አርዕስተ ዜና

ገደብ የሌለው ባለ ራዕይ

804 times

          በአቢብ አለሜ/ኢዜአ/

መሃል አዲስ አበባ ካዛንችስ አካባቢ ነኝ።ከውጪ ለሚያያት አልፎ ሂያጅ ደሳሳ መሳይ በሯ ላይ የሳር ክፍክፍ ያለባት ቤት ውስጥ እግሬ ገብቷል።

በዚህች ቤት መገኘቴ ያላንዳች አይደለም፤ ትልቅ ጉዳይ ነበረኝ። የኢትዮጲያን ሙዚቃ ለዓለም መድረክ በማስተዋወቅ ላይ ያለ አንድ የባሕል ቡድን መሪና ተወዛዋዠን ስለ ኪነ ጥበብ ለማውጋት ነበር።

ፈንድቃ የሚል ጽሑፍ ከሳር ክፍክፉ ላይ ማንበቤን ሳስታውስ እውን ከዚህ ቤት ነው ይሄንን ያህል ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሙዚቀኞች መፍለቅ የቻሉት ስል ራሴን ጠየቅሁ።

ፈንድቃ ለሚለው ቃል ስቃ፤ ተደስታ፤ ዘና ባለ ስሜት ሆና፤ ፊቷን በፈገግታ ሞልታ የሚል ክርክር አልባ ትርጓሜ ሰጥተነው ልናልፍ እንችላለን።

ነገር ግን ፈንድቃ በጎጃምና በጎንደር መካከል የምትገኝ ቦታ ሥያሜ ነው። ታድያ ምሽት ቤቱ ይህንን ስያሜ እንደያዘ ለ27 ዓመታት ባሕላዊ ሙዚቃን በማቅረብ የዘለቀ፤ የኢትዮጲያን ቀደምት ባሕላዊ የአዝማሪ ሙዚቃ ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ የተጓዘ ትልቅ ባህላዊ የምሽት ቤት ነው።

ጠባቧንና ምሽት ላይ መውጫ መግቢያ የሚጠፋባትን ነገር ግን ቱባ ባህል የሚቀዳባትን የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት አቋርጠን ያሸበረቁ ባሕላዊ እቃዎችና ስእሎችን እያየን ከመላኩ በላይ ጋር ወደ ጓሮ በር አለፍን።

ወደ ጓሮ ያቀናነው ልንነጋገርበት ያሰብነውን ጉዳይ ዘወር ብለን ሳንረበሽ ለመከወን እንዲያመቸን በማሰብ ነበር።

ወደ ጀርመን ለመሄድ ሲጣደፍ ነበር በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ያገኘሁት። ጸጉሩ የቀድሞ አርበኛ መሳይ ነው። ጠጋ ብላችሁ ስታወሩት ደግሞ ያ ቴሌቪዢን ላይ ወይም በአካል ሲጨፍርና ሲወዛወዝ ያያችሁት ወጣት አይመስላችሁም። ትሑት፤ፈገግታና እርጋታ የሞላው ሆኖ ታገኙታላችሁ።

ቁጭ ብለን መጨዋወት ጀምረናል። ከተቀመጥንበት ጎን ፈንጠር ብለው ማሲንቆ የያዙ ወጣቶች ጢሪሪሪ--- ጢሪሪሪ እያደረጉ ይገርፉታል። ለምሽት መርሀ ግብራቸው ልምምድና ጥናት ላይ መሆናቸው ነው።

መላኩ ማሲንቆ ወደ ያዘ አንድ ታዳጊ ወጣት እያመላከተ "እየው ይሄንን ልጅ" አለኝ፤ ልጁ 15 ዓመት ገደማ የሚሆነው ቀይ ለግላጋ ነው። "ከላሊበላ ነው መንገድ ላይ ሲጫወት አግኝቼው ያመጣሁት አሁን ጎበዝ ተጫዋች እየሆነ ነው" አለኝ። የኪነ ጥበብ ተተኪዎችን የማፍራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም አወጋኝ።

እየተጨዋወትሁ ያለሁት ለ20 ዓመታት ያህል በፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት ውስጥ ተወዛዋዥ ሆኖ የሰራና አሁን ላይ "ኢትዮ ከለር" የተሰኘ ባሕላዊ የሙዚቃ ባንድን መስርቶ፤ ቤቱን በአዲስ መልክ በማስፋፋት በባለቤትነት እየሰራ ካለው የሙዚቃ ሰው፣ ዳንሰኛና ተወዛዋዠ መላኩ በላይ ጋር ነው።

መላኩ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው፡፡ የትኛውም ትምህርት ቤት ገብቶ ውዝዋዜን አልተማረም። ከእስክስታ ጋር ያስተዋወቁት ልዩ ልዩ የህዝብ በዓላት፣ ጥምቀትና ሠርግ ቤቶች ናቸው፡፡ የእርሱን የህይወት ታሪክ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዳሰውታል። አምስት ዶክመንተሪ ፊልሞች ተሰርተውለታል፡፡

በፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት 12 ዓመታት በታዳሚ ሽልማት ብቻ ሰርቷል። ሌላ ቦታ ተቀጥሮ መስራት ቢችልም ነፍሱ ጋር የተጣባችው እስክስታ ከፈንድቃ እንዲርቅ አልፈቀደችለትም።

በኋላም የኢትዮጵያ ባህልና ማንነት ሳይበረዝና ሳይከለስ ዓለም እንዲያውቀው የማድረግ ትልቅ ውጥን ይዞ ተነሳ፡፡ ተሳክቶለትም ወጣት አዝማሪዎችን ከቴአትር ቤትና ከፈንድቃ የባሕል ምሽት እየወሰደ በአሜሪካ፤ በአውሮፓ፤ በአፍሪካ፤ በሩቅ ምስራቅ አገራት ተዘዋውሮ አገሩን በስፋት አስተዋውቋል።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኪነ ጥበብ አውደ ርዕይ ማሳያ ማዕከል መስርቶ የስዕል፤ የቅርጻ ቅርጽና የንድፍ ስራዎቻቸውን ማሳየትና ማስተዋወቅ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ወጣቶች በየወሩ ስራዎቻቸውን በነጻ እንዲያቀርቡበት አድርጓል።

በዚህ የኪነ ጥበብ ማሳያ ማዕከል ቀድሞ ስራዎችን የሰሩና አሁን በጡረታ ላይ ያሉ የኪነ ጥበብ ሰዎች፤ እንዲሁም መድረክ ያጡ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ያሏቸው ወጣቶች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።

በዚህ ማዕከል በወር አንድ ጊዜ ስለ ንባብ  ውይይት የሚደረግበትና የግጥም ዝግጅቶች የሚቀርቡበት መድረክ በማዘጋጀትም ሕብረተሰቡ ለንባብና ለኪነ ጥበብ ያለው ስሜት እንዲነሳሳ እያደረገ ይገኛል።

ጭፈራን በራሱ መንገድ መጫወት እንደሚያስደስተው የሚናገረው የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ባለቤት መላኩ በላይ "በሰውነቴ እንቅስቃሴና በጭፈራዬ ሁኔታዎችን እገልጻለሁ"ይላል። ሲጨፍር በሰውነቱ ጊዜን፤ ሀዘንን፤ ደስታን፤ ችግርን፤ እለታዊ ሁኔታውን መግለጽ እንደሚያስደስተውም ይናገራል።

በሰው ውስጥ ያለውን ስሜት፣ያስደሰተውን ጉዳይና ልዩ ልዩ ሁነቶችን በራሱ መረዳት መጠን ከምንም አይነት ድምጽ ጋር አዋህዶ በውዝዋዜ መግለጽ መቻሉ የመላኩ ትልቁ ችሎታው ተደርጎ ይወሰድለታል።

ለዚህም መርካቶ ምናለሽ ተራ አካባቢ ካሉ ብረት ቀጥቃጮች ጋር የሰራው ውዝዋዜ፤ ስሜትን አንዴት አድርጎ ከድምጽ ጋር ማዋሐድ እንደሚቻል አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

"አሁን" የሚል ስያሜ በሰጠው በዚህ ዝግጅቱ ላይ ሁሉም ብረት ቀጥቃጮች የራሳቸውን ስራ እየሰሩ፤ ትልቁ ስራና ሐላፊነት ድምጽን ሙዚቃ የማድረጉ ተግባር ደግሞ በተወዛዋዡ ላይ የወደቀ እዳ ነበር።

የብረትና በርሜል ድምጽን ወደ ሙዚቃነት መቀየር ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም እኔ ግን ስሜቴንና ሙዚቃን ለማገናኘት ተጠቅሜበታለሁ ይላል።"የሰውነት ቋንቋ ሙዚቃን ሰዎች አውቶቡስ ላይ ሲሄዱ፤ መብራት ሲሰሩና ሌሎች ተግባራትን ሲከውኑ መስራቱንም ይናገራል።

እሱ በተወዛዋዥነትና በመሪነት ኢትዮ ከለር ባንድ ደግሞ አጃቢ በመሆን በርካታ ሙዚቃዎችን ለዓለም ህዝብ አቅርቧል፤ አሁንም እያቀረበ ይገኛል።

በነዚህ ስራዎቹ የራስን ቀለም ለማሳየት ይረዳው ዘንድም የአገሪቷን የተለያዩ ሙዚቃዎች ባሕርያትና ምንነት ጥናት ማድረጉንም ይናገራል።

ይሁን እንጂ የብሔረሰብ ሙዚቃዎችን እንደ ማሕበረሰቡ አድርጎ መስራት ባይቻልም እንኳን የኢትዮጲያን ሙዚቃ፣ ባሕል፤ ታሪክ ማንነቱን ሳይለቅ በራሱ መንገድ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቁን ይገልጻል።

ኢትዮጵያ የረሀብና የችግር መግለጫ ተደርጋ መጠቀሷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን በመጥቀስ ይህንን መጥፎ ምስል ለመቀየር ትልቅ ስራ ሰርተናል ሲል በኩራት ይናገራል።

አሁንም ገና ብዙ ስራዎች የሚጠበቁን በመሆናቸው በሙዚቃ አማካኝነት እየሰራን ያለነውን የገጽታ ግንባታ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ይላል።

መላኩ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያቀረባቸው የሙዚቃ ስራዎች በርካታ የውጪ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና በሙዚቃው፤ በአኗኗሩ፤ በኪነ ጥበቡ ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ ምክንያት መሆኑንም አጫውቶኛል።

ከማንም፤ ምንም ነገር እንደማይጠብቅና ሁልጊዜ ከለውጥና ከአዳዲስ ነገሮች ጋር በፈጠራ መንገድ መጓዝ እንደሚያስደስተው ይናገራል። "ለምወደውና ላመንኩበት ነገር መኖር የሕይወቴ መርኅ ነው" ይላል።

"ራእይ ማብቂያና ገደብ የለውም" የሚለው መላኩ አሁንም በቻይና፤ በርሊን፤ ሮም፤ ፓሪስ፤ ቶኪዮና ኒዮርክ የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ቅርንጫፍ ከፍቶ ኢትዮጲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ሕልም አለው።

በየክፍላተ አህጉራቱ ሁሉ ፈንድቃ የባሕል ምሽት ቅርንጫፍ እንዲኖረው እፈልጋለሁ የሚለው መላኩ ቀጣይ በናዝሬት፤ ባሕርዳር፤ በደብረ ማርቆስ፤ ጎንደር፤ ላሊበላ፤ ሐዋሳ፤ አርባ ምንጭና በሌሎችም አካባቢዎች ከፍቶ ባሕልንና ማንነትን ማስተዋወቅና፤ የሕብረተሰቡን የኪነ ጥበብ ፍላጎት የማርካት ብርቱ ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል።

ፈንድቃን በሀገር ውስጥ የማስፋፋቱ ዋና ምክንያትም በተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ወጣት አርቲስቶች እድሉን ለማመቻቸት፤ ለሙዚቃ ያላቸውን ፍላጎት ለማነሳሳት፤ ያላቸውን ነገር እንዲወዱት ለማድረግ፤ ያደጉበት ባሕል ትልቅ ዋጋ እንዳለው እንዲገነዘቡ ለማስቻል መሆኑን ይናገራል።

ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ያለውን ጽኑ ፍላጎት እውን ለማድረግ ሁነኛ አማራጭ መሆኑንም ያብራራል። ፈንድቃ ኢላማ አድርጎ የተነሳው ባሕልን በኪነ ጥበብ ለማበልጸግ ነው የሚለው መላኩ ሁልጊዜ ራሳችንን መመልከትና ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ አትኩረን መስራት ይገባናል ይላል።

ኢትዮጵያ ብዙ የሚያኮራ ባሕል፣ ታሪክ፤ ሙዚቃና ማንነት ያላት አገር በመሆኗ እነዚህን ሀብቶቿን ለማጉላትና ለማስተዋወቅ በኪነ ጥበብ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚቻልና እንደሚገባም ጭምር ይገልጻል።

በዚህ ረገድ አዝማሪዎች እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ያብራራል። አንድነት፤ ቁጭት፤ ፍቅር፤ ሰላም፤ ተስፋ፤ ደስታ፤ ብልጽግና፣ ማስታረቅ፤ ታሪክን ስለመጠበቅ፤ ጎጂ ነገሮችን ስለመቅረፍ፣ አገርን ስለመጠበቅ ወዘተ ያሉ ጉዳዮች አዝማሪዎች ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩባቸው ጭብጦች መሆናቸውን በማሳያነት ያነሳል።

ይሁን እንጂ አዝማሪዎች ከሙዚቃ አድማጩና ተመልካቹ የሚያገኙት ገንዘብ ሕይወትን ለመደጎም የሚበቃ ባለመሆኑ በፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ውስጥ የሚሰሩ አዝማሪዎችን በወር 2ሺሕ ብር እየከፈላቸው ይገኛል።

ዓለም አቀፍ እውቅናና ተፈላጊነት ያለው ፈንድቃ የባሕል ምሽት በሰራቸው አያሌ ስራዎች በፈረንሳይ የባሕል ሚኒስቴር የክብር ሜዳልያ ሽልማትና እውቅና ተበርክቶለታል።

"እያገኘን ያለነው ዓለም አቀፍ እውቅና ቢያስደስትም መንግስት ሀገራዊ ባሕልን ለመደገፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አናሳ መሆኑ ግን ያሳዝነኛል" የሚለው መላኩ ለባህልና ኪነጥበብ ትኩረት መሰጠት አለበት ይላል።

ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፈንድቃን እንደማያውቀው በመጥቀስ ዓለም አቀፍ ብዙኋን መገናኛ የሆኑት ቢቢሲ፤ ሲኤንኤን እና ሌሎችም እየመጡ  ሲዘግቡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት አለመስጠቱ  እንደሚያሳፍረውም ገልጿል።

ለ20 ዓመታት ባሕልን፤ ሙዚቃን፤ ኪነ ጥበብንና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ብዙ የተጓዘው መላኩ በርካታ ችግሮችን በግሉ ተቋቁሞ አልፏል። "መንግስት ምን ችግር አለብህ ብሎ ቢጠይቀኝና ቢረዳኝ የት በደረስኩ ነበር" ሲልም ቁጭት አዘል ጥያቄውን ያክላል።

እኔም "ራእይ ማብቂያና ገደብ የለውም" የሚለው መላኩ ተተኪ ወጣቶችን በማፍራትም ሆነ ኪነ ጥበብን በማስተዋወቅ ረገድ ሊሰራ ያሰበው እንዲሳካለት በመመኘት ቱባ ባህል የሚቀዳባትን የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ተሰናብቼ ወጣሁ።

 

Last modified on Tuesday, 13 February 2018 23:43
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን