አርዕስተ ዜና

ዓለም አቀፍ ልምድ ያለው ባለሙያ አለመኖር የዘርፉን እድገት ጎትቷል - የምህንድስና ባለሙያ አለማየሁ አፈወርቅ

03 Jan 2018
2114 times

                     በረከት ሲሳይ (ኢዜአ)

በባህር ማዶ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሙያቸው ተሰማርተው ውጤታማ የሆነ ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ ይታወቃል። አገሪቷ በባዕድ ምድር ካሏት ከሶስት ሚሊዮን በላይ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ መካከል በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው  ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው እያበረከቱ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለተመሳሳይ ዓላማም በውጭ አገር ተምረውና በሙያቸው በተሰማሩበት የሥራ መስክ ልምድ ያካበቱት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ከእነዚህ መካከል ለአስራ አምስት ዓመታት በውጭ አገር በሥራና በትምህርት በተለይም ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በኃላፊነት ሲያስተዳድር የቆየው የምህንድስና ባለሙያ አለማየሁ አፈወርቅ እንግዳችን አድርገነዋል።

አቶ አለማየሁ በአሁኑ ወቅት በ325 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት አራት ሺህ የመስኩ ባለሙያዎች ቀጥሮ በመምራት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከአቶ አለማየሁ አፈወርቅ ጋር የዓለም አቀፍ ልምዱና ከኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ሀሳቡን እንዲያጋራ በሪያድ ቆይታ አድርጓል።

ኢዜአ፤ የትምህርት ዝግጅትህ ምን ይመስላል? 

አቶ አለማየሁ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ በምህድስና፤ ከአውስትራሊያ ሲቢኤስ የቢዝነስ ኮሌጅ በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪዬን  አግኝቻለሁ። አሁን ደግሞ በስዊዝ ኤስቢ ቢዝነስ ትምህርት ቤት በቢዝነስ አስተዳደር ሶስተኛ ዲግሪ ለማግኘት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነኝ። በተጓዳኝም ከጣሊያን ኢሲኦ ኮሚባል ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪ እየሰራሁ ነው።

ኢዜአ፤  ከአገር ከመውጣትህ በፊት ወደ ሥራ ስትሰማራ በየትኞቹ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በሙያ ተሳትፎ አድርገሃል?

አቶ አለማየሁ፤ ከኢትዮጵያ ከመውጣቴ በፊት ለአስር ዓመታት ያህል ሰርቻለሁ። ስራ የጀመርኩት ፊንጫ የስኳር ፋብሪካ ውስጥ ነው። እዚያ ባለሁበት ወቅት ደግሞ ጀማሪ የሳይት ኢንጂነር ነበርኩ። ከዚያም አርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል፣ በሃረር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው ሲኒማ አምፔር ከተቃጠለ በኋላ እድሳት ሲደረግለት በፕሮጀክት ኢንጂነርነት ተሳትፌያለሁ። በፈረንሳይ ጉራራ አካባቢ ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተቆጣጣሪነት ሰርቻለሁ። ሞጆ - አዋሳ መንገድ ሥራ በሳይት ኢንጂነርነትና ተያያዥ የሥልጠና መርሃ ግብሮችን ለውጭ ዜጎች ጭምር እሰራ ነበር። ከዚያም ጣርማ በር ኮምቦልቻ በመሄድ በሙያዬ በጥቅሉ ለአስር ዓመታት ስሰራ ቆይቻለሁ።

ኢዜአ፤ ከአገር ከወጣህ በኋላ በየትኞቹ አገሮች ላይ ሠራህ? ምን ዓይነት ሥራስ ነበር ስታካሂድ የነበረው?

አቶ አለማየሁ፤ ከአገር እንደወጣሁ ለአንድ ዓመት ያክል ዱባይ ቆየሁ፤ ዱባይ ሁለት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ሰርቻለሁ። በሁለቱም ላይ የፕሮጀክት ኢንጂነርነት ስራ ነው ያከናወንኩት። ከዚያም ባህሬን ሄድኩኝ፤ ባህሬን ውስጥ ያልተማርኩትን ያልሰራሁትን ሰምቼ የማላውቀውን በእኔ ልምድ ውስጥ ምንም ያልነበረ ነገር ገጠመኝ። እዚያ ከባህር ውስጥ አፈር አውጥቶ መሬት መፍጠር ሥራ ነበር ስሰራ የቆየሁት። ለዚህ ደግሞ 29 ሚሊዮን ኩዩቢክ ሜትር አሸዋ አውጥተን 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ፈጥረናል። ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ አቡዳቢ በኮንስትራክሽን ማናጀርነት ሄድኩኝ። እዚያም እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ የሚያስገቡ ግዙፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ ሌሎች ተቋሞችን ለዓመታት በኃላፊነት መርቻለሁ። አሁን ደግሞ ሸፖርጂ ለሚባል የዱባይ ኩባንያ እየሰራሁ ነው።

ኢዜአ፤ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የምትመራው ፕሮጀክት ምንድን ነው? ምን ያክል ሰራተኞች ታስተዳድራለህ?

አቶ አለማየሁ፤ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ። ስመጣ በሳይት ኢንጂነርነት ነበር። አሁን ደግሞ በፕሮጀክት ዳይሬክተርነት እየሰራሁ ነው። አሁን በዱባዩ ካምፓኒ ‘ሸፖርጂ’ ሥራ በፕሮጀክት ዳይሬክተርነት የሳዑዲ መንግሥት የኤሌክትሪክ ድርጅት ህንጻ ግንባታን እየመራሁ ነው። በ325 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ግንባታ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ይቀረዋል። አፈጻጸሙም መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ነው። በግንባታ 400 ኢትዮጵያውያን በተለያየ ሙያ ተቀጥረው ሥራቸውን እያከናወኑ ናቸው።

ኢዜአ፤  ከአገር ቤት ለመውጣት ምክንያትህ ምን ነበር? በወቅቱ የነበረውን የግንባታው ዘርፍ ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቶ አለማየሁ፡ ከአገር ቤት የወጣሁት ፈልጌ አይደለም። በወቅቱ በርካታ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ኩባንያዎች መጥተው ነበር። ከእነሱም ጋር በነበረኝ ልምድ የሥራ ጥያቄ ቀርቦልኝ ነው የወጣሁት እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት አልነበረኝም። ፍላጎቱም አልነበረኝም ነበር። በዘርፉ ላለባለሙያ የሚከፈለው በጣም ጥሩ የሚባል ነበር።

ኢዜአ፤ በኢትዮጵያ ያለውን የግንባታ ዘርፍ ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ክፍተቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ክፍተቶች በመኖራቸው ምን ዓይነት ችግርስ እያስከተሉ ናቸው?

አቶ አለማየሁ፡ እኛ አገርና ወጥተህ መካከለኛው ምስራቅም ሆነ ሌላው አገር ስትሄድ በጣም ይለያያል። በተለይም በዱባይ ያለው ግንባታ የዓለም አቀፍ ልምዶችን የቀመረ ስለሆነ ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ቴክኖሎጂውም የሥራ ክፍሉም በሁሉም ደረጃ በጣም ከፍ ያለ ነው። በአገራችን ለዘርፉ ከፍተኛ ገንዘብ ቢፈስም የጥራት ችግር አለባቸው። በአሰራር ረገድ በርካታ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ከእቅድ ጀምሮ ፕሮጀክቱን እስከ ማስረከብ ደረጃ ድረስ ያለውን ቆይታ ስታየው የአሰራር ክፍተት አለበት።

ለዚህ ደግሞ የባለሙያ እጥረት በተለይም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያለው ባለሙያ የለም። በተለይም ለዘርፉ ቴክኖሎጂ ያለው ቅርበት አናሳ ነው። በግንባታ ላይም የባለሙያ ስብጥር አለመኖርና በዚህ ምትክ ሁሉንም ሥራ በአንድ ሰው የማሰራት ሁኔታ ይታያል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የግንባታ ሥራ የሚሰሩና የሚያስፈልገውን ባለሙያ ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት እጥረት አለ። የኮንትራት ባለሙያውም የተለያዩ የሚያስፈልጉ የዘርፉ ሰራተኞችን ቀጥሮ የማሰራት ልምድ የለውም።ከዚያ ይልቅ ሁሉንም ሥራዎች አንድ ኮንትራክተር ብቻ ሲሰራው ይስተዋላል። ይህም ልምድ ሆኗል።

የፕሮጀክት አፈጻጸምን በተመለከተ ደግሞ በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች በጊዜው ባለመጠናቀቃቸው መንግሥትም ግለሰቦችም አላስፈላጊ ወጪ የሚዳርጉበት ሁኔታ አለ። በዚህ የተነሳ በተቀመጠላቸው ዋጋና በጊዜያቸው የተፈጸሙ ፕሮጀክቶች ቁጥርም አናሳ ናቸው። የፋይናንስ ችግር ያለ አይመስለኝም። ችግሩ ከእቅድ ጀምሮ በደንብ ካለመስራት የሚመጣ ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚያስፈልጉ ግብዓች ካለማሟላት የሚመጣ ነው። ይህም በዘርፉ እድገት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ኢዜአ፤ ታዲያ እነዚህን የዘርፉን እድገት የሚያስተጓጉሉ ችግሮች በምን መልኩ መፈታት አለባቸው የሚል ሃሳብ አለህ? 

አቶ አለማየሁ፡ ይህን የአገሪቷ ኢኮኖሚ የሚፈጥረውን አቅም ተከትሎ የሚስተካከል ነው። መንግሥትም በዚህ ላይ እየሰራ ነው። የተለያዩ ማሰልጠኛ ተቋማት እየተከፈቱ ነው። ለምሳሌ ያክል አማካሪ ድርጅቶች እንዳሉ ሁሉ ሥራውን እንዲያስፈጽሙ የሚያስችሉ ጽህፈት ቤቶች እንዲቋቋሙ መንግሥት ማበረታታት አለበት። ይህም ማለት ገለልተኛ ተቋም ሆነው ኮንትራክተሩን፣ አማካሪውንና በዘርፉ የሚሰማሩትን በሙሉ እያገናኘ ሥራው በአግባቡ እንዲሰራ የሚያደርግ ነው። ይህ ስራ በአንድ ኮንትራክተር ብቻ እንዳይወድቅ ያደርጋል። ይህ በራሱ ጥራት ያመጣል፤ አፈጻጸም ያሻሽላል፤ ውድድር ይፈጥራል፤ አላስፈላጊ ከሆኑ ወጪዎች ይታደጋል። ይህ ደግሞ በሂደት በዘርፉ ያለው ሙስናና ብልሹ አሰራር በመቀነስ ፕሮጀክቶች በጊዜ እንዲጠናቀቁ ይረዳል።

የእነዚህ ዘርፎች መከፈት ለአጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። እስካሁን በትምህርት ተደራሽነት ላይ ተሰርቷል። ይህ የተሳካ ይመስለኛል፤ አሁን ደግሞ በጥራት ላይ ቢሰራ እመክራለሁ። አጫጭር የትምህርትና የሥልጠና መርሃ ግብሮችም በመግስትም በባለሀብቱም ሊሰራ ይገባል። በተለይም በግንባታ ደህንነት ላይ መንግሥት ሊሰራ የሚገባው ዋና ጉዳይ መሆን መቻል አለበት። በሌላው ዓለም በደህንነት ላይ ክፍተት ያለበት ተቋራጭ ለሌላ ሥራ እንዳይታጭ ይደረጋል። ስለዚህ በደንብ መታየት አለበት። ከቀደምት ፕሮጀክቶች ልምድ የመውሰድ ዝንባሌም መጠናከር አለበት።

ኢዜአ፤ ወደ አገር ቤት ለመመለስና በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ምን ታስባለህ?

አቶ አለማየሁ፤ ከአምስት ዓመት በፊት የዱባይ የዘርፉ ባለሙያዎችን ይዤ ለመግባት ሞክሬ ነበር። ግን ባለው የአሰራር ክፍተት የተነሳ መግባት አልቻልኩም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዳያስፖራው በአገር ልማት ላይ እንዲሳተፍ የሚያግዙ አሰራሮች ቀልጣፋ ቢሆኑ መልካም ይመስለኛል።

ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ አገር ቤት ለመመለስና ባለኝ ሙያና እውቀት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት አለኝ። ይሁን እንጂ አሁንም በአገር ቤት በስምንት ባንኮች ላይ የአክሲዮን ድርሻ አለኝ። በእንስሳት እርባታ ላይም በተለይም በዶሮ እርባታ ላይ ተሳትፎ  እያደረኩኝ ነው።

ኢዜአ፤ ስለነበረን መልካም ቆይታ አመሰግናለህ።

አቶ አለማየሁ፡ እኔም እድሉን በማግኘቴ አመሰግናለሁ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን