አርዕስተ ዜና

“የደኃ ፈተና”

11 Jan 2018
1639 times

                  ነፃነት አብርሃም (ኢዜአ)

ሕፃናት ሲቦርቁ፣ ሲጫወቱና ሲደሰቱ ማየት ማን ይጠላል? ከጎረቤት ልጆች ጋር በሰፈር ሲሯሯጡ መመልከት፤ በንጹህ አንደበታቸው ሲናገሩ መስማት-ማንም! ሐሴቱ ለወላጅ ብቻ ሳይሆን ለመላው ተመልካች ነው። የጨዋታቸው ዑደት እንደየ እድሜያችው ይለያያል። ከፍ ሲሉ ኳስና መሰል ጨዋታቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር ይጫወታሉ። በዚህ ደስታ በሰጡን የልጆች ጨዋታዎች መካከል የተደበቁ፤ ያላወቅናቸው ጥቃቅን ነገሮች በህይወታችን ላይ ሳንካ እንደሚፈጥሩ ግን ልብ ላንል እንችላለን።

መቼም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዑደት ከተፈጥሮ ጋር ይላተማሉ፤ በዚህ መስተጋብርም አዳዲስ ኩነቶችን ያስተናግዳሉ። ደስታ፣ ሐዘን፣ በሽታ… ወ.ዘ.ተ። በሥነ-ሕይወት ሳይንስ የሰው ልጅ ጤናው ሊታወክ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች የትየለሌ ናቸው። ለሕልፈተ ሕይወቱም መንስኤ የሚሆኑ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች ይገጥሙታል። አጋጣሚዎቹ በጤና ላይ ዕክል ፈጥረው በህክምና ሊፈወሱ ወይም ሕይወት ሊቀጥፉ ይችላሉ።

ወደ ቁምነገሬ ልግባ! ወደ ሰፈራችን ልጅ! ታዳጊው እንደ ልጅነቱ መቦረቁን፣ መደሰቱን፣ መጫወቱን እንጂ ጉዳቱን ማንም አላስተዋለም ነበር። የ14 ወይም 15 ዓመት ገደማ የሚገመተው ታዳጊ በአንድ ወቅት ከእኩዮቹ ጋር በሰፈር ውስጥ እግር ኳስ ይጫወታል፤ በመሃሉም ድንገት ወድቆ እግሩ ላይ ጉዳት ይደርሳል። ወላጆቹና ጓደኞቹ ግን ጉዳቱን አላወቁም። ሲውል ሲያድር ጉዳቱ እየባሰ፣ ቁስሉም እያመረቀዘ እግሩ ማበጥ ይጀምራል። ወላጆቹም ችግሩን አውቀው ወደ ሕክምና ይዘውት ሄዱ። እንዳሰቡት ግን ቀላል ሕመም አልነበረም፤ የቁስሉ ኢንፌክሽን በጊዜ ብዛት ወደ ካንሰርነት መቀየሩን ተረዱ። በአፋጣኝ ውጭ ተልኮ እንዲታከም ተነገራቸው። ግን እንዴት? የኑሮ አቅማቸው አይፈቅድም። አገር ወስጥ አይፈወስ ነገር፤ ውጭ ወስዶ ለማሳከም የድኅነት መዘዝ ሆነና ሲቦርቅ፤ ሲደሰትና ሲጫወት ደጅ የተመለከቱት ሕፃን እጃቸው ላይ አለፈ። የደሀ ፈተና!

ሌላም የሰፈራችን ልጅ በሰፈር በተፈጠረ ግጭት እጁን በዱላ ይመታል፤ ነገር ግን በአፋጣኝ ሕክምና አላገኘም። በተመሳሳይ የዚህ ልጅ ጉዳት ወደ ካንሰር ተቀየረ። "በተመሳሳይ ችግርም ሕይወቱ በከንቱ ማለፉን አስታውሳለሁ።" በእነዚህ ሁለቱ ምሳሌዎች የካንሰር በሽታን ምንነት ከተመለከትን በየቤቱ ምን ያህል ገጠመኞች ይኖራሉ? በዓለማችንስ የምን ያህሉ የሰው ልጅ የመኖር ተስፋ መንምኖ፣ ጨልሞ ቀርቷል? የምን ያህሉ ሕይወትስ ብላሽ ሆኗል?

በሕይወት ውስጥ የካንሰር በሽታን የሚያስከትለውን ክፉኛ ቀውስ በቀላሉ መግለጽ ከባድ ነው። ቀዳሚው የሰው ልጅ ገዳይ በሽታ ነው። ለነገሩ ካንሰር ሲባል የምን ያህሎቻችን ውስጠት ነው የሚረበሸው?

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ካንሰር በሰውነታችን ውስጥ "ያለ ምንም ገደብና ቁጥጥር ይባዛል፤ ሌሎች ጤነኛ የሆኑ ሴሎችን በመውረር መደበኛ ሥራቸውን ያስተጉላል፤ ከዛም በሽታው ይከሰታል" ነው። የበሽታው ስርጭት በአልትራሳውንድ፣ በሲቲ ስካን፣ በኤም አር አይ፣ በኤክስሬይና በቦን ስካን የምርመራ ዘዴዎች ማወቅ ይቻላል ይላሉ። ቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምና፣ "ኬሞቴራፒ"፣ "የሆርሞን ቴራፒና"፣ "ባዮሎጂካል ቴራፒ" ደግሞ በዋናነት ለበሽታው የሚሰጡ ህከምናዎች ናቸው። ትንባሆ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ፣ በሄፓታይተስ ቢ እና ሲ መጠቃት፣ የአካባቢያዊ ብክለትና መሰል ችግሮች ለበሽታው መከሰት እንደ ዋነኛ መንስኤ ይወሰዳሉ።

ከመቶ በላይ የካንሰር በሽታዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የጡት፣ የቆዳ፣ የሳንባና የመተንፈሻ አካላት፣ የአንጀት፣ የደም፣ የማህጸንና ሌሎች የካንሰር አይነቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2015 ባወጣው መረጃ በተጠቀሰው ዓመት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። ይህም በዓመቱ ከተከሰቱት ከስድስት ታማሚዎች መካከል አንዱ በካንሰር አማካኝነት የሚከሰት ሞት መሆኑ ነው። 

በየዓመቱ ደግሞ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በካንሰር ይያዛሉ። ሕክምናውን በበቂ ሁኔታ ማግኘት ከተቻለ ከ30 እስከ 50 በመቶ ሕሙማኑን ማዳን እንደሚቻል ይነገራል። ግን ሕክምናውን ማግኘት ቀላል አይደለም። በሪፖርቱ መሠረት ችግሩ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እ.ኤ.አ በ2020 በካንሰር የሚሞተው ሕዝብ ቁጥር 10 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይተነትናል። በየዓመቱ በአዲስ የሚያዘው ሰው ቁጥርም ወደ 16 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ለካንሰር በሽታ መንስዔ ከሆኑት አንዱ ትምባሆ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ትምባሆ ከ25 እስከ 30 በመቶ ለካንሰር መንስዔ ነው። የአመጋገብ ችግርና ውፍረትም ከ30 እስከ 35 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ። በርግጥ ከ5 በመቶ እስከ 10 በመቶም በዘር ይተላለፋል። በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት ከ15 እስከ 20 በመቶ፣ ጭንቀት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግና ሌሎች ደግሞ 10 በመቶውን እንደሚይዙም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ታክሞ የመዳን ዕድላቸው እንደ ህመሙ ዓይነት፣ ደረጃ፣ ዕድሜና ህክምናው በተሟላ ሁኔታ መስጠት አለመስጠቱ ላይ የተወሰነ ነው። ይኽውም እንደማንኛውም ህመም ማዳን፣ መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል። በቶሎ ከተደረሰበትና በቂ ህክምና ካገኘም ማዳን እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከፍተኛ የክብደት መቀነስ፣ በሰውነት ላይ አዳዲስ ነጠብጣብ መታየት፣ በአንጀትና በኩላሊት ላይ የህመም ስሜት መሰማት፣ ተከታታይና ደረቅ ሣል  መኖር፣  በሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ በጡት) ላይ ጠጠር ያለ ወይም ላላ ያለ እብጠት መከሰት እንዲሁም ቶሎ የማይድን የጉሮሮ ህመም መከሰት ጥቂቶቹ የበሽታው  ምልክቶች ናቸው።

የካንሰር በሽታ የበለፀጉት አገራት ችግር ብቻ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር ይነገራል። ይሁንና ዛሬ ዛሬ በታዳጊ አገራትም አሳሳቢ ችግር እየሆነ መጥቷል። ይህም ህክምናውን በበቂ ሁኔታ ለማግኘትም ሆነ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ለታዳጊ አገራት ፈተና የሆነው። በታዳጊ አገራት በየዓመቱ በካንሰር ምክንያት ህይወቱን የሚያጣው ህዝብ ብዛት በኤች አይ ቪ ኤድስ ከሚሞተው ሰው በእጥፍ እንደሚበልጥ የጤና ድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።

እስኪ ወደ ኢትዮጵያ እንመልከት። በአሁኑ ወቅት የጡት እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። የበሽታው ተጠቂዎች ህክምናውን ባለማግኘታቸው ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ ነው። በተለይ ስለካንሰር በሽታ ያለው ግንዛቤም ሆነ መረጃ አነስተኛ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳሸጋገረው ነው የሚነገረው።  የበሽታው ድብቅ ባህሪይም ለመከላከልም ሆነ ለህክምናው ፈተና ሆኗል።

የችግሩን አስከፊነት በመገንዘብ በአገራችን ምን እየተሰራ ይሆን? ምንስ መደረግ አለበት? የሚለው የሁላችንም ጥያቄና መልስ የሚያሻው ጉዳይ ይመስለኛል። የሕብረተሰቡን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻልም እንኳን መቀነስ በሚያስችል መልኩ የካንሰር ህክምና አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ 5 ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ ዶክተር ብስራት ደሳለኝ እንደሚሉት፤ በሐዋሳ፣ በመቀሌ፣ በጅማ፣ በጎንደርና በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገነቡት የሕክምና ማዕከላት ለአጠቃላይ ግንባታና የህክምና ቁሳቁስ ወጪ የሚሆን 80 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ ነው ሥራው እየተከናወነ ያለው።

እንደ ዶክተር ብስራት ገለጻ፤ በአገሪቱ ከአሁን በፊት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ተወስኖ የቆየውን የካንሰር ህክምና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት ከአዳዲሶቹ ማዕከላት ግንባታ ጎን ለጎን የህክምናና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአትን የማሟላት ተግባራትም እየተከናወነ ይገኛል። ማዕከላቱ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው ዶክተር ብስራት የገለጹት።

አገልግሎቱን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ መስጠት መቻል በሞት የምናጣቸውን ዜጎች ከመታደጉ ባለፈ ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ውጪ የሚሄዱ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ካላስፈላጊ ወጪና እንግልት ይታደጋል። ወደ ፊትም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ የሕክምና ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

"ለወራት፤ ገፋ ሲልም ለዓመታት በማድፈጥ በዝምታ ሕይወትን ከሚቀጥፍ ገዳይ በሽታ ለመጠበቅ ሁላችንም ለራሳችን ትኩረት ማድረግ ይገባል ባይ ነኝ።" ምልክቶች ከተከሰቱ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ ክትትል ማድረግን መዘንጋት የለብንም። ከካንሰር ይጠብቀንማ!!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን