አርዕስተ ዜና

ገዳ ሁሌ

1598 times

ሚፍታህ አህመድ ከኢዜአ

በኦሮሞ ታሪክና በጥንቱ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ገዳ ሁሌ ከፍተኛ ታሪክና ትልቅ ሥፍራ ያለው ነው። ይህ ተቋም ከፍተኛና ወሳኝ የሆነ የኦሮሞ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የፖለቲካም ተቋም እንደሆነ ይገለጻል።

የኦሮሞ ህዝብ  የገዳ ስርአትን በማዕከልነት በባሌ ውስጥ በሚገኘው መዳወላቡን በጋራ ሲጠቀምበት ከቆየ በኃላ በ1450 አካባቢ የገዳን  መታደስ (haroomsa gadaa) በኋላ በየአካባቢው የሚገኙ ኦሮሞዎች መደወላቡ ድረስ ለመመላለስ ያለባቸውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ የመጫ  እና ቱለማ ኦሮሞ ዱከም አካባቢ በሚገኘው  ኦዳነቤ ላይ የገዳ ስርዓትን መፈጸም እንደጀመሩ ይነገራል፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ በኦሮሞ ፎክሎርና ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል የኦሮሞ ባህላዊ ፣ ኃይማኖታዊና ቅርስ ጥበቃ መምህር  አቶ ደሬሳ ዴቡ እንደሚሉት የመጫ ኦሮሞ  የያዘው መሬት ሰፊ ነው ።

 በአሁኑ ጊዜ 9 ዞኖችን ማለትም ምዕራብ ሸዋ  ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ አራቱ ወለጋ  ፣ ኢሉአባቦር ፣ ቡኖ በደሌ እና የጅማ ዞን የሚገኝበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ አከባቢዎች ኦዳነቤ ድረስ በመሄድ የገዳ ጉባኤንና ሌሎች ስርአቶችን ለመፈጸም ስለተቸገሩ   ምዕራብ ሸዋ ኢሉ ገላን ወረዳ ብስል አካባቢ እንዲያከብሩ በድጋሚ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡

በርካታ ህጎችን እንዳወጣ የሚነገርለት የመጫ ኦሮሞ መሪ  መካ ቢለም በየአካባቢው የሚገኙ ኦሮሞች በየስምንት አመቱ ብስል ላይ እና መዳወላቡ እየተገናኙ አዲስ የወጡ እና የተሰረዙ ህጎችን እንደዚሁም ሌሎች ጉዳዮች ይዘው በመመለስ ተግባራዊ እንዲያደረጉና በየአካባቢያቸውም የገዳ ቅርንጫፍ  እንዲመሰረቱ ህግ አውጥቷል፡፡

በዚህ መስረት የጅማ ኦሮሞ ከ240 ዓመት በፊት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና አጠቃላይ የውይይት ዘይቤውን የሚመራው ስርአት በጅማ ዞን  በኦሞናዳ ወረዳ በተመሰረተው  በኦዳ ገዳ ሁሌ ስርአት  መሰረት እንዲፈፀም ሆነ ፡፡ በስርአቱ የጅማ ኦሮሞ ይዳኝበታል ። መሪያቸውን ይመርጣሉ፣ ይተዳደሩበታል ። እንደ ሰርግ፣ ለቅሶ፣ ደቦ የመሳሰሉትን ማህበራዊ ጉዳዮች ይፈጸሙበታል፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ኦዳ ጀላ በየ8 አመቱ ወደ መደወላቡ እየሄዱ የተሻሻሉ ህጎችን የሚያመጡበት ፣ኦዳ ጃኒ ቅድመ ዝግጅት የሚያደረጉበት፣ኦዳ ጃለሌ የእርቅ ስነ-ስርአት የሚፈጽሙበት፣ኦዳ ሙርቲ ውሳኔ የሚተላለፍበት ስረዓት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ኦደ ሁሌን የመሰረቱት ባቡ ኮዬ የተባሉ ሰው ሲሆኑ በከፍታ ቦታ ላይ የሚፈጸምና ለጅማ ኦሮሞ  አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጥ የገዳ ቅርጫፍ የሆነ ስረአት ነው፡፡

                                      የገዳ ሁሌ ስረአት መዳከም

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት  ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ እገሬ እንደገለፁት የገዳ ሁሌ   ባህላዊው ስርአት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ  እስከ 1830 አካባቢ ድረስ በጅማ ኦሮሞ ዘንድ በስፋት የሚታወቅና የሚተገበር እንደነበር በታሪክ ሰነዶች ላይ ተመዝገቦ ይገኛል ።

የኃይማኖትና የታሪክ ሊቃውንትም በጉዳዩ ዙሪያ የሚስማሙ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡ ይህ የገዳ ስርአት ከ1830 ዓም ገዳማ ጀምሮ አሁን እስካለበት ድረስ እድገት ከማሳየት ይልቅ ጉዞውን ቁልቁል ሆኖ እስከመረሳት የደረሰ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ለኦዳ ሁሌ መዳክም ምክንያት ከ1800 ዓ.ም አከባቢ የመጡት  የንጉሳዊያን የአስተዳደር ስርአት በመንስኤነት እንደሚነሳ አቶ ደሬሳ ይናገራሉ፡፡  የንጉሳዊያን ቤተቦችን በተለይ አባዱላዎች ስልጣንን በየስምንት አመቱ እየጠበቁ ለተተኪ ከማስተላለፍ ይልቅ በጠቅላይነት የመያዝ ሁኔታና  በቤተሰብ ማድረጋቸው ለመዳከሙ እንደመንስኤ አንዱ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል ።

ሌላው በ1902 ዓ.ም አካባቢ በየስምንት አመቱ መደወላቡ ላይ በመሄድ ጉባኤ ላይ የመካፈል ባህል በአዋጅ የመከልከሉ ጉዳይ ለመዳከሙ በምክንያትነት ይነሳል፡፡

የኦዳ ሁሉ ስርዓት በወቅቱ በነበረው አስተዳደር ተፅእኖ ቢዳከምም ማህባራዊ፣ ስነምግባራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እስካሁን ድረስ የቀጠለበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአብነትም   ሬጂ፣ ጂጋ፣ በቀሮ፣ በደቦና በዳዶ አብሮ የመስራት፣  የተጣሉ የሚያስታርቁበትን ባህል   እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

                                       ሴቶችና ገዳ ሁሌ

በገዳ ሁሌ ስርአት የአስተዳደር ስልጣን የሚሰጠው ህዝብን ለማገልግል እራሱን ለሰጠ ሰው ነው፡፡ በገዳ ሁሌ የአስተዳደር ኃላፊነት ከባድ ሸክም ነው፡፡ የገዳ ሁሌ ስርአት ተጠናክሮ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ እረጅም እርቀትን ተንቀሳቅሶ ማገልገል የሚጠይቅ በመሆኑ  ሴቶች ካለባቸው ማህበራዊ ኃላፊነትና ጫና ጋር ተዳምሮ ወደ ስልጣን አይመጡም ፡፡

ነገር ግን የተለየ ብቃት ካላት የማስተዳደር ስልጠን ይሰጥ እንደነበር  በጅማ ከተማ የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሙህዲን ጀማል ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም መካ ኦሌ የተባሉ ብልህ ሴት አባገዳ ሆነው ለስምንት አመት አገልግለዋል፡፡ በስልጣን ዘመናቸውም  በብረት፣ በቆዳ ፣ በሸክላ፤ በሽመና እና በንግድ ስራ ችሎታቸው የሚታወቁ ነገር ግን  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚናቁትን የእጅ ባለሙያዎች  ከሰው እኩል መሆናቸውን በሙያቸው ደግሞ ከሌሎች ከማይሰሩት ሰዎች በላይ መሆናቸውን እውቅና የሰጡ የመጀመሪያው አባ ገዳ ሴት መሆናቸውን ይመሰክራሉ፡፡

አባገዳዋ  አዋቂ ሆኖ ከሰው ጋር ከማይማከር  ይልቅ አላዋቂ ሆኖ ከሰው ጋር የሚማከር  ይሻሻል (beekaa namaan hin mari’aannee irra wallaalaa namaan mari’atu wayyaa) በሚል እምነታቸው  በስፋት ይታወቃሉ::

የገዳ ሁሌ ስርአት ከሚታወቅባቸው ባህሪያት አንዱ ሃርሞሳ ገዳ ወይም በገዳ መታደስ  ነው ፡፡ የገዳ ስርአት እንደየወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ እራሱን እያደሰና እየበለጸገ የሚሄድ ስርአት ነው፡፡ በጅማ ኦሮሞ ዘንድ  በስፋት ይተገበር የነበረው የገዳ ስርአት ተዳክሞ ከቆየ በኋላ ጥር 14/2010 ዓ.ም የጅማ ዩኒቭርሲቲ የኦሮሞ ባህል ጥናት ተቋም ከተመሰረተ ከሶስት አመት በኋላ የተዘነጋውን የገዳ ሁሌ ሰርአት ወደ ነበረበት ማህበራዊ መሰረት ለመመለስ ያለመ የምርምር ጉባኤ ተካሄዷል ። የጅማን የገዳ ስርአት የመመለስ ስነስርአትም ተካሔዷል፡፡

በአዲስ የተመሰረተው የገዳ ሁሌ ስርአት በውስጡ ያሉትን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ፣ታሪካዊ፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በደንብ በማውጣት ከማህበረሰቡ ጋር ለማገናኘት በቀጣይ በትኩረት የመስራትን ግብ በማስቀመጥ ሀሮምሳውን(መታደስን) ጉዞ "ሀ" ብሎ ጅምሯል፡፡ ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስና  ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር  የሙህራን፣ የመንግስትና ሁሉንም የህበረተሰቡ ክፍል በንቃት ማሳተፍ ወሳኝ ይሆናል፡፡

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን