አርዕስተ ዜና

ሁለተኛው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት መድረክ

31 Dec 2017
2742 times

         ብርሃኑ ተሰማ (ኢዜአ)

የግብጿ የቱሪስትና የመዝናኛ ከተማ  ሰሞኑን የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ተዋናዮችን ለሁለተኛ ጊዜ  ስታስተናግድ አህጉሪቷን ወደ በለፀጉትና  የተሻለ ሕይወት ወደሚመሩት አገሮች ተርታ ለማሰለፍ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚል ግብ ሰንቃ ነው። ለዚህም ባለሀብቶችና የንግድ ተቋማትን  አብረው ለመሥራት የሚያበቁ ስምምነቶችንና ድርድሮችን ማድረግንም በተጓዳኝ አስተናግዳለች።

በቀይ ባህርና በሲናይ በረሃ መካከል የተመሰረተችው ከተማ ከአገሪቷ 26 የአስተዳደር ክልሎች በደቡብ ሲናይ አስተዳደር የምትገኝ፣ ገቢዋን ከቱሪዝም ያደረገች ውብ ከተማ ናት። በአንድ በኩል የልምላሜና የአረንጓዴነት ገጽታ የሚታይባት በሌላ በኩል ደግሞ የተራቆተ ገላጣ ሜዳና በረሃማ የአየር ጸባይ የሚጫናት ከተማም ናት። የከተማዋ የአየር ጸባይ ከ25 እስከ 46 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ፣ ከዓመቱ ውስጥ ቢያንስ ለስድስት ወራት ቱሪስቶች የሚጎርፉባት ሥፍራም ናት። በዓለም ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎችም ከትመውባታል።

ታዲያ ይህቺን ከተማ ለአፍሪካ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የግብፅ መንግሥትና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድ ማህበረሰብ(ኮሜሳ) መገናኛ እንድትሆንና መድረኩንም ለሁለተኛ ጊዜ በተከታታይ እንድታስተናግድ መርጠዋታል።

አፍሪካ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስመዝግቡ አገሮች ይገኙባታል። በሕዝብ ብዛቷም በአንድ ቢሊዮን ነዋሪዎች ከእስያ ትለጥቃለች። በዚህም ከዓለም 15 በመቶ የሚደርሰውን ሕዝብ ይዛለች። ከዚህ በተቃራኒ አህጉሪቷ በዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላት አስተዋጽኦ ከሁለት በመቶ አይበልጥም። ለአብነትም እኤአ በ2016 ከወጪ ንግዷ 327ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።

በዓመቱም በወጪ ንግድ ዘርፍ  ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ስድስት አገሮች ናቸው። እነዚህም ደቡብ አፍሪካ 74 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ቀዳሚ  ስትሆን፣ ናይጄሪያ 35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 29 ቢሊዮን ዶላር፣ አንጎላ 27ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር፣ ሞሮኮ 22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በመሰብሰብ ተከታታይ ደረጃዎች ሲይዙ፤ ግብፅ በ22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ስድስተኛ ሆናለች።

ሌላው ጉዳይ የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ ንግድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ለአብነትም በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድ ማህበረሰብ (ኮሜሳ) 26 አባል አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ከ10 በመቶ አይበልጥም።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያቶቹ በአባል አገሮች መካከል ያለው ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ፣ ታሪፍ ነክ ያልሆኑና በአቅርቦት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች፣ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘው የንግድ ልውውጥና በኢኮኖሚ ካደጉ አገሮች ጋር ያለው የንግድ ልውውጥ እንደቀጠለ መሆኑ የኮሜሳ ዋና ፀሐፊ ሲንድሶ ንግዌናን የጠቀሰው የግብፁ ‘’ዴይሊ ኒውስ’’ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል።

ሻርም አል ሼክ ከተማ የመጀመሪያውን መድረክ በሰኔ 2008 ስታካሂድ በዚያ ላይ ከ300 በላይ የአንድ ለአንድ የንግድ ግንኙነቶች መፈጠራቸውንና በበርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ለመስራት የጋራ ስምምነቶች መደረጋቸውን መረጃው ያመለክታል። በዚህኛው መድረክ ደግሞ የስድስት አገሮች መሪዎችና ከአንድ ሺ የሚበልጡ ሰዎች እንደተካፈሉበት መረጃዎች ይገልጻሉ።

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት

የመድረኩ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት የአስተናጋጁና የተጋባዠ  አገሮች መሪዎች  በተገኙበት ‘’ዘ ሰሚት’’ በተባለው ትልቁ አዳራሽ ነው የተከናወነው። በመክፈቻውም መሪዎቹ ‘’የውጭ ኢንቨስትመንት ለአፍሪካ ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፤ አፍሪካ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የምታደርገው ጥረት በውስጥ አቅሟና ባላት የተፈጥሮ ሀብት መደገፍ ይገባዋል’’ የሚል-መልዕክት አስተላልፈውበታል።

ለአህጉሪቷ ልማት የግልና የሕዝብ ድርጅቶች ጥምረት፣ ውህደትና ፈጠራ የተሞላበት እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ገበያን ዘልቆ በመግባትም ሕዝቦቿን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና አገር በቀል ባለሀብቶችን የማጣትና በውጭ ባለሀብቶች ብቻ የመመካት አዝማሚያ መለወጥ እንዳለበትም አሳስበዋል።

መድረክ 2017ና ቀጣይ አቅጣጫዎች

አፍሪካን እርስ በርስና ከሌላው ዓለም ጋር በማገናኘት ኢንቨስትመንትን የመሳብና የምርትና የአገልግሎት ልውውጥን የማቀላጠፍ ዓላማ ያለው መድረክ የዘንድሮው መሪ ሀሳቡ ’’ኢንቨስትመንትን ለአካታች ዕድገት’’ (Driving Investment for Inclusive Growth) ነበር።

በመድረኩ የተሳተፉ መሪዎች ቁጥር ካለፈው በቁጥር ብልጫ ባያስመዘግብም፤ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉ መሪ ሆነዋል። የተሳታፊዎቹ ብዛት ወደ 1ሺ 500 እንደሚደርስ አዘጋጆቹ ይገልጻሉ።

በግብፅ መንግሥትና በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ(ኮሜሳ) ትብብር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ከቀዳሚው በተለየ የወጣት ሥራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕሩነሮች) ጉዳይ ትኩረት አግኝተዋል።

መሪዎቹም የተሻለችና ብሩህ ተስፋ ያላት አህጉር ለመገንባትና መንግሥታት ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ወጣቶችም ሥራ ወዳድ ሆነው በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና ለዚሀም ተቀራርቦ መሥራትና መደማመጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በዚህም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የሚለውጥ፣ ታታሪ፣ ፈጣሪና አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት እንደሚቻልም  እምነታቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩም በሥራ ፈጣሪነት የቀረቡት ግብጻዊው የሴሃ ካፒታል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አዛብ በሕክምናው ዘርፍ፣ የሩዋንዳው የሃቦና ሊሚትድ ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄን ቦስኮ ለአረንጓዴ ልማት የሚበጅ ማገዶ በመፍጠር ያስመዘገቡትን ውጤትና የደረሱበትን ደረጃ ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል።

የፓናል ውይይቶች

ርዕሰ ጉዳዩን ተንተርሶም ብዙ የፓናል ውይይቶች ተካሄደዋል። ከነዚህም የአፍሪካ አገሮች በድንበር ተሻጋሪ ንግድ ተጠቃሚ ለመሆን ተቀራርበው መሥራትና ተደጋጋሚ ታክስን ማስወገድ እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ የተሰጠበት የፓናል ውይይት አንዱ ነው። በፓናሉም በተጎራባች አገሮች መካከል የሚካሄደውን ድንበር ተሻጋሪ የንግድ እንቅስቃሴ ለጋራ ጥቅም ማዋል፣ ንግዱን የሚያስፋፉ ፖሊሲዎችን መቅረጽ፣ ሕጎችና መመሪያዎችን አውጥቶ በተግባር መተርጎም እንደሚያሻም ተጠቁመዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን ለመመስረትና የአህጉሪቷን ንግድ ለማቀላጠፍ የወጣው ፖሊሲና ማስተግበሪያዎቹ የአፈጻጸም ችግሮችና ተከታታይነት ስለሚጎድላቸው መፍትሄ እንደሚያሻቸውም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል። ተደጋጋሚ ታክስና ቀረጥ ማስከፈል በአገሮቹ መካከል ያለው ንግድ እንዳያድግ አድርጓታል።ከዚህም በላይ "የሸቀጦችን ዋጋ ያለአግባብ ንረት ስለሚፈጥር ሊወገድ ይገባዋልም" ብለዋል።

የአንጎላው ዩኒቴል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስስ ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ በአገሮች መካከል የሚካሄድ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ሕዝብን ከሕዝብ ለማገናኘት፣ የአገሮችን እምቅ ሀብት ለመጠቀምና አንዱ አገር የሚጎድለውን ከሌላው ለማሟላት ቢውል “ጠቃሚነቱ ጉልህ  ነው” ይላሉ።

አፍሪካውያን እርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከማድረግ ይልቅ “ወደ አውሮፓና አሜሪካ  ገበያዎች ማድላት ይታይባቸዋል” በማለት የሚተቹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የስዊዝ ኢኮኖሚ ዞን ሊቀመንበር አድሚራል መሐመድ ሁሴን ናቸው።

‘’በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄዱት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔዎች ዋነኛ ትኩረታቸው ከሰላምና ጸጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከማንሳት አያልፍም፣ በአንጻሩ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች ጉባዔዎቻቸውን ሲያካሂዱ ትኩረታቸውን ንግድ ላይ ያደርጋሉ’’ ሲሉም ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከጎረቤቶቿ ጋር የንግድ ግንኙነቷን ድንበር ተሻጋሪ ባንክ በመክፈት ሥራ መጀመሯንና ይህንንም የመሠረተ ልማት ተቋማትን በተለይም የመንገዶች ግንባታ በማካሄድ ማስፋፋቷን የደቡብ አፍሪካው ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ዳንኤል ማትጂላ አስታውሰዋል።

በአራተኛው ኢንዱስትሪ አብዮትና በአፍሪካ ባለው አተገባበር ላይ ባተኮረው ሌላው የፓናል ውይይት ደግሞ አህጉሪቷን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ማራመድ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተመልክቷል። ካለኢንዱስትሪ አብዮት ሥራ ፈጠራና ዕድገት እንደማይታሰብ ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ፣ ግሎባላይዜሽንን ጨምሮ በአህጉሪቱ ሕዝቦች ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሕይወት ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴው  መጎልበት እንዳለበት አሳስበዋል።

በዚህም ላይ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድ ማህረሰብ(ኮሜሳ) ዋና ፀሐፊ ሚስተር ሲንዲሶ ንግዌና “በአህጉሪቱ ሥራ ፈጠራን ለማበረታታት ሌላው ዓለም የደረሰችበት ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢነቱ አያጠያይቅም” ብለዋል።

የአህጉሪቷ ወጣቶችን የሥራ ባለቤት ለማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀና ራስን ከወቅቱ ጋር የሚያራምድ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም መንግሥታት ለልማቱ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልጋቸው ያወሱት ደግሞ የቀድሞው የእንግሊዝ የአፍሪካ የውጭና የጋራ ብልጽግና አገሮች ክፍል ኃላፊው ማርክ ሳይመንድስ ናቸው።

ሚስተር ካሪቡ ምቦጄ በሴኔጋልና በፈረንሳይ የሚንቀሳቀሰው የዋሪ ኩባንያ መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። አራተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት አፍሪካን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ስለሚያደርጋት ሊተኮርበት እንደሚገባና ኩባንያቸው በሁለቱ አህጉሮች ያገኘውን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም ሌላ አፍሪካ ለኢንቨስትመንትና ሥራ ፈጠራ ትኩረት በመስጠት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን የሕዝቦቿን ሕይወት ለመቀየር መሥራት እንደሚያስፈልጋት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያሳሰቡበት ውይይትም ተካሂዷል።

በፓናሉም የአፍሪካ ኤክዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ቤኒዲክት ኦራማህ በአፍሪካ የቀላል ኢንዱስትሪ ልማትን ማጠናከርና ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን መመስረት አፍሪካን በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችው ዓለም ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ሲናገሩ የሞሮኮው አቲጃሪዋፋ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር መሐመድ አል ኪታኒ ደግሞ አህጉራዊና በክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማፋጠን የሕዝቦቹን ኑሮ ያሻሽላል የሚል እምነት አላቸው።

የእስልምና ኮርፖሬሽን ለኢንቨስትመንት፣ ለኢንሹራንስና ለወጪ ንግድ ብድር የተባለው ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኦሳማ ቃዪሲም በበኩላቸው፤ አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በማሻሻልና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቷን በማሳደግ ለዕድገቷ  መሥራት እንዳለባት አሳስበዋል።

የአፍሪካ ኤክዚም ባንክና የግብፅ የኤክስፖርት ልማት ባንክ የወጪ ንግድን ለማጠናከር የ500 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በዚሁ ወቅት ተፈራርመዋል። ብድሩ ግብፅ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር የምታደርገውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማቀላጠፍ ይረዳታልም ተብሏል።

ኢትዮጵያ በቻይና-አፍሪካ አጋርነት ፓናል

አፍሪካ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለኢኮኖሚ ዕድገቷ ልትጠቀምበት እንደሚገባ የአህጉሪቱ መሪዎችና ምሁራን ያስገነዘቡት በመድረኩ ማጠቃለያ ዕለት በተደረገ የፓናል ውይይት ነበር።

በፓናሉም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የቻይናና አፍሪካ ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አህጉሪቱ ያሉባትን ችግሮች በፍጥነት በመፍታት ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የንግድ መዳረሻ መሆን እንደምትችልም ተናግረዋል። በማከልም ቻይና የነደፈችው ዓለም አቀፍ የትብብር ፍኖተ ካርታ ለሰው ልጆች የተመቸ ዓለም ለመፍጠር ራዕይ ያለውና አፍሪካንም ተጠቃሚ ስለሚያደርጋት “አፍሪካ ልትጠቀምበት ይገባል” ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባላት ውጤታማ ትብብር ግብርናን መሠረት አድርጎ የተገነባው ኢኮኖሚዋን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው እንቅስቃሴም በመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ፣ በትራንስፖርት፣ በኃይል አቅርቦትና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ድጋፏ ትርጉም ያለው እንደሆነም መስክረዋል።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀን ሐሳብ በመደገፍ ያጠነከሩት ደግሞ ሚስስ ሄለን ሄይ ናቸው። ሄለን የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የበጎ ፈቃድ አምባሳደርና የ’’ሜድ ኢን አፍሪካ’’ ኢኒሼቴቭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው። በአዲስ አበባም የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት ናቸው።

ሚስስ ሄይ ኢትዮጵያ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አመራር ከስድስት ዓመታት በፊት የጀመረችው የኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማ ደረጃ ላይ መድረሱን መስክረዋል። ‘’ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቻይና ባለሀብቶችን ወደ አገሪቱ ሲያስገቡና በጫማ ምርት ላይ እንዲሰማሩ ሲያደርጉ የትኛውም የአፍሪካ አገር በመስኩ አልተሳካላቸውም ነበር። አሁን ግን የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ተራምዷል። ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊማሩና ሊከተሏት ይገባልም’’ ሲሉ የቻይናና አፍሪካ ትብብር ፍሬያማ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ ባለፉት 14 ዓመታት እያስመዘገበችው ባለችው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገትና በተለይም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማቷ በሰጠችው ትኩረት ለአህጉሪቱ ሞዴል እንደሆነች ሲገለጽ የቆየውን ሁኔታ ይህኛው የፓናል ውይይት አጠናክሮታል።

መድረኩ ዕውቅና ያገኙ ኩባንያዎች

መድረኩ ከተካሄደባቸው ቀናት በሁለተኛው ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡ 12 ኩባንያዎች መመረጣቸው ይፋ ተደረገ። ከኩባንያዎቹ ሁለቱ ከኢትዮጵያ ናቸው። በመድረኩ ዕውቅና ለመግኘት ኩባንያዎቹ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ በተለየ መልኩ ነው የተዘጋጀው። ከነዚህም ደረጃውን ያገኙት ኩባንያዎች ከአህጉሪቱ ከ100 በላይ ኩባንያዎች ጋር በግብርናና በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ እንዲሁም በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በተካሄደው ውድድር ነው። ውድድሩ አካታች ዕድገትና በአፍሪካ ውስጥ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴን በመስፈርትነት እንዳካተተም አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ከተመረጡት ሁለት ኩባንያዎች መካከል በግብርና/ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ  የሐማሬሳ የምግብ  ዘይት ፋብሪካ በዘርፉ ባደረገው እንቅስቃሴ ተመርጧል። በሐረሪ ከልል የሚገኘው ፋብሪካው ምርቶቹ በገበያ ውስጥ ያላቸው ተፈላጊነትና ተመራጭነት እያደገ መምጣቱን መግለጫው አመልክቷል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በማር ምርት ላይ የተሰማራው ቤዛም ምርቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ጭምር እያከናወነ ባለው ጥረት ተመራጭ ሆኗል። ኩባንያው ምርቱን  ወደ እንግሊዝ በማስገባት ያስመዘገበው ውጤት አመርቂ በመሆኑ አሁን ወደ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መላኩ ታዋቂነት እንዳተረፈለትም ተገልጿል።

በውድድሩ ከናይጄሪያ  አራት፣ ከግብፅ ደግሞ ሁለት ኩባንያዎች ሲመረጡ፣ ከዚምባብዌ፣ ከኬንያ፣ ከቱኒዚያና ከቶጎ ደግሞ አንዳንድ ኩባንያዎች ከአሸናፊዎቹ መካከል ናቸው።

ሻርም አል ሼክ የአፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማጎልበት ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት አህጉሪቱን ካደጉት፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ካሉትና በመልማት ካሉ አገሮች ጋር በማገናኘት ሚናዋን ዳግም ለመወጣት ጥራለች።

አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ለመስተካከልና የሕዝቦቿን ሕይወት ለመቀየር እንቅስቃሴዋን ማጎልበት የቤት ሥራዋም ነው። ጊዜው የሚጠይቀው የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይልና የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደፊት መራመድ ሆኗልና በተቀናጀና በተግባቦት በመሥራት ለተሻለ ሕይወት መትጋት ያስፈልጋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን