አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ፊልም ጉዞ ሁለት ወደኋላ አንድ ወደፊት

01 Jan 2018
2157 times

                               አቢብ ዓለሜ (ኢዜአ)

ፊልም እንደ ሌሎች የአገራችን ኢንዱስትሪዎች ሁሉ ሊያድግ ሊመነደግ፣ “እሰይ አበጀህ፣ በርታ አያያዝህ ጥሩ ነው” ተብሎ እየተጓዘ መሆኑን ደፍሮ መናገር አይቻልም። እንደሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ሁሉ መመንደግና ማደግ የሚገባው ዘርፍ እንደሆነ ግን ሁሉም ይስማማበታል።

ዛሬ ላይ የፊልም ሰሪዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በገንዘብ፣ በአቅም ማነስ፣ በቅጅ መብትና በሌሎች ሳንካዎች ተተብትበው ከችግሩ ለመውጣት ትግል ላይ ናቸው። ችግሮች ቢገጥሟቸውም እንኳን በራሳቸው ገንዘብና የሰው አቅም “ለተመልካች ይሆናሉ” ያሏቸውን ፊልሞች ከመስራት አልሰነፉም።

የፊልም ተመልካቹ ተዘውትረው በሚቀርቡ የፊልም ሐሳቦች በመሰላቸቱ አዲስ ሀሳብ ማምጣት ያልቻለ በማለት ትችቱን ከመሰንዘር አልፎ ፊቱን ወደ ውጭ ፊልሞች አዙሯል። ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በፈጠረው የውይይት እድል በፊልም ዘርፍ ላይ ያሉ ፈተናዎችን ለይቶ ለማሳየት ሞክሯል።

ፊልሞችን እያወዳደረ የተሻለ የሰሩትን መሸለም፣ ከዓለም አቀፍና ከአገር ውስጥ ፊልሞች ልምድ ልውውጥ በማድረግ የዳበረ ልምድ ማካበት አላማው የሆነው ይህ ፌስቲቫል በየዓመቱ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ በመውጣት ለፊልሙ እድገት ይበጃሉ ያሏቸውን ሐሳቦች ለውይይት እያቀረበ በተቻለው መጠን መፍትሄ ለማምጣት እየተጋ ነው።

"አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ መንገር እስካልጀመሩ ድረስ የአፍሪካ ታሪክ የቅኝ ገዢዎችን ማንነት የሚያሞካሹ ይሆናሉ" በሚል መሪ ሐሳብ አፍሪካውያን ታሪካቸውን በራሳቸው አንደበት ይተርኩ 12ኛው የፊልም ፌስቲቫል መልዕክቱ ነበር። 

‘ሳንኮፋ የታሪክ አተራረክ ጥበብ’ በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው የፊልም ፌስቲቫል አዘጋጅ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ "በየጊዜው የፊልም ፌስቲቫሎችን ብናዘጋጅም እንኳን  የፊልም ኢንዱስትሪው ይበልጥ እየተፈተነ ነው" ሲል ያስረዳል።

በመሆኑም በፊልም ዘርፉ ላይ የሚታዩ አስቸጋሪ ፈተናዎችን ለመፍታት ፌስቲቫሉ የራሱ የሆነ አወንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይናገራል። የተለያዩ ጥናቶች በዘርፉ ላይ የተደረጉ ቢሆንም እንኳን የጥናቱን ውጤት ይዞ ለመፍትሔ በመትጋት ተወዳዳሪና ተወዳጅ ማድረግ አልተቻለም።

በፊልም ሰሪዎች፣ ደራስያን፣ ተዋንያን፣ መንግሥትና ፊልም ተመልካቾች መካከል የጋራ መግባባት ተደርሶ ፊልሙን ከወደቀበት ማንሳት የሚቻልበት ዕድል አሁንም አለ። የኢትዮጵያ ፊልም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችል ያደረጉት የቁሳቁስ እጥረት፣ ያልተደራጀ የፊልም ግብይት ስርዓት፣ በፊልም ሰሪዎችና በመንግሥት በኩል ያለው የላላ ግንኙነት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

ፊልም መስራት ቀላል ነገር አይደለም፤ ከፍተኛ በጀትና  የሰው ኃይል ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ዓቅም ያለው ፊልም ሰሪ ያስፈልጋል። በአገሪቱ ግን ፊልም ሰሪዎች ሁልጊዜ በገንዘብና ብቃት ባለው የሰው ኃይል እጥረት የሚፈተኑ ሆነዋል። ጥራት ያለው ስራ መስራት ያልተቻለው የፊልም ሰሪዎች የገንዘብ አቅም ውስን በመሆኑ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። የዚህ ችግር ድምር ውጤት የሚታየው በተራ ቁሳቁስና በተራ አቀራረብ የሚሰሩ ፊልሞች ተመልካቹ ጋር ሲደርሱ ሰለቹኝ በሚልበት ቅጽበት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት፤ ፊልሙን እንደትልቅ ዘርፍ አይቶ ድጋፍ እያደረገለት አለመሆኑ እርግጥ ጎልቶ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። "ፊልም ማሕበረሰብን ለማስተማር ይጠቅማል ተብሎ አይታሰብም" ብለው የመንግሥትን ድጋፍ “ዝቅተኛ ነው” በማለት የሚወቅሱ የፊልም ባለሙያዎች እየተበራከቱ ነው።

የቅጅ መብት ጉዳይ የኪነ ጥበብ ስራዎች መስራት ከጀመሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ ስሞታ የሚቀርብበት፤ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ቢቋቋምም ግለሰቦች፤ ተቋማትና ድርጅቶች የሰው የፈጠራ ሃብትን ያለ አግባብና ፈቃድ ሲመዘብሩ የሚስተዋል ሀቅ ነው። ይሄ እጣ የፊልሙንም ዘርፍ እየጎዳው ያለ ፈተና ነው።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በውጪ አገሮች በተለይ በአሜሪካ  እየተሸጠ ቢሆንም እንኳን የአገራችን ፊልም ግን አገር ውስጥ የሙዚቃውን ያህል እንኳን በስፋት መሸጥ አልተቻለም። ትምሕርት፤ ዕውቀትና የሙያ ክህሎት ያካበተ የፊልም ባለሙያ አለመኖር ደግሞ ሌላው ችግር ነው። ዛሬ ፊልም ለመስራት ፍላጎት ብቻ በቂ የሚመስልበት፤ ትንሽ ገንዘብ ያለው ሰው ፊልም የሚያዘጋጅበት፤ ከ15 ባልበለጠ ቀናት የፊልም ድርሰት ተጽፎ ለቀረጻ የሚወጣበት ጊዜ ሆኗል።

እርግጥ ነው ተሰጥኦ ለማንኛውም ነገር መሰረት ነው፤ ነገር ግን በትምህርትና በስልጠና ካልታገዘ ሂደቱ የኋልዮሽ ጉዞ ይሆናል። ፍላጎት ያለው ሁሉ ዳይሬክተር፤ የፊልም ጽሑፍ ደራሲ፤ አዘጋጅ፤ የካሜራ ባለሙያ፤ እየሆነ መምጣቱ ደግሞ የፊልም ጥራት ደረጃው እንዲወርድ አድርጓል።

የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሁሉ በየሰፈሩ ካሜራ ይዞ ፊልም ለመስራት የሚሯሯጥ ከሆነ፤ ተዋንያን የነበሩ ሁሉ ድንገት ተነስተው ፊልም ዳይሬክተር “ልሆን ነው” ካሉ፤ ግለሰቦች ሁሉ የፊልም አዘጋጅ ከሆኑ፤ ለእውቅናና ለዝና ብቻ የሚሮጥበት ዘርፍ እንጂ ተወዳዳሪ የፊልም ኢንዱስትሪ መሆን እንደማይቻል እሙን ነው።

ኢትዮጵያ ለውጪ አገር ፊልሞች ትልቅ ገበያ ሆና ሳለ፤ የአገር ውስጥ ፊልሞች ገበያ ደካማ መሆኑ ያነጋግራል። ፊልም ሰሪዎች ሁልጊዜ እንደሚሉት የውጪ አገር ፊልሞች ዘርፉን እየጎዱት ነው። በቅርቡ የተከፈቱ የውጪ አገሮች ፊልሞችን ተርጉመው ለአገር ውስጥ ተመልካች የሚያቀርቡ የሳተላይት ቴሌቪዢን ጣቢያዎች በፊልም ሰሪዎችና በተመልካቹ ላይ ትልቅ ጉዳት እያሳደሩ እንደሆነ በባለሙያዎች በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የአገር ውስጥ ፊልም ሰሪዎች ተስፋ በማጣት የፊልም ስራውን ለቀው መውጣት ወይም የውጪ አገር ፊልሞች በሚሰሩበት መንገድ እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ። ዘርፉ የሚመራው፤ የሚቆጣጠረው፤ በቅርበት ሆኖ የሚያስተዳድረውና የሚደግፈው ተቋምና የተማረ ባለሙያ ያስፈልገዋል።

መንግሥትም ዘርፉ ካለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጠቀሜታ አኳያ በቅርበት ሊደግፈውና ፊልምን ለአገር ሁለንተናዊ ብልጽግና መሣሪያነት ሊጠቀምበት ይገባል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን