አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 05 October 2017

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች ለተነሳው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመሩ ህዝባዊ ጉባዔዎች እንደሚካሄዱ መንግሥት አስታወቀ።

በሁለቱ ክልሎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪነት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራልና የሁለቱ ክልሎች አመራር አባላትና የፀጥታ አካላት የተካፈሉበት የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል።

ውይይቱን የተከታተሉት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ ግጭቱ ያለበትን ደረጃ የሚያመለክት ሪፖርት በውይይት መድረኩ ላይ ቀርቧል። ለጉዳዩ ፈጣንና ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚያስችል አቅጣጫም ተቀምጧል።

በዚሁ መሰረት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመሩ የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች የሚሳተፉባቸው ህዝባዊ ጉባዔዎች እንዲደረጉ አቅጣጫ መቀመጡንም ነው የገለጹት።

የሁለቱም ክልሎች አመራር አባላት ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ አካላትን በማጋለጥ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ግጭቱን የሚያባብስና ህዝብን የሚያጋጭ መረጃ በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ሆነ ግለሰብ እንዳይተላለፍ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀው፤ መመሪያውን ተላልፈው ግጭቱን የብሔር ግጭት አስመስለው የሚያናፍሱ የኮምዩኒኬሽን አካላትና መገናኛ ብዙሃን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመልክተዋል።

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የተቀራረቡና በፍቅር የኖሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ "ግጭቱ የህዝቦችንም ሆነ የተገነባውን ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማይወክል መሆኑ" በውይይቱ መነሳቱንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

በግጭቶቹ አካባቢዎች ኬላዎች መኖራቸውንና ተሽከርካሪዎች በመቆማቸው የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ችግር መፈጠሩን አስታውሰው፤ ከአሁን በኋላ የየትኛውም ክልል የፍትሕም ሆነ የጸጥታ አካል ኬላ አቁሞ እንዳይፈትሽ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

ይህን ሥራ የመቆጣጠሩ ተግባር የፌደራል የፀጥታ አካላት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም ጊዚያዊና ዘላቂ አቅጣጫ መቀመጡን ዶክተር ነገሪ ገልጸው፤ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስራት ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

በግጭቱ የቆሰሉ አካላት አስፈላጊው ህክምና እንደተደረገላቸውና እንደሚደረግላቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎትና ከጤና ጋር የተያያዙ ድጋፎች በክልሎችና በፌደራል መንግስት እንደሚቀርብላቸው አብራርተዋል።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ስፍራ እንዲመለሱ፣ የተዘረፈ ንብረታቸው እንዲመለስ ካልተመለሰም ካሳ እንዲከፈላቸው እንደሚደረግ አብራርተዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም እና አስፈላጊውን ከለላ የመስጠት ኃላፊነቱም ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ክልሎች እንዲሆን ተደርጓል፤ አመራር አባላት አቅጣጫውን በተግባር ለመፈጸም ተስማምተው ቃል ገብተዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የሁለቱ ብሔር ተወላጅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ለደህንነታቸው ስጋት እንዳደረባቸው ቅሬታ ማሰማታቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን የሁለቱ ክልሎች አመራር አባላት ከዩኒቨርሲቲዎቹ አመራር አባላት ጋር በመነጋገርና ተማሪዎችን በቅርበት በማነጋገር "ተማሪዎች እንደማንኛውም ዜጋ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና ለደህንነታቸው ስጋት እንደማይገባቸው ግንዛቤ ሊወሰዱ ይገባል" ብለዋል።

በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር ትምህርት ሚኒስቴር የጀመረው ስራ መኖሩን ጠቁመው ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ወደ ትምህርት ገበታቸው መሄድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 የሴቶች ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢህአዴግ የሴቶች ሊግ ገለጸ።

የሊጉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸም ለመገምገምና የ2010 ዓ.ም እቅድ ዙሪያ የሚመክሩበት የሦስት ቀናት ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ጀምሯል።

የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ ከጥልቅ ተሃድሶ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ሴቶች የሚፈለገውን ያህል ውሳኔ ሰጪና የፖሊቲካዊ ኢኮኖሚ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ቆይተዋል።

ሆኖም ከድርጅቱ ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ መጠነኛ ለውጦች እየተሰትዋሉና አዳዲስ ሴት አመራር አባላት እየታዩ መምጣታቸውን አመልክተው፤ በዚህ በኩል ብዙ መስራት የሚጠይቁ ሁኔታዎች እንዳሉም ነው የተናገሩት።

ከሥራ አስፈጻሚ አባላቱ መካከል ወይዘሮ ወርቀዘቦ ማሞ እንደገለፁት በከተማም ሆነ በገጸር በተለያዩ አደረጃጀቶች  የተሰሩ ስራዎች የተሻለ ውጤት አምጥተዋል፡፡

በቀጣይም የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በበኩላቸው ውጤቱ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በግልጽ የሚታዩ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሊጉ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት የድርጅቱ ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ በሴቶች ላይ ጥሩ መነቃቃት ፈጥሯል፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውም ጨምሯል።

በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በውሳኔ ሰጪነት የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥርም መጨመሩን ገልጸዋል፡፡

የሴቶችን መብት ለማስከበርና ከጥቃት ለመጠበቅ አሁንም የበለጠ መትጋት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ የሴቶቹ በራስ የመተማመን ማነስና በህብረተሰቡ ውሰጥ ያለው የአመለካከት ችግር ሴቶቹን የተሻለ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነውም ብለዋል።

ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም መልካቸውን እያቀያየሩ መምጣታቸው የሴቶች በራስ መተማመንና ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሊጉ በ2010 በጀት ዓመት እነዚህን ችግሮች ለማቃለልና የነበሩትን ጠንካራ ጎኖች ለማጎልበት እንደሚሰራ ተነግሯል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴውን የሚደግፍ 'ኢትዮጵያን ኤዱኬሽን ኔትወርክ'' የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

 የትምህርት፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቱ ያካተታቸው አበይት ተግባራት ናቸው።   

 ፕሮጀክቱን የአዲስ አበባ፣ ባህርዳርና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ደግሞ የኔዘርላንዱ አይ.ቲ .ሲ ዩኒቨርስቲ የቀረጹት ሲሆን፤ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2017 እስከ 2020 ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚተገበር ነው።

 ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከደች ኦርጋናይዜሽን ፎር ኢንተርናይላይዜሽን ኢን ኤዱኬሽን እና ከኔዘርላዱ አይ ቲ ሲ ዩኒቨርስቲ የተዋጣ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተመድቧል።  

 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ገድፍ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ የስነ ምድር መረጃን በዘመናዊ መንገድ በማሰባሰብ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴን መደገፍ ነው።

 ዩኒቨርስቲዎች በመስኩ ያላቸውን አቅም በዘላቂነት ለመገንባትና በአገሪቷ የሚከናወነውን የተፋሰስ ልማት ስራ እንዲደግፉ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም አብራርተዋል።

 በስነ ምድር መረጃ ዙሪያ ዘጠኝ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በትምህርት እድል ወደ ኔዘርላንድ ሄደው በመስኩ ያለውን ቴክኖሎጂና  እውቀት እንዲቀስሙ እንደሚደረግ ተናግረዋል።  

 በዘርፉ ያለው ስርዓተ ትምህርት ያሉበትን ክፍተቶች በመለየት ለመከለስና ስራ ላይ ለማዋል "በፕሮጀክቱ አማካኝነት እንቅስቃሴ ይደረጋል" ነው ያሉት። 

 በዚሁ መሰረት በዩኒቨርስቲዎች ተገምግሞ የተስተካከለው የስነ-ምድር ስርዓተ ትምህርት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲተገብር ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።   

 አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት፤ በፕሮጀክቱ መሰረት ከአዲስ አበባ፣ ባህዳርና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ተማሪዎች በታችኛው ተከዜ፣ ጣናና በሻሌ ተፋሰሶች የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የስነ - ምድር ጥናትና ምርምር ሥራዎች ይሰራሉ። 

 የምርምር ውጤቱም በመጽሀፍ መልክ ተዘጋጅቶ  ለግብርና ስራው እንዲውል "ለሚመለከተው አካል ይሰጣል" ብለዋል። 

 እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ ለግብርና እንቅስቃሴው ግብዓት የሚሆኑ የስነ ምድር መረጃዎችን ለመተንተን በአዲስ አበባ፣ ባህዳርና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች ላብራቶሪዎችና በዘርፉ የርቀት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችሉ የኢዲዮቪዥዋል ማዕከላት ይቋቋማሉ።   

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 የመንግስት ተቋማት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ በጀት አጠቃቀም መመሪያ ሊያዘጋጅ መሆኑን ብሔራዊ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ጽህፈት ቤቱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ በአዲስ አበባ የምክክር መድረኩን አካሂዷል፡፡

የመንግስት ተቋማት  ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየዓመቱ በጀት እንደሚመደብላቸው ይታወቃል።

የተቋማት በጀት አጠቃቀም ከተቋም ተቋም መለያየትና የቫይረሱ የስርጭት መጠን አንደገና ማገርሸቱ  ለበጀት አጠቃቀም መመሪያው መዘጋጀት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

በፅህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበር ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ እንደገለፁት የበሽታው ስርጭት በድጋሚ በማንሰራራት ላይ ሲሆን ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የመንግስት ተቋማት በየዘርፋቸው ተገቢውን የመከላከል ስራ አለመስራታቸው ነው፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ተቋማቱ የበጀታቸውን 2 በመቶ እንዲጠቀሙ መንግስት የፈቀደ ቢሆንም ገንዘቡን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መመሪያው በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ክፍሌ መመሪያው ተቋማቱ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በትክክል መወጣታቸውን የሚቆጣጠርና ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው በሁሉም የአመራር እርከኖች ለሚገኙ አካላት፣ሲቪክ ማህበረሰብ፣የእምነት ተቋማትንና መገናኛ ብዙሃን ስለቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢነት ማሳየት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የበሽታውን የተጋላጭነት መጠን አሁን ካለበት 0.03 በመቶ ወደ 0.01 በመቶ ለመቀነስ እቅድ የተያዘ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የስርጭት መጠኑ 1.18 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 ኢትዮጵያ "የአየር ንብረት ለውጥ አስቸኳይና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት" የሚል አቋም እንዳላት የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ እ.ኤ.አ ከህዳር 2016 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ለ47 ታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ሊቀመንበር እንድትሆን በሞሮኮ መዲና ማራካሽ ላይ መመረጧ ይታወሳል።

በዚህም የ47 ታዳጊ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች በመጪው ህዳር  ጀርመን ለሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት 23ኛው የአየር ንብርት ለውጥ ኮንፍረንስ ቅድመ ዝግጅት ላይ በአዲስ አበባ መወያየት ጀምረዋል።

አፍሪካን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ለዓለም የአየር ንብረት መዛባት ያላቸው ድርሻ ከ 4 በመቶ እንደማይበልጥና በአንጻሩ ከበለጸጉት አገራት ቻይና 23 በመቶ፣ አሜሪካ 19 በመቶ እንዲሁም የአውሮፓ አገራት 13 በመቶ በመያዝ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀዳሚ ናቸው።

አንድ ቢሊዬን የሚጠጋ ህዝብ ያላቸው ታዳጊ አገራት በየቀኑ የተለያዩ አደጋዎችን በማስተናገድ ዜጎቻቸው ህይወታቸውን በአስቸጋሪ መንገድ ይመራሉ ተብሏል።

በ 40 ዓመታት ውስጥ በታሪክ አስከፊ የተባለውና በባንግላዲሽና ኔፓል የደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ ሚሊዬን ዜጎችን ለጉዳት፤ በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለህልፈት መዳረጉ ይታወሳል።

በአፍሪካ በተመሳሳይ በሴራሊዮን በከባድ ዝናብ ምክንያት በተፈጠረ ጭቃ ከ አንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሞት፤ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በዚህ ጉባኤ ላይ እንዳሉት የበለጸጉ አገራት በሚፈጥሩት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጎጂዎች ታዳጊ አገራት ናቸው።

ታዳጊ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ቢሆንም በሚከሰተው አደጋ ቀዳሚ ተጠቂ በመሆናቸው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል የታዳጊ አገራት መሪዎች አንድነት በመፍጠር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር አገራቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተፈረመውን የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ኖርዌይ እ.ኤ.አ በ 2050 የበካይ ጋዝ ልቀቷን ከ 80 አስከ 95 በመቶ ለመቀነስ ባስቀመጠችው እቅድ መሰረት እየተንቀሳቀሰች መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ታዳጊ አገሮች ለሚያደርጉት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በሁለትዮሽም ሆነ በጋራ ግንኙነቶች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

Published in አካባቢ

መቱ መስከረም 25/2010 በኢሉአባቦር ዞን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የመማር ማስተማሩን ሒደት የሚያጠናክሩ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ገለፀ ።

በጽህፈት ቤቱ የዕቅድና ፕሮጄክቶች ስራ ሂደት መሪ አቶ ደሜ ሁንዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰቡ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ትምህርት ቤቶችን የማጠናከርና ለመማር ማስተማር ሂደቱ አመች የማድረግ ስራ ተከናውኗል።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ሁለት አዳዲስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣  የ162 የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፊያና የ2 ሺህ 384 የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች ስራና ጥገና  ይገኙበታል፡፡

የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍም የ42 አዳዲስ ቤቶች ግንባታና የ97 ነባር ቤቶች ጥገና ስራ ተከናውኗል ፡፡

ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር ስራው በዞኑ በሚገኙ 13 ወረዳዎች የሚኖሩ 65 ሺህ 600 የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል ።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ በተከናወኑት የትምህርት ልማት ስራዎች ከ16 ሺህ 800  የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ  አቶ ደሜ ተናግረዋል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 196 ሺህ 376 ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተዋል ።

ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን  እየተከታተሉ ያሉት በዞኑ 13 ወረዳዎች በሚገኙ 416 የአንደኛና  34 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የስርአተ ትምህርት ባለሙያ አቶ ዳንኤል አድማሱ ተናግረዋል ።

Published in ማህበራዊ

ማይጨው መስከረም 25/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ54 ሚሊዮን ብር የተገነቡ 287 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት በቁ።

በዞኑ ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ የትምህርት ልማት ቡድን መሪ አቶ ሳምሶን ተፈሪ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎቹ የተገነቡት በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው።

መማሪያ ክፍሎቹም በዚህ ዓመት ከ11 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሳምሶን እንዳሉት በትምህርት ቤቶቹ ከመማሪያ ክፍሎቹ ጎን ለጎን በግንባታ ላይ የነበሩ 64 የመምህራን መኖሪያ ቤቶችም ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ለግንባታ ሥራው ከዋለው ገንዘብ ውስጥ 44 ሚሊዮን ብር በህዝብ ተሳትፎ የተገኘ ሲሆን 10 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ ከየወረዳዎቹ አስተዳደሮች የተመደበ ነው።

በዞኑ በተያዘው የትምህርት ዘመን በ323 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመቀበል ከታቀደው 192 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን 95 በመቶ የሚሆኑት ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ 18 ሺህ 700 ዎቹ አዲስ የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ቡድን መሪው አያይዘው ገልጸዋል።

የኦፍላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ ጀማል በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው በሚገኝ ትምህርት ቤት ለተካሄደው ማስፋፊያ ግንባታ በጥሬ ገንዘብ 500 ብር ማዋጣታቸውን ተናግረዋል ።

ከእዚህ በተጨማሪ ከአካባቢው የሚገኘውን ቁሳቁስ በማቅረብ እገዛ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

"ከእንስሳት ሽያጭ ካገኘሁት ገቢ ሁለት ሺህ ብር ለትምህርት ቤት ማስፋፊያ ሥራ  ድጋፍ አድርጊያለሁ" ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አሰፋ ዝናቡ ናቸው።

"ልጆቻችን በአቅራቢያቸው ተገቢውን ትምህርት እያገኙ እንዲያድጉ ለወደፊቱም ድጋፌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር መስከረም 25/2010 በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በ721 ሚሊዮን ብር የጠጠር መንገዶች ግንባታ ይካሄዳል።

የክልሉ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጂንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ ለኢዜአ እንደገለጹት የመንገዶቹ ግንባታ የፊታችን ጥቅምት ወር ይጀመራል ።

የክልሉ መንግስት በመደበው 615 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የ318 ኪሎ ሜትር አዳዲስ ጠጠር መንገዶች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት አዲስ ከሚገነቡት መንገዶች ውስጥ ደቡብና ሰሜን ጎንደርን የሚያገናኙ ከጉማራ-ናቪጋ ጊዮርጊስና በደቡብ ወሎ ከአጅባር -ተድባበ ማርያም ተጠቃሽ ናቸው።

"አዲስ የሚገነቡት መንገዶች ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ ተደራሽ ባልሆነባቸውና ለረጅም ጊዜ የመንገድ ጥያቄ ሲቀርብባቸው በቆዩ አካባቢዎች ነው " ብለዋል።

ከፌደራል መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በተመደበ 105 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የ3 ሺህ 214 ኪሎ ሜትር የነባር ጠጠር መንገዶች ጥገና ስራ እንደሚከናወንም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የመንገዶች ግንባታ ለማስጀመር የማሽኖችና ቁሳቁሶች አቅርቦትና ተጓዳኝ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ ነው ።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ በበጀት አመቱ በሚከናወኑ የአዲስና ነባር መንገዶች ግንባታ ለ25 ሺህ 556 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል ።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ627 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የ3 ሺህ 345 ኪሎ ሜትር የአዳዲስና ነባር መንገዶች ግንባታና ጥገና ስራ ማከናወኑን  ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 በመጪዎቹ አምስት ቀናት በአብዛኛው ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ እርጥበቱ እየቀነሰ እንደሚሄድ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

በሌላ በኩል የተራዘመ የክረምት ወቅት ዝናብ ያላቸው የምዕራብ አጋማሽና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነው የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት የሚስተዋልበት ወር መሆኑን አስረድቷል።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በአብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ገናሌ ዳዋና ስምጥ ሸለቆ፣የአባይ ደቡባዊና ምዕራባዊ አጋማሽ፣የታችኛው ተከዜ ከመደበኛ በላይ  የሆነ ዝናብ ያገኛሉ።

በተመሳሳይ የታችኛውና የመካከለኛው አዋሽ ፣ የላይኛውና የመካከለኛው ዋቢ ሸበሌ  እንዲሁም የኦጋዴን ተፋሰሶች መደበኛና በጥቂት ቦታዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል ኤጀንሲው።

ይህ ሁኔታ  በተለይ በደቡባዊ  አጋማሽ በሚገኙ በታችኛው ተፋሰሶች ላይ  ከላይ በሚመጣው የክረምት ዝናብ የወንዝ ፍሰትና የወቅቱ ዝናብ ጋር ተዳምሮ የጎርፍ ስጋት ሊያስከትል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሟል።

ኤጀንሲው አያይዞ በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ  የአገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።

ይህም ሁኔታ ወቅታዊ ዝናብ ማግኘት በሚጀምሩ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስገንዝቧል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ  ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆም በተለይም የደረሱ ሰብሎች እንዳይበላሹ  አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል።

ሶዶ መስከረም 25/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለኦቶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልዩ ልዩ የመማሪያ ቁሳቁሶች ትናንት ድጋፍ አደረገ፡፡

በዩኒቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ኩማ እንደገለጹት ተቋሙ በአካባቢዉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ ለትምህርት ጥራት የሚጠበቅበትን  ለመወጣት ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ተቋሙ ለኦቶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሁን ካደረገው ድጋፍ ውስጥ  ስድስት አጉሊ መነጽሮችን ጨምሮ የተለያዩ የተለያዩ የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችና  የማስተማሪያ  ሶፍትዌሮች ይገኙበታል፡፡

በቀጣይም ለሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶችን በመምረጥ የፈጠራ ማዕከል እንዲሆኑ ለማገዝ ዩኒቨርስቲው ድጋፉን እንደሚሰጥ ዶክተር ብርሃኑ አረጋግጠዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ድጋፍ የተደረጉትን ግብአቶችን በአግባቡ የመጠቀም ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የወላይታ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲዉ ያደረገዉ የቁሳቁስ ድጋፍ ተማሪዎች ለሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ያላቸውን መሰረታዊ ዕውቀት ለማሳደግ ያስችላል" ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ከአሁኑ ሌላ ቀደም ሲልም 15 ኮምፒውተሮችን ድጋፍ እንዳደረገላቸው የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ በረከት ኮቦቶ ናቸው ፡፡

የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች ህብረት ተወካይ አቶ ኢዮብ ቦራና የተረደረገው ድጋፍ ተማሪዎችን ሳይንሳዊ የሆኑ ሙከራዎችን እያዩ ለመማር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን