አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 01 October 2017

ባህር ዳር መስከረም 21/2010 የመብራት፣ ብድር፣ ውሃና የመሬት አቅርቦት ችግር በአማራ ክልል ለተሰማሩ ባለሃብቶች ተግዳሮች መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

 በክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ውጤት ትናንት በባህርዳር ከተማ በተካሄደ የእቅድ ትውውቅና አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 በኮሚሽኑ የፕሮሞሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው አለሙ እንዳሉት የጥናቱ ዋና ዓላማ በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ለይቶ ለመፍታትና የአጋር አካላትን ሚና ለማሳደግ ነው።

 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተካሄደው ጥናት ከ390 በላይ የሚሆኑ በክልሉ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መከናወኑን ገልጸዋል።

 በዚህም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ የገቡ ባላሀብቶች 80 በመቶ የመብራት፣ 56 በመቶ የብድር፣ 47 በመቶ የመሬት አቅርቦትና 43 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የውሃ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል።

 ከመብራት ችግር ውስጥም የሃይል መቆራረጥ እንደሃገር ያለ ቢሆንም በትራንስፎርመርና ቆጣሪ አቅርቦት ያለው ችግር ግን ባለሃብቶቹ ፈጥነው ወደ ግንባታ እንዳይገቡ በማድረግ ፕሮጀክቶቻቸው እንዲጓተት እያደረገ ይገኛል።

 ከመሬት ጋር ተያይዞም በወቅቱ ከሶስተኛ ወገን ነጻ አድርጎ አለማስረከብ፣ የልኬታና የቅየሳ ስራ ላይ ችግሮቹ በስፋት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

 በሚያቀርቡት ፕሮጀክት መሰረት ባንኮች ለጥሬ እቃ ብድር አለመፈቀድ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የአዋጭነት ጥናት ሰርቶ አለማቅረብና አሟልተው ለቀረቡትም ብድሩን ለመስጠት ከአንድ ወር በላይ  የሚወስድ መሆኑን ከባንኮች የተሰበሰበው መረጃ ያሳያል ተብሏል።

 ችግሩን ለመፍታት የተዘረጋው የኢንቨስትመንትና ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መዋቅር በተደራሽነት በኩል 86 በመቶ ቢሆንም ችግሮችን ተከታትሎ ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ግን ከ32 በመቶ ያልበለጠ መሆኑ ተመልክቷል።

 የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ጥናቱ ያመላከታቸው ችግሮችን በክልል፣ በዞንና በወረዳ መዋቅሮች በቁርጠኝነት እልባት መስጠት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።

 በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን በመፍታት ክልሉን ለባለሃብቶችና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረግ የተያዘው የበጀት ዓመት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ''ከዚህ ጋር ተያይዞ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በማጠናከር የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በጋራ በመገምገምና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ መስራት ይኖርብናል'' ብለዋል።

 በአማራ ክልል ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፈ በተሰጠው ትኩረት የኮምበልቻን ከማጠናቀቅ ጀምሮ በባህርዳር፣ ቡሬ፣ ሰሜን ሸዋና ሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እውን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

 በክልሉ በሚገኙ 10 ዞኖችና ሶስት ሜትሮፖሊታንት ከተሞች የተጠናው ጥናት ከ200 በላይ የሚሆኑ የዘርፉ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 21/2010 የኢሬቻ በዓል ምንም ዓይነት ግጭት ሳይከሰት በሰላም መጠናቀቁን የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት አስታወቀ።

በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዛሬም በተለየ ድምቀት ተከብሯል።

የበዓሉ ታዳሚዎች የልምላሜ ምልክት የሆነውን እርጥብ ቄጤማና አበባ ይዘው ወደ ሐይቁ  በመውረድ ነው አምላካቸውን በማመስገን በዓሉን ያከበሩት።

ውሎውን አስመለክቶ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቱ፤ በዓሉ በሰላም ተክብሮ መጠናቀቁ ደስ እንዳሰኛቸው ነው የገለጹት።

አባ ገዳ በየነ እንዳሉት በበዓሉ ላይ “ስድስት ሚሊዮን ህዝብ” ይታደማል ተብሎ ቢጠብቅም  “የተገኘው ህዝብ  ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚገመት” መሆኑ ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡

 "ይህ ሁሉ ህዝብ በአንድ ላይ በዓሉን አክብሮ ምንም ዓይነት ግጭትና የአካል ጉዳት ሳይደርስ መለያየቱ ትልቅ ስኬት” መሆኑን ገልጸው  ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሰላም አስከባሪ ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ለማ ገመቹ በበኩሉ  ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲካሄድ  የተሰጣቸውን ተልዕኮ በስኬት ማጠናቀቃቸውን ገልጿል።

የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የተሰጣቸው ሃላፊነት ትልቅ መሆኑን የተናገረው ወጣቱ፤ “ለተሳታፊ ወጣቶች ቀጣይ ስራ ጥሩ ልምድ ይሆናቸዋል" ብሏል።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተገኙና በባህላዊ አልባሳት ያሸበረቁ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶች፣ የተለያዩ የህብርተሰብ ክፍሎች ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ እሬፈና ወይም የምስጋና ስርዓት በማድረስ በሰላም ተመልሰዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ  መስከረም 21/2010 በሀገሪቱ የስርዓተ ምህዳር ልማት ትግበራ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ  ከብዝሃ ህይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ጋር በመሆን ባዘጋጀው "የብዝሃ ህይወት ሃብት ጥበቃ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው አገራዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የአከባቢ ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በወቅቱ እንደገለፁት የአረንጓዴ ልማት ማሳለጫ በሆነው በስርዓተ- ምህዳር ልማት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ፡፡

"የሰው ልጆች ህልውና ከብዝሃ ህይወት ሃብት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በአግባቡ ካላለማነው በአገራችን እየተከሰተ ባለው የድርቅ ተጽእኖ ላይ ተጨማሪ አደጋዎችን ለማስተናገድ እንገደዳለን" ብለዋል ፡፡

የምንገለገልባቸውን የብዝሃ ህይወት ስናለማ የመሬት ፖሊሲያችን ጋር በማይጣረስና ሀብቱን በማይጎዳ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"ከዚሁ ጎን ለጎን በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈጻሚ ለማድረግ የታሰበውን የስርዓተ ምህዳር ክፍያ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመተግበር የግል ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል " ብለዋል ።

በስነ -ምህዳር አገልግሎት ክፍያ የተመለከተ  ሰነድ ያቀረቡት የፋርም አፍሪካ አማካሪ ዶክተር ሙሉጌታ ልመንህ እንዳሉት በግብርና፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በታሸገ ውሀና መሰል ተግባራት የተሰማሩ ድርጅቶች ቀጥታ ከተፈጥሮ ሀብት አገልግሎት እያገኙ በመሆናቸው ለስነ-ምህዳር ልማት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ።

"የስነ-ምህዳር ልማት ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የአረንጓዴ ልማት መሳካት ከፍተኛ አስተዋፆ አለው "ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ ልማቱ እውን እንዲሆን በግል ተቋማትና በመንግስት መካከል ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አመልከተዋል ።

የስርዓተ ምህዳር ልማት በሙከራ ደረጃ  በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች  እንደሚከናወን ጠቁመዋል ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ስምኦን ሽብሩ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ አርባምንጭና አካባቢው ስነ-ምህዳር በእጅጉ የተጎዳ በመሆኑ በአባያና ጫሞ ሃይቅ ላይ የተደቀነው አደጋ እስከ ቱርካና ሀይቅ ሊዘልቅ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የሃይቆቹ እራስጌ ያለማ በመሆኑ በደለል ከመሞላታቸው በላይ በዓሣ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውና 49ሺህ 300 ሄክታር ሽፋን ያለው የአርባምንጭ የኩልፎ ስርዓተ ምህዳር አደጋ ተጋላጭነት አርባምንጭ ከተማና ዙሪያው ወረዳ እንዲሁም ዲታና ቦንኬ ወረዳዎች የሚገኙ 651 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ስጋት ውስጥ ወድቀዋል " ብለዋል ።

ከ10 ዓመት በፊት በአርባምንጭ ከተማ በጎርፍ ክስተት ከ50 በላይ ሰዎች የሞቱበትና በርካቶች የተፈናቀሉበትን አደጋ ያስታወሱት ዶክተር ስምኦን የህዝቡን የመኖር ህልውና ለማረጋገጥ የዓባያና ጫሞ ሃይቆች እራስጌን ማልማት አማራጭ ሳይሆን ግደታ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የተባበሩት መንግስታት የአገር ውስጥ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሉዊስ ቻምበርሊን በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስታት የህዝባቸውን የመኖር ህልውና ለማረጋገጥ በስርዓተ ምህዳር ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ በመንደፍ ለተፈፃሚነቱ መረባረብ ይገባቸዋል" ብለዋል ፡፡

በአገራዊ ኮንፈረንሱ ከሁሉም ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ መንግስት አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የግል ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል ።

Published in አካባቢ

አዳማ መስከረም 21/2010 የአዳማ ከተማ አስተዳደር በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ ለዓመታት ሳይለማ የተቀመጠ  ከ2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለሱን አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ  ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማዋና አካባቢዋ ተንሰራፍቶ በቆየው ብልሹ አሰራር፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ህዝቡ ለመልካም አስተዳደር እጦት አጋልጦት ቆይቷል።

መሪ ድርጅቱ ኦህዴድ በተጠናቀቀው በጀት አመት ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በከተማዋ የመሬት ዘርፍ ችግሮችን መፍታት ቅድሚያ ተሰጥቶች በትኩረት የተሰራበትና ውጤት የተገኘበት ነበር ።

በበጀት አመቱ በህገ ወጥ መንገድ በግለሰቦችና በኪራይ ሰብሳቢ በባለሃብቶች ተይዞ ሳይለማ የተቀመጠ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ በማስመለስ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል።

የተመለሰው መሬት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች በመስጠት አገልግሎት ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በልማት ስም መሬታቸው ያለአግባብ የተነጠቁ አርሶ አደሮች መሬት እንዲመለስ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

"በአመራሮችና በግለሰቦች ያለአግባብ የተያዙ 70 የመንግስት መኖሪያና የንግድ ቤቶችንም በማስመለስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ለአረጋዊያን ተላልፈዋል" ብለዋል ፡፡

በከተማዋ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን  በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከመስተዳደሩ ጎን ሆኖ ያሳየው ትብብርና ተሳትፎ ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ  ድርሻ እንደነበረው ገልፀዋል።

በምክትል ርዕስ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልአዚዝ ሙሐመድ በበኩላቸው ከጥልቅ ተሃድሶው ወዲህ በክልሉ በኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ ከ10 ዓመት በላይ ሳይለማ የተቀመጠ ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማስመለስ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል መደረጉን ገልፀዋል፡፡

"በዚህም በገጠርና በከተማ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችና ሴቶችን የእርሻ ማሳ፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ችግር ከማቃለል ባለፈ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ማቋቋም ተችሏል" ብለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ መስከረም 21/2010 በደቡብ ክልል የከተሞችን ደረጃ ለማሻሻል ለሚደርገው ጥረት ስኬታማነት ህብረተሰቡ በጽዳትና ውበት ስራ የሚያደርገው ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ 10 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ በርእሰ መስተዳድሩ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ 

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በመንግስት የተጀመሩ የመሰረት ልማት ግንባታዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

“የከተሞች እድገትና የደረጃ መሻሻል ስራ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በዋናነት የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ተከትሎ በሚከናወኑ የከተማ ጽዳትና ውበት ስራ ላይ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የነዋሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የከተሞች ልማት እየተፋጠነ ያለው ከተሞች ራሳቸው ከሚያመነጩት ሀብት መሆኑን ገልጸው ከተማ አስተዳደሮች ገቢያቸውን በሙሉ አቅም በመሰብሰብ የጀመሩትን ልማት እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ከተማ በተፈጥሮ ያላትን ሀብት ወደ ልማት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኦማቆ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዛሬ የተመረቀው የአስፓልት መንገድ የከተማዋን የአስፓልት መንገድ ሽፋን 46 ኪሎ ሜትር እንዳሳደገ ገልጸዋል፡፡

መንገዱ በከተማው የሚገኙ አራት ክፍለ ከተሞችን እርስ በርስና ከዋናው መንገድ ጋር ማገናኘቱን ገልጸዋል፡፡

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰለሞን ደምሴ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ያቀርቡት የነበረው የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ ጥያቄ ምላሽ እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባስመዘገበችው ፈጣን እድገት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን በማፋጠን ኑሮአቸውን እየተሻሻለ እንዲመጣ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ መስከረም 21/2010 በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለው የልማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በውጪ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ገለጹ፡፡

በጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ሰባተኛ  መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የውጭ አገራት የመጡ የክልሉ ተወላጆች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየታየ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ነው፡፡

ከአሜሪካ እንደመጡ የገለጹት ወይዘሮ ዲድሙ አግዋ እንዳሉት በክልሉ ከዚህ ቀደም የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተስፋፋ ከመሆኑም ባሻገር የነበረውም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም ።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተካሄደ ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ በተሻለ ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።

"ሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እርስ በእርሳቸው የሚገናኙባቸው የመንገድ አውታሮች ተገንበተው በመመልከቴ ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

በውጪ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም  በክልሉ እየተካሄዱ ባሉት የልማትና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አያሳዩ መሆኑን ገልፀዋል ።

አቶ ጋልዋክ ፓል በበኩላቸው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ፍላጎት እነዳላቸው ተናግረዋል ።

ለዚህም በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

በተለይም በሀገሪቱ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጄክቶችን ለመደገፍና የሀገሪቱን ገፅታ በማስተዋወቅ በኩል የድርሻቸውን ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ እየተካሄደ ያለው የኮንስትራክሽን ሥራ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ከመሆኑም በተጨማሪ ለወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን መመልከታቸውን የገለጹት ድግሞ አቶ ጎግ ኡቦንግ ናቸው፡፡

አቶ ጎግ አክለውም "በክልሉ ምንም አይነት የስፖርት ማዘውተሪያ ያልነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት  በግንባታ ላይ ያለው የጋምቤላ ስታዲየም መንግስት በሁሉም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመላካች ነው " ብለዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም መስኮች እየታየ ያለው ለውጥ አበረታች መሆኑን የገለፁት አቶ ጎግ" የተጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 21/2010 የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱ ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የወጣቱ ድርሻ የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ፡፡

በበዓሉ ሥነ ስረዓት ላይ ከተገኙ ታዳሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች  ያነጋገሯቸው ወጣቶችና ሴቶች እንደገለጹት፤ በዓሉ ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል፤ አስደስቷቸዋል።

ወይዘሪት አስናቁ አየለ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ባብች ከተማ በዓሉን ለማክበር በስፈራው ተገኝታለች፡፡

በበዓሉ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታደመችው ወይዘሪት አስናቁ፤ ለበዓሉ ዝግጅት ማድረግ የጀመረችው ከሁለት ወራት በፊት እንደነበር ገልጻለች፡፡

"የኢሬቻን በዓል በጉጉት ስጠባበቅ ነበር የቆየሁት፤ ሥርዓታችንም ያስደስታል" ብላለች፡፡ እርሷም እንደ ሌሎች የኦሮሞ ሴቶች በሆራ አርሰዲ በመገኘት ለአምላክ ምስጋና አቅርባለች።

ወጣቱ የበዓሉን ባህላዊ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ መትጋት እንዳለበትም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

በዓሉን ለማክበር ከቡራዩ ከተማ የመጣው ወጣት ገዳ ዋቅቶላ በበኩሉ፤ "በዓሉ ከሌሎች ጊዜያትበተለየ መልኩ እንዲከበር በወጣቶች፣ አባገዳዎችና የአካበባቢው ነዋሪዎች የተደረገው ዝግጅት ድባቡ ለየት እንዲል አድርጎታል" ብሏል፡፡ 

ከምዕራብ ወለጋ ቦጂ ብርመጂ ወረዳ ለሁለተኛ ጊዜ በዓሉ ላይ የተገኘችው ወጣት ሚሚ መላኩ በበኩሏ፤ በዓሉ በተለይ የሴቶችን መብት በማስከበር ለሴቶች ልዩ ቦታ የሰጠ መሆኑን ተናግራለች።

ስለዚህም ባህሉንና እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጸችው።

''ኦሮሞዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በአንድ በተወሰነ ቦታ ለአምላካቸው ወይም ዋቃ ምስጋና የሚያቀርቡበት በዓል ላይ መገኘት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል''ያለው ደግሞ ከሐረርጌ ሚኤሶ በዓሉ ላይ የተገኘው ወጣት መሃመድ አልይ ነው።

ኦሮሞዎች ለበርካታ ዓመታት በዚህ ቦታ በመሰባሰብ የብራ ብርሃን በማየታቸውና ክረምቱ በሰላም ስላለፈ ለአምላካቸው በአንድ ድምጽ ምስጋና የሚያሰሙበት ቦታ ላይ በመገኘቱ ደስታውን ድርብ እንደሚያደርገውም ነው የገለጸው።

ወጣቱም የኢሬቻን በዓል ሊጠብቅ "እሴትና ቋንቋውን ሊያሳድግ ይገባል" ሲል መልእክቱን አስተላልፏል።

ከአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ከሚሴ የመጡት ወጣት መሀመድ ሰይድና ዘሃራ ቃሲም፤ የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱ ተጠብቆና ተከብሮ ለመጪው ትውልድ መተላለፍ እንዳለበት ነው የገለጹት።

በበዓሉ አባ ገዳዎችም ለምለም ቄጠማ ይዘው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መጪው ጊዜ ሁሉም አንድነቱን ጠብቆ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ የሚኖርበት እንዲሆን ተመርቆ በዓሉ በሰላም ተጠናቋ።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ መስከረም 21/2010 የጋምቤላ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን ) የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ።

ንቅናቄው ያካሄደውን ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል።

ንቅናቄው ጉባኤውን ያጠናቀቀው በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ድርጅቱን የሚመሩ ዋናና ምክትል ሊቀመንበሮችን ጨምሮ 35 ማዕካላዊ ኮሚቴ፣ ዘጠኝ ስራ አስፈፃሚዎችና አምስት የኦዲትና የቁጥጥር ኮሚሽነሮችን በመምረጥ ነው።

እንዲሁም ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስኮች በተከናወኑ እቅድ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

ጉባኤው በተጨማሪ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያና የቀጣይ የልማት ትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይቶ በማጽደቅ ተጠናቋል ።

የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የጸረ ድህነት ትግል በማፋጠን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል።

"በክልሉ በተለይም በመንደር ማዕከላት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝቡን ተጠቃሚ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ" ብለዋል ።

ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ድርጅቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እንደሚሰራም ሊቀ መንበሩ አስታውቀዋል።

"ባለፈው ዓመት በጥልቅ ታሀድሶ በህዝቡ ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ድርጀቱ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል አቶ ጋትሉዋክ።

የድርጅቱ አመራሮችና አባላት ወደ ህብረተሰቡ በመግባት ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማት ስራዎች በህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ  የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የጉባኤው አባላት ባወጡት ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በድርጅቱ ከተሃድሶ በፊት የነበሩ የጠባብነትና ብልሹ አሰራሮች ዳግም እንዳይከሰቱ በመታገል የክልሉን ልማት ለማፋጠን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም የክልሉን የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ጥራት በማስጠበቅ፣ ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ ፣ የገቢ አቅም በማሳደግና በሌሎችም የልማት ዘርፎች በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል ።

በክልሉ ካለፈው ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ወዲህ ቀደም ሲል የነበረው ጠባብ አመለካከትና ቡድኝተኝነት ተወግደው ሁሉም አመራር ወደ ስራ በመግባት የተሻለ ልማት መመዝገቡን የገለጹት ደግሞ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ/ጊምቢ መስከረም 21/2010 የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ጅምር ጥረት ቢኖሩም የሚፈልጉትን ያህል እርካታ እያገኙ እንዳልሆነ የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ።

የምስራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ  ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ትናንት በጊምቢና ነቀምቴ ከተሞች ተካሄደዋል።

በጊምቢ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ በዞኑ ከሚገኙ 20 ወረዳዎችና ከሶስት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።

"ነዋሪዎቹ እንዳሉት መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ ማካሄድ ከጀመረ ወዲህ በሰላም ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር መልካም የሚባሉ ለውጦች ቢታዩም ወደ ምንፈልገው ደረጃ አልደረሰም" ብለዋል ።

በአንዳንድ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ቀጠሮ ማብዛትና ባለጉዳዮችን ማጉላላት ፣ የመብራት መቆራረጥና አልፎ አልፎም ለሳምንታት መጥፋት ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን የነጆና የገንጂ ወረዳ ነዋሪ ተወካዮች ገልፀዋል ።

ወጣቶችን ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴ መጓተትና የመንገድ መሰረተ ልማት አለመስፋፋት ሌላው በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ያስከተለ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የምእራብ ወለጋ ዞን ኦህዴድ ፅህፈት ቤት የገጠር ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦጋለ ሹማ መንግስት ከጥልቅ ተሀድሶው ማግስት ጀምሮ ባደረገው ርብርብ በሁሉም ዘርፎች  ለውጥ ማምጣቱን ገልፀዋል፡፡

ሀላፊው እንዳሉት በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን እርካታ በበለጠ ለማረጋገጥ የጥልቅ ተሃድሶው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፡፡

በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአርሶ አደሮች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

ከኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች መካከል የጊዳ አያና ወረዳ የአገር ሽማግሌ አቶ ጣሃ ማሞ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተካሄደዋል ።

"የአካባቢያቸውን ልማት የበለጠ ለማፋጠን ሰላማችን ከመንግስት ጎን ቆመን መጠበቅ አለብን" ብለዋል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የወሰን ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ ልማት የማይፈልጉ ሃይሎች ከህዝቡ ለይቶ በማውጣት ለህግ እንዲቀርቡና  የተፈናቀሉ ወገኖች መልሰው እንዲቋቋሙ መንግስት የጀመረውጥ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ 05  ነዋሪ ወይዘሮ ርስቴ ጨምር በበኩላቸው "በእንስሳት ግብይት፣ በህገወጥ የመሬት ወረራና የመንገድ ላይ  ንግድ፣ እንዲሁም በወጣቶች የስራ ፈጠራ አፈፃፀምና በመንግስት የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች አስተዳደር ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ይታያል"ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች አስተባባሪ አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንደገለጹት የኦሮሞ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር ለሠላሙ ዘብ መቆም አለበት።

እንዲሁም የክልሉን ልማት ለማፋጠንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት  ከድህነት ለመውጣት መረባረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦች ከአንድ የዘር ግንድ የመነጩ ፣ ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ ያላቸውና ፣ የተወራረሰ ቋንቋና ባህል ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ግጭቱ ኪራይ ሰብሳቢዎች የፈጠሩት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀለበሳል'' ብለዋል፡፡

በሁለቱም ህዝቦች መካከል መሰረታዊ ቅራኔ ሊኖር ስለማይችል የጋራ ጠላቶቻቸውን ለህግ አሳልፈው በመስጠት በመቻቻል ፣ በመፈቃቀርና በመከባበር በሰላም አብሮ መኖራቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

Published in ፖለቲካ

ጅግጅጋ መስከረም 21/2010 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በያዝነው ዓመት 4ሺህ 500 ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ በሚገኙ ቢሮዎች ውስጥ  ያሉ ሰራተኞች ትናንት ደም ለግሰዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሰን ኢስማኤል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ትልቅ ስጦታ በሆነው የደም ልገሳ በመሳተፍ የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ አስተዋፅኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በደም እጦት ለአደጋ የሚጋለጡት ወገኖቻችን ለማዳን የሚደረገው ርብርብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ደም የመለገስ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾችን ለማበራከት በመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ በኃይማኖትና ትምህርት ተቋማት ዘንድሮ 4 ሺህ 500 ዩኒት ደም  ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው 4ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ 48 በመቶ ያህሉ ከበጎ ፈቃደኞች የተገኘና 52 በመቶ ደግሞ ከቤተሰብ በምትክ የተለገሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የደም ባንክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ዙቤር መህዴ አዩብ ናቸው፡፡

"በክልሉ ምትክ የደም ልገሳን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በጎዴ፣ ሀርጌሌና ጅግጅጋ ከተሞች የተጀመሩ የደም ባንክ ማዕከላት ተጠናቀው በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ" ብለዋል፡፡

ማዕከላቱ በየአከባቢው የሚኖሩ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን በበጎ ፍቃድ ደም እንዲለግሱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በእለቱ ደም ከለገሱት መካከል አቶ ከሊፍ ዋሊ መሀመድ በሰጡት አስተያየት "የተቸገሩ ወገኖችን ለመታደግ ደም  በመለገሴ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን