አርዕስተ ዜና

የሞት መስመሮችን በመዝጋት ወገኖቻችንን እንታደግ!

30 Dec 2017
2368 times

መብራቱ  ይበልህ ( መቀሌ ኢዜአ )

ድሮ ድሮ  ዕዳጋ ብዕራይ ፣ ወወክማ ፣ እምባ ሰይራ  አልያም በየሰፈሩ የሚገኙ ትናንሽ መጫወቻ ሜዳዎች የመቀሌ ወጣቶች መሰባሰቢያ ስፍራዎች ነበሩ፡፡

ከመቀሌ ወጣ ስትል ደግሞ በአዲግራት ከተማ  ሜዳ ዓጋመ፣ በአድዋ ከተማ ደብርቺ ፣በአክሱም ከተማ ደግሞ ማይአኪ የሚባሉ ስፍራዎች እንዲሁ፡፡

በሌሎች ከተሞችም  ተመሳሳይ ሜዳዎች ማየት የተለመደ ነበር።

አሁን ግን ወጣቶች ተሰባስበው የሚጫወቱባቸው  ስፍራዎች  ደብዛቸው እየጠፋ የመጣ ይመስላል፡፡ 

ዓወት አርአያ ውልደቱም ሆነ  እድገቱ አሕፈሮም ወረዳ እንትጮ ከተማ መሆኑ ይናገራል፡፡ በለጋ የወጣትነት እድሜው በውትድርና የህዝብና የአገር አደራ ተሸክሞ  ለተወሰኑ አመታትም ግዳጁን እንደተወጣ  ይገልጻል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ግን በደለላ ጅንጀና የያዘውን ስራ እንደማያዋጣውና እንደማያልፍለት ይነገረዋል።  “ዕጣ ፈንታህ ሳዑዲ አረቢያ መሄድ ነው“ በማለትም ያሳምነዋል፡፡

ወጣቱ በደላላው  ንግግር  ቅንጣት ያህል አልተጠራጠረም፡፡  ልክ የአገሬ ሰው እንደሚለው “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሞኙ በሬ ሆይ ሳሩን አያህና ገደሉ ሳታይ“  ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ጓዙን ሸክፎ በነገታው ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡

በደላላው አቅጣጫ ጠቋሚነትና በሁለተኛው ተቀባይ አማካኝነት አዲስ አባባ ተክለሀይማኖት ሰፈር  አሸዋ ጊቢ በተባለው ሰፈር አረፈ። አሸዋ ጊቢ ዋል አደር ማለቱንም ቀጠለ፡፡

አሸዋ ጊቢ የወጣቶች መሰባሰቢያ አንዱ ማእከል ነው። ወጣቶቹ የሚሰበሰቡት ግን እንደ ድሮዎቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ለመዝናናት አይደለም።

ለአረብ አገር ጉዞ መገናኛና የጉዞ ቀን ገደብ ማመቻቻ ማእከል  ነው-አሸዋ ጊቢ። በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ወጣቶች በደላሎች አማካኝነት ይሰባሰቡበታል።

ከአዲስ አበባ ጅግጅጋ፣ሶማሌ ላንድ ከዛም ባህር አቋርጦ  ወይም ባህር ውስጥ ቀርቶ የሰቆቃ ህይወት የሚመራበት አደገኛ የሳዑዲ አረቢያ የጉዞ ቀጠና አንድ ተብሎ የሚጀመርበት የሞት መስመር መነሻ መሆኑን ወጣቱ ይናገራል።

ወጣቱ  በደላላዎች አማካኝነት ጅግጅጋ ከተማ መድረሱን ያስረዳል፡፡ከጅግጅጋ ከደላላዎች እጅ አምልጦ  ብዙ ወጪ ሳያስወጣ በራሱ ጊዜ ሱማሊ ላንድ ለመድረስ ያደረገው ሙከራ ግን አልተሳካለትም፡፡

ምክንያቱ  ደግሞ ኬላ ጠባቂው ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ደላላ ሆኖ እንዳገኘው በመግለጽ፡፡

ደላላው ለፖሊስ  ነግሮ  እንዲመለስ እንዳደረገውና ለደላላው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሲከፍለው ግን እስከ ድንበሩ ድረስ መንገዱ አልጋ በአልጋ እንደሆነለት ይናገራል፡፡

በዚህ ጊዜ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር  ደላላዎች ከጸጥታ አካላት ጋር የጠበቀ ግንኝነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡

በየመንገዱ ያለው ችግርና ስቃይ የሚነገር አይደለም ይላል፡፡

ያም ሆኖ ግን ባህር አቋርጦ ሳዑዲ አረቢያ ቢገባም ደህና ነገር አላጋጠመውም፡፡ በለጋ  እድሜው ስድስት አመት ሙሉ በግድ  ፍየል  ጠባቂ አደረጉኝ ይላል፡፡ እምቢ ካለ ደግሞ እስር ቤት እንደሚከቱት ያስፈራሩታል።

በስደት ህይወት በፀሃይ ተቃጥሎ ያጠራቀመው 70ሺህ ብር ይዞ ወደ አገሩ ሲመለስ ደግሞ ሌላ ጋሬጣ ጠበቀው።ወጣት ዓወት እንደሚለው በሌላ ደላላ ዘመድና አራጣ አበዳሪ እጅ ወደቀ።

ከሳዑዲ ያመጣውን ገንዘብ አታልሎ ተቀበለው። ደላላ አታለለኝ አራጣ አበዳሪ ደግሞ ደገመኝ ይላል ዓወት፡፡

ወጣት ዓወት በእጁ የነበረውን 70 ሺህ ብር ሲያጣ ወደ ወረዳ አስተዳደር በመሄድ የአምስት ሺህ ብር ብድር ጠየቀ።ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም ነገር አየውና ከስራ ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን እራሱን በማሳመኑ ነው፡፡

 ወደ ስራ ገብቶም በአገሩ ለማደግ መፍጨርጨር ጀምሯል። በሌላ አነጋገር ወደ ጤናው ተመልሷል ማለት ይቻላል። በአሁኑ ጊዜም የስደትን አስከፊነትና የጉዞ ውጣ ውረዶችን አስመልክቶ  ወጣቶችን በማስተማር አርአያ መሆን ጀምሯል።

ወጣት አድሀና ሀይለ ከመኾኒ፣ አፋር ፣ ጅቡቲ ሌላ በተዘረጋው የሞት መንገድ መሄዱ ይናገራል፡፡ ይህን መስመር ደግሞ በርካታ ወጣቶች ለህልፈት የዳረገ በጣም አደገኛ መንገድ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ወጣት አድሀና ከስደት ከተመለሰ አሁን አምስተኛ ወሩን ይዟል፡፡

የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ጅቡቲ ምድር እንደገቡ በውሀ ጥም 30 ያህሉ የጉዞ ጓዶኞቹ እንደጣ ዝግንን እያለው ይናገራል፡፡የአዳም አፈር እንኳ የሚያለብሳቸው አላገኙም በማለት፡፡

ደላላው የሰው ህይወት መጥፋቱን ደንታው አይደለም፡፡ እንደተራ ነገር ደውላችህ ቤተሰቦቻቸውን መርዶ ንገሩዋቸው እንዳላቸውም ያስታውሳል። በሞትና በህይወት መካከል ሆነው ትእዛዙን ከመፈፀም አማራጭ አልነበራቸውም።

 ከሞት የተረፉ ወጣቶች እንደምንም የመን መድረሳቸውን የሚናገረው ወጣት አድሀና እሱን ተከትሎ ሳዑዲ አረብ የደረሰ ታላቅ ወንድሙም  በመኪና አደጋ በሞት መነጠቁ ሌላ ፈተና ሆነበት፡፡በሰው አገር ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስም ሆነበት፡፡

 የጉዞ ጓደኞቹና የወንድሙ ሞት አሁንም ድረስ በስነ ልቦናው ላይ ተጽኖ እንዳደረሰበት ይናገራል፡፡አሁን ለራሱ ስደት ይብቃኝ ብሏል፡፡ ለሌሎች ወጣቶችም ችግሩን ይነግሯቸዋል፡፡

ሶማሊ ላንድ፣ጅቡቲና ሱዳን  የወጣቶች መውጫ በሮች መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ በወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኝነት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ገብረማሪያም ዘሚካኤል ናቸው፡፡

ባለፈው አመት ወደ ስደት ከሄዱ ወጣቶች በውሀ ጥም፣አልያም በባህር መስመጥና ሌሎች መሰል አደጋዎች 167 ወጣቶች ክልሉ አጥቷል፡፡ 141 ወጣቶች ደግሞ በህይወት ስለመኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

በአንዳንድ የክልሉ ቀበሌዎች እንደተጠናው  ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሲሉ የደርግን መንግስት ለመጣል ወጣቶች ከከፈሉት መስዋእትነት በላይ በህገ ወጥ ስደት የሚጠፋው ህይወት እያሻቀበ መሆኑ መምጣቱ ያሳያል።

አደጋው በጣም አስፈሪና አስከፊ ነው፡፡ ይህን ለመግታት ደግሞ የሀይማኖት ተቋማት ጭምር ሳይቀር ጉትጎታ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ወገኑ የሚወድ ሁሉ ሊያሳስበውና ሊከላከለው የሚገባ ተግባር በመሆኑ የሞት መስመር የሆኑት የስደት መንገዶቹ ሊዘጉ ይገባል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን