አርዕስተ ዜና

እንደ ሕዳር ታሕሳስም፣ ጥርም፣ ...ይታጠኑ ይሆን?

30 Dec 2017
1626 times

                     አስቴር ታደሰ /ኢዜአ/

የቆሻሻ አወጋገድ ልማዳችንን ሳስበው ሁሌም ወደኋላ መቅረታችን ይከነክነኛል። አንዳንዱ 'ንጽሕና ጠበቅኩ' ብሎ ቤቱንና ግቢውን አጽድቶ ቆሻሻውን ከግቢው ውጪ በራፉ ላይ ይደፋል። ሌላው ደግሞ የተጠቀመበት ማንኛውንም ነገር ያገኘው ቦታ ላይ ይጥላል። ይህን ድርጊት ምንይሉታል? አለመሰልጠን? ወይስ ለቆሻሻ ያለ አመለካከት አለመቀየር? 'ቆሻሻ አስወገድን' ብለን ሰው አየን አላየን እያልን ያገኘነው ቦታ ላይ መጣላችን ሊያስወቅሰንና ሊያስተቸን የሚገባ ጉዳይ ነው።

የፍሳሽ ማስወገጃ ተብለው የተዘጋጁ ቱቦዎች በተለያየ ደረቅ ቆሻሻ መድፈንስ ማን አስብሎ ሊያስጠራን ይችላል? ቱቦዎች እየተደፈኑ ፍሳሹ አስፋት ያጥለቀልቃል፤ መተላለፊያ ያሳጣል። በውጤቱስ የመዲናዋ ጎዳናዎች በሙሉ መጥፎ ሽታ በማመንጨት በአፍንጫችን በሽታን ጀባ ይሉናል።

በዓለም ላይ በንጽህናቸው የሚወደሱ  ከተሞች የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ደግሞ የሚወቀሱም አሉ። ከተማን ጽዱ የሚያደርገው የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብም መላቅ ጭምር እንደሆነ ከሩዋንዳ ርእሰ መዲና ከኪጋሊ መማር እንችላለን። ኪጋሊ በጣም ማራኪና ውብ ከሆኑ ከተሞች ተርታ ትመደባለች።

የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት የህንዷ ደልሂ በተቃራኒው ደግሞ ሁለት ገጽታ ተላብሳ 'ጽዱና ቆሻሻ ናት' ይባላል።

አከባቢንና ከተማን ብሎም ሀገርን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ ኃላፊነት ለአንድ አካል የሚተው ተግባር አይደለም። ነዋሪው ወይም ሕብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ካላመጣ  የአካባቢ ንጽሕናን ማስጠበቅ ያዳግታል። የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ከተቻለ ቆሻሻን የማስወገድ ስራውን ማቃለል ይቻላል።

የከተማው አስተዳደር ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻ ለማስጀመር ከመዲናይቱ የህዝብ ክንፍ አባላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት የታዘብኩትን አንድ ገጠመኝ ላስነብባችሁ ወደድኩ። መድረኩ ላይ የተቀመጡት ጽሁፍ አቅራቢ'' ቆሻሻን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ግምባር ቀደም መሪ መሆን አለብን የአንዲት ቆሻሻ መንገድ ላይ መውደቅ ብዙ ቆሻሻዎችን ያመጣል'' እያሉ ገለጻ እያደረጉ ባለበት ወቅት  የመድረኩ አስተባባሪ ለጽሁፍ አቅራቢዋ የከፈተውን የታሸገ ውሃ ሽፋን እዛው መድረኩ ላይ ጥሎት ሲወርድ አብረውኝ የተቀመጡት አዛውንት "ወቸው ጉድ እንግዲህ ማን ከማን ይሆን የሚማረው መቼ ይሆን የምንሰለጥነው" እያሉ ሲያጎተመትሙ ሰማሁ። የእርሳቸው ትዝብት እኔም ተጋባብኝ። ሌላ ገጠመኝ እንዳስታውሰም አደረገኝ።

ለአንድ ስብሰባ ከተለያዩ የውጭ አገሮች ከመጡ ዜጎች ጋር ለዘገባ በታደምንበት ወቅት ውይይቱ እንደተጀመረ ለእያንዳንዳችን በየተቀመጥንበት ጠረጴዛ ላይ የታሸገ ውሃ ታደለ። የውጭ አገር ዜጎች የታሸገውን ውሐ ሲከፍቱ ማሸጊያ ላስቲኩን ያስወገዱበት መንገድ አስተምሮኛል።ይሕም ማሸጊያውን ልጠው  መሬት በመጣል ፋንታ ከውሃው ፕላስቲክ ወገብ ላይ ወሸቅ ማድረጋቸው ነው።

ይህ ምን ያህል ለጽዳት ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ያላቸውን አመለካከትና አስተሳሰብ የሚያሳይ ነው። ከዚህ አይነቱ የጥንቃቄ  ዘዴ መማር ብልህነት ነው። ከዚያ በቀጥታ ወደ ሕሊናዬ የመጣው እኔም ሆንኩኝ ጓደኞቼና ባልደረቦች በአጠቃላይ ቤተሰቦቼና በአካባቢዬ ያለው ማሕበረሰብ የታሸገ ውሃ ስንጠጣ፤ የንጽሕና ወረቀት ስንጠቀም እንዲሁም ሌሎች የምናስወግዳቸውን የማይጠቅሙና ቆሻሻ ነገሮችን በግዴለሽነት የትም ስንጥል ብዙም አካባቢን ይበክላል ብለን ትኩረት እንደማንሰጥ ሳውቅ ተሸማቀቅኩ።

ቢሆንም ግን በአጋጣሚው  ትልቅ ትምህርት አገኘሁበት።ከዚያን ወዲህ በተቻለኝ አቅም እራሴንና እለት ተእለት አብረውኝ የሚውሉ ጓዴኞቼን ለማስተማር እጥራለሁ። ነገር ግን ይሕ ቀላል አይደለም ። የአንድና የሁለት ሰው ጥረት ለውጥ አያመጣም ብዬም አስብና ሁላችንም በየቤታችን ግንዛቤ ብንፈጥርና ከራሳችን ብንጀምር ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል እርግጠኛ እሆናለሁ።

ለዚህ ሁሉ ግን አጽንኦት መስጠት የሚያስፈልገው መጀመሪያ የነዋሪውን አስተሳሰብ መቀየር ነው። ሁሉም ይመለከተኛል ብሎ አካባቢውን ከብክለት ቢከላከል ከጉንፋንና ሌሎች ከቆሻሻ ወለድ በሽታዎች ራሱን መከላከል ይችላል። አሁን ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ልማድ ለመቀየርና ግንዛቤውን ለማሳደግ ሁሉም ጠንከር ያለ  የቤት ስራ መስራት ይጠበቅበታል።

አንድ ሰው ንጹህ አየር ለማግኘት ወይም ለመዝናናትና አዕምሮውን ለማደስ ከቤት ውጭ ነፋሻ አየር ለመቀበል ንጹሕና አረንጓዴያማ አካባቢዎች መሔድ አንዱ አማራጭ ነው። ነገር ግን ለዚህ የመዲናዋን ምቹነት ብንጠይቅ ደግሞ መልሱን ሳይነገረን እናውቀዋለን።በአሁኑ ወቅት የከተማዋን የሚያሸማቅቅ ታሪክ ለመቀየር የተጀመረው ዘመቻ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ልናክልበት የግድ ይለናል።

ስለከተሞች ጽዳት ሲነሳ በተለይ አዲስ አበባ እንደ አዋሳ፣ ባሕርዳር፣ መቀሌና ሌሎች ከተሞች እራስዋን ጽዱ ለማድረግ ለምን እንዳልተቻላት ሲታሰብ ሁሉም ይገረማል። ከተሞቹ የደረሱበት ለመድረስም ብዙ ይቀራታል፤ ይሕ ደግሞ አሁንም በነዋሪዎቹዋ የአስተሳሰብ ለውጥ ያለመምጣቱ ነው። መዲናዋ ከተቆረቆረች ከአንድ መቶ ሃያ አምስት አመታት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም ከነዚሁ ከተሞች በላይ ንጹሕ መሆን የሚጠበቅባት ቢሆንም ጭራሽ ወደኃላ እየተንሸራተተች ነው፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደመሆኑዋ መጠን በንጽሕና ቀዳሚውን ቦታ በመያዝ ተጠቃሽ መሆን ነበረባት፤ እውነታው ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ እየተጓጓዘና እየተባባሰ መጥቷል።

ነዋሪዎቿ ማለዳ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ራሳችንን፣ ቤታችንን፣ ልብሳችንና መጫሚያችን አጽድተን ወደ እየስራችንና ጉዳዮቻችን ለመሔድ የግቢያችንን ወይም የቤታችን በር ስንከፍት ከየጓዳችን ወጥተው በተከመሩ፤ ከተሞሉበት ከረጢት ፈሰው አካባቢውን በመጥፎ ሽታ በሚያውዱ የቆሻሻ ክምሮች መሐል አልፈን መጓዝ አብዛኛው የመዲናዋ ሕዝብ እየተላመደው የመጣ ጉዳይ ነው።

ከከተማዋ እድገትና እየጨመረ ከመጣው የነዋሪዎቿ  ቁጥር ጋር ተዳምሮ የየአካባቢያችን የንጽሕና ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ግልጽ ነው። ከተማዋ ከሁሉም ቦታዎች ከየቤቱ ተሰብስበው በሚጣሉ ቆሻሻዎች የሚወጣው መጥፎ ጠረን ነዋሪዎቹዋን ለበሽታ እየዳረገ መሆኑ ሁሉም በየቤቱ የሚገነዘብ ነው። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂና ባለቤቱም ራሱ መሆኑ ግልጽ ነው፤ በምን ቸገረኝ ስሜት ቆሻሻን ከቤቱ አውጥቶ ሲጥል እንጂ ይጎዳኛል ብሎ ሲያፀዳ የሚታይ ሰው ማየት ብርቅ እየሆነ መጥቷል።

በቅርቡም በተደረገው የጽዳት ዘመቻ ንቅናቄ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፎበታል፡፡ጅምሩ የተሳሳተ አስተሳሰብ በመለወጥ የጽዳት ባህልን ለማጎልበት ያግዛል።

በአዲስ አበባ ''እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እንናንተስ'' በሚል መሪ ሀሳብ የጽዳት ዘመቻ ንቅናቄው መጀመር ብቻ ሳይሆን በየወሩ የሚቀጥል ነው። ዘመቻውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመዲናዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች ጋር በመሆን አስጀምረዋል፤ በዚሁ መሰረትም በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ የመዲናዋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቅናቄ ያጸዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።          

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ "ጽዳት የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው እያንዳንዱ ቤቱን ማጽዳት ከቻለ አገራችንንም ከተማችንም ጽዱ ማድረግ እንችላለን" ብለዋል። ''የጽዳት ጉዳይ ከኑሮ ደረጃ ጋር የሚያያዝ አይደለም'' ያሉት አቶ ኃይለማሪያም፤ ትልቁ ጉዳይ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት መሆኑንም በአጽንኦት ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የክልል ከተሞች በመንገድ ላይ ቆሻሻ እንዳይጣል የሚታገሉ ሰዎች ተፈጥረዋል።መሰል አስተሳሰቦች በሁሉም አከባቢዎች መፈጠር እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአግባቡ ከተያዘ ቆሻሻ ዕዳ ከመሆን ይልቅ የኃብትና የገንዘብ ምንጭ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።       

የመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው ንቅናቄው ከተማዋን ጽዱና ውብ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ። በከተማዋ እድገት የመጣው የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እድገት ምክንያት ለአገልግሎት የሚውሉ ምርቶች፣ ሸቀጦች ተረፈ ምርቶች እንዲጨምሩ አድርገዋል፤ ይህም ደረቅ ቆሻሻ በከፍተኛ ደረጃ እንዲመነጭ ማድረጉን ያስታውሳሉ።    

የከተማው ነዋሪዎች የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የዳበረ ባለመሆኑ መዲናዋን ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆኗንም የሚገልጹት ከንቲባ ድሪባ ''ከየቤቱ በየቀኑ የሚወጣውን ቆሻሻ በዘመቻ ብቻ ማስወገድ አይቻለም'' ይላሉ። ቆሻሻን የሚጸየፍ የሰለጠነ ማሕበረሰብ መፍጠር ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።  

ወርሀዊው የጽዳትና አረንገዴ ልማት ህዝባዊ ተሳትፎ ውጤታማነት የሚለካው እያንዳንዱ በየቀኑ አካባቢውን ማጽዳትና አስተሳሰቡን መቀየር ሲችል ነው። ''ሁላችንም ነዋሪዎች ለከተማዋ ጽዳት በየቀኑ ምን አበረከትኩ? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል" በማለት ከተማዋን ጽዱና ውብ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶች ተቀይሰው እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው ይገልጻሉ።       

ራሱን የቻለ የጽዳት አደረጃጀት በመፍጠር፣ የአሰራር ደንቦችን በመዘርጋት፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ዘመናዊ መሳሪያዎች በመግዛትና ደረጃውን የጠበቀ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ በመገንባት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። 

አስተዳደሩ እንዳስቀመጠው በየወሩ የጽዳት ዘመቻ ለማድረግ መታሰቡን ነው።በአገራችን በአመት አንድ ቀን በወርሃ ሕዳር 12ተኛ ቀን ሁሉም አካባቢውን አጽድቶ ቆሻሻ በማቃጠል ያካበተውን ልምድ በታሕሳስም፣በጥርም በየካቲትና በሁሉም የአመቱ ወራት ይቀጥልበት ይሆን? የአስተሳሰባችንስ ለውጥ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይመጣ ይሆን? ወደፊት የምናየው ይሆናል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን