሺህ ማደጉንና በእዚህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

አቶ አብርሃ እንዳሉት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ ከ10 ዓመታት በፊት በወረዳው 154 ኪሎ ሜትር የነበረ የአስፋልትና የጠጠር መንገድ በአሁኑ ወቅት 498 ኪሎ ሜትር ደርሷል።

ለመንገድ ግንባታው በመንግስትና በአካባቢው ተወላጆች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመው፣ የወረዳው ህዝብም ከእዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ በአማካይ ከ120 ሺህ ህዝብ ነጻ ጉልበት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።

“በተካሄዱ የመንገድ ግንባታ ሥራዎችም በወረዳው የሚገኙ 19 የገጠር ቀበሌዎች እርስ በራሳቸው እንዲተሳሰሩ ተደርጓዋል” ብለዋል።

የወረዳው ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎችም በአሁኑ ወቅት እስከ 57 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ከአስር ዓመታት በፊት በወረዳው 10 ብቻ የነበሩ ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ወቅት የዛላንበሳ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤትን ጨምሮ 22 የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ተናግረዋል።

ለተቋማቱ ግንባታም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ነው አቶ አብርሃ የገለጹት።

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ በጤና ልማት በኩል ሰሞኑን በ52 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ የተደረገው መለስተኛ ሆስፒታልን ጨምሮ 21 ጤና ተቋማት በወረዳው ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በዚህም የወረዳዋ ናዋሪዎች የጤና ተቋማትን በአቅራቢያቸው ለማግኘት ከመቻላቸው በተጨማሪ ሕክምና ፍለጋ ርቀት ይጓዙ የነበረውን እንደቀረላቸው አመልክተዋል።

ከወረዳው ተወላጆች መካከል ወይዘሮ ሀዳስ ወልደገብሪኤል እንዳሉት፣ የፌደራልና የክልሉ መንግስት በሰጡት ልዩ ትኩረት ባለፉት ዓመታት በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በአካባቢያቸው መከናወናቸውንና በእዚህም እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ተጠቅመዋል።

በወረዳው የማርታ ገጠር ገበሌ ነዋሪ ወጣት ተክለወልደጊርግስ ሀፍቱ በበኩሉ፣ በወረዳው በተገነቡ የትምህርት ተቋማት በአካባቢው የመማር ዕድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።

የተገነቡ የጤና ተቋማትም የህብረተሰቡን ጤና ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸውም አመልክቷል።

በወረዳው የፋፂ ከተማ ነዋሪና የ80 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ አቶ ቀይማት ሞኒክ በበኩላቸው አንዳሉት፣ ቀደም ሲል የመሰረተ ልማት አውታሮች ባለመኖራቸው ህዝቡ የትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ቀደም ሲል በአካባቢው ሆስፒታልና የመኪና መንገድ  ባለመኖሩ ባለመኖሩ ሕመምተኛን ተሸክመው ወደአዲግራት ከተማ ሲወስዱ በመንገድ ላይ  የሚሞቱበት አጋጣሚ እንደነበር አቶ ቀይማት  አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ይህ ሁሉ ተሻሽሎ በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ መስከረም 26/2010 በወንጀል የይግባኝ ጉዳዮች ላይ ያለውን የአፈፃፀም ችግር ለማስተካከል በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነ የምዘና ስርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ  የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመለከተ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የተሳተፉበት 15ኛው የጋራ የምክክር መድረክ በአክሱም ከተማ  እየተካሄደ ነው፡፡

በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅና ማፅደቅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ  በወንጀል  የይግባኝ ጉዳዮች በፌደራልና በክልሎች ያለውን የአፈፃፀም ችግር የዳሰሰ ጥናት ለጋራ መድረኩ አቅርበዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ለተሳታፊዎቹ  እንደገለፁት በወንጀል የይግባኝ ጉዳዮች የፌደራልም ይሁን የክልሎች  ጠቅላይ  አቃቤ ህጎች የማሸነፍ ምጣኔያቸው  ዝቅተኛ ነው፡፡

ይህም የወንጀል ጉዳዮች ተገቢውን ውሳኔ እንዳያገኙ፣  የፍትህ ስርዓቱና ህብረተሰቡ በፍትህ ላይ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ችግር ዋና ምክንያት ደግሞ አቃቤ ህጎችና ዳኞች  በይግባኝ ጉዳዮች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ  መሆኑን ዳይሬክተሩ  ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት አመላክተዋል፡፡

አቃቤ ህጎች  ለይግባኝ ጉዳዮች በቂ ክትትልና ብቃት ያላቸው ክርክሮችን ስለማያደርጉ፣ክስ የመሰረተውና  የወንጀሉን ይግባኝ የሚከታተል አቃቤ ህጎች መለዋወጣቸው  ለሽንፈቱ ሌላው ምክንያት ነው፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ የተካሄደው ባለፈው የበጀት ዓመት በደቡብ፣ በትግራይ ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የፍትህ ስርዓቱ አገር አቀፍ በመሆኑ ችግሩን ለማስተካከል የሚበጀውን ዳይሬክተሩ በጥናታዊ ፅሁፋቸው አመላክተዋል፡፡

ይህም "በፌደራልና በክልሎች አሁን ያለውን የአለካክ ስርዓት ወጥ በማድረግ አቃቤ ህግና ተቋሙ፣ሂደቱና ውጤቱ የሚመዘንበት አገር አቀፍ የምዘና ስርአት መዘርጋት አለበት "ነው ያሉት፡፡

የይግባኝ ጉዳዮች ከስር ፍርድ ቤት የተፈፀመው የህግ ፍሬ ስህተት የሚታረምበትና ለፍትህ ስርዓቱ የሚመራበት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

አቃቤ ህጎችና ዳኞች በይግባኝ ጉዳዮች ያላቸውን ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረግ አንዱ የመፍትሄ ሀሳብ ሆኖም ቀርቧል፡፡

ይግባኝ የሚያስብሉና የማያስብሉ ጉዳዮች በአንድ አቃቤ ህግ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ከአንድ በላይ የህግ ባለሙያዎች ውሳኔ ቢሰጥ የተሻለ አፈፃፀም ሊያመጣ ይችላልም ተብሏል፡፡

"በፌደራልና በክልሎች የተለያየ አደረጃጀት ቢኖርም በፍትህ ስርዓት ግን አንድና ያው ነው ያሉት " ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባየ ናቸው፡፡

ምክንያቱም የፍትህ ዋናው ዓላማ  ለዜጎች  ተደራሽ ማድረግና  የህግ ሉአላዊነት ማረጋገጥ  በመሆኑ በክልሎችና በፌዴራል ልዩነትና የተዘበራረቀ አፈፃፀም ሊኖር እንደማይገባ ነው ያመለከቱት፡፡

"በፌደራልና በክልሎች ያለውን የይግባኝ የወንጀል ጉዳዮች የማሸነፍ ምጣኔ ዝቅተኛ  የመሆን ችግር ለማስተካከል ወጥ የሆነ የምዝና ስርዓት ሊኖረን ይገባል "ብለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ፡፡

የይግባኝ ወንጀል ጉዳዮች የሚመዘንበት የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ በማዳበር በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ችግርን ለመፍታት የተጠያቂነትና ወጥ የሆነ የምዘና ስርዓት ለመዘርጋት በቀረበው ምክረ ሀሳብ በክልሎች ይሁንታ አግኝቶ ስርዓት ሆኖ እንዲዘረጋ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቴ ተስፋዬ  በበኩላቸው  የወንጀል ጉዳዮች ማስተዳደር መሰረታዊ ችግር የሚታይበት በመሆኑ ጥናቱ መፍትሄ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ በሌሎች የህግ ጉዳዮች ያለውን አፈፃፀምና የወጥነት ችግር ለቀጣይ ቢካተትበት  የተሻለ ሊሆን  ይችላል " ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ልኡል ካህሳይ ናቸው፡፡

የምክክር መድረኩ ከትናንት ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡

 

Published in ማህበራዊ

መቱ መስከረም 26/2010 በኢሉአባቦር ዞን ከጥልቅ ተሀድሶው ወዲህ በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም በመሰረተ ልማት በኩል አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውን በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ትናንት በመቱ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በኮንፍራንሱ ላይ የተገኙ አንዳንድ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ከጥልቅ ተሀድሶው ወዲህ የኪራይ ሰብሳቢነትና  የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በመሠረተ ልማት አቅርቦት በኩል ያሉ ችግሮች ግን እስካሁን አልተፈቱም፡፡

ከዳሪሙ ወረዳ የተሳተፉት አቶ ሙዘሚል አብዱረህማን እንዳሉት ከጥልቅ ተሀድሶው በፊት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት የተጓተቱና ትኩረት የተነፈጋቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች እስካሁን አልተፈቱም፡፡

በተለይ "ከመቱ እስከ ዳሪሙ ያለው መንገድ በመበላሸቱ የተነሳ ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ አመቺ አይደለም" ያሉት አቶ አብዱራህማን አፋጣኝ ጥገና እንዲደረግለት ጠይቀዋል፡፡

ወረዳው ገበያ ተኮር የሆኑ የግብርና ሰብሎች የሚመረቱበት ቢሆንም በመንገዱ መበላሸት ምክንያት ተሽከርካሪ በብዛት ስለማይገባ ምርት ለገበያ በማቅረብ ረገድ ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡

ከዘጠኝ አመታት በፊት ለመገንባት የታቀደው የኢሉአባቦር ስታዲየም እስካሁን ባለመጀመሩ የአካባቢው የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲዳከም እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመቱ ከተማ ነዋሪ አቶ ጫንያለው ሌሊሶ ናቸው፡፡

ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ ከመጣው የከተማው የንግድና እንቨስትመንት እንቅስቃሴ አንጻር የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ገልፀዋል፡፡

የአየር የትራስፖርት አገልግሎት ለማግኘትም 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ጋምቤላ እንደሚጓዙም ተናግረዋል።

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋት የኦሮሚያ ክልል እና ፌዴራል መንግስት እያደረጉ ያለውን ጥረት እንደሚያግዙም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል፡፡

በተወሰኑ ሀይሎች ድብቅ ፍላጓት  የሁለቱ ክልል ህዝቦች ወዳጅነትና አብሮ የመኖር ባህል አንደማይሸረሸርም ተሳታፊዎቹ  ገልጸዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው ከጥልቅ ተሀድሶው ወዲህ በመልካም አስተዳደርና ልዩ ልዩ ችግሮች የተጓተቱ የልማት ስራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ።

በመቱ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም እስካሁን ከህብረተሰቡ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸው የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ግንባታውን ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአካባቢው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለመጀመርም በአሁኑ ወቅት በሚመለከተው አካል የጥናት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሰማን አባጎጃም በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በማያቋርጥ የተሀድሶ እንቅስቃሴ የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጥልቅ ተሀድሶው በሁሉም ደረጃዎች በህዝቡ የተመረጡ አመራሮች ከማስቀመጥ ጀምሮ ሁሉንም አሰራሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን በመከታተል የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋትም የፌዴራልና የክልሉ መንግስት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች በመጨረሻም በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋምና የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ባወጡት ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡

በኮንፍራንሱ ላይ ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ሶዶ መስከረም 26/2010 በወላይታ ዞን  በመሰረተ ልማት ዘርፍ የተዘመገበውን ስኬት በማስቀጠል በጥራትም ላይ መድገም እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ባለፉት 25 ዓመታት በዞኑ በተከናወኑት የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ይሁን እንጂ  በየዘርፉ ጥራት የተጓደላቸዉ ስራዎች መበራከት መንግስትንም ሆነ ህብረተሰብን ለብክነት እየዳረጉ በመሆኑ የልማቱ ስኬት በጥራትም ላይ ለመድገም ትኩረት መሰጠት አለበትም፡፡

መምህርት ትዕግስት ማርቆስ በወላይታ  የዱጉና ፋንጎ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በሚኖሩበት አካባቢ የመንገድ ችግር በመኖሩ ወደ ሶዶ ለመጓዝ ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የታመመ ሰው ወደ ሆስፒታል ለማድረስና አስቸኳይ ጉዳይ ሲገጥማቸው በእግር ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ወረዳውን ከዞን ማዕከል የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ በመገንባቱ ችግሩ መወገዱን ገልጸዋል፡፡

ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታዎችም በስፋት መከናወናቸውን ጠቁመው በአንዳንድ አካባቢዎች ግን የጥራት መጓደል እንደሚስተዋልና በቀላሉ በጎርፍ እየተበላሸ  መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ የአሮጌ አራዳ ቀበሌ ነዋሪው  የሆኑት አቶ አባተ አያኖ በበኩላቸው " ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በከተማችን የታየው ለውጥ አስገራሚ ነው "ብለዋል፡፡

የከተማዋ እድገት በጣም ፈጣን ከመሆኑ ባለፈ በጭቃ ይቸገሩበት የነበረ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በአስፋልትና በድንጋይ ንጣፍ ተሰርቶ ማየት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም ለውጥ የመጣው ደኢህዴን/ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች የስራ ዕድል አማራጮች  እንዲስፋፉ ማስቻሉን የጠቆሙት አቶ አባተ ልማቱ ሲሰራ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው  አመልክተዋል፡፡

የዞኑ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ ባልደረባ  አቶ ብርሃኑ አሻ እንደገለጹት በአካባቢው  ባለፉት ዓመታት  በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ ክረምት ከበጋ የሚያገለግል ጠጠርና አስፓልትን ጨምሮ  ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተሰርቷል፡፡

" ከምንም ተነስተን እዚህ ደረጃ ለደረስንበት አንጸባራቂ ድል የመሪው ድርጅት ህዝባዊነትና ትክክለኛነት እንዲሁም የማስተባበር አቅምን ያሳያል"ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደዞን አንድ ሰው ተደራሽ መንገድ ለማግኘት በእግር ጉዞ በአማካይ እስከ እስከ አራት ቀናት ይፈጅ የነበር አሁን ሁለት ሰዓት መሆኑን ገልጸው ይህንን ወደ አንድ ሰዓት ለማድረስም  እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

" ይሁን እንጂ በተሰሩ መንገዶችም ሆነ በሌሎች መሰረተ ልማቶች ዙሪያ ነዋሪው የሚያነሳው የጥራት ጉድለት ችግር እውነት ነው" ያሉት አቶ ብርሃኑ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የወላይታ ዞን ደኢህዴን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘብዴዎስ ኤካ በበኩላቸው ድርጅቱ ዞኑን ማስተዳደር ከጀመረበት አንስቶ እየተመዘገቡ የመጡ ለውጦች ህዝብን ያሳተፉና ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ፣የስልክና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ተደራሽነቱ መረጋገጡን የተናገሩት አቶ ዘብዴዎስ  በቀጣይ ጉድለቶችን በማስተካካል የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

መስከረም 26/1/2010 የግብርና እድገት ፕሮግራም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሳካ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አስታወቁ።

የግብርና እድገት ፕሮግራም አፈጻጸምና የአሰራር አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ  የተገኙት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ እንዳስታወቁት ፕሮግራሙ ህብረተሰቡን በማስተባበርና በማንቀሳቀስ በየደረጃው የተቀናጀና የተደራጀ የልማት ስራ ለማከናወን አስችሏል።

ይህም ግብርናው ለኢኮኖሚው ሽግግርና ለህዳሴ ጉዞ መፋጠን የሚያስችሉ ምቹ መደላድሎች እንዲፈጠር የላቀ እገዛ ማድረጉን አመልክተዋል።

ፕሮግራሙ በ2003 ዓ.ም በተመረጡ 84 ኩታገጠም ወረዳዎች የተጀመረ ሲሆን እስከ 2007 ባለው ጊዜ በ96 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ማሳደግና የገበያ ትሰስርና ተደራሽነትን በማሻሻል እንዲሁም ምርቱ ገበያ ተኮር እንዲሆን ማድረግ ነው።

በዚሁ መሠረት በወረዳዎቹ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል የማስፈጸም አቅም ግንባታና ስልጠና፣ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን በሰርቶ ማሳያ መገልገያዎችና ቁሳቁሶች ማደራጀት ይጠቀሳል።

የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተቋማትን የማጠናከር ስራ የተከናወነ ሲሆን የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል  በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች የሰው ሰራሽ አባለዘር ማምረቻ መገንባቱን ጠቁመዋል።

የተሻሻሉ የኮርማና የጊደር ግዥና አቅርቦት መፈጸሙን ገልጸው የአነስተኛ መስኖ፣ 161 የአንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል፣ መጋቢ መንገድ፣ አነስተኛ ድልድይና የገጠር መሰረተ ልማት አውታሮችን በመገንባት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ጥረት መደረጉን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ 

በዚህም ለግብርና ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግር ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ለውጥ የታየበትና ስኬቶችን ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን አስረድተዋል።

በ2008 ዓ.ም የተጀመረው ሁለተኛው የፕሮግራሙ ምዕራፍ ደግሞ ተደራሽነቱን በማስፋት በሰባት ክልሎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ 157 ወረዳዎች በ4 ሺህ 69 ቀበሌዎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኘሮግራሙም በእነዚሁ ቀበሌዎች የሚገኙ 927 ሺህ ሴቶችን ጨምሮ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ  እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የምክክር መድረኩም በፕሮግራሙ ትግበራ ወቅት ያሉትን ክፍተቶች በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የታለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የግብርና እድገት ፕሮግራምና የገጠር መሰረተ ልማት ባለሙያ አቶ ያለው በለጠ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያው ምዕራፍ ስኬቶች እንዳመለከቱት ከ2 ሺህ የሚበልጡ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያዎች በመሳሪያዎችና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ተደርጓል።

አንድ ሺ 409 ጣቢያዎች ደግሞ ጥገናና እድሳት የተደረገላቸው ሲሆን ለ305 ሺህ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ደግሞ የኤክስቴንሽን ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም 41 ሺህ 697 ሄክታር  መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችሉ የ6 ሺህ 217 የመስኖ አውታሮች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን 2 ሺህ 841 የመስኖ ውኃ መሳቢያ ፓምፖች ተሰራጭተዋል፡፡

ኘሮግራሙ ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎችም አማካኝ የሰብል ምርታማነት በሄክታር ከ24 ኩንታል ወደ 31 ኩንታል ማደጉን አመልክተዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ፕሮግራሙ ከሚካሄድባቸው ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቱ መስከረም 26/2010 በኢሉአባቦር ዞን ከህጋዊ የንግድ ሥርአቱ ውጪ ሲሰሩ በነበሩ 667 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ፊዳ ዲሪባ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ወራት በተካሄደው የቁጥጥርና ክትትል ሥራ እርምጃው የተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት የንግድ ስርአቱ ከሚፈቅደው ውጪ ሲሰሩ በመገኘታቸው ነው::

የሸቀጦች ዋጋ ሳይለጥፉ መሸጥ፣ ደረጃውን ያልጠበቀና ፍትሀዊ ያልሆነ ሚዛን መጠቀም፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግና የመሳሰሉት ክፍተቶች የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው ።

ከንግድ ተቋማቱ መካከል ዘጠኙ በተደጋጋሚ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ከጥፋታቸው ባለመመለሳቸው በህግ እንዲጠየቁ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በንግድ ተቋማቱ ላይ በተካሄደ የቁጥጥር ሥራ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ ከተገኙ 373 ተቋማት መካከል 102ቱ ፈቃድ በማውጣት ወደ ህጋዊ መስመሩ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል::

የተቀሩት ተቋማት ዳግም የንግድ ስርአቱን የሚጻረር ተግባር እንዳይፈጽሙ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ነው አቶ ፊዳ የገለጹት::

በዞኑ 13ቱም ወረዳዎች የሸማቹን ማህበረሰብ መብት ለማስከበርና ፍትሀዊ የንግድ ስርአቱን ለማጠናከር በየሁለት ወሩ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም አቶ ፊዳ አብራርተዋል::

በመቱ ከተማ በቤት እቃዎች ንግድ የተሰማሩት አቶ አክመል ሰይድ በሰጡት አስተያየት በንግድ ስርአቱ ዙሪያ በተሰጣቸው ትምህርት ፈቃድ አውጥተው የንግድ ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ ይገኛሉ::

"የዋጋ ዝርዝር በመለጠፍና  ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሳላደርግ ለመስራት የተስማማሁትን ተግባራዊ በማድረጌ ከስጋት ነፃ አድርጎኛል "  ብለዋል::

በከተማው በእህል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ያሲን ሰይድ በበኩላቸው የንግድ ስርአቱን አክብረው መስራታቸው ፍትሀዊ የንግድ ውድድሩን ከማጠናከር ባለፈ ስራቸውን እያቀላጠፈላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

"የዋጋ ዝርዝር በመለጠፍ ሸማቹ የሚፈልገውን ምርት በቀላሉ ለይቶ እንዲሸምት እያደረገ ነው" ሲሉም አመልክተዋል።

በኢሉአባቦር ዞን 9ሺህ 838 የንግድ ተቋማት በንግድ ሥራው ተሰማርተው እንደሚገኙ  ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ::

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 26/2010 "የኢትዮጲያ ልዑካን  ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ" በሚል ርዕስ  የተዘጋጀው የብላቴን ጌታ  ህሩይ ወልደ ስላሴ  መጽሐፍ  በኢትዮጵያ ለዘመናዊ አስተሳሰብ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ስለመጽሐፉ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ገለፁ።

መጽሐፉ የወቅቱ ሹማምንቶች በደጃዝማች ካሳ ኃይሉ መሪነት ወደ እንግሊዝ፣ፈረንሳይና ጣልያን እንዲሁም ጅቡቲና ግብጽ ያደረጉትን ጉዞ ይዳስሳል።

የልዑካኑ አባል የነበሩት ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ መጽሐፉን በ1903 ዓ.ም ቢያዘጋጁትም፤ ከመቶ ዓመታት በላይ ሳይታተም ቆይቶ ባሳለፍነው 2009 ዓ.ም በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አሰናጅነት የኢትዮጲያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ  ለህትመት አብቅቶታል።

አካዳሚው በትናንትናው እለት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ መጽሐፉ ለአገሪቱ ዘመናዊ አስተሳሰብና ርእዮተ ዓለም መጎልበት የነበረውን ፋይዳ የሚዳስሱ ሶስት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

ጽሁፎቹን ያቀረቡ ምሁራን እንዳሉት፤ ደራሲው በመጽሐፋቸው ከአውሮፓና መካከለኛው  ምሥራቅ አገራት ያገኙትን ዘመናዊ አስተሳሰብ እውቀትና ልምድ ያስቀመጡበት እንዲሁም  በአገር ውስጥ  ያለውን ብልሹ አሰራር የሞገቱበት ነው።

የመነሻ ጽሁፍ ካቀረቡ ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር መሰለ ተሬቻ  መጽሐፉ ዘመናዊነት ከባሕል፣ከቋንቋ፣ከእምነትና ከአኗኗር ጋር ያለውን ተዛምዶ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

መጽሐፉ የአውሮፓውያንን  ዘመናዊ የሕክምና እና የዳኝነት ስርዓት በአገር ውስጥ እንዲተገበር መሰረት እንደጣለም ተናግረዋል።

ደራሲው በወቅቱ ምዕራባዊያን ለአፍሪካ ህዝቦች ያላቸውን ንቀት በድፍረት እንደተቹና አፍሪካውያን ከአፋኝ ስርዓት ነፃ ለመውጣት የተለያዩ ስልቶችን መጠቀም እንዳለባቸው መምከራቸውን ዶክተር መሰለ ገልጸዋል።

"ደራሲው ምእራባዊያን አፍሪካዊያንን ለመግዛት የሚጠቀሙበትን ድብቅ ሴራ ለአገሬው ሕዝብ ጽፈውላቸዋል" ያሉት ደግሞ ሌላኛው ጥናት አቅራቢ አቶ ፋሲል መርዓዊ ናቸው።

አቶ ፋሲል ልዑካን ቡድኑ ጣሊያንን በጎበኘበት ወቅት የስራ ክፍፍል አገሪቱን ምን ያህል እንዳሳደጋት ደራሲው እንደተገነዘበ ጠቁመው፤ "ይህ ልምድም በመጽሃፉ ተቀምሮ ተቀምጧል" ብለዋል።

ዶክተር ዮናስ አሽኔ በበኩላቸው መጽሐፉ አውሮፓውያን የደረሱበትን የእድገት ደረጃ  ኢትዮጵያ በቅርብ እንደምትደርስበት ተስፋና ወኔ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ደራሲው አውሮፓውያን ከእድገታቸው ጎን ለጎን ያለባቸውን እንከን በመጽሃፋቸው በግልጽ እንዳሰፈሩም ተናግረዋል።

መጽሃፉ  አውሮፓውያን ከድህነት የወጡበትን ስልት፣ የአገዛዝ ስርዓታቸውንና የዲፕሎማሲ ክህሎታቸውን አፍሪካዊያን እንዲጠቀሙበት ምክር እንደሚሰጥም ዶክተር ዮናስ ገልጸዋል ።

"በእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ ለውጥን የመፈለግ ተግባርና ራስን ነጻ የማውጣት አስተሳሰቦች  እንዳሉ ያሳየ ድንቅ ድርሰት" ሲሉም መጽሃፉን አሞካሽተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 26/2010 ታዋቂው የዓለማችን የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ተጫዋች አሜሪካዊው ጄስ ማርት ለኢትዮጵዊያን የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾችና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ  ቀይ መስቀል ማህበር የጋራ ትብብር የተዘጋጀው ይህ ስልጠና ባለፈው ሳምንት መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው በአዲስ አበባ እየተሰጠ ያለው።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታሪኩ እንዳለው እንደተናገሩት በየክልሉ በዊልቸር ቅርጫት ኳስ በቀጣይ በዓለም የኦሎምፒክ ስፖርት የመሳተፍ ግብ አስቀምጠው እየሰሩ ነው።

አሁን በአለም ታዋቂ በሆነ ባለሙያ ስልጠና መሰጠቱም ለግባቸው ስኬት እንደሚረዳቸው ነው የገለጹት።

በዚህም ለግቡ መሳካት አስፈለጊ ናቸው የተባሉ  የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ አካል ጉዳተኞች የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ሰልጣኞች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች የስልጠናው ተካፍይ ሆነዋል።

በስልጠናው እየተካፈሉ የሚገኙ ሰልጣኞችም በዊልቸር ፈጣን የሆነ አጨዋወት፣ ትክክለኛ አቀባበል፣ ኳስ  ማንጠርና በዊልቸር እንዴት መጋጫት እንደሚቻል ጥሩ ግንዛቤ ፈጥሮልናል ብለዋል።

ይህን ስልጠና ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቅርጯት ኳስ ፌደሬሽንና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስልጠናውን ከመስጠት ባለፈ ክለብ እንዲቋቋም ቢደረግ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑም ተናገረዋል።

በንድፈ ሀሳብና በተግባር እየተሰጠ ያለው ይህ  ስልጠና  ከነገ በስቲያ ይጠናቀቃል።

በስልጠናው እየተካፈሉ ያሉት 90 ሰልጣኞች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 30ዎቹ  የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የዩኒቨርሲት መምህራን፣ ዳኞችና አሰልጣኞች ናቸው።

በ19 ዓመቱ በድንገተኛ የመኪና የዲስክ አጥንት ጉዳት የደረሰበት አሜራካዊ ጀስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አገራት እየዞረ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስልጠና በመስጠት ይታወቃል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መስከረም26/2010 በዓለም ደረጃ የኒውክለር መሣሪያዎች አስወጋጅ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋማት ጥምረት (አይካን) የ2017ቱ የሠላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነ።

ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት በስዊዲናዊው አልፍሬድ ኖቤል የተሰየመው የኖቤል ሽልማት ለዓለም በጎ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ ነው።

የኖቤል ሠላም ሽልማት በከፍተኛ ደረጃ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት የሚስብ ነው።

የኖቤል ኮሚቴ በዛሬው ዕለት የኖቤል የሠላም ተሸላሚ በኖርዌይ ርዕሰ መዲና ኦስሎ ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ ሽልማቱን ያሸነፈው ከሶስት ወር በፊት አገራት ኒውክለር መሣሪያን እንዳይጠቀሙ የሚያስችለው ዓለም አቀፍ ስምምነት አገራት ተቀብለው እንዲፈርሙ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት መሆኑ ተገልጿል።

የኖቤል ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ሚስ ቤሪት ሪስ አንደርሰን እንደገለጹት፤ የሲቪክ ተቋሙ አገራት ኒውክለር መሣሪያን እንዳይጠቀሙ የሚያስችለው  ዓለም አቀፍ ስምምነት በ122 አገራት እንዲፈረም ያደረገው ቅስቀሳ ሽልማቱን እንዲያገኝ አስችሎታል።

ዓለም ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ በኒውክለር መሣሪያ ጉዳይ ስጋት ውስጥ እንደገባች ገልጸው፤ የሰሜን ኮሪያን የኒውክለር ፕሮግራም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኒውክለር መሣሪያ እንዲወገድ በሚደረገውም ጥረት ሲቪክ ተቋሙ ያደረገው ጥረት የሚያበረታታ ነው ተብሏል በሽልማቱ ወቅት።

ተቋሙ የሚሸለመውን 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር፣ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚቀበል የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

በዓለም ደረጃ የኒውክለር መሣሪያዎች አስወጋጅ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋማት ጥምረት (አይካን) እ.ኤ.አ በ2007 የተቋቋመ ሲሆን፤ መቀመጫውን በስዊዘርላንድ መዲናዋ ጄኔቫ አድርጓል።

አይካን ከሌሎች የሲቪክ ማኅበራት ጋርም ኒውክለር መሣሪያዎች እንዲወገድ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርግ ተቋም ነው። 

በሌላ በኩል በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ በትውልድ ጃፓናዊ በዜግነት እንግላዛዊ ደራሲ ካዙኦ ኢሺጉሮ "ሪሜንስ ኦፍ ዘ ደይ" እና "ኔቨር ሌት ሚ ጎ" በሚል ርዕስ የጻፏቸው መጽሐፎች የሰውን ስሜት የመቀስቀስ ሃይል ያላቸው ድርሰቶች በሚል ተሸላሚ ሆነዋል።

ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ሥነ-ጽሑፍ፣ፊዚክስ፣ሕክምና፣ኢኮኖሚክስና ሠላም፤ ሽልማቱ የሚሰጥባቸው ዘርፎች ናቸው።

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን