አርዕስተ ዜና

ፌደራሊዝም- የአብሮነታችን ስጋት ወይስ …?

04 Dec 2017
4239 times

                     እንግዳ መላኩ / ኢዜአ /

ኢትዮጵያ ለተለያዩ እጽዋት ተስማሚ የሆነ የተለያዬ መልክዓ ምድር ባለቤት ነች፡፡ የዓለማችን ዝቅተኛውና በአፍሪካ ደግሞ ከፍተኛው ቦታዎች የሚገኙትም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛነት የሚያረጋግጡት ቅሪተ አካላትስ ቢሆኑ መገኛቸው ከየት ሆነና!

አውሮፓውያን አፍሪካን የመቀራመት ሴራ ጠንስሰው መላ አፍሪካን በመውረር አንጡራ ሃብቷን እንዳሻቸው ሲያግበሰብሱ፣ የአፍሪካን ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ማንነት፣… ሸርሽረው ዜጎቿን ራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ ሲቀርጿቸው ኢትዮጵያ ግን እስካፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ጦር አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ በመመለስ ማንነቷን፣ ቋንቋዋን፣ ወግና ባህሏን ከማስከበሯም በላይ ለሌሎች አፍሪካውያን የነጻነት ትግልም ምክንያት ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ የራሷ ሆሄያትና ቁጥሮች እንዲሁም ያልተበረዘና ያልተከለሰ  የዘመን አቆጣጠር ባለቤትም ነች፡፡ አስደማሚ ታሪካዊ ቅርሶችም አሏት፡፡ የአክሱም ሰማይ ጠቀስ ሃውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ በአጥር የተከበበችዋ የሀረር ከተማ፣  የጎንደር አብያተ መንግስታት፣ የጥያ ትክል ድንጋይ… የጥንታዊ ስልጣኔ አሻራ ያረፈባቸው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካና የዓለማችንም እሴቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የቀድሞው የመንግስታቱ ድርጅት መስራች፣ የአፍረካ ህብረት መቀመጫና ከመስራቾቹም አንዷ ነች፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ ሃብታም ትሁን እንጂ ያልተማከለ ስርዓተ መንግሥት በመመስረት በኩል ግን የዓማችን ጭራ ሆና ቆይታለች፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ያልተማከለ ስርዓተ መንግሥት መተግበር ከተጀመረ ገና ሶስት አስርት ዓመታትን አልተሻገርንም፡፡ ይህም ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ የተገኘ ቢሆንም  ሀገሪቱ ለተጎናጸፈቻቸው ሌሎች ድሎች ሁሉ መሰረት የጣለ አንጸባራቂ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኢትዮጵያውያን በጋራ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ በዓለማችን ውድ በተባሉ  ነገሮች ሁሉ የማትሸጥ የማትለወጥ አንድያ ህይወታቸውንም ሳይቀር ያለምንም ስስት  ከፍለው የተጎናጸፉትን ድል ተከትሎ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመስርቷል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከንጉሳዊና ወታደራዊ ሥርዓቶች ወደ ፌደራሊዝም ስርዓት መሸጋገሩን ለምን መረጠችው?

ኢትዮጵያ ፌደራሊዝምን ከመረጠችባቸው አበይት ምክንያቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ፌደራሊዝም በቀደሙት ስርዓቶች የነበረውን ኢፍትሃዊ የአስተዳደር ስርዓት  ያስተካክለዋል የሚለው እሳቤ ሚዛን መድፋቱ ነው፡፡  ከግማሽ   ምእት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ስልጣናቸው ከህዝብ ሳይሆን ከአምላክ እንደሆነ አድርገው የሚሰብኩ እንደነበሩ የሀገራችን የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው፡፡ በወቅቱ የሀገሪቱ ሀብት ንብረት ብቻ ሳይሆን የመላ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጣ ፋንታም በነገስታቱ የእጅ መዳፍ ውስጥ ወድቆ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ህግጋተ መንግሥታት ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ቅድመ ኢህአዴግ ሶስት የተጻፉ ህግጋተ መንግስታትን አስተናግዳለች፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ በአጼ ኃይለስላሴ አንደኛው ደግሞ በወታደራዊው ስርዓት ተግባራዊ የተደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን የተጻፈ ህገ መንግስት ያጸደቀችው በወርሃ ሃምሌ 1923 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ህገ መንግሥት የሀገሪቱን ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀይማኖቶች፣ ወግ፣ ቋንቋና ባህሎች ከግምት ውስጥ ያስገባ ሳይሆን ለአሃዳዊ አገዛዙ ህጋዊ እውቅና ለመስጠት ከንጉሱ ለህዝቡ የተሰጠ እንደ ነበር ድንጋጌዎቹ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ህገ መንግሥቶች የህግ አውጭ፣ የህግ አስፈጻሚና የዳኝነት ስልጣኑን ሁሉ አጠቃልለው ለንጉሱ ከመስጠታቸውም በላይ ለሀገሪቱ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶችና ባህሎች ልዩነት ቦታ የማይሰጡ፣ ከዚህ ይልቅ ሀገሪቱ አንድ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህል ብቻ ያለው ህዝብ ሀገር መሆኗን የሚያውጁም ነበሩ፡፡ ለዚህ አብነት ይሆነን ዘንድ 24 ጉልተኛ ጳጳሳት፣ መሳፍንት፣ሚኒስትሮችና መኳንንት በፊርማቸው ባጸደቁት የ1923ቱ ህገ መንግስት ከተካተቱ አንቀጾች ውስጥ አንድ ሁለቱን እንመልከት፡፡

አንቀጽ 2 “የኢትዮጵያ መሬት፣ ህዝብም፣ ህጉም በጠቅላላው የንጉሰ ነገሥት ነው፡፡” ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ በሀገሪቱ ህዝብም ሆነ ሃብት ላይ አዛዥ ናዛዡ ንጉሰ ነገሥቱ ብቻ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡

አንቀጽ 3 ደግሞ ስልጣን ከንጉሱ እጅ እንዳይወጣ ብቻ ሳይሆን ስልጣኑን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያወርሱም ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

            “የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ሰሎሞንና ንግሥተ ሳባ ከተባለችው የኢትዮጵያ ንግስት ከተወለደው ቀዳማዊ ምኒሊክ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትውልድ እንዳይወጣ በህግ ተወስኗል፡፡”

ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ 13ቱን ዓመታት ህገ መንግስት ሳያስፈልገው ‘በመሰለኝና ደሳለኝ’ ሀገሪቱን ለመምራት ተፍጨርጭሯል፡፡ ደርግ ሶስተኛውን የሀገሪቱን ህገ መንግስት ያጸደቀው መላ የሀገሪቱ ህዝቦች የተጫነባቸውን የጭቆና ቀንበር ከጫንቃቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣል በአራቱም ማዕዘናት ስርዓቱን መውጫ መግቢያ ባሳጡበት የውድቀቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ ነው፡፡ በ1980 ዓ.ም የጸደቀው ይኼኛው ህገ መንግሥትም ቢሆን ልክ እንደቀድሞዎቹ ህገ መንግሥቶች ሁሉ የመንግስትን ሥልጣን በአንድ ቦታ ሰብስቦ ከማከማቸቱም ባለፈ ለህዝቦች እኩልነትና የስልጣን ባለቤትነት ምንም ቦታ  አልነበረውም፡፡

ሶስቱም ህግጋተ መንግሥታት ከህዝብ የመነጩ፣ ለህዝብ የቆሙና በህዝብ ይሁንታ ያገኙ ሳይሆኑ በህዝቡ ላይ ያለፍላጎቱ የተጫኑ፣ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ የገዢ ቡድኖችን ስልጣን ማማከያ ህግጋት መሆናቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ ፌደራሊዝም የቀደሙ ስርኣቶች በህጎቻቸውም ጭምር አረጋግጠው ለዘመናት በሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ ጭነውት የነበረውን ኢፍትሃዊ አስተዳደር ያስተካክለዋል በሚል ቅድሚያ ያገኘበት ዋነኛው ምክንያትም ይሔው ነበር፡፡

ፌደራሊዝም ትኩረት ያገኘበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ስርዓቱ ሀገሪቱን ካለመረጋጋትና ከመበታተን አደጋ ይታደጋታል ከሚል ድምዳሜ ላይ በመደረሱ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም የኤርትራ ነጻነት ግንባር፣ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር፣ የአፋር ነጻነት ግንባር፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ግንባር፣ የሲዳማ ነጻነት ግንባር፣ የምዕራብ ሶማሌ ነጻነት ግንባርና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር በደርግ ላይ ነፍጥ ያነሱ ዐበይት ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ ሰፋፊ ግዛቶችን በቁጥጥራቸው ስር አውለውም ነበር፡፡

የኢህአዴግ ሰራዊት ግንቦት 20/1983 ዓ.ም ግዙፉን አምባገነናዊ ስርዓት ቢገረስሰውም የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ግን ሌላ ስጋት ተደቅኖበት ነበር፡፡ እነዚህን የታጠቁና ሰፋፊ ግዛቶችን በእጃቸው አስገብተው የነበሩ ድርጅቶችን ፍላጎት የማሟላቱ ጉዳይ ሌላ ስጋት ደቅኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሰኔ መጨረሻ አካባቢ ኢህአዴግ በሀገሪቱ ላይ የተደቀነውን ስጋት ለመቅረፍና የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የታጠቁትንም ሆነ ያልታጠቁትን ተቃዋሚ ኃይሎች ያካተተ የአምስት ቀናት የሰላም ኮንፈረንስ አካሔደ፡፡

በዚህ የሰላም መድረክ 31 የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ የፌደራሊዝም ስርዓተ መንግሥት ተመራጭ ሆኖ የተገኘውም ለዘመናት ዓይንና ጆሮ ተነፍገው ለነበሩት የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ነጻነታቸውን ለማረጋገጥና የመንግስትን ሥልጣን በመጋራት በሀገሪቱ የተደቀነውን የመገነጣጠል ስጋት ለማስወገድ ከፌደራሊዝም የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ነው፡፡

ፌደራሊዝም ተመራጭ የሆነበት ሌላኛው ምክንያት ከ80 በላይ የሚሆኑት የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት በመመስረት ተቻችለውና ተፋቅረው እንዲኖሩ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር በመረጋገጡ ነው፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ ፌደራል ሥርዓት መላ የሃገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለምንም መሸማቀቅ ቋንቋቸውን፣ ሃይማኖታቸውንና ወግ ባህቸውን እንዲያሳድጉ፣ ከሀገሪቱ ሃብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ አንዱ ከሌላው ጋር በመቻቻልና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖረው  አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ስርዓተ መንግሥት መመራት በመቻሏ የዜጎች የዘመናት ጥያቄዎች እልባት አግኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ መላ የሀገሪቱ ህዝቦች በተባበረ ክንዳቸው ግዙፉንና አስፈሪውን ወታደራዊ ኃይል አሽቀንጥረው እንደጣሉት ሁሉ ጥንተ ጣላታቸውን ድህነት በሙሉ አቅማቸው ተፋልመው ወደ ሌላ ድል፣ ወደ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ አግዟቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በፌደራላዊ ስርዓቱ እየተመራ መላ ዓለምን ያስጨበጨበ አንጸባራቂ ድል ሲያስመዘግብ ሩብ ምዕት ዓመት አልወሰደበትም፡፡

ኢትዮጵያ ከዚያ ሁሉ ውጣ ውረድ ተመንጥቃ ወጥታ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ከጀመረች አስር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ያሉ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ሳንካ ባይሆኑባት ደግሞ በየዓመቱ የምታስመዘግበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ከዚህም በላይ ይመነደግ እንደነበር ለመተንበይ የኢኮኖሚ ተንታኝ መሆንን አይጠይቅም፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተመራችበት ፌደራላዊ ስርዓት ሀገሪቱ ስትንደረደርበት የነበረውን የኋልዮሽ ጉዞ እንዲገታ አድርጎ ወደ ፊት አስወንጭፏታል፡፡ በመሰረተቻቸው እንደ የተባበሩት መንግሥታትና አፍሪካ ህብረት ባሉት ተቋማት ያላት ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተሰሚነቷም በዚያው ልክ ወደ ፊት ተወንጭፏል፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 46 (1) መሰረት ክልሎች የተዋቀሩት “በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ” ላይ በመመስረት ነው፡፡ አንቀጽ 39 ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተጎናጸፏቸውን ራስን በራስ ከማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚደርሱ መብቶችን በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመገልገል፣ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት አንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብታቸውም ህገ መንግሥታዊ እውቅና አግኝቷል፡፡

እነዚህና መሰል ድንጋጌዎች  መላ የሀገሪቱ ህዝቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው በመቻቻል እንዲኖሩ ትልቁን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ ይህም በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሀገሪቱ ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩት ሃብት ንብረት ዋስትና እንዲያገኝና ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚም ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፡ 

ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓተ መንግሥቷን በህገ መንግሥቷ ባጸደቀችበት 15ኛ ዓመት  ከ5ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጋር ባዘጋጀችው 5ኛው ዓለም ዓቀፍ የፌደራሊዝም ጉባዔ በጥቂት ዐመታት ውስጥ የተጎናጸፈችውን ስኬት ዓለም አድንቆላታል፡፡ በአህጉረ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው፣ ከ45 በላይ ጽሁፎች በቀረቡበትና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ600 የሚልቁ ዓለም ዓቀፍ ጉባዔተኞች በተሳተፉበት ጉባዔ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸውን ውበታቸው ብዝሃነታቸውን ደግሞ ጥንካሬያቸው አድርገው  የተጓዙባቸውን የ15 ዓመታት ጉዞ ለመላ ዓለም አሳይተዋል፡፡

እውነታው ይህ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንቅልፍ የሚነሳቸው እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ተደማጭነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ በየጊዜው እየጎለበተ መምጣቱ የእግር እሳት የሚሆንባቸው  የውጭና የውስጥ ጠላቶች ደግሞ የሀገሪቱን የስኬት ጉዞ ለማደነቃቀፍ እንቅልፍ አጥተው ሰርተዋል፡፡ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ከብሔር ጋር ለማገናኘት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የሁከትና ብጥብጥ መነሻ ለማድረግ፣ ከውሃና ግጦሽ ጋር በተያያዘ በወሰን አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን አካባቢያዊና ክልላዊ መልክ ለማስያዝ ተሸቀዳድመዋል፡፡

አሁን አሁን ደግሞ የስርዓቱ ተቀናቃኞች ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ የክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በፌደራል ስርዓቱ የአወቃቀር ችግር ምክንያት የመጡ አድርገው ወደ ማራገብ ተሸጋግረዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን በሀገሪቱ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችና አለመግበባቶች የፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር የወለዳቸው ችግሮች ሳይሆኑ “በተሳሳተ አመለካከት፣ አስተሳሰብና ተግባራዊ እንቅስቃሴምክንያት የተከሰቱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የተለየው የተሳሳተ አስተሳሰብ ደግሞ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መነሻ እንዳለውም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ህዝብን በእኩል አይን ከመመልከት ይልቅ “አንደኛውን ወገን የራሳቸው፣ ሌላኛውን ደግሞ የሌላ ህዝብ” አድርገው የሚቆጥሩ አመራሮች፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞችና የጸጥታ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

ህዝብን ማዕከል ያደረገውን ፌደራላዊ አደረጃጀት እየሸረሸሩ መሬትን ማዕከል ያደረገ  አስተሳሰብ  እንዲያቆጠቁጥ የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸው በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው መረጋገጡንም አቶ ኃይለማርያም አንስተዋል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ለመመከት የተካሔደው ትግል ደካማ በመሆኑ ምክንያት በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የድንበር አካባቢዎች ግጭቶቹ መከሰታቸውን ያብራሩት አቶ ኃይለማርያም ይህን የተዛባ ፖለቲካዊ አመለካከት ለማስተካከል ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ፌደራሊዝም እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ እንዲሁም ሰፊ የግዛት ወሰን ባላቸው  ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመተግበር ተመራጭ ስርዓተ መንግሥት ነው፡፡ የትክክለኛው ፌደራሊዝም መነሻው ዴሞክራሲ እንደመሆኑ መጠንም በኢትዮጵያ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱ የስልጣን ክፍፍል በህገ መንግሥቱና በህግ የበላይነት ተረጋግጧል፡፡  

በብዙዎች ዘንድ ከጅምሩ የፌደራሊዝም ስርዓቱ ኢትዮጵያን “ይበታትናታል” የሚል ስጋት ቢያሳድርባቸውም ስርዓቱ ከመበታተን ይልቅ ለዜጎች የአንድነታቸው ማሰሪያ፣ የአብሮነታቸውም መሰረት ሆኗቸዋል፡፡ የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት የተረጋገጠው፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ የተፋጠነው፣ የዜጎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወት የተሻሻለው፣ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ የጀመረው፣ ዓለም ዓቀፍ ተሰሚነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷም የጨመረው ከፌደራል ስርዓቱ በኋላ መሆኑን ለመረዳት በዘርፉ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማድረግ አያሻም፡፡ እነዚህና ሌሎች አያሌ ማስረጃዎች ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን ይበታትናታል የሚለው ስጋት ከስጋት የዘለለ ጉዳይ ላለመሆኑ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን