አርዕስተ ዜና

'የጤናው ዘርፍ ፈተና........ '

4577 times

አስቴር ታደሰ (ኢዜአ)                     

አንድ አባባል አለ፤ ‘መድሃኒት ያድናልም ይገላልም’ የሚል። ዛሬ አለም ከደረሰችበት የስልጣኔ ጣሪያ ጋር አብሮ የሚሄድ የዘመነና እጅግ ፈዋሽ መድሃኒት እየተመረተ ለገበያ እየዋለ በርካታ ግለሰቦች ጤናቸውን መጠበቅ ችለዋል። የተሻለ የመፈወስ ዓቅም ያላቸው መድሃኒቶች ለገበያ መብቃታቸውን የሰው ልጅ የመኖር እድሜ ጣሪያ ከፍ እንዲል አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው። መድሃኒት የማዳኑን ያህል የከፋ ጉዳት የሚያደርስም ሊሆን ይችላል።

መድሃኒት ጥራቱን ጠብቆ ካልተመረተ የመፈወስ አቅሙ መዳከም ብቻ ሳይሆን ለጤና መቃወስ የሚዳርግ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። የመድሃኒት የፈዋሽነት ዓቅም መዳከም መንስዔዎች ብዙ ቢሆንም መድሃኒት ከሚያመርቱ ተቋማት ውጪ በህገወጥ መንገድ ተመርተው ወደገበያ መቀላቀላቸውና የሃሰተኛ መድሃኒት አምራቾች መበራከት ነው። በቅርቡ የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ላይ ሃሰተኛ መድሃኒት የቀጣዩ ጊዜ የህብረተሰብ ጤና ስጋት ምንጭ ሊሆን እንሚችል አመላክቷል።

በአለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመጣው ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የተሻሻሉና የሰው ልጆችን ስቃይ ቀንሰው  ህይወትን የሚታደጉ መድሃኒቶችይፈበረካሉ። መንግስታትም መድሃኒቶች እንዲመረቱና ሕዝቦቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ጠንካራ የሚባል ስርአት ይዘረጋሉ። እነዚሁ አገሮች በዓመት ለመድሃኒት ግዥ በቂ የሚሆን በጀት መድበው የመድሃኒት አቅርቦቱ ተደራሽ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። መንግስታቱ  ለግዥ ብቻ ሳይሆን ለመድሐኒት የምርት ሒደት ድጋፍ ለማድረግም ትኩረታቸው ከፍ ያለ ነው። የዚህ ድጋፍ ውጤትም የአንድን አገር የጤና አገልግሎት በማሳደግና በተለያዩ ሕመሞች ተይዘው የሚሞቱ ሰዎችንም ቁጥር ከመቀነሱም ባሻገር የገቢ ምንጭን ያሳድጋል።

መድሐኒት በበቂ ሁኔታ መመረቱ ደግሞ ታማሚዎች የከፋ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትና ከገቡም በኋላ በፍጥነት እንዲፈወሱ ያደርጋል፤ በምድር ላይ የሚኖሩበትን እድሜም ወይም የእድሜ ጣራቸውን በማራዘም ረገድ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ነገር ግን በተቃራኒው በአሁኑ ወቅት ባደጉትም ሆነ ባላደጉት አገሮች ከደረጃ በታች የሆኑ መድሃኒቶች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት እያሳሰበ ነው። ድርጅቱ በዚሁ መስክ በቅርቡ ባወጣው መረጃ የሐሰት ወይም ተመሳስለው የተመረቱ መድኃኒቶች ሕገወጥ ንግድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ቀጥሎ ትልቅ ገንዘብ የሚዘዋወርበት እየሆነ መምጣቱን ነው ያስታወቀው።

በዚህ መስክ አምራቾችና ጅምላ አከፋፋይ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አዘዋዋሪዎች፣ ቸርቻሪዎችና ተጠቃሚዎች ያሉበት ሲሆን፣ በተለይ የአዘዋዋሪዎቹ ብዛትና አቅም ከፍተኛ መሆኑ ችግሩን ስር የሰደደ እንዲሆን አድርጎታል። እነዚህ አካላት በየአገሮቹ ፖሊሲና ሕግ እስከማስቀየር የሚደርስ ጡንቻ አላቸው፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ወይም አንድ አካል በአግባቡ እንዳይንቀሳቀስና እንዲዳከም ማድረግ የሚያስችል ተግባራትን ለማካሔድም አቅም እንዳላቸውም የድርጅቱ መረጃ ይጠቁማል።

ሆኖም  ሪፖርቱ በዓለም በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙት የአፍሪካ አገሮች የሐሰት ወይም ተመሳስለው የተሠሩና ከደረጃ በታች የሆኑ፣ ጥራታተውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች እየተሰራጩ መሆኑን አረጋግጬያለሁ ብሏል። የዚህ ድርጊት ወትሮም በፈተና የተተበተበውን የጤና አገልግሎት የበለጠ በማወሳበሰብ ነገሩን ሁሉ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል።

በሐሰትና ከደረጃ በታች በሆኑ መድሐኒቶች ምክንያት በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ብቻ 72 ሺሕ ሕፃናት ከሳንባ ምች፣ 69 ሺሕ አዋቂዎች ደግሞ ከወባ በሽታዎች መዳን አቅቷቸው ሞተዋል፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ከሚቀርቡ መድኃኒቶች አንድ አሥረኛ ያህሉ የውሸት፣ በሽታን የማያድኑና ጥራታቸውም ከደረጃ በታች መሆናቸውን ድርጅቱ እንደደረሰበት ይጠቅሳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቅርቡ እንደገለጹት፤ የውሸት መድኃኒት የዓለም ፈተና ነው። በተለይ እአአ ከ2013 ወዲህ በአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሐሰትና ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች ገበያ ላይ ስለመዋላቸውና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ስለመሆናቸው ነው፡፡

በዚህም ሳቢያ ከ2013 ወዲህ ብቻ ለድርጅቱ 1 ሺ 500 የሐሰት ወይም የጥራት ደረጃቸው የወረዱ መድኃኒቶች ስለመገኘታቸው ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከእነዚህ ሃሰተኛ መድኃኒቶች ውስጥ ሕዝብ በአብዛኛው የሚጠቀምባቸው ፀረ ተዋህስያን (አንቲባዮቲክስ) ይገኙበታል፡፡ በተለይ በመካከለኛና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ አገሮችን የሚፈትነውን ወባ ለመቆጣጠር ከሚውሉ መድኃኒቶችም የሐሰት መድሃኒት ስለመኖሩ ተደጋጋሚ መረጃ ለድርጅቱ ደርሷል።

ለድርጅቱ ከደረሱ ከነዚህ ጥቆማዎች ውስጥ 42 በመቶው ከአፍሪካ፣ 21 በመቶው ከአሜሪካ እንዲሁም 21 በመቶው ከአውሮፓ ናቸው፡፡ ለድርጅቱ የቀረበው ሪፖርት በዓለም ይሰራጫል ከሚባለው የሃሰት መድኃኒት ቅንጣት ያህሉ ብቻ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡ ከምዕራብ ፓስፊክ ደግሞ ስምንት በመቶ፣ ከምሥራቅ ሜዲትራኒያን ስድሰት በመቶ እንዲሁም ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ሁለት በመቶ ብቻ ሪፖርት መደረጉም ችግሩ ግዙፍ ቢሆንም መረጃው በትክክል እንደማይደርስ ነው የተገለፀው።

በዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒትና ክትባት ተደራሽነት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ማሪኒላ ሲማው እንደሚሉት፣ የሐሰት መድኃኒቶች የሚያደርሱት ጉዳት በሕሙማኑና በታማሚዎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም በሽታን እየተላመደ ያስቸገረውን ባክቴሪያ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ የተጋረጠ ፈተና ነው፡፡ መድኃኒት የማዳን ኃይሉ እየቀነሰ በመጣበት በዚህ ወቅትም የውሸትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመድኃኒት ዓይነቶች እየተሠራጩ መሆናቸው ለጤናው ዘርፍ ፈታኝ ሆኗል፡፡

በተለይ በታንዛኒያና በናይጄሪያ የሐሰትና ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶች ዝውውር ከአሥር በመቶ በላይ በመሆኑ የችግሩ ስፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደሚሉት፤ በአገራችን ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ መድኃኒቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ቁጥጥር ይደረጋል። መድኃኒቱ ለገበያ ከመሠራጨቱ በፊት የላቦራቶሪ ጥራት ምርመራ እንደሚካሔድና ገበያ ላይም ከዋለ በኋላም የድህረ ገበያ ቅኝት እንደሚሠራና የሐሰትና ተመሳስለው የተመረቱ ወይም ደረጃቸውን ያልጠበቁት እንደሚለዩ ይናገራሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ባደረገው ምርመራም፣ በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ጋምቤላ ክልል አንድ የፀረ የወባ መድኃኒት የሀሰት ወይም ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቶ ነበር፡፡ በወቅቱ መድኃኒቱ በኮንትሮባንድ አዲስ አበባ  እንደገባና ጋምቤላ ውስጥ ሲሸጥ እንደተገኝም ነው የገለጹት።

ባለሥልጣኑ በተለይ ኅብረተሰቡ በብዛት የሚጠቀምባቸው ፀረ ተዋህስያን፣ ፀረ-ወባና ሌሎችም “ችግር ሊያመጡ ይችላሉ” የሚባሉ መድኃኒቶችን በመለየትና በላቦራቶሪ በመመርመር ችግር ያለባቸው ከሆኑ ለገበያ እንዳይቀርቡና ከቀረቡም ወዲያው እንዲሰበሰቡ ያደርጋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው፣ ተመሳስለውም ሆነ ከደረጃ በታች የሚሠሩት መድኃኒቶች ሕብረተሰቡ ይጠቀምባቸዋል ተብለው የሚገመቱት መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆኑ የካንሰር መድኃኒቶችን ጨምሮ በውድ ዋጋ የሚገዙትንም ያካትታል፡፡

“የመድኃኒቶችን ትክክለኛነትና ፈዋሽነት ማረጋገጥ እንደ አገር ከፍተኛ ወጪና ባለሙያ የሚጠይቅ ነው” ይላሉ አቶ ገዛኸኝ፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ ከመንግስት የሚመደብለትን በጀት ጨምሮ የሕብረተሰቡን  ጤና ለመጠበቅ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል።

የሐሰተኛ መድኃኒቶች ዝውውር ደረጃ ይለያይ እንጂ በሁሉም አገሮች የሚከሰት ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ የወባ በሽታ መድኃኒቶች እስከ 65 በመቶ ድረስ የሚሆኑት ተመሳስለው በመሠራታቸው በየዓመቱ ከ100 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መዳን ሲችሉ ፈዋሽ ያልሆነ ነገር እየወሰዱ ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

በዓለም ደረጃ በወባ በሽታ ብቻ እስከ 450 ሺሕ ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ ሲገመት፣ ይህም ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ችግር ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች የወባ መድኃኒት፣ ለባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሚያገለግሉ ፀረ ተዋህሲያን እና የወሊድ መከላከያዎች፣ በአሜሪካ ደግሞ የኮሌስትሮል መድኃኒቶች ተመሳሳለው ተገኝተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር በ1995 ዓ.ም. በውጭ አገር ተመርተው ወደ አሜሪካ ከገቡት መድኃኒቶች 18 ሚሊዮን ኪኒን የሐሰት ሆነው መገኘታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ ሃሰተኛ ሆነው ከተገኙት ውስጥ ለካንሰር፣ ለአካል መቆጣት፣ ለአለርጂ፣ ለአስም ተብለው የተዘጋጁ ናቸው፡፡

በታዳጊም ሆነ በበለጸጉት አገሮች ለስኳር በሽታ የሚሆኑ ኢንሱሊኖችን ጨምሮ ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚሆኑ መድኃኒቶችም የሀሰት እየሆኑ መገኘታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያመላክታል፡፡ ድርጅቱ ባደረገው ፍተሻ ከበቆሎ ዱቄት ወይም ከድንች የተሰሩ የወባ መድሐኒት ተብለው ለገበያ መቅረባቸውንና በመድሐኒቶቹ ላይ የተለጠፈው መግለጫ እውነት እንደሚመስል ይህም በሽታን መከላከል ሳይቻል ቀርቶ ለሞት ወይም ለከፍተኛ ጉዳት ይዳርጋል።

የሐሰት መድኃኒቶች ላይ ጎጂ ኬሚካሎችም እንደሚጨመሩ ይህም ጉበት እንደሚያቃጥል፣ ኩላሊትን እንደሚያውክ፣ አዕምሮን እንደሚያቃውስና የደም ሴሎችን እንደሚያበላሽም የአለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ሃሰተኛ መድሃኒት በማምረት ገንዘብ የሰበሰቡ ራስ ወዳዶች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የጤና እክል ለሚያጋጥማቸው የሰው ልጆች ሞት መንስዔ እየሆኑ ነው። የሃሰተኛ መድሃኒት ስርጭት እየተባባሰ መምጣትም ለጤና ዘርፍ ፈተና ነው።

 

በመሆኑም ይሕንን ችግር ለመከላከል አኳያ መንግስት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ መድሐኒቶችንም ሆነ አገር ውስጥ የሚመረቱት ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር፣ ክትትልና ፍተሻ የበለጠ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር ይኖርበታል። ሕብረተሰቡም የሚያደረገውን የቁጥጥር ስራ በመደገፍ ቢሳተፍና  በተለይም መድሐኒቶችን ሲገዛ ጥንቃቄ ቢያደርግ ፤ የመድሃኒት መሸጫ መደብር ባለሙያዎችና ባለንብረቾችም ትክክለኛ የሆኑና ፈዋሽነታቸው

የተረጋገጠ መድሃኒቶችን ለሕብረተሰቡ ቢያቀርቡ አለ አግባብ የሚጠፋውን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት መታደግ ይቻላል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን