አርዕስተ ዜና

የሩብ ምዕት ዓመቱ ፌደራላዊ ስርዓታችን….

23 Dec 2017
2439 times

                                             እንግዳ መላኩ/ኢዜአ

የዓለማችን ሁለት አምስተኛ ያህሉ ህዝብ በፌደራላዊ ስርዓተ መንግሥት ይተዳደራል፡፡ አብዛኞች እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ አውስትራሊያ፣… ያሉ ታላላቅ ሀገራት በፌደራላዊ ስርዓት የሚመሩ ናቸው፡፡ እንደ ናይጀርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ የመሳሰሉ ታዳጊ ሀገራትም ስኬታማ የሚባል የፌደራል ስርዓት መስርተዋል፡፡

የስልጣን ክፍፍል፣ የተለያየ ሃላፊነትና ተግባር ያላቸው ሁለት ምክር ቤቶች መኖራቸው እንዲሁም  የህገ መንግሥት ገላጋይ ተቋማት መመስረታቸው ፌደራላዊ ስርዓተ መንግስት የሚከተሉ ሀገራትን ያመሳስሏቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን  በሁሉም ሀገራት ያለው ፌደራላዊ የአስተዳደር ስርዓት ፍጹም አንድ አይነት ነው ማለት አይደለም፡፡

ሰፊ የግዛት ወሰን ያላቸው ሀገራት የአስተዳደር ስርዓታቸውን ለማሳለጥና ህብረተሰቡንም በቅርበት ለመድረስ /ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያመቻቸው ፌደራላዊ ስርዓትን ይመርጣሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚነሱ  ግጭቶችን  ለማስወገድና የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያመች ዘንድም ፌደራላዊ ስርዓት ቀዳሚ ምርጫ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያሏቸው ሀገራትም እንዲሁ ብዝሃነታቸውን በአግባቡ ለማስተናገድ ፌደራላዊ ስርዓተ መንግሥትን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ እንደ ካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ሰዊዘርላንድ፣ ህንድና ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሀገራትን በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እየተመራች ሁለት አስርት ዓመታትን ተሻግራለች፡፡ ይህን የሀገሪቱን  የ26 ዓመታት የፌደራሊዝም ጉዞ የሚተቹም የሚያደንቁም አካላት አሉ፡፡ ብዙዎቹ ሀገሪቱ ከነበረችበት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ወጥታ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘችባቸውን ሁሉን አቀፍ ለውጦች በአስረጅነት በማጣቀስ ጨቅላ ፌደራላዊ ስርዓቷን ያሞካሹላታል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን አጣቅሰው የሀገሪቱን ፌደራለዊ ስርዓት የሚነቅፉ ወገኖችም አሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግና መንግስት አስተዳደር ትምህርት ክፍል (college of law and governance)  በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የፌደራል ጥናቶች ማዕከል  መምህሩ ዶክተር ስዩም መስፍን ግን የኢትዮጵያን ፌደራላዊ ስርዓት አብዝቶ ለማሞካሸትም ሆነ ለመተቸት ጊዜው አይደለም የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚያነሱት የእድሜውን ለጋነት ነው፡፡ ፌደራላዊ ስርዓቱ በየጊዜው እየተሻሻሉ ከሚሄዱ እንከኖቹ ጋርም ቢሆን መልካም በሚባል ጉዞ ላይ መሆኑን ግን ዶክተር መስፍን አልሸሸጉም፡፡ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ስርዓቱ በተገረሰሰበት ማግስት ፌደራላዊ ስርዓትን ተቀዳሚ ምርጫዋ ማድረጓ ተገቢና ወቅታዊ እንደነበርም ነው አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩት፡፡

የቀድሞው የፌደራልና አርብቶ-አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስትርና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ካሳ ተክለ ብርሃን ከአንድ የሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዓት በዋናነት ማንነትን መሰረት ያደረገ ይሁን እንጂ መልክዓ ምድራዊ መነሻም አለው፡፡ ለዚህም በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክልሎች የሚኖሩ ከአንድ በላይ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ማንነት ጠብቀው የጋራ ማንነታቸውንም አክብረው እየኖሩ መሆናቸውን በማሳያነት አጣቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት መደባዊና ብሔራዊ ጭቆናዎችን አስተናግዳለች፡፡ እነዚህን ጭቆናዎች ለማስወገድና በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ለመመስረት እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ማንነትን ለማስከበር በርካታ መስዋዕትነትን የጠየቁ ጦርነቶችም ተካሂደዋል፡፡ ጦርነቱ በድል መጠናቀቁን ተከትሎ እውን የሆነው ፈደራላዊ ስርዓትና ህገ መንግሥት ለዜጎች ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ወግ፣ ባህልና ማንነት እውቅና በመስጠቱ የቋንቋና የማንነት ጉዳዮች የስጋት ምንጭ ከመሆን ይልቅ በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ አንድነት  መሰረት ወደ መሆን ተሸጋግረዋል፡፡

ፌደራላዊ ዴሞክራሲያውዊ ስርዓቱን ከማጎልበት ጋር በተያያዘ በተለይ እስከ 1997ቱ ሀገር ዓቀፍ ምርጫ ድረስ የነበረው የፖለቲካ ምህዳር ሰፊና ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነቱም የተሻለ እንደነበር  ዶክተር ስዩም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውክልና እየሰፋ እንደነበር ይገልጹና ከምርጫ 97 በኋላ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የፓርላማ መቀመጫዎች በገዥው ፓርቲ መያዛቸው ግን ትክክል ነው የሚል እምነት የላቸውም፡፡ መልካም ጅማሮ ያስመዘገበውን ፌደራላዊ ስርዓት ለማጎልበትና ህልውናውን ለማረጋገጥ ካስፈለገ ወቅቱን የጠበቁ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያምናሉ፡፡  

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ለብዝሃነት ትልቅ ትኩረት የሚሰጡ ሀገራት ብዝሃነቱን መሰረት ያደረጉና የተለያየ ርዕዮተ ዓለም የሚያንጸባርቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያመች ዘንድ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥልቅ ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በዚህም የምርጫ ስርዓቱ 20  ከመቶ ተመጣጣኝና 80 በመቶ ደግሞ አብላጫ ድምጽ እንዲሆን ከውሳኔ ላይ መደረሱን  ዶክተር ስዩም አድንቀዋል፡፡  የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት ደግሞ በገዥውና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት የህገ መንግሥት ማሻሻያዎችን  ጨምሮ ወደሌሎች ዘርፎች ሊሰፋ ይገባል የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም እንደሚሉት የፌደራል ስርዓቱ በተለይ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ለዚህም በየክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፉ የመንገድ፣ የትምህርትና ጤና መሰረተ ልማቶችን በአብነት አንስተዋል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ህዝቦች “በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲዳኙና በማንነታቸው እንዲኮሩ እንዲሁም ሃይማኖት፣ ባህልና ወጋቸውን እንዲሁም ታሪካቸውን  እንዲንከባከቡና እንዲያሳድጉ” በር ከፍቶላቸዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት ጨምሮ  በንብረትና በአካል ላይ ጉዳት ያስከተሉ  ግጭቶችና አለመግባባቶች ተከስተዋል፡፡ የግጭቶቹ መንስዔ ምንም ይሁን ምን በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸ ግን  አይደገፍም፡፡ የተወሰኑ አካላት  እነዚህን ግጭቶችና አለመግባባቶች የሀገሪቱ ፌደራላዊ ስርዓት ውጤቶች አድርገው ይፈርጇቸዋል፡፡ ፌደራላዊ ስርዓቱ  ከአንድነት ይልቅ ለመለያየት በር ከፍቷል የሚሉ አስተያቶችን የሚሰነዝሩትም ቢሆኑ ለማጣቀሻነት የሚያነሱት እነዚህን ግጭቶች ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ እርግጥ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዓት ለዚህ መሰሉ ግጭት በር የሚከፍትና ለመለያየትም የሚገፋፋ ይሆን?

ዶክተር ስዩም መስፍን እንደሚሉት ግጭት ለየትኛውም የዓለም ሀገር አዲስ አይደለም፡፡  ዛሬ በፌደራል ስርዓቱ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት በነበሩት ስርኣቶችም በተለይ በወሰን አካባቢዎች መሰል ግጭቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር ስዩም የግጭቶቹ አካሔድና መገለጫዎች ግን ከሌላው ጊዜ የተለዩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን በአብነትያነሳሉ፡፡

ዶክተር ስዩም በቅርቡ እየተስተዋሉ ላሉ ግጭቶች ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ህገ መንግስቱ ለብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተሳሳተ መልኩ ከመረዳትና ከመተረጎም የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን አሁን በአንድ ክልል ውስጥ ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ እንዲሁም በጋብቻና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች ተሳስሮ የሚኖረው ዜጋ ሳይቀር የዘር ሀረግ እየመዘዘ  “አንተ የኔ ያኛው ደግሞ የሌላ”  መባባል ጀምሯል፡፡

ዶክተር ስዩም ለዚህ በማሳያነት የሚያነሱት  በቅርቡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ነው፡፡ የግጭቱ መንስዔ የወሰን ጉዳይ ነው ቢባል እንኳን ግጭቱ በወሰን አካባቢ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ብቻ መሆን ሲገባው መሀል ሀገር ጎጆ ቀልሶ ህይወቱን የመሰረተውን የሌላ ክልል ተወላጅ እያሰሱ ማጥቃትና አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ማስገደድ ግን ግጭቱ ከወሰን ያለፈ ጉዳይ እንዳለው ያመላክታል፡፡ ይህ አይነቱ አመለካከት ህብረተሰቡን ብቻ ሳይሆን በአመራር ደረጃ ያለውን አካልም ሳይቀር እየተጠናወተው መሆኑን ነው ዶክተር ስዩም የሚናገሩት፡፡

ዶክተር ስዩም ለግጭቶቹ በምክንያትነት የሚያነሱት ሌላኛው ጉዳይ  ከአፈጻጸም ጉድለት ጋር ይያያዛል፡፡ ያለውን ፌደራላዊ ስርዓት  በአግባቡ መተግበር ቢቻል “በተለያየ ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ሰላማዊና ተቋማዊ በሆነ መንገድ” መፍታት አስቸጋሪ እንደማይሆን የሚናገሩት ዶክተር ስዩም  የመንግሥት አመራሮች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዴሞክራሲና መሰል ተቋማትን በአግባቡ አለመጠቀማቸውና ግጭቶችንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት አለመታተራቸው እንዲሁም በተለያየ አካባቢ ከማንነትና መሰል ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡና በወቅቱ አለማስተናገዳቸው ለግጭቶች በር ይከፍታሉ ባይ ናቸው፡፡

አምባሳደር ካሳ ተክለ ብርሃንም ግጭቶች በዋናነት ከአመራርና ከዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር እንዲሁም ከድህነት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ እኛ የራሳችንን ማንነት የምንፈልገውንና የምንወደውን ያህል ሌላውም ማንነቱን እንደሚወደውና እውቅና እንዲሰጥለት እንደሚፈልግ ከልብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አምባሳደር ካሳ  እንደሚሉት ዴሞክራሲን ከፍላጎት በዘለለ መልኩ የህብረተሰቡ፣ የተቋማትና የአመራሩ ባህል በማድረጉ ረገድ ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችም  ከፌደራላዊ ስርዓቱ ሳይሆን ከዴሞክራሲ ባህል አለመዳበርና ከአመራር ችግሮች የሚመነጩ  ናቸው፡፡

አምባሳደር ለግጭቶች መፈጠር ያስቀመጡት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ድህነት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስኬታማ ስራዎች በርካቶች ከድህነት ቢላቀቁም አብዛኛው ህብረተሰብ አሁንም ቢሆን “ድህነትን በቅጡ መዋጋት” አለመጀመሩን የሚናገሩት አምባሳደር ካሳ በተለይ ወጣቱ ሃይል ጉልበቱን እውቀቱንና የአካባቢውን ጸጋ ተጠቅሞ ድህነትን የመዋጋት ሃላፊነት እንዳለበት ነው በአጽንኦት የሚናገሩት፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ እያከናወነም ነው፡፡ የቅርብ ጊዜውን ብንመለከት እንኳን 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት መድቦ የገጠሩንም የከተማውንም ወጣት ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሃ ግብር ዘርግቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ወጣቱን  ኃይል በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የወጣቱ የስራ ባህልና የስነ ልቡና ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ የአመራሩ ድክመትም በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

እንደ አምባሳደር ካሳ ማብራሪያ ህብረተሰቡ በነዚህና መሰል ችግሮች ምክንያት “አልተጠቀምኩም ብሎ ሲያስብ የጎዳኝ እገሌ ነው” ወደ ሚል ድምዳሜ ያመራል፡፡ ይህ አስተሳሰቡ ደግሞ ለዘመናት አብሮት የኖረውንና የሚኖረውን  የቅርብ ወዳጁንም ጭምር በጠላትነት ወደ መፈረጅ ያሸጋግረዋል፡፡  በተለይ ደግሞ ይህን አስተሳሰብ በማራገብና ህብረተሰቡንም በማደናገር ተገቢ ያልሆነ ጥፋት እንዲፈጸም ምክንያት የሚሆኑ ኃይሎች መኖራቸውንም አምባሳደር ካሳ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመሬት ችግር ባይኖርባትም ህብረተሰቡ ለመሬት ያለው አመለካከት ግን “ከህዝብም በላይ” ተደርጎ እንደሚታይ ያብራሩት አምባሳደር ካሳ  ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችም ምንጫቸው የፌደራል ስርዓቱ ሳይሆን የወሰኑን ጉዳይ  ከህዝቦች ግንኙነትና ከቀጣይ አብሮነት ጋር አያይዞ ካለመመልከት የሚመነጩ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ ፌደራላዊ ስርዓቱ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩባቸው አካባቢዎች ልማቱን እንዲያፋጥኑ፣ የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ፣ የህብረተሰቡን ታሪክ እንዲጠብቁና እንዲያሳድጉ፣ ቋንቋ፣ ወግ ባህላቸው እንዲከበር ህገመንግሥታዊ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ይህ እውቅና በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የተሰጠ እንጂ ይኼኛው አካባቢ ለዚህሕኛው ያኛው ደግሞ ለዚያኛው ብቻ የሚል አጥር አላስቀመጠም፡፡ ለዚህም ነው አምባሳደር ካሳ ፌደራላዊ ስርዓቱ ለግጭት መንስዔ ሆኗል የሚለውን አስተያየት የማይቀበሉት፡፡ ከዚህ ይልቅ ችግሮቹ ከአመራርና ከዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ነው የሚያምኑት፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 46 የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በ9 ክልሎች መዋቀሩን ይደነግጋል፡፡ ክልሎቹ የተዋቀሩት የህዝቦችን አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ  መሰረት አድርጎ መሆኑም በዚሁ አንቀጽ ስር በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ በክልሎች መካከል ወሰን ተቀምጧል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምል እንዳብራሩት እነዘህ  ወሰኖች የክልል መንግስታት የየራሳቸውን አስተዳደራዊ ወሰኖች አውቀው “የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ እንዲሆኑ፣ ህዝቡን ለልማት እንዲያነሳሱ፣ … የሚካለሉ ወሰኖች” እንጂ በክልሎች መካከል የተቀመጡ “ግንብና አጥሮች አይደሉም፡፡” በተለይ በወሰን አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች አንደኛው ከሌላኛው ጋር እንደ ጋብቻ ባሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች የተሳሰሩ፣ በሀዘን በደስታው የማይለያዩ፣ ጠንካራ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የፈጠሩ፣ ተመሳሳይ ወግና ቋንቋ የሚጋሩ እንደመሆናቸው መጠን በነዚህ ህዝቦች መካከል የሚደረገው የወሰን ማካለል ስራ ለአስተዳደር ምቹ ከማድረግ አልፎ አንዱን ክልል ከሌላኛው የሚለያይ ድንበርና አጥር ሊሆን አይገባም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉት “በዋናነት በፖለቲካ አመራር ደረጃ ላይ ያለው አካል  የአስተሳሰብና ተግባር ችግሮች ሲቃለሉ ነው”፡፡ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችን መቀነስ የሚቻልበት ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ድህነትን ታግሎ ማሸነፍ ሲቻል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው “ኢትዮጵያ ከድህነት መውጣት የምትችለው ወጣቱ ኃይል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲችል  መሆኑን” ከወጣቱ ጋር  መተማመን ያስፈልጋል የሚል አቋም አላቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቱ ኃይል በሀገሪቱ ጸረ ድህነት ትግል ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ “የሚያስችለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ” ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከወጣቱ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ የመመለሱ ስራም ለነገ የሚባል አለመሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያስገነዘቡት፡፡ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ዛሬም ድረስ ከወጣቶቹ የሚነሱት ጥያቄዎች  በቀጣይ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት በመንግሥት በኩል የተለዩ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን  በወጣቶቹ አካባቢ የሚስተዋሉ ከአመለካከትና ግንዛቤ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች “ለእያንዳንዱ ጥያቄያቸው ድንጋይ በመወርወር፣ ዓመጽ በማካሔድ፣ መኪና በማቃጠል…” ምላሽ ለማግኘት የሚሔዱበት መንገድ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡ ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደትን መከተል ካልቻሉና “የትግል ስልታቸውን በአግባቡ አሳምረው ካልሔዱ ሀገራቸውንም ራሳቸውንም ይጎዳሉ”፡፡  ይህ እንዳይሆን ወጣቱን ሃይል ስለ ህግ የበላይነት ማስተማርና ህገ መንግስታዊ ግንዛቤውን ማሳደግ ቀጣይ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና መንግስት አስተዳደር ትምህርት ክፍል የፌደራል ጥናቶች ምሁሩ  ዶክተር ስዩም መስፍንም ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት ተጠቅመው ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩና የሚሰሩ ዜጎችን መብት የማስከበሩ ጉዳይ በቸልታ ሊታለፍ  እንደማይገባው ይገልጻሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ ምክንያት የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ከማባባስ ይልቅ ግጭቶቹ የሚረግቡበትንና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ ቢከተሉ ችግሮቹ በቀላሉ ሊቀለበሱ እንደሚችሉም ነው ዶክተር ስዩም ያብራሩት፡፡  ምሁራን በፌደራላዊ ስርዓቱ ዙሪያ ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ፣ መንግስትም እነዚህን ጥናትና ምርምሮች በግብዓትነት መጠቀም ቢችሉ ደግሞ የስርዓቱን ጠናክራ ጎኖች ለማስቀጠልና በጥናቱ የተገኙ እንከኖችንም ለማስተካከል ሰፊ እድል ይሰጣል፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን