አርዕስተ ዜና

ከውሃ ምንጭነት … ወደ ኃይል ማማነት!

27 Dec 2017
2260 times

 

 

              ደሳለኝ ካሳ /ኢዜአ/

አምስት ያህል  የወጥ ድስቶችን  ጥዳ  ለምሳ ለማድረስ እየተጣደፈች  ነው፡፡ ሁሉም  ድስቶች   በኤሌክትሪክ ኃይል  በሚሰሩ  ምዳጃዎች  ላይ  ነው  የተጣዱት፡፡ ድስቶቹ  ከኤሌክትሪኩ ያገኙትን ኃይል ተጠቅመው እኔ እቀድም እኔ እቀድም በሚያደርጉት ፍክክር  የያዙት ነገር  ሲፍለቀለቅ ይታያል፡፡

ይህች  ወጣት  አለም ጸሃይ  ሚኒልክ  ትባላለች፡፡ ስድስት ኪሎ በተለምዶ መነን  ተብሎ   በሚጠራው አካባቢ  ምግብ  እየሸጠች ነው  ኑሮዋን የምትመራው፡፡

የስራዋ  በሀሪ  ከጠዋቱ  12፡00 ሰአት  እስከ  ምሽቱ 4፡00 ሰአት ድረስ  ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እንድትቆራኝ  አድርጓታል፡፡  

“ከመጥፋቱና   ከመቆራረጡ   ውጭ   ለኤሌክትሪክ  ኃይል ምን ይወጣለታል!   ያሰብከውን  ታደርግበታለህ፣ ትዕዛዝ በጥራትና  በፍጥነት  ታደርስበታለህ::”  በማለት ስራዋን እያቀላጠፈላትና እያቀለለላትም መሆኑን አጫውታናለች፡፡

ዓለምፀሃይ የኤሌክትሪክን ጠቀሜታ በሚገባ ትገንዘብ እንጂ መቆራረጡ ግን ሁሌም ያማርራታል፡፡  በስራ አካባቢዋ በየቀኑ ከሶስስት እስከ ስድስት ጊዜ መብራት ስለሚቆራረጥ በስራዋ ላይ መስተጓጎልን እያስከተለባት መሆኑንም ነው በምሬት የምትገልጸው፡፡

ወጣቷ እንደምትለው በተለይ በተለይ ደንበኞች ምግብ አዘው እየጠበቁ መብራቱ ድንገት ሲጠፋ በጣም ትሳቀቃለች፡፡  ደንበኞችን ላለመመለስ በፍጥነት ከሰል አያይዛ የደንኞቿን ፍላጎት ለማሟላት ትሞክራለች፡፡ ይህ ግን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉም ሌላ ጊዜ እንደሚወስድባትና ለጤናዋም መልካም እንዳልሆነ አልደበቀችም፡፡

ችግሩን ደውለው ቢያሳውቁም ባለሙያዎቹ ለጥገና የሚመጡት ከአምስት ቀናት በኋላ መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰውም ነው ዓለምፀሃይ ያጫወተችን፡፡ ለምሬት የዳረጋት የሃይል  መቆራረጡ እንጂ በኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀሙ “በጭስ ከመጨናበስና በጥላሸት ከመጎሳቆል” ግን ታድጓታል፡፡  

ወይዘሮ በላይነሽ ደመቀ ደግሞ በጡረታ ዘመናቸው እንጀራ እየጋገሩ ለደንበኞቻቸው በማቅረብ ኑሯቸውን መደጎም ከጀመሩ ከዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ እንጀራውን የሚጋግሩት በኤሌክትሪክ ሃይል በመሆኑ በስተርጅና ማገዶ ፍለጋ ከመንከራተት ድነዋል፤ ስራቸውም ቀሎላቸዋል፡፡ እኝህ  እናት  እንደሚሉት  ለኤሌክተሪክ ሃይል የሚከፍሉት  እንጨት ለመግዛት  ከሚያወጡት  ያነስ  መሆኑ ከዋጋ አንጻርም  የተሻለ ነው፡፡  የኤሌክትሪክ መቆራረጡ የተለመደ ቢሆንም ችግሩ ግን  የዓለምጸሃይን ያህል ለምሬት አልዳረጋቸውም፡፡  መብራት ቢጠፋም ብዙ ሳይቆይ ስለሚመጣ በስራቸው ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንደሌለውም ነው የሚናገሩት፡፡

ወይዘሮ  ጸኃይ ወርቁ የተባሉት የመዲናዋ ነዋሪም የምግብ ፍጆታቸውን በኤሌክትሪክ ኃይል ማብሰል ከጀመሩ 20 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ወይዘሮ  ጸሀይ እንደሚሉት  የኤሌክትሪክ  ሃይል መጠቀማቸው “እሳት ለማቀጣጠል ወዲወዲህ ከመንጎራደድ፣ አመድ ሲከማች  አፍሶ ከመድፋት፣ በእሳት ነበልባል  ከመገረፍ፣…” ገላግሏቸዋል፡፡

የኤሌክትክ ኃይል መጠቀም እንደ እንጨትና ከሰል ቤትን እንደማያቆሽሽ የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሀይ የአገልግሎት ክፍያውም ለማገዶ እንጨት ከሚያወጡት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ አልፎ አልፎ ሲጠፋ ከሚያደርሰው መስተጓጎልና የአደጋ ስጋቱ በስተቀር   የኤሌክትሪክ ሃይል  መጠቀም  የኑሮን  ጫና  እንዳቀለለላቸው ነው  የሚናገሩት፡፡ 

በኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ  አገልግሎት   የኮምዩኒኬሽን   ዳይሬክተሩ አቶ  ገብረ  እግዚአብሔር  ታፈረ    እንደሚሉት   ህብረተሰቡ   ከማገዶ   ወደ   ኤሌክትሪክ   ሃይል   ተጠቃሚነት    እንዲሸጋገር    እያደረጉ  ካሉ   መልካም   አጋጣሚዎች   መካከል   የኤሌክትሪክ  አግልግሎት  ታሪፉ     እርካሽ   መሆን   በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

 እንደ   ኬንያና ሱዳን   ባሉ ጎረቤት   ሃገራት   ሳይቀር   የአገልግሎት  ክፍያው  በኪሎዋት  እስከ  16  የአሜሪካ ሳንቲም እንደሚደርስ ገልጸው ኢትዮጵያ  ግን   በኪሎዋት ሁለት  የአሜሪካ ሳንቲም   ብቻ  እንደምታስከፍል አብራርተዋል፡፡

እድገቱና  ኢንፍሌሽኑ    ከጊዜ ወደ  ጊዜ    እየጨመረ   ቢመጣም   አነስተኛ  ገቢ ያላቸውን  የህብረተሰብ    ክፍሎች   ተጠቃሚነት    ለማረጋገጥና    የኢንቨስትመንት   ፍሰቱን   ከግምት  ውስጥ በማስገባት  በመንግሥት ድጎማ እየተደረገለት   በአገልግሎት ታሪፉ  ላይ  ጭማሪ   አለመደረጉንም    ነው    ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ይህም  የተጠቃሚው   ቁጥር   እንዲጨምርና  የአኗኗር  ዘይቤውም   በዚያው  ልክ  እንዲሻሻል አድርጎል፡፡ ዘመናዊነት   ከኤሌክትሪክ  አገልግሎት  ጋር  ጥብቅ   ቁርኝት   አለው  የሚሉት  ዳይሬክተሩ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረው ማህበረሰብ  አገልግሎቱን   በተሟላ መልኩ ማግኘት   ሲጀምር  ደግሞ በሁለተናዊ   አኗኗር ዘይቤው   ላይ   ስር ነቀል  ለውጥ  እንደሚያመጣም   ነው  ያብራሩት፡፡      

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የኃይል መቆራረጡ በዋናነት የሚከሰተው  ከኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ቴክኒካዊ  ችግሮች እንዳሉ ሆነው የትራንስፎርመሮች  ማርጀትና   ከስታንዳርድ  ውጭ  መሆን እንዲሁም  ደረጃቸውን ያልጠበቁ መገልገያ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ለሃይል ብክነቱ በመንስዔነት ተጠቅሰዋል፡፡

“የኤሌክትሪክ   ሃይል  የሃገሪቱን  ህዳሴ  ወደፊትም  ወደ ኋላም  የመጎተት   አቅም  አለው”  የሚሉት አቶ ገብረ    እግዚአብሔር   በሃል  መቆራረጥ  የሚከሰተውን    ችግር   ለመቅረፍ  ያመች ዘንድም   ያረጁ ትራንስፎርመሮችን የመቀየር፣ ሃይል የማተላለፍ አቅማቸውን የማሳደግና ከኮንክሪት የተሰሩ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን የመትከል ስራዎችን  በበጀት ዓመቱ ለማጠቃለል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ  አዲስ  አበባን  ጨምሮ  አዳማን፣  ሃዋሳን፣ መቀሌን፣ ደሴንና ባህር ዳርን   የሚያጠቃልሉ ሲሆኑ ቀጣይ ደግሞ በተመረጡ  ስደስት   ከተሞች የማስፋፊያ   ስራው  እንደሚቀጥል   አመላክተዋል፡፡  እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከ66  ኪሎ ቮልት   በታች   አቅም  ያላቸውን  ትራንስፎርመሮች   የማሳደጉ  ስራ  ሲጠናቀቅ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው  የመዲናዋ  ችግር  ይቀረፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከስር ከስር ለመፍታት ቀጣይነት ያለው ስራ  መስራትን እንደሚጠይቅም ነው ዳይሬክተሩ ያሰመሩበት፡፡

የማሻሻያ ስራ በተደረገባቸው አካባቢዎች ችግሩ ቀለል ቢልም የማሻሻያ ስራ ባልተሰራባቸው አካባቢዎች ግን ችግሩ ሰፊ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ  የችግሩ ስፋት   በአንድ  ከተማ ሳይቀር ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ገልጸዋል፡፡

አቶ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት  ከችግሩ መስፋት በተጨማሪ ደንበኞች ችግር ሲገጥማቸው በሰዓቱ አለማስመዝገባቸውና የስራ መደራረብ በተለያየ ምክንያት አገልግሎቱ ሲቋረጥ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት ሆነውባቸዋል፡፡

 ለመሆኑ  የኤሌክትሪክ ኃይል  አቅርቦት ታሪካዊ ዳራ ምን ይመስላል?

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲዝል በሚሰሩ ጀነሬተሮች አማካኝነት የብርሃን ብልጭታ የታየው በ1890  ዓ.ም እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  በ1904 ዓ.ም ደግሞ  ከአቃቂ ወንዝ  ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ሜጋዋት  የኤልክትሪክ ኃይል  ለማመንጨት ተችሏል፡፡ ከታዳሽ ሃይል ኤሌክትሪክ  ማመንጨት ከተጀመረ አንድ ምዕት ዓመት ቢቆጠርም እስከ 1983 ዓ.ም የሀገሪቱ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ370 ሜጋ ዋት አላለፈም፡፡ ተደራሽነቱም በ320 ከተሞች ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክተሪክ አቅርቦቱን  ከ4ሺህ ሜጋዋት በላይ ከማሳደግ በተጨማሪ ተደራሽነቱንም   ወደ 6ሺህ 387 ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ማስፋት ተችሏል ፡፡

የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ  ኃይል  የውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ  ምስክር ነጋሽ እንደሚሉት  በግንባታ ላይ ያሉ  ፕሮጀክቶች  ተጠናቀው  በሙሉ አቅማቸው ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ  የሃይል  አቅርቦቱ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ይላል፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ደግሞ  የኃይል አቅርቦቱን ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡

አቶ ምስክር በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት አድርገው እንዳብራሩት ኢትዮጵያ ከውኃ እስከ 50 ሺህ ሜጋዋት፣ ከነፋስ እስከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜጋዋት፣ ከእንፋሎት (ጂኦተርማል) 10 ሺህሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል  የማመንጨት  አላት፡፡

6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ 63 በመቶው ተጠናቋል፡፡ የገናሌ ዳዋ ፕሮጀክትም 94 በመቶ የሚሆነው ግንባታ የተከናወነለት ሲሆን ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ  254 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል፡፡ ግንባታው ሊቋጭ 4 በመቶ ብቻ የሚቀረው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም 750 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከውሃና ነፋስ በተጨማሪ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምራለች፡፡ ከአሎቶ ላንጋኖ ብቻ በሶስት ምዕራፍ 70 ሜጋዋት የኤልክትክ ኃይል  ለማመንጨት  እየተሰራ ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ  በኦሮሚያ ክልል ታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በአራት ቢሊዮን ዶላር ከእንፋሎት 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ  ሃይል ማመንጨት ለሚያስችሉ ሁለት ፕሮጀክቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ውል ታስሯል፡፡  

በሀገሪቱ በመከናወን ላይ ያሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስፋፊያ  ስራዎች ኢትዮጵያን ከውሃ ምንጭነት ወደ ሃይል ማማነት ያሸጋግሯታል፡፡ ይህ ደግሞ  በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከማሟላት በተጓዳኝ  የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላታል፡፡ ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር  ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ያጎለብተዋል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የከባቢ አየር ብክለትን በመቀነስ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እውን ያደርገዋል፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስተሪ መሪ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን እንቅስቃሴም ያፋጥንላታል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን