አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 04 October 2017

መቱ መስከረም 24/2010 በኢሉአባቦር ዞን በገበያ ተኮር የግብርና ሰብሎች የሚለማው መሬት መጠን እያደገ መምጣቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ብርሀኑ እረና ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በዘንድሮው የመኸር  አዝመራ ገበያ ተኮር በሆኑ የሰሊጥ፣ ሩዝ፣ ኦቾሎኒ፣ ሩዝና ኑግ የሰብል አይነቶች ከ3 ሺህ 690 ሔክታር በላይ መሬት እየለማ ነው፡፡

ልማቱ በዋነኛነት ለሰብሎቹ ተስማሚ በሆኑ የዳሪሙ፣ ቡሬ፣ ኖጳና አልጌ ወረዳዎች እንደሚካሄድና ከ1ሺህ 400 በላይ አርሶአደሮች እየተሳተፉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

''በምርት ወቅቱ በሰብሎቹ እየለማ ያለው መሬት መጠን ከአለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በ263 ሔክታር፤ የተሳታፊ አርሶ አደሮች ቁጥር ደግሞ በ200  ብልጫ አለው'' ብለዋል ።

አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ በሚያስገኙ የግብርና ሰብሎች ልማት ይበልጥ እንዲሳተፉና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በተከታታይ በተሰጠው ትምህርት ልማቱ እየተስፋፋ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይነት ወደ ሌሎች ተስማሚ ወረዳዎች ልማቱን  በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ብርሀኑ አመልክተዋል፡፡

በአመቱ በሰብሎቹ እየለማ ካለው መሬት ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅና ባለፈው የምርት ወቅት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር  ከግማሽ በላይ ብልጫ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

በዞኑ የዳሪሙ ወረዳ ቤና ቀበሌ አርሶአደር አብዱልቃድር አወል በሰጡት አስተያየት በወቅቱ እያለሙ ካለው ሁለት ሄክታር ማሳ ከግማሽ የሚበልጠው  በሩዝ ሸፍነዋል፡፡

እያለሙት  ካለው የሩዝ ሰብል ከ45 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል ።

አርሶ አደር ጅላ አህመድ በበኩላቸው በአንድ ሔክታር መሬት ላይ እያለሙት ያለው ሩዝና ሰሊጥ ቡቃያው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ ተጠቃሚ ያደርገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል ።

በኢሉአባቦር ዞን  በተያዘው የምርት ወቅት በአጠቃላይ የአገዳ ፣ ብርዕና ቅባት ሰብሎች ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኖ እየለማ ነው ተብሏል ።

 

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ መስከረም 24/2010 ከጌዴኦ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ ፡፡

የግድቡ ዋንጫ በጌዴኦ ዞን የነበረው ቆይታ መጠናቀቁን አስመልክቶ ዛሬ የሽኝት መርሀ-ግብር በዲላ ከተማ ስታዲየም ተካሂዷል ፡፡

በቦንድ ግዥው ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ የነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማትም የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እጅ ተቀብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው በእዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ምክር ቤት የገቢ ማሰባሰብ ተግባር ከጀመረበት አንስቶ በአንደኛና ሁለተኛ ዙር ከዞኑ 36 ሚሊዮን 199 ሺህ ብር ተሰብስቧል።

ዋንጫው ወደ ዞኑ ከገባበት ከመስከረም 13 ጀምሮ ይህንን ጨምሮ አጠቃላይ የሕብረተሰቡን ድጋፍ ወደ 100 ሚሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና ዋንጫው በዞኑ በነበረው ቆይታ ከገጠርና ከተማ ነዋሪዎች፣ ከመንግስት ሠራተኞች እንዲሁም ከተቋማት ከ78 ሚሊዮን 438 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

ይህም ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከጌዴኦ ዞን የተገኘውን አጠቃላይ ድጋፍ 114 ሚሊዮን 638 ሺህ ብር ማድረሱን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የሚገመቱ 172 በሬዎች፣ 35 በግና ፍየሎች፣ ዶሮዎች፣ ቡና፣ ቆጮ፣ ማር እና ሌሎች የአይነት ስጦታዎች ከህብረተሰቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

"የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ በዞናችን ያደረገው ቆይታ ሕዝቡ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ መሳካት ያለውን ቁርጠኝነት የገለፀበት ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም በምናደርገው ልማታዊ እንቅስቃሴ ከጎናችን መሆኑን ያሳየበት ነው" ብለዋል ፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው፣ "መላው የጌዴኦ ህዝብ የህዳሴውን ግድብ አላማና ጠቀሜታ ጠንቅቆ በመረዳቱ ድጋፉን አሳይቶናል" ብለዋል ፡፡

ይህንን የዘመናት ቁጭት ለማስቀረት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ የተቻለው መንግስት ድህነትን ታሪክ አድርጎ ለማስቀረት ከሚያደገው ጥረት ጎን የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት መቆም በመቻላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡

መላው የዞኑ ህዝብ ድህነትን ለማሸነፍ የጀመረውን አንድነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከፍተኛ ቦንድ በመግዛት የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል በዲላ ከተማ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት አቶ አወል ጣሀ የሕዳሴው ግድብ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳታቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል ፡፡

ግድቡ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩም አስረድተዋል፡፡

በጌዴኦ እና አጎራባች ዞኖች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን የገለጹት ሌላው የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ ከድር በርጊቾ በበኩላቸው፣ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት የዋንጫና የምስክር ወረቀት መሸለማቸውን ተናግረዋል።

በጉጂ ዞንም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ያወሱት አቶ ከድር፣ በቀጣይ በሲዳማ ዞንም በሚኖረው የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ ላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በጌዴኦ ዞን የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ዛሬ ቀጣይ ተረካቢ ወደሆነው ሲዳማ ዞን ተሸኝቷል።

በመረሀ-ግብሩ የጌዴኦና አጎራባች ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የየወረዳው ተወካዮች፣ የባህል አባቶችና የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

     

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2010 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የበለፀጉ አገሮች ለታዳጊዎቹ የሚሰጡት ድጋፍ እንዲጨምርና ለተጎጂው ማህበረሰብ እንዲደርስ እየሰራች መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የአካባቢ ድርጅት ታዳጊ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከለጋሾች ጋር በአዲስ አበባ እየተወያየ ነው።

በውይይቱ የተገኙት የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቃሬ ጫዊቻ እንደገለፁት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሰጠው ድጋፍ እንዲጨምርና አስተማማኝ እንዲሆን አቋም ይዛ እየሰራች ትገኛለች።

ታዳጊ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖና ጉዳት በራሳቸው አቅም ለመቀነስ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ከበለፀጉ አገሮች የሚሰጠው ድጋፍ እንዲጨምር "አቋም ይዘናል" ብለዋል።

"የሚገባው የድጋፍ ቃል በመንግስት በኩል ሲሆን አስተማማኝ ይሆናል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ድጋፉ የሚሰጥበትን ባህላዊ አሰራር በመቀየር ድጋፉ እንዲጨምር ጥረቷን ትቀጥላለች ነው ያሉት።

በዚህ መሰረት በዓለምአቀፍ ህጎችና ስምምነቶች መሰረት የሚደረገው ድጋፍ የሚታወቅና በሂደት ሳይባክን የህብረተሰብ ኑሮ የሚቀይር ሥራ እንዲሰራበት አቋሟን እያራመደች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ድጋፎች አግኝታለች።

ጎጂ ኬሚካሎችን ለማስወገድ የተጠየቀው ድጋፍ በመገኘቱ የማስወገድ እንቅስቃሴው መጀመሩንም ተናግረዋል።

የዓለምአቀፉ የአካባቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማካሪ ክላውስ አስትረፕ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም የሚረዳ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየመከርን ነው ብለዋል።

የሚሰጠው ድጋፍ ስነ-ምህዳርንና በሰው ልጆችና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ውይይቱ እ.አ.አ ከ2018 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ለሰባተኛ ጊዜ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በርካታ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቋቋም እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ኢትዮጵያ አደጋው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በአገር ደረጃ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሩ አገራት መካከል ቀዳሚ መሆኗንም አክለዋል።

አገሪቱ የአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት በመስራቷ ለውጦች አምጥታለች ሲሉም ተናግረዋል።

ተጨባጭ ለውጥ በታየበት አገር ላይ ድርድሮችና ውይይቶችን ማካሄድ ዕቅዶችና በተጨባጭ የተገኙ ለውጦችን ለመመልከት ስለሚረዳ "ውይይታችንን በአዲስ አበባ እያካሔድን ነው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ መሰብሰቡን የዓለም አቀፍ የአካባቢ ድርጅት አማካሪው ገልፀዋል።

ድርጅቱ 183 አባል አገራት ያሉት ሲሆን 143 አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚያደርጉት ጥረት ድጋፍ ያደርጋል።

በዛሬው ውይይት የ25 ለጋሽ ድርጅቶችና የ40 አገራት ተወካዮችን ጨምሮ 150 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደቱ በየአራት ዓመቱ የሚከናወን ሲሆን የአሁኑ እ.አ.አ ከ2018 እስከ 2022 ባለው ጊዜ የሚሰጥ ልገሳ ነው።

ድጋፍ የማሰባሰቡና ድርድሩ በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ሲሆን ቀጣዩ በመጪው ጥር በብራዚል እና በስዊድን ይካሄዳል።

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በግጭቱ ለተፈናቀሉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔረሰብ አባላትም ለማድረግ የተጎጂዎችን ቁጥርና ሌሎች መረጃዎች በማሰባሰብ ላይ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአስተዳደሩ ካቢኔ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኞች የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል።

የገንዘብ ድጋፉን ዛሬ ለክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ማስረከቡንም ነው የተናገሩት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2010 ዜጎች የሰንደቅ ዓላማቸውን ክብር ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በተቆርቋሪነት መንፈስ ሊወጡ እንደሚገባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መከበሩ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል መሆኑን ተናግረዋል።

በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ ሦስት መሠረት ኅብረተሰቡ ለሰንደቅ ዓላማ የተሰጠውን ትርጉምና ክብር አስጠብቆ ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሰንደቅ ዓላማ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥትም ሆነ በወንጀል ሕጉ የራሱ ክብርና ትርጉም ያለው ቢሆንም፤ በአንዳንድ ግለሰቦችና ተቋማት ይህን ክብርና ሥርዓት መተላለፍ ይስተዋላል ብለዋል።

በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማን ክብር ለማስጠበቅ የሕግ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አቶ አማኑኤል አሳስበዋል ። 

በዓመት አንዴ ከሚከበረው ቀን ባሻገር ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብርና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በትምህርት ቤቶችና በሲቪክ ማኅበራት ለወጣቱ የሚሰጠው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሊጠናከር እንደሚገባም አክለዋል።  

ዕለቱ ከአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አለመጎልበት ጋር ተያይዞ በየአካባቢው የሚከሰቱ አለመግባባቶች በኅብረተሰቡ የሚፈቱበት አግባብ የሚጠናከርበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በውይይቶች፣ በጥያቄና መልስ ውድድሮችና በሠላማዊ ሰልፎች በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን፤ የማጠቃለያ በዓሉ ጥቅምት 6 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ይሆናል።

"ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል" የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን መሪ ሃሳብ ነው።

Published in ፖለቲካ
Wednesday, 04 October 2017 23:25

እሬቻ

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2010 የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎቻቸው ተከስቶ የነበረው ግጭት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እያከናወኑት ያለውን የማረጋጋትና ሠላም የማስፈን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ ስለነበረው ግጭት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የክልሎቹን አመራሮች አወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንዳሉት፤ ግጭቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እየተሰሩ ያሉ የማረጋጋትና ሠላም የማስፈን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

በግጭቱ ምክንያት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋሙ ሥራ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።

በግጭቱ ወቅት ሰብዓዊ ጥሰት የፈጸሙ ተጠርጣሪ አካላትን ወደ ሕግ ማቅረብ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታውን እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

ጉዳዩን እንዲያጠና በፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት የተሰጠው አካል ዝርዝር መረጃ እንዲያቀርብ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የሁለቱም ክልሎች ሕዝቦች ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት፣ ለሰው ልጅ የሚሰጡት ትልቅ ዋጋ፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል ነገም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ በሠላማዊ መንገድ የመፍታት እሴት እንዳይሸረሸር ማድረግ ከሁሉም አካል የሚጠበቅ መሆኑ አንዳለ ሆኖ፤ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ቀጣይነት ያለው ወጣቶችን የመምከርና የማስተማር፣ የማስታረቅና ስሜታዊነትን የማረጋጋት ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

Published in ፖለቲካ

ነገሌ መስከረም 24/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዚህ ዓመት 17 ሺህ 907 ሄክታር የቡና ማሳ የመጀመሪያ ምርት እንደሚሰጥ የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አብዲሳ ለማ እንደገለጹት፣ ማሳው ለምርት በመብቃቱ ዘንድሮ 611 ሺህ 950 ኩንታል ጀንፈል የቡና ምርት እንደሚገኝ በቅድመ ምርት ትንበያ ተረጋግጧል።

የቡና ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የቡና ጥራት መጓደል ለመከላከል በ153 የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት ለአርሶአደሮች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ በልማቱ እየተሳተፉ ካሉ 73 ሺህ 65 አርሶና ከፊል አርብቶአደሮች ውስጥ 5 ሺህ 627ቱ ሴቶች ናቸው።

በዞኑ ሻኪሶ ወረዳ የዲባ በቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር መኮንን ዱሎ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ በ12 ሄክታር መሬት ላይ ከሚሰበስቡት ቡና 190 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

በክረምቱ በነበረው አመቺ የዝናብ ስርጭት ተጨማሪ 30 ሺህ ችግኝ መትከላቸውንም ጠቁመዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር አረፋ ቡኖ በበኩላቸው፣ በ10 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የቡና ተክል 150 ኩንታል የእሸት ቡና ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

"ዘንድሮ የምሰበስበው የቡና ምርት ካለፈው ዓመት በ70 ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በዞኑ በ10 ወረዳዎች 88 ሺህ 367 ሄክታር መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የቡና ምርትም ባለፈው ዓመት ከተገኘው በ210 ሺህ ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2010 የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ያቀረበው የሃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ በየዕለቱ በአማካይ ሃያ ሺ ብር ለማውጣት መገደዱን ገለጸ።

ፋብሪካው በቅጥር ግቢው ለሚኖሩ ሰራተኞቹ መኖሪያ ቤትና ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲያገኙ ከአምስት ዓመታት በፊት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ  ቢከፍልም እስካሁን ምላሽ ያለማግኘቱን ይገልጻል።

ለልማት ተነሺዎቹ መንደር እስከ አሁን ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት ባለማሟላቱ ነዋሪዎቹ ለመግባት አልቻሉም። ይህም ሆኖ ፋብሪካው ለሠራተኞቹ የኤሌትሪክ አገልግሎት ለማሟላት በየዕለቱ ሁለት ሺ ሊትር ነዳጅ እየገዛ ለማቅረብ ተገዷል።

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ዳጋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ አገልግሎቱ በወቅቱ ምላሽ ባለመስጠቱ በየዕለቱ በአማካይ እስከ ሃያ ሺህ ብር እያወጣ ነው።

በኤሌትሪክ ሃይል አለማግኘት የተነሳ የፋብሪካው ሰራተኞች በተደጋጋሚ ስራ ሲያቆሙ እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በማሰብ በነዳጅ የሚሰራ ጄነሬተር ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅኖችና የምስራቅ ሪጅን የዲስትሪቢዩሽን ኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ገመቹ ይመር፤ በፋብሪካው የሠራተኞች መንደር የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ጉዳይ ላይ ለተጠየቁት ጥያቄ "እኔ ያለኝ መረጃ  ተሰርቶ ማለቁን ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች በቦታው በተገኙበት ወቅት የተጠየቀው የኤሌትሪክ ሃይል አለመቅረቡንና መብራት አለመግባቱን ተመልክተዋል።

ፋብሪካው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ ቢያከናውንም እስካሁን ኩይሳ ተብሎ የሚጠራው የልማት ተነሺዎች መንደር የኤሌትሪክ ኃይል መስመር ያልተዘረጋለት "የቤቶቹ ግንባታ ባለመጠናቀቁ ነው" ብለዋል።

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በበኩሉ እንደገለጸው፤ የቤቶቹ ግንባታ ከአንድ ዓመት በፊት ቢጠናቀቅም ነዋሪዎቹ ለመግባት አልቻሉም። ከኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ጋር በተደረገው ውል መሰረትም የቤቶቹ ግንባታ መጠናቀቅ አይጠበቅም።

አቶ ገመቹ እንደሚሉት ከቤቶቹ ግንባታ ጋር ካልተያያዘ ጉዳዩ ምርመራ ተደርጎበት ተጠያቂው አካል ይለያል።

እንደ አቶ ገመቹ ገለጻ፤ በአካባቢው የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲሰራ መደረጉና  የግብአት እጥረት ለችግሩ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት የሰሜን አዲስ አበባ ዋየር ቢዝነስ ኃላፊ አቶ አንድነት ደጉ በበኩላቸው፤ ለፋብሪካው ሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች ኤሌትሪክ ሃይል ለማስገባት የተፈጸመው ክፍያ ዓመታትን አስቆጥሯል ስለተባለው ጉዳይ ሙሉ መረጃው እንደሌላቸው ይናገራሉ። ጉዳዩን የሚያጣሩ ባለሙያዎችንም ወደ ስፍራው መላኩን ይገልጻሉ።

ባለሙያዎቹ በፊንጫ አካባቢ ያሉትን ጉዳዮች አጥርተው በሚያመጡት መረጃ መሰረት ስራው እንደሚከናወን ኃላፊው  ተናግረዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ መስከረም 24/2010 ለሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት ቀጣይነት ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሠላምና ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ አሳሰቡ።

የህዝብ ክንፍ አደረጃጀት ፣ማህበራትና ሌሎችም አካላት የተሳተፉበት 14ኛው የፌዴራልና የክልል የጋራ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሀገሪቷ ከግብርና መር የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ለማፋጠን በአሰሪዎችና ሠራተኞች መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነትና መልካም ግንኙነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

"የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በስኬት ለማጠናቀቅና ሀገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሠላምና ደህንነትን በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት  ይጠበቅብናል" ብለዋል።

ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ ግንባር  ቀደም ሚና ያላቸውና ወሳኝ የልማት አካል የሆኑት አሠሪና ሠራተኞች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አሰራር መተግባር ይገባል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት የኢንዱስትሪ ሰላምና ደህንነት እክል እንዳይገጥመው ማድረግ  ምርታማነትን በመጨመር የገበያ ተወዳዳሪነትን አድማስ ያሰፋል ።

ለሀገሪቱ  የሥራ ሥምሪት፣ብሔራዊ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲዎችና ህጎች ተግባራዊነትና ውጤታማነት አስፈፃሚ አካላት፣ማህበራትና የህዝብ ክንፍ አደረጃጀቶች ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከአሠሪና ሠራተኛ ወገን ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ለኢንዱስትሪ  ሠላም ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነም ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ የባለሃብቱን ምርታማነት ለመጨመርና የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ታደለ ይመር ናቸው።

ፌዴሬሽኑ ተደራሽነቱን በማስፋት ባለሃብቶች በየአካባቢያቸውና በየዘርፉ እንዲደራጁ በማድረግ ከ30 ሺህ በላይ አባላት ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አቶ ታደለ እንዳመለከቱት በስራ ቦታ የሰው ኃይሉ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ፣በአሰሪዎችና ሠራተኞች መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ  አለመግባባቶች በሰለጠነና በጥናት ለመፍታት በተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም ሊደርሱ የሚችሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የከፋ ችግር ሳያስከትሉ መከላከል እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

"በቀጣይነትም ከአሠሪና ሠራተኛ ወገን ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሀገሪቱ  የሥራ ሥምሪት፣ብሔራዊ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲዎች አተገባበር፣የአሠሪና ሠራተኛ ህጎች ውጤታማነት ላይ ርብርብ እናደርጋለን "ብለዋል።

" የኢንዱስትሪ ሰላምና ማህበራዊ ጥበቃ ለኢትዮጵያ ህዳሴ "  በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤው የፌዴራልና የክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች ፣ የህዝብ ክንፍ አደረጃጀትና ማህበራት እየተሳተፉ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን