አርዕስተ ዜና

"ስሚኝማ ኤልዳዬ!"

06 Jan 2018
1831 times

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

ስሚኝማ ኤልዳዬ! ህጻን ሲወለድ አስታወስሽ? በንጋትም ሆነ በመዓልት፤ ምጥ የያዛት እናት ስትንጎራደድ፣ ስትንቧች ስቃይዋ ያስጨነቃቸው ጎረቤቶች ሲንቆራጠጡ፤ አንደኛዋ ሰኞ መደብ ሌላኛዋ ማክሰኞ፣ በጭቃ ደረጃዎች፣ በከብቶች ግርግም በራፍ፣ በጉበኑ ስርቻ ተወሽቀው 'ማርያም ማርያም' ሲሉ፤ ወንዶችም ከጎጆ ቤቱ ደጃፍ ተኮልኩለው ትርታቸው ሲደልቅ፤ አንደበታቸው በአይዞነት መንፈስ ቃላት ሲለዋወጥ፤ ምናልባትም እንግዳ ሰላላ ድምጽ ማቃጨሉን ተከትሎ የ'እልል'ሆታ ሲከተል ታወሰሽ? ቤት ካፈራው ገንፎ ተገንፍቶ ሲቀመስ ልብ አልሽልኝ?

ኦ! ይቅርታ! ለካስ አንቺ እንዲህ አይነት ዝባዝንኬ ነገር አይገለጽልሽም። 'ኩሉ ነገር ዘይኃልቅ ውስተ ቤተ ድውያን' እንዲሉ! ነገረ ውልደት በቤተ ድውያን/ሆስፒታል/ በዘመን አፈራሽ ህክምና መከናወኑ ነው የሚገባሽ። ሚጢጢዬ እህትሽ ከእናትሽ ማህጸን ወደ እቅፍ መሸጋገሯን እንጂ ቅድመ አያትሽ በዚህ ባልኩሽ ዑደት ወደ ዓለም በራፍ መምጣቷ አይታወስሽም!

እሺ ይሄን ስሚኝ! ስለ አያቴ ልንገርሽ! ያው ወርኃ ታኅሣሥ ማለቁ አይደል። በነገርሽ ላይ ‘ታኅሣሥ’ የሚለው ቃል ‘ኀሠሠ’ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ምርመራ ፍለጋ የሚል አንድምታ እንዳለው የቋንቋ ሊቃውንት ያትታሉ። ወቅቱ መኸር ነውና ከምርት ፍለጋ (ስብሰባ ጋር አያይዘውም ይፈትቱታል። ስለ ገና ማዕበል ሳትሰሚ አትቀሪም፤ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የቀለም ምርታቸው የሚሰበሰቡበት፤ የካፌ ቆይታቸውን የሚያረጋግጡበት ወቅት ነውና ምርቱ ካማረ አማረ፤ ካላማረ ማዕበል መታቸው ይባላል። ከማዕበል ይጠብቅሽ-ኤልዳዬ። ታኅሣሥ ሲገባደድ ጥር ይከተላል አይደል! በውርኃ ጥር ደግሞ ከጥምቀት ጀምሮ የበርካታ ታቦታት የንግስ በዓላት የሚከበርበት ነው (በኔ ትውልድ ቀዬ)። እና ታኅሣሥ ሲገባደድ፤ ጥር ሲብት የትምህርት ውጤት ማዕበል ብቻ ሳይሆን የፍቅር ማዕበልም ይከሰታል። (አንቺን ይግጠምሽ አይግጠምሽ ባላውቅም)። ለምሳሌ በዚህ ሰሞን እንዲህ ይዜማል፡-

ማዕበሉ የመታት እሷ

                                 "ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣

                                  እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎና..."

 

ማዕበሉ የገረፈው እሱም

                              "በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣

                              እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ…." ይላል።

 

እናም "ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣

ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ…" እየተባለ በጥንዶች ዘንድ ይዜማል እንግዲህ።

መቸም አንዱን ጥሎ አንዱን ነው ወደ አያቴ ልምጣልሽ! አያቴ ታኅሣሥ ከመገባደዱ ቀደም ብሎ እንጎቻ ታስነጉታለች፤ አሻሮ ታስቆላለች፤ የውኃ ቅሏን ታዘጋጃለች፤ ልብሰ መንኩስናዋንም ታመቻቻለች፤ ከመንደሩ መሰሎቿ ጋርም ጉዞ ትጀምራለች - ወደ ላልይበላ። የገናን በዓልን ለማክበር- አብያተ ክርስቲያናትን ለመሳለም።

'ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ' ነውና ምሳሌው 'ለምን አያትህ ወደ ላልይበላ ትሄዳለች' ማለትሽ አይቀርም። ቀደም ሲል 'ህጻን ሲወለድ አስታወስሽ' ማለቴ ካለነገር አይምሰልሽ። መቸም ህጻን ሲወለድ የቤተሰብ፣ ጎረቤትና አድባሩ ደስታው የት የሌለ ነው። እና ከዛሬ 2 ሺ 10 ዓመታት በፊት ቀደም ሲል እንዳልኩሽ አይነት ደሳሳ ቤት አንዲት ነፍሰጡር እናት ቤተልሔም በተባለች ከተማ ውስጥ ግርግም (ከብቶች በረት) ውስጥ ምጥ ተይዛ እየተንቆራጠጠች ነበር፤ ተገላገለችም። ታኅሣሥ 29! የዳዊት ከተማ ነዋሪዎችም ተደነቁ፤ እልልታ ሆነ።

"እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል" ተባለ።  ሰማያዊያንና ምድራዊያን ነገዶች፣ ነብያትና መላዕክት ያወደሱት፤ እረኞች ያወሩለት፤ ሐዋርያት ያከበሩት፣ ኃአጣን  የዳኑበት፤ ግዞተኞች የተፈቱበት፤ ክርስቲያኖች የወረሱት ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ። ሰብዓ ሰገልም በአብሪ ኮከብ እየተመሩ ለህጻኑ ስጦታዎች ይዘው ወደ እየሩሳሌም ገሰገሱ። ከነዚህ ሰብዓ ሰገሎች መካከል "ኢትዮጵያዊያንም ነበሩበት" ይላል ታሪከ ቤተ ክርስቲያን። ከዚያም ከየዓለማቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚነጉዱ ክርስቲያኖች ሁሉ የእምነቱ ተከታይ ኢትዮጵያውያንም የክርስቶስን ልደት ለመዘከር በየዓመቱ መሄድ ጀመሩ።

 

ከዛሬ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ግን የወቅቱ የዛግዌ ንጉስ (ቅዱስ ላልይበላ) የኢትዮጵያውያን ድካም አሳሰበው። እናም ክርስቲያኖች ክርስቶስን ልደት በአገራቸው እንዲያከብሩ ዳግማዊ እየሩሳሌም ማነጽ ፈለገ። እስካሁንም አምሳላቸው ያልተገኘላቸው ወደፊትም ይታነጻሉ ተብለው የማይታሰቡ ውቅር አብያተ ክረስቲያናትንም አሳነጸ። ምዕመናኑም የመካከለኛው ምስራቅ ድካም ቀርቶላቸው "ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም" (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ) እያሉ በየዓመቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን ያከብራሉ፤ በላልይበላ፡፡ አያቴም ስንቋን ይዛ የመሄዷ ምስጢር ይህ ነው።

መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና! እነዚህ ወደር አልባ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አደጋ ላይ መሆናቸውን ሳትሰሚ አልቀረሽም። አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጣቸው ለማንነታችንና ታሪካችን አሻራ ቅርሶች ለምን ጊዜም ላናጋኛቸው የመፈራረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ነው የሚነገረው። የሚመለከተው ተቋም ፈንድ ማሰባሰብ፣ ተቆጣጣሪ ጽህፈት ቤት ማቋቋምና ጥናት ማድረግ ሥራዎች እንደሚያደርግ ሲናገር ተደምጧል። ዞሮ ዞሮ መገንባት ቢያቅተን 'ተመን አልባ' ሀብቶችን መንከባከብና መጠበቅ ለነገ የማይባል ለሁላችን ኃላፊነት ነውና እንረባረብ ማለቴ ነው።

ወደ በዓል አከባበር ስመለስ። መስቀልና ጥምቀት በተለየ ድምቀት የሚከበርባቸው ከተሞች እንዳሉ ሁሉ የገና በዓልም በላልይበላ በልዩ ሁኔታ ይከበራል። በቤተ ክርስቲያን ከታህሳስ 23 ቀን ጀምሮ በአገልግሎት ይታደራል። በታኅሣሥ 28 ማታም ጥንግ ድርብና ጥቁር ካባ በለበሱ ካህናት የራሱ ቀለምና ዜማ ያለው ሥርዓተ ማህሌት ሌሊቱ በወረብና ዝማሬ እየቀረበ ይታደራል። በዕለቱም በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምዕመናን መንፈሳዊ በዓሉን ለማክበርና ከ'በረከቱ ለመሳተፍ'፤ ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት ይጎርፋሉ።

በዓሉ ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ፋይዳ የጎላ ነው። የልደት በዓል በመላው ዓለም የሚከበርም ሆነ በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ቢከበርም በላልይበላ ግን (የቅዱስ ላልይበላ ልደት በመሆኑም) በልዩ ድምቀት ነው የሚከበረው።

"በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ" እንዲሉ አበው በገና በዓል ሲከበር በርካታ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች አሉ። አሁን እኔ ሳድግ የዋንዛ ገና ቆርጨ፣ አለስልሸ፣ ከሰፈሩ ጉብላሊት ጋር ከሰፊው መስክ እንቁራ(ሩር) ስላጋ የነበሩኝ ትዝታዎች ውል ውል ይለኝ አይደል? ሌላውም እንደየአካባቢውና አስተዳደጉ ሁሉም የራሱ እልፍ ገጠመኞች ይኖሩታል። የበዓል ሰሞን ገበያ መቼም ባለአመል ነው። እናም ዶሮም ሆነ በግ ለመገብየት ወደ ገበያ ጎራ ያለ አባወራ፤ አስቤዛ ለመሸመት ወደ ጉልት ከተፍ ያለች እናት፣ የስጦታ ዕቃዎችን ለመገብየት ወደ ገበያ ማዕከላት ያቀና ገብያተኛ የመስረቅ፤ የመጭበርበር አጋጣሚዎች ይኖሩታል። የግርግር ገበያ መዘዙ እልቁ ቢስ ነው እቴ! ሐሰተኛ የፍጆታ ምርቶችም ሆነ ጤናማ ያልሆነ እንስሳት ይገበያል። በበዓል ሰሞን በቅርጫም ሆነ በግብዣ ወቅት የሚፈጠረው በጎም፤ ክፉም ገጠመኞች ስለሚኖሩም በዓሉን ብዙዎቹ ይናፍቁታል። ቤት ብቻም አይደል! በምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጭ የንግድ ድርጅቶች ደስታና ፈንጠዚያ ይከወናል። ይህን ተከትሎ በዚህ ቅጽበት ሞራላዊ ደስታ ልክ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ኪሳራዎች ይከሰታሉ። ፍቅረኞች ተናፋቂ ጊዜ የሚያሳልፉበት፣ ለጋብቻ ደወል የሚደዋወሉበት ዕለትም ይሆናል። ልጅ የሚያገኝ፣ ሎተሪ የሚደርሰው፣ ሌላም ሌላም አጋጣሚዎች። እናም በየፊናው 'የገና ስጦታዎች' አሉ። 'ስጦታ' ዋጋው ብቻ ሳይሆን "ባህሉም አይሏል" እያሉ አይደል ታዛቢዎች።

ኤልዳዬ ስጦታ እንደምትወጅ አውቃለሁ! አንቺ ደግሞ ያው በቅርብ ወራት ምንዛሬው በሶስት ብር መጨመሩን ተከትሎ ይሁን አይሁን ባላውቅም እንደው ይገርምሻል ሁሉ ነገር እሳት ሆኗል። የሶሲ ቡና በሁለት ብር፣ የሸምሱ እንጀራ በአንድ ብር፣ የምጥን ሽሮ በአምሰት ብር፣. . . ጨምረዋል። የአልባሳት፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋን ለዛውም በበዓል ወቅት ልብ በይ እንግዲህ። የእንቁላል፤ የቅርጫ ስጋ፣ የዶሮ፣ የበግ. . . እረ ስንቱ ተወርቶ አያ!

እና ምን ማለቴ መሰለሽ ያው ደመወዙ እዚያው፤ የቁስና አገልግሎቱ ዋጋ እየናረ አካሄዳቸው አልጣጣም ብለዋል። ለዚህ ነው አንጀት አራሽ ስጦታዎችን ያቀርባል ብለሽ እንደማጠብቂ ተስፋ እማደርገው። (በርግጥ የገና ዛፍና መሰል ስጦታዎች ከባህልም ትፈልጊ አይመስለኝም) ያም ሆኖ ግን አንድ ስጦታ አለኝ። ከእናንተ ቤት ፊት ለፊት ካለው ሱቅ አስቀምጨልሻለሁ። የላኪና ተቀባይ አድራሻ የለውም።

ለመለየት እንዲያመችሽ ግን “ላልይበላን እንታደግ” የሚል ምልክት ከጀርባው ተጽፎበታል።

መልካም፤ ደግ ደጉን እምንሰማበት ቸር አውዳ ዓመት ይሁንልሽማ ኤልዳዬ!!

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን