አርዕስተ ዜና

የተለየ ህብረት የሚሻው የህብረቱ የዕድገት ሳንካ- ሙስና

4185 times

                             በሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

ዋሽንግተን ፖስት በአንድ ወቅት ባወጣው እትሙ በደቡብ አፍሪካ አንድ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎቸ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ወጥተው ማስቲካና ከረሜላ ለመግዛት ሲፈልጉ  የጥበቃ ሰራተኛውን በገንዘብ ይደልሉት እንደነበር አስነብቧል፡፡ ይህም በሃገሪቱ ሙስና ምን ያህል ከስር ጀምሮ እየተኮተኮተ በማደግ ባህል ሊሆን ወደ ሚችልበት ደረጃ እንደደ አመላካች   መሆኑን በዘገባው ጠቅሷል፡፡

በአንድ ወቅት እንዲት የዘጠኝ ዓመት የዚምባቡዌ ህጻን ሀገር አማን ብላ ወደ ትምህርት ቤት በማምራት ሳለች በአንድ ግለሰብ ትደፈራለች፡፡ ይባስ ብሎ ደፋሪዋ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ በደሙ ውስጥ ስለነበረበት በለጋ እድሜዋ የበሽታው ተጠቂ ሆነች፡፡ ደፋሪዋ ለህግ ቀርቦ ወህኒ ቢወረወርም ለወህኒ ቤቱ የጥበቃ አካላት መደለያ ሰጥቶ ከእስር ቤቱ በምስጢር ሲወጣ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ይሄኛው ድርጊት ደግሞ ሙስና ለፍትህ መዛባት ምን ያህል በር እንደሚከፍት በግልጽ ያሳያል፡፡ ለማሳያነት እነዚህን አነሳን እንጂ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሙስናና መገለጫዎቹ እጅጉን በርካታ ናቸው፡፡

የዓለም ሃገራትን የሙስና ደረጃ እየገመገመ በተለያየ ጊዜ ሪፖርቶችን የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው አለም አቀፍ ተቋም እኤአ በ2015 ብቻ ከሰሃራ በታች የሚኖሩ የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ውስጥ 75 ሚሊዮን የሚጠጉት ጉዳያቸውን ለማስፈፀም አላስፈላጊ ጉርሻ ተጠይቀው ከፍለዋል። እንደ ጥናቱ ጉቦው የተከፈለው ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ቅጣት ለማምለጥ እንዲሁም አብዛኞቹ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲባል ነው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ቬራ ሶንግዌ ሙስናን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “ሙስና አፍሪካን እየበላት ነው፤ የአፍሪካ ወጣቶች ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልጋል” ብለዋል። ከፋይናንስ ወጪና ገቢ ጋር በተያያዘ ብቻ አፍሪካ በያመቱ 50 ቢሊዮን ዶላሮችን እያጣች መሆኗን ገልጸው ወጣቶችም ጉዳዩን በቸልታ እየተመለከቱት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንቴግሪቲ የተባለ ተቋም የአለም ባንክን ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው  አፍሪካ ከሙስና ጋር በተያያዘ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ታጣለች። ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የወጣ ሌላ መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ ሙስና አህጉሪቱን  በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር ያሳጣታል። የገንዘቡ መጠን አጠቃላይ ከአህጉሪቱ ጥቅል ምርት መጠን 25 በመቶውን ይይዛል።

በአፍሪካ ለደሃው ማህበረሰብ ሊዳረሱ የሚገባቸው የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች በሙስና ምክንያት እየተስተጓጎሉ በርካቶች ለስቃይና ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ስንመለከት ችግሩ እጅጉን አሳሳቢና ፈጣን ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡

አፍሪካ በሙስና ምክንያት የምታጣው ሃብት የአህጉሪቱን ጥቅል ምርት እድገት በ0.13 በመቶ እየጎተተው መሆኑን ያብራሩት ሚስ ሶንግዌ  የተቋማት የማስፈፀም አቅም መላላት እንዲሁም በዚሁ ሳቢያ የሚፈጠር የተጠያቂነት ማነስ ሙስና ጉልበቱን እንዲያፈረጥም እንደረዳውም ነው ያብራሩት፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው የፈረንጆቹ 2018  አህጉሪቱ ሙስናን የምትዋጋበት ከመሆኑም ባለፈ የተለያዩ የሪፎርም ውሳኔዎች የሚተላለፉበት አመት እንደሚሆን ተናግረዋል። ለዚህም  ህበረተሰቡን ወደ ብልፅግና የሚወስዱ ጠንካራ ተቋማትን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

“ሙስና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን የመመስረት ሂደትን እንዲሁም ማህበረ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦችን ብሎም ሰላምና ደህንነትን የማስፈን ጥረትን ያዳክማል።” ብለዋል ሙሳ ፋቂ ማሃማት።

የተለያየ ስርዓተ መንግሥት ባላቸው የአፍሪካ ሀገራት የተንሰራፋው ሙስና ከየሀገራቱ ስርዓተ መንግስት ጋር ራሱን አስማምቶ የየሀገራቱ ሳንካ ሆኖ ውሎ አድሯል፡፡ ዴሚክራሲያዊ ስርአትን በገነቡ ሃገራት የሚፈፀመው የሙስና አይነት አምባገነናዊና የሃሳብ የበላይነት ጠላታቸው በሆኑ መንግስታት ከሚታየው የማጭበርበር አይነት በእጅጉ የተለየ ነው። ሁለቱንም አይነት መንግስታት በውስጧ ይዛ የምትገኘው አህጉረ አፍሪካ ለችገሩ መላ ስታበጅ እንደየባህርያቸው መሆን እንዳለበትም አያጠያይቅም።

ህብረቱ በመንግስትም ሆነ በግለሰብ መዝባሪዎች የሚፈጸሙ የዝርፊያ ተግባራት በተስፋፉበት በዚህ ወቅት ሙስናን የውይይት አጀንዳ ማድረጉ ከተገቢም በላይ ነው፡፡ ከቀናት በፊት የተጠናቀቀው  30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “ዘላቂ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለአፍሪካ ስር ነቀል ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል፡፡ በህብረቱ ጉባኤ ሙስናን የተመለከተ መሪ ሃሳብ  የውይይት አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሙስና እያደረሰ ባለው ቀውስ ዙሪያ ከመነጋገርና ድርጊቱን በአጽንኦት ከማውገዝ ባለፈ  መንግስታትና የሚመለከታቸው አካላት ወደ ተግባር ሊቀይሯቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ከፊቶቻቸው መደቀናቸውንም ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።

ሙስናን በመዋጋቱ ሂደት መንግሥታት የስራ አጦችን ቁጥር የመቀነሱን ተግባር ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊያደርጉት ይገባል፡፡ የወጣቶች አህጉር እየተባለች በምትጠራው አፍሪካ ወጣቶች ስራ አግኝተው የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ማድረግ የተቀደሰ ሃሳብ ከመሆኑም ባለፈ ሃገራት ለትግበራ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ሊያስቀምጡት የሚገባ ጉዳይ ነው። በዘንድሮው የህብረቱ ጉባኤ ላይ  ከተነሱት ጉዳዮች የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ በማሳደግ የአህጉሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ጉዞ የተሳለጠ ማድረግ አንዱ ነውና የግሉም ክፍለ ኢኮኖሚ ለወጣቶች የስራ ዕድልን የማመቻቸት ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቃል። የወጣቶችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ክህሎት የማዳበሩም ስራም መዘንጋት አይኖርበትም።

አፍሪካ በሁሉም የመንግስት የአስተዳደር እርከን ውስጥ የሚታየውን ያለአግባብ የመጠቀም አዝማሚያ የመግታቱን ጉዳይ ጊዜ ልትሰጠው አይገባም። በተለይ በታችኛው የአስተዳደር ደረጃ ላይ የሚስተዋለውን ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። በፍትህ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ተጋሪ እንዲሆኑ በማድረግ የፍርድ ሂደቶች እንዳይዛቡ ማድረግም አንዲሁ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባውም። በየስራ ዘርፉ የሚስተዋሉ የተጭበረበሩ አሰራሮችን ለማረም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ሊነደፉ ይገባል። ጎን ለጎን ደግሞ ሁለቱንም አይነት ሌቦችን (የመንግስትና የግለሰብ) አደብ ሊያስይዝ የሚችል ህግ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ከአባል ሃገራቱ ይጠበቃል።

በተጨማሪም እያንዳንዱ የህብረቱ አባል ሃገር ሙስናን የሚከላከል ወይም የፀረ ሙሰና ተቋም ማቋቋም ይኖርበታል፤ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን እንዲበቃ ማድረግና በፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ውስጥ ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰራ ማድረጉም እንዲሁ ለማለት ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ መሆን የለበትም። ተቋማቱም በተደራጀና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ሆነው መመስረት ይኖርባቸዋል።  ህብረተሰቡ ገንቢ የሆነ ሚና እንዲጫወት የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተውላችው ሊደራጁም  ይገባል።

መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሙስና በሃገር ብሎም በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ሊያደርስ ስልሚችለው ጠንቅ ሳይታክቱ መስበክ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ፀረ ሙስና አመለካከትን ይዞ ሙስናን በመዋጋቱ ሂደት የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በየተቋማቱ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በምርመራ ጋዜጠኝነት በማጋለጥ የተጠያቂነት አሰራር በተጠናከረ መሰረት ላይ እንዲገነባ መስራት ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል መገናኛ ብዙሃኑ ከወትሮው የተሻለና የተለወጠ አስተሳሰብ ይዘው ሙስናን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ሌት ተቀን መትጋት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን መረዳት ያሻል።

ማላዊን እኤአ ከ2004 እስከ ዕለተ ሞታቸው 2012 ዓ.ም በፕሬዝዳንትነት ያስተዳደሩት ቤንጉዋ ሙታሪካ ሁሌ የሚታወሱበት አንድ ጠንካራ ሃሳብ ነበራቸው። ‘’African dream is not one person dream. It’s a dream of all people’’ “የአፍሪካውያን ህልም የአንድ ሰው ህልም ሳይሆን የመላው አህጉሪቷ ህዝቦች ህልም ነው” እንደማለት ነው። ስለሆነም አፍሪካውያን በህብረት ያለሙትን ህልም በህብረት እውን ለማድረግ ከፊታቸው የተጋረጠውን ሙስና የተባለ ሳንካ መንቀል ይጠበቅባቸዋል። ህብረታቸውን በሚገልፀው አመታዊ ጉባኤ ላይ ድርጊቱን ማውገዛቸውም ከምንጊዜውም በላይ ወቅታዊና ቀበቷቸውን ጠበቅ አድርገው ለመዝመት  የቀድሞውን ፕሬዝዳንት መልዕክት የጥንካሬ እርካብ ሊያደርጉትም ይገባል።        

ሙስናን የመዋጋቱን ተግባር ለህብረቱ ብሎም በህብረቱ ውስጥ ለሚገኙ ሃገራት ብቻ መተው ሳይሆን እያንዳንዱ የአፍሪካ ዜጋ ከሙስና ተግባር በተቃራኒው ሊቆም  ይገባል። ለመቋጨት ያህልም ዘንድሮ የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት ለመምራት የተመረጡት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ  በስልጣን ዘመናቸው የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተው ለዚህም የህብረቱን አባል ሀገራት መሪዎች ድጋፍ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካውያን መሪዎችም ለአፍሪካ መሻሻል ይረዳሉ ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመከሩበት 30ኛው ጉበዔ ለአህጉሪቱ ሪፎርም  ይበጃሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ከተናጠል ይልቅ በህበረት መንቀሳቀሱ አዋጪ መሆኑን ተስማምተውበታል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን