አርዕስተ ዜና

በድሬዳዋ ለውጥ የለወጠው የትምህርት ስኬት

26 Nov 2017
4375 times

ሀብታሙ ገዜ ኢዜአ

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በድሬዳዋ አስተዳደር ለውጥ ከተመዘገበባቸው ማህበራዊ ልማቶች መካከል ትምህርት ቀዳሚ ነው። እንደዛሬው ትምህርት ቤቶች ገጠር መንደር ድረስ ሳይስፋፉ ትምህርት ፍለጋ መኳተን የትናንት ትዝታ ነበር።

ዛሬ ግን ነበር ሆኖ ቀርቷል፡፡

ያኔ ትምህርት በበቂ ሁኔታ ባለመዳረሱ የአካባቢው ወጣቶች የእርሻ መሬት ተቀራምተው ሕይወታቸውን መምራት ብቸኛ እጣ ፋንታቸው ነበር፡፡ ይህን መንፈስ ለመለወጥና አዲሱ ትውልድ ሌላም የተሻለ ነገን እንዲያልም ባለፉት ዓመታት ትምህርትን በአስተዳደሩ ለማዳረስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በ38ቱ የአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የተስፋፋው ትምህርት በአሁኑ ወቅት በነዋሪዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ጀምሯል።

በዋሂል ክላስተር የኡሉል ሞጆ ገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ኡስማን መሐመድ እንዳሉት እርሳቸውና በዘመናቸው የነበሩት ፤ ዛሬ ልጆቻቸው ተምረው እየኖሩ ያሉትን ዘመናዊ የተሻለ ኑሮ የማጣጣም ዕድል አልነበራቸውም፡፡

ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት በአካባቢያቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከፈቱ ሁሉም ልጆቹን ለተሻለ ደረጃ ለማብቃት እንዲተጋ አድርጎታል ይላሉ። “ልጆች ብቻ ሳይሆን የእኔ እኩዮችንም  ለመማር አነቃቅቶናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ኡስማን እንዳሉት በመንደራቸው የደረሰው ትምህርት ሰዎችን እየለወጠ ነው፤  ከቀበሌያቸው በዲፕሎማ፣ በዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየለወጡ የሚገኙት ብዙ ናቸው፡፡

ላለፉት ሃያ ዓመታት ትምህርት በአካባቢው በመስፋፋቱ ተምረው ሕብረተሰቡን የሚያክሙ አሉ ፤ የሕብረተሰቡን የውሃ ችግር እያቃለሉ ያሉና ወንድሞቻቸውን እያስተማሩ የሚገኙ መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

በውሃ ምህንድስና ተመርቆ በድሬዳዋ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት እያገለገለ የሚገኘው ወጣት መሐመድ አብደላ የአቶ ኡስማንን ሃሳብ ይጋራል፡፡

“ትምህርት ቤቶች እኔ ወደአደኩበት ገጠር ባይስፋፋ ኖሮ አሁን ላለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር” ያለው ወጣቱ በአካባቢያቸው ትምህርትን ከማስፋፋት ባለፈ የገጠር ልጆች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጿል።

ትምህርትን በፍትሃዊነት ተደራሽ በማድረግ የተመዘገበው ውጤት በትምህርት ጥራት እንዲደገም ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጸው።

በለገኦዳ ጉጉንፈታ ገጠር ቀበሌ በማህበረሰቡ ተሰሚ የሆኑት አቶ ሙሜ አደም በበኩላቸው “ትምህርት የልማት ሁሉ መሰረት መሆኑ ገብቶናል ። ትምህርት ከሌለ ጤና፣ መንገድ፣ ውሃ፣ ልማት፣ ሠላም ስለማይኖር ልጆቻችን በትምህርታቸው እንዲበረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የድሬደዋ ገጠር ቀበሌዎች በሙሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ መሆናቸውን ተመልክቷል። በሕብረተሰቡም ዘንድ ትምህርት የብዙ ነገር መሰረት መሆኑ ግንዛቤ እየተያዘ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ከገጠር በቅለው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል። በመንግስት መስሪያ ቤት ተመድበው በሀገራቸው ልማት የድርሻቸውን የተወጡም እንዲሁ፤

በእዚህ የሚስማሙት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰመድ መሐመድ የትምህርት ውጤት በማህበረሰቡ ለውጥና በሀገር እድገት እንደሚለካ ይናገራሉ፡፡

በድሬዳዋ ባለፉት 20 ዓመታት በዋሂል ገጠር ክላስተር የመጣውን ለውጥና ከዚህ አካባቢ ተነስተው ለአስተዳደር ብሎም በሀገር ልማት ላይ አወንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙ ሙሁራን በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ የትምህርት ውጤትም ይህን ነው” ይላሉ።

እንደ አቶ አብዱልሰመድ ገለጻ ከሃያ ዓመት በፊት በአስተዳደሩ ጥቂት አንደኛ ትምህርት ቤቶች ብቻ እንደነበሩና በአሁ ወቅት ቁጥራቸው ወደ 46 ከፍ ብሏል፡፡ ቀደም ሲል ሕብረተሰቡ ትምህርት እንዲስፋፋ በጠየቀው ጥያቄ መሰረት በገጠር ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ከአሥር ዓመት በፊት በአስተዳደሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሣትፎ 20 በመቶ የነበረው ወደ 43 በመቶ አድጓል ።  ሁሉም ታዳጊ ልጆች በመንደራቸው ትምህርትን የመከታተል እድል አግኝቷል፡፡ በገጠርም በከተማም ሦስት ብቻ የነበሩት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሁን ቁጥራቸው 11 ደርሷል።

የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥም አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን በአደረጃትና በአሰራር የማዘመን፣ የመምህራን አቅም በሥልጠና የማሳደግ፣ በትምህርት ቤቶች ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን የማሳደግ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ላቦራቶሪ፣ መጻህፍትና ቁሳቁስ ለማሟላት የተሠሩ ሥራዎችም ውጤት እያስገኙ መሆኑን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰላም ገልፀዋል፡፡

በትምህርት ቢሮ የልማት እቅድና በጀት ዝግጅት ባለሙያ አቶ ግርማቸው አለነ  በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅና የተማሪ ክፍል ጥምርታ ደረጃውን ለመጠበቅ አምና በ17 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የተጀመሩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ዘንድሮ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ ከፊሉም ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ነው የገለጹት።

በገጠርና በከተማ በሚገኙ 11 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተገነቡበት 131 የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍት፣ ቤተሙከራና የትምህርት ማበልጸጊያ በቀጣይ የመማር ማስተማሩ ሂደት ጥራቱን እንዲጠብቅ ያግዛሉ ብለዋል፡፡

እንደ ባለሙያ ገለጻ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ የተለያዩ ሥራዎች ቢሰሩም በአስተዳደሩ ካሉ ትምህርት ቤቶች ከ75 እስከ 80 በመቶዎቹ የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ አላሟሉም፡፡ “ በቀጣይ ብዙ መልፋትና መስራት ይጠይቃል ” ብለዋል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ከተዘጋጀባቸው የአስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች መካከል የአዲስ ከተማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡ በትምህርት ቤታቸው ባለሁለት ፎቅ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተሙከራ ተገንብተዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ መሰረት መሰለ “መማሪያ ክፍሎቹ የተማሪ መምህር ጥምርታን ከ75 ወደ 50 በማውረድ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ ያስችላል” ይላሉ፡፡ የሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት አበርክቶአቸው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።

የእዚሁ ትምህርት ቤት የወላጅ፣ መምህር ተማሪ ሕብረት አባል አቶ አማረ በለጠ በበኩላቸው የመማሪያ ክፍሎቹ ተገንብተው እስኪጠናቀቁ ድረስ  የአካባቢው ሕብረተሰብ በእውቀቱ፣ በጉልበቱና በቁሳቁስ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ትምህርትን ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት የነዋሪው የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው “መንግስት በትምህርት መስክ እያከናወነ ያለው ልማትና ለውጥ ሊበረታታም ይገባል” ብለዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ71 ሺህ በላይ ተማሪዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። በሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶችም 14ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን