አርዕስተ ዜና

ጠባብም ትምክህተኛም ህዝብ የለም !

28 Nov 2017
4417 times

                                     ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ

 ሕገ-መንግስታችን  የህዝቦችን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መብቶች በተሟላና በሰለጠነ አኳኋን የመለሰ የሁሉም ሕጎች የበላይ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም ፌደራላዊ ስርዓታችንን በማያቋርጥ ሂደት ለመገንባት ፅኑ መሰረትና ምሶሶ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ብዝሃነትን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችለው የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ በሚፈለገው ደረጃ ስላልተያዘና ስላልተስፋፋ በአሁኑ ጊዜ የተመዘገቡትን ውጤቶች የሚፈታተኑ ችግሮች እዚህም እዚያም ሲከሰቱ ይስተዋላል።

እነዚህ የትምክህተኝነት ፣ ጠባብነትና ፅንፈኝነት አስተሳሰቦች ልዩ ትኩረት አግኝተው ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲከስሙ ካልተደረገ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱንና ሀገራችንን ወደ ኋላ የመመለስ አደገኛ አዝማሚያ ሊያስከትሉ ይችላሉ ።

ትምክህተኝነትንና ጠባብነትን ማክሸፍ የሚቻለው ማህበራዊ መሰረታቸውን በቅጡ በመረዳትና ጠንካራ ስትራተጂዎችንና አቅጣጫዎችን በመንደፍ የተቀናጀ ትግል በማካሄድ በምትኩ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን አስተሳሰብ የበላይነት በማረጋገጥ ነው ።

በፌደራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኝነት ዳይሬክተር ጄነራል፣ አቶ ፀጋብርሃን ታደሰ ትምክህተኝነት አንዱን ማህበረሰብ ወይም የህብረተሰብ ክፍል ከሌላው ማህበረሰብ ወይም የህብረተሰብ ክፍል የበላይ አድርጎ የሚወስድ የተዛባ ማህበራዊ ግንኙነት መገለጫ ነው ይሉታል፡፡

ትምክህተኝነት ከቅድመ-ስልጣኔ ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣ የግንኙነት መገለጫ ቢሆንም በስልጣኔ ሂደትም ዘመናዊነትን እየተላበሰ፣ አንዳንድ ጊዜም የከፋ መልክ እየያዘ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ችግር ነው፡፡

በአንድ ወቅት ህንድን ይመራ የነበረው የካስት ስርዓት የህንድን ህዝብ በአምስት እርከኖች በመከፋፈል በከፍተኛው ጫፍ ላይ በሁሉም ማህበራዊ ግንኙነት የበላይ ተደርገው የሚወሰዱ ብራሂምስ የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ፣ በታችኛው ጫፍ ደግሞ ዝቅተኛ ወይም የማይነኩ (Untouchable) ተብለው የሚወሰዱ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ ።

በአሜሪካ የነጮችን (በተለይ የአንግሎ-ሳክሰን ፕሮቴስታንት) የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በመቀጠል የጥቁሮችን አብዮት እንደቀሰቀሰ ይታወቃል፡፡

ሂትለር በጀርመን ስልጣን እንደተቆጣጠረ የአርያን ዘሮችን ከሌሎች ህዝቦች የበለጡ አድርጎ በማቅረብ የጀርመን ህዝብ የተሳሳተ የበላይነት ስሜት እንዲይዝ ማድረጉንና በመጨረሻም ከአምስት ሚሊዮን በላይ አይሁዶችን እንደጨፈጨፈ የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በብሄር ብሄረሰብ ላይ የተመሰረተ የተዛባ ግንኙነት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የታየ ችግር ሳይሆን በዓለማችንም በስፋት ጎልቶ የሚታይ የተሳሳተ የማህበራዊ ግንኙነት መልክ ነው፡፡ 

አቶ ፀጋብርሃን ታደሰ በሃገራችን የትምክህተኝነት ምንጭ የቀድሞ ገዥ መደቦች ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ ገዢ መደቦች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ በአማራ ህዝብ ስም ሲነግዱ የነበሩ ናቸው፡፡

ገዢ መደቦቹ ሁለት መልክ ያለው ስትራተጂ ሲከተሉ ነበር፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያን አንድነት እንደሽፋን መጠቀም ነው፡፡ የአማራ ህዝብ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማት ጥያቄ እንዳያነሳ በአንድነት ስም ለማሳሳትና ጥያቄ ሲያነሳም በማፈን የራሳቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ ተረባርበዋል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመብት ጥያቄዎችን እንዳያነሱ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ለማፈንና ጥያቄ ሲያነሱም ፀረ-አንድነት በሚል ቅስቀሳ ለመጨፍለቅ ርብርብ አድርገዋል፡፡

በእርግጥ እነዚህን ገዥ መደቦች ምሳሌ ደርግን ብንመለከት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አንዳንድ ግለሰቦችን በስርዓቱ ውስጥ በማካተት ገዢው መደብ የሁሉንም ውክልና ያለው እንዲመስል ለማሳሳት ሞክሯል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች በግላቸው ያገኙት ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ስልጣን ቢኖርም የስርዓቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ይዘትና መዋቅር የሚለውጡ ወይም የመጡበትን ብሄር የሚወክሉ አልነበሩም፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ 

ከዚህ በመነሳት ትምክህተኛ የሚባል ህዝብ እንደሌለ መደምደም ይገባል፡፡  በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የትምክህተኝነት ዋና ሃይል የአማራን ህዝብ ሽፋን ያደረገ የጥገኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ሃይል ነው፡፡ ይኽው የትምክህት ሃይል በአሁኑ ጊዜ የሚጠቀምበት ስትራተጂና ስልት ሶስት መልክ አለው።

አንዱ እንደድሮው የአማራን ህዝብ በማደናገር መጠቀሚያ ለማድረግ መንቀሳቀስ ሲሆን  ትምክህተኝነት ሲወገዝ የአማራ ህዝብ እንደተወገዘ አድርጎ የሀሰት መረጃ ያሰራጫል፡፡ 

የአፈፃፀም ችግሮች በሁሉም ክልሎች እየተከሰቱና የችግሩ ፈጣሪዎች በየደረጃው የሚገኙ የየክልሉ አስፈፃሚ አካላት መሆናቸው እየታወቀ የአማራን ህዝብ ብቻ ለማጥቃት ተብሎ የሚፈፀሙ አድርጎ ይሰብካል፡፡

ሁለተኛው ስትራተጂ በብሄሮች ብሄረሰቦች መካከል ቅራኔና ግጭት እንዲፈጠርና እንዲባባስ ማድረግ ነው፡፡ ተገቢ ያልሆነ ድጋፍን ለመሸመትና ከጎኑ ለማሰለፍ የትግራይ የበላይነት አለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ መንግስት ነው፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም የወያኔ ድርጅት ነው በማለት ይቀሰቅሳል፡፡ ከጠባብ ሃይሎች በመታረቅም በጋራ ይሰራል፡፡

የትግራይ የበላይነት አለ ለማለት የሚያሰላው ስሌት በፌደራል አስፈፃሚ አካል ያሉትን ሰዎች ብቻ በመቁጠር ነው፡፡

ሶስተኛው የትምክህት ሃይል ስትራተጂ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ኪራይ ሰባሳቢነትን በማባባስ በዚህ ችግር የተዘፈቁ የመንግስትም ሆነ የግል ሰዎች መሳሪያ ማድረግ ነው፡፡ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያካሂደውን ዘመቻ እንዳይሳካ በከፍተኛ ሁኔታ ይረባረባል፡፡

ህዝቡ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱለት ጥያቄ ሲያነሳ የተለያዩ አሳሳች ቅስቀሳዎችን በመጨመር የህግ የበላይነት እንዲጣስና ወደ ሁከትና ዓመፅ እንዲያመራ የመገፋፋት ሚና እንደሚጫወት ዳይሬክተር ጀነራሉ ያስረዳሉ ።

ዓመፁ እንዲስፋፋ አመራር ይሰጣል፣ ዓመፁን በማስቆም ሂደት ህይወትና ንብረት እንዲጠፋ ይገፋፋል፣ በሂደት ቅሬታዎች እየተባባሱ እንቢተኝነትና ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ይረባረባል፡፡

ስለሆነም የትምክህት ሃይል የአማራን ህዝብ ሽፋን በማድረግ እነዚህን ስትራተጂዎች እየተከተለ የራሱን የበላይነትና የብሄሮች ብሄረሰቦችን የበታችነት የሚያረጋግጥበትን የድሮ ስርዓት ለማስመለስ የሞት ሽረት ትግል እያካሄደ ይገኛል፡፡ 

በዚህም የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ የህዝብና የግለሰብ ንብረት እንዲወድም ፣ሰላም እንዲደፈርስና  ልማት እንዲቆም ፣ ህዝብና ህዝብ እንዲበጣበጥና በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ሌት ተቀን ይጣደፋል፡፡ ትምክህት በቅድሚያ የሚጎዳው ሽፋን አድርጎ የሚጠቀምበትን ህዝብ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በሚፈፅመው ፀረ-ሰላም ድርጊት በቅድሚያ እየተጎዳ ያለው የአማራ ህዝብ ነው

ጠባብነትም ልክ እንደ ትምክህተኝነት ሁሉ የተዛባ ግንኙነት መገለጫ ነው ፡፡ ካለፈው ወይም በተጨባጭ ከሚታየው የትምክህተኝነት ችግር በመነሳት ጠባብነትም በብሄሮች ብሄረሰቦች መካከል የነበረውንና ያለውን ትስስርና የአብሮነት ገመድ ለመበጣጠስ የሚረባረብ ሃይል ነው፡፡

የጠባብነት ቡድን ዋና ዓላማ በተሸሸገበት ብሄር ብሄረሰብ ገዢ መደብ በመሆን የኪራይ ሰብሳቢት ፍላጎትን ማሟላት ነው፡፡

የጠባብነት ሃይል እንደየሁኔታው የተለያዩ ስልቶች የሚጠቀም ሆኖ ዋናው ስትራተጂና ዓላማ መነጣጠል ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ብሄራዊ ጭቆና ተወግዶ የብሄሮች ብሄረሰቦች እኩልነት በተረጋገጠበትና ፌደራላዊ ስርዓት በተመሰረተበት ከ26 ዓመታት በኋላም የጠባብነት ዝንባሌዎችና ተግባራት ጎልተው እየታዩ ናቸው፡፡

የጠባብነት ሃይል ዋና ባህርይ የብሄር ካባን በመልበስ የኪራይ ሰብሳቢነትን ዓላማ ማሳካት ሲሆን ትምክህተኛው የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ ስልቶችም እያጣጣመ በተመሳሳይ መንገድ ይጠቀምባቸዋል ፡፡ ስትራተጂዎቹንም በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

አንደኛው የየብሄሩን ህዝብ በተለያዩ ቅስቀሳዎች በማሳሳት ከጎኑ ማሰለፍ ነው፡፡ ብሄራዊ ጭቆና በሌለበት ሁኔታ አሁንም የተለየ መልክ ይዞ መጣ እንጂ አልተወገደም በማለት ህዝብ ለማሳሳት ይሞክራል፡፡

የልማት ዕቅዶችና የድጎማ በጀት የየብሄሩ ተወካዮች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚወስኑት መሆኑ እየታወቀ ፍትሃዊ የልማት ዕቅድና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አልተረጋገጠም በማለት ውዥንብር ለመፍጠር ይረባረባል፡፡

ሁለተኛ በብሄሮች ብሄረሰቦች መካከል ግጭት በመቀስቀስ መራራቅና ቅራኔ እንዲባባስ፣ መነጣጠል እንዲፈጠርና በዚህ ሂደት የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱን ለማሳካት ይንቀሳቅሳል፡፡

የየብሄሩ ጥገኛና ፀረ-ህዝብ ሃይል ወዳጅ አድርጎ ማየትና ለጠባብ ዓላማ ለማሰለፍም ይረባረባል። 

ለምሳሌ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱት የጠባብነት አራማጅ ግለሰቦች የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ ከሌሎች ወንድም ህዝብ ጋር እያራራቁት ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ከልማታዊ መንገድ የወጡ ጥገኞች ሁል ጊዜም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ጠላቶች መሆናቸው የማይለወጥ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አሰላለፍ እውነታ ነው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ጠባቦች በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የትግራይ ህዝብ ወዳጅ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፣ አልፎ-ተርፎም የስርዓቱ ጠበቆች በመምሰል የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡

የእነዚህ ጥገኞች ቅስቀሳ ዕውነት መስሎት የሚቀበል ዜጋም የጠባብነት ሰለባ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የልማታዊነትና የጥገኝነትን ጎራ የማቀላቀል አዝማሚያ እያስከተለ ይገኛል፡፡

የጠባብነት አስተሳሰብ የትግራይ ህዝብ በፌደራል መንግስት የሚኒስትርነት ቦታው አነስተኛ ነው በሚል መልክም ይገለፃል ፡፡ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት የጠባብነት አስተሳሰብ መሳሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡

ጥገኛው ባለሃብት በትግራይ ህዝብ ስም በመነገድ ራሱን የስርዓቱ ዋነኛ ጠበቃ አድርጎ መውሰድና የሌሎችን ድርሻ አለአግባብ አሳንሶ ማየት፣ በትግራይ ህዝብ የትግል መስዋዕትነት በመነገድ የበላይነት ስሜትን ለማሳደግ መሞከር፣ በሂደትም ራሱን ወደ ገዥ መደብ ለመቀየር መፈለግ ይታይበታል፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግደው የጠባብነት ቡድን ስትራተጂዎችም  ተመሳሳይ ናቸው ፡፡ መገነጣጠል የሚሳካው በብሄሮች ብሄረሰቦች መካከል ግጭት ሲከሰትና ሲባባስ በመሆኑ ዕቅድ ነድፎ ግጭቶችን ለማቀጣጠል ይረባረባል ፡፡ ሌሎችን ብሄረሰቦች ከጎኑ ለማሰለፍም የትግራይ የበላይነት አለ በማለት ይቀሰቅሳል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩበት የራሱ ልጆች ሆነው ሳለ የትግራይ የበላይነት የፈጠረው ነው ብሎ ለማሳመን ይጥራል ፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች መሬትን እየቸበቸበ ለጥገኛው የትግራይ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ አማራ ወዘተ ባለሃብት ሰጥቶ ሲያበቃ ይህንን በደል የፈፀሙ የአስተዳደር አካላትን ከመጠየቅ ይልቅ በትግራይ የበላይነት ለማሳበብ ይፍጨረጨራል።

ትምክህተኝነትን እንደጭራቅ ሲመለከት የነበረ የጠባብነት ቡድን የተቀዳበት ምንጭ ጥገኝነት በመሆኑ ከትምክህተኛው ሃይል ተባብሮ የዘረኝነት ቅስቀሳ በማካሄድ ለጥፋት ሲዘምት ይታያል፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ስም እየነገደም የበላይነትን ለመያዝ ሲረባረብ ይታያል፡፡

ጠባቡ ሃይል የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲባባስ ዓመፅን በመቀስቀስ ልማቶች እንዲወድሙና የውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት ተስፋ እንዲጨልም አመራር ይሰጣል፡፡

ሁከትን ለመቀልበስ በሚደረግ ጥረት የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ ቅሬታዎች እንዲባባሱና የህግ የበላይነት እንዲጣስ ይረባረባል፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይፈቱ ዕንቅፋት ሆኖ ይቆማል።

የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን በብሄር ስም ወዳጅ አድርጎ በመውሰድ እንዳይጠየቁ በከፍተኛ ሁኔታ ይረባረባል ፡፡ ችግሮችን በማባባስ ስልጣን ለመቆጣጠር ሊያግዙት ከሚችሉ ሁሉም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን በመሰለፍና ድጋፍ በመጠየቅ ኢትዮጵያ ወደ መጨረሻው ትርምስ እንድትገባ ሌት ተቀን ሲሰራ ይታያል፡፡ ከዚህ አኳያ ጠባብ የሚባል ህዝብ የሌለ መሆኑንና ጠባብነት ጥገኛው ሃይል የየብሄርን ካባ በመልበስ የሚያስፋፋው የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡              

የትምክህትና የጠባብ ሃይሎች ባለፉት 26 ዓመታት ያልተሳካላቸውን ምኞት በአሁኑ ጊዜ በስርዓቱ ላይ አደጋ መደቀን የቻሉበትን ምቹ ሁኔታ ማየት ጠቃሚ ነው ።

አቶ ፀጋብርሃን እንደሚሉት በመጀመሪያ ደረጃ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እስካልተለወጠ ድረስ እነዚህ ሃይሎች መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ አንደኛው ምቹ ሁኔታ በሃገሪቱ ከተፈጠረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማታዊነት ንቅናቄና የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእድገቱ ልክ የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የውጤቱ ተቋዳሽ መሆን አልቻሉም፣ ይህ የፍትሃዊነት ክፍተት በተለይ በወጣቶች አካባቢ ጎልቶ ይታያል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁን የደረሱበት ደረጃ የተዛባ ግንኙነት አራማጅ ሃይሎች ከማንም ጊዜ የተሻለ ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡

ለአንዱ ብሄረሰብ የተሻለ አስተዳደር ለሌላው ግን ብልሹ አስተዳደር እንደሚዘረጋለት አድርገው በማቅረብ በብሄሮችና ብሄረሰቦች መካከል መጠራጠር፣ ቅራኔና ግጭት እንዲፈጠር እየተረባረቡ ይገኛሉ ፡፡

የተዛባ ግንኙነት አራማጅ ሃይሎች ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙትን መብቶች ከማስጠበቅ ይልቅ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመቀልበስ ይረባረባሉ ።

እነዚህ ሀይሎች የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነትን በማባባስ ብቻ ሳይሆን ለከፋፋይ ፖለቲካ በሚያገለግል መልኩ ማንነቶች አብረው ለመኖር የገቡትን ቃል-ኪዳን ለመበጣጠስ ሲረባረቡ ይታያሉ፡፡ 

የሃይማኖት እኩልነት በመረጋገጡ ያልተዋጠላቸውና የአንድን ሃይማኖት የበላይነት ማስቀጠል የሚፈልጉ ጥቂት የፅንፈኝነት ሃይሎች ገዥዎች የፈጠሩትን ያለፈው የተዛባ የሃይማኖት ግንኙነት ለማስመለስና ለማስቀጠል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ፡፡

በሌላ በኩል የተረጋገጠውን የሃይማኖትና የእምነት እኩልነት መነሻ አድርገው ነገር ግን በተራቸው አዲስ የተዛባ የሃይማኖት ግንኙነትን ለመፍጠርና ለማስቀጠል የሚረባረቡ ዘመነኛ ፅንፈኞች ይታያሉ፡፡ የሁለቱም ፅንፈኞች ዋና ዓላማ የሃይማኖት እኩልነትን በመፃረር የተዛባ ግንኙነትን መፍጠርና ማስቀጠል ነው፡፡

የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ህዳር 2009 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገመንግስትና የሃይማኖት ብዝሃነት አያያዝ በሚል ርእስ ባሳተመው ጥራዝ የፅንፈኛው ሃይል የመነሻውና የመድረሻው ሚስጢር በዋነኛነት አራት ናቸው ።

በሃይማኖት ሽፋን የኪራይ ሰብሳቢነትን ፍላጎት ማሳካት ፣ በአቋራጭ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ፣ መንግስታዊ ሃይማኖት አሊያም ሃይማኖታዊ መንግስት መመስረትና የህዳሴ ጉዞአችንን ማጨናገፍና አገራችንን ማፈራረስ ነው ።

ጠባብነት፣ ትምክህተኝነትና ፅንፈኝነት  በስርዓቱ ላይ የደቀኑት አደጋ በጉልህ እየታየ መጥቷል፡፡ የጥገኝነትን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በብሄር ካባ ትምክህተኝነትና ጠባብነትን ማራመድና ማስፋፋት ውጤት ይገኝበታል በሚል ቀቢፀ ተስፋ እየተራመደ ያለ አደጋ ነው፡፡

ነገር ግን ጥገኝነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋትና ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን እንዲይዝ  በማድረግ የሚወገዱ አደጋዎች ናቸው ፡፡

ሆኖም ትምክህተኝነትና ጠባብነት በተለየ መንገድ ትግል ካልተደረገባቸው በርካታ ተከታይ እያፈሩ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገልና ልማታዊነትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በማወሳሰብ ስርዐትን ማናጋትና የህዝቦችን አብሮነት መበጣጠስ እንደሚችሉ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ስለሆነም በትምክህተኝነትና ጠባብነት ላይ የማያቋርጥና ጠንካራ ትግል የማካሄዱ ጉዳይ በቁርጠኝነት ሊሰራበት እንደሚገባ አቶ ፀጋብርሃን ታደሰ በአፅንኦት ይናገራሉ።

“ ማንኛውም ፈፃሚና አስፈፃሚ ከእነዚህ አመለካከቶች ራሱን ነፃ በማድረግ በሌሎች የሚታዩ ዝንባሌዎችን በፅናት መታገል አለበት” ባይ ናቸው ።

የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካይዳኪ ገዛኽኽኽኸኽኝ “ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የመገንባት ትግሉ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመዋጋት ውጪ የሚታሰብ አይደለም “ ይላሉ ።

“ ትምክህትና ጠባብነት የኪራይ ሰብሳቢዎች የመጨረሻ ዋሻዎች ናቸው  “ የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመሰረቱ በመናድ ጠባብነትና ትምክህተኝነትን ማስወገድ ይቻላል ባይ ናቸው ።

ትምክህትና ጠባብነት በፅናት መታገል ማለት የህዳሴ ጉዞአችንን የማስቀጠል የጋራ ፍላጎት ማሳካት ማለት በመሆኑ ሁላችንም ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንተናነቀው የሚገባ አጀንዳ መሆን አለበትም ይላሉ ።

በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ በሚገኙ ጥቂት አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የወሰን አለመግባባት በሁለቱም ህዝቦች ቀና ተነሳሽነት በውይይት መፈታቱ ጠባብም ሆነ ትምክህተኛ ህዝብ አለመኖሩን ያሳያል። ለዚህም ነው ሁለቱም ህዝቦች ሲጋጩ የሳቁት ጠባብና ትምክህተኛ ሃይሎች እርቀ ሰላም ሲያወርዱ ደግሞ ሲያላዝኑ የተስተዋሉት።

ፀረ ሰላም ሃይሎቹ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ህዝቦች መካከል የጫሩት እሳት ዘላቂ መስሎአቸው ለጊዜው ቢቦርቁም ጠባብም ሆነ ትምክህተኛ ህዝብ ስለሌለ ነገ በሁለቱም ህዝቦች መካከል የነበረው የቀደመ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም ። ይልቁንም የጥፋት ሃይሎቹ ያኔ በፈፀሙት ጥፋት ተጠያቂ ሆነው ማየታችን የማይቀር ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን