አርዕስተ ዜና

ፈሩን የለቀቀው የመናኸሪያ መስተንግዶ

4582 times

የፀዳወርቅ ታደለ (ኢዜአ)

የሰው ልጅ የዕለት ጉርሱን ለመሙላት ከላይ ታች በሚልበት የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በርካታ መሰናክሎችና ስኬቶች ማሳለፍ ተፈጥሯዊና የተለመደ እንደሆነ ጥርጥር የለውም ታዲያ ከከፍተኛ የስራ ኃላፊነት እስከ ዝቅተኛ የስራ ደረጃ ድረስ ሁሉም በየፈርጁ ተፍ ተፍ ይላል፤ የሚገባውን ያገኛል። አንዳንዴ ግን ይህ የህይወት ውጣ ውረድ በስርዓት አልበኝነትና በህገወጥነት ይታጀባል። እንዲህ ሲሆን ሌሎች ለችግር ይጋለጣሉ። እኔም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከታዘብኩትንና ካስደመመኝ የአውቶቡስ ተራ(መናኸሪያ) ገጠመኞቼ ላጋራችሁ።

በቅርቡ ለስራ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ለመጓዝ ቃሊቲ መናኸሪያ ተገኝቼ ነበር። በዕለቱ በቀኑ ክፍለ ጊዜ በቃሊቲ መናኸሪያ የሚካሄደውን ስለማውቅ፣ ምናልባት ምሽት ላይ ብጓዝ ግርግሩም ይቀንሳል ብዬ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ መነኸሪያ ደረስኩ። ገና የመናኸሪያ  መግቢያ በር ላይ ከመድረሴ ነበር ያ በቀን የማውቀው አስቀያሚ ወከባ የተቀበለኝ። ታዲያ እንደተለመደው ግርግሩ ሲባባስ ቆም አልኩ፤ አፍታም ሳይቆይ “እናቱ አዳማ ነሽ፣ ሃዋሳ ሻሸመኔ፣ ሞጆ’’ የሚሉ አዋኪ ድምጾች ከየት አቅጣጫ እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳላውቀው በአንድ  አፍታ ዙሪያዬን በወጣቶቹ ተከበብኩ። የትኛውን ሰምቼ ለየትኛው እንኳን እንደምመልስ በቅጡ አላወቅኩም።

እንዲሁ በደመነፍስ ‘አዳማ ነኝ’ ከማለቴ ሶስት ወጣቶች ይዘውኝ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ይስቡኝ ጀመር። በዚህ መሃል በእኔ ግዛት ማነው ከእኔ ወዲያ በሚመስልበት መልኩ አንድ ፈርጠም ያለ ወጣት አምባጓሮ መፍጠር ጀመረ። ከሌሎች ወጣቶች ጋር ግብግብ ውስጥ ገባ። ነውር የተባሉ ስድቦችን (በመናኸሪያ አካባቢ የተለመዱ ቢሆንም) ሁሉ ካከናነባቸው በኋላ እጄን እየጎተተ ሃይ ሩፍ (high roof) በመባል የሚታወቀው ሚኒ ባስ ተሽከርካሪ ውስጥ ሳልወድ በግዴ አስገባኝ። መኪናው ባዶ ስለነበረ ቶሎ ሊሞላ ስለመቻሉ ሁኔታው ያስፈራ ስለነበረ ፈራ ተባ እያልኩ ጠየቅኩት።”እኔ አንድ ቃል ነው የምናገረው፤ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሞልተን እንወጣለን’’ አለኝ በዚያ በሚያስፈራ ድምጹ። ይበልጥ ደግሞ በተሽከርካሪ መብራት ገጽታውን ስመለከተው ሰውነቴ ራደ።

ተሽከርካሪ ውስጥ እንደገባሁም ሁለት ተጓዦች የተሳፋሪውን መምጣት በመጠባበቅ ቦታቸው ላይ ተቀምጠው እንዳየሁ አዳማ ነው የሚሄደው? ብዬ ጠየኩ። “አዎ የአዳማ መኪና ነው’’ የሚል ምላሽ ሸምገል ካሉ አባት አገኘሁ። ወዲያውኑ ሁለተኛው ተሳፋሪ ሳታረጋግጪ ነው እንዴ የተሳፈርሽው የሚል የፌዝ ጥያቄ ሰነዘረልኝ። ጥያቄው ያበሳጫል፤ የምጠይቅበት አፍታ ባገኘሁና ጠያይቄ በራሴ ፍላጎት በተሳፈርኩ ብዬ የትዝብት ምላሼን ሰጠሁት።

ይህ ሰው እንዳለውም አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከትንሽ እስከ ትልቅ አንዳንዴም እየተቆጣ፣ ሌሎቹንም እየገፈታተረ፣ እያስፈራራም ተሽከርካሪውን ሞላ። የሚገርመው ደግሞ አሽከርካሪ ራሱ መሆኑ ነው። ቀጥሎ ደግሞ ትልቁ ትግል የተካሄደው ተሽከርካሪውን ከመናኸሪያ ጊቢ ይዞ ለመውጣት በተደረገው ጥረት ነው።

ሁሉም ሚኒ ባሶች የመናኸሪያው መውጫ በር ላይ ተደርድረው ነበር ተሳፋሪ ለማስገባት የሚታገሉት። እንዲህ አይነት ፈሩን የለቀቀ ሁኔታ እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም። ሾፌሩ ሌሎች አሽከርካሪዎችን እየተሳደበ፣ አንዳንዴም ለመማታት እየቃጣው፣ እኔም አሁን ከአሁን ተጋጨን እያልኩ በጭንቀት ተወጥሬ መናኸሪያውን ለቀን ወጣን። የዚያን ቀን ከየትኛውም ጊዜ በላይ መናኸሪያ ስርዓት አልበኝነት እንደሰፈነ ተረዳሁ።

ነገሩ ወዲህ ነው። መናኸሪያ ውስጥ ድሮውንም የተጓዥ መብት መቼ ተከብሮ ያውቅና ነው። አንዱ በእድሜ ጠና ያሉ ተሳፋሪ ብቻቸውን ስሜታቸውን ያወራሉ። ሌላው በጸጥታ ጉዞውን ጀምሯል። ይህ ማለት ችግሩ ከመለመዱ የተነሳ ምን ያህል ትክክለኛ ነገር መስሎ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኝ መረዳት ችያለሁ። ተሳፋሪውን “ እስከመቼ እየገፈታተሩ፣ ትንሽ እንኳን ለሰው ክብር ሳይሰጡ በግዴታ እንድንሳፈር የሚያደርጉን ። ሃይ ባይ የሌለ ይመስል’’ ብሎ በምሬት ያወራል።

እኔም ደግሜ ማሰብና ማሰላሰል ጀመርኩ። ይሄ ሁሉ ስድብ፣ ዱላ ቀረሽ ግብግብ የተሳፋሪን ምቾት በሚነሳ  መልኩ የግዴታ ውዴታ በሚመስል መልኩ የተጓዙልን ጉትጎታ ለእለት እንጀራ እንደሆነ አሰብኩና ወይ የእንጀራ ነገር አልኩ። ምንም እንኳን ለእነሱ የዕለተ ተዕለተ ተግባራቸው ቢሆንም ስራው በትክክለኛ መንገድ ቢሰራ ሁሉም ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም ወይ? አልኩ። ለነገሩ መናኸሪያ ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ግለሰቦች ገንዘብ የሚያገኙት በህገ ወጥ መንገድ (ሌትን ጨምሮ) እንደሆነ የብዙዎች ግምት ነው። በተለይ በበዓል ወቅት ወደ ክልል ከተሞች ጉዞ ለማድረግ ሲነሱ ፈተናው እንደሚበረክት መታዘብ ይቻላል። የትራንስፖርት ዋጋ በዕጥፍ ይጨምራል፣ የሌባውም ቁጥር ያን ያህል ይሆናል።

እኔን ከበውኝ ከነበሩት ወጣቶች (ረዳት ሹፌሮች) መካከል ጎትቶ ወደ ተሽከርካሪው ያስገባኝ፣ አሽከርካሪ ‘ይህ ግዛቴ ነው’ ያለበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ጀመረኩ። ከተሳፈሩት ግለሰቦች መካከል አጠገቤ ተቀመጦ በምሬት ሲያወራ የነበረውን ሰው “ተራ አስከባሪዎች ግን የሉም?’’ አልኩት። 

ሰውየው ብዙ ጊዜ እንደሚመላለስ ነግሮኝ “ ህግ አስከባሪዎች ቢኖሩም ባይኖሩም ብዙ ለውጥ የለውም። ህግ ቢከበር ኖሮማ መናኸሪያ ውስጥ ህግ የለም የሚል ድምዳሜ ላይ አልደርስም ነበር።’’ ሲል መለሰልኝ። ሁሌ ተመሳሳይ ነገር እንደሚከሰት አረጋገጠልኝ። በእርግጥ ምሽት ላይ ስርዓት አልበኝነቱ የከፋ መሆኑም አልሸሸገም። እንዲህ እንዲህ እያወጋን በግዴታም ሆነ በፈቃዳችን መንገዳችንን ቀጠልን። እኔና ከጎኔ የተቀመጡት ጎልማሳ የተሽከርካሪ ላይ ጉዞ ተሞክሮዎቻችንን እያወጋን ጉዟችንን ቀጥለናል።   

መቼም ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመጓዝ አቅሙ ያለው በአውሮፕላን፣ ሌሎች ደግሞ መናኸሪያ ጎራ እያሉ የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም ግዴታ ነው። መናህሪያ በመሰረቱ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ቦታ ላይ ማግኘት በራሱ ለተጓዥ እፎይታን ያጎናጽፋል።

ይሁን እንጂ የሚጓዘው ሰው ፍላጎቱንና ምቾቱን ተነጥቆ በግዴታ ተራ አስከባሪው፣ የተሽከርካሪው ሹፌርም  ሆነ ረዳቱ እያዋከቡ በማይፈልገው ሁኔታ እንዲሳፈር ማስገደዱ የተለመደ የመናኸሪያ ተግባር ከሆነ ዘመናትን አስቆጥሯል። አለፍ ሲልም መናኸሪያ አካባቢ ዘረፋ፣ መጭበርበርና መሰል ወንጀሎች እንደሚፈጸምበትም የማይካድ ሃቅና የየዕለት ክሰተት ነው። ይህ ሁኔታ ለዘመናት የቀጠለ በመሆኑ ተጓዥም ወደ መናኸሪያ አገልግሎት ለማግኘት በሄደበት ወቅት አንድ ያልጠበቀው  ነገር ቢያጋጥመው ከተራ ምሬት ያለፈ ምንም ማድረግ እንደማይችል ያውቀዋል።

ከሁሉም በላይ ግን ስሜትን በሚጎዳ መልኩ ማመነጫጨቅና የስድብ ውርጅብኝ ማስተናገዱ በጣም ስብዕናን ይጎዳል። ይባስ ብሎ ገንዘብን አውጥቶ ለሚጓዘው ግለሰብ ምቾቱንና ፍላጎቱን ሳይጠብቁ እንዳሻቸው ‘ግዛቴ ነው’ በሚል አስተሳሰብ በግዴታ ተሽከርካሪያቸው ውስጥ ገፈታትሮ ማስገባት ከዚያም ግለሰቡ ‘ይመቸውም አይመቸው ጉዳዩ ነው’ በሚል አስተሳሰብ አጭቆ መጓዝ ከመለመድ ባሻገር የሹፌሮችና የረዳቶች መብት እስኪመስል ድረስ የተረሳ ጉዳይ ሆኗል።

በተለይ ደግሞ ከልብስ ሻንጣ ጀምሮ እቃ ይዞ በመናኸሪያዎች ውስጥ ማለፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በላይ መመስከር የሚችል ያለ አይመስለኝም።…

በማመናጨቅና በማስገደድ ህብረተሰቡን አጭቆ የሚጓዝ አሽከርካሪ በየመንገዱ ለሚቆጣጠሩ በቅርበት የሚገኙ  (በመናኸሪያ በራፍ ላይ) 'የትራፊክ ፖሊሶች የደንቡን እየተቀበሉ ስራቸውን ዘንግተዋል' ከሚለው ሃሜት ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት መስመር እየለቀቀ የመጣውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስተካከል ተግተው መስራት ይኖርባቸዋል። የተሳፋሪን ምቾት በሚነሳ መልኩ ተሳፋሪን ይዞ በሚጓዝ አሽከርካሪ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወስዱና ለዜጎች ዘብ የሚቆሙ የትራፊክ ፖሊሶች እንዳሉም አልዘነጋሁም።

ደግሞ የሚገርመው አገር ያወቀው ጸሃይ የሞቀው የክፍያ ታሪፍ ሰዓቱ መምሸት ሲጀምር እየጨመረ እየጨመረ ይሄዳል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ አዳማ በትክክለኛው ታሪፍ 35 ብር ሲሆን፤ ምሽት አንድ ሰአት 40 ብር ይሆናል። ሰአቱ እየመሸ በሄደ ቁጥር ብሩም በእጥፍ እየጨመረ የመሄዱ ጉዳይ የሚመለከተው አካል ያውቀው ይሆን ወይስ እንዳላየ ችላ ብሎት?

እውነት የመናህሪያዎችን አሰራር ማሻሻል፣ የተጓዥን መብትና ግዴታ ማሳወቅ፣ የአሽከርካሪንና የረዳትን መብት እስከምን ድረስ እንደሆነ ማሳወቅ፤ ግዴታቸውንም የሚወጡበት አግባብ መስመር ማስያዝ የሚያስችል አካል ስራውን በአግባቡ መስራት ለምን አቃተው???

እንደኔ ከበፊት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመናኸሪያ አካባቢ ስርዓት አልበኝነት የተዋሃደው አካል የተበራከተ ይመስለኛል። ህብረተሰቡን ዘወትር በሚያማርር መልኩ መናኸሪያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ያልተገቡ ተግባራትን የሚያስቆም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም። በዚህ መልኩ ለትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊው ህብረተሰብ ፈተና እየሆነ ያለውን ፈር የለቀቀ የመናኸሪያ መስተንግዶ በአፋጣኝ መስመር ማስያዝ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ የማምጣት ሃላፊነት የሚያርፈው ሁሉም ላይ ነው። ህግ አስከባሪ አካላት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎችና የተሽከርካሪ ባለቤቶች ችግሩን ለመፍታት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን