አርዕስተ ዜና

የመቻቻል ተምሳሌት - ኢትዮጵያ

08 Jan 2018
2500 times

በወልደሚካኤል ገ/መድህን  (አክሱም ኢዜአ )

ባለ3 ሺህ አመት የእድሜ ባለጸጋ፣የታሪክና ስልጣኔ መሰረት፣የነገስታትና የነጻነት አብነት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የ90 ሚሊዮን ህዝብ እናትና የብዝሃነት ማማ፣ የፊደልና የዘመን አቆጣጠር ባለቤት ኢትዮጵያ ስትባል ውስጡ ደስ የማይለው ፍጡር የለም ። እንኳንም የኛ ሆነች እኛም የእሷ ሆንን ያስብላል ።

ካለ ህብር አበባ ውበት እንደሌለው ሁሉ ካለ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦቿ ኢትዮጵያም  ውበት አይኖራትም ። ከ85 በላይ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አቅፋ የያዘች ሀገር የህልውናዋ መሰረቶች ህዝቦቿ ናቸው ። የህዝቦቿ የአንድነት መሰባሰቢያ አውድማ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት ።

የኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሰላም ፣ ልማት ፣ እድገትና ብልፅግና ተጠብቆ የሚኖረው ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸውን ውበታቸው አድርገው ተባብረው ፣ ተከባብረውና ተቻችለው በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን አንድነታቸው አጠናክረው ሲቀጥሉ ነው ።

ለፅሁፌ መነሻ የሆነው በአክሱም ዩኒቨርሲቲ “ ቱሪዝም ለሰላምና አብሮነት “ በሚል መሪ ቃል ለ8ኛ ጊዜ  የቱሪዝም ሳምንት ተከብሮ ነበር ። በበዓሉ ላይ ከተሳተፉ ሙሁራን መካከል የታሪክ፣ቋንቋና ፍልስፍና ተማራማሪና በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ  አንዱ ነበሩ ። ስለ ሰላምና አብሮ መኖር አስፈላጊነትም ንግግር አድርገው ነበር ።

“በአንድ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ሳስተምር ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር ታሪክና ስልጣኔ አላት ወይ ? ብለው ተሳታፊዎች ጠየቁኝ “ ብለው ንግግራቸውን ጀመሩ ። “ እንዴ ! ኢትዮጵያ እኮ በመፅሀፍ ቅዱስና በላቲንና በግሪክ ቋንቋዎች ጭምር ተደጋግማ የተጠቀሰች አገር ናት ። የእናንተ አገር ግን አንድ ጊዜም እንኳን አልተጠቀሰም “ በማለት ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅ አገር መሆንዋን ነገርኳቸው ይላሉ ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት  በ6ተኛው ክፍለ ዘመን በሮማዊያን ፕሮኮፒስ በሚል በላቲን ቋንቋ የተጻፈው መጽሓፍ  በአለም ላይ ሶስት ትልቅ መንግስታትና ህዝብ አሉ ።እነሱም ሮም ፣ኢራንና ኢትዮጵያን/አክሱማውያን/ ናቸው ተብሎ ተጽፎ ነበር።ስለዚህ  ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በአለም የታወቀች፣ ትልቅ ስፍራና ታሪክ ያላት አገር ናት ።

ሄግል የተባለው የጀርመን ፈላስፋ  “የራሱ ፊደል የሌለው ህዝብና ሃገር ታሪክ የለውም” ብሎ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ ። ኢትዮጵያ ግን የራሷ ፊደል አላት ። ታሪካችንና ባህላችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲነገር የነበረና ያለ በመሆኑ  ባለ ደማቅ ታሪኮች ነን በማለት አስረድተዋል።

የሳባውያንና የግእዝ ፊደል ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ባህልዋና ታሪክዋን አስቀምጣ ኖራለች የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሄ ፊደል በመኖሩ በአለም ላይ ከፍተኛ ስፍራ እንድትይዝ እና  ኢትዮጵያ ከመጀመሪያ ጀምሮ የራሷ ጽሑፍና ታሪክ እንዲኖራት ማስቻሉን ገልፀዋል ።

በአለም ላይ የኢትዮጵያ ስም እንደ ባንዴራ እየተውለበለበ ነው ። የዓለም ጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው ሲታገሉ ኢትዮጵያን ምሳሌ በማድረግ ነው ።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንደሚሉት አገራችን በብዙ ነገር ለአለም ተምሳሌ ናት ። የኢትዮጵያን እሴቶችና የባህል መገለጫ  የሆኑት መቻቻል፣መከባበር፣አብሮ መኖርና መደጋገፍ  በአለም ማህበረሰብ ዘንድ በተምሳሌትነት እንድትቀመጥ እንዳደረጋት አብራርተዋል ።

የሚያሳዝነው ግን ይህ ለአለም ማህበረሰብ ምሳሌ የሆነውን ባህላችንን፣ታሪካችንና ነጻነታችንን እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ትኩረት እንሰጠውም ።ታሪካችንንም አናውቀም ። ስለሆነም ባህላችንን እናጠናክር ! የተማራማሪው ምክር ነው።

በሰዎች መካከል በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ የሚገኙት ግጭቶችና በብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ ገጽታ የሚያላበሱበት ሁኔታ አሳፋሪ እንደሆነ፣የቆየውን አብሮ መኖር፣የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር እንደሚገባና ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ወስዶ መንቀሳቀስ እንዳለበት  ሙሁሩ ያሳስባሉ ።

ህዝቡ አብሮ መኖር ይፈልጋል ። ሰላም ይሻል ። የሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤው ህዝብ ነው የሚል እምነት የላቸውም ። ተማርን የሚሉ አንዳንድ ሃይሎች የሚፈጥሩት ነውና ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል የሚል አስተያየትም  ሰንዝረዋል ።

ልዩነታችን እንደ አበባ ማየት አስፈላጊ ነው ። አበባ ቀይ፣ብጫ፣ነጭ፣ሰማያዊና ሌሎች ህብር እንዳለውና እንደሚያምር  ብዝሃነታችንም  እንደ አበባ ያማረ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ልዩነታችንንና ታሪካችችን አውቀን በማመዛዘን እየኮራንና እየተባብርን ብናድግ  ለመልካም ነገር የሚውል ሀብት ነው ይላሉ ።

ፊት ለፊታችን ያለው ሁለት መንገድ ነው አንዱ የጥፋት ሲሆን ሁለተኛው የሰላም፣ የልማት፣የእድገትና የመተባበር  መንገዱን ይዘን ወደፊት መራመድ አለብን ሲሉም ይመክራሉ ።

ሰላም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሰረት ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ለሰላም ዘብ በመቆም ልማታችንን በማፋጠን በእድገት ጎዳና ወደ ፊት በመራመድ ተምሳሌነታችንን ማደስ ይጠበቅብናል ሲሉ ይመክራሉ ።

በመጨረሻ ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ ሰው እንዴት አቃተው በሚል ርዕስ በቅርቡ የለገሱንን  አጭር ግጥም ላካፍላችሁ እና ተወያዩበት።

          ሰው እንዴት አቃተው?

ጦጣን ጦጣ አይገድለው ዝንጀሮን ዝንጀሮ

ጅብን ጅብ አይገድለው ቀበሮን ቀበሮ

ሲደላው ተጫውቶ ሲርበው አድኖ ወይንም ስር ጭሮ

እንስሳን እንኳን ሲኖር እንደዚህ ተባብሮ

ስንት የሚያስብበት እያለው አእምሮ

ከተፈጥሮ ልቆ ብዙ ተመራምሮ

ሰው እንዴት አቃተው መኖር ተከባብሮ?

ሰው እንዴት አቃተው መኖር ተፈቃቅሮ?

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን