አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 02 October 2017

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 በኢትዮጵያ ምቹና እኩል የስራ ስምሪት እድል ለመፍጠር፣ የሰራተኛ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንዲቻል የተቀረጸው አገር አቀፍ የሥራ ስምሪት ፖሊሲ ዛሬ ይፋ ሆነ።

ፖሊሲውን የሚመራና የሚያስተባብር ብሔራዊ የስራ ስምሪት ምክር ቤትም እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው ፖሊሲውን ይፋ ያደረገው።

ፖሊሲው ሲተገበር የስራ አጥነት ቁጥርን በመቀነስ ለዜጎች ምቹ የስራ እድል እንዲፈጠር፣ የስራ ስምሪት ክፍተቶችን በመሙላት አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ለኢንቨስትመንትና ለስራ እድል ፈጠራ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና የስራ ባህልን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደሚያስችል ተጠቁሟል ።

በአገሪቷ የስራ ስምሪት አገልግሎት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎት ለማስተናገድ እንዲቻል ፖሊሲው ትኩረት መስጠቱ ነው የተመለከተው።

ፖሊሲው ተግባራዊ ሲሆን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ሊገቱ የሚችሉ ምቹ የስራ ስምሪት በገጠሩ ለመፍጠር እንደሚቻልም ተጠቁሟል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገትና የሰው ሃይል አኳያ ሲታይ አሁን ያለው የስራ አቅርቦት ተመጣጣኝ አይደለም። ይህም በአገሪቷ ለሚታየው የስራ አጥነት ችግር ምክንያት ሆኗል።

መንግስት የህዝቦችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዜጎች ምቹ በሆኑ የስራ መስኮች መሰማራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

አገር አቀፍ የስራ ስምሪት ፖሊሲ ሲተገበር መስራት ለሚችሉ ዜጎች ምቹና እኩል የስራ ስምሪት እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በቀጣይ መንግስት ፖሊሲውን የሚመራና የሚያስተባብር ብሔራዊ የስራ ስምሪት ምክር ቤት እንደሚያቋቁምም ተናግረዋል።

ብሔራዊ ምክር ቤቱም ምቹ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩና ውጤታማ በሆነ አግባብ እንዲፈጸሙ የሚመራና የሚያስተባብር እንደሚሆን ተገልጿል።

በሁሉም የአገሪቷ ክልሎችና ወረዳዎች ምቹና ምርታማ የስራ ስምሪት መፈጠሩን ለማረጋገጥ ከብሔራዊ የስራ ስምሪት ምክር ቤት አወቃቀር ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምክር ቤቶች በክልሎችና በወረዳ ደረጃ እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።

የስራ ስምሪት ሲባል አንድ ሰው በቅጥር ወይም በግል ስራ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ በአንድ የኦኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ የሚያመለክት መሆኑ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር መስከረም 22/2010 የሀገሪቱን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በሚያስችሉ የመካከለኛና ከፍተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚነስቴሩ እየተገነቡ ያሉትን የርብ፣ የመገጭና የሰረባ ግድብ፣ የመስኖ ፓምፕና ካናል ግንባታ ያሉበትን ደረጃ ሚንስቴሩ ከአማራ ክልል የመስኖ ልማት ክትትል ኮሚቴ ጋር በመሆን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ገምግሟል።

ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዘላቂ እድገት እንዲያስመዘገብ ወጥነት ያለው የአመራረት ዘይቤ መከተል ይገባል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመስኖ የሚለማ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳለ መረጋገጡን ገልጸው፣ ይህን መሬት ደረጃ በደረጃ ወደ ልማት ማስገባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለእዚህም የገፅና የከርሰ ምድር እንዲሁም የዝናብ ውሃን በዘመናዊ መንገድ በመገደብና በማውጣት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የግብርና ሥራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመት መጨረሻ ድረስ 280 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማ የመካከለኛና ከፍተኛ መስኖ ግንባታዎችን ለማከናወን ግብ ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሚገነቡት የርብ፣ የመገጭና ሰራባ የመስኖ ግድብ፣ የካናልና የፓንፕ ግንባታዎች የእዚህ ዕቅድ አካል መሆናቸውንና ሥራውም በክትትል ኮሚቴ እየተገመገመ በሚቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የርብ መስኖ ግድብ ግንባታ መቶ በመቶ መጠናቀቁንና በቅርቡ ይመረቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ኢንጂነር ስለሺ እንዳሉት፣ የመገጭ ሰራባ የፓንፕ መስኖ ዝርጋታ 93 በመቶ፣ የመገጭ ግድብ 40 በመቶና የርብ መስኖ ልማት መሬት ዝግጅት ሥራ 53 በመቶ ተከናውኗል።

በተያዘው ዓመት ሁሉንም ግንባታዎች ለማጠናቀቅ ባላድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ መድረኩ አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፣ ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያስነሳ የነበረው የርብ መስኖ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን በአዎንታዊነት አንስተዋል።

"ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ የርብ፣ መገጭና ሰራባ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታን በማጠናቀቅ የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባደረግነው ክትትልና ድጋፍ የተገኘ ውጤት ነው" ብለዋል።

የርብ ግድብ ውሃ በመያዙ ሰው ሰራሽ ሐይቅ መፍጠር ተችሏል ያሉት አቶ ገዱ፣ ይህን ፕሮጀክት ፈጥኖ ወደ ልማት ለማስገባት፣ ቀሪ የካናል ግንባታ ሥራን ለማጠናቀቅና የካሳ ክፍያን ለመፈጸም አሁንም የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ገዱ ገለጻ፣ በርብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ብቻ ከ3 ሺህ 500 በላይ አባውራዎች በክረምትና በበጋ እንዲያመርቱ በማስቻል በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚያቀርቡበት ዕድል ይፈጠራል።

"በቀጣይ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በመስራት ግድቦቹ ከደለል ስጋት ነጻ ከማድረግ ባሻገር ሕብረተሰቡ በአማራጭ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተሰማርቶ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እንዲረጋግጥ መስራት አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

በእዚህም የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ከክልሉ ግብርና፣ ውሃ፣ መሬት አስተዳደርና ሌሎች ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዘበዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አያሌው ደምሴ በሰጡት አስተያየት የርብ ግድብ የፋርጣ፣ ፎገራና እብናት ወረዳዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ ቢዘገይም አሁን ላይ በመጠናቀቁ ቀሪ ሥራዎችን ፈጥኖ በመስራት አካባቢውን በመስኖ ልማት ታዋቂ ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አመልክተዋል።

ለግድቡ ስጋት ሆኖ የሚነሳውን ደለል ለመከላከል ባለፉት አራት ዓመታት ተከታታይ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፣ በቀጣይም የወረዳ መስተዳድሮች ሕብረተሰቡን አነቃንቀው እንዲሰሩ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በሚንስትሩ የሚመራ የልዑካን ቡድን የመገጭ፣ ሰረባና ርብ መስኖ ግድብና ሌሎች ተያያዥ ፕሮጀክቶችን ባለፉት ሦስት ቀናት መጎብኘቱ ይታወሳል ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ መስከረም 22/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችን ከአዲስ አበባና ሻሸመኔ ተቀብሎ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለማጓጓዝ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ተገነ ለኢዜአ እንደገለጹት ለተማሪዎች አቀባበል ለማድረግ የሚያስችል ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው፡፡

በጎ ፈቃደኛ ነባር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና አመራሮችን በማሳተፍ የተዋቀረው ይኸው ኮሚቴ አዲስ ተማሪዎች የእንግድነት ስሜት እንዳይሰማቸው ይሰራል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ይፋ በሚያደርገው የመግቢያ ወቅትም ተማሪዎችን ከአዲስ አበባና ሻሸመኔ ተቀብለው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚያጓጉዙ አውቶብሶችን ከወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያና የመንገድና ትራንስፖርት ስምሪት ክፍል ጋር በመቀናጀት ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ 

''በቀን እስከ ሶስት መኪና በመመደብ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል'' ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ50 የመጀመሪያና በ32 የድህረ ምረቃ መርሀ ግብሮች ከ10 ሺህ በላይ ነባር ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡                                                           

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 አትሌት አልማዝ አያና የ2017 የዓለም ምርጥ አትሌቶች ተብሎ በዕጩነት ከቀረቡ 20 አትሌቶች መካከል አንዷ ሆነች።

ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የ2017 ምርጥ የሴቶችና ወንዶች 20 ዕጩ አትሌቶችን  ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት አልማዝ አያና ከሴቶች ምድብ በአንደኝነት ተመርጣለች።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተወለደችው የ24 ዓመቷ አልማዝ ሩጫ የጀመረችው በ1 ሺህ 500 ሜትርና በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ርቀቶች ነው።

ወደ መከላከያ ክለብ ከገባች በኋላ በ5 ሺህ እና በ 10 ሺህ ሜትር ሩጫ  ውጤታማ መሆን ችላለች።

ከአልማዝ በመቀጠል የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ የሆነችው ማሪያ ላስቲስኬን ከሩሲያ፣ ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት ተወዳዳሪ ሄለን ኦቢሪ እንዲሁም አውስትራሊያዊቷ የመሰናክል ተወዳዳሪ ሳሊ ፒርሰን በምርጫው ተካተዋል።

በተጨማሪም ክሮሺያዊቷ የዲስከስ ወርዋሪ ሳንድራ ፔርኮቪች፣ደቡብ አፍሪካዊቷ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ካስተር ሴሜኒያና የርዝመት ዘላይ ተወዳዳሪ ብሪትኒ ሪስ ከአሜሪካ ከ20ዎቹ ዕጩዎች ዝርዝር ላይ ተካተዋል።

በወንዶች የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ የሆነው ደቡብ አፍሪካዊ ዋይድ ቫን ኒከርክ፣የመዶሻ ውርወራ ተወዳዳሪ ፓወል ፋጄክ ከፖላንድ፣የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ሳም ሄንድሪክስ ከአሜሪካ፣የጦር ወርዋሪ ጆሀንስ ቬተር ከጀርመን በምርጦቹ እጩ ውስጥ ተካተዋል።

እንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ፣ኬንያዊው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ኤሊያህ ማናንጎይ፣የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ኦማር ማክሌዎድ፣አሜሪካዊው የስሉዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ክርስቲያን ቴይለርና ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪ ሉቮ ማንዮንጋ በእጩነት ቀርበዋል።

በዕጩነት ከቀረቡ 20 አትሌቶች የማህበሩ ምክር ቤት፣ ቤተሰቦችና የአትሌቲክስ ደጋፊዎች በሚሰጡት ድምጽ ከሁለቱም ፆታዎች ሦስት አትሌቶች በምርጥነት ይመረጣሉ።

ከእነዚህ ውስጥ የዓመቱ ምርጥ አትሌት የሚሆኑ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶች በታህሳስ መጀመሪያ በፈረንሳይ ሞናኮ ይፋ ይደረጋል።

እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው ምርጫ በሴቶች አልማዝ አያና በወንዶች የአጭር ርቀት ንጉስ ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች በመባል መመረጣቸው የሚታወቅ ነው።

በወንዶች አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1998፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና በ2005፣ አትሌት መሰረት ደፋር በ2007 እንዲሁም አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ2015 ምርጥ አትሌት በመባል ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ዕግድ በተጣለባቸው ኩባንያዎች ንብረት ዕጣ ፈንታ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ንብረታቸው የታገደባቸው 7 የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ዕገዳው ‘ይነሳ አይነሳ’ በሚለው ጉዳይ ላይ በፖሊስ፣ ጠበቆችና በድርጅቶቹ ተወካዮች መካከል ክርክር ተደርጓል።

ዕገዳው የተጣለባቸው ድርጅቶች ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን፣ አሰር ኮንስትራክሽን፣ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን፣ ስህን ጎበና እና መሰረት ዓለሙ ናቸው።

በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው ዓርብ ተጀምሮ ባለመጠናቀቁ ለዛሬ በተላለፈው የቃል ክርክር ከመሰረት ዓለሙ በስተቀር ክርክር ተደርጓል።

ከነዚህም መካከል የየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ አቶ ቅባቱ አበራ የድርጅቱ ተዘዋዋሪ የባንክ ሂሳብ በመታገዱ 5 አገራዊ የመንገድ ፕሮጀክቶችና የስኳር ፕሮጀክቶች መቆማቸውን፣ የድርጅቱ ሰራተኞች ከሀምሌ ወር ጀምሮ ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ስራ እየለቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከባንክ የተበደረውን ገንዘብ ሳይሰራበት ወለድ እየተጠየቁ መሆኑንና ከወደብ መግባት የነበረባቸው የፕሮጀክት መሳሪዎች ወደብ ላይ ተቀምጠው ተጨማሪ ወጭ እየጠየቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአሰር ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ የማነ አብርሃ በ2000 ዓ.ም የመንግስት ስራ በመልቀቅ 4 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሃብት ምንጫቸው ሳይታወቅ 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት አካብተው ተገኝተዋል ተብለው ንብረታቸው ታግዷል፡፡

የአሰር ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅና የድርጅቱ 35 በመቶ ድርሻ ባለቤት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሚካኤል አብርሃ ሰባት ፕሮጀክቶች መቆማቸውን፣ በቋሚ ወጭዎች፣ በወደብ እቃዎች፣ በትራንዚትና በሌሎች ክፍያዎች ድርጅቱ ኪሳራ ውስጥ መሆኑን አንስተዋል።

በአጠቃላይ በእስካሁኑ እገዳ ድርጅቱ ከ 69 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል።

ኮንስትራክሽን ድርጅቱ የታገደው አቶ የማነ አብርሃ የተባሉ የአክሲዮን ባለድርሻን ምክንያት በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግለሰቡ የአክሲዮን ባለድርሻ እንጂ የድርጅቱ ባለቤት ባለመሆናቸው የእሳቸው ድርሻ ተለይቶ መታገድ ሲገባው አጠቃላይ የድርጅቱ ንብረት በመታገዱ ሌሎች ባለአክሲዮኖችን መጉዳቱንና፤ የድርጅቱም ሕልውና አደጋ ውስጥ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በወሰደው የመንገድ ፕሮጀክት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስና ተያያዠ ጉዳዮች በተመለከተ እገዳ የተጣለበት የዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን ድርጅቱ ለሰራተኞችና ለሌላ ሶስተኛ ወገን ክፍያ መፈጸም አለመቻሉን አብራርተዋል።

የድርጅቶቹ ተወካዮችና ጠበቆቻቸው በድርጅቶቹ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ የአገር ጭምር መሆኑን ጠቅሰው የስራ ማስኬጃ ተዘዋዋሪ ሂሳቦች እንዲለቀቁ ተከራክረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ የታገዱ ንብረቶች አስተዳዳሪ እንዲሾም ማመልከቱን ጠቅሶ፤ ለንብረቶቹ ጠባቂና አስተዳዳሪ ከተሾመ የደመወዝና ሌሎች ጉዳዮች መፈታት እንደሚችሉ፤ ነገር ግን አሁን ባለበት ሁኔታ እግዱ ቢነሳ በንብረቶች ላይ ምዝበራ ይፈጸማል በማለት ተከራክሯል።

ግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤትም በዕገዳው ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በቀጠሮው አጠቃላይ የታገዱ ንብረቶች መጠን፣የታገዱ ንብረቶች ዝርዝር፣ በእያንዳንዱ አመልካች ግለሰቦች የገቢና ወጭ እንዲሁም የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ምጣኔያቸውን እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ችሎቱ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስትና ህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት በማድረስ 20 ክሶች የቀረቡባቸውን በአቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ የተካተቱ የ12 ተከሳሾችን ጉዳይ ተመልክቶ የክስ መቃወሚያቸውን ለመስማት ለጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከተከሳሾቹ መካከል የትራንስናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ድርጅት ዳታ አናሊስት አቶ እዮብ በልሁ የተባሉት በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፈቅዷል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 በመዲናዋ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኮሌጆች የመግቢያ ነጥብ ይፋ ሳይሆን ምዝገባ እንዳይጀምሩ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

አንዳንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኮሌጆች የመግቢያ ነጥቡ ይፋ ሳይደረግ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ማስታወቂያ እየለጠፉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስቧል።

በመዲናዋ 75 የመንግስትና የግልና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኮሌጆች ሲኖሩ አዲስ ተማሪዎችን መቀበል የሚችሉት በ2009 ዓ.ም አፈፃፀማቸው ከ68 በመቶ በላይ ተማሪዎቻቸውን በብቃት ምዘና ያሳለፉት እንደሚሆኑ ቢሮው አስታውቋል።

ቢሮው ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው የተቋማት ዓቅም ግንባታ ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሲሳይ አብርሃ እንደገለፁት፤ ከተማ አስተዳደሩ የራሱን የቴክኒክና ሙያ መግቢያ ነጥብ ይፋ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው።

ዛሬ በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ይፋ የሆነው የመግቢያ ነጥብ አገር አቀፍ መሆኑን ጠቅሰው የከተማ አስተዳደሩ የራሱን ነጥብ የመወሰን ስልጣን ስላለው ይህንኑ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

የመግቢያ ነጥቡ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንና ተማሪዎች የመመዝገቢያ ነጥብ ሳይገለፅ መመዝገብ እንደሌለባቸው ነው ኃላፊው ያስገነዘቡት።

አንዳንድ ተቋማት የመግቢያ ነጥብ ይፋ ሳይደረግ የምዝገባ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ላይ እንደሚገኙና ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለማስተማር ፍቃድ የተሰጣቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኮሌጆች በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉና፤ የመግቢያ ውጤቱም እንደሚገለፅ የተናገሩት አቶ ሲሳይ ተማሪዎች ይህንን እያረጋገጡ መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በከተማዋ ከሚገኙት 75 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኮሌጆች ምን ያህሉ አዲስ ተማሪዎችን መመዝገብ ይችላሉ? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ የመለየት ሥራው ሲጠናቀቅ ይፋ ይሆናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት መስፈርቱን ያላሟሉና ሙሉ ለሙሉ የማስተማር ፈቃዳቸውን የተቀሙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማሰልጠኛ  ተቋማትና ኮሌጆች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 ለብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ስኬታማነት የፋይናንስ ተቋማት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ትግበራን ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ስትራቴጂውን ለማሳካት ክፍያዎች በባንክ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እንዲያልፉ ማድረግ፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ ስርጭትን ማስፋፋትና የኔትወርክ ደረጃ ጥራትን ማረጋገጥ ከቅድሚያ ተግባራት መካከል ጠቅሰዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳረስ፣ የኤሌክትሪክ ስርጭትን ማስፋፋትና መቆራረጥን መቀነስ በተጨማሪ መከናወን ያለባቸው ተግባራት እንደሆኑም አክለዋል።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራቸውን በኤሌክትሮኒክስ አሰራር እንዲፈጽሙ ማድረግ እንዲሁም የፋይናንስ እውቀትና ክህሎት በመደበኛ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

መንግስት የስትራቴጂውን አድማስ ለማስፋትና የተቀመጡትን ግቦች ማሳካት የሚያስችል የማስተባበሪያና የማስፈጸሚያ አደረጃጀት እንዲዘረጋም ምክትል ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂውን ግብና የሚያስፈልጉትን ተግባራትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ዘርፉ የተረጋጋ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቁጠባ፣ በብድር፣ በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት፣ በሀዋላና መድን እንዲሁም በአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች ማለትም በቅርንጫፍ ስርጭት፣ በወኪል ባንኪንግ፣ በክፍያ ማሽኖችና በመሳሰሉት በዘርፉ ለውጦች ተመዝግበዋል።

ይሁንና የአገሪቱ የፋይናንስ አካታችነት ከሌሎች አዳጊ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጻር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በዋናነት የፋይናንስና ተዛማጅ መሰረተ ልማቶች አለመዳበርን በምክንያትነት አንስተዋል።

የፋይናንስ ምርቶችና አገልግሎቶች ጥራትና የአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች ርቀት፣ አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ፋይናንስ ስርዓት ያለው ዕውቀትና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንና በቂ የፋይናንስ ተገልጋዮች ጥበቃ አለመኖር ለዘርፉ አለማደግ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የዘርፉን ችግሮች ለማቃለልና በሂደትም ለማስወገድ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት አጀንዳዎች መሰረት በማድረግ የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተቀርጾ ለትግበራ መቅረቡንም አመልክተዋል።

ስትራቴጂው የፋይናንስ ተጓዳኝ መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር፣ የተለያዩ ተስማሚ የፋይናንስ ምርቶች፣ አገልግሎቶችና የአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች አቅርቦት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ እንደሆነም አብራርተዋል።

ጠንካራ የፋይናንስ ተገልጋዮች ጥበቃ ማዕቀፍ ለመዘርጋት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ዕውቀትና ግንዛቤ ደረጃን ማሳደግም እንዲሁ።

ይህም ቁጠባን ለማበረታታት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር፣ አዳዲስ የማምረቻ ኢንዱስሪዎችና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ለማስፋፋት እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ በር ከፋች ተግባራትን ማከናወን ያስችላል ብለዋል።

የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስታራቴጂ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 22/2010 ኢትዮጵያ የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ምንም አይነት ጥያቄ አለማቅረቧን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገለጸ።

የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ጥያቄ  ማቅረቧን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

የአገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ውድድር፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮንፌደሬሽኑ አስታውቋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ለኢዜአ እንደገለጹት  የቻን አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለካፍ ያስገባነው ሰነድ የለም ብለዋል።

ውድድሩን ለማስተናገድ ኬኒያ የተመረጠች ቢሆንም በቂ ዝግጅት እያደረገች ባለመሆኑ የአስተናጋጅነት መብቷ መነጠቋን ተከትሎ ውድድሩን እናዘጋጅ ወይስ አናዘጋጅ? በሚል ውይይት እንደተደረገ ገልጸው ነገር ግን ውድድሩን ለማስተናገድ በይፋ የቀረበ ጥያቄ እንደሌለ ገልጸዋል።

በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በ2020 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ናት፤ የአሁኑን ውድድር ለማዘጋጀት ጥያቄ ከምናቀርብ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚካሄድው ውድድር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባል የሚል ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ያስረዱት አቶ ጁነዲን።

ውድድሩ ከሶስት ወር በኋላ ነው የሚካሄደው ለዛም የሚሆኑ ስታዲየሞችና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ባለው ጊዜ ለማዘጋጀት ስለማይቻል ለ2020ው ውድድር ትኩረት መደረግ እንዳለበት ውሳኔ መተላለፉን አብራርተዋል።   

ካፍ መረጃውን ከየት አምጥቶ ነው ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች ያለው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባለች የሚለውን መረጃ ከየት እንዳመጣው የምናውቀው ነገር የለም" ሲሉ አቶ ጁነዲን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር እንድታዘጋጅ ከአንድ ዓመት በፊት በይፋ መመረጧን አስታውሰዋል።

የካፍ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በ2018 የሚካሄደውን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሌላ አገር እንዲያስተናግድ በ15 ቀናት ውስጥ አዲስ አዘጋጅ አገር እንዲመረጥ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የአገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ 16 አገሮች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የዘንድሮው ውድድር ለአምስተኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።

 

Published in ስፖርት

ሽሬ መስከረም 22/2010 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አማራጭ የኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት እንዳለው በአካባቢው በደን ውጤቶች ላይ የተመሰረተውን የኃይል ፍላጎት በአማራጭ  ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ለመተካት በተለይ ባለፉት  አምስት ዓመታት የተሻለ ስራ ተከናውኗል፡፡

በዚህም በየዓመቱ ከሰባ ሺህ  በላይ አባወራና እማወራ አርሶ አደሮች አማራጭ የኃይል ቆጣቢ ቴክኖጂዎችን  እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ካልአዩ ብርሃነ ሰሞኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂው  ተጠቃሚዎች ቁጥር  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በዚያው ልክ የኃይል ፍላጎቱ ለማሟላት በደን ላይ ይደርስ የነበረው ጭፍጨፋ እየቀነሰ ነው።

ለአርሶ አደሮቹ ከቀረቡት ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች መካከል ማጎዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና በፀሓይ ብርሃን የሚሰሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ይገኙበታል፡፡

በአርሶ አደሩ ጉልበት፣  በአካባቢ ቁሳቁሶችና በእንስስት እዳሪ የሚዘጋጀው ባዮ ጋዝም ለኃይል አማራጭነት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አቶ ካልአዩ አመልክተዋል።

ከተጠቃሚዎች መካከል የታህታይ ቆራሮ ወረዳ  አርሶ አደር ነጋሲ በርኽ  በሰጡት አስተያየት ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምረው በፀሓይ ብርሃን የሚሰራ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ለኑሯቸው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል።

አርሶ አደር ግርማይ አታላይ የተባሉ ሌላው የወረዳው ነዋሪ በበኩላቸው በመኖሪያ ቤታቸው ባዘጋጁት ባዮጋዝ የኃይል ፍላጎታቸው በማሟላት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ለማገዶና ለመብራት የሚጠቀሙት ከደን ዛፍ በመቁረጥ እንደነበርም አርሶ አደሮቹ ጠቅሰዋል፡፡

የዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት እንዳመለከተው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ እስካሁን   ከ350 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን አማራጭ የኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ነው፡፡

በተያዘው ዓመት በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ከ100 ሺህ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና ሌሎችም የኃይል አማራጮችን  ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ታቅዷል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ማይጨው መስከረም22/2010 በማይጨው ከተማ  ከአራት ወር በፊት ስራ የጀመረው የራያ የንባብና የመረጃ ማዕከል የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለፁ።

ማእከሉ በ10 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባ መሆኑ ታውቋል።

ወጣቶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ማእከሉ በበቂ መጻህፍትና በመረጃ መስጫ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ባለመሆኑ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ።

በከተማው ነዋሪና የሁለተኛ አመት የዩኒቨርሰቲ ተማሪ ወጣት አድሃኖም ታደሰ እንደገለፀው በማእከሉ ከጥቂት የዘጠነኛና 10ኛ ክፍል የትምህርት መፅሃፍት በስተቀር ለሁሉም ደረጃ የሚመጥን ማጣቀሻና ለጠቅላላ እውቀት የሚሆኑ መጻህፍት የለም ።

"በክረምት የእረፍት ጊዜዬን በማእከሉ በንባብ በማሳለፍ ጠቃሚ መረጃ ለማሰባሰብ ብፈልግም ሳይሳካልኝ ቀርቷል " ብሏል ።

ሌላው የመሰናዶ ተማሪ ወጣት ቢንያም ግርማይ  በበኩሉ በማእከሉ ለደረጃው የሚሆን ማጣቀሻ መጽሀፍ አለመኖሩን ገልጿል።

ማእከሉ በመፃህፍትም ሆነ በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ደረጃ በሚፈለገው አግባብ የተደራጀ አለመሆኑን የገለፀው ደግሞ ወጣት ብርሃኑ ታደሰ ነው ።

የራያ የንባብና መረጃ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ጓንጉል ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ማእከሉ 10 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ ግንባታው ተጠናቆ ከሰኔ 2009 ጀምሮ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል ።

ማእከሉ በአንድ ጊዜ 400 ሰዎችን የሚያስተናግድ ሁለገብ የንባብ ቤት ጨምሮ የዲጅታልና የህፃናት ቤተ -መጻሃፍት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካተተ ነው።

ይሁንና  ማዕከሉ እስከ  6 ሺህ 500 የሚደርሱ መፃህፍቶችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለተለያዩ የትምህርት አይነቶች በሚሆኑ 1 ሺህ 500 መፃህፍት አገልግሎት እየሰጠ ነው ።

ማእከሉ ያለበትን የመጽሃፍትና ሌሎች ቁሳቁሶች እጥረት ለመፍታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

ማዕከሉ ያሉትን 28 ኮምፒውተሮች ቁጥር ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ተጨማሪ 30 ኮምፒተሮች ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በድጋፍ መገኘታቸውን ገልፀዋል ።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ በቅርቡ ከውጭ አገር ከሚገኙ ተቋማት በድጋፍ በተገኘ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዲጂታል ቤተ መፃህፍት አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ተስፋይ ኪዳኑ በበኩላቸው የማዕከሉን የመፀሃፍት ችግር ለማስወገድ ኮሚቴ ተቋቁሞ መጽሃፍቶችን በጥራዝና ለኮምፒውተር በሚሆን ቅጅ የማሰባሰብ ስራ ተጀምሯል።

በመቀሌና አዲስ አበባ ከተሞች ከሚኖሩ ግለሰቦችና ተቋማት ለመፃሃፍት ግዥ የሚውል የገንዘብ እርዳታ እየተሰባሰበ መሆኑንም ከንቲባው ተናግረዋል።

ከንቲባው እንዳሉት እስከ በጀት አመቱ አጋማሽ ድረስ ማእከሉን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ  አደራጅቶ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ።

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን