አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 10 October 2017

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 የታዋቂው የባሕላዊ ሙዚቃ፣ መዲናና ዘለሰኛ ተጫዋች ኃብተሚካኤል ደምሴ ስርዓተ ቀብር በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።

ድምጻዊው ትናንት በደረሰበት የመኪና አደጋ ነው ሕይወቱ ያለፈው።

ትናንት ረፋድ አራት ሰዓት ላይ አበበ ቢቂላ ስቴድዬም አካባቢ ተሽከርካሪውን አቁሞ መንገድ በመሻገር ላይ እያለ ነበር የመገጨት አደጋ የደረሰበት።

በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ወደ ጳውሎስና አቤት ሆስፒታሎች ቢወስዱትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

በስርዓተ ቀብሩ ላይ የተነበበው የህይወት ታሪኩ እንደሚያመለክተው፤ ድምጻዊው ኃብተሚካኤል ከአቶ ደምሴ ጓንጉል እና ከወይዘሮ መነን አልዩ በ1944 ዓ.ም በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር በለጋንቦ ወረዳ ደረባ በምትባል አካባቢ ነው የተወለደው።

ማሲንቆ በመጫወት በ1960ዎቹ መባቻ ወደ ሙዚቃው ዓለም ብቅ ያለው ኃብተሚካኤል፤ በርካታ ባሕላዊና በመዲናና ዘለሰኛ የተቃኙ ዜማዎችን ለሕዝብ አበርክቷል።

ከህይወት ታሪኩ መረዳት እንደሚቻለው ወደ ስራ ዓለም የተቀላቀለው በ1971 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ ስራውን የጀመረውም በአገር ፍቅር ቲያትር ተፈትኖ አንደኛ በመውጣት በባህል ክፍል ውስጥ ተመድቧል።

ኃብተሚካኤል በ1983 ዓ.ም “ወሎ ያፈራት” የተሰኘ አልበም ለህዝብ ካደረሰ በኋላ በተለያዩ መድረኮች በመጋበዝ ስራዎቹን አቅርቧል፤ አድናቆትም አትርፏል።

ኃብተሚካኤል ደምሴ 25 ያህል የሙዚቃ ካሴቶችን የሰራ ሲሆን በሙዚቃው ዓለም አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደነበርም ተወስቷል።

በባሕላዊ ዜማዎች ቅኝት የሚታወቀው ኃብተሚካኤል በተለያዩ ተውኔቶች ላይም ተሳትፏል። ከነዚህም መካከል ታጋይ ሲፋለም፣ መስታወትና ባልቻ አባ ነፍሶ ይጠቀሳሉ።

ድምጻዊ ኃብተሚካኤል የአገሩን ባሕላዊ ሙዚቃ ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ በኬንያ፣ ግሪክ፣ ሆላንድ፣ እንግሊዝና ጀርመን በመዘዋወር ባቀረባቸው ስራዎቹም አድናቆትን አትርፏል።

የአራት ወንድና የሦስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ድምጻዊ ኃብተሚካኤል ደምሴ በደረሰበት የመኪና አደጋ  መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም በ66 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የድምጻዊ ኃብተሚካኤል ደምሴ ስርዓተ ቀብር በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲፈጸም ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹና አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 የጀርመን ተራድኦ ኮሚሽን /ጂ.አይ.ዜድ/ በአሲዳማ አፈር ለተጠቁ አራት ክልሎች አፈርን በኖራ ምርት ለማከም የሚያግዙ መሳሪያዎች  አበረከተ።

 ኮሚሽኑ የተቀናጀ የአፈር ምርታማነት አስተዳደር ፕሮጀክ አማካኝነት መሳሪያዎቹን ለኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች አበርክቷል።

 መሳሪያዎቹ የኖራ ድንጋዮችን ወደ ኖራ ፋብሪካ የሚያቀርቡ፣ የተፈጨ ኖራ ወደ እርሻ ቦታ የሚያደርሱና በእርሻው ላይ የሚበትኑ ናቸው።

 የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሃ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቱ በግብርና ትራንስፎርሜሽን የያዘችውን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ አጀንዳ ለማሳካት የአፈር አሲዳማነት ችግር እየሆነባት ነው።

 አሲዳማ አፈር ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች እንደሚከሰት ገልፀው በአገሪቱ ለእርሻ ከሚውለው መሬት 43 በመቶው አሲዳማ አፈር እንዳለው ተናግረዋል።

 አሲዳማ አፈሩን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂ መጠቀም የተሻለው አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው ከኮሚሽኑ  የተበረከቱት የማጓጓዣና የማሰራጫ መሳሪያዎች ችግሩን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

 የአፈር አሲዳማነት በአራቱ ክልሎች ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ባለፈው ዓመት በየቀኑ ከ200 እስከ 300 ኩንታል ኖራ የሚያመርቱ ተንቀሳቃሽ የኖራ ማምረቻ መሳሪያዎች እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።

 ''ይህም በቂ ባለመሆኑ ክልሎች ተጨማሪ የኖራ ፋብሪካዎች መገንባት አለባቸው፣ ዛሬ የተሰጡት መሳሪያዎችም ሰርቶ ማሳያ ናቸው፣ ውጤታማ ከሆኑ በስፋት ይሰራባቸዋል'' ብለዋል።

 የአፈር አሲዳማነትና የመሬት መሸርሸር እንዳይከሰት የተፈጥሮ ጥበቃ ስራን በስፋት መስራት እንዲሁም የከብቶች ፍግና ኮምፖስት መጠቀም ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል ።

 በጀርመን ልማት ትብብር የኢትዮጵያና ጅቡቲ ኃላፊ ሚስተር ሀንስፒተር ሽዌር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ226 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ከአሲዳማነት እንዲያገግም የያዘችው እቅድ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

 የተበረከቱት መሳሪያዎች ይህንኑ እንደሚያግዙና ጂ.አይ.ዜድ ለእቅዱ ተፈፃሚነትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

 የጀርመን ተራድኦ ኮሚሽን /ጂ.አይ.ዜድ/ 'የተቀናጀ የአፈር ምርታማነት አስተዳደር' ፕሮጀክት በ2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስከ 2013 ዓ.ም ይዘልቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሚገኘው ብሔራዊ የባሕል ማዕከል የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሕብረ ብሔራዊነት በሚወክል መልኩ አዲስ ግንባታ ሊደረግለት መሆኑ ተገለፀ።

የባህል ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በማዕከሉ የሚገኘው አንድ አዳራሽ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህልና እሴቶች የሚያሳይ ሆኖ ባለመገኘቱ የማስፋፊያ ግንባታው አስፈልጓል።

አሁን ያለውን የማዕከሉን ቅጥር ግቢ ጨምሮ 34 ሺህ 500 ካሬ ሜትር መሬት ለግንባታው መፈቀዱን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ኢትዮጵያዊ የኪነ ህንጻ ጥበብን የተላበሰና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ እንደሚገነባ ተናግረዋል።

ዶክተር እልፍነሽ የማዕከሉ ረቂቅ ዲዛይን በሚመለከት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣዩ ዓመት የማዕከሉን ግንባታ ለማስጀመር መታቀዱን ጠቁመዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው እስከ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ሊደረግበት እንደሚችል መገመቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

አዲስ የሚገነባው ማዕከል 3 ሺህ 500 ታዳሚዎችን የሚይዝ ሁለገብ አዳራሽ፣ የዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ አምፊ ትያትር፣ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ ቤተ መጽሐፍትና ቤተ መዛግብት እንዲሁም ሌሎች ክፍሎችን ያጠቃልላል።

ማዕከሉ የአገር ገፅታን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዲዛይኑ ግብዓት የሚሆን አስተያየት መስጠት እንደሚችልም አስታውቀዋል።

 

Published in ማህበራዊ

ጅማ መስከረም 30/2010 በጅማ ከተማ በመደበው 180 ሚሊዮን ብር ወጪ  የልማት ስራዎች እየተካሄደ ነው፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ኢስማኢል አባሳንቢ  እንደገለጹት ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተካሄደ ካለው የልማት  ስራዎች መካከል በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመረ  ከ13 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን  የድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ግንባታ ይገኝበታል፡፡

እንዲሁም ቀደም ብለው ለተገነቡ የሶስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራና የቤተ መጸሐፍት ቁሳቁሰችን ማሟላት፣ የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራዎች በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ ናቸው፡፡

ካለፈው ዓመት የዞሩ የአዌይቱ የህዝብ መዝናኛና የጅማ ከተማ ወጣቶች ማዕከላት እድሳትና ሌሎችንም ስራዎች እንዳሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

ለልማት ስራዎቹ ማስፈጸሚያ የተመደበው በጀት የሚሸፈነው ከመንግስት ፣ከአለም ባንክና ከህብረተሰቡ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የጅማ ከተማ ነዋሪ  ወጣት ሶፊያ አሊ የአዌዩቱ መናፈሻ ለዓመታት አገልግሎት ሳይስጥ መቀመጡ ህብረተሰቡን የመዝናኛ አማራጭ ከማሰጣቱም በላይ የከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ  ገድቦ መቆየቱን ተናግሯል።

ለተለያዩ ጉዳይ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች ቆይታ ለማራዘም ምቹ የሆኑ የመዝናኛ ስፍራዎችን ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቁሟል።

ለከተማዋ ልማትና እድገት መፋጠን አስተዳደሩና ነዋሪዎቹ ተባብረውና ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም  ጠቁሟል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010  የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ማቀዱን አስታወቀ።

 ጽህፈት ቤቱ በ2010 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ መክሯል።

 የጽሕፈት ቤቱ የፕሮጀክት ማኔጅመንትና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ እቅዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ጽህፈት ቤቱ በተያዘው ዓመት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ ገቢ የማሰባሰብ ተግባር ላይ ያተኩራል።

 ገቢው ለዚሁ ተብሎ በሚዘጋጁ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች፣ከቦንድ ሽያጭ  እና መሰል የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት በ2010 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚያሰባስብም ጠቁመዋል።

 የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ፤ በተለይም የአርሶና አርብቶ አደሩን፣ የባለኃብቱንና የዲያስፖራውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ከፍ ማድረግ በቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

 የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት "በተያዘው ዓመት በተለይ ባለኃብቱ ለግድቡ ግንባታ የገባውን ቃል ሙሉ ለሙሉ እንዲፈጽም የማስተባበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ።

 ባለኃብቱ ለግንባታው የገባውን ቃል በወቅቱ ለማስረከብ በሥራ መደራረብ ጫና ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተው፤ ይህንኑ ተግዳሮት ለማቃለልም ጽህፈት ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት።

 በዘንድሮው ዓመት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግም የቶሞቦላ ሎተሪዎች እንደሚዘጋጁና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኩልም እንደሚሸጡ ነው የገለጹት።

 የግድቡ ግንባታ የሕዝብ ክንፍ አስተባባሪ የክብር አምባሳደር አቶ ሙኡዝ ገብረሕይወት እንዳሉት፤ ሕዝቡ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

 ''ነገር ግን ይህ የተጠናከረ ተሳትፎ በተጀመረበት መልኩ እንዲቀጥልና ግንባታውም ከዳር እስኪደርስ ሕዝቡን የማስተባበር ሥራው በይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል'' ነው ያሉት።

 የሲቪክ ማኅበራት ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ተክሉ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተለይ የሲቪከ ማኅበራት ድርሻ አናሳ መሆኑን ነው የገለጹት ።

 በመላው አገሪቱ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፤ የሚጠበቅባቸውንና ወጥነት ያለውን ተሳትፎ በማድረጉ ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ነው ያሉት።

 ከኢትዮጵ ሃይማኖቶች ጉባኤ የተወከሉት አቶ አዳነ ደቻሳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ዓመት ከቦንድ ሽያጭና ከሌሎች መስኮች ለማግኘት የታቀደውን ገቢ ለማሳደግ የ8100 የስልክ አጭር የጽሁፍ መልዕክትን ጨምሮ ሌሎችም አዳዲስ ሐሳቦች ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ነው ያሉት።

 የኢትዮጱያ ዲያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው፤ በውጭ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግድቡን በተመለከተ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተከታታይ የውይይት መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

 ምክር ቤቱ በ2009 በጀት ዓመት ከመንግስት ሰራተኛው፣ከዲያስፖራው፣ከባለሃብቱና ከሕብረተሰቡ  በቦንድ ሽያጭ፣ሎተሪ፣ ከአጭር የጽሁፍ መልዕክትና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለግድቡ ግንባታ አሰባስቧል።

 በአጠቃላይ ከመላው ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን 2010 በጀት ዓመት ደግሞ የሕብረተሰቡን ድጋፍ ወደ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እቅድ ተቀምጧል።

 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሕዝቡ በበጎ ፈቃደኝነት በሚሰበሰብ ገንዘብና በመንግስት ወጪ በመካሄድ ላይ ሲሆን ግንባታው 60 በመቶ  ተጠናቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ተግባር የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጠየቁ።

 ፕሬዚዳንቱ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን አባላትና የለጋሽ አገራት ተወካዮችን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

 ውይይታቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ ነበር።

 የኢትዮጵያ መንግስት ከማኅበሩ ጋር በመሆን ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ምላሽ በመስጠት በኩል በሰራቸው ስራዎች ላይም ተወያይተዋል።

 በአፋር ክልል ተከስቶ በነበረው ድርቅ ማኅበሩ ከመንግስት ጋር በመሆን ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን አውስተዋል።

 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በዚህ ዙሪያ እያደረገ ያለውን ሰብዓዊ ተግባር ያደነቁት ፕሬዚዳንት ሙላቱ መንግስት ከማኅበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራና ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

 የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ማኅበሩን በማበረታታት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ ለድርቅ ምላሽ በመስጠት በኩል በማኅበሩ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

 በአፋር ክልል ተከስቶ በነበረው ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እንስሳትን መልሰው ማርባት እንዲችሉ የማከፋፈልና የምግብና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተከናወኑ ተግባራትን ጠቅሰዋል።

 ማኅበሩ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆን ድርቅ ከመከሰቱ በፊት የቅድመ መከላከል ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

 የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ፀሃፊ ዶክተር ጀሚላህ ማህሙድ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ከማህበሩ ጋር  እየሰራ እንደሚገኝና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

 የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰራቸውን ስራዎች እንደሚጎበኝ ተነግሯል።

Published in ኢኮኖሚ

 ጋምቤላ መስከረም 30/2010 በጋምቤላ ክልል የጊኒዎርም በሽታን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስታወቁ።

በክልሉ አቦቦ ወረዳ የበሽታው ስርጭት እንደገና ማገርሸቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጋትሉዋክ ቱት ወረዳውን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት በሽታው ከክልሉ ብሎም ከሀገሪቱ ለማጥፋት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም ባለድረሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

በክልሉ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት በተከናወኑ ስራዎች በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሶ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እንደገና ማገርሸቱን ተናግረዋል።

ይህም ሊሆን የቻለው ህብረተሰቡ ንጽህናውን ያልጠበቀ ውሃ ከመጠቀሙ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ገልፀዋል።

በመሆኑም  ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሽታውን ለማጥፋት ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ላለው ጥረት ስኬታማነት የክልሉ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በሽታውን  ለመቆጣጠርና ለማጥፋት  በተከናወኑ ስራዎች በሽታው መቀነስ ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት ተቃርቦ እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን በክልሉ አቦቦ ወረዳ የበሽታው ስርጭት እንደገና ማገርሸቱን ገልጿል።

በክልሉ ቀደም ሲል በየዓመቱ  በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ሁለትና ሶስት ብቻ የነበረ ሲሆን ሰሞኑን ብቻ ሰባት ሰዎች በሽታው እንደተገኘባቸው አስታውቀዋል።

''በበሽታው ተጠቅተው የተገኙት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በባለሀብቶች ለጉልበት ስራ የመጡ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸው ባለሃብቶች ለሰራተኞች ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ ሊያቀረቡ ይገባል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዮት ብሄራዊ የጊኒዎርም ማጥፋያ ፕሮግራም አስተባበሪ አቶ ጌታነህ አብራሃም በበኩላቸው ባለፉት 14 ወራት አንድም ምልክት ሳታይ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሽታው እንደገና መከሰቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም ኢንስትቲዮቱ ከክልሉ ጤና ቢሮና በዘርፍ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሰፊ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የውጭ ምንዛሬና የባንኮች የወለድ ተመን ላይ ማስተካከያ ማድረጉን አስታወቀ።

ማስተካከያው "የዋጋ ንረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አይፈጥርም" ተብሏል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ቢታቀድም፤ የ2008 እና የ2009 በጀት ዓመት አፈጻጸም የሸቀጦች የወጪ ንግድ ዕድገት በተቀዛቀዘ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

የባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከ1996 እስከ 2004 ዓ.ም የአገሪቷ የወጪ ንግድ አፈፃፀም በፍጥነት ያደገበት ጊዜ ነበር።

በእነዚህ ዓመታት የወጪ ንግዱ ምርት አማካይ ዓመታዊ ዕድገት 24 ነጥብ 1 በመቶ ደርሶ እንደነበር ነው የሚታወሰው።

ዶክተር ዮሐንስ እንደሚናገሩት፤ በወቅቱ ለወጪ ንግድ ዕድገቱ ዋነኛ ምክንያቶች የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ምርትና ምርታማነት ማሳየቱ እንዲሁም በዓለም ገበያ የዋና ዋና ወጪ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ነበር።

ለአብነትም ቡና በዓመት በአማካይ የ14 ነጥብ 1 በመቶ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የ26 ነጥብ 5 በመቶና ወርቅ የ23 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማሳየታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካን ዶላር በተነጻጻሪ ከሌሎች የንግድ ሸሪኮች ገንዘብ ጋር የነበረው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከመረጋጋቱ ባለፈ በመጠኑም ቢሆን ቅናሽ ያሳየበት ወቅት በመሆኑ ነው።

በዚህ ሳቢያም የአገሪቷ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ተወዳዳሪነት እንዲጨምር "የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል" ብለዋል።

ከ2005 እስከ 2009 በጀት ዓመት የግብርናው ምርትና ምርታማነት ተጠናክሮ ቢቀጥልም የዓለም የፋይናንስ ድቀትን ተከትሎ በዓለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በመቀነሱና የአሜሪካን ዶላር ከሌሎች የንግድ ሸሪኮች ገንዘብ ጋር ያለው ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ የወጪ ንግድ ላይ መቀዛቀዝ ተፈጥሯል።

ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ወርቅ ከፍተኛ የዋጋ መቀነስ ካጋጠማቸው የወጪ ምርቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ባንኩ በማክሮ ኢኮኖሚ በኩል የወጪ ንግድ ምርቶችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከርና አገራዊ ቁጠባን ለማሳደግ የውጭ ምንዛሬና የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

በዚህ መሰረት ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን የ15 በመቶ ማስተካከያ የተደረገበት ሲሆን፤ ዝቅተኛ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የወለድ ተመን ከአምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ይህም ማለት ዛሬ የነበረው የአንድ የአሜሪካን ዶላር የባንኮች የመግዣ ዋጋ 23 ነጥብ 4177 ሲሆን፤ ከነገ ጀምሮ በ26 ነጥብ 9303 የሚገዛ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ማስተካከያው "በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዘርፎችን የትርፍ ህዳግ ለማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የትርፍ ህዳግ ለመቀነስ ያስችላል" ብለዋል።

በሌላ በኩል የአገር ውስጥ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ለአስፈላጊ ኢንቨስትመንቶች እንዲውሉ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ ዝቅተኛ የወለድ ተመን ከአምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉንም ነው ያብራሩት።

ማስተካከያ የተደረገው የረጅም ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ ጥናት ተደርጎ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዮሃንስ፤ ማስተካከያው አጠቃላይ የዋጋ ንረት ላይና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የጎላ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አንስተዋል።

ቀደም ሲል በአገሪቷ የዋጋ ንረት የሚከሰተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸው እንደነበር የተናገሩት ምክትል ገዥው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አለመታየቱን አንስተዋል።

ይህም "የዋጋ ንረት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ተጽዕኖ ይቀንሰዋል" ብለዋል።

ማስተካከያው የጥቁር ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይችልም ለመቀነስ እንደሚያግዝ ዶክተር ዮሃንስ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ማስተካከያው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በትላልቅ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ጠቁመው፤ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ በኮንትሮባንድ የሚወጡ የወጪ ምርቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ነው ዶክተር ዮሃንስ የተናገሩት።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010 የውኃ ላይ አረሞችን ለማጥፋት ቴክኖሎጂን መሠረት ላደረጉ መፍትሄዎች ትኩረት መስጠቱን የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

'የተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት' አምስተኛ ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

ምክር ቤቱ የውኃ ኃብት አስተዳደሩ ፍትሃዊና አሳታፊ እንዲሆን ብሎም የህዝቡን ጥቅም ማዕከል ባደረገና የተፈጥሮ ስነ ምህዳርን ቀጣይነት ባረጋገጠ መልኩ በቅንጅት እንዲመራ ለማስቻል የተቋቋመ ምክር ቤት ነው ።

የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በስብሰባው መክፈቻ እንዳሉት በውኃ አካላት ላይ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መጤ አረሞችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው።

በጣና ኃይቅ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የእምቦጭ አረምን፣ በአዋሳ ሀይቅና በሌሎች ተፋሰሶች ላይ የተከሰቱ አረሞችን ለማጥፋት 'በኢኮ ኃይድሮሎጂ' ጽንሰ ሃሳብ መሠረት ለማጥፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እነዚህን አረሞች ወደ ማደበሪያና ሌሎች ጠቃሚ ነገሮች ለመቀየር የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሟል ነው ያሉት።

ኮሚቴው ቴክኖሎጂዎችን የሚመርጥ፣ የትግበራ አፈጻጸማቸውን የሚገመግም እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥናቶች የሚያካሄድ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነት እምቦጭን ወደ 'ኦርጋኒክ' ማዳበሪያነት ለመቀየር የአዋጭነት ጥናት የተካሄደ ሲሆን ጥናቱን ለመተግበርም 'ኤቲ-ኮንሰልቲንግ' ከተባለ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል።

አያይዘውም አሁን ካሉት 12 ተፋሰሶች ውስጥ የአባይ፣ የአዋሽና የስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ብቻ በባለስልጣን ደረጃ መቋቋማቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ሌሎች ተፋሰሶችንም በዴስክ ደረጃ የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከነዚህም መካከል ጊቤ ኦሞ፣ ተከዜና መረብ እንዲሁም ገናሌ ዳዋ ዴስክ ተቋቁሞ ተፋሰሶቹ በፍትሃዊነትና በትክክለኛው መንገድ ጥቅም እንዲሰጡ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ተፋሰሶች ለዘላቂ ልማት መሠረት የሚሆኑ ስራዎች ይሰራል ብለዋል።

''ውኃ የሁሉም ልማቶች የመግቢያ በር እንደመሆኑ መጠን በተፋሰሶቹ አማካኝነት ይህን ሃብት በአግባቡ ማልማት የሚያስችል መሠረት ያለው ስራ እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

የተፋሰስ ባለስልጣኖቹ ከዚህ ባሻገር ጎርፍና የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የመከላከል ስራዎችን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉም ነው ያሉት።

በ2009 ዓ.ም በተፋሰስ አስተዳደሩ በአባይ፣ በስምጥ ሸለቆ ሓይቆች፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ በተከዜና አዋሽ ተፋሰሶች አካበቢ በተሰራው የተቀናጀ ስራ ከ550 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም ተደርጓል።

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ስራ ጋር በተያያዘ ከ32 ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ በውሎው የ2009 ዓ.ም የስራ አፈጸጸምን ገምግሞ ለ2010 ዓ.ም ደግሞ አቅጣጫ ያስቀምጣል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን  መቋቋም የሚቻልበትና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመስኖ ልማት ላይ ማሰማራት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ዙሪያም ይመክራል።

አዲስ አበባ መስከረም 30/2010  በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት እንደተቻለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሸን ገለጸ።

ኮሚሽኑ እ.አ.አ ከ2010/11 እስከ 2015/16 የነበረውን የኢትዮጵያ የድህነት ምጣኔ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ትንተና ውጤት ይፋ አድርጓል።

 ጥናቱ በሁሉም የሀገሪቷ ገጠርና ከተማ የሚኖሩ 30 ሺህ 255 የቤተሰብ ኃላፊዎችን በናሙናነት የወሰደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲፒ) እና የልማት አጋር ቡድን (ዳግ) በቴክኒክና በግብዓት ድጋፍ ተሳትፈውበታል።

 በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም እንደገለጹት፤ በድህነት የሚኖሩ ዜጎችን ምጣኔ በ2010/11 ከነበረበት 29 ነጥብ 6 በመቶ በ2015/16 ወደ 23 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

 ምንም እንኳን ጥናቱ በተካሄደባቸው ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ቢጨምርም በድህነት የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር መቀነሱን ነው የተናገሩት።

 በተጠቀሱት አምስት ዓመታት የምግብ አቅርቦት ችግር በተመሳሳይ ከ33 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 24 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፤ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢም ከ377 ወደ 794 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል።

 ለድህነት ምጣኔው መቀነስ በከተማና በገጠር በመንግሥት የተተገበሩ ድህነት ተኮር የልማት ተግባራት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

 መንግሥት በተለይ የገጠሩን ማኅበረሰብ ከድህነት ለማውጣት በርካታ ተግባራትን ቢያከናውንም በአንጻሩ በገጠር አካባቢ ያለው የድህነት ምጣኔ ከከተማው ከፍ እንደሚል ነው የተናገሩት። 

 አቶ ጌታቸው በተመሳሳይ የአምስት ዓመት ጊዜ የገቢ ልዩነት ምጣኔ መመዘኛ (ጊኒ ኮፊሸንት) ከነበረበት 0 ነጥብ 30 ወደ 0 ነጥብ 33 ማደጉን ገልጸው "ይህ አነስተኛ ጭማሪ በሃብታምና ደሃ መካከል የተጋነነ የገቢ ልዩነት እንደሌለ ያሳያል" ነው ያሉት።

 ጥናቱን በቴክኒክና ግብዓት የደገፈውን የልማት አጋር ቡድን የወከሉት አንድሬ ገሂኦኔ ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚዊ ዕድገትና የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎችን እንዳስመዘገበች ጠቁመው በጥናቱ ሰፊ ዳሰሳ መደረጉን ገልጸዋል።

 "ጥናቱ በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋር ድርጅቶች በሀገሪቱ ድህነትን ለመቀነስ ለሚያከናውኑት ተግባር መሠረታዊ ፋይዳ አለው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው መንግሥት በኤልኒኖ አማካኝነት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 13 ቢሊዮን ብር መድቦ በመሥራቱ ድርቁ በድህነት ምጣኔ ምዘና ላይ የጎላ ልዩነት እንዳላመጣ ተናግረዋል።

 መንግሥት የድርቁን አደጋ ለመከላከል የተጠቀሰውን ብር መድቦ ባይንቀሳቀስ ኖሮ የድህነት ምጣኔው 28 በመቶ ይሆን እንደነበርም አብራርተዋል።

 በኢትዮጵያ የቤተሰብ ገቢና ፍጆታ ወጪ እንዲሁም የኑሮ ደህንነት ክትትል ጥናት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን እ.አ.አ ከ1995/96 ጀምሮ ለአምስት ጊዜያት ተከናውኗል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን