አርዕስተ ዜና

ትግራይን በጨረፍታ

06 Jan 2018
2828 times

መብራህቱ ይበልህ ኢዜአ

በቅርቡ በካሊፎንያ ዩኒቨርስቲ የአርኬኦሎጂ ምሁራን ተመራማሪዎች በቁፋሮ የተገኘው ጥንታዊ ከተማ የኢትዮጵያን የታሪክ ዘመን ከፍታ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡

በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሴ ከተማ አቅራቢያ ማይ አድራሻ በተባለ ስፍራ 700 ቤቶች የያዘ ጥናታዊ ከተማ መገኘቱ አዲስ ታሪክ መሆኑን  እየተነገረ ነው፡፡

ከክርሰቶስ ልደት በፊት 1ሺህ 250 ዓመት የነበረ ስለመሆኑ ታውቋል። በዚህም የበርካታ  መገናኛ ብዙሀንና ማህበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል ፡፡ የሶስት ሺህ ዘመን ታሪካችንም በ250 አመታት ከፍ እንዲል አድርጎታል ማለት ነው፡፡

በክልሉ ያሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ቁጥር  እንዲጨምርና ዘርፈ ብዙ መስህቦች እንዲኖሩት ያደርገዋል ማለት ነው፡፡

’’ land of open museum’’ እየተባለ ይጠራል ፡፡ የተገለጠ የቅርስና ሙዝየም ምድር እንደማለት ነው ፡፡ የክልሉ መጠሪያ ከሆነም  ቆይቷል፡፡

የአርክኦሎጂ ቁፋሮው ይህን እውነታን ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ክልሉ እንደ የታሪክ ብዘሀነቱ፣እንደ ተፈጥራዊ መስህብነቱ፣እንደ ንግስናና የሀይማኖት ጀማሪነቱ ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ነገር ቢቀረውም በመስህብ ስፍራዎች ብዛቱና ስብጥሩ ግን በግንባር ቀደምትነት  ያስቀምጠዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች ከመብዛታቸው አንጻር የትኛው ተነስቶ የትኛው እንደሚቆይ ያስቸግራል፡፡

በአራተኛው ክፍለ ዘመን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የተስአቱ ቅድሳን ማረፊያ አክሱም መሆኑ ይታወቃል፡፡

’’አባ ጸህማ፣አባ ገሪማ፣አቡነ አሊፍ፣አቡነ ሀፍጼ፣አቡነ የማእታ፣አቡነ ጴንጠልዮንና አቡነ አረጋዊ’’ ከተስአቱ ቅድሳን መካካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የእነዚሁ ተስአቱ ቅድሳን ማረፊያዎች ትግራይ ውስጥ ይገኛሉ ፡፡ በገመድ የሚወጣው የአቡነ አረጋዊ ገዳምና 1ሺህ 600 አመት ያስቆጠረው የብራና መጽሀፍ መገኛ የሆነውን የአባገሪማ ገዳም ድንቅ የታሪካችን መግለጫዎች ተብለው ሊወሰዱ ይችላሉ ።

የሀይማኖት መቻቻልና የዲፕሎማሲ ማሳያ የሆነው አልነጃሺ መስጊድና አስሀባዎች ወይም ተከታዮች ያረፉበት ስፍራም ሌላው  የቱሪስት መዳረሻ  ነው፡፡

በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በሳዑዲ ሀገር በተነሳ የሀይማኖት ግጭት ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸውን  ሀበሻ ምድር ሂደው እንዲጠለሉ ባዘዙዋቸው መሰረት ረዥም መንገድ አቆራርጠው ያረፉበት ነጋሽ ከተማ የዘርፈ ብዙ መገለጫ ሀብታችን ነው፡፡

የአድዋ ጦርነትና ጦርነቱ የተካሄደባቸው ስፍራዎች የተራራዎች ስብሰብ  ሌላው የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገላጫና የአንገዛም ባይነት ማሳያዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን የጥቁር ህዝቦችም  አሸናፊነት መገላጫና ድንቅ የጀግንነትና የአንገዛም ባይነት ታሪካችን ተደማሪ ሀብት የሚገኝበት የመስህብ ስፍራ መሆኑ ነው፡፡

የፈላስፋው ያሬድ ዘ አክስማዊ መገኛ ምድር ትግራይ የብዝሀ ታሪክ ባለቤት ያደርገዋል ፡፡ የዜማ  ድርሰት ፈላስፋ ታላቁ ቅዱስ ያሬድና ከግእዝ ቋንቋ ጋር የተያያዙ ሀብቶቻችን  የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን ናቸው ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የሚታወቁ ’’እዝል’’፣’’ግእዝ፣’’አራራይ’’ የሚባሉ የዜማ መደቦች ከፈላስፋ ታላቁ ቅዱስ ያሬድ የተለገሱን ገፀ በረከቶች ለቱሪዝም መስህብነት ፋይዳቸው የጎላ ነው ፡፡

ከዚሁ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በዘመናኛ አጠራር  ’’ኖታ’’ተብለው የሚታወቁ  ከሰባት በላይ የዜማ ምልክቶች  በፈላስፋ ያሬድ የተፈጠሩ ስለ መሆናቸው ማንም ይስማማባቸዋል፡፡

የአክሱም ሀውልቶች፣መካነ መቃብሮች፣የበርካታ የአገራችን ነገስታት ዘውድ በአክሱም ጽዮን ማሪያም መገኘቱ የአገራችን ታሪክ ይበልጥ እንዲጎላ ያደርገዋል፡፡

የአጼ ዮሀንስ ቤተመንግስት ፣ የደጃች አብርሀ ’’ካስትል’’ና መቀሌ ከተማ የሚገኙ ጥንታዊና ባህላዊ የትግራይ ቤቶችም ሌላው የቱሪስት አውድ ናቸው፡፡

የሰማእታት ሀውልት ፣ እንዳዮሱስ ተራራ የሚገኙ የጣልያን ወታደር መቃብሮችም የጀግንነታችን ነጋሪ ስፍራዎች ናቸው፡፡የአሸናፊነታችንና የባለ ብዙ ታሪካችን መገለጫዎች ጭምር ፡፡

ኢህአፓ የትጥቅ ትግል የጀመረበት የአሲምባ ተራራዎች ተፈጥራዊ አቀማመጥም  የኢሮብ ብሄረሰብ እሴትና ባህላዊ ቅርስ  አዲስ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

አንድ የአሜሪካን ኩባንያ ቀልብ በመግዛቱ የአሲምባ ተራራዎች ለማስገብኘት  ስራ መጀመሩን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይለ ይገልጻሉ፡፡

እንኳን ለውጭ ዜጋ ለኢትዮጵያውን ጭምር የቱ ተይዞ የትኛው በይደር እንዲቆይ ለመለየት የሚያሳሳ ምድር ነው - ትግራይ ፡፡ 

ገርዓልታና አካባቢው የሚገኝ መልከ አምድራዊ አቀማመጥና ውቅር አብያተ ክርስትያናት መጎብኘትም  እውነትም ትግራይ የታሪክ ምድር ያስብላል፡፡

ኢዛናና ሳይዛና የተባሉ ቀደምት ነገስታት ያስፈለፈልዋቸው ውቅር አብያተ ክርስትያናት በውስጣቸው ብዙ ገድል ታቅፈዋል፡፡

ዴስአና ሕጉም ብርዳ ጥብቅ የተፈጥሮ ደንም የመስህቡ   አካል ናቸው፡፡ነፋሻማ አየር ከመለገሳቸው በተጨማሪ የበርካታ ብዝሀ ህይወት መገኛና ለመድሀኒትነት አገልግሎት የሚውሉ በርካታ እጽዋት የያዙ ጥብቅ ደኖች በጣፋጭ መአዛ ታውደው ከሩቅ ይጣራሉ ።

ትግራይን  በወፍ በጨረፍታ  እንዲህ ትመስላለችና እንጎብኛት ፣ እንደሰትባታለን !  እንረካባታለን ! እንኮራባታለን ! ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን