አርዕስተ ዜና

ብርሃን ፈንጣቂው ጅምር

09 Jan 2018
2126 times

            መሀመድ ዓሊ (ኢዜአ)

 ከሰው ልጅ የስሜት ህዋሳት አንዱ የሆነውን የአይን ክፍልን ለአይነ ስውርነት ከሚዳርጉት መንስዔዎች መካከል የአይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract) ፣ የአይን ማዝ (ትራኮማ) እና ግላኮማ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 የትራኮማ በሽታ ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል በሽታዎች (Neglected Tropical Disease) ተብለው በተቀመጡ በሽታዎች ተርታ የሚመደብ ነው። ይህ በሽታ በአብዛኛው በግል እና አካባቢ ንፅህና ጉድለት የሚከሰት ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ የአይን ብርሃንን የማሳጣት ጉዳት ያደርሳል።

ሆኖም ግን በአግባቡ ህክምና ከተደረገ 80 በመቶ ያህል የአይነ ስውርነት  በማከም ማስወገድ ይቻላል ይላሉ የጤና ባለሞያዎች። 

በሀገራችን ያለውን የአይን ሞራ ግርዶሽ ስርጭት ስንመለከት ሶማሊ ክልል 5 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን  ያመላክታል፡፡

ከዚሁ ቁጥር ውስጥ በቀላሉ አስቀድሞ መከላከል በሚቻል በሽታዎች  ለአይነ ስውርነት የተጋለጡ 400 ሺህ አዛውንቶች መኖራቸውን ይነገራል ፡፡ 

 ቁጥሮች እንደሚያመላክቱት በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች ከፍተኛው ስርጭት የሚስተዋለው በዚሁ በምስራቅ ኢትዮጰያ በሚገኘው ሶማሊ ክልል ነው።

በክልሉ ያለውን  የአይን  ሞራ  ግርዶሽ  ስፋት መነሻ በማድረግ እና ሌሎችም የአይን ህመም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳድግ የጤና አገልግሎት ባልተስፋፋበቸው  የገጠር አርብቶ አደር አካባቢዎች ርብርብ እየተደረገ ነው ።

 የአይን ህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በሰኔ 2007 ዓ.ም የተቋቋመው ተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድን ዛሬ በአይን ግርዶሽ ሲሰቃዩ የነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከነበረባቸው  ህመም እንዲላቀቁ መልካም አጋጣሚ ሆኗል፡፡

በክልሉ አፍዴር ዞን ሀርጌሌ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ኢባዱ መዓልን አብዲላሂ ሁለቱም አይናቸው ማየት ተስኖአቸው የወለዷዋቸውን ስድስት ልጆች በአይናቸው ለማየትና ለመንከባከብ የታደሉ አልነበሩም  ይህ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የአይን ህመም ሲሰቃዩ ቆይተዋል፡፡

ወይዘሮ ኢባዱ በተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድኑ በተደረገላቸው ነጻ  የአይን ቀዶ ህክምና የአይን ብርሃናቸው በበራላቸው ቅጽበት የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ‘’ዛሬ ሀርገሌ ነው ያለሁት ማየት ቻልኩኝ ’’ ሲሉ ተነፈሱ ።

በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ሀሰንም ለሀያ ዓመታት በአንደኛው አይናቸው ማየት እንደማይችሉና ከሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሁለተኛው አይናቸው ማየት በማቆሙ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ያስታውሳሉ ።

 የህክምና ቡድኑ አባላት ወደ አካባቢያቸው መጥተው ባደረጉላቸው ቀዶ ጥገና ከነበረባቸው የአይን ህመም ተላቅቀው የአይን ብርሃናቸው በመመለሱ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት በሚከተለው መልኩ ነበር ። ‘’ትናንት በሰዎች እየተደገፍኩና እየተመራሁ ነበር ህይወቴን የምመራው  ዛሬ ግን  እይታዬን መልሼ አግኝቼዋለሁ ፡፡ በጣም ተደስቻለሁ ። ፈጣሪ ይመስገን’’፡፡

 ለረጅም አመታት ሲሰቃዩበት የነበረውን ከአይን ህመም ነጻ ሆነው ወደ ብርሃን አለም መሸጋገራቸውን  የተናገሩት ሌላዋ የሲቲ ዞን አይሻ ወረዳ ነዋሪ  ወይዘሮ ሐሊማ ኢብራሂም አላሌ ናቸው ፡፡

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ  በዓይናቸው ላይ ችግር እንደተፈጠረባቸው የገለፁት ወይዘሮ ሐሊማ ‘’ማየት አልችልም ነበር ። አጠገቤ ያለውን ውሀና ምግብ ሰው ካልሰጠኝ በስተቀር ወስጄ መጠቀምም ሆነ ልጆቼ ሲያለቅሱ መያዝና መንከባከብ አልችልም ነበር ፡፡ የትናንት ህይወቴ ጨለማ ነበር ። ዛሬ ግን የአይኔ ብርሃን ተመልሶልኛል፡፡ ለዚህ ላበቁኝ ለአላህና ለክልሉ መንግስት ምስጋና አቀርባለሁ ’’ ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለበሽታው በስፋት መከሰት ምክንያት  የበሽታውን ምንነት አለመረዳት እንደሆነ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው ያስረዳሉ። አቶ መሀመድ ሀሰን የተባሉ የወረዳው ነዋሪ  “በፊት ህመሙን ቀለል አድርገን ነበር የምናየው። በምን እንደሚመጣብንም አናውቅም ነበር። ከእድሜ ጋር የሚመጣ አድርገን ስለምናሳብ ምንም ማድረግ አልቻልንም ነበር’’ በማለት ይገልጹታል።

እንደ ወይዘሮ ሐሊማ እና አቶ መሀመድ ሀሰን ሁሉ ሌሎችም እስካ አሁን በተንቀሳቃሽ ህክምና በተሰጠባቸው በክልሉ በ31 ወረዳዎች የሚገኙና በአይን ህክምና እጥረት ለረጅም አመታት ሲሰቃዩ የነበሩት አርብቶ አደር አዛውንቶች የአይን ቆብ ቀዶ ህክምና ተሰርቶላቸው  ብርሃናቸው ወደነበረበት መመለሱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ኢስማኤል ተናግረዋል፡፡

አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ያላቸው አስራ ስምንት የህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈው የአይን ህክምና ቡድን በክልሉ የተለያየ አከባቢዎችን በመንቀሳቀስ የአይን ቆብ ቀዶ ህክምና በማድረግ እንዲሁም ለአይነ ስውርነት መነሻ የሆነውን የአፍላ ትራኮማ በማከም ፣ መድሃኒትና መነፅር ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በነፃ በመስጠት በጠቅላላው ከ49 ሺህ ሰዎች በላይ ነፃ የአይን ህክምና ተጠቃሚ ማድረጋቸውንም   ገልጸዋል፡፡

የተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል በክልሉ የአይን በሽታው ካለው ስፋትና ስርጭት አንጸር ነጻ የህክምና አገልግሎት በማስፋፋት በ2010 በጀት ዓመት 20 ወረዳዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የተጀመረው የአይን ብርሀን ጉዞ ተጠናክሮ ለማስቀጠል በቂ ዝግጀት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው በንጹህ ውሃ ጉድለት የሚከሰተውን ትራኮማ የአይን ህመም በሽታውን በዘላቂነት ለመቅረፍ የህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዋነኛው የአይነ ስውርነት ከሚያመጡ በሽታዎች አንዱ ካትሪክት ወይም የአይን ሞራ ግርዶሽ 49 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ከትራኮማ የሚመጣ መሆኑን 2016 በማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተደረገው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡

በትራኮማ የሚመጣው የአይነ ሞራ ግርዶሽ ለመከላከል የአፍላ ትራኮማ መድኃኒት ተደራሽ በማድረግ ወደ አይነ ስውርነት ከመሸጋገሩ በፊት ለመቆጣጠር የክልሉ ጤና ቢሮ መድኃኒቶችን ለሁሉም ተቋማት ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት በቢሮው የተላላፊ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር  የአይነ ስውርነት መከላከለያ ህክምና ቡድን መሪ አቶ አህመድ በዴ ዱኣሌ ናቸው፡፡

አቶ አህመድ የበሽታው ስፋት መጠን አስደንጋጭ መሆኑን ገልፀው የሚያስቆጨው ነገር በአምስት ሰዎች ላይ ከተከሰተው አይነስውርነት የ4ቱን ቀድሞ በመከላከል ወይም በማከም ማስቀረት የሚቻል መሆኑ ነው ይላሉ 

ከአመት ወደ አመት እየጨመረ የመጣው የአይን ሞራ ግርዶሽ ለማከም በሊባን፣ በአፍዴር፣ በሲቲ፣ በኖጎብ፣ በቆራሃይና ጀረር ዞኖች ከሚገኙ 31 ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑና የማየት ችግር ለነበረባቸው  ወገኖች በተደረገላቸው የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ዳግም ብርሃናቸውን ማገኘት ችለዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ነው።

በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካይነት በተሰጠው ትምህርት መሰረት መፀዳጃ ቤት መስራታቸውን እና በዚያም እየተጠቀሙ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ሐሊማ፤ ይህ አይነቱ የጤና ትምህርት የአይን ሞራ ግርዶሽና ትራኮማን አስቀድሞ ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ማህበረሰቡን ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ማህበረሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ፣ መፀዳጃ ቤቶችን በማዘጋጀትና በአግባቡ በመጠቀም ትራኮማን እንዲካላከል እያስተማሩ መሆናቸውም ለማየት ተችሏል። ለትራኮማ እና ተያያዥ ለሆኑ በሽታዎች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶችና አረጋውን ደግሞ ዋነኛዎቹ የስልጠናው ተሳታፊዎች ናቸው።

እነዚህን ሴቶች በጤና ልማት ቡድን፣ አንድ ለአምስት እና በመሳሰሉት በማደራጀት እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ እና ትምህርት እንዲወስዱ እየተደረገም ይገኛል። ጥረቱ የሚደነቅ ውጤቱ ደግሞ ብርሃን የሚያስፈነጥቅ ነውና በርቱ እንላለን !

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን