አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 11 October 2017

አሶሳ ጥቅምት 1/2010 የፌዴራል መንግስት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች የሀገሪቱን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  ለሁለቱ ምክር ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ የዓመቱን የመንግስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክተው ንግግር  ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

ይህንን ተከትሎ ኢዜአ  ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ፣ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት የሰጠው  ትኩረት የሚበረታታ ነው፡፡ 

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አሻግሬ ስዩም በሰጡት አስተያየት በፕሬዝደንቱ የተመለከቱት የዓመቱ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫዎች መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከህዝብ ጋር በመወያየት የለያቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ግንዛቤ መፍጠሩ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው "ይህንን ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማከናወን መታቀዱም መልካም ነው "ብለዋል፡፡

መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ጠቅሰዋል፡፡

ይህም መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን ለመታገል የደረሰበትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነው አስተያየት ሰጪው የተናገሩት፡፡

በፕሬዝዳንቱ ንግግር የመምህራን ጉዳይ መካተቱ መንግስት ለመምህራን ልማት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይ የገለፁት ደግሞ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዳምጠው ተሰማ ናቸው፡፡

የመምህራንን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻልና የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በክልሎች የሚገኙ ናቸው፡፡

የክልል መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

"በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን ቅጥር በአካባቢዊነት የሚፈፀም መሆኑ ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት ሊሆን ስለሚችል የተጠናከረ ክትትል ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ሀረር ጥቅምት 1/2010 የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ምክር ቤት በክልሉ እያደገ የመጣውን የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘረፉ የሚገኘውን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰራ ነው።

አለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በክልል ደረጃ ትናንት በሐረር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ያስሚን ዘካርያ እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር በየዓመቱ እድገት እያሳየ ነው።

"በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፈራዎችን ከጎበኙ 107 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በጎብኚዎች ቁጥርም ሆነ በገቢ የተመዘገው ውጤከ2006 ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ለአብነት ጠቅሰዋል ።

እያደገ የመጣውን የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠል በዚህ ዓመት ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ የቱሪዝም ምክር ቤት በክልል ደረጃ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።

ምክር ቤቱ የቱሪስት መስብ መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች መቹ ከማድረግ ጀምሮ በዘርፉ ከአገልግሎት አሰጣት ጋር የሚታዩ ችግሮችና መሰል ተግዳሮቶችን በጥናት ለይቶ ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎችን ተቀብለው በሚያሰተናግዱ የሆቴል ተቋማትና አስጎብኚ ማህበራት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል ለሥራ ኃላፊዎቻቸውና ለሰራተኞቻቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ወደ መስህብ ስፍራዎች የሚያደርሱ መንገዶችን ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ወይዘሮ ያስሚን ጠቅሰዋል።

"የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም በኩል ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት በዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የታገዘ የጥናትና ምርምር ሥራ  እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል በከተማው በአስጎብኚነት ስራ የተሰማሩት አቶ ቴዎድሮስ በላይ እንዳሉት  

በከተማው የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ጉድለት ለመፍታትና መንገዶችን ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ቢሮው በከተማው ከሚገኙ ሆቴሎች ጋር በመቀናጀት ለተቋማቱ ሠራተኞች እየሰጠ ያለው ስለጠናና የክትትል ስራ በስራችን ላይ ለውጥ እንድናመጣ አድርጎናል" ያሉት ደግሞ የበላይነህ ሆቴል ተወካይ አቶ ዮናስ ወልደማሪያም ናቸው።

በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች የሚታየውንና በጎብኚዎች የሚዘወተረውን "የጅብ ምገባ ትርኢት" በአንድ ቦታ ለማሳየት የተጀመረው የግንባታ ስራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

በሐረሪ ክልል በቱሪስቶች ከሚጎበኙት ቅርሶች መካከል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊ የጀጎል ግንብና በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቦ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞች፣ አድባራትና የጅብ ምገባ ትርኢት ተጠቃሽ ናቸው።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ጥቅምት 1/2010 ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስታወቁ።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገረቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ችቦ የአቀባበል ስነ- ስርዓት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል አፈ-ጉባኤው አቶ ጁል ናንጋል እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና የኩራት መገለጫ ለሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የክልሉ ሕዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

''ያለማንም ድጋፍና እርዳታ የኢትዮጵያ ህዝብ  ባለው  ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት የጀመረው ግድብ  እውን እስኪሆን ዛሬም እንደ ትናንቱ ድጋፋችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

ግድቡ በተለይም ለተጀመረው  የልማት፣ የፀረ- ድህነት ትግልና የህዳሴ ጉዞ ስኬት የላቀ ጠቀሜታ የሚኖረው በመሆኑ ህዝቡ ድጋፉን በቦንድ ግዥም ሆነ በስጦታ ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡኳይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ ህዝብ ከእዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ በቦንድ፣ በሎተሪ ግዥና በስጦታ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ግድቡ በህዝብ ተሳትፎ የሚገነባ እንደመሆኑ በቀጣይም የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተጀመረው ገቢ የማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የህዳሴውን ግድብ ችቦ በክልሉ ሦስት የብሔረሰብ ዞኖች በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች በማዘዋወርና ህዝቡን በማነሳሳት በተያዘው በጀት ዓመት 60 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አንዳንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ እውን እስኪሆን ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጋምቤላ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት አቶ ቸኮል በለጠ ግድቡ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከእዚህ ቀደም በሁለት ዙር የ75 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ቸኮል፣ በቀጣይም ተጨማሪ የቦንድ ግዥ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን በቦንድ ግዥም ሆነ ሌላ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቴዎድሮስ መኮንን ናቸው።

ግድቡ የሀገሪቱን እያደገች መምጣት ከሚያረጋግጡ ማሳያዎች አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለት ችቦው በጋምቤላ ስታዲየም አጀብ ተደርጎለት ለከተማ መስተዳድሩ የቅብብሎች ስነ ስርዓት ተካሄዶለታል።

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ ጥቅምት 01/2010 በአፋር ክልል እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን የሚያስተናግደው አፋር ክልል ሰመራ እየተከናወኑ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያና ሌሎችንም የመሰረተ ልማት ስራዎች የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት  በአፋር እየተከናወኑ ያሉት የመሰረተ ልማት ስራዎች ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው፡፡

በተለይም ከአጭር ግዜ አንጻር በቅርቡ ከሚከበረው 12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር ተያየዞ የሚከነወኑ የመሰረተ-ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ መንግሰት ጋር በመተባባር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ቀደም ብሎ የተጀመሩ የሰመራ አውሮፕላን ማረፊየና የመንገድ ግንባታዎች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ሰራዎች የሃገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የበለጠ እንዲጠናከሩ  ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጰያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማ በበኩላቸው አፋር ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር የሚያገናኙ ልዩ ልዩ የመንገድ ስራዎች  በእቅዳቸው መሰረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ያለውን  እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የቱሪስት መስህብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚስችሉ የዲዲግሳአላ-ያሎ-ኒኤሌ መንገድና የአዋሽ አርባ-ዱለሳ-ደብረብርሃን እንዲሁም የዳሉል-ባዳ መንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም  በጀት ዓመቱ ወደስራ የሚገቡ ከአህመዴአ- አፍዴራና ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ከ12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር ተያየዞ   የ3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሰመራ ከተማ የአስፓልት መንገድ ማስፋፋያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ለበዓሉ እንደሚደርስም ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሮጺዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ላይችሉህ መጨጌያው እንዳሉት 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ወደ አስፓልት ደረጃ የማሳደግ ስራው 94 በመቶ ተጠናቋል፡፡

የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ በማጠናቀቅ ለበዓሉ እንግዶችን ማስተናገድ በሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ድርጅታቸው ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2010 የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ክብር ከፍ ለማድረግ የወጣቱን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞችና አመራሮች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች 10ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል" በሚል መሪ ሓሳብ ዛሬ በመስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አክብረዋል።

ሰራተኞቹ እንዳሉት በሕገ መንግሥቱ እቅውና የተሰጠውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባለ ሰማያዊ አርማ ባንዲራ ምንነትና የአርማውን ትርጉም የመረዳት ችግር አለ።

አገሪቱ በየዘመናቱ የተቃጡባትን ወረራዎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወራሪዎችን የመከተችና ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር የተዋደቁ ጀግኖች እናት ናት።

ሰንደቅ አላማ ለኢትዮጲያዊያን አርበኞች በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ለአገራቸው ሰንደቅ አላማ ክብር ከፍ ብሎ መውለብለብና ለሉዓላዊነታቸው መከበር የተሰውለት በመሆኑ የማንነትና የአልደፈርም ባይነትም መገለጫ ነው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አውቅና የተሰጠው አረንጓዴ ቢጫ ቀይና ባለ ሰማያዊ አርማ ሰንደቅ አላማ የሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦችን አንድነትና እኩልነት የሚያንጸባርቅ የሉዓላዊነት ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞቹ እንዳሉት ወጣቶቹ  ከግንዛቤ ማነስ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ያለውን ባንዲራ ባለማወቅ ፤የአንድ ብሔርን የሚወክል ባንዲራ ይዘው ይታያሉ።

መንግሥት የሕዝቡ አመለካከት ላይ የለውጥ ሥራ መስራት አለበት ያለችው ወይዘሮ ረድኤት ከበደ አገርን የሚወክለውን አንድ ባንዲራ ሁሉም ሰው እንዲረዳውና እንዲያከብረው ትምህርት መሰጠት አለበት ትላለች።

ዓመትን ጠብቆ የባንዲራ ቀን ሲደርስ ብቻ ከመስራት ይልቅ ፤በትምህርት ቤቶችና በስራ ቦታዎች የሰንደቅ አላማ ምንነትን የሚያስገነዝቡ ትምህርቶችን መስጠት ይገባል ነው ያለችው።

ሌላው የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ አቶ አድማሱ ወንድማገኝ ሁሉም ሰው የሰንደቅ አላማ ትርጉም ሊገባውና ሊዘምርለት ይገባል ይላሉ።

"ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር ትርጉም ነው" ያሉት አቶ አድማሱ መንግሥት አሁን ላይ ላለው የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ የሰጠውን የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ነጻነት ትርጉም  ለኅብተረሰቡ የማስገንዘብ ተግባራትን በስፋት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

"ልጅ ሆኜ ሰንደቅ አላማ ሲሰቀልና ሲወርድ እንቆም ነበር"  ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ ፤ቀድሞ የነበረው የሰንደቅ አላማ ስርዐት መቀጠል አለበት ይላሉ።

በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁሉም ሰው የሰንደቅ አላማን ትርጉምና ምንነት ማስተማርና ማስገንዘብ አማራጭ ነው ብለዋል።

በተያያዘ ዜና 10ኛውን የሰንደቅ አላማ በዓል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ፣የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰራተኞችና ሌሎችም ተጠሪ ተቋማት በየተቋሞቻቸው መሰብሰቢያ አዳራሾች አክብረዋል።

 

የዘንድሮው 10ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 01/2010 ወጣቱ ትውልድ ለሰንደቅ ዓላማው ያለው ክብር ይበልጥ እንዲጎለብት ተከታታይ የማስተማር ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ተነገረ።

10ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአዲስ አበባ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች በመከበር ላይ ይገኛል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ የደንብ ማስከበር ሠራተኞች፣ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶችና  የህብረተሰብ ክፍሎች ዕለቱን አክብረዋል።

በአገሪቷ የሰንደቅ ዓላማ ምንነትና ሊሰጠው ስለሚገባው ክብርም ውይይት አካሂደዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ወጣቱን ትውልድ ስለ አገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ምንነትና ስለተከፈለለት ዋጋ በማስተማር ፍቅርና አክብሮች እንዲሰጠው ማድረግ ያስፈልጋል።

አቶ በቀለ ሚደቅሳ አንዳንድ ወጣቶች በግንዛቤ ማነስ ምክንያት ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው "መንግሥት በህገ መንግስት የፀደቀውን ሰንደቅ ዓላማ ምንነት ለአሁኑ ትውልድ የማሳወቅ ሥራ በቀጣይነት ማከናወን አለበት" ብለዋል።

ወጣቱ ለአገሩ ሰንደቅ ዓላማ ክብር እንዳይኖረው ማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች በመኖራቸው የሰደቅ ዓላማ አዋጁ በትክክል መተግበር እንዳለበትም ተናግረዋል።

"ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ያለመቆም፣ ሠዓቱን ጠብቆ ያለመስቀልና ማውረድ፤ ሌሎች ክፍተቶችም በስፋት ይስተዋላሉ" ያሉት ደግሞ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ወጋየሁ ኃይሉ ናቸው።

በውጭ አገር የሚኖሩ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የሃይማኖት እኩልነትን የሚያመለክተው ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማና ሌሎች ምልክቶችን በመያዝ ወጣቱን እያሳሳቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአገር ውስጥም መሰል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላት እንዳሉ የተናገሩት አቶ ወጋየሁ "እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነትና ትርጓሜ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።

አስር አለቃ መዓዛ ደበበ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማን በክብር መያዝ ሲገባ ለልብስ፣ ለኮፍያ፣ ለሻሽና ለሌሎች ተግባራት ሲውሉ መመልከት እየተለመደ መምጣቱን ይናገራሉ።

ሰንደቅ ዓላማን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታና ቦታ መጠቀም በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን በመጠቆም ድርጊቱ ታዳጊዎችንም  በተሳሳተ መንገድ የሚቀርጽ   በመሆኑ ከወዲሁ ሊታረም እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ጥቅምት 1/2010 ኢትዮጵያና ኢራን የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል መህዲ አቃ ጃፋሪ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ማሳደግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ቀጥታ የንግድ ግንኙነት ማጠናከርን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ትርኢቶች ማካሔድን ጨምሮ  የተግባቦትና የባንክ ትብብርን ማጎልበትና  የቢዝነስ ጉብኝቶችን ማመቻቸት የሚቻልባቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ ሀገራቸው ከኢራን ጋር ያላትን  ግንኙነት ለማሳደግ እንዲሁም የኢኮኖሚና ንግድ ትብብሩን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡     

የኢራኑ ዲፕሎማት ኡጋንዳንና ቡሩንዲን ጎብኝተው ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝታቸው ማሳረጊያ አድርገዋታል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከኢፌዴሪ ማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትርና ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጀነራል ዳይሬክተር ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ቆይታቸው የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የጎበኙ ሲሆን ከሃላፊዎቹ ጋርም ሀሳብ መለዋወጣቸውን የኢራን ዜና አገልግሎት (IRNA) በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ማይጨው ጥቅምት 1/2010 በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ አንዳንድ የራያ አላማጣ ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ።

በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም የሸፈኑትን የስንዴ ምርጥ ዘርን ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምድ እንዲሆን በወረዳው "መረዋ ፀፀራ" የገጠር ቀበሌ የመስክ ጉብኝት ትናንት ተካሄዷል።

ማሳቸው ከተጎበኘላቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ኃይሉ በርሄ እንዳሉት ቀድሞ ከሚጠቀሙት የአካበቢ ስንዴ ይልቅ ምርጥ ዘሩ ይበልጥ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ 

ምርጥ ዘሩ በሽታን ከመቋቋም ባለፈ የሰብሉ ግንድ ወፍራምና ፍሬውም በአጭር ጊዜ የሚደርስ መሆኑን አርሶአደሩ ተናግረዋል።

"በመስመር የዘራሁትን የስንዴ ምርጥ ዘር ሦስት ጊዜ በማረሜ ሰብሌ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል" ያሉት አርሶ አደሩ  በእዚህም በሄክታር ከ20 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመኸር እርሻ የስንዴ ምርጥ ዘር ተጠቅመው ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ማልማታቸውንና ሰብሉ በአነስተኛ የዝናብ ውሃ በአጭር ጊዜ ለምርት መድረሱን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር እልፉ ወርቄ ናቸው።

የእርሻ ሥራቸውን በአግባቡ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን የገለጹት ወይዘሮ እልፉ፣ በአሁኑ ወቅት ሰብላቸው ለምርት መድረሱንና ከእዚህ ቀደም ከሚያገኙት የምርት መጠን ከሁለት እጥፍ በላይ አገኛለሁ የሚል ተስፋ አንዳላቸው ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ሰብላቸውን በመስመር በመዝራትና ማዳበሪያ በመጠቀም ያለሙ የአካባቢው ገበሬዎች በትንሽ የዝናብ ውሃ ሰብላቸው በሦስት ወር ጊዜ ለምርት ደርሶ ማየታቸውንና እርሳቸው ይህን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው መጸጸታቸውን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አርሶአደር ገብረ ብርሃኑ ናቸው።

በመጪው የመኸር ወቅት ሁሉንም የግብርና ፓኬጆች በመጠቀምና የባለሙያ ምክር በመቀበል የሰብል ልማት ሥራ ለማከናውን የሚያስችል ልምድ ከመስክ ጉብኝቱ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በአላማጣ እርሻ ምርምር ማዕከል የማህበረ ኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ስርፀት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሐጎስ ኪዳኑእንደተናገሩት ማዕከሉ በዞኑ አምስት ወረዳዎች በመኸር እርሻ ሥራ ከሚሳተፉ የአካባቢው አርሶአደሮች ጋር በመተባበር አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን  እያለማ ይገኛል።

በአካባቢው አርሶ አደሮች እርሻ መሬት ከሚለሙት ሰብሎች መካከል "ሳቢኒ" እና "ኢኤች 1847" የተሰኙ የቢራ ገብሶችን ጨምሮ በማዕከሉ ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ "ቦሴት፣ ኪንግበርግ፣ ዋልቂና ሐሸንገ" የተባሉ የጤፍ፣ የዳቦ ስንዴና የአተር ምርጥ ዘሮች ይገኙባቿዋል።

የሰብል ምርጥ ዘሮቹ የቢጫ ዋግ በሽታንና የአቀንጭራ አረምን በመቋቋም በአነስተኛ የዝናብ ውሃ በሦስት ወር ለምርት የሚደርሱ እና በአማካይ በሄክታር ከ21 እስከ 50 ኩንታል ምርት የመስጠት አቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርጥ ዘሮቹ በአካበቢው በሚኖሩ 700 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ እየለሙ ሲሆኑ፣ በመጪው የመኸር ወቅት በወረዳው አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በስፋት እንዲለሙ ይደረጋል ብለዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ኃይለ ካሳ በበኩላቸው በ2009/10 የመኸር አዝመራ በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ከ143 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል።

በሰብል ከተሸፈነው የእርሻ መሬት ውስጥም 56 በመቶ የሚሆነው በመስመር የተዘራ ሲሆን፣ ለሰብል ልማቱም ከ55 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉንም  አስረድተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አምቦ ጥቅምት 01/2010 በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚንቀሳቀሱ የመንገድ ስራ ተቋራጮችና አማካሪ መሃንዲሶች 755 ሺህ ብር ለመለገስ ወሰኑ፡፡

የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀነኒሳ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ገንዘቡን ለመለገስ የወሰኑት 22 የመንገድ ስራ ተቋራጮችና መሃንዲሶች ትናንት በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ነው።

በዚህም የወሰኑትን ገንዘብ  በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ገቢ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን  ጠቅሰዋል።

ድጋፍ ለማድረግ ከተስማሙት መካከል አቶ ጋሮምሳ ፊጣ በሰጡት አስተያየት የተፈናቀሉ ወገኖች  መልሶ ለማቋቋም እገዛቸውን ወደፊትም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

120 ሺህ ብር ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን የተናገሩት አቶ ደቾ ደሜ በበኩላቸው "ተፈናቃዮቹ ከደረሰባቸው ችግር አንፃር የሰጠሁት ገንዘብ አነስተኛ ነው" ብለዋል።

በቀጣይ ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስ  ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Wednesday, 11 October 2017 21:10

ህዳሴ ለምን ?

ገብረህይወት ካሕሳይ  ኢዜአ

ህዳሴ ግድብ፣ ህዳሴ ቴሌኮም፣  ህዳሴ ካፌ ፣ ህዳሴ ሞባይል ……. ህዳሴ ! ይህ ህዳሴ ተራ ስያሜ ወይስ የጠለቀ ትርጉም ይኖረው ይሆን ? አብረን እንየው። ሌሎች ህዳሴዎች ይቆዩና የኢትዮዽያን ህዳሴ እንመልከት።

የቀደምት ስልጣኔ አውራ፣ የገናና ታሪክ ባለቤት፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ ቡናን ለዓለም ያበረከተች፣ የጤፍ ምንጭና የነፃነት ተምሳሌት - ኢትዮዽያ።

እውን ኢትዮዽያችን መታደስ ያስፈልጋት ይሆን? የአክሱም ሀውልቶችንና የላሊበላ ውቅር አቢያተክርስቲያናትን የቀየሱ ጭንቅላቶችና የገነቡ እጆች፣ በጎራዴ መድፍን ያንበረከከ ወኔ የማን ሆነና እኛ እንታደስ?

ህዳሴ (Renaissance) በፊት የነበረውን መመለስ ማለት ነው። ዳግም መወለድ ወይም እንደገና ህይወት መዝራት (Rebirth or Revival) ብለንም ልንወስደው እንችላለን። እንታደሳለን ስንል ድህነትን በልማት ኋላቀርነትን ደግሞ በዴሞክራሲ እናሸንፈዋለን ማለታችን ነው።

ለመታደሳችን ምክንያቱ ዝቅጠት ነው። የችግሩ ምንጮች ቀደምት መሪዎቻችን ቢሆኑም የዝቅጠት ሰለባ የሆንነው ግን እኛው ህዝቦቿና አገራችን ኢትዮዽያ ናት። የዝቅጠት ውጤት ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነት ነው። ድህነትና ኋላቀርነት መገለጫችን ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

ዘመናዊ ኢኮኖሚና ጠንካራ ዴሞክራሲ የገነቡ የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ  በህዳሴ ውስጥ ያለፉ ናቸው። በግሪክና ሮማ ስልጣኔ ዘመን ገናና ታሪክ የነበራቸው አገራት እንደ ኢትዮዽያ ሁሉ በአንድ ወቅት ካጋጠማቸው ውድቀት ለማንሰራራት “ህዳሴ“ የሚል ቃል ተጠቅመዋል።

 እ.ኤ.አ ከ1050 እስከ 1300 በአውሮፓ የተሻለ ስልጣኔ የታየበት ጊዜ ሲሆን ከ1300 እስከ 1450 ደግሞ ረሀብ፣ በሽታና ጦርነትን ጨምሮ በርካታ ቀውሶች የተከሰቱበት ወቅት ነበር።

ግሪክና ሮማ ከስልጣኔ ወደ ኋላ በመቅረታቸው ምክንያት ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ጊዜ ውስጥ የፍልስፍና፣ የስነፅሁፍና የባህል ንቅናቄ ፈጥረው እንደገና ማንሰራራት ችለዋል ።

የኢትዮዽያ ህዝቦችም በአንድ ወቅት በዓለም የሰለጠኑ ተብለው ከሚጠሩ አገራት ጋር የሚመጣጠን ስልጣኔ ገንብተው እንደነበር ይታወቃል። በሒደት ግን አኩሪ ስልጣኔያችን ከስሞ አገራችን የድህነት፣ የረሃብ፣ የጦርነትና የብጥብጥ ተምሳሌት ተደርጋ እስከመወሰድ ደረጃ ደርሳ ነበር።  

የኢትዮዽያ ህዳሴ የተጀመረዉ ከአዲሱ ሚሊኒየም ወዲህ ነው። ዘመኑ የኢትዮዽያ ህዳሴ የሚጀመርበት ነው ብለን ተስፋ የሰነቅንበት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብለን ፈጣን አገራዊ እድገት ማስመዝገብ ከመጀመራችን ጋር ተያይዞ የብዙሃንን ተስፋ ያጫረ ጉዳይ ስለነበረ ነው።

የኢትዮዽያን ህዳሴ የማረጋገጥ ግብ መላው የአገራችንን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ለማንቀሳቀስ የሚችልና የረጅም ጊዜ የትግል መሳሪያ ሆኖ የማገልገል አቅም ያለው በመሆኑ ህዳሴው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።

አገራችን በስልጣኔ ወደ ኋላ ልትቀር የቻለችው በውስጧ ያቀፈችውን ብዝሃነት ማስተናገድ ስለተሳናት፣ ይህንኑ ተከትሎ በማያባራ ቀውስና ግጭት ስትናጥ በመኖሯ ፣ በተመረጠና ውጤታማ መንገድ የሚከተል ልማታዊ መንግስት መመስረትና ማስቀጠል ባለመቿላ ነው።

በሌላ አነጋገር የአገራችን ህዳሴ እውን ሊሆን የሚችለው የንቅዘቷ መሰረታዊ ምክንያት  የሆኑትን ድህነትንና ኋላቀርነትን በብቃት የሚያስወግድ ልማታዊነትን ከዴሞክራሲያዊነት ጋር ያጣመረ መንግስት መመስረት ስትችል ብቻ መሆኑ ነው።

የኢትዮዽያ የህዳሴ ጉዞ ያለፉት ዓመታትን ጨምሮ ከ40 እስከ 45 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።ኮሪያና ታይዋን እኛ አሁን ካለንበት የእድገት ደረጃ ከሚመሳሰል ሁኔታ ተነስተው 50 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከበለፀጉ አገራት ተርታ መሰለፍ ችለዋል።

እኛም ኮሪያና ታይዋን ያሳኩትን ግብ ለማሳካት የነደፍነውን የጉዞ መስመር ነው የኢትዮዽያ ህዳሴ ብለን የምንጠራው ።

 በፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካይዳኪ ገዛኽኝ ኮሪያና ታይዋን ያሳኩትን የኢኮኖሚ እድገት ኢትዮጵያ የማታሳካበት ምክንያት አይኖርም ባይ ናቸው ።

የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ በሶስት ዋናዋና ምእራፎች ተከፋፍሎ የተቀመጠ ነው ይላሉ ። አንደኛው አገሮች ከድህነት አዙሪት መውጣት የሚጀምሩበትና ወደ ዝቅተኛው መካከለኛ ገቢ (Lower middle income) መሸጋገሪያ ምእራፍ ነው። እኛም ጉዞውን ጀምረነዋል።

በዚህ ምእራፍ የነፍሰ ወከፍ ገቢ ከ100 የአሜሪካ ዶላር ወደ አንድ ሺህ ዶላር አካባቢ ማድረስ ሲሆን አሁን እያስመዘገብነው ባለው እድገት መቀጠል ከተቻለ በ2017ዓ.ም ማሳካት እንደምንችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አቶ ካይዳኪ እንደሚሉት ከሆነ የአገራችን ነፍስ ወከፍ ገቢ በ1983 ዓ.ም ከ100 ዶላር በታች ነበረ። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎሜሽን እቅድ በ2002 ዓ.ም ሲጀመር 377 ዶላር ብቻ ነበር። እቅዱ በ2007 ዓ.ም ሲጠናቀቅ ደግሞ ወደ 691 ዶላር  ከፍ ማለቱን ያስረዳሉ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጀመሪያ ዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን 794 ዶላር ማድረስ ተችሏል። የ2009 ዓ.ም ሃገራዊ እድገታችንም የሚበረታታ ነበር። ዘንድሮም ከ11 በመቶ በላይ እድገት ለማስመዝገብ ታቅዷል። በዚሁ ፍጥነት ከተጓዝን ከ2017 ዓ.ም በፊት ተልእኳችንን ማሳካት እንችላለን የሚል እምነት አላቸው።

ሁለተኛው ምእራፍ ወደ ከፍተኛው መካከለኛ ገቢ (Upper middle income) የምንሸጋገርበት ጊዜ ሲሆን ከ2017 ዓ.ም በኋላ ከ15 እስከ 20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚፈፀም ነው። የነፍስ ወከፍ ገቢያችንንም ከአንድ ሺህ ዶላር ወደ 5 ሺህ ዶላር የምናደርስበት ይሆናል።

የመጨረሻው ምእራፍ ከፍተኛ ገቢ (upper income or high income) ካላቸው ሃገራት ተርታ የምንሰለፍበት ይሆናል። የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን ከ5 ሺህ ወደ 10 ሺህ ዶላር ለማሳደግ በጣም ፈታኝ ጉዞ የሚደረግበት ምእራፍ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ ምእራፍ ተጨማሪ 15 ዓመታትን የሚጠይቅ ሲሆን በአጠቃላይ ሶስቱን ምእራፎች በፍጥነት መጓዝ ከቻልን እንደ ኮሪያና ታይዋን ከ40 እስከ 45 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ልንደርስበት እንችላለን በማለትም ያስረዳሉ። ፈጣን እድገቱ ሲቀጥልና ፍጥነቱ ያልተቆራረጠ ከሆነ አዎን! ህዳሴው እውን ይሆናል።

የህዳሴው ጉዞአችን ሊሳካ የሚችለው ኪራይ ሰብሳቢነት ሲወገድ ብቻ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል መጀመሪያ ከጥበትና ከትምክህት መላቀቅን ይጠይቃል። በግብር፣ በመሬት፣ በንግድ ስርዓት፣ በግዥና ኮንትራት አስተዳደር የሚታዩ የሙስና ችግሮችን በማፅዳትና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይጠይቃል።

ለኢትዮጵያ ህዳሴ ቆመናል ስንል ለእንደዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ጉዞ ታጥቀን ተነስተናል ማለት መሆኑን በጥብቅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ለአንድ ረጅም የማራቶን ሩጫ የሚደረግ ሳይሆን በዱላ ቅብብሎሽ መልክ ለሚከናወኑ በርካታ የማራቶን ሩጫዎች ተሰልፈናል ማለት ነው።

በሌላ አነጋገር በረዥም የለውጥና የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ሒደት ውስጥ የልማታዊ ዴሞክራሲ ቀጣይነትን ማረጋገጥ መሆኑ ነው።ይህንኑ ለማረጋገጥ ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት መስመሩን ቀጣይነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስምረውበታል።

ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ምእራፎች የሚያስተሳስሩ፣ ደረጃ በደረጃ እያደጉና እየጎለበቱ የሚሄዱ አራት አቅጣጫዎችን ወይም ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል። ቀዳሚው የልማታዊ መንግስትን ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛው የቴክኖሎጂ እድገትን ቀጣይነት መረጋገጥ ይሆናል። ሶስተኛው የመሰረተ ልማት እድገት ቀጣይነት ማረጋገጥ ሲሆን አራተኛው ለቀጣይ ለውጥ የሚያመች ሁኔታ መፍጠር ነው።

 በህዳሴው ጉዞ የመጀመሪያው ምእራፍ ለማሳካት የተነደፉት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች በእስከ አሁኑ ሂደት አመርቂ በሚባለው መልኩ በመተግበር ላይ ናቸው። አሁን በውስጣችን የተጫረው ተስፋና አንፀባራቂ ውጤቱ በፅናት ከሰራን ካሰብነው መድረስ እንደምንችል አመላካች ናቸው።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የክትትልና ግምገማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ዋለልኝ  እንደሚሉት ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በጋራ ርብርብ ይሳካል።

በእቅዱ የመጀመሪያው የትግበራ ዓመት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተውን ከባድ ድርቅ በኢኮኖሚው ላይ ተፅእኖ አሳድሮ ማለፉን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ መንግስትና ህዝብ በጋራ ባደረጉት ርብርብ የአንድ ሰው ህይወት እንዳይጠፋ ማድረግ ችለዋል። ይህም ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የፈጠረው አቅም ነው።

ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ አገራዊ እድገት የማስመዝገብ ግብ ያስቀመጠ ቢሆንም ያጋጠመውን ከባድ ድርቅ በመቋቋም በ2008 ዓም 8 በመቶ እድገት መመዝገቡ ትልቅ እመርታ መሆኑን ያስረዳሉ።

በእቅዱ ሁለተኛው የትግበራ ዓመት ማለትም በ2009 ዓም የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ደግሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት 10 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ዘንድሮም 11 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የህዳሴው መስመር በርካታ መሰረታዊ መስኮችን ታሳቢ አድርጎ የሚራመድ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የሚጓዝ ስለመሆኑም ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው። በአንድ በኩል የዜጎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነተ ማረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማስፈን ስራ ጎን ለጎን እየተሰራ ነው ።

ለአብነት ያክል ጥቂቶችን እንግለፅ ከተባለ እንኳን የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣ የገጠር የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም፣ለአቅመ ደካማ አረጋዊያንና የአካል ጉዳተኞች የቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራም ፣ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ፕሮግራም ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ ፕሮግራሞች ዜጎችን የልማቱና የእድገቱ ተጠቃሚዎች ከማድረጋቸውም በላይ አገራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከማሳደግ አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ።

ለማሳያነት ይረዳን ዘንድ የየፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ እንደገለፁት በ2009 ዓም ብቻ  በመደበኛ የስራ እድል ፈጠራና በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በዘንድሮው ዓመትም 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዷል።

ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተነደፈው ፕሮግራም በሙከራ ደረጃ በ11 ዋና ዋና ከተሞች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በሂደት 972 የአገራችን ከተሞችን ያካትታል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በዛብህ እንዳሉት በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ 159 ሺህ ዜጎች በአካባቢ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚዎች ማድረግ ተችሏል።

መስራት የማይችሉ 30 ሺህ 400 አቅመ ደካማ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ደግሞ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። እነዚህ ተግባራት ብዙ ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው።ከሁሉም በላይ ግን ከእድገቱና ከልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ተነጥሎ የሚቀር የህብረተሰብ ክፍል አይኖርም።

የህዳሴ ጉዞው ሁላችንንም የሚያነቃቃ የረዥም ርቀት መዘውር ነው ስንል ድህነትን በልማት ኋላ ቀርነትን በዴሞክራሲ የማሸነፍ አጀንዳ የሁላችንም በመሆኑ ነው። የህዳሴው መስመር በሒደት ከበለፀጉ ሀገራት ጎራ የሚያሰልፈን ብቸኛው መንገድ እስከ ሆነ ድረስ መታደስ ማን ይጠላል?  እንታደሳለን እንጂ !።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ዜና ሓተታ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን